2020 ጃንዋሪ 14, ማክሰኞ

የይሁዳው አንበሳ በሠሜን አሜሪካ


የይሁዳው አንበሳ በሠሜን አሜሪካ፣
የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አሜሪካውያን ስለ አፍሪካ ያላቸውን ዕይታ የቀየዱበት  መንገድ
ደራሲ - ቲዎዶር ቬስታል (ፒኤችዲ)
ማጠቃለያ ነክ ዳሰሳ - መዘምር ግርማ
‹‹የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ዕቅድ አገሪቱን (ኢትዮጵያን፣ ሰፋ ሲልም አፍሪካን ለማለት ነው) መረጋጋት ለመንሣት የምትጋለጥባቸውን የጎሣ፣ የኃይማኖትና ሌሎች ክፍፍሎችን በመጠቀም በማያበራ የውስጥ ግጭት ውስጥ አስገብቶ ማቆየት መሆን ይገባዋል›› ሄኒሪ ኪሲንጅር
ይህ መጽሐፍ ከታተመ ዐሥር ዓመት ሆነው፡፡ ይሁን እንጂ መጽሐፉን ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ጀምሬ ትቼው ቆይቼ ሰሞኑን እንደገና ጀምሬ ጨረስኩት፡፡ መጽሐፉን ለማንበብ ያነሣሣኝ ደጃዝማች ወልደሠማያት ገብረወልድ ለናሁ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለመጠይቅ ከጠቀሱት በኋላ ነው፡፡ የቃለመጠይቃቸው ይዘት በሸገር ኤፍኤም ለመዓዛ ከሰጡት ከሃያ ክፍሎች በላይ ካለው ቃለመጠይቅ ጋር የተያያዘና ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊቆጭበት የሚገባ ነው፡፡ ንግግራቸው ሶቬቶች የኢትዮጵያን ግብርና በትራክተርና በኮምባይነር በማድረግ ለማሳደግ ስላደረጉት 100 ሚሊዮን ዶላር ምጣኔሐብታዊ ድጋፍና ይህም ሥራ ላይ እንዳይውል አሜሪካ ስላስተባበረችው 1953 የአለቃ ነዋይ ቤተሰብ መፈንቅለ-መንግሥት ነው፡፡ 
ዳሰሳዬ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የቀረበ ሲሆን የደራሲውን በርካታ ጥቅሶች ስላካተተ በትዕግስት እንድታነቡትና ፍሰት ባይኖረው እንድትታገሱኝ እለምናለሁ፡፡ ተረፈ በዚህ በአማርኛው ዳሰሳ የበለጠ ነጻነት ይሰማኛል፡፡ አንደኛ ቋንቋውን በሚገባ ስለምችልና ኢትዮጵያውያን ስለሚያበነቡልኝ ሲሆን፤ በእንግሊዝኛው ግን ምንም እንኳን መረጃው ለህዝብ ይፋ የሆነ የአሜሪካ መንግሥት ምስጢር ቢሆንም አሜሪካውያን ወዳጆቼ እንዳይከፉ ስለምጠነቀቅ ነው፡፡
ግርማዊነታቸው ኒውዮርክ ከተማ አደባባይ አንቆጥቁጦ የተቀበላቸውና በዋይት ሃውስ ያደሩ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ናቸው፡፡ ማናቸውም የዓለም መሪ ያላደረገውን ከእ... 1954 - 1973 ወደ ዋሽንግተን ስድስት ጉዞዎችን ያደረጉ ናቸው፡፡ እንደ ደራሲው አገላለጽ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በአሜሪካ ምን ያህል ገናና እና ተወዳጅ እንደሆኑ በአሁኒቷ ኢትዮጵያ አይታወቅም፡፡ ምክንያቱም ከሳቸው ተከትሎ የመጡት ሁለት አገዛዞች ስማቸውን ስላጠፉት ነው፡፡
የምንዳስሰው መጽሐፍ የሚከተሉትን ጥያቄዎች የመመለስ ስራን ተወጥቷል፡፡
. ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በአሜሪካ ለምንድነው ይህን ያህል ዝና የተቀዳጁት
