2021 ጃንዋሪ 21, ሐሙስ

የግል ቤተመጻሕፍት ለመክፈትና ለማንቀሳቀስ ስላደረኴቸው ነገሮች

 


(ፍላጎቱ ያላቸው እንዲጀምሩት በማሰብ የተጻፈ)

1.       መጻሕፍት በሽያጭ የማገኝባቸውን ቦታዎች አወቅሁ፡፡ እነዚህ ቦታዎች በአዲስ አበባ ያሉ የመጻሕፍት ማከፋፈያ መደብሮች ናቸው፡፡ መጀመሪያ ላይ ያገለገሉ መጻሕፍትንም እገዛ ነበር፡፡ በኋላ ግን ሻጩ ከየት አምጥቶ እንደሚሸጥልኝ ስለማላውቅ ትቻለሁ፡፡ ግለሰቦች ሲለግሱም እቀበላለሁ፡፡

2.       ሰፋ ያለ ቤት ተከራየሁ፡፡ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ መደርደሪያና መጻሕፍት አሟላሁ፡፡

3.       ሰራተኛ ቀጠርኩ፡፡ እኔም እሰራለሁ፡፡

4.       ንግድ ፈቃድ ‹‹የጽሕፈት መሳሪያና መጻሕፍት ችርቻሮ ንግድ›› በሚል ዘርፍ አወጣሁ፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ በንግድ ሕጉ ቤተመጻሕፍት የሚል ስለሌለ ይህን ዘርፍ መምረጥ ግድ ይላል፡፡ ግብር የሚተምኑ ሰዎች ሲመጡ የምሰራውን ስራ አይተው ግብር መተመን እንጂ ሌላ ይህን አትስራ የሚሉት ነገር የለም፡፡

5.       ስለቤተመጻሕፍት አሰራር ለማንበብ ሞከርኩ፡፡ በአማርኛ በዚህ ዘርፍ የተጻፈ ነገር ያለው ኮድ ኢትዮጵያ ያዘጋጀው ያልታተመ ሞጁል ነው፡፡

6.       ለቤተመጻሕፍቱ መጀመሪያ ሥራ ማስኬጃ የተወሰኑ አስርት ሺዎች ብር ተጠቅሜያለሁ፡፡ 

7.       የተለያዩ የቤተመጻሕፍት መርሃግብሮችን ጀምሬያለሁ፡፡ ለምሳሌ የውይይትና ሥነጽሑፍ ምሽት፣ የጉዞ መርሐግብር፣ ሥልጠና ወዘተ፡፡

8.       ሥራውን ልጀምር አካባቢ የጠየኳቸው ሰዎች ቢዝነስ ፕላን እንዳለኝ ጠይቀውኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ስለቢዝነስ ፕላን የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ለማዘጋጀትም አልሞከርኩም፡፡ ይህ ትልቅ ድክመቴ ነው፡፡ የሚጀምር ሰው ቢያዘጋጅ መልካም ነው፡፡

9.       ‹‹ይህን ስራ ስትሰራ ዓላማህ ምንድነው? በትክክል ጥርት ያለ ዓላማ ሊኖርህ ይገባል!›› ያለኝ ሰው ነበር፡፡ ያንንም ጥርት አድርጌ አለማወቄን እንደ ድክመት አየዋለሁ፡፡ ዓላማችንን ካላወቅን ተስፋ መቁረጥ ሊከተልና ስራውም አደጋ ላይ ሊወድቅ ስለሚችል ከመጀመራችን በፊት ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ማድረግ እንደማልፈልግ፣ በነጻ ማስነበብን፣ በቅናሽ ዋጋ ማከራየትንና መሸጥን ያካተተ ስራ እንደምሰራ አውቀው ነበር፡፡ አሁንም በዚያ እንደገፋሁበት ነኝ፡፡ አሁን ላይ ሆኜም ሳስበው ከኪራይ ቤት ብቆይ እመርጣለሁ፡፡ ቤት የመስራትን ጣጣ አልፈልገውም፡፡ የቤት ኪራይ ከከበደ መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ ገንዘብ የማመነጭበትን መንገድ እፈልጋሁ፡፡

