2022 ጁን 24, ዓርብ

ዓለም ወደፊት እኛ ግን ወደኋላ

 



ከመቼውም ጊዜ በላይ በዚህ ክፍለዘመን ዓለም በቴክኖሎጂ ውጤቶችና በስልጣኔ አስተሳሰብ እየተሳሰረችና አንድ መንደር እየሆነች ነው፡፡ የሰዎች ተንቀሳቅሶ የመስራትና የመኖር ዕድል እየሰፋ ነው፡፡ ምን ይህ ብቻ! ባሉበትም ሆኖ ከሌላው የዓለም ክፍል ጋር ትስስር ማድረግና እቤትዎም ቁጭ ብለው በሌላው ዓለም ለሚገኝ ድርጅት የመስራት ዕድልዎ ሰፍቷል፡፡ ራሱን ከዓለም አጥሮና ዜጎቹን ዕድል ነፍጎ ለአስርት ዓመታት ለኖረ አገር ይህ በደንብ ባይገባውም፡፡ ቢሆንም ግን እንደ ኢትዮጵያ ካለ የትስስርና የእንቅስቃሴ ዕድሎች ከተቆላለፉበት አገርም የሚወጣው ከሚገመተው በላይ ነው፡፡ የማያስገባ ቢሆንም ጥሶ የሚወጣበት ብዙ ነው፡፡

በእርግጥ ይህን ጉዳይ ልናይ የሚገባን ከአንዱ የዓለም ክፍል ወደ ሌላው ያለው ልዩነትና አንድነት ምን ይመስላል የሚለውን በማጤን ነው፡፡ አሁን ሰዎች ከምንጊዜውም በላይ የዓለም ዜጎች ነን ብለው ስለሚያምኑ እራሳቸውን በአንድ ኃይማኖት፣ ብሔር ወይም የሙያ ማህበር የመግለጣቸውና በዚያም የመመካት ዕድላቸው እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በስብስቦች የመርካትና የመመካት ዕድል ቀንሷል፡፡ በአሜሪካ የሚታየው ይህ ነው፡፡ በ1999 እ.ኤ.አ. 70 በመቶ አሜሪካውያን የኃይማኖት ተቋም አባል ነን ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ይህ አሐዝ  ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በ2018 ወደ 50 በመቶ ወርዷል፡፡ ይባስ ብሎ በ2020 ወደ 47 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ ዛሬ ከሁለት ዓመት በኋላ ይህ ቁጥር የት ደርሶ ይሆን? የሙያ ማህበራትን የማደግ ሁኔታ ባጠና አንድ ጥናት እንደታየውም 68 በመቶ ድርጅቶች የማደግ ዕድል አጥተናል ብለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 11 በመቶዎቹ ከነጭራሹ ጠፍተዋል፡፡ 25 በመቶዎቹ ደግሞ አላደጉም፡፡ 32 በመቶዎቹ ደግሞ 1-5 በመቶ ብቻ ነው ለማደግ የቻሉት፡፡ በማንነት ላይ የተመሰረቱ ማህበራትም ቢሆኑ የአባልነታቸው ሁኔታ ተቀዛቅዟል፡፡ በአጠቃላይ በማናቸውም ዓይነት ስብስብ ወይም ማህበር ባለፉት የተወሰኑ አስርት ዓመታት አባልነት በአማካይ ከሩብ በላይ ቀንሷል፡፡ በአንዳንድ ልዩ ሁኔታዎችና ለማንነት ትልቅ ግምት በሚሰጥባቸው ከመካከለኛው ዘመን ፈቅ ባላለ አስተሳሰብ ላይ ባሉ አገራትና ዝግ ማህበረሰቦች ግን የዚህ ተቃራኒው ይስተዋላል፡፡ በተለይ አውሮፓ በዘር የመከፋፈል ባህሉን ወደ አፍሪካ በማራገፍ ራሱ መሆን ባለበት ጎዳና እየሄደ ነው፡፡ ከእነዚህ ሰለባዎች አንዷ የኛዋ ኢትዮጵያ ለመሆኗ ጥርጥር የለውም፡፡ ለዚህም ቀጥሎ የተመለከተውን አብነት እንይ፡፡