. ንጉሠነገሥቱ አሜሪካ ለአፍሪካ ያላት ፖሊሲና አመለካከት ላይ ይህን ያህል ተጽዕኖ ለማሳደር የቻሉ ብቸኛ ሰው እንዴት ሊሆኑ ቻሉ
. የንጉሠ ነገሥቱ ይፋዊ ጉብኝቶች አሜሪካ ለሁለት ዐሥርት ዓመታት ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ ያሏትን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዎቸ እንዴት ሊያንጸባርቁ ቻሉ  
መጽሐፉ የኢትዮጵያን መልከዓምድር፣ ታሪክና ባህል በአጭሩ በማስተዋወቅ ይጀምራል፡፡ የራስ ተፈሪ ታሪክና የአባታቸው የራስ መኮንን የህይወት ጉዞ ይከተላል፡፡ ራስ ተፈሪ  በኢጀርሳ ጎሮ (ሐረርጌ) ተወለዱ፡፡ ውጪ ተጉዘው ከነበሩ ሹም የተወለዱት ራስ ተፈሪ በሐረር የቤተክህነት ትምህርትና አማርኛ ከካህናት እንዲሁም ፈረንሳይኛ በስፍራው ከነበሩ የውጭ ዜጋ የሃይማኖት ሰው ተማሩ፡፡ አባታቸውን በልጅነት ዕድሜያቸው ያጡት ተፈሪ አስተዳደጋቸው ፈተና አልተለየውም፡፡ የንጉሥ ሣህለሥላሴ ዘር በመሆናቸውና የንግሥናውን መንበር ይቀናቀናሉ ተብሎ በመታሰቡ በተለያዩ ሩቅ ክፍላተ-ሃገራት እየተበደቡ እንዲሰሩና ከአዲስ አበባ እንዲርቁ  ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ አመራርን ከአባታቸውና ከነዚህ ውጣውረድ ካነበረባቸው ጊዜያት ስለተማሩ የራሳቸው የመሪነት ብልሃት ይዘው ብቅ ሊሉ ችለዋል፡፡ ይህም ጥንቃቄ የተሞላበት አገር የማዘመን አካሄድ መሆኑ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ አስቸጋሪውን መሰናክል እየሰባበሩ ከሥልጣን ማማ ላይ ለመውጣት ችለዋል፡፡
ተፈሪ በብዙ መንገድ ብቸኛው፣ የመጀመሪያው ወዘተ የሚሉ አማላይ ቅጽሎችን ለማግኘት የቻሉ የምኒልክ መንበር ወራሽ ናቸው፡፡ ለውጪ ጉብኝት አገራቸውን ለአራት ወር ተኩል ለቀው ለመሄድ የመጀመሪያው ናቸው፡፡ ታይም መጽሔት የዓመቱ ሰው ብሎ የሰየማቸው ሁለቴ ነው፡፡ አንደኛው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተብለው በነገሡ ወቅት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በፋሽስት ወረራ ወቅት ተጋድሎ ባደረጉ ጊዜ ነው፡፡  
የሞሶሎኒ ወረራ ንጉሠነገሥቱን ወደ እንግሊዝ እንዲሰደዱ ያስገደደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በእንግሊዝ በነበሩበት ጊዜ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያፉት ንጉሠነገሥቱ ምን ያህል ብረት እንደሆኑ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ አንድ አብነት እንይ - በዚህ የጦርነት ወቅት 1936 ለገና በዓል ለአሜሪካ ሕዝብ በቢቢሲ ሬዲዮ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ለማስተላለፍ የሄዱበት ሁኔታ ግሩም ነው፡፡ የመኪና አደጋ ደርሶባቸውና የጉልበት መሰንጠቅ አጋጥሟቸው እንኳን መልዕክቱን ከማድረስ አልቦዘኑም፡፡ በእንግሊዝ ጥላ ስር አገራቸው ነጻ እስክትወጣ ድረስ አያሌ ፈተናዎችን አልፈዋል፡፡
