2017 ሜይ 24, ረቡዕ

የትምህርት ቤቶቹ የስፖርት ድግስ፤ የጉዞ ማስታወሻ፤ መዘምር ግርማ እንደጠረቀው



በየሁለት ዓመቱ የኩሳዬ ትምህርት ቤትና የዳዎ ትምህርት ቤት የስፖርት ፌስቲቫል ስለሚካሄድ በ10/9/2009 ወደስፍራው ያቀናነው ሦስት የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ልዑካን ቡድን አባላት አረፋፍደን ነበር የደረስነው፡፡ መቼም በቅጥቅጥ መኪና ስንጓዝ ይቺ ቅጥቅጥ ለምን ከአገራችን እንደማትጠፋ ጠየቅ አደርጋለሁ፡፡ ለሰው መሳፈሪያ የሚሆን መኪና ይመጥነናል፡፡ መኪና መግዣ ገንዘብ እንደሆነ መውጣቱ አልቀረ፡፡ ስለሆነም የሚመለከተው ይመልከተው በማለት ወደሌላ ጉዳይ አልፋለሁ፡፡ ለዚያውም አዳሩ ካፍ እስከገደፉ ጢም ብሎ ሞልቶ ነው የሚሄደው፡፡  ኮርቶመጋላ ላይ ሳይቀር ሰው እንደሚጫን አገሬው መኪና ውስጥ ሲያወራ ነበር፡፡ ይህን መቼም አታኑም አይደል!በእጃቸው ጥብቅ አድርገው ብረቷን ይዘው በአየር ላይ እየተንሳፉ ሲሄዱ መኪናዋ እንደፎቅ ሆነች ማለት ነው፡፡ የጭነት መኪና እንዳሆነ ግንዛቤ አድርጉ፡፡
እነዋሪ ልንደርስ ስንል ተማሪዎች ይዞ ይጓዝ የነበረ መኪና መንገዱን ስቶ ዘንበል ማለቱን ስናይ እንኳንም ተሳፋሪዎቹ አልተጎዱ አልን፡፡
የእነዋሪ ጥብስ፣ ያው የጅሩ ሰንጋ ባጠቃላይ፣ ልዩ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡ በልተናልና ግድ ስለሚለን! ሸክላ ጥብስ ስለማልወድ ይህንን ግማሽ ኪሎ ስጋ አስጠብስልን አልኩት፡፡ ሦስት ነን፡፡ ‹‹በቃ ውስጥ ስለሚጠበስላችሁ 15 ብር ያስጨምራል - የዘይቱ ምናምን - መቶ ብራችሁ ቻለ›› አለን፡፡ እስኪ ይሁን እያልን ገባንና መጣች ያች የፈረደባት ጥብስ፡፡ እንጀራው በመረቅ ሟሙቶ እንጀራ አነሰን፡፡ ግማሽ እንጀራ ጨመሩ - ሦስት ብር አስጨመሩን፡፡ አንድ እንጀራ ስድስት ብር ነው ማለት ነው ብዬ ለነዋሪ አዘንኩ፡፡ የጅሩ ሆቴል ቆይታችን ይህን ይመስላል፡፡ በየመንገዱ የማውቃቸውን ሰዎ ሰላም እያልኩ ወደ መናኸሪያ!
ከእነዋሪ ኩሳዬ ቅርብ መንገድ ስለሆነ ክፍያውም ስድስት ብር ብቻ ነው፡፡ ኩሳዬ ደርሰን የኩሳዬን እምብርት (የራስ አበበን ግቢ) ጎበኘን፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ሐውልት ሊገነባ እንደታቀደ ሰምቻለሁ፡፡ ይበል ብያለሁ፡፡ ኩሳዬ ላይ ቦታ ስንጠይቀው ‹‹ካስፋልቱ ሄድ ብሎ›› ያለን ልጅ አስቆኛል፡፡ አስፋልት ጅሩን አያውቃትም - እነዋሪ ከተማው ውስጥ ግን ለህዝቡ ጤና ተብሎ ተሰርቷል መሰለኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነት አሰራር ተጀምሯል በወረዳ ከተሞች፡፡ ቁልቋል በከበባቸው ቤቶች የሚኖሩት ኩሳዬዎች የውሃ ነገር አልሞላላቸውም፡፡ ውሃ ላይ ቆመው ውሃ ስለሚጠማቸው በአህያ መጫን ግድ ይላቸዋል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ መጀመሪያም የተጋነነ በጀት ክልሉ ያዘ፡፡ ያንንም ገንዘብ ያለአግባብ አባክነው ጥቅም ላይ ሳያውሉ ቀሩ፡፡ የተበላሸ ዕቃ ገጠሙለት፡፡ ችግሩን ለማስተካከል እየተሞከረ መሆኑን ያየሁት አምና ተሰቅሎ የነበረው የላሜራ ብይድ የውሃ ጋን ወርዶ ዘንድሮ የፕላስቲኩ ስለተሰቀለ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኑ ቅርብ እንደሆነ ያየነው ከጎበኘነው በኋላ ነው፡፡ በውሃው ልማትም ሆነ በቤተክርስቲያኑ ስራ ሁለት ሰዎች ተደጋግሞ ይመሰገናሉ - አንደኛው በትምህርት ሌላኛው በመከላከያ ዘርፍ ያሉ ናቸው፡፡ ማን ማን እንደሆኑ ገምቱ፡፡
