2022 ኦገስት 20, ቅዳሜ

የአካባቢ ተወላጆችን እርዱን የሚሉ ተቋማት ሲመጡ

 የአካባቢ ተወላጆችን እርዱን የሚሉ ተቋማት ሲመጡ


በቅርብ ዓመታት ከሣሢት የመንግሥት ተቋማት የእርዳታ ጥሪ አስተላልፈውልኝ ነበር። እናንተም ከተወላችሁበት አካባቢ ወይም ከምትኖሩበት አካባቢ ተመሳሳይ ጥሪዎች ቀርበውላችሁ ያውቁ ይሆናል። በእኔ በኩል ኮቪድ በገባ ጊዜ የሙቀት መለኪያ እንድገዛ፣ ትምህርት ቤቶችን በየወቅቱ እንዳግዝ፣ የወረዳ ተቋማትን እንድደግፍ ወዘተ ጥሪ ቀርቦልኛል። በተቻለኝ መጠን ያገዝኳቸው ወይም ሌሎች እንዲያግዟቸው የጠየኩላቸው ይኖራሉ። ያላገዝኳቸውም እንዲሁ። 

ይህ በዚህ እንዳለ ከሣሢት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2012 የቀረበልኝ ጥሪ ነበር። ለዚህ ጥሪ ምላሽ የተሰጠ አልመሰለኝም። በወቅቱም ሰዎች እንዲያግዟቸው ጠይቄ ነበር፤ አልተሳካም እንጂ። 

ርዕሰመምህሩ ደብረብርሃን ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት መጥተው ነበር ደብዳቤውን የሰጡኝ። የመጻሕፍትን እጥረት በተወላጆች ተሳትፎ ለመፍታት መሞከራቸው ጥሩ ነው። የአካባቢውን አቅም አሟጠው መጠቀምም ያለባቸው ይመስለኛል። በወቅቱ ስለትምህርት ቤቱ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ጠይቄያቸው መረጃ ሰጥተውኛል። እነሱም ራሱን የቻለ የቤተመጻሕፍት ሠራተኛ የለም። ቤተመጻሕፍቱ እስከ ሕዳር ዝግ ነበር። ፕላዝማ በመብራት ምክንያት አይሰራም። ኮምፒውተር ሁለት ላብ ቢያስፈልግም አንድ ብቻ ነው ያለው። በብሔራዊ ፈተና ከ400 ተማሪዎች 10ኛ ወደ 11ኛ ያለፉት 100 ብቻ ናቸው። 

ለነዚህ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የሁሉንም ወገን ጥረት ይጠይቃል። በወቅቱ የተነጋገርናቸው የመፍትሔ ሃሳቦች ቢኖሩም የተወሰነ መጨመር ይቻላል። ለምሳሌ የመብራቱ ጉዳይ አንገብጋቢ በመሆኑ መፍትሔ እንዲያገኝ አስተዳደራዊ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል። ያለዚያ ፕላዝማውም ሆነ ኮምፒውተር ላቡ ጥቅም አይሰጥም ማለት ነው። የቤተመጻሕፍቱ ጉዳይ ሰራተኛ ካልተገኘ በበጎፈቃደኞች ሊሰራ ይገባዋል። ከመምህራን፣ ከአስተዳደር ሰራተኞችና ከተማሪዎች የሰው ኃይል ፍላጎቱን ማሟላት አስፈላጊ ነው። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የሚያልፈውን ተማሪ ቁጥር ለመጨመርና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ያግዛል። ተመሳሳይ ሁኔታዎች በክልሉ ባሉ ሌሎች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ የሁላችንም ክትትልና እገዛ ያስፈልጋል። አግዙን ብለው ለሚመጡትም ሆነ ሄደን አይተን ክፍተቱን ለይተን ለምናግዛቸው ተቋማት እገዛው ግድ የገንዘብና የቁሳቁስ ሳይሆን የዕውቀት፣ የክህሎት፣ የጊዜና የምክር ሊሆን ይችላል። እስኪ ምን ታዘባችሁ? የአማራ የሠላም ጓድስ ምን ይስራ?