የነ እንግሊዝ የተባበረው ግንባር ጥቃት ጣሊያንን ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ቀንድ በወራት ውስጥ ጠራርጎ ያወጣል - ይህም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የመጀመሪያ ድላቸው ሆኖ ይመዘገባል፡፡ የኋላ ኋላ ኢትዮጵያ በእንግሊዝ ወታደራዊ አገዛዝ ስር ወድቃ የመከፋል ስጋት ተጋረጠባት፡፡ ያንን አደጋ ለመቀልበስ የአሜሪካን እገዛ መጠየቅ ግድ ይል ነበር፡፡ እንዲህም ሆነ - ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በምስጢር ወደ ካይሮ ተጉዘው ፕሬዚዳንት ሩዝቬልትን አገኙ፡፡ አመርቂ ውጤት የሚያመጣ ቃል ተገባላቸው፡፡ ቸርችልም የንጉሠነገሥቱን መምጣት አዲስ አበባ ካለው ባለሥልጣናቸው ሰምተው ካይሮ በመሄድ ጥሩ የማይባል ንግግር ከቀኃሥ ጋር አደረጉ፡፡
‹‹ቀኃሥ ከአገራቸው 7000 ማይል ርቀው ይህን ያህል ሊወደዱ የቻሉት ለምንድነው?›› ሲል ይጠይቃል ደራሲው፡፡ የወቅት አጠቃቀማቸውንና ዕድሎችን በትክክል የመጠቀማቸውን ነገር ጨምሮ በርካታ ምክንያቶችን ያቀርባል፡፡
‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት እየተጋጋለ በሄደበት ወቅት ቀኃሥ የኮሚኒስትን መረራ ለመግታት የሚጠቅሙ ሁነኛ አጋር ነበሩ፡፡›› ይህንንም ያስመሰከሩት በኤርትራ የሚገኘውን ሁነኛ የመገናኛ ማዕከል ቃኘው ሻለቃን ለአሜሪካ በመስጠታቸው ነው፡፡ በወቅቱ ለመገናኛ ማዕከልነት የሰጠ የሚባለው ቃኘው 1943 ... በአሜሪካውያን እንደገና ታድሶ ፔንታጎንን ያገለግል ጀመር፡፡ 1970 3000 አሜሪካውያንና ቤተሰቦቻው በቃኘው ይኖሩ እንደነበር ስንገነዘብ ምን ያህል ትልቅ ስራ ይሰራበት እንደነበር መገንዘብ እንችላለን፡፡
ፖይንት ፎር የተባለው የፕሬዚዳንት ትሩማን መርሐግብር የሦስተኛውን ዓለም አገራት በልማት የሚያግዝ ነበር፡፡ ኢትዮጵያም በዚህና በሌሎች መርሐግብሮች ተጠቃሚ ነበረች፡፡ የቃኘውን ኪራይ ለመክፈልና የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር እነዚህን የመሳሰሉ እገዛዎች ይደረጉ ነበር፡፡ የቀኃሥና የአሜሪካ መንግሥታት ግንኙነት የኮሪያ ጦርነት ሲፈነዳም የበለጠ ለመጠናከር ቻለ፡፡ ኢትዮጵያ በሦስት ዙሮች 5000 ሰራዊት አሰልፋ ተዋግታ የጋራ ጸጥታ አራማጅነቷን አስመስክራለችና፡፡ የኢትዮጵያንና የአሜሪካን ግንኙነት ያጠናከረው ሌላው ጉዳይ ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል ያደረገችው ድጋፍ ነው፡፡    
ደራሲው የቀኃሥን የአሜሪካ ጉዞዎች ለትንታኔውና ለድምዳሜው መነሻና መድረሻ አድርጎ ተጠቅሟል፡፡ የክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል የቀኃሥን የአሜሪካ ጉዞ የተመለከተ መጽሐፍና ሌሎችም በርካታ ሰነዶችን እንደተጠቀመ ገልጧል፡፡