10.   መጽሐፍ ስለማከራየት መግለጽ ያለብኝ ነገር ቢኖር በመታወቂያ ማከራየት አክሳሪ መሆኑን ነው፡፡ በቤተመጻሕፍታችን ከ200 በላይ ያልተመለሱ መጻሕፍት አሉ፡፡ በመሆኑም ከሁለት ዓመት አገልግሎት በኋላ ገንዘብ በማስያዝ እንዲከራዩ አድርገናል፡፡ ይህ አሰራር በእርግጥ ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች እንዳይከራዩ ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ ከሚያስከትለው ችግር አንጻር ሁነኛ መፍትሔ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ መከራየት የማይችል ሰው ቤተመጻሕፍቱ ባቀረበለት በነጻ የማንበብ ዕድል ይጠቀማል፡፡

11.   ‹‹ስራው አትራፊ ነው ወይ?›› ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ‹‹አንባቢ ባለበት ከተማ ሊያተርፍ ይችላል›› የሚል መልስ እሰጣለሁ፡፡ ወይም ከአትራፊ ቢዝነስ ጋር በጥምረት ሊሰራ ይችላል፡፡ ስራው የንባብ ጉዳይ ለሚስበውና ቤተመጻሕፍት ኖሮት ለማየት ለሚፈልግ ሰው ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያና ህብረተሰብን ማገልገያ መንገድ ነው፡፡

12.   ለተጨማሪ መረጃ ቢጠይቁኝ ለማገዝ ዝግጁ ነኝ፡፡ ምናልባት ስለ ቤተመጻሕፍቱ መረጃ ለሌላችሁ ሰዎች ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ይባላል፡፡ መገኛው ደብረ ብርሃን ነው፡፡ መጋቢት 2008 ዓ.ም ተመሰረተ፡፡ ንብረትነቱም የግል ሲሆን፤ በቤተመጻሕፍቱ በነጻ ማንበብ፣ በቀን 1 ብር በመክፈል መከራየትና እንዲሁም መግዛት ይቻላል፡፡

2021 ጃንዋሪ 12, ማክሰኞ

ንባብ ተኮር የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ለሁላችሁም

ከመዘምር ግርማ (mezemirgirma@gmail.com)

ዛሬ ላስተዋውቃችሁ የፈለኩት ጉዳይ ማናቸውም ሰው መጽሐፍ ሻጭ እንዲሆን ለማድረግ የሚቻልበት ዕድል መኖሩን ነው፡፡ ማንም ሰው ከቤቱ፣ ከመስሪያ ቤቱ ወይም ከተመቸው ቦታ ሁሉ ሊሰራው የሚችለው ይህ ሥራ ብዙ መነሻ ገንዘብ የማይጠይቅና የጊዜ ነጻነትም ያለው ነው፡፡ መጻሕፍትን ከደራስያን፣ ከአሳታሚዎች፣ ከሻጮችና አንብበወው ከሚሸጡ ግለሰቦች በመውሰድ ለተጠቃሚዎች ማድረስ ይቻላል፡፡ ይህን ሥራ በሚገባ ለመስራት አዳዲስና ያገለገሉ መጻሕፍት የሚገኙባቸውን ቦታዎች ማጥናት፣ ተፈላጊ መጻሕፍትን ማወቅና አንባቢ መሆን ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የመጻሕፍትን መገኛ ካወቅንና መጻሕፍቱንም ካነበብናቸው ዳሰሳ መጻፍ፣ ተናግረን ማሳመንና መሸጥ እንችላለን፡፡  ይህ ብቻ ሳይሆን በደንብ ባለመተዋወቃቸው ምክንያት ያልተሸጡ መጻሕፍትን አንብቦ ጥሩ ይዘታቸውን ለማስተዋወቅ ለአንባቢ ማድረስ ይቻላል፡፡  የዚህኛው ዓይነት ሥራ ጠቀሜታው ብዙ ቁጥር ያለውን መጽሐፍ በአንድ ጊዜ ለማግኘትና ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት መቻሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ዘአልኬሚስት የተባለው የፓውሎ ኮሊዮ መጽሐፍ በስድስት ወራት ሁለት ኮፒዎች ብቻ ተሸጦ ከብዙ ጊዜያት በኋላ በአንድ አጋጣሚ በሚሊዮኖች ቅጂዎች የተሸጠ መሆኑን ማስታወስ ግድ ይላል፡፡