2022 ኦገስት 19, ዓርብ

የአሜሪካ ጋዜጣ የዘገበለት የደብረብርሃኑ የስፖርት ማዘውተሪያና የነገ ተስፋው

የአሜሪካ ጋዜጣ የዘገበለት የደብረብርሃኑ የስፖርት ማዘውተሪያና የነገ ተስፋው

በመዘምር ግርማ

ከአማራ የሠላም ጓድ

 

ሠን ኒውስ የተባለው የአሜሪካ ጋዜጣ እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 24፣ 2012 ያወጣው ዘገባ ‹‹ችግርን ሮጦ ማምለጥ›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ነበር፡፡ ዘገባው 9300 ጫማ ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ያላት በማለት በሚያስተዋውቃት ደብረብርሃን አሜሪካውያን በጎፈቃደኞች እንዴት እንደሚኖሩ በማስተዋወቅ ይጀምራል፡፡  የከብቱና የበጉ ጩኸት ከእንቅልፋቸው እንደሚያነቃቸው ያስተዋውቅና የሚሰሩበት ሁኔታ አውድ ያስቀምጣል፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች የሚለዩዋት ታሪካዊ፣ ባህላዊና ማህበረሰባዊ ሁኔታዎች መኖራቸውን ይገልጻል፡፡ በዚህች አገር በምትገኘው ደበረብርሃን ከተማ የሚኖሩት ሁለት ባልና ሚስት በጎፈቃደኞች የመሰረተልማት ችግር ቢገጥማቸውም፣ የዉኃው ነገር ግን አይነሣ ይላችኋል፡፡ በከተማው የሚገኘው የታሸገ ዉኃ አቅራቢ ድርጅት በጥራቱ አቻ የማይገኝለትን የደብረብርሃንን ዉኃ አሽጎ ይሸጣል ይለናል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት እንደሆነ በሠን ኒውስ ዘገባውን ያቀረበችው በጎፈቃደኛ ኤሪን ፖርቲሎ ወይንም የመረጃ ምንጮቿ ያውቃሉ፡፡ እንደዘገባው ሁለቱ በጎፈቃደኞች አሜሪካውያን 17 በመቶ የደብረብርሃን ነዋሪ ይኖርበታል በተባለው የከተማ ዳርቻ ያለውን የድህነት ሁኔታ ተረድተው የበጎፈቃድ ስራቸውን ይሰራሉ፡፡ ከነዚህ ቦታዎች አንዷ የሆነችው ዛንጅራ ኑሯቸውን ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ሁኔታ የሚመሩ አርሶአደሮች እንደሚኖሩባት፣ ልጆች በተለይም ሴቶቹ ወደ ትምህርት ቤት የመሄድም ሆነ ትምህርታቸውን የመቀጠላቸው ሁኔታ አስጊ መሆኑን እንዲሁም ወደ አቅራቢያዋ ከተማ ደብረብርሃን ስደት ግድ የሚል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከከተማዋ አራት ማይል የምትርቀው ዛንጅራ ልጆቿን ወደ ደብረብርሃን ስትልክ ነገሮች አልጋ ባልጋ ሆነው አይጠብቋቸውም፤ ሕይወት የራሷን ፈተና ትደቅናለች፤ ቢደፈሩስ፣ ኤች.አይ.ቪ ቢይዛቸውስ  ይለናል፡፡ ከአገሪቱም ሆነ ከክልሉ ከፍተኛ የቫይረሱ ስርጭት በደብርብርሃን እንዳለ ዘገባው አስነብቧል፡፡

