2018 ዲሴምበር 1, ቅዳሜ

Learn Amharic in English

ኦባንግ ሜቶ በደብረ ብርሃን




በመዘምር ግርማ
19.3.2011

-የንግግሩ ሁኔታ የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግን ይመስላል፡፡
- አማርኛው አድምጡኝ አድምጡኝ ይላል፡፡



ወደ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መጥተው ንግግር እንደሚያደርጉ በግሌ ከአንድ ሳምንት በፊት ሰምቼ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በግልጽ ማስታወቂያ የተነገረው መምጫቸው ሲቃረብ ነበር፡፡ ረቡዕ ሕዳር 19. 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ የዩኒቨርሲቲው
ማኅበረሰብ በሰዓቱ ወደ መመረቂያ አዳራሽ መትመም ጀመረ፡፡ ተማሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ የተለያየ ልምድና የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሰራተኞች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች የፊተኛውን ረድፍ ይዘው በጉጉት ይጠብቁ ያዙ፡፡ እንግዳው ምን ሊናገሩ እንደሚችሉ ያወጋሉ፡፡
በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሰራተኛ የሆነው አቶ ጌታመሳይ አሳልፈው ተማሪዎችን በተመደበላቸው ቦታ ለማስቀመጥ ሲጥርና ይህም ተግባር ሲያስችግረው ያየው መምህር ጌታቸው ገብሩ ከአጠገቤ ተነስቶ ‹‹እኔስ ባስተባብር›› ብሎ ስርዓት አበጅቶ ተማሪዎችን፣ ሰራተኞችንና መምህራንን በየተመደበላቸው ስፍራ ማስቀመጥ ያዘ፡፡ ከዚህም የተማርኩት አንድ ሰው ቆሞ ከመመልከት ይመለከተኛል ብሎ መስራት እንዳለበት ነው፡፡ እኔ ያላደረኩትን ስላደረገ ጌታቸው በዚህ ይለያል ማለት ነው፡፡ ቆይተን እንደምናየው የአቶ ኦባንግም ንግግር ይህን ዓይነት የተግባር ስራ ጅማሮ መልዕክት የተላለፈበት ነበር፡፡
አንድ ሱፍ የለበሰና መነጽር ያደረገ ሰው በሩ ላይ በግርማ ሞገስ ሲታይ ማህበረሰቡ የጠበቀውን በማግኘቱ በአግራሞት ልቡ ወከክ አለ፡፡ እንደኔ ምልከታ ከወትሮው ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ውጪ ብዙም የተለየ ነገር በማታይበት ግቢ ንግግር የሚያደርግ እንግዳ መምጣቱ ለሁላችንም አዲስ ነገር ነው፡፡ እስከዛሬ የመጡ ቢኖሩም በአንድ ኬሌጅ የስብሰባ ዝግጅት ወይም ትምህርታዊ ጉባኤ ሊሳተፉ ስለሚሆን ሁላችንንም የሚያሳትፍ ላይሆን ይችላል፡፡
ኦባንግ ሜቶ ከእድሜያቸውም ሆነ ለሰው ካላቸው ቅርበት የተነሳ አንቱ ሊባሉ ሳይሆን እንደ ታላቅ ወንድም አንተ ቢባሉ ይሻላል ብዬ ስለማስብ አንባቢዬን ይቅርታ በመጠየቅ አንተ እያልኩ ጽሑፌን እቀጥላለሁ፡፡ የመድረክ ዝግጅቱ ተደረገ፡፡ በዚህም የቅድመ ዝግጅት ሂደት ድምጽ ማጉያው መስራቱን ለማረጋገጥ ባለሙያው አቶ እጀጌታው በተለያዩ ያገራችን ቋንቋዎች ‹‹ሙከራ 1፣ 2፣ 3›› እያሉ ተሳታፊውን አዝናንተዋል፡፡ ክስተቱ ለየቋንቋዎቹ ተናጋሪዎች ለእናንተም እውቅና እንሰጣለን ዓይነት መልዕክት የተላለፈበት ይመስለኛል፡፡ እዚህ ባይተዋር የለም ማለቱ መሰለኝ ባለሙያው፡፡
የእንግሊዝኛ ትምህርት ክፍል ኃላፊው ዶክተር ታደለ ፈንታው መድረክ መሪ ነበሩ፡፡ ስለ አብሮነት አንዳንድ ነገሮችን እየተናገሩና ስለኦባንግም መረጃ እየሰጡን መድረኩን በሚገባ አስተናብረዋል፡፡ ዝግጅቱ በማህበራዊ ሳይንስና ሰብዓዊነት ኮሌጅ አስተባባሪነት የተዘጋጀ መሆኑን እዚህ ጋ መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ ለወደፊቱም እንደዚህ ዓይነት ዝግጅት ቢካሄድ መልካም ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ለዚህ ተግባራዊነት በዝግጅቱ ላይ ቃል ገብቷል፡፡
አዲስ የተመረጡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኃይለማርያም ብርቄ የመክፈቻ ንግግር አድርገው እንግዳውን ጋብዘዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን ትንሿ ኢትዮጵያ እንደሆነችና የጋራ መግባባት ሊኖረን እንደሚገባ ያስገነዘቡት ፕሬዚዳንቱ በኦባንግ ንግግር መርካታቸውን መስክረዋል፡፡ የእንግዳው ማንነትና የህይወት ልምድም በዶክተር ታደለ ቀርቧል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከመጀመሪያው ጀምረው እስከ ዝግጅቱ ፍጻሜ ድረስ በማወያየትና የአቶ ኦባንግን ንግግር በመከታተል አብረውን ስለቆዩ ማመስገን ይገባናል፡፡ ወደፊትም የእውነት የትምህርት ተቋም ይኖረን ዘንድ የሚያግዙ እንደዚህ ዓይነት ዝግጅቶችን በማቀድ፣ በመፍቀድና በማካሄድ ደብረ ብርሃንን እንደስሟ ብርሃን ያደርጓታል ብዬ አምናለሁ፡፡