ትምህርት ቤት ስንደርስ ፌስቲቫሉ ቀልጧል፡፡ ተማሪዎች ቡድናቸው ግብ ሲያስመዘግብ እየጨፈሩ ሜዳውን ይዞራሉ፡፡ ሳሲት ትምህርት ቤት ዓመታዊ የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር ሲካሄድ የነበረውን የልጅነት ትውስታ ቀሰቀሰብኝ፡፡ 1500 ሜትር የፈላ ትምህርት ቤት በተለይም የውቤ ነበር፡፡ ሳሲቶች ምን እንደምናሸንፍ ጠፋኝ፡፡ እምቧይባድ አጭር ርቀት ላይ ዳኜ የተባለ ተርብ ነበረው፡፡ የወረዳው ምርጦች  ሸዋሮቢት ሄደው በስፖርትም በጥያቄና መልስም ተወዳድረዋል፡፡ ተሳታፊ የነበራችሁ ትዝታችሁን ጻፉልን፡፡ ዳምጠው አድማሱን እንዲጽፍ ለማነሳሳት ነው፡፡ ተመለስን ወደ ጅሩ ፡-  አቶ አሳምነውን አግኝተነው በቤተመጻሕፍቱ አቀባበል አደረገልን፡፡ በጥሩ ሁኔታ የተያዘ ቤተመጻሕፍት ነው፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሰራዊት ከሚለው መጽሐፍ ስለ ራስ አበበ አረጋይ አበበልን፡፡ ከዚያም ወደ መምህራን ቤት ሄደን ተጋበዝን፡፡ ስለትምህርትና ስለተለያዩ ነገሮች ተነሣ፡፡ መምህራንና ሰራተኞች ያላቸው ቤተሰባዊ ፍቅር ያስደስታል!
አቶ አሳምነው ባለፈው ዓመት የለገስኳቸውን መጻሕፍት ከርዕሰመምህሩ ቢሮ ተቀብሎ አምጥቶ መዝግቦ አሳየኝ፡፡ እስከዛሬ ድረስ ለጥቅም ሳይውሉ መክረማቸው እሱንም አሳዝኖታል፡፡ የ580 ብር መጻሕፍት አግዘኸናል ያለኝ ግን አልተዋጠልኝም፡፡ እኔ ጊዜው ረዝሞ ካልረሳሁት በስተቀር የአንድ ሺህ ብር መጽሐፍ ነበር የሰጠኋቸው፡፡ ጠፍቶባቸው ይሆን እንዴ? አቶ አሳምነው መምህራንን ››እናንተ ሳይኮሎጂ አታነቡ፣ ምን አታነቡ፤ መመሪያውን አታውቁት፤ በቀደም ያ ልጅ መባረር የለበትም ብዬ መመሪያውን ያሳየኋችሁ እኔ ነኝ›› እያለ ይወቅሳቸዋል፡፡ ድፍረቱ ገረመኝ፡፡ እኛ መምህራን እናነባለን እንዴ? በፊት የሕብረተሰብ መምህር እንደነበረና አሁን በፍላጎቱ ወደ ቤተመጻሕፍት ሰራተኝነት እንደገባ ነገረኝ፡፡ ተግባቢና የዕውቀት ሰው ነው፡፡ መምህሩ በሳይክል ብር እያለ እነዋሪ ነው የሚውለው የሚል ነገርም አወጋኝ፡፡ ቤት ስራ ጀምረዋልና ከክፍለጊዜያቸው በኋላ ትምህርት ቤት ግቢ አይታዩም፡፡ ባለፈው ዓመት ለመደራጀት ገንዘብ ስላጡ ቦታውን ለገበሬ ሊሸጡት ነው ያለኝ ነገር ለማናቸውም ተስተካክሏል ማለት ነው፡፡ የአቶ አሳምነው ባለቤት የበቻሬ የልጅ ልጅ በመሆኗ ከራስ አበበ ትዛመዳለች - ራስ አበበ አረጋይ በቻሬ፡፡
ለውድድር ከመጣው ከዳው ትምህርት ቤት አንድ የደብረ ብርሃኑን የራስ አበበ ቤተመጻሕፍት የሚያውቅ መምህር አገኘን፡፡ መምህሩ በክረምት መርሃግብር ዩኒቨርሲቲ ስለሚማር ነሐሴ 12፣ 2008 ባደረግነው የአጤ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ልደት አከባበርና ውይይት ላይ እንደተገኘ ሲነግረኝ አስታወስኩት፡፡ ትምህርት ቤቶቹ በስልጠና ቢታገዙ ጥሩ ነው የሚል ሐሳብ መጥቶልኛል፡፡
