2016 ዲሴምበር 31, ቅዳሜ

አምቦ በዚህ ሰሞን


(ማሳሰቢያ፡- ማስታወሻዬን በሰዓቱ ለማድረስ ከሞባይል ላይ መገልበጥ ያለበት የአንድ ሰዓት ቃለመጠይቅ አለኝ፡፡ በዚህም ምክንያት ሙሉው ጽሑፍ እስኪደርስ በዚች አዝግሙ፡፡ አስተያየታችሁን ግን አትንፈጉኝ፡፡)

በመዘምር ግርማ
ሕዳር 25፣ 2009 ዓ.ም.
ስለ አምቦ ምን ስሰማ ነበር?
መኖሪያ ቤቴ ከሚገኝባት ከደጋማዋ ደብረብርሃን ወደ አምቦ ለመሄድ ስነሳ ስለ አምቦ መረጃ ለማሰባሰብ እንኳን ጊዜ አላገኘሁም ነበር፡፡ አንድ አካባቢውን የሚያውቁ ሰው ግን ‹‹አምቦ ቅርብ ነች፡፡ ትንሽ ሞቅ ትላለች፡፡ ነቀምት ብትዘልቅ ግን ጥሩ ነበር፡፡ ትክክለኛዋ ኢትዮጵያ ያለችው ወለጋ ነው፡፡ እዚህ ጋ ምንጭ፣ እዚያ ጋ ፏፏቴ፣ አለፍ ብሎ ጫካ … እንዴት ደስ እንደሚል!›› ብለውኛል፡፡
‹‹ከወለጋ ቀጥሎ ኦሮሞነትን ጠንከር አድርጎ የሚይዝ፣ ጀግናና ጠንካራ ሕዝብ ነው የአምቦ ሕዝብ፡፡ ጥሩ አየር አለው፤ ለጥ ያለ ሜዳ ነው፤ ፍራፍሬ አለው፡፡›› ብለውኛል አንድ ኦሮሞ ምሁር፡፡
‹‹በደርግ ጊዜ ጥይት ፋብሪካ ስለነበርና ፋብሪካውም የአምቦ ሕዝብ ጀግና በመሆኑ እንደተሰራ ስለሚነገር የአምቦ ሕዝብ ይህ መንግስት ሲገባ በጣም የተጋተረ ሕዝብ ነው፡፡ በዚያም ምክንያት አምቦ አሁን ምንም ዓይነት ልማት የለውም፡፡›› የሚለውን አስተያየት ስሰማው ቆይቻለሁ፡፡ ልማቱንም ሆነ ጥፋቱን አይቼ እንደምናገር ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡
ስለ አምቦ የነገሩኝ ሌላ ሰው እንዳሉት ‹‹ሰፋሪዎቹ ኦሮሞዎች ስለሆኑ ኦሮምኛ በብቸኝነት የሚወራበት ቋንቋ ነው፡፡ በምርጫ 97 ብዙ ሰው ሞቷል፡፡ ህዝቡ ንቅ ነው፡፡ የህዝብ ጥላቻ ግን የለበትም፡፡››
‹‹ዳዊት ስትደግም ስመህ ነው የሚከፈተው፤ እንጀራም ስትበላ ዝም ብሎ አይዘነጠልም›› እንዲል ጋሽ ሳሙኤል ይህን ጽሁፍ በዚህ መልኩ ከምንጀምረው እስኪ ለርስዎ የክፍል ስራ ይሰጥዎት፡፡ ውድ አንባቢ እውነት እውነት ስለ አምቦ ምን ያስባሉ? የተወሰኑ ነጥቦችን እስኪ ይጻፉልኝ፡፡
አጥንታችን ድረስ ፍርሐት ገባ
በመኪናችን ከሁለቱም በፊት የተለጠፉትን የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አርማዎች ላጥን፡፡ ታርጋው ግን ሊነሳ አይችልም፡፡ ወደፊት ለዩኒቨርሲቲ ስራ ስንንቀሳቀስ የግል መኪና ታርጋ (ኮድ 2 ወይም 3) ሊሰጠን ይገባል፡፡ ለደህንነታችን ሲባል የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አውቶቡስ ባለፈው ሰንዳፋ ላይ ተመትቷል፡፡ አዳማም ላይ ሰራተኞቻችን ተደብድበዋል፡፡ አርማችንን ስንልጥ ‹‹ዚስ ኢዝ ቢዮንድ ወርድስ›› አሉ አንዱ የታሪክ ሊቅ በብስጭት፡፡ ‹‹የእኛን ኦሮምኛ እንደ ኦሮምኛ አይቆጥሩትም›› የሚለውን የመሳሰሉ አስተያየቶች ይሰጡ ጀመር፡፡ ‹‹እኛስ እንዲህ አለፍን፤ ልጆቻችንስ ወደፊትስ?›› ያሉም አሉ፡፡
‹‹ሩዋንዳ ወደነበረው እየሄድን ነው›› ብለው ወደኔ ጠቆም አደረጉ፡፡
‹‹ዛፍ የለም፤ ተራሮች በዛፍ አልተሸፈኑም›› የሚል ምልከታውን እያነሳልን አብሮን የተጓዘው የቡድናችን አባል አንዲትን ለልማት ስራ የመጡ እንግሊዛዊት አስታወሰኝ፡፡ ‹‹ሁለት ሰዓት ሙሉ ተጉዘን የረባ ዛፍ ሳናይ እንቅር›› ነበር ያሉት እንግሊዟ፡፡
የሩዋንዳው ነገር ግን መልሶ ትዝ አለኝ፡፡ የዘር ማጥፋትን በወጣትነቷ ያየችው ሩዋንዳዊት ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ አንዴ ወደ ሰርግ ስትሄድ የነበረውን ስሜቷን ጽፋዋለች፡፡ እኔም ያን ዓይነት ፍርሐት ተሰማኝ፡፡ ስጋትና ጭንቀት ተደራረበብኝ፡፡ ሁቱትሲ ከገጽ 53-54 እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹ከተወሰኑ ወራት በኋላ ከዚህ የባሰ የሚረብሽ ክስተት ገጠመኝ፡፡ ዳማሲንና እኔ ከማታባ ወደ ኪጋሊ ለሠርግ እንሄዳለን፡፡ ረጅም፣ ወበቃማና አቧራማውን ጉዞ እያገባደድን ሳለን የመንገደኞች ማጓጓዣ ተሸከርካሪያችን ድንገት ቆመ፡፡
ቢያንስ 300 የሚሆኑ ኢንተርሃምዌዎች መንገዳችንን ዘግተው ቆመዋል፤ የሁሉም አለባበስ ለዓይን ይቀፋል፤ አስተያየታቸውም እጅግ ያስፈራል፡፡ ብዙዎቹ አላፊ አግዳሚው ላይ እየጮሁና እየተሳሰደቡ በቡድን ሲጨፍሩ የጠጡ ወይንም አደንዛዥ እጽ የወሰዱ ይመስላሉ፡፡ ነጂው ወደፊት ለመሄድ በጣም ስለፈራ ተሸከርካሪውን ወደኋላ ሊመልሰው እንደሆነ ነገረን፡፡ አብረነው የሁለት ሰዓቱን ለውጥ መንገድ እንድንሄድ፣ አሊያም ወጥተን በእግራችን እንድናዘግም አማራጭ ሰጠን፡፡
‹‹ተሽከርካሪው ውስጥ እንቆይ›› አለ ዳማሲን፡፡ ‹‹እነዚህ ሰዎች አብደዋል፡፡›› እኔ ግን በተለይ በነዚህ ወረበሎች ተግባር ለመፍራት ባለመፍቀዴና በሌሎችም ምክንያቶች ተሸከርካሪው ላይ መቆየቱን አልመረጥኩትም፡፡
‹‹እንውረድ እንጂ ሠርጉ ያመልጠናል እኮ›› አልኩት፡፡ ‹‹በእግራችን ብናዘግም ቤተ-ክርስቲያኑ ጋ አሁን እንደርሳለን፡፡››
ከተጓዦቹ ግማሽ ከሚሆኑት ጋር ወረድን፡፡ እንደወጣንም አልፏቸው የሚሄደውን ሰው መታወቂያ ከሚያዩት ኢንተርሃምዌዎች ብዙዎቹ ገጀራ እንደያዙ አየን፡፡ ንዴት ተሰማኝና ‹‹ማነው መብቱን የሰጣቸው?›› ስል ጠየቅሁ፡፡
ዳማሲን ተጨንቆ ‹‹ብንመለስ ጥሩ ይመስለኛል፣ ኢማኪዩሌ፡፡ ስለነዚህ ሰዎች መጥፎ ነገሮች ሰምቻለሁ፡፡ ተይ በእግራችን ወደ ቤታችን እንመለስ›› አለኝ፡፡
‹‹በእግራችን? በተሽከርካሪ አራት ሰዓት የፈጀብን በእግራችንማ በሦስት ቀንም አያልቅልን፡፡ ደግሞ እውነት እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን እንደ ጸጥታ አስከባሪ አደራጅተው እኛ ቱትሲዎች ስለሆንን ብቻ ጉልበታቸውን ሊያሳዩን አይገባም፡፡››
የዳማሲን ፊት ላይ ከሚነበበው ፍርሃት ይልቅ የኢንተርሃምዌዎቹ ነገር ቀላል ሆኖ አገኘሁት፡፡ ሁልጊዜ ሳቂታ ገጽታ የነበረውና ምናልባትም ከማውቃቸው ሰዎች ሁሉ ጠንካራው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ግን በእርግጥ እንደፈራ አየሁ፡፡ ለወትሮው ምን እንደሚሻል እጠይቀው የነበረ ቢሆንም አንዳች ነገር ወደፊት እንድሄድ ገፋፋኝ፡፡