ዓለም ራሱን በስልጣኔ ጎዳና እየመራ ነው፡፡ በዚህ ዘመን መደረስ የሚቻልበትን እያሳየን ነው፡፡ ይህን የሰውነት ደረጃና የመሰባሰብን ጣጣ የመተው ልክ ያመጣው የስልጣኔ ትሩፋት ለእኛም ደርሷል፡፡ በአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም በሌሎች አህጉራት ያለው የቴክኖሎጂ ውጤት በማግስቱ እኛም ጋ በሚገባበት በዚህ ዘመን እኛ የምንሸርበው ሕይወታችንን የሚያቀል ሳይሆን ችግርን የሚያባብስ ነገር ነው፡፡ በችግር ላይ ችግር የሚደራርቡ ፖለቲከኞች፣ ልሂቃን፣ ነጋዴዎች፣ ምሁራን ወዘተ በየቀኑ እየፈሉ አገሪቱ ከድጡ ወደማጡ እያመራች ትገኛለች፡፡ የእኛ አገርና አህጉር  ከመቼውም በዘለለ በዘረኝነት አባዜ ተጠምዷል፡፡ በኢትዮጵያ የዘር ጥቃትን፣ ግድያንና ዘርተኮር እንቅስቃሴዎችን መስማት ዋል አደር ብሏል፡፡ በሰላምም ሆነ በችግር ጊዜ የሚታሰበው በዘር ነው፡፡ አገሪቱን ሰቅዞ የያዘው አሰቃቂ የግድያ ዜናና ዘመቻ ወሬ ለአንድ ሳምንት አልለቀቀንም፡፡ በዚህ ዝቅጠት ውስጥ ሆነንም አሁንም የዘር አባዜ አይለቀንም፡፡ በዚያው ላይ ኃይማኖት እንጨምርበታለን፡፡ አካባቢያዊነትም አለ፡፡ የመከፋፈያ መንገዱ የትየለሌ ነው፡፡ እንደ አገር ይህን ለማስቆምና የተሻለና በሰውነት የምንንቀሳቀስበትን ዕድል ለመፍጠር አንፈልግም፡፡ ከ1500 በላይ አማሮች በወለጋ በግፍ በተጨፈጨፉበት በዚህ ሳምንትም ከዚህ አባዜ ለመውጣት የምትፈልግ ሳይሆን የዘር አዙሪቷ ውስጥ የምትባትል አገር ውስጥ ነን፡፡ በአጠቃላይ የኋሊት ጉዞውን ተያይዘነዋል፡፡ መድረሻችን አይታወቅም፡፡ መፍትሔ ያለው ዜጋ ካለ አሁኑኑ ያንን መፍትሔ ቢሻ ውድመቱን በተወሰነ መጠን ሊቀንሰው ይችላል፡፡ እንጂማ የታቀደልንን የጥፋት መጠን መገንዘብ ያዳግታል፡፡ በሌላው ዓለም እየቀነሰ የመጣው በቡድን ማሰብና መንቀሳቀስ እዚህ አደገኛ አቅጣጫ የያዘው ለምን ይሆን? አገራዊ፣ ቀጣናዊ ዓለምአቀፋዊ እጆቹ የእማን ይሆኑ?

2022 ጁን 19, እሑድ

በጠባሴ መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ከሰባት ዓመታት በኋላ - አይ አገሬ!

 

በመዘምር ግርማ

12/10/2014 ዓ.ም.

 