አቶ ኦባንግ ሜቶ ንግግሩን የጀመረው በእንግሊዝኛ ነበር፡፡ የተወሰኑ ደቂቃዎችን በእንግሊዝኛ ካቀረበ በኋላ ስለቋንቋ አጠቃቀሙ አንዳንድ ነገር መናገር ጀመረ፡፡ ‹‹ለእኔ የሚቀናኝ እንግሊዝኛ ነው፡፡ በልጅነቴ እስከ ስድስተኛ ክፍል የተማርኩት አማርኛ እየጠፋብኝ ስለሆነ አሁን እንደገና እየተማርኩ ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት ጎንደር ሄጄ አማርኛ መምህር ልሆን እችላለሁ›› ብሏል፡፡ ከዚህም በማስከተል ንግግሩን በአመዛኙ በአማርኛና አልፎ አልፎ አንዳንድ ጥቅሶችን በእንግሊዝኛ አቅርቧል፡፡
ውድ አንባቢዬ፣ ይህን ያህል ደጅ ካስጠናሁዎት ዘንዳ አሁን ኦባንግ በደብረ ብርሃን ምን ተናገረ ወደሚለው እንምጣ፡፡  

ማንነቱ
ኦባንግ እንደየሁኔታው የአኝዋክ ተወላጅ፣ ጥቁር፣ ውጪ የተማረ፣ ኢትዮጵያዊ ወዘተ ሊባል ይችላል፡፡ የሰብዓዊ መብት ታጋይ የሚለው ግን እኛም ዛሬ ስለሱ እንጽፍ ዘንድ ያስገደደን ስለሆነ በዚህ ብንጠራው ጥሩ ይመስላል፡፡ ኦባንግ የተለየ ግርማ ሞገስ አለው ሲል ከተናገረው ከዶክተር ታደለ ጋር የማይስማማ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ እርጋታ፣ ቅንነት፣ ትህትና ወዘተ መልካም ቃላትን ሁሉ ብንደረድር ለኦባንግ ይገባዋል፡፡