የሠላም ጓድ በጎፈቃደኞች የሆኑት ኤሪን ፖርቲሎና ባለቤቷ ቶኒ የትውልድህን አድን ድርጅት መስራቾች ከሆኑት ከአድማሱ ወንዳፍራሽና ዳንኤል በቀለ ጋር በመሆን በዛንጅራ ያለውን ሁኔታ ለማሻሻል የሠሩት ሥራ አለ፡፡ የሩጫ ባህል ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ ለማሳየት እ.ኤ.አ. በታህሳስ 2012 በኦሎምፒክ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ልዑካን ሲሳተፉ ህዝቡ በየካፌውና በየመጠጥ ቤቱ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ መከታተሉ ተዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች የሰሯቸው ሆቴሎችና ህንጻዎች የአገሪቱ ከተሞች ድምቀት መሆናቸውን ዘገባው አስነበብቦ ሲያበቃ ደብረብርሃንም የዚህ ዕድል ተቋዳሽ መሆኗን አልሸሸገም፡፡ ጽሑፉ ሩጫ ለገጠር ሴቶች ልጆች ነፃነትን እንደሚያጎናጽፍ አትቶ ይህን እውን ለማድረግ ያለመውን ውጥን ያስተዋውቃል፡፡ ይህም የመሮጫ መም ነው፡፡ መሙ በትምህርት ቤቱ የእግርኳስ ሜዳ ዙሪያ የተሰራ ሲሆን፤ ለውስብስብ ችግሮቹ የመፍትሔ አካል ተደርጎ ተወስዷል፡፡ የተደራጁ ስፖርታዊ እቅስቃሴዎች በራስ መተማመንንና ዕድገትን እንደሚያመጡ፣ በሴቶችም ላይ የውሳኔ ሰጪነትን እንደሚጎለብቱ የሚያሳዩ ጥናቶችን ጠቅሶ፤ ስፖርት የሴቶች ልጆችን የመማር ዕድል እንደሚያሰፋ አስገንዝቧል፡፡ የድህንትን አዙሪት በጣጥሶ አዲስ ዕድልን የሚከፍት ለተባለለት ለዚህ ስራ በጎፈቃደኞቹ በሠላም ጓድ ድረገጽና በአሜሪካ ይኖሩበት በነበረው በላ ክሩ የገቢ ማሰባሰቢያ በማደራጀት፣ ትምህርት ቤቱ ቦታ በመስጠትና ስራ ተቋራጭ በመፈለግ እንዲሁም የጉልበት ተሳትፎ በማስተባበር ተረባርበውበታል፡፡ ‹‹የሠላም ጓድ ነገረስራው ትስስርን መፍጠሪያ ነው፡፡ ያሳደገኝን ማኅበረሰብ ከተቀበለኝ ማኅበረሰብ ጋር ለማስተሳሰር እፈልጋለሁ›› በሚለው የቶኒ ጥቅስ ዘገባው ይጠናቀቃል፡፡

በዚህ ዘገባ የተጠቀሰው መምህር ዳንኤል በቀለ በፊት በዛንጅራ ትምህርት ቤት የአውነት ማጎልመሻ መምህር ነበር፡፡ ከሰባት ዓመታት በፊት ወደ ጠባሴ መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት፣ ደብረ ብርሃን፣ የሠላም ጓዶችን ለማግኘት ስሄድ

በትምህርት ቤቱ አገኘው ስለነበር እንተዋወቃለን፡፡ በዚህ ዓመት 2014 ዓ.ም. ሚያዝያ 26 ቀን ወደምሰራበት ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሚከታተለውን የክረምት የዲግሪ ፕሮግራም አስመልክቶ መጥቶ ሳገኘው ‹‹እባክህ ዛንጅራ ሄደን የመሮጫ መሙን እይልን፡፡ እድሳትም እናድርግለት፣ ለሠላም ጓዶቹን እንጻፍላቸው፡፡ ከዘያም ለሌሎች ትምህርት ቤቶችና የስፖርት ማዘውተሪያዎች አርአያ ይሆን ዘንድ ፎቶውን አንስተን፣ የአሰራር ሂደቱን ዘርዝረን ጽፈን እናስተዋውቅ›› አለኝ፡፡ 