ከሰባት ዓመታት በፊት የማውቀውን ይህን ትምህርት ቤት ከዛሬ ነገ እጎበኘዋለሁ ስል ስንት ጊዜ ሆነኝ፡፡ በዚህ ዓመት የአሜሪካ የሠላም ጓዶችን ስራ መልሶ ለማየትና ለማነቃቃት በማሰብ ሽር ጉድ ስል መጀመሪያ ከመጡልኝ አንዱ ይህ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ስለሆነም ሦስት ሆነን ለመጎብኘት ከተቀጣጠርነው ውስጥ እኔ ሰኔ አንድ ቀን 3፡30 ላይ ቀድሜ ተገኝቻለሁ፡፡ በቅድሚያም ያቀናሁት ወደ ቀድሞ የአሜሪካ የሠላም ጓዷ ወደ ዲሻንታል የመማሪያ ማዕከል ወይም ቢሮ ነው፡፡ ስልጠና ይሰጥበት፣ ተማሪዎች ያነቡበትና ይማሩበት የነበረ ቆንጆ ክፍል ነበር፡፡ እሷ በፊት ቅርጻቅርጽ፣ በልዩ ልዩ የእንግሊዝኛ መጻሕፍት፣ በስልጠና ፖስተሮች ታስውበው ነበር፡፡ ለተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ወይም ሲፒዲ ስልጠና እገዛ ስትሰጥና እንግሊዝኛ ስታሰለጥን ጥቁር አሜሪካዊቷን ወጣት በጎፈቃደኛ አግዣታለሁ - በትርጉምና በመሳሰለው የሙያ ስራ፡፡ አሁን ክፍሉ ዝግ ነው፡፡ በመስኮት ለማየት ሞከርኩ፡፡ በዚያም ቅጽበት ያየሁት ቆሻሻ የተዘጋ ክፍልን እንጂ ያንን ያማረና ግቡ ግቡ ብሎ የሚጋብዘውን የዲሻንታልን ቢሮ አልነበረም፡፡ አሁን ያረጁ ኮምፒውተሮች፣ ካርቶኖች፣ ወረቀቶች፣ ጠርሙሶች ወዘተ በየቦታው እንደ እብድ ቤት ተበታትነው አቆሽሸውታል፡፡ ቆሻሻ፣ የተዘበራረቀ ዕቃ የተቀመጠበት መጋዘን፣ ተስፋ አስቆራጭ ትዕይንት ቀልቤን ገፈፈው፡፡

ከዚህ በኋላ የመምህራን ማዕከል ወደነበረው ስፍራ ስሄድ ሁለት መምህራን ኮምፒውተር ሲነካኩ ደረስኩ፡፡ ወንዶች ናቸው፡፡ ሁለት ሴቶች መምህራን ደግሞ ጥግ ይዘው ለዕለቱ ክፍል ይዘገጃጃሉ፤ ወረቀትም ያርማሉ፡፡ ተዋውቄ የመጣሁበትን ጉዳይ ነገርኳቸው፡፡ መምህራኑ አዳዲስ መሆናቸውን ነገሩኝ፡፡ ርዕሰመምህሩና ምክትሉም ስብሰባ ሄደዋል ተባልኩ፡፡ ሁለት ዕጩ መምህራን ከመምህራን ትምህርት ኮሌጅ መጥተው በቢሮው ውስጥ ከመምህራኑ አጠገብ ተቀምጠው የደወሉን መደወል ይጠባበቃሉ፡፡

አንድ ስለ ትምህርት ጉዳይ ለማውራት ቅርብ የሆነ መምህር አገኘሁ፡፡ በቅርቡ የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ችግር ለመፍታት የሚጠቅም ያለውን ዕቅድ አውጥቶ ማዘጋጀቱን ገልጾ ያንንም ዕቅድ አሳየኝ፡፡ ተማሪዎች ያለባቸውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችግር የተመለከተ ነው፡፡ ያንን ዕቅድ በትምህርት ቤቱ በኩል ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማስላክና እገዛ ለማግኘት ከቀናነት ማነስ አለመቻሉን ነገረኝ፡፡  ከእርሱ ጋር ስናወጋ ሌሎች መመህራን ከክፍል ወጥተው እየመጡና በፊትም የማውቃቸው እየተጨመሩ ሲሄዱ ሰላምታ ለመለዋወጥና አንዳንድ ትዝታ ለማውጋት ቻልኩ፡፡ መምህሩ ‹‹ዋናው ችግር ተለባስሶና ተሸፋፍኖ የመሄድ ችግር አለ›› በማለት ከላይ እስከታች ያሉ ችግሮች ለመማር ማስተማሩ ስራ እንቅፋት መሆናቸውን ገለጸልኝ፡፡ በቅርቡ በደብረሲና ትምህርት ቤት ሃምሳኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ አከባበር ወቅት ያገኘኋቸው መምህር እንዳሉኝ ‹‹ትምህርት ቤት ርዕሰመምህሩን ይመስላል፡፡››