‹‹ና አልፈናቸው እንሂድ›› አልኩት፡፡ ‹‹ምንም አንሆንም፡፡››
‹‹ያንን እንዴት አወቅሽ? እንደማይገድሉን ያሳሰበሽ ምንድነው? መንግሥት የፈለጉትን እንዲፈጽሙ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ጸጥታ አስከባሪ አይነካቸውም፡፡››
‹‹ችግር በሚገጥመን ቁጥር የምትለውን እናድርግ ዳማሲን፡፡ እንጸልይ፤ እግዚአብሔር እንደሚጠብቀንም እንተማመን፡፡››
ከቁጡ ጽንፈኞቹ ቡድን አሥር እርምጃ ርቀት ላይ በመንገዱ ዳር ቆመን ጸለይን፡፡ እግዚአብሔር ለአጭሯ መልዕክት ይቅር እንዲለኝ ጠይቄው በደኅና ወደ ቤተ-ክርስቲያኑ እንደርስ ዘንድ ግን የእርሱን ድጋፍ እንደምንፈልግ ነገርኩት፡፡ ወደኬላው ሄድኩ፤ የተወሰኑ ወጣት ወንዶች አይተውኝ በገጀራዎቻቸው ጭኖቻቸውን መታ መታ ያደርጋሉ፡፡
‹‹አይ በፍጹም፣ አይሆንም ኢማኪዩሌ… ስለዚህ ነገር እርግጠኛ ነሽ?››
‹‹አዎን፣ አዎን በቃ ምንም እንዳልተከሰተ ሁን - እንዲያውም ምናልባት መቁጠሪያህን ከኪስህ ብታወጣ ሳይሻልህ አይቀርም፡፡››
ወደ ኢተርሃምዌዎቹ ስንሄድ መቁጠሪያዬን በእጄ አጥብቄ ይዣለሁ፡፡ ደርዘን የሚሆኑት ከበቡን፣ ላይ ታች አዩኝና መታወቂያ ደብተራችንን እንድናሳይ ጠየቁን፡፡ በመጀመሪያ ዓይናቸው ላይ ትክ ብዬ አየኋቸው፡፡ ከዚያም ፈገግ አልኩ፡፡ በመጨረሻም ሰነዶቹን ሰጠኋቸው፡፡ በጣም ደፋር በመሆን እንዳስቸገርኳቸው ታየኝ - አንዲት ቱትሲ ሴት እነርሱንም ሆነ ገጀራዎቻቸውን ለምን እንደማትፈራ ሊገባቸው አልቻለም፡፡ መታወቂያዎቻችንን መልሰው ሰጥተውን አሳለፉን፣ ሆኖም ግን በዳማሲን ዓይኖች ውስጥ ያየሁትን ፍራቻ በፍጹም አልረሳውም፡፡ ሲፈራ ሳየው የመጀመሪያ ጊዜዬ ሲሆን በሩዋንዳ ላይ አንዳች ክፉ ነገር እንደመጣባት የሚያሳየውን ስሜቴን ላናውጠው አልተቻለኝም፡፡››
ፍኖተ-ሠላም
በመንገዳችን ምንም ዓይነት ችግር ሳይገጥመን አምቦ ገባን፡፡ ይሄ ሁሉ ፍርሐት ታዲያ የምን ይሉታል ስል ራሴን ታዘብኩ፡፡ አምቦን ያለ ስሟ ስም እንድናወጣላት ያደረገን ምንድነው?
አፋን ኦሮሞ - አፋን ሰበ ጉዳ
ጨልሟል፡፡ ጋቢና ያለው ጓደኛችን መስኮቱን ከፍቶ ‹‹መናኸሪያው የት ነው›› ብሎ አንዱን ወጣት ጠየቀው፡፡ መናኸሪያ አካባቢ አልጋ አይጠፋም ብሎ ነው፡፡ ‹‹ማል ጀደኒ?›› ሲለው የሚመልሰው ጠፋውና መልሶ መስኮቱን ዘጋው፡፡ ‹‹አንተ ታዲያ ኦሮምኛ እሞካክራለሁ ትል አልነበረም እንዴ?›› ብትሉኝ መልስ አለኝ፡፡ ስለ እውነት ለመናገር መናኸሪያ የሚል ቃል በኦሮምኛ ማንም አላስተማረኝም፡፡ ቢያንስ እኔም ይጠቅመኛል ብዬ አልጠየኩም፡፡ እኔ ይጠቅመኛል ብዬ ያሰብኩት መነ ጭሲቻ፣ ሲሬ፣ ኛታ፣ ወልገኢ ምናምን ነበር፡፡ የአማን ቃዲሮ፣ የታሪኩ አነጋ፣ የነብዩ ዓለማየሁ፣ የለሜሳ፣ የዝናወርቅ፣ የጥላሁን ግርፍ ነኝ፡፡ ይህን ስላላስተማሩኝ ወቀስኳቸው፡፡ አስበላችሁኝ! አልኳቸው፡፡ ከአምቦ መልስ ግን ያው መናኸሪያን እንደሚጠቀሙና እጅግ ካስፈለገ ቡፈታ ኮንኮላታ ሊባል እንደሚችል ነግረውኛል፡፡ አዳዲስ የኦሮምኛ ቃላት እና አገላለጾች እየፈሉ ነው በዘመናችን፡፡ በቋንቋው ቀናት፣ ወራት፣ ወቅቶች ሳይቀር እንደተሰየሙ ልብ ይሏል፡፡
ቀጥሎ ሌላ መንገደኛን ጠየቀ ጓደኛዬ፡፡ ‹‹ችግር የለም ላሳያችሁ›› ብሎ መኪናው ውስጥ ገብቶ ወደ ጀባትና ሜጫ ሆቴል ወሰደን፡፡ በአምቦ ማዕድን ውሃ ለ15 ዓመታት የሰራው ይህ ግለሰብ ቤተክርስቲያን ስሞ መምጣቱ ነበር እኛን ሲያገኘን፡፡ አልጋበዝም ብሎ ተሰናበተን፡፡ ‹‹አኒ ኢጆሌኮፊ ሴና መሌ ገቲ ዲሴ ሂንደርቡ›› የሚሉት አቶ ቤለማ ፉታሳ ሆቴል ነው ጅባትና ሜጫ፡፡
‹‹ኦሮምኛ የማንችል ሰዎች ግን ጉዳችን ነው፡፡ እናቴ ትችላለች፤ እኔ ግን አልችልም›› ላለችው የስብሰባችን ተሳታፊ ‹‹እንደ ሞባይል እኮ ነው ቋንቋ ማወቅ ማለት፡፡ እንማራለን፤ እንጠቀምበታለን፡፡›› በማለት የቋንቋው ተናጋሪ የሆነ መምህር ምላሽ ሰጣት፡፡
አምቦ ላይ ኦሮምኛንና አማርኛን አቀላቅሎ መናገር የተለመደ ነው፡፡ ለሁለቱም ቋንቋ ጆሮውን ከፍቶ ነው ሰው የሚጠብቀው፡፡ በአንጻሩ ምንም ኦሮምኛ የማይችሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አግኝቻለሁ፡፡ የአማራና ደቡብ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው እንደሚበዙ ሰምቻለሁ፡፡ አዳማ ላይ ካየሁት የሚለይ ከተማ ነው አምቦ በቋንቋ አጠቃቀም፡፡ አዳማ ሄዱ ማለት ባህርዳር ሄዱ ማለት ነው - በየድርጅቱ በር ላይ ከተጻፈው የኦሮምኛ ማስታወቂያ በስተቀረ፡፡
‹‹የአዳማ ሰው ከሌላው እስካሁን ከማውቀው ሰው ትንሽ መልኩ ለየት አለብኝ›› ያለኝ ጓደኛዬ እንደነበር አብረውኝ አምቦ ለሄዱት ስናገር አልተቀበሉኝም፡፡ ‹‹አሁን ከጋምቤላ በቀር እና ትንሽ ከአንዳንድ ደቡቦች በቀር እኛ ይሄን ያህል የሚወራ ልዩነት አለን?›› ነበር ያሉኝ፡፡
ሐገረ ሕይወት - አምቦ፣ አምቦ - ሐገረ ሕይወት
ዳግማዊ ምንሊክ የዳኑበት ፍልውሃ ነው፡፡ ሐገረ ሕይወት ሲሉ ሰየሟት ከተማዋን፡፡ አሁን አምቦ በሚባለው ስሟ ነው የምትታወቀው፡፡ መዋኛ ገንዳዎች አሉ፡፡ ፍልውሃ በሽ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሳይቀር አለ፡፡
የጀበና ቡና ያጥለቀለቃት ከተማ መሆኗን ለመታዘብ አፍታም አይፈጅብዎት፡፡ ሁሉም በየደጁ ቡና ይሸጣል፡፡ ሁሉም ጋ 3 ብር ነው የቡናው ዋጋ፡፡ ከፕላስቲክ ዘንቢል የሚሰሩ ሰዎችም በየዛፉ ስር ይታያሉ፡፡
ድንቂሲሳ ተመስገን እንደታዘበው ከአንድ ለእናቱ አስፋልቷ ጀርባ ብትጓዙ አምቦ ከተማ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ያለች ነች፡፡ እስኪ ይህን ኋላቀርነት ለማሻሻል የሚረዳን ሐሳብ ሰንዝሩ አንባቢያን፡፡
ደብረብርሃን ላይ በደንብ የማይሰማው ቅዳሴ አምቦ ላይ እጓዳዎ ድረስ ይመጣል፡፡ አነስተኛ የእስልምና እምነት ተከታዮች ቁጥር እንዳለና ወንጌላዊው ግን በርከት እንደሚል አጣርቻለሁ፡፡
ላሊሴ እንደነገረችኝ የስራ አጥነት ችግር ተንሰራፍቷል፡፡ የቀጣሪ ያለመኖር ችግር ነው ስራ አጥ ያደረገን ትላለች፡፡ ሰርግ እጠራሃለሁ ብላኛለቸ፡፡
በአንድ ወር ሁለት ጊዜ ከደብረ ብርሃን መውጣት ቱሪስት ያስብላል እንዴ?