እና ምን አለፋችሁ መቼ በትምህርት ቤትና በራስ አበበ ግቢ ጉብኝት ያበቃል የኛ ቆይታ! ይህ ተርብ የቤተመጻሕፍት ሰራተኛ አገር ላሳያችሁ ብሎ ይዞን መሄድ፡፡ የቲያትር ቤት የወንበር አቀማመጥ በመሰለ አደራደር የተደረደሩ ተራሮችን አይተን ሆዳችን ባባ፤ ደስ አለን፤ ብረሩ ብረሩ አለን፤ የሳሲትን መንገድም አቅጣጫውን አየሁት፡፡ በነገራችን ላይ የሞጃና ወደራንና የሞረትና ጅሩን ወረዳዎች የሚያገናኝ የጠጠር መንገድ እየተሰራ ነው፡፡ ጅሩ ቅርባችን ሳይሆን አይቀርም ለሞጃዎች፡፡ ሳሲት ብዙ ወሬዎች አሉ ስለጅሩ፡፡ ስርጦቹን ራስ አበበና ወታደሮቻቸው እየወጡ እየወረዱ ከጣሊያን ጋር እንደሚዋጉባቸው አሳምን ሲነግረኝ እኔ ራሴ ይህን አስቸጋሪ መንገድ መሄድ እንደሚከብደኝ እያሰብኩ አድናቆቴን ለሸዋ አርበኞች! ‹‹እዚች ጋ አንድ ጀግና ተመቶ አርፏል፡፡ መጀመሪያ መሳሪያ አልነበራቸውም - በኋላ ግን ማርከው የኃይል ሚዛኑ ተስተካከለ›› እያለ ታሪክን የኋሊት አስቃኘን፡፡ የውሃ ጋኑ ታች ቆላው ላይ ነው፡፡ ውሃው ሞልቶ ይፈሳል፤ በባህላዊ መስኖ የለማውን አገር አየነው፡፡ ባለመስኖዎቹና የኩሳዬ ነዋሪዎ በውሃ ያለባቸውን ግጭት ፍቱላቸው - አስታርቋቸው - እትዬ ዘወድነሽ መሯታል የውሃው መቆራረጥ ነገር፡፡ ሚኪና ሩት አገሩን ማስጎብኘት እንደሚቻል ሃሳብ እያቀረቡ እኛ አገራችንን የማየት ልማድ ለምን እንደሌለን ሲጠይቁኝ ነበር፡፡ እነዚህን በሃያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች በማስጎብኘቴ ደስ ብሎኛል፡፡ ሚኪ ጸጉሩን እንደራስ አበበ አጎፍሮ ነበር፡፡ ሁለት ገጽ የጉዞ ማስታወሻ በወረቀት ጽፎ ኮምፒውተር ቤት ሰጥቷል፡፡ ከዚያ በፍላሽ ወስዶ ለእናንተ ለማጋራት፡፡ ደረሰልህ ወይ በሉት ደውላችሁ - 0912906228 - አንቺ ማነሽ- አደራ መጥበስ አይቻልም፡፡
ማታ ተመልሰን በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ያው ሐሙስ ስለነበር የውይይትና የስነጽሑፍ ምሽቱ ላይ የጉዟችንን ሪፖርት አቀረብን፡፡ እኔ ስለ ሕዝቡ፣ ሚኪ ስለ አካባቢው እና ሩት ስለ ታሪኩ፡፡ ያልሄዱ ቢቆጫቸውም አሳምን የላከላቸውን የጅሩ ዳቦ እንዳምናው እየበሉ ታድመዋል፡፡ የሚጋገረው ዳቦ ብዛት ለቁጥር አዳጋች ነው፡፡ የስፖርት ወይስ የዳቦ ፌስቲቫል! ለጥቅምት አቦ ሁላችሁም ተጠርታችኋል፡፡ ያኔ አገሩ ይለመልማል - ይምራል አሉ፡፡
ረስቼው 1. በፈረስ ሲታረስ ለመጀመሪያ ጊዜ አየሁ፡፡
ረስቼው 2. መኪና ውስጥ ስንሄድ ያገኘኋቸው እናት ንቃተህሊና ይገርማል፡፡ ሸዋዎች ቀላሎች አይደሉም ያስብላችኋል!
ረስቼው 3. መንገዱን አስፋልት እንዲያደርጉት መቀስቀስ ያሻል፡፡
ረስቼው 4. የኩሳዬን ትምህርት ቤት ያሰራው ሜንሽን ነው፡፡
ረስቼው 5. ኩሳዬ ብዬ በይነመረብ ላይ በአማርኛ ብፈልግ ብዙ ነገር አገኘሁ፡፡ በነገራችን ላይ በአማርኛ ጉግል ላይ ብትፈልጉ ብዙ ነገር አለ፡፡
በመጨረሻም ሌላ ብዙ አውቄ የረሳኋቸው ነገሮች ስላሉ ሄዳችሁ እንድታዩ ይሁን!


