ረቡዕ 27 ሜይ 2026

የጅማ ከተማ ቆይታዬ

 




 

 የጅማ ከተማ ቆይታዬ

የመጨረሻው ረቂቅ

መዘምር ግርማ
ግንቦት 21 2018 ..

በደብረብርሃን ከተማ ከማይታወቁ አካላት በስልክ በሚደርሱኝ ማስፈራሪያዎች ምክንያት ባለኝ ገንዘብ ሁሉ የፍርሃት ግዢ (panic shopping) በማድረግ ላይ ሳለሁ ለአንድ ማህበራዊ ጉዳይ ወደ ጅማ ከተማ መሄድ እንዳለብኝ ከቤተሰብ ተደወለልኝ። "እንኳን እናቴ ሞታ እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ይለኛል" እንዲሉ ተነስቼ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ አቀናሁ። እስከ 26 ዓመቴ ድረስ ከአዲስ አበባ 200 .. ሬዲየስ ርቄ ተጉዤ የማላውቅ ቢሆንም ከዚያ ጊዜ በኋላ የጉዞ ዕድሎችን አግኝቻለሁ። የአገሬን ሁሉንም ክልሎች ብጎበኝ ብዬ እመኛለሁ። የአፍሪካንም ሁሉንም አገሮች እንዲሁ።

ወደ ጅማ ለመሄድ ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባ ስናቀና አሰልቺ ፈተሻዎችን እያለፍን ነበር። አዲስ አበባ ከመሸ ደርሰን ዘነበወርቅ በሚገኘው አዲስ የጅማ በር መናኸሪያ አካባቢ አደርን። ሰባት ነን። በማግስቱ ተነስተን ዓለምገና፣ ሰበታ እያልን ጉዞ ቀጠልን፡፡ ከአዲስ አበባ ወጣ ስንል ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባ ስንገባ እንዳየነው ሁሉ "Building the future city" ማለትም "የወደፊቷን ከተማ በመገንባት ላይ" የሚል ጽሑፍ በየቦታው አይተናል። የሸገር ከተማ መሆኑ ነው። ማስታወቂያዎች ከላይ በአፋን ኦሮሞ ከታች በአማርኛ መሆናቸው በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ይባል የነበረውና አሁን ሸገር ከተማ የሆነው ክልል ውስጥ መሆናችንን ያሳያል። ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እስክንገባ ድረስ እንደዚያው ነው። ጉራጌኛ በሚነገርበት በዚህ ስፍራ ግን ነገሩ ሌላ ነው። ማስታወቂያዎች በአማርኛ ናቸው። ይህን ምልክት ስናይ ወልቂጤ ደረስን ማለት ነው። ወልቂጤ ደማቅ ከተማ ስትሆን መንገደኞችን ለማስተናገድ ተፍ ተፍ የሚሉ የስራ ሰዎች አሏት፡፡ በጉራጌ አገር የስራ ባህል ምን እንደሚመስል ለማጥናትና የዚያን ልምድ ወደ ሰሜን ሸዋ ለማምጣት ሃሳብ የነበረው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ መምህር ወዳጄ ትዝ አለኝ፡፡

ወልቂጤ ላይ ምሳ በልተን መንገዳችንን ስንቀጥል ልምላሜው እየጨመረ ይሄዳል። ጊቤ በረሃ እንደ ስሙ ሞቃት ቢሆንም ደኑና ልምላሜው ግን ልዩ ነው። መኪናችን ጎማው በመፈንዳቱ በዚሁ ክልል ሳጃ ከተማ ቆመን አሰራን። የየም ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ሳጃ በአዲስ አበባ ካሉት ሐውልቶች የበለጠ ጥበባዊ ገጽታዎች የሚንፀባረቁበት የመሰለኝ ሐውልት አሰርታለች። የሰዎች ሐውልቶች ሲሆኑ የኒያላ ቀንድ የተሸከመና ጦርና ጋሻ የያዘው በይበልጥ አሁን ትዝ ይሉኛል። የሰባተኛና የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎችን ጎሚስታ አጠገብ አግኝቼ ስለ ትምህርት ስጠይቃቸው ትምህርት በየምሳ ቋንቋ መሆኑን ነገሩኝ። የምሳ ለማይገባቸው በአማርኛም እንደሚያስረዱ ነገሩኝ።