ከደብረብርሃን የየዕለት ውሎ ልማዴ ወጣ ማለቴ አስደስቶኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲ መሄድ - ኮምፒውተር መጎርጎር - ፌስቡክ ላይ መጣድ -- ማታ ላይ ራስ አበበ ቤተመጻሕፍት ደረስ ማለት - ከዚያ ጌጤ ግሮሰሪ ጎራ ማለት - አምሽቼ እቤት መግባት - በጊዜ አጠቃቀም ችግሬ መናደድ!
በዚህ ወር ለአራት ቀናት መሐል ሜዳ፣ ለአራት ቀናት አምቦ ማሳለፌ ትንሽ የእለት አዋዋሌን ቀየር እንዳደርግ አድርጎኛል፡፡ ቱሪስት መባሌን ግን እንጃልኝ!
በሌላ ዜና
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ አምቦ ላይ ይደነቃሉ፡፡ በምን የሚደነቁ መሰለዎት? የአማራና ኦሮሞ እውነተኛው የዘር ምንጭ የሚለውን የፍቅር ምንጭ የሆነ መጽሐፍ መቶ ኮፒ ገዝቼ እንዳከፋፍል አንድ የአምቦ ሰው መክሮኛል፡፡ ገንዘብ ቢኖርማ!
አምቦ የገባን ዕለት ምሽት
በዚህ ምሽት አቶ በቀለ ባየታ ቶለሳን መንገድ ላይ አገኘናቸው፡፡ ‹‹እናተ አምቦ ላይ ሆናችሁ በቀኝ ትሄዳላችሁ እንዴ?›› ብለው ገሰጹን፡፡ እንግዶች መሆናችንን ታዝበዋል መሰል ‹‹ኑ በግራ›› ብለው የዘውን ሄዱ፡፡ ጠይም፣ ግዙፍ አዛውንት ናቸው፡፡ ምግብ ፈልገን እንደምንዞር ሲረዱ ወደ ባላምባራስ ገብረሥላሴ ቤት ይዘውን ሄዱ፡፡ ምግብ መኖር አለመኖሩን እራሳቸው ገብተው ጠይቀው እንድንገባ ጋበዙን፡፡ እኛን ከፊት ለፊታቸው አስቀምጠው እንደ ስብሰባ መሪ ተመቻችተው ተቀመጡ፡፡ ከማያልቀው የወግ ማዕዳቸው ለሦስት ሰዓት እንዳቋደሱን ስነግራችሁ በአግራሞት ነው፡፡
ወቅታዊውን የፖለቲካ ሁኔታ መረዳቸውን ለማሳየት ይመስላል እንዲህ ተቀኙ፡- ‹‹ከውጭ አገር ሱቅ በሪሞት ኮንትሮል ሲያዘጉ ኢህአዴግ በጉልበት ሊያስከፍት ይሞክራል፡፡ በፖለቲካ እንደተበለጠ ጥርጥር የለውም፡፡ የሚሻለው የውጭዎቹን በፖለቲካ ለመወዳዳር መሞከር ነው፡፡›› አሉ፡፡
ከመንግስትም ላለመጣላት ይመስላል ‹‹እኔ ከመንግስታት ሁሉ የምወደው ኢህአዴግን ነው›› ሲሉ ጨመሩ፡፡ ‹‹ምክንያቱም እንዲህ ዝነኛ የሆንኩት በሱ ጊዜ ነዋ!››
ባይ ዘ ዌይና ኮማንድ ፖስት የሚሉትን ሐረጋት በየደቂቃው ይጠቀማሉ፡፡ ሌላም እንግሊዝኛ አለቻቸው - ኮንትሪቢውሽን ትባላለች፡፡ የራት ሂሳቡ አንድ ሰው ላይ እንዳይጫን ሁላችሁም ብር አውጡ ሲሉ መከሩን፡፡ ይህ ጥበብ ኮንትሪቢውሽን ይባላል በእርሳቸው እንግሊዝኛ፡፡ እንግሊዝኛቸው ለክፉ አይሰጥም፡፡ ትግሪኛም በጥሩ ሁኔታ አብሮን ከተጓዘው የኤርትራ ተወላጅ ጋር አውርተዋል፡፡ ሽን የሚለውን ቅጽል ተጠቅመው ሌላ ቃልም ለዓለም አስተዋውቀዋል ጋሽ በቄ - ቶኩሜሽን ትባላለች፡፡ አንድነት ኃይል ነው ለማለት ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነቴን ነው እንጂ ዘር ቆጠራ አላውቅም፡፡ እኔ ሥልጣን ብይዝ ለኦሮሞ ካዳላሁ ምም ሰው አትበሉኝ፡፡ እናቴ አማራ ነች፡፡›› የሚለውን ለማጠናከር ነው ቶኩሜሽንን የተጠቀሙት፡፡
‹‹አብሮ ተኝቶ ገላ መደባበቅ ምንድነው?›› ላሉን ለአቶ በቀለ የመጣንበትን ጉዳይ ለመናገር ብዙም አላቅማማንም፡፡ የመጣንበትን ጉዳይ ሲረዱ አሁንም ሌላ ቅኔ ተቀኙ፡-
‹‹በጭፍን ጨለማ እንዳይቀር ገሚሱ
የነቃ እንዲነቃ ያዘዋል ሳይንሱ››
ደብረብርሃንና አምቦ እህትማማች ከተሞች እንዲሆኑ እንዲረዱን ጥያቄ ስጠይቃቸው እንዲህ ሲሉ መለሱልኝ፡- ‹‹እህትማማችማ ናቸው እኮ! እናንተ አልገባችሁም እንጂ፡፡ ይቺ ሐገረ-ሕይወት ነች! ያች ደብረ ብርሃን፡፡ ኢየሱስ እኔ መንገድም፣ ብርሃንም ሕይወትም ነኝ ብሏል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ አንድ አድርጓቸዋል፡፡›› በማለት መለሱልኝ፡፡ በየሄድኩበት የማይለቀኝን አይሁድ ተጠቅመው ምሳሌ ቢሰጡም ምላሻቸው ደስ ብሎኛል፡፡
አምቦ ላይ ከእርሳቸው በፊት የሚመርቅ እንደሌለና የኢሬቻው የዘንድሮ መራቂም እንደሆኑ ለመረዳት እያለሁ፡፡
በአበበች ሆቴል
አበበች መታፈሪያ ከአምቦ ባለሐብቶች አንዷና የአካባቢው የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ናቸው፡፡ በየረብሻና ግርግሩ (እንደፈለጋችሁ ልትጠሩት ትችላላችሁ - ካጠፋሁ ይቅርታ የፖለቲካ ዓላማ ግን የለኝ በቃላት አጠቃቀሜ) ሆቴላቸው ዱላ ይቀምሳል፡፡ ሥልጠናችን የነበረው በምቹው ሆቴል ነበር፡፡
‹‹የአካባቢው ማህበረሰብ በእንግዳ ተቀባይነቱና አክባሪነቱ የታወቀ ነው፡፡ ሰላማዊና የማይረሳ ጊዜ እንደምታሳልፉ ተስፋ አደርጋለሁ፡:›› በማለት አቀባበል ያደረጉልን አንድ ባለስልጣን ስንለይም ‹‹ደብረ ብርሃኖችማ አንድ ነን እኮ፡፡ ዱሮ እኮ አንድ ነበርን- ሸዋ! አሁንም ግን አንድ ነን፡፡›› ብለውናል፡፡ እኛም አጨብጭበንላቸዋል፡፡
አስተናጋጃችን አምቦ ዩኒቨርሲቲ አራት ካምፓሶች ሲኖሩት ግቢውን ስጎበኝ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ቤተመጻሕፍትንም አይቼ አድንቄያለሁ፡፡
ቡድናችን ጉደርን ለመጎብኘት የነበረው እቅድ ተሰረዘ፡፡ ዶክተር መረራ በመታሰራቸው የተነሳ ነው ይህ መሆኑ፡፡
ሃሳብ እንጂ ብር የለኝም የሚለው ዩኔስኮ ባዘጋጀው በሞባይል ስልክ፣ በታብሌትና በላፕቶፕ የተደገፈ ተግባር-ተኮር የጎልማሶች ስልጠና ላይ ለመገኘት ነበር ዘጠኝ ሰዎ ያለው ቡድናችን ወደ አምቦ ያቀናው፡፡ ‹‹በታብሌት እንዲማሩ የሚለው የሚያጋጭ ይመስለኛል - ንብረት ስለሆነ፡፡›› ያሉ ሰው ነበሩ፡፡ ፊደል ቆጥሮ የጨረሰ ሰው ታብሌት አያሻውም ያለው ማነው? አዲስ አበባ የሚገኘው ሊሴ ገብረማርያም ለአንድ ተማሪ በዓመት 110 000 ብር፣ አሜሪካን ስኩል 8 000 ዶላር በተርም በሚያስከፍሉበት አገር ለአንድ ጎልማሳ የ220 ዶላር ታብሌት ማይክሮሶፍት ልስጥ ሲል የአስተማሪ ምቀኛ ገባው፡፡ ይህ ምቀኝነት ግን አይሰራም ብዬ አስባለሁ፡፡
