2015 ማርች 29, እሑድ

ከመንዝ ጓሳ እስከ እንግድዋሻ



የጉዞ ማስታወሻ
ከመንዝ ጓሳ እስከ እንግድዋሻ
መዘምር ግርማ እንደተረከው
መንደርደሪያ
ከአንድ ወር በላይ ዝግጅት የተደረገበት እና ከየካቲት 27 እስከ 29፣ 2007 ዓ.ም. በመንዝ ጌራ ምድር፣ በደብረሲና እና በሞጃ እና ወደራ ሊካሄድ የታሰበው ጉዞ በተለመደው የሰዓት መሸራረፍ ምክንያት መነሻው ከጠዋቱ 12፡00 ተብሎ የነበረው 2፡00 ላይ ይጀመራል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሽንጠ - ረጃጅም ‹‹ፈረሶች›› የአባይን ውሃ ቀምሰው ለመምጣት ወንዝ በመውረዳቸው በኪራይ ‹‹በቅሎ›› ይህን የባህል ማዕከል ተቀጥላ ጉዞ ጸሐይ ሞቅ ስትል ‹‹በቅሎዬ ስገሪ አርጊው ነሃ ነሃ፣ ወደ ሰላድንጋይ ወደ ሞፈር ውሃ›› እያልን በተውሶ ግጥም ጀመርንው፡፡
የጉዟችንን መርሃ-ግብር በየመገናኛ አውታሩ፣ ፊት-ገጽን ጨምሮ፣ በትነን፣ ተጓዡን ቀስቅሰን፣ የየወረዳዎቹን አመራሮች አነጋግረን እና አስደግሰን ስናበቃ የአባይ ጉዞ የእኛን ጉዞ ልናደርግ ባሰብንው ቀን ይደረጋል ሲባል የራስ ምታታችን ሆነ፡፡ አንድም ተጓዡ አባይን መርጦ የግቢው ዘፈን ‹‹እንጉርጉሮ ይብቃ›› ሲሆን፣ ሁለትም ‹‹ምን መንዝ ለቅሶ ተከትለን ብንሄድስ እናየው የለም?›› የሚሉት ገሸሽ ሲሉ፣ ሶስትም ‹‹ጉዞው አርብ ስለሆነ አይፈቀድልንም የሚለው ሰራተኛ ሲበረክት››፣  አራትም የባህል ማዕከሉ ሃላፊ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የጥበብ ድግስ ሊሳተፍ ሄዶ ያለ ሃሙስ ሳይመጣ ሲቀር እኔ ይህ ጉዞ እንዲደረግ ለማዕከሉ አባላት በስብሰባችን ያሳመንኩት፣ የየወረዳዎቹን አመራሮች ስፍራቸውድረስ ሄጄ ያነጋገርኩት እና የክተት አዋጅ ያወጅኩት ሰውዬ ሆዬ ‹‹እሸሸግበት ጥግ አጣሁ›› ፡፡
የዕለቱ ለት ያስረፈደን ተጓዦች በቡድን በየምንሄድበት ስፍራ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መማሪያ ክፍሎች ውስጥ ለማደር የምንተኛበትን ፍራሽ መኪና ላይ መጫኑ ነበር፡፡ ፍራሽ ሰጭው ያርፍድ፣ ወይንስ የኛ ችግር ይሁን አልተገለጠልኝም፡፡ ባለፈው ዓመት የአሜሪካ ሰላም ጓድ በዩኒቨርሲቲያችን ከተለያዩ በሶስት ክልል ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለመጡ 64 ሴቶች ልጆች ባዘጋጀው የአንድ ሳምንት መርሃ-ግብር ስሳተፍ አንድን ዝግጅት እንከን-አልባ ማድረግ እንዴት እንደሚቻል ካየሁበት ጋር ያሁኑን ሳነጻጽረው ምድርና ሰማይ ነው፡፡
በሰዓቱ ራሴ ብየው የነበረው ለጥቅስ የሚበቃ ቃሌ ‹‹ሁለት ሰዓት እኮ ማራቶን የሚገባበት ሰዓት ነው›› የሚል ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ሰሜን ሸዋ አንድ ወረዳ ላይ ሁለት ሚሊዮን ችግኞችን ሊተክል ላይ ታች ከሚለው ከአድህኖ የተቀናጀ የገጠር ልማት የመጣው አበበ ግሩም በብስጩ ድምጽ ‹‹የቅንጅት ችግር አለ - የተባለው ሰዓትና የተነሳንበት የሁለት ሰዓት ክፍተት አለው፡፡ እኔ በሰዓቱ ነው የመጣሁት፡፡ ሌላ ነገር ደግሞ፣ ፍራሽ ለመጫን እና ከመናኸሪያ መውጫ ለማምጣት ሲባል መኪናው በተባለው ሰዓት ዝግጁ አልነበረም›› ሲል አማሯል፡፡