2017 ሜይ 12, ዓርብ

2017 ሜይ 9, ማክሰኞ

አሁንም አርበኞች አሉ!




ማሳሰቢያ፡- ይህ ጽሑፍ የዘንድሮውን የአርበኞች በዓል አከባበር አስመልክቶ የተጻፈ በመሆኑ የአንዲት ግራርንና የአርበኞችን ታሪክ በጥልቀት አይዳስስም፡፡ ያንን የምትፈልጉ አንባብያን ባለፉት ዓመታት የጻፍኳቸውን ጽሑፎች እንድታነቡ እመክራለሁ፡፡
በዓል በሚበዛበት በዚህ በሚያዝያ ወር፣ በተለይ በመጨረሻው ሳምንት፣ ስራ በዝቶብኝ ከረምኩ፡፡ በወሩ የመጨረሻው እሁድ ቅዳሜ የተለያዩ ጥሪዎች ነበሩብኝ፡፡
ሀ.  የዩኒቨርሲቲያችን ባህል ማዕከል ዓመታዊውን አገር አቀፍ ዓውደ ጥናት ያካሂድ ነበር፡፡
ለ. ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት 75ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ ያዘጋጅ ነበር፡፡
ሐ. የሞጃ አርበኞች ዓመታዊ በዓል ነበራቸው፡፡
መ. የአንዱ ወዳጄ ሠርግ ነበር፡፡
ሠ. የጓደኛዬ ልጅ ክርስትና ነበር፡፡