1954 ቀኃሥ ወደ አሜሪካን አገር ትልቅ ንጉሣዊ ጉዞ አድርገዋል፡፡ ግንቦት 26 ቀን ቀኃሥ በፕሬዚዳንት አይዘንአወር አውሮፕላን ተሳፍረው ዋሽንግተን ብሔራዊ አየር ማረፊያ ደረሱ፡፡ የሃገሩ ልማድም ስላልነበረ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በቦታው ተገኝተው አልተቀበሏቸውም፡፡ በዚህ ግርታ ውስጥ እንዳሉ በምክትል ፕሬዚዳቱ አቀባበል የተደረገላቸው ቀኃሥ ውጪ ከተማሩት ንጉሣውያን ቤተሰቦች ልዑል ሳህለሥላሴና ልዕልት ሰብለ፣ ከጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉና ከልጅ እንዳልካቸው ከሌሎችም ተጓዦች ጋር ነበሩ፡፡ በዋይት ሃውስ ፕሬዚዳንት አይዘንአወር ስለቀኃሥ ሲናገሩ ‹‹የነፃነትና የእድገት ተከላካይ በመሆን ገናና ስም የገነቡ›› ሲሉ በማሞካሸት ነበር፡፡  ለቀኃሥ አራት ዋና ዋና የድጋፍ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ፐሬዚዳንት አይዘንአወር ‹‹የአሜሪካ መንግሥት የሚሰራቸው ስራዎች ከበርካታ ዓለምአቀፍ ግዴታዎቻችን አንጻር መታየት ስላለባቸው የሚፈልጋቸውን ሁሉ ተግባራት መፈጸም ሊያዳግተው ይችላል፡፡›› ብለዋል፡፡
በአንድ የአሜሪካ ስቴዲየም ቀኃሥ የቤዝቦል ጨዋታ ባዩ ጊዜ መከታተል አልከበዳቸውም ነበር ተብሏል፡፡ ምክንያቱም ጨዋታው ገናን ስለሚመስል ነው፡፡ የገና ጨዋታም የፊልድ ሆኪና የቤዝቦል ድብልቅ በሚል ተገልጧል፡፡ ቀኃሥ በጉዟቸው ከተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር፤ ሽልማቶችን፣ ሜዳዮችን፣ በአማርኛና በግዕዝ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን፣ መስቀሎችን፣ ጋሻዎችንና ጦሮችን በመስጠትና ልዩ ልዩ ስፍራዎችን በመጎብኘት ነበር፡፡ በመጀመሪያው ጉዟቸው .ዳብልዩ. የተባለውን የአውሮፕላን አምራች መጎብኘታቸው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ መጠንሰስ አግዟል፡፡
አማላይ ልቦለድ በሚመስል መልኩ የተጻፈው መጽሐፉ የተሳካለት አንድም አስገራሚ ታሪክ ያላቸውን ንጉሠነገሥት ታሪክ ስለዘገበ ነው፡፡ በሰሜን አሜሪካ ቆይታቸው ካናዳንም የጎበኙት ቀኃሥ ከመስተንግዶውና ከጉብኝቱም በላይ ፈረንሳይኛ በየቦታው የመኖሩን ነገር አደናንቀዋል፡፡ ሜክሲኮ በሄዱ ጊዜም የኢትዮጵያ አደባይ የተባለውን ስፍራ አይተው አድንቀዋል፡፡ ከዚያ መልስ በአዲስ አበባም ለሜክሲኮ ተመሳሳይ አደባባይ ሰይመውላታል፡፡ ሜክሲኮ 1930ዎቹ የመከራ ወቅት የኢትዮጵያን ነጻነት ከደገፉ አምስት አገራት አንዷ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ዝነኛ የነበሩት ንጉሠነገሥት በጦርነት ለተንኮታኮተችው ጀርመን በኢትዮጵያ የተመረተ ብርድ ልብስ መለገሳቸውም ሁነኛ የህዝብ ግንኙነት ስራ ነው፡፡