በጉዞው ዋዜማ በፊት ገጽ ያማረርኩት ምሬት አሁንም የመስሪያ ቤቴን ክቡራን ሃላፊዎች ምላሽ ይፈልጋል፡፡ ምሬቱን ቃል በቃል እርስዎም አንብበው ይፍረዱ፡፡ ‹‹በዩኒቨርሲቲያችን ወደ አባይ ግድብ ለሚሄዱ ተጓዦች ውሎ አበል ተከፍሎ ለባህል ማዕከል ተጓዦች ግን ያልተከፈለው ለምንድነው? ሁሉም ዩኒቨርሲቲው በሚሰጣቸው ምንዳ የሚተዳደሩ አይደሉምን? የዩኒቨርሲቲው አመራር አምኖባቸው የፈቀዳቸው ጉዞዎች ሆነው ሳለ ለአንዱ እንደ ልጅ ለሌላው እንደ እንጀራ ልጅ ለምን ይደረጋል? አባይ ግድብ የሚሄዱትም ጉብኝት፣ ይሄም ጉብኝት!›› የሚል ነበር፡፡

አርብ የካቲት 27፣ የምንሊክ መስኮት
‹‹የምንሊክ መስኮት በጣም ነው የሚያስፈራው፤ በህልሜ ነው የሚመጣው፡፡ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ ንጹህ አየር ነው ያገኘሁት፡፡ ›› በማለት በአጫጭር አረፍተ ነገሮች ጣርማበር አቅራቢያ ባለው ገደላማ ስፍራ ጫፍ ወጥተን ቆላውን በአጉሊ መነጽር እያየን የተሰማትን ሁኔታ የገለጸችው እኔን አባቷን ተከትላ የሄደችው የሶስተኛ ክፍል ተማሪዋ ልጄ ሳትሆን የስራ ባልደረባዬ ተዋበች አብዱ ነች፡፡ ውብ ሃሳብ በተቆጠቡ ቃላት!
‹‹ስለ መስኮቱ ምንም አልነገራችሁን እኮ›› ያለው ኪሩቤል ሮሬሳ እንደመሃንዲስነቱ እቅጩን ይፈልጋል፡፡ እኛ የቋንቋ አስተማሪዎቹ አስተባባሪዎች ግን ቋንቋ አጥሮን ይሁን ቅንጅት ይችን ጉዳይ ረስተናት ኖሯል፡፡ ስፍራው የስጋ ደዌ በሽተኞች ይጣሉበታል እንዲሁም አርበኞች ይሸሸጉበታል መባሉን ብንነግረው ጥሩ ምስል ይኖረው ነበር ኪሩቤል፡፡
ጃንሆይ አጼ ኃይለ ስላሤ አንድ ወቅት በጣርማበር ወይንም በሌላ ስሟ በጫሬ ሲያልፉ በመስኮት ወጣ ብለው ለነዋሪው ‹‹እኛ እምንለው! እዚህ እምትኖሩት ወዳችሁ ነው ወይንስ ተገዳችሁ? ቆፈኑን እንዴት ቻላችሁት ልጆቼ? ተዉ ሰፈራ እንውሰዳችሁ!›› ቢሏቸው ‹‹አይ ጃንሆይ ይችን የመሰለች ወርቅ አገር የት ያገኙልናል?›› ብለው መልሰውላቸዋል እየተባለ በሚተረትላት ትንሽዬ የሰው-ሰራሽ ዋሻ ዳር ከተማ ትኩስ አንባሻ በሻይ ግሩም ቁርስ በላን፡፡ ያንን ዋሻ ሲቆፍር ሰዉ እንዴት እንደተሰቃየ ማን ያውቃል? የዳኛቸው ወርቁን የእንግሊዝኛ ልብ ወለድ ‹‹ማሚቴን›› አስታወስኩ፡፡ ፍራሽ ጭነው፣ እኛን ተሸክመው ዳገታማውን የኮረኮንች ጎዳና የጀመሩት በቅሎዎቻችን ምስጋና ይግባቸውና የመንዝን የጉዞ ጠፍር እንሰበስብ ገባን፡፡
አርባሃራ መድሃኔዓለም
መዘዞን እና ባሽን አልፈን ይገም ከተማ ስንደርስ አንዱ ከዕቅዳችን ውጭ በስነ- ትምህርቱ መምህር በመኮንን ጌታቸው ምክር ያካተትንው ዘንድሮ ሰዎች አርባሃራ መድሃኔዓለም ሲሉት ወደሰማሁት ገዳም አጭር የእግር መንገድ ጀመርን፡፡ አፋፍ ስንደርስ ሹል ጉልላቱ ብቅ ብሎ ሲታየን በውበቱ ተማርከን ሹሌን አልን፡፡
ከቤተክርስቲያኑ ጉዞ መልስ አንድ ሃይለኛው ወልደሃኔ ሙሉነህ የሚባል የ11 ዓመት ልጅና የይገም ትምህርት ቤት የ5ኛ መ ክፍል ተማሪ ውጤቱን የሚያሳይ መግለጫ ይዞ አይቼው ወዳረፍንበት ሻይ ቤት ጠርቼ ሳይለት አማርኛ 42 ከመቶ እና ሌላውንም በአብዛኛው ከዚያ ያልተሻለ አምጥቶ ሳይ አዘንኩ፡፡ አማካይ ውጤቱ 53.7 ሆኖ ከ48 ተማሪ 31ኛ የወጣውን ይህን ተማሪ መምህርት በስንትወርቅ ታደሰ ‹‹የተማሪው ውጤት ጥሩ ቢሆንም ከዚህ የበለጠ እንዲሻሻል የወላጅ ድጋፍና ክትትል አይለየው›› ሲሉ የውጤት መግለጫው ላይ በጻፉት ማስታወሻ አሞካሽተውታል፡፡ እርሱንና ሌሎች ልጆችን አስቤ የያዝኳቸውን ብዕሮች፣ እርሳሶች፣ ከረሜላዎች፣ ቸኮሌቶችና ሌሎችም ዕቃዎች በመስጠት በአስርት ብሮች በሚሆን ወጭ እነርሱን አስደስቼ እኔም ተደሰትኩ፡፡ መከርኳቸውም፡፡
አንተ ጎዳና 
መንዝ ተኮር አመራሮችና የምርጫ ተወዳዳሪዎች አንዲት የቤት ስራ ልስጣችሁ፡፡ ከጣርማበር ጀምሮ እስከ መሃል ሜዳ ያለው መንገድ ጭራሽ የሚገርም ነው፡፡ ከ1955-58 ባሉት አመታት የመንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ መንገዱን ያሰራው በህይወት የሌለው ዶክተር ኢንጂኔር ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህም ሆነ ራሱን አደራጅቶ አውቶቡስ ገዝቶ መናኸሪያ ሰርቶ እና ጮካ ጮካ መኪና አስተዳዳሪዎች መርጦ ክቤ የተመታው የመንዝና ግሼ ህዝብ ሞተውም ሆነ ቆመው ያዝናሉ፡፡ የጌራ ምድር ወረዳ አስተዳዳሪው  አቶ ሙሉጌታ ‹‹መንዝ አምስት ወይንም ስድስት ወረዳዎችን ይይዛል›› ብለውኝ ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ህዝብ ከብሄራዊው ዳቦ ትንሽ ይገምጥ ዘንድ ለምን አትሯሯጡለትም? እነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ድንቅ ስራ እንኳን ብትሰሩ እንግዳ በየት መጥቶ ያመሰግናችኋል? በመሃል ሜዳ - መርሃቤቴው የአስፋልት መንገድ ጥሩ ጅማሮነት ግን እንስማማለን፡፡  ‹‹መንዝ የተረሳና ልማት የጠማው አካባቢ ነው›› የሚለው የአቶ ሙሉጌታ ቃል በጆሯችሁ ሊያቃጭል ይገባል፡፡ በጄ?
መንዝ ጓሳ
ጓሳ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ደርሰን ገና ሳንጎበኝ ምሳ በልተን ለመመለስ ወደ መሃል ሜዳ ስንጓዝ በስተግራ ባለው ሜዳ የዝንጀሮ መንጋ ፈሶበት አየን፡፡ ረጅም መንገድ እያየናቸው ሄድን፡፡ ያው ግን አብዛኛው የኛ ሰው ግድም የሰጠው አልመሰለኝ - ለእንስሳ ያለው ፍቅር ዝቅ በማለቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ‹‹ምግቡ ጥሩ ነው፤ ርካሽ ነው፤ በዚህ ዋጋ ይህ ምግብ እዚህ ቦታ መገኘቱ አሪፍ ነው›› ያለኝን ጎብኝ ከእንስሶቹ ይልቅ ምግቡ አስደስቶት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ኢንስፔክተር ይሁን ሽፈራው ከአብዛኛው ሰው በተለየ ሁኔታ ‹‹ሰሜን ሸዋ ውስጥ ያለሁም አልመሰለኝ፤ በአረንጓዴ ወቅት ብንመጣ እንዴት ያምራል! የዝንጀሮ መንጋው ያስደስታል፤ የምንሊክ መስኮት ላይ ሆነህ የኅብረተሰቡን አሰፋፈር ስታይ ያስደንቅሃል›› ሲል ያልጠበቀው ነገር እዚህ ስፍራ በመኖሩ አደነቀ፡፡
ማማ፣ ጌራ እና ላሎ የሚባሉ ሶስት ከጎንደር የመጡ ወንድማማቾች ከ400 ዓመታት በፊት ያቋቋሙት ነው በተባለው መንዝ ጓሳ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ከምሳ በኋላ 25 ኪሎሜትሩን መንገድ ከመሃል ሜዳ ተመልሰን ደረስን፡፡ አስጎብኛችን አቶ አበበ ጥሩ ማብራሪያ ካደረገልን በኋላ ጥያቄዎችንም ጠያይቀንና የእንግዶቹን ማረፊያዎች ቃኝተን በእግር የተለያዩ የስፍራውን አካባቢዎች ለማየት እንቅስቃሴ ጀመርን፡፡ ስፋቱ ከ72 እስከ 100 ስኩየር ኪሎሜትር ይሆናል የሚባለውን ስፍራ ለመጎብኘት የሶስት ቀናትና የአራት ሌሊት ቆይታ ያስፈልጋል፡፡ የኛ ጉብኝት ግን መጠነኛ ቅኝት ነው የሚሆነው፡፡ በጽድ ጫካ ውስጥ አልፈን የአስታና የጓሳ ምድሩን በሚገባ ከቃኘን በኋላ ይፋትን የምናይበት ስፍራ ላይ ደረስን፡፡ ከዚያ ደጋማ ስፍራ ቁልቁል ወደ አጣዬ ማማተር ልብን ይሰውራል፡፡ የጦስኙ ሽታ፣ በስፍራው መሆን የሚሰጠው የአዕምሮ ሰላም፣ የንፋሱ ሽውታ እና የመልከዓምድሩ አይነ ግቡነት እዚሁ ዋሉ እደሩ ብሎ አንቆ ይይዛል፡፡ አሜሪካውያኑ ተመራማሪዎች እዚያ መኖሪያ  ሰርተው የሚኖሩት መች በደህና ነው! አንዱ ግን የሚኖርበት ቤት የድንጋይ ካቡ ተንዶበት ሞቷል ሲሉኝ አንጀቴን በላው፤ እናቱ ውሃ ግተው ሳያስታምሙት ማረፉ ያሳዝናል! ለጉብኝታችን ይረዳ ዘንድ የያዝንው የእግር ኳስ ስለነበር እየተጫወትን ትንሽ ጊዜ ካሳለፍን በኋላ ቀይ ቀበሮ ትገኝበታለች ወደተባለው ስፍራ ሄድን፡፡ በዚያም በየቀበሮ ጉድጓዱ ብንዟዟር ቀበሮ የገባችበት ይጠፋል፡፡ አበበ እንደተጨነቀ ያስታውቃል፡፡ ‹‹እዚህ ጋ በዚህ ሰዓት ብዙ ቀን ትታይ ነበር፤ ትናንትም አይቻታለሁ›› በማለት ተቆጨ፡፡ በዚህ ስፍራ የማታ ጸሐይ እየሞቅንና እያወራን ፎቶ ስንነሳ፣ በአጉሊ መነጽርም ቀበሮ ስናፈላልግ ቆየን፡፡ ከአንድ እስከ ሁለት ሰዓት ከሚሆን ቆይታ በኋላ ተሳፍረን ወደ መሃል ሜዳ እየጨፈርን ሄድን፡፡
በተያዘልን በነጻነት ቡና ቤት ራት እየበላን እና መጠጥ እየጠጣን ከወረዳው አመራሮች ጋር ስለ መንዝ ጓሳ ውይይት አደረግን፡፡ በውይይቱ ላይ ከኛ ከጎብኝዎች ወገን የተነሳው የመጀመሪያው ነገር ‹‹የመንዝ ህዝብ ራሱ ስፍራውን ማየት አለበት፤ ሰርግን የመሳሰሉ በዓላትን እዚያ እያከበረ አውቆ ማሳወቅ አለበት፡፡ ከሌላ ፓርክ ለምን ብርቅዬ እንስሳትን አታመጡም?›› የሚል ሲሆን ሃላፊዎቹም አምነውበት ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ተግባብተናል፡፡ ከሌላ ፓርክ እንስሳት አምጡ ለሚለው ሃሳብ ተመራመሩበት የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በጣም አንገብጋቢ የነበረው ጥያቄያቸው ግን ‹‹በጓሳው ምድር ላይ እንደ አረም እየበቀለ ጓሳውን ሊያጠፋው በደረሰው አረም በ‹‹ነጭሎ›› ላይ እንድትመራመሩልን የድረሱልን ጥሪ እናስተላልፋለን!›› የሚል ነው፡፡ ‹‹ጓሳ ልብሴ፣ ጓሳ ጉርሴ›› እያለ በጓሳው ክልል ውስጥ የቤት እንስሳት ለሚያስገቡ ሰዎች እንስሳቶቻቸውን እስከማረድ የሚከብድ ቅጣት እየጣለ ስፍራውን ጠብቆ ላኖረው ኅብረተሰብ የጓሳ አደጋ ላይ መውደቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያሳውጅ ነው፡፡ ‹‹ጓሳ እንዴት ቆየ ተብሎ ቢጠናልን እና የአካባቢ ጥበቃው ወደፊትም በዘመናዊ መንገድ እንዲካሄድ ያግዘን ነበር›› ሲሉ የወረዳው ሃላፊዎች ሌላ ጥያቄን ለዩኒቨርሲቲው ልዑካን አቅርበዋል፡፡ ‹‹የቱሪዝም ትምህርት ክፍል ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ላይ ቢከፈት ለእኛ ያግዘን ነበር›› ብለው መንዞች ባቀረቡት ሃሳብ ግን አልስማማም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ደቡብ፣ ሰሜን፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ኢትዮጵያን ማን ሊጎበኝለት ነው መንዝ የሚሄደው? የትኛው ትምህርት ክፍል ነው በሰሜን ሸዋ ላይ እዚህ ግባ የሚባል የመስክ ጉብኝት ተማሪዎቹን ይዞ የሚወጣው? ቱሪዝምስ ቢከፈት መንዝና ሌሎች የሰሜን ሸዋን ስፍራዎች በአይኑ ሙሉ ያያቸዋል ወይ? ሰሜን ሸዋ መች ለሽርሽር ያመቻል?