ያናገርኩት መምህር በትምህርት አስተዳደር ረገድ ያለ ችግር የፈጠረውን ፈተና ለመገንዘብ ችሏል፡፡ ‹‹ወላጅ ለመጥራት ደብዳቤ ጻፉልኝ ስል አድበሰበሱ›› አለኝ፡፡ ‹‹አመራሩ ወላጅን ማግኘት አይፈልግም፡፡›› የኮምፒውተርን ጉዳይ አንስቶ ሲነግረኝ ሲጠቀሙበት ያየሁትን ኮምቲውተር በስንት ግፊት ከመጋዘን አስወጥቶ እንደሚጠቀም አነሳልኝ፡፡ በዚያም ምክንያት ሌሎቹም መምህራን ለመጠቀም ችለዋል፡፡ በአገሪቱ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶየኮምፒተር ትምህርት ለመስጠት መታቀዱን ገልፆ ከተማው ላይ ሳይቀር መብራትና መሰረተልማት በሌለበት ገጠር እንዴት ሊሆን ይችላል ሲል ይሞግታል፡፡ ‹‹ፈተና በሰሌዳ ጽፈን ነው፡፡ ኮፒ ራሱ እዚህ ጽፈህ ነው ሌላ ቦታ ፕሪንት የምታደርገው፡፡ ያላቸውን የጥቅም ትስስር አታውቅም፡፡ መግዛት አቅቷቸው አይደለም፡፡ የግል ትምህርት ቤት ላይ ያለው እዚህ የለም፡፡ የመንግስት ተቋም ከግል ለምን ያንሳል?›› ይላል በቁጭት፡፡ መምህሩ እሮሮውን ማንም ሊሰማው የማይችልና ቢሰማውም ‹‹እስኪ እስኪሰለቸው ይጩህ›› የሚባል ትጉህ ዜጋ ነው፡፡ ትውልድ የሚለውን ቃል በየንግግሩ መሃል ይጠቀማል፡፡

ቤተመጻሕፍቱን አስመልክቶ ሲገልጽ የሌለ መጽሐፍ የለም ይላል፡፡ የሚጠቀም ሰው አለመኖሩ ግን ያናድደዋል - መምህራን ጭምር፡፡ ‹‹የዱሮ የኢትዮጵያ ካርታ ያለበት መጽሐፍ ለመወገድ ተዘጋጅቶ አገኘሁት፡፡ የቤተመጻሕፍት ሰራተኛው ያንን ካርታና መጽሐፉ የያዛቸውን ቁምነገሮች ሳሳየው አላነበበውም ነበር፡፡ እንዴት ሽፋኑ ስለተገነጠለ ብቻ ይወገዳል! በርካታና ልዩ ልዩ መጻሕፍት ናቸው እኮ›› ብሎኛል በንዴት፡፡ የንባብ ፍቅር ያለው ሰው ለቤተመጻሕፍቱ ቢመደብለት ጥሩ መሆኑን ገልጾልኛል፡፡ ኢንተርኔት ኮኔክሽን የለም፤ ኮምፒውተር ላቡ በተሟላ ሁኔታ አገልግሎት አይሰጥም፤ ላይብረሪው ከግርማ ሞገስ በላይ ጥቅም አልሰጠም የምሬት ቃላት ጎርፍ!

‹‹እዚህ ሰዓት ጠብቆ የሚጠፋ መምህር የራሱን ልጅ በግል ትምህርት ቤት ያስተምራል፡፡ ምናለ የራሳቸውንም ልጆች እዚህ አስመዝግበው በጥራት ቢያስተምሩ!›› አለኝ፡፡ ‹‹መምህሩ ጠቃሚ ስልጠና አበል ከሌለ አይሰለጥንም፡፡ መምህር ግን የዕውቀት አባት ነው፡፡ መምህሩ ገብቶ መውጣቱን ነው የሚያየው፡፡ ዩኒቨርሲቲ በየትምህርቱ ያለውን የማስተማር ስራ ቢከታተልልን ጥሩ ነው፡፡ ትምህርት እየተሰጠ ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ትውልድ መግደል ነው፡፡›› ችግሩ በዚህ ትምህርት ቤት ብቻ ሳይገደብ በገጠር ትምህርት ቤት በሳምንት ሁለት ቀንም አያስተምሩም ብሎኛል፡፡ ገጠር ላይ ከሚማሩበት የማይማሩበት ቀን ይበልጣል ብሎ ያምናል፡፡ እንደእርሱ ከወረዳ ከተማ በራቁ ቁጥር ቁጥጥሩ ስለሚላላ ነው፡፡