ግራና ቀኝ በአገር በቀል ዛፍ ጫካዎች ታጅበን ከመሸ ወደ ጅማ ስንጠጋ በአዲስ አበባ ያለው የከተማ ማስዋብ እዚያም ቀጥሎ አገኘነው። ሰፋፊ የመኪና መንገዶች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ ትልልቅ የመንገድ ዳር መብራቶች፣ በየቦታው የተሳሉ ስዕሎች ወዘተ እዚያም አሉ። በምሽትም የጎዳና ዳር ልማት ግንባታው ተጧጡፏል። የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ፖስተሮች በየቦታው ተሰቅለዋል። እንደ ወልቂጤው የፓርቲው ማስታወቂያ ግን በየንግድ ድርጅቶቹ የታተሙ መሆናቸው አልተጻፈባቸውም። ወልቂጤ "ብልፅግና ፓርቲን ይምረጡ፤  ሀለመ ሆቴል፣ ረሰሸ ቡቲክ፣ እንትን ሸቀጣሸቀጥ ወዘተ" የሚል የለበትም። በምሽት በባጃጅና በቤተሰብ መኪና ወደ ቤት ሄድን፡፡ ድባቡ የአንድ የአውሮፓ፣ እስያ ወይም አሜሪካ ከተማ ይመስላል፡፡

በቀጣዩ ቀን ከመካነየሱስ ሰፈር ፈረንጅ አራዳ ወደተባለው ቦታ ለመሄድ ቦታው ስለጠፋኝ የጠየቅሁት ባለ ባጃጅ የወሰደኝ 100 ብር ሲሆን ርቀቱ 100 ሜትር ብዙም አይርቅም ነበር። አዞሮ ሲያወርደኝ ነበር ቅርበሩ የገባኝ፡፡ ታማኝነትን ብዙዎች ጋ ላናገኘው እንችላለን፡፡ ይህ ባለ ባጃጅም እኔ እንግዳ ከደብረብርሃን የመጣሁ መሆኔን ሲረዳ ፖለቲካ ሊያነሳ ሞክሮ ነበር፡፡ እኔም እሱ ያነሳው የብሔር ፖለቲካ ጦስ ከነጭራሹ እስካልተወገደ ድረስ እከሌ እከሊት አጠፉ፣ ተጠቀሙ ማለቱ እንደማይጠቅም ነግሬው ከዚያ በኋላ አላስቀጠልኩትም፡፡ 

ጅማ መግቢያ ላይ የነበረችው በፎቶ የምናውቃት የጀበና ሐውልት በመንገድ ልማቱ ምክንያት ፈርሳለች አሉ። የፈረንጅ አራዳው አዲሱ የስኒ ሐውልት ቡናን ለማስታወስ የተሠራ ይመስላል። በፏፏቴ ተከቧል፡፡ ወጣት ፎቶ አንሺዎች ፎቶ ተነሱ እያሉ ይወተውታሉ፡፡ ከሱ አጠገብ የተሰራው የአባ ገዳ ምርኩዝ ያለው ሐውልት በዙሪያው የአባ ጅፋር ሐውልቶች ተሰርተውበታል። ከአሁን በፊት በዚያ ቦታ የአንበሳ ሐውልቶች እንደነበሩ ተነግሮኛል። የከተማውን ድምቀት ጅማ ዩኒቨርስቲን ከዉጪ አይቼዋለሁ።

የጅማ ቤተመንግሥት ከአፄ ኃይለሥላሴ ጀምሮ መሪዎች ሲመጡ የሚያርፉበት መሆኑን ተረድቻለሁ። ዙሪያውን ጎብኝቼዋለሁ። በሚድሮክ ኢትዮጵያ እየታደሰ ነው። የስብሰባ አዳራሽን ጨምሮ ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች አሉት፡፡ እንደ ሌሎች የጅማ ህንጻዎች ነጭ ቀለም ተቀብቷል፡፡

ቤተመንግሥቱን ስጎበኝ መረጃ የጠየኳቸው አንድ መንገደኛ አዛውንት ስለ ቤተመንግሥቱና ስለ ሕይወታቸው አስረዱኝ። ሕይወት በጅማ ምን እንደሚመስል ጠየኳቸው። ከተማው እያማረ መሄዱን፣ በአንፃሩ ለመንገድና ለልማቱ ስራ ግን ሰው መፈናቀሉን ገለፁልኝ። ኑሮ መወደዱን አንድ ፈረሱላ ጤፍ የገዙበትን ዋጋ እየነገሩኝ በሂሳብ ማሽን ሳሰላው አንድ ኪሎ 158 ብር መሆኑን ተረዳሁ። በመስሪያ ቤቶች አማርኛ የሚናገርና ይህችን ማተብ ያሰረ በአግባቡ አይስተናገድም ብለውኛል። ይህም ማንነትንና ኃይማኖትን መሠረት አድርጎ የሚያገል አሰራር መኖሩን ያመለክታል። ቢስተካከል ጥሩ ነው ባይ ነኝ። የጅማውን አውሮፕላን ማረፊያ ከሩቅ አሳይተውኝ ተለያየን፡፡

ለማህበራዊ ጉዳይ ሄዶ ጉብኝት ማሰብ እንደ ቅንጦት ቢታይም እንደምንም ብዬ አንድ ቦታ አይቼ ልመለስ ብዬ ስለ አባ ጅፋር ቤተመንግሥት ጠይቄ ለመጎብኘት አሰብኩ። በእድሳት ላይ መሆኑንና እድሳቱ ወደ ማለቂያው መሆኑን አንድ ሰው አስረዱኝ። አልቆ ተመርቋል ያሉኝም ነበሩ። ቦታውን ግን ተራራ ላይ እንደሆነ ጠቁመውኝ ማዶ ለማዶ ከሩቅ አይቼዋለሁ። ወደፊት ማየት ያለብኝ ቦታ መሆኑን ተረድቻለሁ። የአባ ጅፋርን ታሪክ ጠለቅ ብሎ ማወቅ ያስፈልጋል። በትምህርት ቤት ስንማር የቆየነውን የአምስቱን የጊቤ ንጉሣዊ ግዛቶችንም እንዲሁ።

አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትንም ጎብኝቻለሁ። ትምህርት በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ይሰጥበታል።

በልምላሜዋ ማስደመሟን የማታቆመው ጅማ ሞቃትም ነች። ከደብረብርሃን ፍፁም ተቃራኒ መሆኗ ነው። የጫት ተጠቃሚው በርከት ይላል። ቡና በብዛት ይጠጣል። ሰዉ ተግባቢ ነው። ስንሄድ የፍተሻ እንግልት ፈጽሞ አልነበረም። ለዚህም አብረውኝ የተጓዙት ወገኖቼ አድናቆታቸውን ገልፀዋል። አሁን በመንገዳችን ላይም ሆነ በየከተሞቹ ያየነውን ዓይነት የእንግዳ መስተንግዶ ለወደፊቱም ይቆይልን። የኑሮውን መወደድና ጥሩ ጤፍ ያለመኖሩን ሁኔታ የተመለከቱ ዘመዶቼ መሬቱ በደንብ ቢታረስና ጤፉም ቢታረም የሚል ሃሳብ አንስተዋል፡፡ ልክ ይሆናል፡፡ ወደፊት ከዚያ ደረጃ መድረሳችንና የኑሮ ሁኔታ መሻሻሉ አይቀርም ባይ ነኝ፡፡

