2019 ጁላይ 9, ማክሰኞ

ታላቁ ጥቁር


የመጽሐፍ ዳሠሣ
የመጽሐፉ ርዕስ - ታላቁ ጥቁር፣ ኢትዮ አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ
የገጽ ብዛት - 473 ዋጋ - 225 ብር
ደራሲ - ንጉሤ አየለ ተካ፤
ዳሠሣ አቅራቢ - መዘምር ግርማ mezemir@yahoo.com

መንደርደሪያ
.. 1903 በኢትዮጵያና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል የንግድና የዲፕሎማሲ ወዳጅነት ለመመስረት ሮበርት ስኪነር የተባለ መልዕክተኛ ከፕሬዚዳንት ቲዮዶር ሩዝቬልት ወደ ዐፄ ምኒልክ የተላከ ቡድንን መርቶ ነበር፡፡ የዚህ የአሜሪካ መንግሥት የመጀመሪያ መልዕክተኛ ቡድን ዓላማ በሚገባ አልታወቀም ብለው የሚያምኑት ደራሲ ንጉሤ አየለ በአሜሪካ ሙዚየሞችና አብያተ-መጻሕፍት ያላሰለሰ የመረጃ ፍለጋና ምርምር አድርገው በሁለቱ አገራት መካከል የነበረውን ግንኙነት ሁኔታ አስገንዝበዋል፡፡ በተፈጥሯዊ አቀማመጣቸው ምንም የማይገናኙትን አገራት ለማስተሳሰር የተፈለገበት አንዱ አነሳሽ ምክንያት የኢትዮጵያ ቡና በሦስተኛ ወገን በኩል ወደ አሜሪካ መቅረቡና የአሜሪካ ካኪ ጨርቅ በኢትዮጵያ ገበያ የሌሎች አገራት ዜጎች በሆኑ ነጋዴዎች በትርፍ መሸጡ ነበር፡፡ የወቅቱ የምዕራባውያን ጽሑፎች የአጼ ምኒልክን ታላቅነት ስለሚመሰክሩና ከጥቁሮች ሁሉ በበላይነት ስለሚያስቀምጧቸው ታላቁ ጥቁር የሚለው ስያሜ ለመጽሐፉ እንደተመረጠ ተገልጧል፡፡ 
ቀደም ብሎ ፓልመር የተባሉ አሜሪካዊ የሃገራቸውን የተወካዮች ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ይኖረው ዘንድ ጠይቀው ነበር፡፡ ዐፄ ዮሐንስ አራተኛም የግብጽና የቀይ ባሕር ጉዳይ ስላሳሰባቸው ስምምነት ፍለጋ ወደ አሜሪካ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ዐፄ ዮሐንስን ካሳሰቧቸው ጉዳዮች አንዱ በአሜሪካን የእርስ በርስ ጦርነቶች የተሳተፉ ቅጥረኛ ወታደራዊ አዛዦች በአሰልጣኝነትና በአዝማችነት ኢትዮጵያን ከግብጽ ወገን ሆነው መውጋታቸው ነው፡፡ 70 ዓመት ታሪክ የነበራት አሜሪካ 3000 ዘመን ካስቆጠረችው ከኢትዮጵያ ጋር የወዳጅነትና የቃልኪዳን ውል እንዲመሰርቱ ቀደም ብሎ እነዚህ ሃሳቦች ቢቀርቡም በትጋት የወተወተውና ጉዳዩንም ከግብ ያደረሰው አሜሪካዊ (ስኪነር) ምን ታይቶት ነበር ብሎ ለሚጠይቅ አንባቢ የዛሬ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ስፋት ምስክር ነው፡፡

የስኪነር መጓዝ ወሬ