በ1956 ለኢትዮጵያ ጦር ማጠናከሪያ የ5 ሚሊየን ዶላር እርዳታ ተደረገ፡፡ ለሌሎች በጋራ ስምምነት ለተደረገላቸው ስራዎች ደግሞ ሌላ 5 ሚሊየን ዶላር ተመድቧል፡፡ የኢትዮጵያ ዘውዳዊ መንግስት ግን አለመርካቱን እንደወትሮው እንደገለጸ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ገለልተኛ አቋምና ግፋ ሲልም የሶቭዬትን ድጋፍ ወደመጠየቅ አዘነበለ፡፡ የሶዬቶች እንቅስቃሴም በ1956 በሃገሪቱ ጨማምሮ ነበር፡፡ የእንግሊዝን ነገር በተለመከተ ከአስር ዓመታት ማንገራገር በኋላ በ1951 ለቃ መውጣቷ አንድ እርምጃ ነው፡፡ ያቄሙት ንጉሠነገሥት በ1959 ሞስኮን ጎብኝተው ከሶቭየት የ100 ሚሊየን ዶላር እርዳታ መዛቅ ቻሉ፡፡ ይህም የገንዘብ መጠን አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከሰጠችው ገንዘብ ድምር በብዙ እጥፍ ይበልጣል፡፡ሲ.አይ.ኤ. ሶቭየት ወደ ኢትዮጵያ ሰርጋ እንዳትገባ ስጋት ገባው፡፡ ንጉሠነገሥቱም ለቃኘው ሻለቃ መመስረት በነሻ የሆነውን ስምምነት ለመሻ ር የማሰባቸው ጭምጭምታ ይሰማ ጀመር፡፡
የአፍሪካ፣ የሶማሊና የአፍሪካ ቀንድ ነጻ መውጣት አሜሪካን ሶቭት ወደ አካባቢው እንዳትስፋፋ ያሰጋት ጀመር፡፡ የሶማሊ ነጻ መውጣት ኢትዮጵያ የምትተነኮስባቸውን መንገዶች ስላበዛባት አሜሪካንን የመሳሪያና የመከላከያ ስልጠና እንድታደርግላት ደጋግማ እንድትለምን ምክንያት ሆነ፡፡ ይህንንም ልመና ተለማኟ በሚገባ አላሟላችም፡፡ የእንግሊዝ ውጥን የሆነው ታላቋ ሶማሊያ ጉዳይ የኢትዮጵያን የልማት ትኩረት በአያሌው ያሰናከለ መሆኑን የአሜሪካ ባሥልጣናት በበርካታ ምልከታዎቻቸው ያቃማጡት ነው፡፡ ችግሩ ይህ ችግር ሳይሻሻል ለምን ወደ ልማት አታተኩሩም እያሉ የሚናገሩት ነገር ነው፡፡ ከዚያም 1960 ዓይኑን አፍጥጦና ጥርሱን አግጥጦ ቀኃሥ ላይ ‹‹መጣሁብዎ!›› ይላቸዋል፡፡  መፈንቅለ-መንግሥቱን አስታወሳችሁት! የቀኃሥ የሥልጣን መሠረት የተነቃነቀበት ነው፡፡በዚህ ሴራ አሜሪካ ራሷ ንቁ ተሳታፊ እንደነበረች እርግጥ ነው፡፡  በሶቭዬቶች ድጋፍና ቅርርብ ያልተደሰቱት አሜሪካውያን ከድራማው ጀርባ ነበሩ፡፡ የአሜሪካው የአዲስ አበባ አምባሳደር ከአድመኞቹ ጋር እንደነበርና በአረንጓዴ ምንጣፉ ግድያ ወቅት በመስኮት ዘሎ መጥፋቱ በዚህ መጽሐፍ ጸገልጧል፡፡ ይህ ግድያ በገነተ-ልዑል ቤተመንግሥት የኢትዮጵያን ነፃነት በማፍቀር የሚታወቁት ልምድ ያካበቱና በእሳት የተፈተኑ ባለሥልጣናት የተገደሉበት ነው፡፡ የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚንስትርና የደህንነት ሰው የሆኑት ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊና ታዋቂው አርበኛ ራስ አበበ አረጋይ  ከተገደሉት 18 ሰዎች ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ አሜሪካውያንና ሌሎች የምዕራባውያን አገራት ትልቅ ነጥብ አስቆጥረዋል፡፡
የ1963ቱ ሁለተኛው የቀኃሥ የአሜሪከ ጉዞ ንጉሠነገሥቱ ፕሬዚዳንት ኬኔዲን ያገኙበት  ነበር፡፡ ኬኔዲ ባደረገው ንግግር 29 አገራተ ነጻ የወጡበት የስድሳዎቹ መጀመሪያ የራሱ ፈተናዎች ያሉት መሆኑን ገለጸ፡፡ ለንጉሠነገሥቱም አቋሙን በእርግጥ ነግሯቸዋል፡፡ ‹‹አሜሪካ የማትፈጽመውን ቃል አትገባም›› ብሏቸዋል፡፡ ሶማሊያንም ሶቭዬቶችን እንዳትቀላቀል ለመከላከል በመሳሪያ ድጋፍ እንደሚይዛት ነግሯቸዋል፡፡