ዘበኛውም ጨዋታችንን ተቀላቅለው ‹‹ይህ ትልቅ ተቋም ስብሰባ የለ፣ ቤተሰብ አይጠራ፣ ልጆቹ ጠባይ የላቸው፣ ደሞዝ አይጨመር›› ሲሉ አማረዋል፡፡ የትምህርት ቤት ጥበቃ 1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በአካባቢው ማህበረሰብ ይሸፈን ስሚባል ህብረተሰቡ ደምወዝ እንደሚከፍል ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡

‹‹ተማሪው ፍላጎቱ ደካማ ሆነ፡፡ የአማርኛና እንግሊዝኛ የፊደል ገበታ 7 ክፍል በየክፍሉ ለጥፌያለሁ፡፡ የማስተምረው ከዚህ ነው የሚወጣው እላቸዋለሁ፡፡ አያነቡም፤ የተወሰነ ተማሪ ነው የሚሰራው፡፡ ቤተሰብ አምጡ ስል አያመጡም፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ በድህነት ነው የሚኖረው፡፡ ልጆቹ ምግብ ሳይበሉ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ 22 ተማሪ ውጪ በሚኖሩ በጎፈቃደኞች ድጋፍ የትምህርት ቤት ምገባ ይደረግለታል፡፡ ቤተሰቦቻችሁ የት ይሰራሉ ስላቸው ዳሸን፣ ሐበሻ፣ ዩኒቨርሲቲ፣ ጽዳት፣ እንጀራ ጋገራ፣ ይላሉ፡፡ ለምን ጎበዝ አትሆኑም ታዲያ የነሱ ልጆች ከሆናችሁ ስል የሚያለቅሱም አሉ፡፡››

በትምህርት ቤቱ ያገኘሁት ሌላ መምህር ስለአመጣጤ ስነግረው በፊት አጣዬ ሲያስተምር ክፍል ገብታ እንግሊዝኛ የምታስተምር አሜሪካዊት እንደነበረች አወጋልኝ፡፡ ስለሷም ልዩ ልዩ የሚያስታውሰው ነገር አለው፡፡ ብቻዋን ገጠር ሄዳ ዋሻ ውስጥ ገብታ ገበሬዎች ይዘዋት እንደመጡና በጥርጣሬ እንደሚያያት ነገረኝ፡፡ አንዷ ደግሞ ውሻዋን ትታ መሄድ ከብዷት እንደነበርና ሃዘን እንደተሰማት አወጋልኝ፡፡ ‹‹እርጉሞች ናቸው›› የሚል ንግግርም ጨመረ፡፡ ከተጠቃሚ አገር ዜጎች በኩል በባህል ብረዛና በፖለቲካ ጥርጣሬ አሜሪካውያኑ በሚሰሩት ስራ ሁሉ ጣልቃ እንደሚገባባቸው ከበፊቱም ያስተዋልኩት ስለሆነ አልደነቀኝም፡፡ ‹‹በየዋህነት ለማገዝ አዝነው ነወይ የመጡት?›› ይላል መምህሩ፡፡ ጥሩ ነገሮች የጀመራቸው ሃላፊ ወይም ሰው ሲሄድ ይቆማሉ በሚለው ላይ ግን አሜሪካውያኑ ሲሄዱ የጀመሩት ስራ አለመቀጠሉን አስመልቶ አንዳንድ ምልከታን አውስቶልኛል፡፡ ተስማምተንማል፡፡ የዘላቂነት ችግር አለ፡፡ አሜሪካውያኑ የኛን ስራ ለዘላለም ሊሰሩልን አልመጡም - መንገድ ሊያሳዩን እንጂ!