እጅግ የሳበኝ የሞባይል ትምህርት ተግባራዊ ሆኖ ለማየት እሻለሁ፡፡ እኛ የሚነበበውን ነገር ለማዘጋጀት ነበር እዚያ ሦስት ቀን የቆየነው፡፡
ከስብሰባው ላይ ከሳቡኝ ነገሮች አንዳንዶቹ፡-
‹‹አምፖል ብትቀባባው ከተቃጠለ እኮ አይሰራም፡፡ እንደሚባለው ችግሮቻንን ከምንጫቸው ማየት ይኖርብናል፡፡›› ልቀጥል -
ሁሌ ማነቃነቅ ምንድነው? ንቅናቄ? ወይ መትከል ነው ወይ መንቀል ነው፡፡
ምንሊክን ግማሹ በግራ ግማሹ በቀኝ ያስቀምጣቸዋል፤ እኔ ግን መሐል ላይ ነው የማደርጋቸው፡፡ የትምህርት አዋጃቸውን እዩልኝ- ልጁን ያላስተማረ ርስቱን ይቀማል፡፡

ከሃያ ሳምንታት በኋላ (After Twenty Weeks)




የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቀድሞ (2008 ዓ.ም. ተመራቂ) ተማሪዎች ስራ ከያዙ ገና በጣት የሚቆጠሩ ወራት ብቻ ነው ያስቆጠሩት፡፡ ቢበዛ አራት ወር ቢሆናቸው ነው፡፡ የንግድ ባንክን ፈተና እየተፈተኑ ባለበት ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ስለ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ይወያያሉ፡፡ ‹‹ለዩኒቨርሲቲያችን ምን እናድርግ?›› በማለት ያሰቡትን ለማሳካት በየሳምንቱ በመስቀል አደባባይ ይገናኙ ነበር፡፡ ብዛት ያለው ህዝብ በዚያ ስፍራ ባንዴ መገኘቱ ደግሞ ስብሰባዎቻቸው ፍቃድ ስላልነበሯቸው አንድ ፈተና ነበር፡፡ ለማንኛውም በሃሳቡ ያመኑትና እስከመጨረሻው የዘለቁት ምሩቃን ገንዘብ አዋጥተው በዩኒቨርሲቲው ሲማሩ ይቸግሯቸው የነበሩትን የአካውንቲንግ፣ የማኔጅመንት እና የኢኮኖሚክስ መጻሕፍት ገዙ፡፡
በትናንትናው ዕለት በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት አዳራሽ የተጋበዝን እንግዶች አድናቆታችን ልክ አልነበረውም፡፡ ቅልብጭ ያለቸው መርሃ ግብራቸው የምሩቃኑ ተወካዮች ከአዲስ አበባ ድረስ ረፍታቸውን ተጠቅመው በመምጣት የተሳተፉባት፣ ብሎም መምህራን፣ ኃላፊዎችና ተማሪዎች የተጋበዙባት ነበረች፡፡ የምሩቃኑ ሰብሳቢ አቶ መሰረት መምህራን ፈተና የሚያወጡት ከነዚህ ከተገዙት መጻሕፍት እንደሆነ ጠቅሶ ተማሪዎች አንብበው ውጤታቸውን እንዲያሻሽሉና ግንዛቤያቸውን እንዲያዳብሩ መክሯል፡፡መሰረትም ሆነ ጓደኛው ኦሜጋ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲን አመስግነዋል፡፡ ቤታቸው እንደሆነና አብረውት እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል፡፡ ኦ ሄንሪ የጻፈው ‹‹አፍተር ትዌንቲ ይርስ›› የሚለውን አጭር ልቦለድ መሰረት አድርገው ከሃያ ዓመታት በኋላ የተገናኙ የባህርዳር ተማሪዎች ነበሩ፡፡ መሰረት የእነዚህን ተማሪዎች አርዓያነት በመጥቀስ ወደፊት ዩኒቨርሲቲያቸውን እንዲያስታውሱ ተማሪዎችን አሳስቧል፡፡ የነመሰረት ተግባር ሃያ ዓመትም ያልቆየና ምናልባትም ሃያ ሳምንታት የቆየ ድንቅ ተግባር መሆኑን መገንዘብና አርዓያነታቸውን መከተል ያስፈልጋል እላለሁ፡፡  
የመጨረሻው መጀመሪያ፡-
በስፍራው በመገኘት የመከሩንን ዶክተር ሰይድን አመሰግናለሁ፡፡ የኮሌጁ ዲን አቶ ደረጀና የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ለቀና ትብብራቸውና የምሩቃኑን ምኞት ለማሳካት ላደረጉት እገዛ ምስጋና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ባለፉት ወራት በትምህርት ብዛትና በተከታታይ ምዘና ጋጋታ ሰልችቼ ለነበርኩት ለመምህራቸው እነ መሰረት ‹‹መጻሕፍትን እንዴት እናንብብ›› በሚል ርዕስ የ15 ደቂቃ ገለጻ እንዳደርግ ስለጋበዙኝና አስደሳች ቆይታ እንዳደርግ ምክንያት ስለሆኑኝ አመሰግናለሁ፡፡  
ለማሳረግ ያህል፡-
አንድ መርሃ ግብር የተሳካለት ከሆነና ስሜትን ቆንጥጦ የሚይዝ ከሆነ እንባ እንባ ይለኛል፡፡ ትናንትም የተሳካ ዝግጅት ያደረጉት ምሩቃኑ እንባ እንባ እንዳስባሉኝ መደበቅ አይኖርብኝም፡፡


2016 ዲሴምበር 3, ቅዳሜ

መንዝ - የፍቅር ወንዝ! የጉዞ ማስታወሻዎችና አዳዲስ ምልከታዎች - በመዘምር ግርማ


የቅርብ ሩቅ
አርብ፣ ህዳር 2 ቀን 2009 ዓ. ም ወደ መሐል ሜዳ ስጓዝ አራተኛው የመንዝ ጉዞዬ መሆኑ ነው፡፡
የአስፋልት መንገዳችንን ጣርማበር ላይ ስናሳርግና መናፈሻ ሆቴል ገብተን ምሳ ስንበላ የመቀኘት ሃሳብ መጣልኝና ተቀኘሁ፤ እንደሚከተለው፡-
‹‹ገደል አስበስተሽ ያን ፍልፈል ሰላቶ፣
መጣብሽ ጣርማበር ቻይናው አፉን ከፍቶ
ወይ ግፍ!››
መሰለም እንደሚከተለው ገጠመ፡-
‹‹ከደብረብርሃን ወደ መሐል ሜዳ
ሾልኬ ሄድኩኝ በገደል ቀዳዳ፡፡››
በሁለተኛው ግጥም እንደተመለከተው በገደል ቀዳዳ ሾልከን አይደለም መሐል ሜዳ የምንሄደው፤ ዋሻውን ትተን በላዩ እንጂ፡፡ ግጥሙ ቤት ይመታ ዘንድ ነው ትንሽ እውነታው የተፋለሰው፡፡ ወደፊት ከአጣዬ መሐል ሜዳ እየተሰራ ያለው መንገድ ሲጠናቀቅ ግን በዋሻው የመሹለክ ሕልማችን እውን ይሆናል፡፡ በዋሻው ሾልከን፣ በአጣዬ ዞረን፣ ታየኝ እኮ ስንሽከረከር፡፡ የአጣዬ - መሐል ሜዳ መንገድ ነው የጣርማበር - መሐል ሜዳ መቅደም የነበረበት ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡
ከጣርማበር በኋላ ያለው 152 ኪሎሜትር ኮረኮንች መንገድ የሚያንገጫግጭ፣ አቧራ የረበበበት፣ አሰልቺና መፈጠርን የሚያስጠላ ነው - ባላጋንን! በዚሁ መንገድ ላይ እያዘገምን ሳለ የሚከተለውን ማስታወሻ በፌስቡክ ለወዳጆቼ አጋራሁ፡- ‹‹በመኪና ጉዞ ለደብረብርሃን ከመሐል ሜዳ ይልቅ አዋሳ ትቀርባለች። የመሐል ሜዳው አየር ማረፊያ አይሰራም እንዴ? ወይስ አዋሳ ሄደን ዘመድ እንጠይቅ?›› ይህን ማለቴ መንገድ መስራቱ ከከበደ አየር ማረፊያውን መስራት እንደ አማራጭ ይወሰድ ከሚል ነው፡፡
መሐል ሜዳ አቅራቢያ ከሚገኘው ጓሳ የማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራ ስንደርስ ለጉብኝት ወረድን፡፡ አሥር ደቂቃ ባልሞላ ቆይታችን ብርዱ እንዴት እንዳደረገን መናገር ይከብደኛል፡፡ አንጀት የሚገባ ብርድ! ሎጁን አይተንና ገለጻ ተደርጎልን ስንወጣ ሁለት ወንድና ሴት ፈረንጅ ጎብኝዎች በፊልድ መኪና ወደ ማደሪያቸው ሲመጡ አየናቸው፡፡ ውርጭ ላይ ሊያድሩ! ለነገሩ ምድጃና ዝተት ስላለ ይሞቃቸው ይሆናል፡፡ ባይሞቃቸውም ችግር የለውም - ፈረንጅ አይደሉ? ብርድ ስለሚወዱ ኤምባሲዎቻቸው ሁሉ ወደ እንጦጦ የተጠጉ ናቸው ብሎኛል አንድ አስተዋይ ሰው፡፡ መኪናቸው ውስጥ ደግሞ ትልቅ ውሻ ጭነዋል - በዚህ ትዕይንትም ደንገጥ ማለታችን አልቀረም፡፡ ጥቂት ቀደም ብሎ ሦስት ልጆች ከትምህርት ቤት ወደ ቤታቸው ያለውን ረጅም መንገድ እንድንሸኛቸው እሸት ተሸክመው መንገድ ላይ ጠብቀውን ነበር፡፡ ቤታቸው ትምህርት ቤቱ ጋ ስላልሆነ የሰውን አተር እሸት በእጀ-መናኛቸው ወስደው ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም እነዚህ ልጆች ያንን ሁሉ መንገድ በእግራቸው እንዲሄዱ ተፈርዶባቸው ይህ ወደል ውሻ በመኪና ሲንሸራሸር ማየት አያናድድም? ወደ መሐል ሜዳ በምናደርገው ጉዞ ላይ ቀይ ቀበሮ በመኪናው መስኮት እያየንና የጓሳን ውበት እያደነቅን ሄድን፡፡ በመሐል አንዱ መምህር ‹‹የሜዳ አህያ!›› እያለ በመስኮቱ ለጓደኞቹ ያሳያል፡፡ ብቅ ብለን ብናይ ለማዳው አህያ ነው በጓሳ ክልል ውስጥ የሚሮጠው፡፡ የኛ ሞኝነት ነው እንጅ በ3400 ሜትር ከፍታ ላይ የሜዳ አህያ ምን ይሰራል?

መሐል ሜዳ - ሜዳ መሐል
ሲቪል መሐንዲስና የሥራ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህ የስራና የሕይወት ታሪካቸውን በሚያትተው መጽሐፋቸው ላይ ‹የመሐል ሜዳ ከተማ መቆርቆር› በሚል ርዕስ ስር የሚከተለውን አካተዋል፡፡ ‹‹በ1959 ዓ. ም.፣ በመንዝ ጌራ ምድር፣ በመሐል ሜዳ፣ እንደ ጎዴ ዓይነት ከተማ ተቆረቆረ፡፡ ይህ ቦታ ከአዲስ አበባ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የሕዝቡ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ዐይነተኛ ሥራ፣ እርሻና በግ ርቢ ነው፡፡ የመሐል ሜዳ ከተማ፣ በአባይ ሸለቆ ጥናት ኤክስፐርቶች እና በልዩ ልዩ ሚኒስቴሮች ኤክስፐርቶች ተጠንተው በቀረቡት ሐሳቦች መሠረት የተቆረቆረ ከተማ ነው፡፡ ለመንዝ ሕዝብ አስተዳደር ማዕከላዊ ቦታ ሆኖ በመገኘቱም ነው፡፡ ይህንን ቀበሌ ካለበት ሁኔታ በማንሳት፣ የእርሻና የበግ ርቢ ውጤት የልማት አስተዋጽኦ እየተሻሻለና እያደገ እንዲሔድ ለማድረግ፣ የአውራጃ አስተዳደር ከተማ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ የአገር አስተዳደር ሚኒስቴር የከተማውን ፕላን፣ የሥራ ሚኒስቴር ደግሞ፣ የመንግስት ሕንፃዎች እንዲሰሩ ተደረገ›› (60)
የሚገርም ንድፍ ያላት ከተማ መሆኗን ማንም አይክድም - መሐል ሜዳ! ግራና ቀኝ የሚያስኬዱ ሰፋፊ መንገዶችና በመሃላቸው ሰፊ አትክልት የተተከለበት መናፈሻ አለ፡፡ ከተማዋ በተመሰረተችበት በ1959 ዓ.ም ግንቦት 29 ቀን ጃንሆይ መሐል ሜዳ ሄደው የቆሙበት ሥፍራ ላይ ለመንዝና ግሼ አርበኞች አነስተኛ መታሰቢያ ሐውልት ተሰርቷል፡፡ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ሆነው ንጉሠ ነገሥቱን በሰልፍ የተቀበሉ አንድ ሰው በስፍራው አግኝቼ ለማዋራት በቃሁ፡፡ መሐል ሜዳ ላይ በንጉሡ ጊዜ አንድ አሜሪካዊ እንደነበረና በሱም ምክንያት ፕሮቴስታንት የሆኑ ሰዎች እንደነበሩ ነገሩኝ፡፡ አሁን በመሐል ሜዳም ሆነ በቀያ የፕሮቴስታንቶቹ ብዛት በመቶዎች እንደሆነ እኝህ አባት ገምተዋል፡፡ የዚህ ማስታወሻ ጸሐፊ አንዱ ኃይማኖት ከሌላው ይበልጣል ወይንም ያንሳል የሚል አመለካከት ባይኖረውም የመንዞች ማንነት በዚህ ሁኔታ እየተሸረሸረ መሄዱ በጽኑ ያሳስበዋል፡፡ ሕዝቡ ኃይማኖቱ ተቀይሮና አስተሳሰቡ ተሸርሽሮ እስኪያልቅ ድረስም የውጪው ዓለም እንደማይተኛ ይታየዋል፡፡ በመሐል ሜዳ አቅራቢያ በምትገኘው በፀሐይ ሲና ሁለት ወጣት ወንዶች አሜሪካውያን፣ በሞላሌ ደግሞ አንድ እንደነበሩ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ሁሉንም ደርግ ከሀገር አስወጥቷቸዋል አሉ፡፡ ስለንጉሡ የመንዝ ጉብኝት ብዙ የተባለና የተቀለደ ነገር ስላለ መንዞችን እንድትጠይቋቸው የቤት ሥራ ልስጣችሁ፡፡ ጃማይካዎች ጃንሆይ የረገጡትን መሬት ሁሉ መጎብኘት ስለሚፈልጉ እንደዚህ ዓይነት ቦታ አፈላልግ ያልከኝ ወዳጄ ሆይ፣ ይሄው አንድ ነጥብ አስቆጥሬያለሁ፡፡
መሐል ሜዳ ደርሰን በዝነኛው ነጻነት ሆቴል አረፍን፡፡ ግማሾቻችን አልጋ ስላላገኘን ወደ ነጻነት ሆቴል ቁጥር ሁለት ተዛወርን፡፡ የብርዱን ነገር ዝም ነው፡፡ እግሬን ስታጠብ ያየኝ አንድ መምህር ‹‹ምኑ ቂል ነው እናንተ! አሁን ትታጠባለህ እንዴ!›› ብሎኛል፡፡ አስተያየት ሰጪው እውነቱን ነው የተናገረው፡፡ እንዲሁ ማታ ላይ እግር የመታጠብ ልማድ ነው እንዲህ ያስደረገኝ፡፡ ‹‹እምዬ ደብረብርሃን ማሪኝ!›› ነው ያልነው የብርዱን ጽናትና ተወዳዳሪ አልባነት ባየን ጊዜ፡፡ ‹‹በመኝታ ክፍላችን በር ስር ያልፍ የነበረ ሰራተኛ ለሌሎቹ ሰራተኞች ጮክ ብሎ ‹‹አንድ ጭማሪ ብርድልብስ›› ሲል ሰምተን የተለመደ ትዕዛዝ መሆኑ ነው? ብለን ደንቆናል፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ መንዞች ደብረብርሃን ሲመጡ በረደን ማለታቸው ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ከሆነ ግን የብርዱና የንፋሱ ዓይነት መለያየቱ ነው አንዳችን ሌላው ጋ ስንሄድ እንዲበርደን ያደረገው፡፡ እኔ ሳሲት ወይም ሰላድንጋይ ስሄድ አሁን አሁን ይበርደኝ ይዟል!