እኔም በዚህ ሃሳብ ተስማምቼ ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ዛንጅራ ሌላ ዮናስ ጋሻው የተባለ ወጣት ይዘን ሄድን፡፡ በባጃጅ 100 ብር ኮንትራክ ከፍለን ሄደን የተወሰኑ መቶ ሜትሮችን በእግራችን ሄደናል፡፡ ደብረብርሃንና ዛንጅራ አዲስ እየተሰሩ ባሉ የደብረ ብርሃን ማስፋፊያ መንደሮች ምክንያት እየገጠሙ ነው፡፡ እዚያም ደርሰን በትምህርት ቤቱ የእግርኳስ ሜዳ ዙሪያ የተሰራውን መም አየነው፡፡ ስለ አሰራር ሂደቱም መምህር ዳንኤል አስረዳን፡፡ የመሮጫ ትራኩ በበሬ ታርሶ፣ በህብረተሰብ ተሳትፎ ተቆፍሮ የተሰራ ሲሆን፤ በተሰበሰበው ገንዘብ ከደብረዘይት ቀይ አሸዋ መጥቶ ተደልድሏል፡፡ አሁንም አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም እድሳትና ክትትል ያስፈልገዋል፡፡ የመሮጫ መሙ ያለበትን ቦታ ትምህርት ቤቱ ለገበሬዎች ለእርሻ ማሳነት አከራይቶ እንደነበር ዳንኤል ነግሮናል፡፡ ይህንን ዕጣ የሚጋራ ሌላ በትምህርት ቤቱ ግቢ ያለ ሰፊ ሜዳ ማሳ ሆኖ አይተናል፡፡ ያም ለስፖርት ማዘውተሪያነት ጥቅም ላይ መዋል ያለበት ይመስላል፡፡ ዳንኤል ከአስር ዓመታት በኋላ ይህን ቦታ ማየቱ በስራው የተደሰተ ሲሆን የበለጠ መሰራት እንዳለበት ነግሮናል፡፡ በትምህርት ቤቱ ግቢ የአትክልት ስፍራ በማዘጋጀት አሜሪካውያኑ ከሯጭ ተማሪዎች ጋር ያለሙ እንደነበርና አትክልቱንም ይመግቧቸው እንደነበር የፎቶ ማስረጃ ጭምር በማሳየት አስታውሶናል፡፡ ‹‹እኔም የሠላም ጓድ ነኝ!›› የሚለው ዳንኤል ህብረተሰቡን በአትሌቲክስ የመለወጥ ህልሙ አሁንም አለ፡፡

ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ጠባሴ መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ለተመሳሳይ ጉብኝነት ሄደን የሌላኛዋን አሜሪካዊት የዲሻንቴል ሲንግልተንን የትምህርት ፕሮጀክቶች ቀጣይነት ሁኔታ ስንጎበኝና ምንም የቀጠለ ነገር አለመኖሩንና የሰራችው ሁሉ ደብዛው መጥፋቱን አይተን ስንናደድ ያጽናናን የዳንኤል የዛንጅራ ፎቶዎችና የሰን ኒውስ ጋዜጣ ገጾች ናቸው፡፡

የዛንጅራውን የስፖርት ማዘውተሪያ ጉዳይ ለሌላ ቀን እናስቀምጠዋለን፡፡ በደብረብርሃን የዉጪ ፕሮጀክቶች ፍጻሜ የማያኙበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ በደብረብርሃን የፈረንሳይ እህትማማች ከተማ በብሉምኒል እገዛ ደረጃውን የጠበቀ የዉኃ ልማት መሰራቱ ይወሳል፡፡ ያም በሰን ኒውስ ዘገባ የተጠቀሰው ዉኃ ነው፡፡ የስቴድየም ግንባታም ታቅዶ እንዲቀር ተድጓል፡፡ በጠባሴ መድኃኔዓለም ትምህርት ቤትም ፈረንሳዮች ያሰሯቸው ደረጃቸውን የጠበቁ የመጸዳጃ ቤት ህንጻዎች አገልግሎት ሳይሰጡ እንደቆሙ ናቸው፡፡