ኬኔዲ የአፍሪካ አገሮችን ሰላምጓዶችን በመላክና እርዳታን በእጥፍ በማሳደግ አግዟቸዋል፡፡ ሰላም ጓድ የተባለው መርሐግብርም ልክ እንደ ፖይንት ፎር ያለ ነው፡፡
በ1960ዎቹ መጀመሪያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በቀኃሥ ብልህ አመራር ተመሠረተ፡፡ ኃይለሥላሴ የአሜሪካ የቀዝቃዛው ጦርነት አጋርና የጋራ ሰላም አራማጅ በመሆናቸው ወደ ኮንጎ ወታደሮችን ለሰላም ማስከበር ዘመቻ ልከዋል፡፡ ከ1963 ጉዟቸው ትንሸ ቀደም ብሎ በሐረር ከአሜሪካው አምባሰደር ጋር ውይይት ያደረጉት ንጉሠነገሥቱ ኢትዮጵያና ህዝቧ ይህን ያህል ያነሰ እገዛና መከዳትን ከአሜሪካ መንግስት እንደማይጠብቁ ተናግረዋል፡፡ በዚህ የግል ውይይታቸው በርካታ ቅራኔዎችን አንስተው የተወያዩ ይመስላል፡፡ ስለ መፈንቅለ-መንግሥቱም ጭምር፡፡ ምንም እንኳን ከብራዚል ሲመለሱ በአየር ማረፊያ የተቀበላቸውን ሪቻርድ የተባለውን አምባሳደር አድማውን ስለማስቆሙ በማመስገን ስም ቢሸረድዱትም፡፡
በሁለተኛው ጉዞም ንጉሠ ነገሥቱ የአሜሪካውያንን ልብ ያሸፈቱ ይመስላል፡፡ እዚች ጋ በማህህራዊ ሚዲያ በሚዘዋወሩ የዚህ ጉዞ ምስሎች ላይ ሃሳብ መስጠት ይኖርብናል፡፡ ይኸውም ጉዞው የደመቀው በአሜሪካ ህዝብ መልካም ጉጉትና ፍላጎት ብቻ አለመሆኑን ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የመንግስት ጉተጎታና ጉብኝቱን የማድመቅ ስራ ስለተሰራ ነው፡፡ የራሱ ምስጢር እንዳለው ለመረዳት የላይኛውን አንቀጽ መሰንጠቅ ያሻል፡፡ ይህ ጊዜ አሜሪካ በቃኘውና ከፍ ሲልም በአፍሪካ ቀንድ የነበራትን ይዞታ ያጠናከረችበትም ነው፡፡ እዚህ ላይ አንዲት ትንሽ ምልከታም አለችን - ጃንሆይ መጥፎ ዕድል አለቻቸው እንዴ ትላለች፡፡ ይህንንም ለማለት የተገደድንበት ምክንያት ሁለት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች እሳቸው ባገኟቸው በሳምንታት ጊዜ ውስጥ መሞታቸው ነው፡፡ ሩዝቬልትና ኬኔዲ!   ‹‹በሁላችንም ዘንድ ኬኔዲ ትልቅ ትውስታ ይኖራቸዋል›› ሲሉ በቀብሩ ላይ የተናገሩት ቀኃሥ ውድ ወጪ አውጥተው ወደ አሜሪካ በፍጥነት ለቀብር መገኘት ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያም የሐዘን ቀን አውጀዋል፡፡   
ሁሉም ነገር የራሱ የሆነ መልካም ዘመን እንዳለው ሁሉ ክፉ ቀንም ዳር ዳር ይልበታል፡፡ እንጃ ብቻ! የጆንሰንንም ሆነ ሦስቱን የኒክሰን ዘመን የቀኃሥ የአሜሪካ ጉብኝቶች ይህ አረፍተነገር ላይገልጻቸው ይችላል፡፡ እርካታ የለሽ ሲባሉ በደራሲው የተገለጹት እነዚህ ጊዜያት ለምን ነበር ቢሉ የሚከተሉትን ሃሳቦች አሰላስሉ፡፡ ጆንሰን ‹‹ዓለማችንን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በዓለም ላይ ካሉ አዛውንት የአገር መሪዎች ብዬ ከምወስዳቸው ሰው ጋር ሃሳብ መለዋወጤ ደስታ እንደሰጠኝ ሳልገልጽ አላልፍም፡፡›› ብሏቸዋል ጎብኚውን፡፡