ሐሙስ (26/8/9)
ይህን ሁሉ ዝግጅት አብሮ ማስኬድ ስላቃተኝ ተጨነቅሁ፡፡ ዘወትር ሐሙስ ማታ በሚከናወነው የውይይትና የሥነጽሑፍ ምሽታችን የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ቤተሰቦችን ስለ አርበኞች አወያየን፡፡ በዚሁ ሳምንት በቤተመጻሕፍቱ የአርበኞችን ሳምንት አስመልክተን በሁሉም የሽያጭ መጻሕፍት ላይ የ10 በመቶ የዋጋ ቅናሽ አድርገን ነበር፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ገዛዝተዋል፡፡ እንደሚያነቡም ባለ ሙሉ ተስፋ ነን፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት ታሪክ አዋቂው አቅራቢያችን አቶ አዲሱ ሞላወርቅ የጅሩ ተወላጅ በመሆናቸው ስለራስ አበበም ሆነ ስለሌሎቹ አርበኞች ሲሰሙ ያደጉ መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ እስኪ ከትምህርታቸው በጥቂቱ ላቃምሳችሁ፡- ‹‹የአገሩን ታሪክ የማያውቅ ህዝብና አባቱን የማያውቅ አንድ ነው፡፡ ትውልዱ ታሪክ-ጠል እና አባቶቻችን የሚንቋቸውን አውሮፓውያንን የሚናፍቅ ሆኗል፡፡ ታሪክን ለማሳወቅ ሃላፊነት ያለብን በመሆኑ እንዲያነቡና አባቶቻችን ሳያነቡና ሳይማሩ የአገር እሳቤ እንዴት እንዳዳበሩ እንዲገነዘቡ ማገዝ ያስፈልገናል፡፡ ስለ አያቶቻችን ሳናውቅ አገራዊ ስሜት ልናሳድግ አንችልም፡፡ አባቶቻችንና እናቶቻችን ከ1000 ኪሎሜትር በላይ ሄደው ሞተው ያቆዩልንን ታሪክ ለምንድነው የማናቆየውና የማንወደው ብላችሁ እስኪ ጠይቁ፡፡ የኛን ታሪክ በብዛት የጻፉት ነጮች ናቸው - እንደፈለጉት እያደረጉ፡፡ እኛ ምን እየሰራን ነው?››
ዐስራ ስድስት ሰዎች በተገኘንበት ውይይት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ስለነበር እናንተ ያልተገኛችሁት ሰዎች ደግሞ እስኪ ለጥያቄዎቹ የየራሳችሁን መልስ ስጡን፡-
ሀ. ቅኝ ተገዝተናል ወይስ አልተገዛንም?
ለ. መገዛት ነው መወረር የሚለውን ሰው አወቀልን አላወቀልን ምን እንጠቀማለን?
ሐ. የሞሶሎኒ ዕቅድ ተሳክቶ ነበር ወይ?
መ. ስለዚህ ታሪክ ማውራታችን አሁን ምን ይጠቅመናል?
ሠ. ሃገራዊ ስሜት ጠፍቶ እንዴት ጠበን ጠበን ጋጣ ውስጥ መጣን?
ረ. የአሁኑ ትውልድ ስለ ሐገር ሲነሳ የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ለምን ይላል?

አርብ (27/8/9))
በማግስቱ አርብ ጠዋት ጉዞ ነበረብን፡፡ ወደ አንዲት ግራር፣ ሳሲት አቅራቢያ፣ በሰላድንጋይ መንገድ፣ እንሄድ ነበር፡፡ ጠዋት መናኸሪያ ደረስኩ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የሚሄደውና ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ከኔ ጋር የሄደው ሳለአምላክ ጥላሁን መጣ፡፡ እኔም ባለፈው ዓመት ስላልሄድኩ እንደሱው ነኝ፡፡ ቆየት ብላ ሩት መጣች፡፡ የራስ አበበ ቤተመጻህፍት ባልደረባ ነች፡፡ ከዚያም ለዚሁ ዝግጅት ስትል በዋዜማው ከአዲስ አበባ የመጣችው ብርቱካን ካብትህይመርም ብቅ አለች፡፡
በመጀመሪያ እኔ ሰው ካልመጣ እመለሳለሁ ይል የነበረው መምህር ሳለ አሁን እየተረጋጋ መጣ፡፡ ቆየት ብለው ሁለት የህግ መምህራን ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ ገጣሚው መስፍን ወንድወሰንና ባልደረባው አብርሃም ተቀላቀሉን፡፡ ከሆነ አይቀር ብለን ከመናኸሪያው ፊት ለፊት በመሰራት ላይ ባለው ህንጻ ምድር ቤት ላይ ቁርስ እንበላ ያዝን፡፡ የአዲስ አበባው የማህደረ ሸዋ ልዑካን የሆኑ ሁለት ወጣት ትውልደ -ሞጃ ጋዜጠኞች መጡና ቁርሳቸውን በልተው ወደ ሰላድንጋይ በሚሄደው መኪና ውስጥ ገባን፡፡ እዚያም ያለ ስራ አልተቀመጥንም ነበር፡-
ሀ. ቼ በለው ኧረ ቼ በለውን እየተቀባበልን ዘፈንን
ለ. ከዚያም ለተሳፋሪው የምናውቀውን የአርበኞች ታሪክ ለማስገንዘብ ተነስቼ ስጀምር መቀዛቀዝ ታየኝ፡፡ ወዲያው አካሄዴን ቀይሬ በአርበኞች ግጥም መጣሁ - በጥሞናና በፍላጎት መከታተል መጀመራቸውን ሳውቅ ወደ ጉዳዬ ገባሁ፡፡ በጥያቄና መልስም በደንብ ሊዳብር የቻለ ውይይት አደረግን፡፡