አንድ ጣታችንን ሌላ ሰው ላይ ስንጠቁም ሦስቱ ራሳችን ላይ ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ጥቅስ በሚገባው ቦታ ተጠቅሞበታል ኦባንግ፡፡ አሁን አገራችን ከገባችበት አጣብቂኝ ለመውጣት ብቸኛ ሙሴ አለ አይደለም የኦባንግ ንግግር፡፡ ሁላችንም ለጠፋው ጥፋት መድህን መሆን አለብን ይለናል፡፡ 
‹‹ከእናንተ እንጂ ዶክተር ዓቢይ አይደለም፡፡ ከእናንተ እንጂ ከዶክተር ኃይለማርያም አይደለም፡፡ ከእናንተ ነው ይህች አገር ብዙ የምትጠብቀው፡፡ ለውጥ ማምጣት የምንችለው 100 ሚሊዮኑ ሲተጋ ነው እንጂ በተወሰኑ ሰዎች አይደለም፡፡›› ይለናል መርፌ ቢወድቅ በሚሰማበት፣ ኮሽታ ባልነበረበት ትልቁ አዳራሽ የተገኘው ጥቁር ሰው!
 ‹‹ይህች ጥንታዊት ከተማ፣ ይህች የእምዬ ምኒልክ እትብት የተቀበረባት ስፍራ፣ ይህች ውብ ስፍራ፣ ደብረ ብርሃን እንደዚህ የሆነችው ደሃ ስለሆንን አይደለም - የአመራር ድህነት፣ የአስተዳደር ችግር፣ የቅንነት መጥፋት ስላጠቃን እንጂ›› ይለናል የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መስራች ኦባንግ፡፡
በአኝዋክ ባህል የመጀመሪያ ልጅ ኦባንግ እንደሚባል ሰምቼ ነበር፡፡ ኦባንግ እውነተኛ የኢትዮጵያ የበኩር ልጅ መሆን አስመስክሯል፡፡ የታሰሩ፣ የተገደሉ፣ የተሰደዱ፣ የተንገላቱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ እንደሚያሳስበው ብቻ አይደለም የተረዳነው፡፡ አገር ውስጥና ውጪ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ጉዳይ እየተከታተለ የሚታገዙበትንና ችግራቸው የሚፈታበትን መንገድ የሚቀይሰው ከአኝዋክ ወይም ከጋምቤላ ስለመጡ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር አብረን በመኖራችን ስለሚያውቃቸው እንጂ፡፡ ያስተማረውን ህዝብ ለመካስ እንጂ!
በጃፓን፣ በማልታ፣ በኖርዌይ፣ በሜክሲኮ በበርካታ አገሮች በመዘዋወር ችግር ላይ ያሉና ቀን የከፋባቸውን ኢትዮጵያውያን አግኝቶ አጽናንቷል፡፡ ከጎናቸው እንዳለ አስመስክሯል፡፡ ከሃያ በላይ ሃገር ዞሮ ዜጎቻችንን የሚረዳው ህሊና ስላለው ነው፡፡ ከጎሳ ይልቅ ሰብዓዊነትን እናስቀድም በሚል መርህ የሚንቀሳቀሰውን የኦባንግን ጅማሮ ለማግኘት በበይነመረብ solidaritymovement.orgን መጠቀም ይችላሉ፡፡ ለተጀመረው ተስፋ ሰጪ ጉዞ ሁላችንም አለኝታነታችንን ማሳየት አለብን፡፡ 

ለብሔራዊ መከባበርና መተሳሰብ መንገዱ የተጠረገበት ስብሰባ ዋና ክፍል የኦባንግ ገለጻ ነው፡፡ ርዕሱም THE WAY FORWARD: CAN THE RIGHT CHANGE BE SUSTAINED IN ETHIOPIA? ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ለውጥ ማለትም በውጪ የነበሩ ኦባንግን ጨምሮ በአሸባሪነት የተፈረጁና አገራቸው እንዳይገቡ እገዳ የተጣለባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋጮች መግባታቸው፣ እስረኞች መለቀቃቸው፣ ከኤርትራ ጋር የነበረው ፍጥጫ ወደ ሰላማዊ ጉርብትና መቀየሩ፣ ሚዲያዎች በነጻነት እንዲሰሩ መፈቀዱ፣ ለሃገራዊ መግባባት መንገድ እየተጠረገ መሆኑ፣ አሁን ያለው አጠቃላይ የለውጥ ተስፋና የዶክተር ዓቢይ ቡድን እያስመዘገበ ያው ውጤት የንግግሩ ማጠንጠኛ ነበር፡፡ እንደዚህ ተገናኝተን ስለ ሰብዓዊነታችን፣ ስለኢትዮጵያዊነታችንም ሆነ ስለችግሮቻችን መነጋገር ወንጀለኛና አሸባሪነት ተደርጎ እንደነበረና መሰብሰባችን በራሱ አሁን ያለው ለውጥ ውጤት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ለውጥ ትክክለኛ እንሆነ፣ ልንንከባከበው እንደሚገባ፣ በተለይም ወጣቱ ዋነኛ የለውጡ ጠበቃ መሆን እንደሚኖርበት ኦባንግ አስገንዝቧል፡፡ ይህን ለውጥ ለማምጣትም ሆነ ኢትዮጵያን እንደሃገር ለማቆየት ለተጉና ሕይወታቸው ላለፈ ሁሉ የሕሊና ጸሎት በማድረግ ነበር ዝግጅቱ የተጀመረው፡፡

