2015 ኦገስት 29, ቅዳሜ

የንጉሱን እትብት ፍለጋ




የጉዞ ማስታወሻ  በመዘም ግርማ
ወደ ቤቴ ስሸሽ ብመታና ብሞት አስከሬኔን እዚያው ተውት፤ ከጠላት ጋር ግንባር ለግንባር ስፋለም ከሞትኩ ግን አጽሜ ወደ ትውልድ ስፍራዬ ይምጣ - ፊታውራሪ ገበየሁ
በደብረብርሃን ከተማ ጅሩ መንገድ የተገናኘንው አራት የዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች ባዶ እጃችንና ቁርስ ሳናደርግ በእግር የኮረኮንቹን ጉዞ ተያያዝንው - ሰኞ የካቲት 16፣ 2007 በጠዋት፡፡ የጉዟችን መዳረሻ አጼ ምንሊክ የተወለዱበትና የአድዋው ጀግና የፊታውራሪ ገበየሁ አጽም ያረፈበት አንጎለላ ኪዳነምህረት ነው፡፡ በእግራችን አንድ ሰዓት ገደማ የፈጀብን 10 ኪሎሜትር የሚሆነው መንገድ አስፋልት ቢሆን አይጠላም፡፡
በስፍራው እንደደረስን ሶስት ነጫጭ ፈረሶች አውድማ ላይ ገለባ ሲበሉ አይቼ ከጓደኞቼ ተለይቼ ሄጄ ፎቶ እያነሳሁ ከባለፈረሶቹ ጋር አወራለሁ፡፡ ‹‹ይህን ጽድ ማን ተከለው?›› አልኳቸው በመንገድ ዳር ዳር የተተከለ ጽድ አይቼ፡፡ መንገዱ ወደ አጼ ምንልክ መታሰቢያ ክሊኒክ እንደሚወስድና ጽዱም ክሊኒኩ ሲሰራ እንደተተከለ ነገሩኝ፡፡ ጓደኞቼን ካረፉበት ጠርቼ ክሊኒኩንና ሐውልቱን ጎበኘን፡፡ ክሊኒኩም ተከፍቶ የሚያውቅ አይመስልም - የሸረሪት ድር አድርቶበታል፡፡
ከዚህ ስፍራም ወደ  ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ሄድን፤ እናም በዚያ የነበረውን የንግስ ስነስርዓት ታደምን፡፡ አንድ ሰው ሰራሽ ጥንታዊ የዋሻ ምሽግን፣ አጼ ምንሊክ የተከሉትን ሾላ እና የመብረቅ መከላከያ ዛፍ ጎበኘን፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አንጀታችሁን የሚበላው ወደቤቴ ስሸሽ ብመታና ብሞት አስከሬኔን እዚያው ተውት፤ ከጠላት ጋር ግንባር ለግንባር ስፋለም ከሞትኩ ግን አጽሜ ወደ ትውልድ ስፍራዬ ይምጣ  ያለውን የፊታውራሪ ገበየሁን አጽም በአንድ የቤተክርስቲያኑ ግቢ ያለ ክፍል ውስጥ ስታዩ ነው፡፡ ከተቀበረና ከአድዋ ድል ከሰባት አመት በኋላ አጽሙ እንደመጣ የተነገረን ጎራው ገበየሁ ከድሉ በኋላ በጃንሜዳ የጦር አበጋዞች በፈረስ ሲያልፉ የእርሱ ፈረስ ብቻውን ከፊት ሲያልፍ ያዩት አጼ ምንሊክ ተንሰቅስቀው እንዳለቀሱለት ይነገራል፡፡
በቤተክርስቲያኑ ያገኘናቸው እና እዚያው የሚኖሩት መነኩሴ ከጃንሆይ ጋር ለኬኔዲ ቀብር ዲሲ የሄዱ፣ ኮርያና ኮንጎ ለዘመተው ሻለቃ ጦር የነፍስ አባት ሆነው አብረው ተጉዘው የነበሩ፣ በደርግ የታሰሩና የተደበደቡ መሆናቸውን ሲነግሩን ያልጠበቅንውን ነገር በመስማታችን ተገርመናል፡፡ በ1916 ዓ.ም. ነው የተወለድኩት ብለውናል፡፡