ሰላድንጋይ
ይህች የጠበለተኛ ከተማ እያማረባት ነው፡፡ አዲሱ ህንጻ ንብረትነቱ የአብቁተ ነው አሉ፡፡ መኪናው ከዱሮው በተለየ መልኩ ይርመሰመሳል፡፡ ባጃጁ ምኑ ቅጡ! ያለ ብዙ ረፍት በቀጥታ ወደ ሳሲት አመራን፡፡ ሳሲት መገንጠያ ባለው የመንግስት አስተዳደር ጽ/ቤት በአንዲት ፒካፕ መኪና ላይ በርካታ ወጣቶች ተጭነዋል፡፡ የወረዳው የባህል ቡድን አባላት መሆናቸውን ነጋሪ አላስፈለገኝም፡፡ በባንዲራ አሸብርቀው መኪናችንን ተከተሏት፡፡ የሳሲቱ መንገድ አስፋልትን ያስንቃል፡፡ የአገራችን መንገድ በአካባቢችን በሚገኘው ቀይ አፈር የተሰራ ነው፡፡

ሳሲት
ሳሲቶችን ተዘዋውሬ ሰላም አልኳቸው፡፡ በሁለት ዓመቴ ስላገኘኋቸው ደስ አለኝ፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት በጻፍኩት ማስታወሻ እንዳስተናገደችን የገለጽኩት እህታችን ዘነበች አስፋው በጸና ታማ ነበር፡፡ አሁን እያገገመች ባለችበት ሁኔታ ሄጄ መጠየቄ ደስ አለኝ፡፡ ራበን ባዩ ስለበዛ ምግብ ቤት ገብተው ምግብ ተመግበው በባጃጅ ወደ አንዲት ግራር አቀናን፡፡ አንድ ባጃጅ አምስት ሰው የምትይዝ አነስተኛ ታክሲ ነች እዚያ፡፡ ምቹው መንገዳችን አገሩን ለመቃኘት ሁነኛ እድል ሰጪ ነው፡፡