ሮበርት ስኪነር ይፋዊ የአቻ ወዳጅነት ከኢትዮጵያ ጋር የመመስረትን አስፈላጊነት ደግሞ ሲያነሳ ከፈረንሣይ ማርሴ የአሜሪካ ቆንስልነቱ ጎን ለጎን የኢትዮጵያንም ጉዳይ ይመረምርና ፍላጎትም አድሮበት ስለነበር ነው፡፡ የወዳጅነት እንመስርት ተማጽኖው ለሦስት ጊዜያት ያህል በኮንግረስ ውድቅ ስለተደረገበት ጥረቱ ረጅም ጊዜ ወስዷል፡፡ ከሩዝቬልት በፊት የነበሩት የፕሬዚዳንት ማኪንሊ የልብ ወዳጅ፣ የምርጫ ዘመቻ አጋር እና ተሿሚ የነበረው ስኪነር ለዕቅዱ መሳካት ይረዱት የነበሩት ሰው ከአጥቂዎች በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸው ለዕቅዱ ገቢራዊነት ጊዜ ወስዶበታል፡፡
ወጣም ወረደ ብዙ መሰናክሎችን አልፎ የማኪንሊ ምክትል በነበሩትና ኋላ ላይ በፕሬዚዳንትነት በተኳቸው በሩዝቬልት ፈቃድ ስኪነር ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ ማሰቡ የአውሮፓና አሜሪካን ጋዜጦችን በሰፊው አነገጋገረ፡፡ ለመሄድ ሲዘጋጅም ኢትዮጵያና አሜሪካ ይፈርሙት ዘንድ በአሜሪካ በኩል የተዘጋጀው ውል እንደ ውጫሌው ውል ሁሉ ውዝግብ እንዳይፈጥርና አመኔታ ይኖረው ዘንድ ወደ አማርኛ በጥንቃቄ መተርጎም ነበረበት፡፡ አማርኛ ቋንቋንና ግዕዝን በመጻሕፍት ብቻ በመታገዝ ችለው የነበሩት የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ኢኖ ሊትማን ውሉን በጥንቃቄ ተረጎሙት፡፡
‹‹የወዳጅነት፣ የሁለት ወገን ዲፕሎማሲያዊ ተቋማትን የማቋቋምና የንግድ ስምምነት›› የተባለው ውል የዱር እንስሳትንናእጽዋትን ዝርያ መለዋወጥን ጭምር የያዘ ነበር፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ አሜሪካንን እንዲጎበኙ የሴንት ሊዊስ ትርዒት መቶኛ ዓመት አከባበር ሁነኛ አጋጣሚ ሆኖ ስለተወሰደ ግብዣ እንዲደረግም ተወስኗል፡፡
የምኒልክ ጊዜና ከሱ ቀደም ብሎ ያለው ወቅትም ኢትዮጵያ በአሜሪካ ጋዜጦች ትነሳ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ በጋዜጦችም የተነሱትን ጉዳዮች መጽሐፉ ዳሷቸዋል፡፡ የዐፄ ቴዎድሮስና የእንግሊዞች እሰጥ አገባ፣ የዐፄ ዮሐንስና የራስ አሉላ ታሪክ፣ የዐፄ ምኒልክ የዓድዋ ድል ዋነኞቹ የወሬዎቹ ማጠንጠኛዎች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ የአድዋ ጦርነት ዝግጅት፣ አፈጻጸምና ድህረ ጦርነት ሂደት የምኒልክ ጥበብ አንዱ መገለጫ ነው፡፡
በስኪነር ጉዞ ያልተደሰተች አገር ብትኖር ፈረንሳይ ነበረች፡፡ በስኪነር ጉዞ ዝግጅት ወቅት ምኒልክና ጣይቱ አሜሪካንን ሊጎበኙ ነው የሚለው ዜና በአያሌው ተናፍሶ ነበር፡፡ የጣሊያን ጋዜጦችም ምኒልክ አይመጡም ሲሉ በሰፊው አሟርተዋል፡፡

አነጋጋሪው ጉዞ
ስኪነር ከአሜሪካ ማርሴ፣ ከማርሴ ቤሩት ደረሰ፡፡ ከዚያም ስለ ክብሩና ደህንነቱ የሚያጅበው ልዩ የአሜሪካ ጦር አስከተለ፡፡ ጅቡቲም ደርሶ ለኢትዮጵያ ጉዞው ዝግጅት ጀመረ፡፡ አቶ ዮሴፍ ገላን በጅቡቲ የምኒልክ ወኪል ተቀብለው ወልደሚካኤል የተባለ አስተርጓሚ እንዲቀጥር አደረጉት፡፡ በመጨረሻም አንበሳ በተባለው ባቡር ወደ ድሬደዋ ተጓዙ፡፡ ድሬዳዋም የምኒልክ አስተዳደር የተቆጣጠረው ክልል ለመሆኑ ግልጽ ምልክት እንደሰጠው ስኪነር ጽፏል፡፡ የቡድኑ አባላት ወደ ሐረር አውሮፓን የሚያውቁትን ራስ መኮንንን ለመጠየቅ ሄደው ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ አጼ ምኒልክም ከመናገሻ ከተማቸው በስልክ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል፡፡ በሐረር ስለነበሩ የውጪ ዜጎች ሁኔታና በስርቆት ወንጀል ስለተፈረደባቸው ሰዎች እጅና እግር መቆረጥ ጽፈዋል፡፡  ያን ጊዜ ሕጉ እንደዚያ ነበር፡፡  

ዊሊያም ኤሊስና አንድሩ ካርኒጌ
ከሰኪነር ሌላ በኢትዮጵያ ፍቅር የተነደፈ የምኒልክ እንግዳ ዊሊያም ኤሊስ ነበር፡፡ የመጣው ግን በሌላ የግሉ የጉዞ መርሐ-ግብር ነው፡፡ ከስኪነር ጋር የተገናኙት ኤሊስ አዲስ አበባን ጎብኝቶ ሲመለስ ነው፡፡ ምኒልክ ለኤሊስ አሜሪካ ፍላጎቷ የንግድ በመሆኑ ከሌላው ነጭ ዓለም እንደሚለያት ነግረውታል፡፡ ታዋቂውን አሜሪካዊ ባለሃብት አንድሩ ካርኒጌን ስለ ኢትዮጵያ እንዲያስቡ ያደረገው ኤሊስ ነው፡፡ ጥረቱ ከዳር ባይደርስም እኝህን ለጥቁሮች ተቆርቋሪ የነበሩ ባለሃብት ስለ ኢትዮጵያ ማስገንዘቡ ማለፊያ ነው፡፡
የመልዕክተኞቹአዲስ አበባ ትዝብት
ከድሬዳዋ በኋላ የእግር መንገዱ ለስኪነርና ለቡድኑ አድካሚና የጸጥታውም ሁኔታ አስቸጋሪ ነበር፡፡ 20 ቀን አዲስ አበባ ደረሱ፡፡ የቡድኑ አባል የሆነው ዶክተር ፒስ አዲስ አበባ በገቡ ጊዜ በነበረው የግብር አዳራሽ ዝግጅት ወቅት ‹‹በዓለም ላይ ታላቅና እጅግ ኃያል የሆኑት የጥቁር ገዥ ዳግማዊ ምኒልክ በዙፋኑ ላይ ተቀምጠዋል›› ይላል፡፡ በገባ ዕለት ምኒልክ ተቀብለው አነጋገሩት፡፡ ይህም ያኔ በዓለም ላይ የተለመደውን ለሣምንታት እንግዳ ማጉላላት ያስቀረ ተግባር ነበር፡፡ የምኒልክ ግብር 10 000 ሰዎችን ያስተናግዳል፡፡ እግረ መንገዱን ስኪነር የአውሮፓን አምባሳደሮች አናግሯል፡፡ በወቅቱ በአዲስ አበባ የነበሩ የአውሮፓ ሚስዮኖች ያላቸው ተልዕኮ ፖለቲካዊ ሚና መሆኑንም ስኪነር ታዝቧል፡፡ ሩሲያውያን ሐኪም ቤት ከፍተው በነጻ ያክማሉ፡፡ እንደ መልዕክተኛው ትዝብት በአዲስ አበባ የነበረው ማራኪ ሕንጻ የምኒልክ አዳራሽ ብቻ ነበር፡፡

