ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ በሕግ አምላክ
ትርጉም (ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ)
አአዩ ፕሬስ 2007
የገጽ ብዛት - 331
ዋጋ - 97 ብር
ይህ መጽሐፍ በሌላኛው እትሙ ሰውን
ማሰቃየትን እኛ የፈጠርነው እንዲመስላቸው እንዳረገና የሃሳብ ብዙህነትንና የአማራጭ ሃሳብ መንሸራሸርን እስካሁን አለመቀበላችን ታሪካዊ
ሥር እንዳለው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የጻፉለት ነው፡፡ አራት ገድሎችን፣ ማለትም ገድለ አባ እስጢፋኖስን፣ ገድለ አበው ወአኀውን፣
ገድለ አባ አበክረዙን እና ገድለ አባ እዝራን ከግዕዝ ወደ አማርኛ ተርጉመው ለአንባቢያን ያደረሱት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በአጼ
ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ-መንግሥት (1426-1460) በዚህ አስተምህሮ ተከታዮች ላይ የተላለፈውን ውሳኔ በአማርኛ ያስነብቡናል፡፡ ለአብ፣
ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ በቀር (ለወላዲተ አምላክ) ሥዕል፣ ለመስቀል፣ ለንጉሥ አንሰግድም የሚሉት የመስራቹ የአባ እስጢፋኖስ ተከታዮች
ከቤተክርስቲያን ቀደምት ታዋቂ ሰነዶች ዉጪ የሆኑትን መጻሕፍት አይቀበሉም፡፡ እነዚህ እስጢፋኖሳውያን በንጉሡ ችሎት ቀርበው ከካህናተ
ደብተራ ጋር በግልጽ ክርክር ያደርጉና ይፈረድባቸው ጀመር፡፡ የእንቅስቃሴው ተመልካቾች አልፎ አልፎ የፖለቲካ ገጽታ የሚሰጡት ይህ
እርምጃ ከአንዳንድ ወገኖች የንጉሡን ፍትሐዊነት ማሳያ አድርጎ ይወሰዳል፡፡
የስቃዮቹ ዓይነት በርካታ ሲሆን
የሠውነት ክፍልን መቁረጥ፣ ጅማት መምዘዝ፣ ግርፋትና፣ ድብደባን ሁሉ ያጠቃለለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እስከ ሃያኛው ክፍለዘመን
ድረስ እነዚህን የመሳሰሉ በአካላዊ ጉዳቶች እንደሚፈጽም ‹‹ተፈሪ መኮንን›› በሚለው መጽሐፍ ሳይቀር ተጠቅሷል፡፡ ይህም ቅጣቱ የባህላችን
አካል የሆነ ከሆነ በነዚህ የሃይማኖት ተቃዋሚዎች ላይ የተጋነነ ቅጣት ተፈጽሟል የሚሉትን ሰዎች መከራከሪያ ውድቅ ሊያደርግ ይችላል፡፡
ከንጉሡ በኩል ያሉ ምክንያቶችን
ያየን እንደሆነ፤ በብዛት አከራክረው ውሣኔ ይሰጣሉ እንጂ በግብታዊነት ግፍ አይፈጽሙም፡፡ በደብረ ብርሃን የብርሃን መውረድን አስመልክቶ
ሁለቱም አካላት፣ ከዘርዓያዕቆብም ሆነ ከእስጢፋኖስ በኩል ያሉት፣ ለኛ ከአምላክ የተላከ መልዕክት ነው ይላሉ፡፡ ይህን ነገር ከሳይንሳዊ
አተያይ የሚያዩት ደግሞ በደብረብርሃን ያለፈችው ሃሊስ ኮሜት ነች፤ ይህም ምንም ዓይነት ተዓምር ሳይሆን የተለመደ ሂደት ነው ይላሉ፡፡
እንቅስቃሴው ሴቶችም አሉበት፡፡
‹‹ትወጋ እንደሆነ እንደወንድ ውጋ›› ብላ አንድን ሰውነት በስለት የሚወጋ የአጼ ዘርዓያዕቆብ ወታደር የተናገረችውን ሴት ደቂቀ
እስጢፋኖሳዊ ማየት ይቻላል፡፡ ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ራሳቸው የጻፏቸው የብራና ሰነዶች ናቸው ተተርጉመው ለአማርኛ አንባቢያን የደረሱት፡፡
የእንቅስቃሴው መስፋፋት የሚያሳስብና
ሥርዓትንና ሐይማኖትን ወደተለየ አቅጣጫ የሚወስድ እንደነበረ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ሃሳባችንን አንቀይርም እያሉ ለእርድ የቀረቡት
እስጢፋኖሳውያን ዓላማቸው ምን እንደሆነ የሚያሳስብ ሲሆን ምናልባት የፖለቲካ ዓላማ ይኖራቸው ይሆን ያስብላል፡፡ 15ኛው ክፍለዘመን
ላይ የነበረው ይህ እንቅስቃሴ በአውሮፓ የመጣውን የተሃድሶ እንቅስቃሴ የሚቀድምና የሃገሪቱን ታሪክ የሚቀይር እንደነበረ መገንዘብ
ይቻላል፡፡ በአንጻሩ ሲታይ የንጉሡ ሰራተኞችና ሹሞች በትግራይም የእንቅስቃሴውን ተከታዮች ይቀጡ ስለነበር የፖለቲካ አይመስለኝም፡፡
በትግራይ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ክፍላተሃገራትና አውራጃዎች ተከታዮች አፍርተዋል፡፡ ይህም የአንድ አካባቢ እንቅስቃሴ ሳይሆን የአገሪቱ
ምዕመናንን ያካተተ ብልጭ ብሎ የጠፋ ክስተት ያደርገዋል፡፡