የደግነት ጥጉ!
ወደመጣንበት እስከምንመለስ ድረስ የቤርጎ ክፍያ አልተጠየቅንም፡፡ ይህም መምህራኑን አስገርሟል፡፡ ሰው የማመን ጥግ! ሹሮ በድስት አርብ ማታ በላን እንጂ ከዚያ ውጪ ያለው ምግብ በሙሉ ስጋ ነክ ብቻ ነው፡፡ ቅቤው ከአምስት ዓመት በኋላ አይኖርም የሚል መላምት አብረውኝ በነበሩት ምሁራን ተሰጥቷል፡፡ ምግብ ቤቶች ውስጥ አትክልት ያለበት ምግብ የጠፋበት ምክንያት የከተማዋ ከአትክልት ማምረቻዎች መራቅ ወይንም የኅብረተሰቡ የአመጋገብ ልማድ ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ደብረብርሃን ላይ በጾም ቀን ምግብ ቤት ሄዶ እንደማይመገብ ነግሮኝ ነበር፡፡ ያቀረበውም ምክንያት የሹሮ የሹሮ እቤቱ መብላት እንደሚችል ነበር፡፡ ይቺ አስተሳሰብ መንዝም ትኖር ይሆን? መጠጥ ደግሞ ብርዱን ለመቋቋም ጥሩ መፍትሔ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ጋቢም ዘመድ ሰጥቶኝ ለብሼ ብርዱን ቀንሶልኛል፡፡ ምንም ተባለ ምን ይህን መስተንግዶ ያየን መምህራን ስለ መንዝ ክፉ ለማውራት አንችልም - የበላነው እንጀራ ያንቀናል! መንዝ አለመታደል ሆኖ ያላዩት ሰዎች ብዙ ክፉ ሲያወሩበት ይሰማል፡፡ ክፉው ከምኑ ላይ ነው ብለን እንጠይቃለን! የተሳሳተ አመለካከት እንዴት እንደሚቀረጽ የስነልቦና ምሁራን የሚናገሩትን ካለ እዚህ ጋ እንጋብዛለን፡፡ መንዞች፣ ሌሎች ስለነሱ ያላቸውን አመለካከት ለማሻሻል መስራት ይኖርባቸዋል!
ዘመድ በሚል የወል ቃል ከምጠራቸው ግን ላመሰግን ግድ ይለኛል፡፡ ሸዋዬ ተስንቱ እኔን፣ ዳዊትንና መሰለን በደንብ አስተናግዶናል፡፡ ኧረ እንዲያው የአማርኛ ማጠር ምንድነው! አንቀባሮናል ነው የሚባለው! ማሰሮ በሚያካክል ጠርሙስ የቀረበልን ዋልያ ቢራ መቼም አይረሳንም! ደግሞ ባናት ባናቱ! የቆረጥነውን ጮማ የሚገልጽ አማርኛ በቋንቋው ዲግሪ የሰጠኝ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አላስተማረኝም! (አማርኛን በንዑስ መማሬን ልብ ይሏል) መንገሻ ገበያውን ጥሎ ለኛ ሲል ሲንከራተት የዋለና ያመሸ ትሁት ሰው ነው፡፡ አሁን መንገሻ 12ኛ ክፍል የደረሰች ልጅ አለችኝ ቢል ማን ያምነዋል! መንዝ ወጣት ያደርጋል ልበል! አቶ ከበደ ደብረብርሃን ላይ ጭማቂ ቤት ከፍተው እንደነበርና ታክሲ ነጂም እንደነበሩ አውግተውናል፡፡ ኤርትራን ጭምር ያውቃሉ፡፡ አባታዊ አቀባበላቸውና የሐገር ቅፍራቸው ይምጣብኝ! ከእርሳቸው ጋር ስለ ኢትዮጵያ ማውራት የሰሞኑን የኢንተርኔት ክርክርና ግርግር ሲሰማ ለከረመ ሰው መድኅን ነው፡፡ ደስታ ደግሞ ወጣት ልጅ ሲሆን ባለትዳር መሆኑን መስማቴ አስደንግጦኛል፡፡ ቢያንስ ከሸዋዬ የሚያንስ ይመስለኛላ በዕድሜ! ሸዋዬ ትዳር ሲመሰርት ሰርግ እንደሚጠራኝ አልጠራጠርም፡፡ የጋሽ ጌታቸው ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድና ጎረቤት ግሩም ዘመዶቻችን ናችሁ - በግብዣችሁ አስመስክራኋልና! ባልና ሚስት አሳድረውት በምግብ የበደሉትን የቆሎ ተማሪ ታሪክና አዲስ አበባ ወንድማቸው ዘንድ ሄደው የመጡበትን አስቂኝ ወግ ያወጉልን ጋሽ ተዋበ ጨዋታ አዋቂ ናቸው፡፡ ጋሽ ተስንቱ ነፍሳቸውን ይማረውና ጋሽ ተዋበን አንድ ቅዳሜ ጠዋት የስጋ ቤቱን ሂሳብ እንዲቀበሉ ይጠይቋቸዋል አሉ፡፡ ‹‹ተው እንዲያው እንዳልቸገር በኋላ ሲብዛዛ›› አሉ አሉ እየተባለ ይተረታል፡፡ የያገሩ ደማም!
ገበያው
አዙሪት የያዛት በግ ታሪክ እመጓ ላይ ላነበባችሁ ሰዎች አንድ የዓይን ምስክርነት አለን፡፡ ከ350 ብር በታች ወይ ፍንክች! የተባለላትን በግ ገዥው 300 ብር ሊገዟት ቢቋምጡም አልሆነም፡፡ ‹‹አዙሪት አደለም፤ ባሪያ ውግ ነው፤ አሁን ትነሳለች›› ይላል ባለቤቷ፡፡ አንዱ ገዥ ታዲያ አልስማማ ሲሉ ‹‹አይ መንዜ›› ብሎ ሄደ፡፡ ከተሜው ራሱን እንደ መንዜ አልቆጠረም ማለት ይሆን? ያው አንተ አንቺ መባባል ደግሞ ብርቅ ነው፡፡ ይህንንም እያየን አውግተንበታል፡፡
የበግ ጸጉር ምርት
አንድ ተራ ተሰጥቶት የሚገበያዩት አንድ ነገር መንዝ ውስጥ አለ፡፡ ይህም የበግ ጸጉር ምርት ነው፡፡ የበግ ጸጉር በኪሎ 15 ብር ይሸጣል፡፡ የገዙትን የበግ ጸጉር ይፈትሉትና ኩባውን መልሰው ይሸጡታል ወይም ዝተት አለያም ምንጣፍ ይሰሩበታል፡፡ አንድ ውስጡ በበግ ጸጉር የተሞላ ፍራሽ 280 ብር ሲሸጥ አይተናል፡፡ ገበሬዎች WELCOME የሚል ጽሑፍ ያለበት ምንጣፍ ሰርተው ወደ ገበያ ይዘው ሲመጡ አይተን ፈገግ ማለታችን አልቀረም፡፡ በራሳችን ቋንቋም እየጻፍን እንድንሸጥ አስቤያለሁ፡፡ ማናቸውንም ነገር መጻፍም ሆነ መሳል እንደሚቻል ባሙያዎቹ ነግረውኛል፡፡ ጀርመኖች የስጋጃውን አሰራር ለማሻሻል እየሰሩ መሆኑን የባህል ጽ/ቤቱ አቶ ኤርሚያስ ሹክ ብሎኛል፡፡ አሜሪካውያን በፊት ይህን ነበር የሚሰሩት፡፡
መንዞች ግን እዚህ ጋ አንድ ወቀሳ ተቀበሉኝ፡፡ እባካችሁ በየበራችሁ ላይ የቻይና ምንጣፍ አታድርጉ! የራሳችሁን ስጋጃ ራሳችሁ ካልተጠቀማችሁበት ሌላው እንዴት ይወደዋል? ባለቤቱ ያቀለለውን…
የመሐል ሜዳውን አሮጌ አየር ማረፊያ አየነው! እንደ ግብር ከፋይነታችን ስራ እንዲጀምር ግፊት ለማድረግ አስበናል!