በአንዳንድ ሱቆች ትልልቅ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ፎቶዎች መስቀላቸውን ሳይ የናይሮቢ ጉዞዬን አስታወሱኝ። በኬኒያ እያንዳንዱ የቢዝነስ ተቋም የወቅቱን ፕሬዚዳንት ፎቶ መስቀል ይጠበቅበታል። ምናልባት ጅማ ላይ ይህ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአካባቢው ተወላጅ በመሆናቸው ይሆን? እንደዚህ እንዳልል የፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ፎቶዎችም አልፎ አልፎ ይታያሉ። ካገኘኋቸው ሰዎች ከፊሉ ስለ ጅማ ውበት መጨመርና አዲስ አበባን መምሰል ያወራሉ። ምናልባት ይህ ሐሳብ በኛ በእንግዶቹም ዘንድ ይኖራል። የቀደመው የሕወሃት ስርዓት የነፍጠኛ ከተሞች ብሎ ካዳከማቸው አንዷ እንደነበረች የሚወራላት ጅማ አሁን ቀን ወጥቶላት ይሆን?

ከሌሎች የአገሪቱ ወይም የክልሉ (ኦሮሚያ) አካባቢዎች በተለየ ጅማ ሰላማዊ ትመስላለች። በብሔር ፖለቲካ በተከፋፈለች አገር ብኖርም የጅማ ልምላሜና የወገኖቻችን ልባዊ መስተንግዶ አሁንም በኢትዮጵያ ያለኝን መተማመን አድሶልኛል። ጅማን አልፌ አጋሮን ወይም ሊሙን ለመጎብኘትና በአውሮፕላን ለመመለስ አስቤ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረገጽ ከጅማ ወደ አዲስ አበባ መሳፈሪያ ክፍያ 18,500 ብር ማለቱን ማየቴ ሃሳቤን አስቀይሮኛል። አፈላለጌም one way ወይም ለመመለስ ብቻ እንጂ ደርሶመልስ አልነበረም። በዚህ የተጋነነ ዋጋ ወይም ስህተት ምክንያት ከጅማ በአውቶቡስ ተመለስኩ። ሌሎችን ስጠይቅ 7,000 መሆኑን ይነግሩኛል። አንዳንዶቹ እርግጠኛ አለመሆናቸውንና ምናልባት ለኢድ በዓል ጨምሮ ከሆነ እንደማያውቁ ገምተዋል።  

ከዓመታት በፊት አፋን ኦሮሞ በፊት እየተማርኩ የነበረ ቢሆንም አሁን አብዛኛውን ረስቼዋለሁ። በቃላት ደረጃ ግን ሲነጋገሩ ይሰማኛል። ጅማ ሁለቱንም ቋንቋዎች በመንገድ ላይ መስማት የተለመደ ነው። ወደ ጅማ ንሄድ ስንነሳ ከኋላ ወንበር እያንዳንቸውለአራት ሰዎች ቦታ እይዛለሁ ያሉ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ተጣልተው ሲሰዳደቡ አይተናል። የጠቡም ምክንያት ወንበሩ ስድስት እንጂ ስምንት ሰዎችን ስለማይዝ እኔ ይዣለሁ፣ እኔ ይዣለሁ የሚል ነበር። በኦሮምኛም በአማርኛም ይሰዳደቡ ነበር። በኋላ ረዳቱ አስማማቸውና ትርፎቹ ቆመው ሄዱ። ይህ ፀብ በሁለት የተለያዩ ቋንቋዎች ተናጋሪዎች መካከል ቢሆንስ ብዬ አሰብኩ። ስንሄድም ስንመጣም አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ሙስሊሞች ነበሩ። የኢድ ሰሞን በመሆኑ ይሆን ሙስሊሞች በአካባቢው በመብዛታቸው?

ሌላ ነጥብ ላንሳ። አንዲት በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ያለች ግለሰብ ለችኝ ነው። ትውልዷ የአማራና የኦሮሞ ነው። ከምርቃት በኋላ ተሾማ እንደነበር ነገረችኝ። ቢሮዋ የሚገቡ ሰዎች ስሟን ያያሉ። ከሷ እስከ አያቷ የአማርኛ መሆኑን አይተው እንዴት ትሾማለች ማለታቸውንና ኃላፊነቱን መልቀቋን አስረዳችኝ። ይህች ሰው አማርኛንም በኦሮምኛ ቅላፄ ስለምትናገር ከኦሮሚያ ዉጪስ ለመስራት ትችላለች? በቅንነት መልሱልኝ። ኢትዮጵያዊነት ብዙ ፈተና አለበት። 