ግለሰቦች፣ ባለሙያዎች፣ የተማርን ሰዎች ሙያችንን፣ ዕውቀታችንን፣ ጊዜያችንን፣ ክህሎታችንን የምንጠቀምበትን መንገድ ፈልገን ድህነትን ለመዋጋትና ፈጠራን ለማሳደግ መስራት ይኖርብናል፡፡ ይህ ሁሉ የአሜሪካ የሠላም ጓዶች ሥራዎችን የመጎብኘት ተግባር በልዩ ልዩ የአማራ ክልል ከተሞች ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም የአሜሪካ የሠላም ጓዶች የሠሯቸውን ሥራዎች የአሰራር ሁኔታ ለመገምገም፣ የቀጠለ ካለ ለማየት እና ያንን አይተን የሚቀጥልበትን ሁኔታ ለመፈለግ ነው፡፡ ይህ አንዱ መንገድ ሲሆን፤ በደብረብርሃን፣ በዛንጅራ፣ በመሐልሜዳ፣ በመንዲዳ፣ በደብረሲናና በሣሢት ያለውን ሁኔታ ስንችል እየተዟዟርን ጎብኝተናል፤ ሳንችል እዚያው ባሉ በጎፈቃደኞች አማካይነት እንዲታዩ አድርገናል፡፡ ከዚያም ትምህርት እየወሰድን ነው፡፡ ማናቸውንም ከሠላም ጓዶች ጋር የሠሩ ሰዎችን እያገኘን እያነጋገርን ነው፡፡ በዚህ ብቻ ሳናበቃ፣ ከአሜሪካ የሠላም ጓድ ድረገጽ የአፈጻጸምና የሥልጠናን ጨምሮ ሌሎችን በመቶዎች ገጾች የሚቆጠሩ ሰነዶችን እየመረመርን ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ‹‹የአማራ የሠላም ጓድ›› ተወለደ፡፡ የአማራ የሠላም ጓድ የአሜሪካውን እንደ አስፈላጊነቱ የሚከተል ሲሆን ለኛ አውድ አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን ማሻሻያዎች አድርጓል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-

እርዳታ አንቀበልም፡፡ በጎፈቃደኞቻችን ባሉበት ይሰራሉ እንጂ ወደ ሌሎች ቦታዎች አይንቀሳቀሱም፤ ባይሆን በአገር ውስጥ ከአማራ ክልል ዉጪ ካሉ የክልሉ ተወላጆችና የቀድሞ ነዋሪዎች እንዲሁም በዉጪ አገር ከሚኖሩ ዜጎቻችን ጋር ኢንተርኔትን በመጠቀም በትብብር ይሰራሉ፡፡ በመደበኛ መዋቅር አንመዘገብም፡፡

የአማራ የሠላም ጓድ ከግንቦት ጀምሮ ከላይ የተጠቀሱትን እንቅስቃሴዎች እያካሄደ ሲሆን፤ በጠባሴ መድኃኔዓለም ዲሻንቴል ሰርታቸው ከነበሩት ስራዎች አንዱን በመሐል ሜዳ የነበረው ማይክ ከሰራው ጋር በማቀናጀት ተግብረናል፡፡ ይኸውም ከጠበሴ መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ከየክፍሉ በእንግሊዝኛ ዝቅተኛ ውጤት ያመጡትን አምስት ልጆች በድምሩ 44 ተማሪዎች መልምለን ለ16 ክፍለጊዜያት መሰረታዊ አንግሊዝኛ ምግብ እየመገብን ማስተማራችን ይጠቀሳል፡፡ የተማሩትን የሚያነቃቃ የአራት ክፍለጊዜያት ትምህርት በመስከረም ወር ይወስዳሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ልዩ ልዩ የሠላም ጓዳችንን ሰነዶች በማዘጋጀት እያሰራጨን ህብረተሰቡ እንዲውቀንና አንብቦ ሕይወቱን የሚለውጡ ስራዎችን እንዲሰራ እያደረግን ነው፡፡ አመራር ለመምረጥ፣ አባላትን ለመመልመልና ለማሰልጠንና ራሳችንን ለማጠናከር ከሐምሌ 25 እስከ ጥር 25 ባለው ጊዜ በአመዛኙ በኦንላይን እየሰራን ነው፡፡   

ለበለጠ መረጃ ‹‹CorpsAmhara የአማራ የሠላም ጓድ›› ብለው በፌስቡክና በቴሌግራም ይቀላቀሉን፡፡ ኢሜል mezemirgirma@gmail.com         

 

 










በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...