ባየው ነገር መደሰቱን ገልጾ ‹‹ሰዉን የሚያስደስት ነገር ይኖር ይሆን? እያልኩ እየፈራሁ ነው የመጣሁት፤ ሰዉ አንሄድም ሲል ግን ሰብረን ነው የመጣንው›› ያለው የባህል ማዕከሉ ሃላፊ ዝናወርቅ አሰፋ የገባቸውን ቃሎች ዩኒቨርሲቲው ቢፈጽም አበጀህ ያስብለዋል፡፡
አስታ እና ጅብራን የሚያካትት የእጽዋት ቅርስ፣ አንኮበር ሶረኔን እና ቅልጥም ሰባሪን ጨምሮ ብርቅዬ አዕዋፍን፣ ቀይ ቀበሮንና ጭላዳ ዝንጀሮን የመሰሉ በሃገራችን ብቻ የሚገኙ እንስሳትን የሚይዘው ጥብቅ ስፍራ የመንገድ ችግር ብቻ አይደለም ያለበት፡፡ የእንግዶች ማረፊያው ምድጃ እና ኩሽና ከማከራየት በዘለለ ምግብ ቢያዘጋጅ እና የአገልግሎቱን አድማስ ቢያሰፋ ጥሩ ይሆናል፡፡ ‹‹አንድ እንግዳ ቢመጣ ለማስተናገድ የተሟላ ነገር የለም›› እንዲል አበበ ግሩም፡፡
ጎንደር ፣ ባሌ፣ አቡነ ዮሴፍ (ወሎ) እና ጓሳ ብቻ ያለችው ቀይ ቀበሮ በሌላው ዓለም እግር እስኪነቃ ቢዞሩ አያገኘኟትም፡፡ በማግስቱ 12፡00 ሰዓት ላይ ወደ ደብረሲና የመልስ ጉዞ ስናደርግ ይህችን ብርቅዬ እንስሳ መንገዳችንን ስታቋርጥ አይተናት ቆመን እና ቀርበን ለማየት በቃን፡፡ ለአበበም ስልክ ደውዬ እንዳየኋት ነግሬ አስደሰትኩት፡፡ 
ስንመለስ አበበ እንዲህ እያለ ያስቀን ገባ -
‹‹ሚስት ከመዘዞ፣ ምን ተይዞ፤
ሚስት ከማማ፣ ከሆነማ፤
ሚስት ከግሼ፣ ይሁን እሺ፡፡››
ቁም ነገርም አለው አቤ፣ ‹‹የመንዝ ኅብረተሰብ ችግር ውስጥ ያለ ስለሆነ የአካባቢ ጥበቃው ከእርከን ስራ በዘለለ ቢሰራበት›› የሚል፡፡
ከደብረሲና መልስ ይህ አስተያየት ተሰጥቷል - ‹‹ከላልይበላው ጉዟችን ይህኛው በልጦብኛል፤ ሁሉ ነገር በቅንጅት ተደርጓል፡፡ በቡድን ተበልቷል፤ ታድሯል፤ ቀድሞ እዲዘጋጅ ተደርጓል›› ተዋበች አብዱ፡፡ ተዋበች ግን የዘነጋሽው ነገር ቢኖር ትምህርት ቤት ውስጥ እንድናድር ወረዳውን አናግረን የነበረው ነገር ሳይፈጸምልን ቀርቶ ነጻነት ቡና ቤት አድረናል፡፡ በእርግጥ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ‹‹የአንድ አልጋ እየከፈላችሁ ፍራሻችሁን መሬት ላይ እያነጠፋችሁ አምስትም ስድስትም እየሆችሁ በነጻ ተኙ›› ብለው ባለቤቱ አቶ ካሳዬ ስለፈቀዱልን በሙሉ ተጓዡም በአንድ ቤት ባይሆን የተወሰንን ሰዎች እየሆንን በትናንሽ ቡድኖች ስናወራ አድረናል፡፡