ሁለት የምኒልክ ታማኝ የውጪ ዜጎች ስዊዙ ቢትወደድ ኢልግና ፈረንሳዊው ሸፍኔ ናቸው፡፡ ምኒልክ ካደረጉት ወግ ውስጥ ካነሷቸው ሃሳቦች ‹‹ለምን የአማርኛ ታይፕራይተር አይኖርም?›› የሚል ነበር፡፡ ይህን ስኪነር የእንግሊዝኛ ታይፕራይር ሲያበረክትላቸው ያሉት ነው፡፡ ለምንልክ ስጦታዎች ተበርክተዋል፡፡ በአዲስ አበባ እነስኪነር ባቋቋሙት ካምፕ ሩዝቬልት በተባለው ጊዜያዊ ሰፈር ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ግብዣ ተደርጓል፡፡ ኬኩን በሻምፓኝ ውስጥየነከሩ የተመገቡ መኳንንት ጉዳይ የምዕራባውያን ባህል በሃገራችን የነበረውን እንግድነት ያሳያል፡፡
የዝሆን ጥርስ፣ ጦር፣ ጎራዴና የአንበሳ ግልገሎች ከምኒልክ ለሩዝቬልት በስጦታ ተላኩ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነገር ቢኖር በአሁኑ ወቅት በማሲሊን ሙዚየም ለመታሰቢያነት የተቀመጠው ጎራዴ ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሀ ሀበ እግዚአብሔር›› የሚል ጽሑፍ አለበት፡፡ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ስለ ጎራዴው ስሪት (በዉጪ ተሰራ በሚል ስለተገለጸ) ለሙዚየሙ ማሳሰቢያና እርማት ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ቡድኑ ከታዘባቸው ነገሮ ስንጠቃቅስ አይሪሹሐበሻማኪልቪ እንግሊዝኛን ረስቶ ፈጽሞ ባላገር መስሎ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ግሪካዊው የአድዋ ዘማችሐበሻባላምባራስ ጊዮርጊስ የአዲስ አበባ ድምቀት ከሆኑ የውጭ ሰዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ሁለት መቶ የውጪ ዜጎች በነበሩባትና 12 ዕድሜ የነበራት የአዲስ አበባ ከተማ 50 000 የሃገሬው ነዋሪ ከትሞ ነበር፡፡ የአሜሪካ መርከቦችና የንግድ ተቋማት በኢትዮጵያ ያለመኖር እና ኢትዮጵያውያንን ወደ ውጪ ልኮ የማስተማር ጉዳይ ስኪነር ለምኒልክ ያነሳቸው ነበሩ፡፡ የሆነው ሆኖ፣ ውሉ በዐፄ ምኒልክ ተፈርሞ በአሜሪካ ሴኔትም መጽደቅ ነበረበት፡፡
የጥቁሮች ምስጢራዊ ማህበር
በሌላ ወገን የአሜሪካ ጋዜጦች ምኒልክ ይመጣሉ ብለው እየዘገቡ ነበር፡፡ ቤኔቶ ሲልቬይን ምኒልክን በወቅቱ የጎበኘ ጥቁር ነው፡፡ የሃይቲ ሪፑብሊክን ፕሬዚዳንት መልዕክት ለምኒልክ ያደረሰና የአንዳች ምስጢራዊ የፓን አፍሪካ ሰንሰለት አባል ነው ተብሎ የሚታሰብ ነው፡፡ የሃይቲው መሪ አሌክሲስና ዐፄ ምኒሊክ አንድ የጋራ ዕቅድ እንደሚኖራቸው ተጠርጥሯል፡፡
እነ ስኪነር የመልስ ጉዟቸውን ጀምረው አሌክሲስን መንገድ ላይ እንዴት እንዳገኙት የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ለተለያዩ ግምቶች ግን ክፍት የሆነ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ በነገራችን ላይ በጉዞ ላይ አንዱ የአምበሳ ደቦል ሞቷል፡፡ የቅፍለት ቡድኑም ተመልሶ ድሬዳዋ ደረሰ፡፡ አሜሪካውያኑም በቅፍለቱ ላገዟቸው ኢትዮጵያውያን ተቀጣሪዎቻቸው ክፍያቸውን ከፈሉ፡፡ ዕቃም አከፋፈሏቸው፡፡ ሐበሾቹ ባቡሩን ተከትለው በመሮጥ ልብ የሚነካም ስንብት አደረጉ፡፡