መንዝ ላይ አውሮፕላን ማረፊያ ነበር አልነበረም በሚል ክርክር ተጠምደን ለነበርነው ማስረጃ አለ! ከማስረጃው በፊት ግን በወዳጃችን በጋሽ ጌታቸው ቤት መንዝ ላይ አውሮፕላን አርፎ ያውቃል አያውቅም የሚል ክርክር ተነስቶ እንደነበር ልጠቁም፡፡ ከአንድ ሰው በስተቀር ስለመንዝ የአውሮፕላን ወሬ የሚያውቅ አልነበረም፡፡ በማግስቱ ስንጎበኝ ያገኘነው ማስረጃ የአውሮፕላኑ ማኮብኮቢያ ነው፡፡ አሁን ወደ አሞራ ማረፊያነት የተቀየረው ይህ ሜዳ መልሶ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሆን አንዲት ልጅ በፌስቡክ አስተያየቷ መገንጠልን መክራለች፡፡ ‹ኢትዮጵያ ግን ሳንገነጠልም ታሰራልናለች› ብዬ ልናገር ግድ አለኝ፡፡ ከአስጎብኝዎቻችን መቻኮል የተነሣ አውሮፕላን ማረፊያውን ሳናይ ማኮብኮቢያውን ብቻ ያየነው ማኮብኮቢያው ራሱ በጣም ረጅም ስለሆነ ነው፡፡ ዝም ብላ airstrip ነገር አይደለችም ያየናት ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
ደብረብርሃን ተመልሼ አንዳንድ ሰዎችን ስለመንዝና የአውሮፕላን ወግ ለመጠየቅ ሞክሬያለሁ፡፡ አንድ በመንዝ ህዝብ ዘንድ በአደራጅነታቸው የታወቁ ምሁር እንዳሉት ከሆነ ሰዉ ሁሉ ስንቅ እየያዘ ለሳምንት ያህል አውሮፕላን ማረፊያውን ለመስራት ይሄድ ነበር፡፡ ከእርሳቸውም ቤት አውሮፕላን ማረፊያውን ለመስራት የሄዱ ነበሩ፡፡ ከምቦልቻ ላይ አውሮፕላን ማረፊያ ስላለ ይሄኛው አያስፈልገንም ሲሉ አውግተውኛል፡፡ እኔ ግን አልስማማም - ከምቦልቻ ወሎ፣ መንዝ ሸዋ! ከአዲስ አበባ በ332 ኪሎሜትር ርቀት (ቅርበት አላልኩም) ላይ ሆነን በአየር መጓዝ ይብዛብን እንዴ!
መንዝ ላይ የበሰለ ምግብ መሸጥ ውርደት እንደነበርና ፀሐይ ሲና ላይ ቤተክርስቲያን ያሰሩ አንድ ታዋቂ መንዜ 25 ጉራጌዎችን ወስደው ህዝቡን ምግብ መሸጥና ንግድ አንዳስለመዱም ነግረውኛል እኝህ መምህር፡፡
ለአምስት ዓመት ደርግን ብቻውን የተዋጋ ህዝብ ተብሎ የሚሞካሸው የመንዝ ህዝብ ለአንቶኖቭና ለሌሎችም አውሮፕላኖች አዲስ አልነበረም ቢሏችሁ እንዳይገርማችሁ፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው በዚህ መቅረቱ ልብ ሰነባሪ ነው የሚሉት ደብረ ብርሃን ላይ ያናገርኳቸው አንድ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ‹‹መንዝ ካለው የመንገድ አለመመቸት የተነሣ የአየር ጉዞ አማራጭና ቀልጣፋ የመጓጓዣ አማራጭ ሊሆን ይችላል›› ብለው ያስባሉ፡፡
በሌላ አስገራሚ ወሬ፡-
ሬም፣ የአምሳ በር፣ ንገት ስለሚባሉ ስፍራዎች ሰምታችሁ ታቃላችሁ? ግሼ ውስጥ ያሉ መንደሮች ናቸው፡፡ የአውሮፕላን አደጋ ወሬ የነገሩኝ መምህር ትዝታቸው አሁንም ትኩስ ነው፡፡ የመንዝ ሳይሆን የለንደን ወሬ ይመስላችኋል፡፡ መንገድ ላይ አግኝቻቸው ወደ 20 ደቂቃ ለሚጠጋ ጊዜ በፀሐይ ላይ ቆመው አናገሩኝ፡፡ እርሳቸው ልጅ ሆነው እንደዚህ ያሉ ትልልቅ ሂደቶችን ማስታወስ በማይችሉበት ወቅት እናታቸው ያዩትን ስለነገሯቸው ያዩ ያህል ነው ንግግራቸው፡፡ እናታቸው ያዩት አውሮፕላን በሸለቆ ውስጥ ይሄድ ነበር፡፡ በተራሮች የተከበበችው የንገት ሸለቆ ለአውሮፕላን ጉዞ አትመችም፡፡ አውሮፕላኑን እዚያ ምን አመጣው ከተባለ ደግሞ ጉም ይሆናል መልሱ፡፡ ደመናና ጉም ሲያስቸግረው ብርሃን ፍለጋ ወደ ንገት መጣ፡፡ ወደላይ ወደ ሰማይ መውጫ መንገድ ሲፈልግም መንገድ ያገኘ መሰለውና ሽቅብ ሄደ፡፡ ከተራራው ወጣ እንዳለ ደግሞ ሜዳ ያገኘ መሰለውና ከሌላው ተራራ ጋር ተጋጨ፡፡ ከገደል ገደል ይላተምና የአደጋው ድምጽም ከሸለቆ ሸለቆ ያስተጋባ ጀመር፡፡ አንድ በስራ ላይ የነበሩ እና ወሬውን ያዩ ገበሬ በመደናገጥና ሕዝብም እንዲደርስ በማሰብ ‹‹ውውው የመንግስት ሮቢላ!!›› እያሉ መጮሃቸው ይተረታል፡፡ ሙሽሮች ናቸው አሉ የተሳፈሩት፡፡ በሕይወት አልተረፉም፡፡ ከአውሮፕላኑ ስብርባሪ ውስጥ ገንዘብ ተገኘ፡፡ ያንን ገንዘብም ቀድመው የደረሱ ግማሹን ወሰዱት፡፡ በኋላ አስተዳዳሪዎቹ መጥተው አገሩ ሲረጋጋ እየገረፉ ገንዘቡን ተቀበሏቸው፡፡ የዘረፉትም የአውሮፕላን ብር ሌባ የሚል ስም ወጣላቸው፡፡ የአውሮፕላኑ ቁርጥራጭም በየማሳው የወፍ ማስፈራሪያ ይሆን ዘንድ ተተከለ፡፡ የቤት ቁሳቁስም ተሰራበት፡፡ በአጭሩ በሸዋ አማርኛ ራስ አበበ አረጋይ የጣሏትን አውሮፕላን ዓይነት ዕጣ ገጠመው!