የመንዝን ጉዳይ ሳንጨርስ በመጨረሻም ደብረ ብርሃን ከተመለስኩ በኋላ ስለ ጓሳ የሰማሁትን ወግ ላውጋችሁ፡፡ በቀደምት ጊዜያት ጓሳ በጣም ሽፍታ የሚበዛበት ስፍራ ስለነበር ተማሪን ጨምሮ ማንም ሰው በታጣቂ አጀብ ነበር የሚያልፍበት፡፡  ባለቤታቸው ሳር እያበላቸው ሳይሆን ወደሌላ ስፍራ ጓሳን አቋርጦ እየሄደ እንደሆነ ለማረጋገጥ ከብቶች አፋቸውን ታስረው የሚሄዱበት የነበረው ይህ ስፍራ አንድ ሰው ከብቶቹን አስገብቶበት ሳር ሲያበላ ከተገኘ ከብቱ ይታረድበታል፤ እርሱም ይገረፋል፡፡ አንደኛው አስገራፊ አቶ ወልዴ ሸረሸር ይባሉ እንደነበር መንዜው አቶ ቀማው አጫውተውኛል፡፡ ወደፊት ከአቶ ወልዴ ልጆች ጋር ብራና ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ትሞክራለች፡፡
ቅዳሜ፣ የካቲት 28፣ ደብረሲና
በጣርማበር ዋሻ እንደደረስን ጠባቂዎቹን አስፈቅደን በዋሻው ውስጥ በእግር መንገዱ የእግር ጉዞ አድርገን ይፋት እና ደብረሲና በግልጽ በሚታዩበት ስፍራ ላይ ስንደርስ ዝናወርቅ ከዳኛቸው ወርቁ ልብወለድ ከአደፍርስ ላይ ስለነዚህ ስፍራዎች የሚያትተውን የመጀመሪያውን ገጽ አነበበልን፡፡ ከዚያም ደብረሲና ከተማ ገብተን የደራሲ ዳኛቸው ወርቁን አደባባይ እና ሐውልት አየን፡፡ የዳኛቸው ወርቁ ሐውልት በአዲስ መልክ ተሰርቶ በማየታችን ባለፈው ዓመት ወደስፍራው በግላችን ደራሲውን ለማሰብ ተጉዘን የነበርንው ጓደኛሞች ተደሰትን፡፡ ከዚህ በኋላ ቁርሳችንን በልተንና ፍራፍሬ ገዝተን ወደ ሰላድንጋይ ከተማ ጉዟችንን ጀመርን፡፡
በሰሜን ሸዋ የታወቀ መስህብ አንኮበርና መንዝ ጌራ ነው፡፡ ከነዚህ ስፍራዎች ሌላ ያልታወቀ ስፍራ ልናይ ነው የሄድንው በቀጣዩ ቀን፡፡ ሰላድንጋይ ከተማ ሳንደርስ ተጓዡ ደብረምጥማቅ ማርያም ላይ ወርዶ በእግር ወደ ጻድቃኔ ማርያም ሄዶ ተሳልሞ ሰላድንጋይ ከተማ ሊገባ ቻለ፡፡ ከዚያም ከአንድ አለት ወደተፈለፈለው ወደ ዳግማዊ ላሊበላ ምስካበ ሃዙናን መድሃኔዓለም ገዳም አቀናን፡፡ 41 የሱባዔ ክፍሎች ያሉትና ሶስት አብያተ ክርስቲናትን በአንድ በር ገብተው የሚያዩበት ገዳም በጥቂት ሰዎች ለመሰራት ሁለት ዓመትም አልፈጀበት፡፡ በዋነኝነት ፍልፍል አብያተክርስቲያኑን የሰሩት፣ ያሰሩት እና አሁንም እያስተዳደሩት ያሉት አባት ናቸው እኛን ያስገበኙን፡፡
ቀጥሎ ሰላድንጋይን ሰላድንጋይ ያስባላትን ግዙፍ ድንጋይ ጎብኝተን እላዩ ላይ ቆመን ፎቶ ተነስተን ወደ አጼ ምንሊክ ቅድም አያት ወደ ልዕልት ዘነበወርቅ ሰገነት አቅንተን ጉብኝታችንን ጀመርን፡፡ ይህን ስፍራ በቅርቡ በስፍራው የተተከለውና እየተገነባ ያለው የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ግዛቱን ተሻምቶታል፡፡ ከሰገነቱም ቤተክርስቲያኑ ጎልቶ ይታያል፡፡ ምን ይሻል ይሆን?