በጉዞው አብረውኝ ስለተሳተፉት ከገጠር የመጡ ወዳጆቼም አንዳንድ ምልከታዎች አሉኝ፡፡ የትውልድ አካባቢያችን የጦርነት ቀጣና ሆኖ ዓመታትን እያሳለፈ ስለሆነ ስለተከሰተው ሁሉ ያስረዱኛል፡፡ እነሱ በዚህ ጉዞ ለመሳተፍ በድንገት እንደተጠሩ ጦርነት ስለነበር በዕለቱ ሳይችሉ ቀርተው በማግስቱ ስለበረደ ነበር የመጡት፡፡ ማን የሞተ ቀን ምን እንደሆነ፣ በየትኛው ጦርነት የከባድ መሳሪያው ድምጽ ሽብር እንደተፈጠረ፣ በሁሉም ቤተክርስቲየኖች መቀበሪያ ቦታ እንዳለቀ፣ ከሟቹ መብዛት የተነሳ ፍትሃት ሳይደረግ የሚቀበረው እንደሚበዛ ወዘተ ነግረውኛል፡፡ አንዷ አክስቴ ስንመለስ አብራኝ ስለተቀመጠች ብዙ አውግታኛለች፡፡ ትምህርቷን በልጅነቷ ከስድስተኛ ክፍል እንዳቋረጠች አስታውሳኛለች፡፡ ከንግግሯ የአገላለጽ ብቃት እንዳላት ገብቶኛል፡፡ ያመነችበትን መናገሯም እንዲሁ አስገራሚ ነው፡፡ በስብሰባዎች ላየ ማን ምን እንዳለ በትክክል ታስታውሳለች፡፡ ሌሊት 9፡30 ከጅማ ልንነሳ ስንል ትልቋ አክስታችን በመቁጠሪያ ስትቆጥር እሷ ውዳሴ ማርያም ትደግም ነበር፡፡ ኃይማኖትና አስተዳደርን ያጣመረ ትረካ አቅርባልኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለውን ፖለቲካ የምትተነትነው ከኃይማኖቷና በቤተክርስቲያን ሰባኪዎች ካሉት በመነሳት ነው፡፡ በሁለቱም ወገን የሚዋጋው ብሔሩ ምንም ይሁን ምን፣ ከማንም ይወግን ከማን የእግዚአብሔር ፍጡር መሆኑን አስታውሳ እነሱን መግደል ደግሞ ኃፂአታቸው ወደ ገዳዩ እንደሚተላለፍ ማመኗን ነግራኛለች፡፡ ይህን መሟገቻ ስታቀርብም ሟቾቹ ባይገደሉ ኖሮ ምናልባት ንስሃ ሊገቡና ከሃፂአታቸው ሊነፁ ይችሉ እንደነበር በማንሳት ነው፡፡

በሊሙ ከተማ በደርግ ጊዜ ሲማር አንድ የሚያውቃቸው ጎረቤቱ የሆኑ ኦሮሞ እናት የነጥላሁን ገሠሠ የኦሮምኛ ሙዚቃ ሲከፈት ያለቅሱ እንደነበር የነገረኝም አለ፡፡

በጉዞው ወጣቶችም ሆኑ አዛውንቶቹ ዘመዶቼ ሁሉም የየራሳቸውን ዕይታ ሲያንፀባርቁ አይቻለሁ፡፡ ሰላም ሰፍኖ ሰው ወጥቶ የሚገባበት ጊዜ እንዲመጣ እመኛለሁ፡፡   

 

የጅማ ከተማ ቆይታዬ

  ‎ ‎     የጅማ ከተማ ቆይታዬ የመጨረሻው ረቂቅ ‎ መዘምር ግርማ ‎ ግንቦት 21 ፣ 2018 ዓ . ም . ‎ ‎ በደብረብርሃን ከተማ ከማይታወቁ አካላት በስልክ በሚደርሱኝ ማስፈራሪያዎች...