አንዲት ግራር
ግራር ጋ ልንደርስ ትንሽ ሲቀረን ዓለም ገና የምትባል ‹ከተማ› ቢጤ ተቆርቁራ በማየታችን ለካ ቆይተናል የሚል ስሜት ተሰማን፡፡ ግራር ደረስን፡፡ እኒያ በሩቅ ሲታዩን የነበሩት ሰዎች አሁን ቀርበው ሲያዩዋቸው ፈገግታቸው ደስ ይላል፡፡ ማንነታቸውም ተረዳን፡፡ የወደቀችውን ግራር ወደ ጎን አድርገን ክብ ሰርተን ቆምን፡፡ የዕለቱ መርሃ-ግብር በግሩም ሁኔታ ቀጠለ፡፡ የሞጃ አርበኞች ሰብሳቢው የአቶ አያሌውና የወረዳው አፈጉባኤ የአቶ ለጤ ንግግሮች ዝግጅታችንን በጥሩ ሁኔታ ከፈቱልን፡፡ ከእንግዶች ደግሞ የአዲስ አበቦቹ ጋሻው ደበበና የተክለሐይማኖት ማሞ ተራ ተከታይ ነበር፡፡ ጋሻው ያቀረበው ግጥም አበባበቡም ሆነ ይዘቱ ግሩም ነበር፡፡ ግጥሙ ልብ ይገባል፡፡ አንዴ እጄን ከደረቴ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከኪሴ ያስደርገኝ ነበር፡፡ ተክለሐይማኖት ስለ ማህደረ ሸዋ ገለጻ አድርጎ ዓላማቸውንና የአባላቱን መልዕክት አደረሰ፡፡ በየመሃሉ የሞጃ ባህል ቡድን ውዝዋዜና ግጥም ሌሎችንም ስራዎች አቅርቧል፡፡ አባቶችም ፉካሮና ቀረርቶ አቀረቡ፡፡ አንድ ካህን ቡራኬ ሰጥተው ዳቦ ቁረስ ተባልኩ፡፡ ‹‹ኧረ አይሆንም ስንት ትልቅ ሰው እያለ›› ብልም አልሆነም፡፡ ቆረስኩ፡፡ ዳቦ ታደለ፡፡ አረቄም ተሰጠን፡፡ የዘንድሮው በዓል በመንግስት ሃላፊዎች፣ በሞንታርቦና በባህል ቡድን የታጀበ ቢሆንም ከነዋሪው ህዝብ በኩልና ከተማሪው የቁጥር መመናመን ይታይ ነበር፡፡ አንደኛው ምክንያት በአካባቢው ለቅሶ መኖሩ መሆኑን ሰማን፡፡ አሸዋ፣ ድንጋይ፣ ሲሚንቶና ብሎኬት ተዘጋጅቶለት የግንባታውን መጀመር እየተጠባበቀ የሚገኘው የአንዲት ግራር አጥር የሞጃ ሃላፊዎች ቀና ውጥን ነው፡፡ በርቱልን፡፡ ይህ ጅምር ብዙ ስራዎች እንዲሰሩ ሌሎችን ያነሳሳል፡፡

የመልስ ጉዞ
በፒክአፕ መኪናዋ እንግዶቹ ቅድሚያ ተሰጥቶን ወደ ሳሲት አቀናን፡፡ ከዚያም ሳለአምላክ ቤቴን እንዳሳየው በጠየቀኝ መሰረት ወደ እናቴ ቤት ወሰድኳቸው፡፡ ትንሽ ቀደም ብዬ እንደምንመጣ የነገርኳት ታናሽ እህቴ ጋበዘችን፡፡ ቡና ተፈላ፡፡ አያቴንም አገኘኋት፡፡ ደስ የሚል ጊዜ አሳልፈን እንግዶቼን ሰላድንጋይ ድረስ ሸኝቼ ልመለስ መኪና ውስጥ ገባን፡፡ ሰላድንጋይም በገና ሆቴል ወረዳው ሌላ ግብዣ አዘጋጅቶ ኖሮ በጥሩ ሁኔታ ተጋበዝን፡፡ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን፣ የአፈ- ጉባኤና የባህል ጽ/ቤቶች ሰዎች ለእኛ ሲሉ ተፍ ተፍ ሲሉ ስለነበር ውለታቸው አለብን፡፡ እንግዶቼን ወደ ደብረብርሃን ሸኝቼ ወደ ሳሲት ልመለስ ነው ሰል ጋዜጠኞቹም እኛም ልንመለስ ነው አሉ፡፡ ሦስታችን ተመልሰን በተክለሐይማኖት ቤት አመሸን፡፡ እስከ ሦስት ሰዓትም አቶ ደምሴ ስለአርበኞች ግሩም ትምህርት ሰጡን፡፡ አንድ የሚሳሳቱት ነገር የለም፡፡ እኔ እንዲያውም ለእርሳቸው ቃለመጠይቅ ማድረግ ከአቅማችን በላይ መሆኑን ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ወደ ቤቴ ሄጄ ከቤተሰብ ጋር ስጫወት ቆየሁና ሌሊቱን ይታይ የነበረ አንድ ጽሑፍ ስለነበረኝ ሳይ አደርኩ፡፡ በማግስቱም ዘመዶቼን ጠያይቄ ጠዋት 3፡30 ወደ ሰላድንጋይ ሄድኩ፡፡ እዚያም ዘመድ ጠያይቄ ሰመሻሽ ወደ ደብረብርሃን ተመለስኩ፡፡ ብዙ የተዘነጋ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ የነበራችሁ ሰዎች በአስተያየት አዳብሩልኝ፡፡ በመጨረሻም አርበኞቻችንን ያከበርነው ሁሉ የዚህ ዘመን አርበኞች ነን፡፡ ተቃዋሚ አለ?



































በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...