የተጓጓላት አገር
ኢትዮጵያ ጃፓን ናት ወይስ ኤልዶራዶ የሚል ሃሳብ በአሜሪካ ጋዜጦች መንሸራሸር ጀመረ፡፡ ሃገሪቱ የወርቅ ጉድጓዶች አሉባት የሚሉ ግምቶችም ተጻፉ፡፡ አገሪቱ ያልለማ የከርሠ-ምድር ሐብት እንዳላት ይታወቃል፡፡ ምኒልክ የማዕድን መፈለግና ማውጣት ፈቃድ ለተለያዩ አካላት በየቦታው ሰጥተዋል፡፡ ሪፖርቱ ለኮንግረስ ቀረበ፤ ጸደቀም፡፡ ስኪነር ከኢትዮጵያ የዛፍና የአዝዕርት ዘር ወስዷል፡፡ ይህንን ለሕዝብ ይፋ አላደረገም፡፡ ከምኒልክ የወሰደው ግን ፈቃዱን አግኝቶ ነበር፡፡ በአሜሪካ ተመልሶ ስኪነር ሪፖርቱን ለንግድና ግብርና መስሪያ ቤቶች አቀረበ፡፡ የቦስተን ሕዝብ እንስሳቱን ለማየት ጓጓ፡፡ አንድ አሜሪካዊ ባለስልጣን ከውጭ አገር መንግሥታት ሥጦታ መቀበል በሕግ ስለሚከለከል ሩዝቬልት አንበሳውን የህዝብ ንብረት ለሆነው ለፓርክ ለመስጠት ተገደዱ፡፡ በሩዝቬልት የተፈረመው የምኒልክ ውል ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ ተላከ፡፡ ቆንስል ስኪነርም ከማርሴ የኢትዮጵያን ጉዳይ ደርቦ እንዲሰራ ተደረገ፡፡ ደብዳቤውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያደርሱ ከተላኩት ሰዎች አንዱ የሆነው ሉሚስ አውሮፓ ላይ ተሰውሮ ሲፈለግ ቆይቶ ሞቶ ተገኘ፡፡ የአወዛጋቢው ሞት ምክንያት የሌሎች መንግሥታት ሴራ ይሁን ወይንስ አደጋ አልታወቀም፡፡ በሞቱ ጥርጣሬ ውስጥ የወደቀው ኤሊስ ግን መልዕክቱን ለምኒልክ አደረሰ፡፡ ‹‹ምኒልክ በምስራቁ ዓለም ያሉ አገር ገንቢ ናቸው›› ይላል ኤሊስ፡፡ ኤሊስም በተራው ለሩዝቬልት የእንስሳት ስጦታ ወሰደላቸው፡፡ ከእንስሳቱም ሁለቱ በመንገድ ላይ ሞቱ፡፡ ምኒልክም በጸጥታ ስጋት ወደ ንግድ ትርኢቱ ሳይሄዱ ቀሩ፡፡    
ማጠቃለያ
ታላቁ ጥቁር የሕትመት መገናኛ ብዙሃን ላይ የተደረገ ጥልቀት ያለው ምርምር ነው፡፡ ይህ ስራ የገጽ መብዛት ይታይበታል፡፡ በአንድ ጋዜጣ የተነሳው ጉዳይ ከሌላውም ይጠቀስና ተመሳሳይ ሃሳብ ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ይጻፋል፡፡ ወጣም ወረደ ኢትዮጵያ የዓለምን ትኩረት ትስብ የነበረች የተከበረች መንግሥት መሆኗንና መሪዋም ተደናቂና ተከባሪ መሆናቸውን ያስገነዝባል፡፡ እንዲያነቡት በመጋበዝ እንሰነባበት፡፡      

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...