በበኩሌ ስለሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ተርጉሜው የነበረውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ ለእንግዳው አበርክቻለሁ፡፡ ለእርቅና ለአብሮነት ለሚያደረርገው ስራ የበኩሌን ለመወጣት ፍላጎትም አለኝ፡፡

ተሳታፊ የነበራችሁ ሰዎች ‹‹እስካሁን ያጠፋነውን በመቶ ዓመት አለንመልሰውም›› ሲል የተናገረውን እንዴት አያችሁት? ‹‹ሳናውቀው የጎሳ አስተሳሰብ ተጠቂ ነን›› ያለውንስ? የዘነጋኋቸውን ነጥቦችም እያነሳሳችሁ ብንወያይበት ጥሩ ነው እላለሁ፡፡

አንድ የኦባንግ አብሮ አደግ በቅርቡ አዲስ አበባ ሻይ ቡና ለማለት በተገኛኑበት ጊዜ ‹‹እኔ ጉራጌ ነኝ፡፡ ጉራጌ ነኝ፡ ጉራጌ፣ ጉራጌ…›› እያለ እንዳስቸገረውና ይህንም ዛሬ ያወቀው ይመስል እንደደጋገመበት ነግሮናል፡፡ የጎሰኝነትን አባዜና የገባንበትን አጣብቂኝ በብዙ ምሳሌዎች አስረድቶናል፡፡ ‹‹በምርጫችን አይደለም ከተፈጠርንበት ብሔር የተፈጠርነው›› ይለናል፡፡ 
ኦባንግ ውጪ ሲማር ከ3000 ተማሪ ብቸኛው ጥቁር እንደነበረ ነግሮናል፡፡ ‹‹ጥቁርነቴ ትዝ አይለኝም፡፡ ቆዳየን ልጆች በአግራሞት ቢነካኩም፡፡ በትምህርት ቤታችን በጣም ጥቁር ልጅ አለ እያሉ ለቤተሰብ ቢናገሩም፡፡›› ይለናል፡፡

ሕገመንግስቱ ስላለበት ችግርም ነጻ አውጪዎች ያወጡት እንደሆነና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተሳትፎ እንዳልነበረበት አስገንዝቧል፡፡ ‹‹ነጻ አውጪዎቹ ከማነው ነጻ የሚወጡት - ከኢትዮጵያ ነው፡፡ እነሱ ኢትዮጵያን መሪ ለመሆን በቁና ይህን ሁሉ ጥፋት አመጡ፡፡›› ብሎናል፡፡

ከንግግሩ በኋላ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ ተሳታፊዎችን ከዝግጅቱ በኋላ አናግሬ በዝግጅቱ እንደረኩ ነግረውኛል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ምሳሌ የሚሆን ንግግር ነው፡፡ እንደሱ ዓይነት ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ እንደዚያ የምናገር ምሁር ቢኖር አገራችን ትለወጥ ነበር፡፡›› ወዘተ በማለት ለንግግሩ ያላቸውን አድናቆት ነግረውኛል፡፡

ሰላማዊ የትምህርት ሂደት የሚካሄድበት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ስለ እርቅ፣ ሰላም፣ የፍትሕ መመለስ በሃገሪቱ እየተዘዋወረ ከዜጎች ጋር መነጋገርና ያለውን ሁኔታ በመረዳት ላይ ያለውን የሰብዓዊ መብት ታጋይ መጋበዙ ያስመሰግነዋል፡፡

ሰብዓዊነት ይለምልም!

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...