መጻሕፍትን ለማን እሸጣለሁ የሚለው አንድ አሳሳቢ ጉዳይ ሊሆንብዎት ይችላል፡፡ ይህን እርስዎ እንደ አንድ የቤት ስራ ወስደው እነማን ማንበብ ይችላሉ ብለው እንዲያስቡ ያስፈልጋል፡፡ ማንበብ የሚችሉ ሰዎችን ወደ አእምሮዎ ማምጣት ከቻሉ እንዴት ላስነብባቸው የሚለው ይከተላል፡፡ ማንበብ ጀምረው ከሆነ በዚያው እንዲቀጥሉ የፈለጉትን መጻሕፍት ያቅርቡላቸው፡፡ በየመስሪያ ቤቱና በየሰፈሩ የመጻሕፍት ዕቁብ መስርተውም ለመጻሕፍት ዕቁቡ መጽሐፍ ያቅርቡ፡፡ የማንበብ ልምድ የሌላቸው ከሆኑም ልምዱን እንዲያጎለብቱ አድርገው ወደ ንባብ ዓለም ያስገቧቸው፡፡ ሰዎች በሚፈልጉት ነገር ማንበብ ቢጀምሩ ጥሩ ነው፡፡ ከሚፈልጉት ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ኃይማኖት ዝንባሌ ላላቸው ደንበኞችዎ ከአንድ የመጻሕፍት መደብር የኃይማኖት ማጻሕፍት ስብስብ ያሉ መጻሕፍትን ፎቶ አንስተው ያስመርጧቸው፡፡ የመረጡትንም ያቅርቡ፡፡ የሥራ ፈጠራ ዝንባሌ ላላቸው፣ የስነልቦና መጻሕፍት ለሚወዱ፣ የቴክኖሎጂ ለሚያዘወትሩ ወዘተ እያጠኑ ያቅርቡ፡፡ ለስራዎም ሃያ አምስት በመቶና ከዚያ በላይ ኮሚሽን ያገኛሉ፡፡ በቅርብዎ ያሉትን አንባቢያን ካካለሉ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በቢዝነስ ካርድ ወይም በሌላ ሁነኛ መንገድ ስለስራዎት ማስታወቂያ ይስሩ፡፡ ይህም ማስታወቂያ ወደ ክፍለሃገርና ወደ ውጪ ሃገር መጻሕፍትን መላክ ያስችልዎታል፡፡ መጻሕፍት ተቀባዮች ያምኑዎት ዘንድ ግድ ስለሚል እምነትን የሚገነቡ ነገሮችን ይመርምሩ፡፡

ሌላው ወሳኝ ነገር የእርስዎ አንባቢት በመሆኑ እርስዎ በቤትዎ የመጻሕፍት ስብስብ ይኑርዎ፡፡ ያንን ስብስብ ለማንበብም ሆነ ድንገት ሲታዘዙ ለመሸጥ ይጠቀሙበት፡፡ በሃገራችን ንባብ ገና ያልተነካና የማደግ እድሉ ሰፊ የሆነ ዘርፍ በመሆኑ ለብዙ ሺ ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በትንሹ አዟሪዎችንና አነስተኛ ሱቅ ያላቸውን ወገኖች ይመልከቱ፡፡ ለውጣቸው በየቀኑ የሚታይ ነው፡፡ ከማናቸውም ስራ ጋር የሚያስኬዱትና ትውልድን በማነጽ ላይ ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ የሚያስችልዎትን ይህን ዘርፍ ቢቀላቀሉ እንኳን ደህና መጡ ብለን እጃችንን ዘርግተን እንቀበልዎታለን፡፡ ከምረቃ በኋላ ሥራ አጥ ሆነው ቀን በቀን ገንዘባቸውን በመከስከስ ላይ ያሉ ወጣቶች የማንበብ ችሎታ እያላቸው ያንን ኢንቬስትመንት ለምን እንደማይጠቀሙት አይገባኝም! እነዚህ ወጣቶች ዕድሜያቸውን ያሳለፉት በመማር ስለሆነ ያንን ትምህርት ቢያንስ የአንባቢያንን ፍላጎት የሚያረካ መጽሐፍ በመምረጥ መጠቀምና መጽሐፉን ሸጠው ኮሚሽን ማግኘት ይቻላቸዋል፡፡

የኦንላይን ገበያ ወደሃገራችን እየገባ ስለሆነ በቅርብ ጊዜ መጻሕፍትን ማናቸውም ሰው መሸጥ እንደሚችል ከሌሎች ሃገራት ልምድ ማየት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ አሁኑኑ መጀመር ለወደፊቱ ልምድ እንዲኖርዎ ያስችላል፡፡

ጥያቄ ካላችሁ በአስተያየት መስጫው ላይ ብቻ ጻፉልኝ፡፡ ይህም የጥያቄዎችን መደጋገም ለማስቀረትና ምልልሱን ሁሉም አባል እንዲያየው ማለት ነው፡፡

መልካም ስራ!


በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...