በዚህ ሰሞን በአዲስ አበባ ያለው የአሜሪካን ኤምባሲ ወደ ስቴት ዲፖርትመንት አሜሪካ እግሮቿን ኢትዮጵያ ላይ እንድትተክል ዕድል ማግኘቷን እያዳነቀ ሲጽፍ ነበር፡፡ምክንያቱም ኢትዮጵያ በአሜሪካ እጅግ ትኩረት ከተሰጣቸው ጥቂት የአፍሪካ አገሮች አንዷ ስለነበረች ነው፡፡  በ1964 ወደ አፍሪካ መግቢያ በር የተባለችው ሃገራችን በፊት በፊት ቅርብ ምስራቅና መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ትነደደብ ነበር - በአሜሪካውያን፡፡ ቴክኖሎጂ እያደገ ሲሄድ የቃኘው ሻለቃ ዋጋ እየቀነሰ እንደሚሄድ አሜሪካውያን ቢያውቁትም እነ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ግን መያዣ አድርገውታል፡፡ በየሰስብሰባው እኛ ስንቱ አገር ሲለምነን እኮ ነው ለናንተ የሰጠነው ይሏቸዋል፡፡ የአሜሪካን ኤምባሲ ስለኢትዮጵያ የስልጣን ሽግግር በጣም እንደሚጨነቅ የሚያሳዩ ፍንጮች አሉ፡፡  ‹‹አይበለውና ንጉሡ ቢሞቱ!›› ሲል የጻፈው አለ፡፡ የማያባራ ቅራኔ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ሶማሊያ ነጻ ወጥታ፣ ባንዲራዋ ላይ አምስቱን ሶማሌዎች የሚያመለክቱ አምስት ክዋክብት ደርድራ የጦርነት ነጋሪት ሰትመታ (በምርጫ የተመረጠ መሪ ባላት ጊዜ እንኳን ሳይቀር) የሶቭዬቶች ድጋፍ ይጎርፍላት ነበር፡፡ ይህን ንጉሠነገሥቱን አስጨነቃቸው፡፡ አሜሪካም ፍላጎታቸውን አታረካም፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ታሪካዊውን የጃማይካ ጉዞ በ1964 አደረጉ፡፡ ራስታዎቹም ፈጣሪ የሚሉትን ሰው ለማግኘት ቻሉ፡፡  
በ1971 14 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተባበሩት መንግሥታት በኒውዮርክ በኢትዮጵያ ባለው የተማሪዎች ይዞታ ላይ ሰልፍ አደረጉ፡፡ ሶማሌዎችም በቀኃሥ ላይ ሠልፍ ለማድረግ አልቦዘኑም፡፡ በተያያዘ ትውስታ ሉሉ የተባለው የንጉሠ ነገሥቱ ውሻ በርካታ የጋዜጣ ሽፋኖችን ለማግኘት ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የውስጥ የደፈጣ ውጊያዎችን በመድጠጥና ከጎረቤት አገራት የሚመጣውን ወረራ ለመመከት የሚያስችለውን የመከላከያ ዝግጅት በማድረግ ተጠምዶ ነበር፡፡ ይህም የበጀቱን ሩብ ያህል ይይዝበት ነበር፡፡  ይልቅ በአገር ዕድገት ላይ ለምን አያተኩርም የሚል ትችት ይቀርብበት ነበር፡፡ ትክክለኛ ወይስ ሁኔታዎችን ያላመዛዘነ ትችት? በሌላ በኩል ፀረ-ቀኃሥ ተቃውሞ ውጪ በምዕራብ አገራት ተምረው በተመለሱ ተማሪዎች ዘንድ ሳይታወቅ መቀጣጠሉ ለአሜሪካም እንግዳ ነበር፡፡ ሰላዮቻቸው ወሬውን ቶሎ ቶሎ አላደረሷቸውም፡፡
በ1969፣70ና 73 የኒክሰን ዘመን የቀኃሥ የአሜሪካ ይፋዊ ጉብኝቶች የጦርመሳሪያና የወታደራዊ ሥልጠና ድጋፍ የተጠየቀባቸው ነበሩ፡፡  በአንደኛው ጉዞ ወቅት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ንጉሠ ነገሥቱ ያሉ መስሏቸው በዋሽንግተን የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰብረው ገብተው አጥቅተው ነበር፡፡