ሕዝቡ አጼ ምኒልክ በተወለዱበት ስፍራና በቤተክርስቲያን እንግዶችን ደግሶ ያበላል፤ ለንጉሱና ለጎራው ገበየሁ ያለው ፍቅርም የትዬለሌ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ ነዋሪው አንዱ ሰፈር ጠላ፣ ሌላኛው ዳቦ፣ ግማሹ እንጀራና ወጥ ታዞ አዘጋጅቶ ማየታችን እና መጋበዛችን ነው፡፡
የሕዝቡ አቀባበልና መስተንግዶ እጅግ የሚያስደስት የነበረ መሆኑን የምናሳይባቸው አንዲት ደግ እናት ቤተክርስቲያኑን ለቀን ስንወጣ አገኘን፡፡ እንጀራ እንዳልበላን ስንነግራቸው ወደቤቴ እንሂድ አሉን፡፡ እርምጃቸው ፈጣን ስለነበረ ከእርሳቸው ጋር መጓዝ አድካሚ ነበር፡፡ ሮጥ ሮጥ እያልን አብረናቸው እያወራ ሄድን፡፡ የሚቸኩሉት አጼ ምንሊክ በተወለዱበት ስፍራ ምግብ ማቅረብ ስላለባቸው የእድር ዳኛ እንዳይቀጣቸው እንደሆነ ነገሩን፡፡ በ1974 ዓ.ም. አጼ ምንሊክ በተወለዱበት ስፍራ ላይ በ15 አመት እድሜያቸው ትዳር ይዘው መንግስት ከስፍራው እንዲለቁ ያዛቸዋል፡፡ የእርሳቸው ቤተሰብና ሌሎች ልቀቁ የተባሉ አምስት አባወራዎች ‹‹አንለቅም፤ ሌላ ቦታም ቤት ለመስራት አቅም የለንም›› ሲሉ መንግስት ለእያንዳንዳቸው አርባ ቆርቆሮ እና አምስት እሽግ ምስማር ይሰጣቸዋል፡፡ አሁንም ‹‹አንለቅም አቅም የለንም ቤቱን ለመስራት›› ይላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ቀበሌው ታዝዞ ቤታቸውን ሰርቶ አጥሩን አጥሮ ያስረክባቸዋል፡፡ እነሱም በአዲሱ ቤታቸው ይገባሉ፤ የአጼ  ምንልክ መታሰቢያ ሀውልትና ክሊኒክም ይሰራል፡፡ ‹‹በወቅቱ ልጆቻችንን ሲያምብን ወስደን ገና አንድ መርፌ ሲወጉ ይድኑልን ነበር፤ ስፍራው የአጼ ምንሊክም ስለሆነ በረከትም ነበረው፡፡ አሁን ቁስል የሚጠርጉ ናቸው ያሉት እንደበፊቶቹ ጥሩ ሐኪሞች አይደሉም፣ እኔም ለመንግስት አቤት እንበል እያልኩ ነበር የሰማኝ የለም፡፡ እኔ አሁን በቅርቡ በጠና ታምሜ በየሆስፒታሉ ስዞር ሳይሻለኝ ቀርቶ ዶክተር አያናው ራሱ አክሞኝ ነው የዳንኩት፤ በሃብት ላይ ሐብት ይስጠው›› አሉን፡፡
በእርሳቸው ቤት የነበረው ግብዣ አስደሳች የነበረ ሲሆን ጠዋት ሐውልቱን ያስጎበኘንን ልጅ ገዘሃኝንም ዘመዳቸው ኖሮ እዚያው አገኘንው፡፡ በጥሩ ሁኔታም አስተናገደን፡፡ በሬውንም ፎቶ እንዳነሳውም ጠየቀኝ፡፡ በዚህ ቤት ውስጥም ሆነ በቤተክርስቲያን ውስጥ አማርኛም ሆነ ኦሮምኛ በእኩል ይነገራሉ፡፡ ተናጋዎቹ በአብዛኛው ሁለቱንም ቋንቋዎች አፉን እንደፈታባቸው ሰው ሁሉ እኩል አቀላጥፈው ይናገሯቸዋል፡፡ ዱቢሳ አማኑኤል የሚባል ቤተክርስቲያንም በቅርብ እንዳለ ነገሩን፡፡ የተደባለቀ ህዝብ ነው፡፡ ገዛሃኝ እንደገና ከዚያ ቤት ተሰናብተን ወደ ራሱ ቤት ወስዶ ጋበዘን፡፡ ‹‹ኑ አጎቴ ቤትም ግቡ›› አለን ከዚያ በኋላ፡፡ በጣም ስለጠገብንም ሰላምታ ብቻ ሰጥተናቸው ስንሄድ ቅር እያላቸው ነበር፡፡ ከባልንጀሮቼ አንዱ በኦሮምኛ አንዱን ወጣት አስር ልጅ ውለድ ሲል መክሮታል- እኔ መጀመሪያ አስራሁለት ያልኩትን በማሻሻል፡፡ ሰኞ ኦሮምኛ የምለማማድባት የተባረከች ቀን ነበረች፡፡ ጽሑፉን ከወደዱት እና ከቻሉ አንጎለላን እንደኛ ሄደው ይጎብኟት እልዎታለሁ፡፡

ባለቤት-አልባው ቤተ-መንግስት



የጉዞ ማስታወሻ

በመዘምር ግርማ
አምሃየሱስ 1733 በመሰረቷት በአንኮበር ያለው ቤተመንግስት ሎጅ የዛሬው መዳረሻችን ነው፡፡ በመግቢያው በር አካባቢ ሆነን ወደ ዋናው ቤተመንግስት የሚያወጡ 468 ደረጃዎች እንዳሉ ተነገረን፡፡ እንሄድባቸዋልን ብላችሁ ነው? በሌላ ከብረት የተሰራ መደገፊያ አጥር ባለው መንገድ ሄደን ግቢውን ጎብኝተን ስንመለስ ነው የምንወርድባቸው፡፡ ሾላ፣ ጎተራ፣ የፈረንሳይ ቆንስላ፣ የእንግሊዝ ቆንስላ የሚባሉ ስፍራዎች እንዳሉ ተነገረን፤ አየናቸውም፡፡ ጋጀሎ የተባለው የጣሊያኖች ቆንስላ ግን ከስፍራው አራት ወይንም አምስት ሰዓት ያስኬዳል፡፡ የራቀበት ምክንያቱ መልዕክተኞቹ የነዋሪውን ሃይማኖት እንዳያስቀይሩ ነበር አሉ፡፡ በዚያ ስፍራ ለተቀበረው ጣሊያናዊ የእጽዋት ተመራማሪ መታሰቢያ የባህላዊ መድሃኒቶች ምርምር በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲና በጣሊያኖች ይካሄዳል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥንም የሚለካ ማሽን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቤተመንግስት ሎጁ ግቢ ውስጥ ተክሏል፡፡አልዩ አምባ፣ ደብረሲና፣ እመ ምህረት እና ወፍ ዋሻ በየገለጻው መሃል የምትሰሟቸው አጎራባች ስፍራዎች ናቸው፡፡
በአንኮበር ወረዳ 96 አብያተ ክርስቲያናት ሲኖሩ 56 ጥንታዊ ናቸው፡፡ በቤተክርስቲያኑ ሙዚየም አስር አስር ብር ከፍለን በሶስት ዙር እንጎበኝ ያዝን፤ ከመግቢያ ክፍያው 25 ብር በተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡ ሙዚየሙ አነስተኛ ቤት ሲሆን ዘመናዊ ሙዚየምም በአቅራቢያው እየተገነባ ነው፡፡ በየቤተክርስቲያኑ እና እቃ ቤቱ የተበታተኑትን ቅርሶች አሰባስቦ ለማስጎብኘት ጥሩ መላ ተዘይዷል፡፡ በሙዚየሙ ካየናቸው ውስጥ የብርና የነሃስ መቋሚያዎች፣ የወርቅ፣ የብርና የነሃስ ዘውዶች፣ ባለአምሰት መን ነገስታቱ የሚለብሱት ድርብ ብልኮ፣ በፈረስ ሲሄዱ እንዲመቻቸው የሚለብሱት ተነፋነፍ መሰል በእጅ የሚሰራ ባለወንበር ሰናፌል ሱሪ፣ ጥብቆ እና ዙሪያው ብር የሆነ የሞሰበወርቅ ልብስ ይገኙበታል፡፡ ከአድዋ መልስ የሞተው የምንሊክ ፈረስ የአባዞቢል ልብስ /ግላሱ እና ሰገጡ/ 118 አመቱ ነው፡፡ እሱንም አይተናል፡፡
ምን ይሄ ብቻ! እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ ከአሜሪካ ያስመለሱት የአጼ ምኒልክ የእጃቸው ዳዊት፣ ራስ መኮንን ያስመጡት እና 1928 አንኮበር ሙሉ በሙሉ በጣሊያን ስትመታ ጥቃት ደርሶበት የተሰነጠቀ የብር ደወል፣ አድዋ ደርሶ የመጣ ንጉስ ሳህለስላሤ ከህንድ ያስመጡት ልብሰ-ተክህኖ /መጎናጸፊያ/ በቀርቀሃ መያዣ የሚያዝ እና እዚያው የሚሰራ 15 ሰው የሚያጠላ ድባብ፣ 15 ኪሎ የሚመዝን የአጼ ምንሊክና የእቴጌ ጣይቱ የወርቅ ሊሻን እና የወርቅ ጥላ፣ዳር ዳሩ ወርቅ የሆነ የንጉስ ሳህለስላሴ የወርቅ ሰናፊሊ ቦታ ቦታቸውን ይዘው እዩኝ እዩኝ ይሏችኋል - እናንተ መሄዱን ከያዛችሁት! የወሌ ብጡልና የሌሎችም ፎቶዎች፣ ጣሊያን ያቃጠለው ቤተክርስቲያን የሸክላ ጉልላት እና የብር ከበሮ ሌሎቹ የስፍራው ስጦታዎች ናቸው፡፡ ዘማቾች ወደ አድዋ ሲሄዱ ሁሉም ነጭ ልብስ ለብሶ የቤተክርስቲያን ካህናት አረንጓዴ ሱሪ በቀይ ገበር ይለብሳሉ- ማነታቸው እንዲለይና ቅዳሴው እንዳይታጎል:: የካህናቱ ልብስ ታዲያ በክብር ተቀምጧል፡፡
ጥንታውያኑ አባቶች ከዕጽዋት ቀለም ሰርተው የጻፏቸውን የብራና መጻህፍት አይተናል:: አቡሻሃር (የዘመን አቆጣጠር የሚያሳይ መጽሐፍ) ስንክሳር፣ ግብረ ህማማት እና ፈትሉን ሰም ነክረው እንደሸራ ተጠቅመው የሰሩትን ስዕል አድንቀናል፡፡ የካቲተት 16 1888 በአውሳ ግምባር የተማረከን መሳሪያ እና ምንሊክ በአድዋ የያዙትን መሳሪያ አይተናል፡፡ የአጼ ምንሊክን መሳሪያ ለመንካት ሁሉም ተሸቀዳደመ፡፡

አዋጅ ለማወጅ ምንሊክ ገበያ አቁመው ነበር፡፡ እዚያ ገበያ ላይም ነጋሪት የሚጎሰምበትን ስፍራ አይተናል - ከሙዚየም መልስ ፡፡ 42 ነጋሪት በወቅቱ የነበረ ሲሆን አብዛኛው በያገሩ ተበታትኖ አሁን አንዱ ብቻ ነው ያለው፡፡ ህዝቡን ሰርቶ ለማሰራት ንጉስ ሳህለስላሤ ተሸክመው 10 ኪሜ ርቀት ያመጡት 2 ሜትር 60 ሴንቲሜትር የሚሆን ጠፍጣፋ ድንጋይ ጣሊያን ባነደደው የመድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን ፍርስራሽ በረንዳ ላይ አይተናል፡፡ ጉድ በሉ ብርታታቸውን!