ሳሲት - እንግድዋሻ
ከዚህ በኋላ ጉዞ ከሰላድንጋይ በስተምዕራብ 20 ኪሎሜትር ወደምትርቀው ወደ ሳሲት ከተማ የተደረገ ሲሆን ራት ተበልቶ ሜንሽን ፊዩር ሜንሽን ባሰራው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እረፍት ልናደርግ ስንሄድ ህዝቡ በሆታ ነበር የተቀበለን፡፡ ህዝባችን የተማረ ሰውን እንዴት እንደሚያከብር ልብ በሉ፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር፣ የዘጋቢ ፊልም ትዕይንት፣ የስነ-ጽሁፍ ምሽት እና ምክክር ተደርጎ በሁለት መማሪያ ክፍሎች እያወራን እንድናድር ተደረገ፡፡
በማግስቱ እንግዱ በተባሉ የአገሩ አቅኝ ስም የተሰየመውን አንድ ግዙፍ ታሪካዊ ዋሻ ለማየት ጠዋት 1፡00 ላይ የእግር ጉዟችንን ሳሲት ከተማን ለቀን ወደ ሰሜን አቅጣጫ የጠዋት ጸሐይ እየሞቅን፣ እዚያው ያስጋገርንውን ሁለት ዳቦ በሞሰብ ይዘን ጉዞ ጀመርን፡፡ ጥሩ ጫማ አንዲያደርጉ ለተጓዦች በበተንንው ማሳሰቢያ አስቀድመን ያሳወቅን ቢሆንም በነጠላ ጫማም የመጡ ነበሩ፡፡ አብረውን ካደሩትና ሞቅ ባለ መልኩ ካስተናገዱን የወረዳው የባህል ቡድን አባላትና ሰራተኞች እንዲሁም ከሳሲት ነዋሪዎች ጋር የምናደርገውን ጉዞ እኔ ከፊት ካለው ተጓዥ ጋር ሆኜ ነበር የምጓዘው፡፡ ዋሻው በር ጋ ልንደርስ ስንል ያለችውን አስቸጋሪ መንገድ ትተው በቀናው መንገድ እንዲመጡ እኔና ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች ስንነግራቸው የማይሰሙን ሰዎች ነበሩ፡፡ አደጋ ሊደርስባቸው ብሎ የዳኑ ሁለት ሰዎችም ነበሩ፡፡ ገና እዋሻው ውስጥ ከመግባታችን ከኋላ ከነበረው ቡድን ያሉ ተጓዦች ‹‹እንደዚህ አይነት መንገድ እንደሆነ አልነገርከንም፣ ቁልቁለት አለው አላልክም፣ አሁን ጸሐዩ ሳይበረታ እንመለስ›› ሲሉ አስገረሙኝ፡፡ ገና ዋሻውን ሳያዩት፣ ውስጣውስጡን ሳይጎበኙት፣ እዚያ የተገኘውን በርካታ የአገሬውን ነዋሪ ትተው መሄድ ሳይከብዳቸው፣ ሊመጣ ትንሽ ጊዜ የቀረውን ዳቦና ጠላ ሳይቀምሱት እንዲሁም ዋሻው ውስጥ ለማድረግ ያሰብናቸውን ብዙ መርሃ-ግብሮች ሳይታደሙ እንሂድ ሲሉ ደነቀኝ፡፡ አንድ አካባቢውን የሚያውቅና እየደጋገፈ የሚወስዳቸው ወጣት ሰጥተናቸው ተመለሱ፡፡ የቀረው ግማሹ ሰው ከአገሬው ጋር ግሩም ጊዜ ማለቂያውን ባላየንው ዋሻ ውስጥ አሳለፈ፡፡ በጠዋት እንደምንመጣ እንዳልተነገራቸው የነገሩን የዋሻው አቅራቢያ ስፍራ ነዋሪዎች የእድራቸውን ስብሰባ ከጠዋቱ አራት ሰዓት በዋሻው ውስጥ እንደጠሩ ነገሩን፡፡
ዋሻው ቢያንስ እኛ በዚያን ቀን ያየንው ክፍሉ የአንድ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ የሚያክል ሲሆን ከጣልያን የአምስት አመት ቆይታ ጋር የሚያያዝ ታሪክ አለው፡፡ ካሳዬ ወንዳፈረው የተባለ አርበኛ የእኔን አያት ዘነበ ድረሴን ጨምሮ የሳሲትና አካባቢውን ህዝብ በሙሉ ከነከብቱ እዚህ ዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እየተዋጋ አድኖበታል ማለትን ሰምቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዶክተር ሲቪል መሃንዲስ ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህም የህይወት ታሪካቸውን በሚተርከው መጽሃፋቸው ላይ ሳሲት አቅራቢያ ባለ ትልቅ ዋሻ እርሳቸው የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳሉ በመጋቢት 1931 ዓ.ም. ቤተሰቦቻቸው የነበሩበት ከ300 በላይ ጠመንጃ የያዘ ጦር የነበረው ህዝብ ተጨፍጭፎ ሴቶችና ህጻናት ስላልተገደሉ ተርፌ ለዚህ በቃሁ ይላሉ፡፡ ይህ ዋሻ ለእኔ እንግድዋሻ ይመስለኛል መጽሃፋቸው ላይ ካለው ገለጻ አንጻር ሳስተያየው፡፡ ስለዋሻው ታሪክና የወደፊት ሁኔታ ውይይት ተካሂዶ ሁሉም አካላት የየራሳቸውን የቤት ስራ ወሰዱ፡፡ በተለይ ነዋሪው መንገዱን ለማስተካካል ቁርጠኛ መሆኑን ገለጸ፡፡ የምሁራንን አትኩሮት ስለሚፈልግ የዩኒቨርሲቲያችን የታሪክና ተዛማጅ ጥናቶች ሊቃውንት ሄደው ቢጎበኙት የሚል ሃሳብ ዋሻው ውስጥ የተገኘንው ሰዎች ሰንዝረናል፡፡