‹‹ቆላው ውስጥ አውሮፕላን ደመና አስቸግሮት ሲያርፍ ምግብና ጠላ እንወስድ ነበር›› ብለው እኝሁ ምሁር አውግተውኛል፡፡ ‹በአደጋ አውሮፕላን ቢያርፍ አይገርምም› ብትሉ ተሳስታችኋል፡፡ ለመጓጓዣም አውሮፕላንን መንዝ ተጠቅማለች፡፡ ለጉብኝት፣ ባለስልጣኖችን ለማድረስ፣ የእርዳታ እህል ለማመላለስና ለሌሎችም ዓላማዎች አውሮፕላኖች መንዝ ብዙ ጊዜ አርፈዋል፡፡ ‹‹አውሮፕላን እያየን እኮ ነው ያደግነው! ወደኋላ እንደሄድን ይሰማኛል›› ይሉኛል እኚሁ ምሁር በቁጭት፡፡ ተራ የአውሮፕላን ማየትን ያለፉት በመጀመሪያዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪነታው ወቅት እንደሆነ የሚናገሩት ምሁሩ አውሮፕላን ሲመጣ ተሯሩጠው እንደሚሄዱ ይናገራሉ፡፡ አንድ ትዝታቸውም እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
የማይረሳ የህጻን ሞት! ፡-
አንድ የእርዳታ ሰጪዎቹ ፈረንጆች ልጅ (ስምንት ዓመት ገደማ ይሆነዋል አሉ) መጋዘን ውስጥ የእርዳታ እህል የያዘ ጆንያ ወድቆበት ሞተ፡፡ ሲላቀሱ ያዩትን ሳይኮሎጂስቱ ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ፈረንጆቹ ሐዘኑ ልባቸው ገባ›› አሉ፡፡
ግራም ነፈሰ ቀኝ ‹‹መንዝ ሩቅ ስለሆነ አውሮፕላን ያስፈልገዋል›› ይሏችኋል፡፡
‹መንዜ› ፈረንጆች
ጓሳ ውስጥ ፈረንጆች ካምፕ አላቸው፡፡ ዶ/ር ካናታ መንዝ ውስጥ የሚኖር ሚሽነሪ ሐኪም ነበር፡፡ ዶናልድ ሌቪን መንዝ ኖሮ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ የሰላም ጓዶች አሁንም አሉ፡፡ መሐል ሜዳ መሰናዶ 12ኛ ክፍል የምታስተምረውም የእንግሊዝኛ መምህርት አሜሪካዊት ነች፡፡ ለማንኛውም የመንዝና የፈረንጆች ግንኙነት አንድ ትኩረታችንን የሚስብ ነገር ነው፡፡ ንገት ላይ ስለተከሰከሰችው አውሮፕላን መረጃ ለማፈላለግ ወደ ኢንተርኔት ገብቼ በነበረበት ወቅት ስለሌላ ወደ መንዝ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ስለሄዱ ግለሰብ የሚያትት መጽሐፍ አገኘሁ፡፡ እንደሚከተለው እንግሊዝኛውን እንዳለ በፎቶ አቀርዋለሁ፡፡ ፎቶው ካልከፈተላችሁ Our God Still Speaks ብላችሁ ፈልጉ፡፡
በተያያዘ ወሬ
የልጅ ኢያሱ ጉግስ መጫወቻ መንዝ መኖሩን ተገንዝቤያለሁ፡፡ የአሁኑን የመንግስት አስተዳደር ሁኔታ አስመልክቶ ብዙም ለመሰለል ባልችልም ቅሉ መንዝ ላይ የቤተሰብ ፖሊስ እንዳለ ደርሼበታለሁ፡፡
‹ኤቲኤም በመጠቀም የመጀመሪያው ነኝ መሰለኝ ማሽኑ በጣም አዲስ ነው› አለኝ አንድ ወዳጄ፡፡ ‹ሙዚቃም ጋበዘኝ ማሽኑ› ሲል አከለ፡፡ ጨዋታ አዋቂው ወሎዬ ጓዴ ለረጅም ሰዓት ለርቀት ትምህርት ተማሪዎቹ ማጠናከሪያ እንዳስተማረና በበቃኝ እንዳሰናበታቸው አውግቶልኛል፡፡
የባህል ነገር
መንዝ ላይ አልፎ አልፎ የስነጽሑፍ ምሽት ይካሄዳል፡፡ ስፖንሰር በማፈላለግ ቢራ ይጋበዛል፤ ሻማ እያበሩም ይመሰጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት ግን ለባህል ግድ የሚሰጠው አስተዳደር ቢኖር እንዴት በሰመረ! በሐገራችን በጣም ከተበደሉ ዘርፎች አንዱ ባሕል ስለሆነ የሰራተኞቹ ድካም አጋዥ የለውም፡፡ ስለ ባህልም ሆነ ስለ ማናቸውም ስራ መዘመንና መሻሻል ስታወሯቸው ብዙ የመንግስት ሰራተኞችም ሆኑ ነዋሪዎች የዩኒቨርሲቲውን እገዛ ይጠይቃሉ፡፡ ስለዚህ እኛም መልዕክቱን አድርሰናል፡፡
አንዳንድ ተጠያቂዎች እንዳሉትና እኔም እንዳየሁት
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ሸዋ ከከፈታቸው ስድስት የርቀት ትምህርት ማስተባበሪያ ማዕከላት አንዱ በመሐል ሜዳ ስለሚገኝ ነበር ከመምህራን የስራ ባልደረቦቼ ጋር ወደ ስፍራው የተጓዝኩት፡፡
የርቀት ትምህርቱን አሰጣጥ አስመልክቶ የጠየኳቸው አንድ መምህር እንዳሉት ተማሪዎቹ በዚያ ብርድ ተጠብሰው ነው ብሩን የሚያገኙትና የሚከፍሉት፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲው ግን ፈተና ስላከበደባቸው ከግማሽ በላይ ተማሪ ወድቋል፡፡ ለምን እንደርቀትነቱ አይታይም?›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
ሌሎች ምልከታዎቻቸውንም እኝሁ ከደቡብ ኢትዮጵያ የሚወለዱ ምሁር አውግተውኛል፡፡ ‹‹ልገስግስ ልሂዳ የሚለውን ዘፈን እንኳን አንዴ ነው የሰማነው፤ ዘመናዊ ዘፈን ነው ያለው በየስፍራው፡፡ ሆቴል አላየሁም፡፡ ሌላ ቦታ ስጋ ቤቱ ውጪ ላይ ነው ያለው፡፡ መሐል ሜዳ ግን ስጋው ጓዳ ነው፡፡ በዚያ ላይ ሴቶች ናቸው ስጋ የሚሸጡት፡፡ በዚያ የገጠር ከተማ ውስጥ ሁለት፣ ሦስት ሺሻ ቤት ማየቴ አስደንግጦኛል፡፡ በመምጫችን ዋዜማ ካልሆነ በቀር መብራት ያለመጥፋቱ ግሩም ነው፡፡ ገበያው ደግሞ ያልተደለደለ ቦታ ነው - ገደላማ - ድንጋይ - ቁልቁለት - ዳገት! ቱቶሪያል መስጫ ዋይትቦርድ፣ ኤልሲዲ ቢኖር ጥሩ ይመስለኛል፡፡ አሁን መንገድ ላይ ተገናኘን እንጂ ብዙ ነገር እነግርህ ነበር፡፡››
‹‹ካምፓስ እንጂ የርቀት ትምህርት ቅርንጫፍ መክፈት ሌሎች ብዙ የግል ኮሌጆች ስላሉ ብዙም አያበረክትም፡፡ ካምፓስ ለእድገት ይጠቅማል፤ መንገዱ ወደፊት ዋና መንገድ ስለሚሆን የህዝብ ለህዝብ ፍሰትንና ገበያን ስለሚያበረታታ ጥሩ ነው፡፡ ‹አንዱን ካምፓስ በደንብ መጠቀምና ጥራቱን ማስጠበቅ ነው› ይላል ዩኒቨርሲው ሲጠየቅ፡፡ እስኪ የዩኒቨርሲቲውን ቦርድ ወይም ዞኑን ጠይቅ፡፡ የዩኒቨርሲተው ኃላፊዎች ብዙም ያመኑበት አይመስለኝም›› የሚለው የአንድ የአካባቢው ተወላጅ መምህር ሃሳብ ነው፡፡
ደቦ በሚል ስም የተከፈተው ቤተመጻሕፍት የአንዲት የከተማው ተወላጅ እንስት ዶክተር ስራ መሆኑን ሰምቼ ደስ ብሎኛል፡፡ ፈረስ የሚያስፈትን አዳራሽ! የኮድ ኢትዮጵያን ቤተመጻሕፍትም አይተናል፡፡ ትንሽ ትኩረት ቢጨመርለትና መጻሕፍቱ ቢታዩ መልካም ነው፡፡ የመሐል ሜዳ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራልን ግዝፈት አይቼ ምን አሰብኩ መሰላችሁ - አቤት ማማሩ ነው ያልኩት! ከተማው ውስጥ አስፋልት ረግጫለሁ - ጥራቱ የተጓደለ ቢሆንም፡፡ ወደ ዓለም ከተማ የሚወስደው የአዲሱ መንገድ አካል ነው መሰለኝ፡፡
‹‹መንዝ ትኩረት አጥታለች፡፡ የመሰረተ-ልማት ችግር አለባት፡፡ መሐል ሜዳ አቧራውን ለማስታገስ ኮብልስቶን እንኳን ቢሰራ ምን አለበት?›› እያሉ አንዱ መምህር ሲያወሩ ሁሉም መምህር እየሰማ በመስማመት ራሱን ይነቀንቃል፡፡
የመጨረሻው መጀመሪያ
‹‹አገርሽ ሄጄ መጣሁ፤ በጣም ደስ የሚል አገር ነው ያላችሁ›› ያልኳት አንድ የመሐል ሜዳ ልጅ በአስተያየቴ አልተደሰተችም፡፡ ‹‹ሰዉ ክፉ ነው! ምናልባት አገሩ ጥሩ ሊሆን ይችላል!›› ስትል መለሰችልኝ፡፡ እኔም አንዳንዴ ስለትውልድ ስፍራዬ ስለ ሳሲት የሚሰማኝን ነገር ነው የተናገረችው፡፡ አብሬያቸው ብዙ ስቆይ ፀባያቸው ይቀየር አይቀየር ባላውቅም በአሁኑ ቆይታዬ ግን መንዞች ተወዳጅ ናቸው!
በመጨረሻም
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ትምህርት ክፍል ከዞኑ ባህል ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ሰሞኑን የውይይትና ጉብኝት መርሃ-ግብር ነበራቸው፡፡ በዚህም ወቅት መንዝ ጓሳንና መሐል ሜዳን ጎብኝተዋል፡፡ ለአትኩሮታቸውና ለጥረታቸውም አመሰግናለሁ፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያውን ነገር ግን አደራ! ቶሎ እንዲሰራልን እንደ ግብር ከፋይነቴ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
መጪው የጉዞ ማስታወሻችን ስለ አምቦ ይሆናል፡፡
አቹማ ወልሃገራ!








በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...