ምንሊክና ጣይቱ 1875 .. በአንኮበር ነው የተጋቡት፡፡ የአንኮበርን 1928 ጣሊያን ባላባቶቹን ልምታ ብሎ በከባድ መሳሪያ ካቃጠለው በኋላ ጎረቤላ ከተማ ተመሰረተች፡፡ አዲስ ዓለም፣ እንጦጦ እያሉ አዲስ አበባ የገቡት ምንሊክ ትተው የሄዱት ስፍራ አንኮበር ላይ ሎጁን መስራት የተቻለው የቀድሞ ስፍራው ምን ይመስል እንደነበር ሰው በማጠያየቅ እና ፎቶ በማየት ነበር፡፡ የቀድሞውን ቤተ-መንግስት ስፍራዎች መለየት ተችሎ በግል ባለሃብት ለምርምር ቁፋሮ እንዲያመች ተብሎ ሎጁ ከምድር ሁለት ሜትር ከፍ ብሎ የተሰራ ነው፡፡ አሁንም ሎጁ ያረፈበት ምድር በተመራማሪዎች ይበረበራል - ፍቃድ ይዘው ከመጡ፡፡ ከዚህ ሰገነት በረንዳ ላይ ሆኖ እስከ አፋር ይታያል አሉ፡፡ ጠጅዎን እየኮመኮሙ መቆጣጠር ነው የአፋሮችንና የአርጎቦችን አገር! ታሪክ፣ ባህል እና ተፈጥሮ ተሸጠው እንጀራ ሲሆኑ በአይናችን አየን፡፡
በመጠኑም ቢሆን ግን አሁን በማህበረሰብ አቀፍ ኢኮቱሪዝም የአካባቢው ህዝብ ይጠቀማል፡፡ የተለያየ ቀናትና ሰዓታት ርዝማኔ ያለው የእግር ጉዞ ወደ ታሪካዊ እና ሰው ሰራሽ ስፍራዎች ይደረጋል፡፡ በዚህን ጊዜ አርሶ አደሩ መንገድ ይመራል፡፡ ፈረስ በማቅረብ፣ እቤቱ ለሚመጡት ጎብኝዎች የግብርና ስራ በማሰራትና የምግብ ዝግጅት ላይ በማሳተፍም ያስተናግዳል፡፡ በሎጁ ግቢ ውስጥ ያለው ባህላዊ ቤት የገበሬው ቤት ሞዴል ሲሆን በገበሬው ቤት መሄድ ለማይችሉ ጎብኝዎች 20 ዶላር የሚችለውን ያሳያል፡፡ 20 ዶላር ፊደል መማር፣ በኩራዝ መጠቀም፣ ቡና በጉልቻ ማፍላት፣ ጥጥ መፈልቀቅ፣ በመቃ እሳት ማንደድ እና ገብስ በሙቀጫ መሸከሸክ ይቻላል፡፡ ፡፡
‹‹የዘንድሮ የመስቀል በዓል በስፍራው ተከብሯል፤ ከበዓል አዘጋጅ ድርጅቶች ጋር በስፍራው አከባበር የተደረገ ሲሆን በዚህም ምክንያት የጎብኝው ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል፡፡ መንፈሳዊ ጉዞ አዘጋጅ ማህበራት እና ብዙ ጎብኝዎች ወደ ስፍራው እንዳይመጡ ዋነኛ ችግሩ የመንገድ ነው፡፡ ይህን ቦታ ከጠላት ለመሸሸጊያነት እንጅ ለቤተመንግስት አልነበረም ነገስታቱ ያቋቋሙት፡፡ ስፍራው የተዳከመው የዘይላ መንገድ ሲቆም ቢሆንም አሁንም በተሸለ መንገድ መታወስ ይችል ነበር፡፡ ለልምድ ልውውጥ ከሰሜን ሸዋ ውጭ እንሄዳለን፤ ሰሜን ሸዋ ውስጥ አለመሄዳችን ግን ድክመት ነው›› ያሉኝ አቶ ማሙሽን የዞኑን ቱሪዝም ለማቀናጀት የባህል ሃላፊዎች ቢያግዟቸው እላለሁ፡፡ ሱናርማ እና በጋ ቱርስ የተባሉ ድርጅቶች ወፍ ዋሻ ላይ የጀመሩት የቲሪስት ስፍራዎችን የማጎልበት ስራ መጓተቱ አንድ ችግር ነው ስለተባለ ምን ነካችሁ በሏቸው፡፡ ለጠየኳቸው ሁለት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነው ይህን ያወቅሁት፡፡


‹‹ወርቅ የተነጠፈበት የሚመስለኝ የምንሊክ አገር እንዲህ ያለ ነው ለካ›› ያሉ አንድ ተጓዥ አስቀውኛል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በምንሊክ ጊዜ ያመጡት የስልክ መስመር መከላከያ ስላልነበረው መብረቅ መታው፡፡ ስልክ መጀመሪያ እዚህ ጀምሮ አሁን ግን መጨረሻ ስልክ የገባለት ስፍራ ነው - ይታያችሁ የእድሉ ነገር፡፡ የጎብኝው ቁጥር ማነሱ እና እንዲያውም የውጭ ዜጎች ያው አልፎ አልፎም ቢሆን ስፍራውን ማዘውተራቸው የታሪኩ ባለቤቶችስ የታሉ ያስብላል፡፡ ዋጋው አባሯቸው እንዳይሆን የሎጁ ሃላፊዎች ቢያስቡበት ምናለ? አልጋና ዋና ዋና አገልግሎቶችን ብትጠይቁ ጨዋታው በዶላር ነው፡፡ አካባቢውን ማገዝ ካለባቸው መስሪያ ቤቶች አንዱ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሲሆን በባህል ማዕከል ሲምፖዚየም ብቻ ነው የቱሪዝም ባለድርሻዎችን የሚጠራው - ከዚያ ዝም ይላል - ከስፍራው ያገኘንው ወቀሳ ነው፡፡ ምንሊክ ያስተከሉትን የመጀመሪውን ባህርዛፍ ቆሞ አየንው፡፡ ባህር ዛፍ ስል የቤተክርስቲያኑ የሙጋድ እንጨት ፈላጭ የነበሩት ዘውዴ ነሲቡ ትዝ አሉኝ፡፡ እንደ እርሳቸው ዓይነት ስራ በመስራት የሚተዳደሩት አባት ለመጸወታቸው ጎብኝ ‹‹የነፍስ ገበያ ይሁንላችሁ›› እያሉ ይመርቃሉ፡፡
በላ ልበልሃ የሚባባሉበትን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አይተን ምንሊክ ከቴዎድሮስ የተማሩትን ታክስ አስተዳደር ተግባራዊ አድርገው እንደነበር ሰማን፡፡ ምንሊክ ቴዎድሮስ ሲሞቱ ሃዘን አውጀው ካላዘናችሁ እኔ ጫካ ሄጄ አዝናለሁ ብለው ነበር አሉ ለጋሻ ጃግሬዎቻቸው፡፡ ያውቃሏ ውለታቸውን!