በዋሻው መግቢያ ላይ ተቀምጦ የወረዳው የባህል ቡድን አባል የሆነችን ትንሽ ልጅ ያናግር የነበረው መምህር ዘላለም ተሸመ ‹‹ይህች ልጅ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን አንደኛ ነው የምትወጣው፤ አድጋ ሳይንቲስት ሆና በዚህ ዋሻ ላይ መመራመር ትፈልጋለች፤ አስጨብጭብላት›› ብሎኝ ለህዝቡ ነግሬ አስጨበጨብኩላት፡፡  
የወረዳው የባህል ቡድን የጀመረው ዘፈንና ፉካሮ በአባቶች ፉካሮና ሽላሎ ተተክቶ ከአፍታ በኋላም ሁለቱም ይፈራረቁ ገቡ፡፡
‹‹ጣሊያን መንገድ ሰሪ እንግሊዝ መሪ ነው፣
የዚህ ሁሉ ጠቅላይ ኃይለ ስላሤ ነው››
ሲሉ የፎከሩት አባት ከጃንሆይ ወዲህ የነገሱትን ስድስት አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ረስተዋቸው ነው መሰለኝ፡፡ ወይንም ከነዚህ ሁሉ እንደ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሁሉ ጃንሆይን አስበልጠው ሳይሆን አይቀርም፡፡
‹‹እናንተ የዋሻውን ታሪክ ማግዘፍ ስለፈለጋችሁ አንደኛው ሰውዬ እኔ ልጅ ሆኜ የማውቀው አባቴ እዚህ ዋሻ ውስጥ ፍየሎች ሲገቡብኝ ለማስወጣት ስመጣ ይህ ዋሻ እኮ አባቶቻችን ጣሊያንን የተዋጉበት ነው ሲለኝ ነው፤ የማውቀው ይህን ብቻ ነው ሲል ምንም አልሰማችሁትም፡፡  እስኪ ሌላ ሰው ደግሞ ይናገር ብላችሁ እሱን ችላ አላችሁት፤›› አለኝ መምህር ዘላለም ተሾመ ከጉዞው መልስ፡፡  ይህን ትችት በመጠኑም ቢሆን የምቀበለው ሰውየውን አቋርጠናቸው ከሆነና ትህትና ነፍገናቸው ከሆነ ነው፡፡ ታሪኩን የተሻለ የሚያውቁት ሰዎች ስላሉ እነሱ ይናገሩ ለማለት አስቤ ነበር በኔ ቤት፡፡ ‹‹ከመንዝ ይልቅ ለተጉለት ታዳላለህ፤ መሃል ሜዳ ከተማንና ገበያውን ቅዳሜ ጠዋት እንድንጎበኝና እንድንገበይ የታቀደው ሲሰረዝና በጠዋት ወደ ደብረሲና እንሂድ ሲባል እያወቅህ ዝም ብለሃል›› ያለኝን ግን አልቀበለውም፡፡ ምክንያቱም ገበያው ደብረሲና መገብየት ይችላል ብዬ በማሰብና ለቀሩት ስፍራዎች መጎብኛ በቂ ጊዜ ለማግኘት አስቤ ስለሆነ፡፡
‹‹እንግድዋሻን ያላዩት ሰዎች እንዲያዩት ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ እንደምሰብክ ቃል እገባለሁ፡፡ መንገዱ ግን ቶሎ ቢሰራ ጥሩ ነው - አንድ ሰው ቢጎዳ ገጽታ ስለሚያጠፋ›› ይላል አበበ፡፡
በመጨረሻም በሁሉም በጎበኘናቸው ስፍራዎች ስለተደረገልን መስተንግዶ፣ ስለተጓዦች መነሳሳት እንዲሁም ዩኒቨርሲቲያችን ስላደረገልን ትብብር በማመስገን መምህር ዘላለም ተሾመ ስለ አጠቃላይ ጉዞው ስሜቱን በገለጸበት አረፍተ ነገር ሃሳቤን ልቋጭ - ‹‹አርብ ዕለት በጓሳ ምድራዊ ዓለማችንን አየን፤ በማግስቱ ቅዳሜ በምስካበ ኃዙናን መድሃኔዓለም ገዳም የእግዚአብሔር መንበር ገነትን አየን፤ ነገር ግን እሁድ በመጨረሻም የሚያሳቅቀውንና የሚያስፈራውን የሲዖልን መንገድ አየን፡፡›› 














































Funny Dance and Music, Ethiopia

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...