የውስጥ አመጾች በተጋጋሉበት ቀኃሥ የአፍሪካ አገራትን ያሸማግሉ ያዙ፡፡ አስር የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሲወጡና ሲወርዱ ያዩት እድሜጠገብ መሪ የሙስሊምና የኮሚኒዝም ወደ አፍሪካ ቀንድ መምጣት ያሰጋቸው ነበር፡፡ አገራቸው 60 በመቶውን የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ወታደራዊ ድጋፍ ታገኝ ነበር - በዘመነ ኒክሰን፡፡ ያ ዘመን ግን ሃገሪቱን መቆጣጠር አዳጋች የሆነበት ነበር፡፡
የተማሪዎች አመጽ እየተፋፋመና ፀረ-አሜሪካ አቋሞች በግልጽ እየተንጸባረቁ በሄዱ ጊዜ የሠላም ጓዶች በየትምህርት ቤቱ ተደብድበዋል፤ ጥላቻ ተንጸባርቆባቸዋል፤ የባህል ወረራ አስፈጻሚዎች በሚልም ተብጠልጥለዋል፡፡ የኒከሰንም አስተዳደር በራሱ የውስጥ ችግሮች ይፈተንና ለኢትዮጵያ ትኩረት መስጠት ይሳነው ጀመር፡፡
ረጅም ጊዜ ማለትም ለሺዎች ዓመታት የመራውና የመጨረሻው ንጉሠነገሥቱ በማርክሲስት ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት መሪዎች የተገደሉበት የኢትዮጵያ ፊውዳል ሥርዓት ተፈጸመ፡፡
‹‹የአፍሪካ ቀንድ አገራት እየተዳከሙ መሄድ በሄንሪ ኪሲንጀር የተተነበየ ይመስላል፡፡ ኪሲንጀር በ1972 ራሱ ‹ዓለምን የሚመራው ኮሚቴ› ብሎ የሚጠራው የአሜሪካ ብሔራዊ የጸጥታ ምክርቤት ኃላፊ የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ እንድ ምስጢራዊ ሪፖርት ጽፎ ነበር፡፡ የአሜሪካ ፖሊሲ አገሪቱ ተጋላጭ የሆነችባቸውን የጎሣ፣ የኃይማኖትና ሌሎች ክፍሎችን ተጠቅሞ አለመረጋጋት ውስጥ በመክተት በማያባራ የውስጥ ግጭት ውስጥ ማኖር መሆን እንደሚገባው ያሳስባል፡፡ ይህን የኪሲንጀር ምክር አሜሪካ በሚገባ እንደተከተለችው ማየት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ከዚያ ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ቀንድም በመታመስ ላይ ስለሆነ፡፡››
ይህን ከላይ የተጠቀሰውን ጨካኝ ሐሳብ ያመነጨው ኪሲንጀር ከናዚ ጭፍጨፋ የተረፈ አይሁድ አሜሪካዊ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የ96 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ነው፡፡
ደራሲው በሚከተለው የምርምሩ ጽንሰ-ሐሳብ መጽሐፉን ይደመድማል፡-
‹‹በአሜሪካውያን ትውስታ ውስጥ የተቀመጡት (የአጼ ኃይለሥላሴ) አዎንታዊ ምስሎችና ተዛምዶዎች በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዝርያ ያለው ፕሬዚዳንት መመረጥ ላይ የራሳቸው ሚና ነበራቸው፡፡››
መጽሐፉን አንብባችሁ በየሙያችሁ እንድትተነትኑት እጋብዛችኋለሁ፡፡ ደራሲውም ኢትዮጵያውያን ይህን እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡


በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...