የአድዋ ድልን ለመዘከር በዚህ ወር ልንሄድባቸው ካሰብናቸው ስፍራዎች አንዱና የመጀመሪያው የነበረው አጼ ምንልክ የተወለዱበትና የጎራው ገበየሁ አጽም ያረፈበት አንጎለላ ነበር፡፡ የካቲት 16 እሱን ጎብኝተን ቀጥሎ እቅድ የያዝንለትን ሌላ ከደብረ ብርሃን አቅራቢያ የሚገኝ ስፍራ ልቼን ለመጎብኘት እንዳሰብንው ሳይሳካ ሲቀር የአንኮበር ጉዞ እንዳይታጎል ሰግተን ነበር፡፡ ሦሥተኛው ስፍራ አንኮበር፣ የካቲት 23 ቀን 2007 .ም፣ ሰኞ፣ ስራም ዝግ ስለሆነ ብዙ ሰው ይሄድበታል ብለን አስበን የነበረ ቢሆንም በየምክንያቱ አራት ሰውም ለማሰባሰብ ከብዶን ባሳር እኔ፣ ይድነቃቸው ሶሎሞን፣ ተክለሃይማኖት ገብረማርያም እና ጌጤ ፈለገ ከጠዋቱ 120 ከደብረብርሃን መናኸሪያ መኪናው በእዬዬ ተነስቶልን ጎረቤላ ከተማ 310 ላይ ደረስን - 42 ኪሜ የኮረኮንች መንገድ ጉዞን አጠናቀን፡፡
ከጎረቤላ ከተማ ወደ አንኮበር አጭር የእግር ጉዞ ስናደርግ አምና በአሜሪካ ሰላም ጓድ ድጋፍ ከየትምህርት ቤቱ የመጡ ታዳጊ ሴት ተማሪዎችን ይዘን ወደዚህ ስፍራ ያደረግንው ጉዞ ትዝ አለኝ፡፡ አምና ማርቸዲሳችን ተቀርቅሮበት ከነበረው ስፍራ በታች ስንደርስ አንድ በባንዲራ ያሸበረቀ መኪና ይመጣል፡፡ እንዲያሳፍረን ስንለምን አቁሞልን ስንገባ መኪና ውስጥ ያሉት የማውቃቸው ሞጃዎች ኖረዋል፡፡ በእዚህ ዕለት እዚህ ስፍራ በፍጹም አልጠበቅኋቸውም ነበር፤ ምክንያቱም አገር በቀል ቱሪዝም ብዙም አልተለመደምና ነው፡፡የሞጃ ባህል እና ቱሪዝም /ቤት የሚያስተባብረው የአገርህን እወቅ ክበብ በአንኮበር ቤተመንግስት አብሮን ጉብኝት ሲያደርግ ሁላችንም ተደስተናል፡፡ ለጉብኝት በመነሳሳታቸው አድንቁልኝ፡፡ ግን ከሞጃ እውነት አስር መኪና ጎብኝ ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ ወደ ጉብኝቱ ያልሄደው ሰው በዚያን ቀን ምን ሰራሁ ብሎ ራሱን ቢጠይቅ መልሱ ምን እንደሚሆን እንጃ፡፡ እባካችሁ ሞጃዎች ባህል ወዳዱን ልጃችሁ አቶ ሃይሌ ገብረማርያምን ተጠቀሙበት፡፡ እንደ አንኮበሩ አስጎብኛችን ገለጻ ‹‹ታሪክ ከጓሮ ነውና የሚጀምረው፡፡›› ከአርብ የካቲት 27 እስከ እሁድ የካቲት 29 ደግሞ በመንዝና ተጉለት የዩኒቨርሲቲያችን የባህል ማዕከል አባላት የሆንን ከመቶ በላይ ሰዎች የምናደርገውን ጉዞም ከዚህ ቅጥ አምባሩ ከጠፋበት ጽሑፌ በተሻለ እንደማስጎበኛችሁ ቃል ልግባ!
በዚች ግጥም እንሰናበት -
እንጦጦ አፋፉ ላይ ብርድ እንዳይበርደን፣
እግዚአብሔር መርቆ ጣይቱን ሰጠን፡፡

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...