በትምህርት ቤቱ እንደዱሮው ሁሉ ውኃና የረባ መጻዳጃ  የለም፡፡ ፈረንሳዮች በተለይም የእህት ከተማችን የብሉምኒል ከተማ ሰዎች ያሰሩት ሁለት ብሎክ ደረጃውን የጠበቀ መጸዳጃ አሁንም ጥቅም ሳይሰጥ አስር ዓመት አልፎታል፡፡ አጠቃላይ የዘመናዊ መጸዳጃው ስራ ባዮጋዝም ስለነበረውና የሱ ማሰሪያ ገንዘብ ስለተበላ ፕሮጀክቱ መቆሙንና ተማሪውና መምህሩ ደረጃዋን ባልጠበቀች አነስተኛ መጸዳጃ እየተሰቃየ አንደሚገኝ ታዝቤያለሁ፡፡

ከቆይታ በኋላ ዲሻንታልን የምታውቅ ተማሪ አገኘሁ፡፡ ተማሪዋ የ11ኛ ክፍል ተማሪና ስለትምህርት ቤቱ ታሪክ አሳይመንት ለመስራት የመጣች ነች፡፡ የዲሻንታልን ስራዎች አስታወሰች፡፡ ከአንዳንድ መምህራን ‹‹እሷ ምን ያልሰራችው አለ!›› የሚል በድፍን የመግለጥ ዘዴ የተሻለ ማብራሪያ ሰጥታኛለች፡፡ በፊት ዲሻንታል ላሰልጥን ስትል የሚመጣው መምህር በጣት የሚቆጠር መሆኑን ታዝቤ ነበር፡፡ መምህራኑ ምንም ባያስታውሱም አይገርመኝም፡፡

የእንግሊዝኛ መምህሯ ቀለም መጥተው ተዋውቃኝ ከሒሳብ መምህሩ ሙሉጌታ  ጋር ተነጋግረው በስድስተኛና ሰባተኛ ክፍል ባሉ ስድስት ክፍሎች ያሉ በእንግሊዝኛ ዝቅተኛ ውጤት ያላቸውን አምስት አምስት ተማሪዎች መረጡልኝ፡፡ ዓላማዬ በፊት ዲሻንታል እንደሰራችው አንድ ፕሮጀክት ዓይነት መስራት ነው፡፡ እነዚህን ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ጎበዝ ማድረግ፡፡ ወደ ትምህርት ቤቱ ከሄድኩበት ሰኔ 1 ቀን 2014 ጀምሮ እስከዛሬ ሰኔ 12 2014 ድረስ ለአምስት ክፍለጊዜያት በግል ቤተመጻሕፍቴ በራስ አበበ አረጋይ ተማሪዎቹ እየመጡ እንግሊዝኛ በተለይ አጠናኑ ላይ በማተኮር አስተምሬያለሁ፡፡ ማስተማር ብቻም ሳይሆን የመሐልሜዳው በጎፈቃደኛ ማይክ ‹ማይክ ፊድ› በሚል ያካሂደው የነበረውን የምገባ አሰራር ከዲሸንታል የማስተማር ሞዴል ጋር በማቀናጀት እያስተማርኩና እየመገብኩ ነው፡፡ ስመግብም በራሴ ወጪ ነው፡፡ ለወደፊቱም የምሰራው የአማራ የሠላም ጓድ ስራ እርዳታ ሳይቀበል በአካበባቢያችን ባለው ሀብት በመጠቀም የበጎፈቃድ ስራን እንዲሰራ እፈልጋለሁ፡፡ ገና በጥናትና ዕቅድ ላይ ያለ ቢሆንም፡፡

በዕለቱ ሁለቱ ጓደኞቼ መጥተው ትምህርት ቤቱን ጎበኘን፡፡ ቤተመጻሕፍቱ እጅግ ያመማረና ግዙፍ መሆኑን አየን፡፡ አስነባቢውን አቶ ዓለማየሁን ከአሁን በፊት በቤተመጻሕፍታችን ከሪጊስ ዩኒቨርሲቲ ላይብረሪ ዲን ከጃኔት ሊ ጋር በሰጠነው ስልጠናም ስለማስታውሳቸው ለመግባባትና ስለ ስራ ሁኔታ ለመጠየቅ ጊዜ አልወሰደብኝም፡፡ የበፊቶቹ የዲሻንታልን ስራዎችም አየን፡፡ ለማርች 8 የሴቶች ቀን ጄፍ ከተባለው በጎፈቃደኛና ከተማሪዎች ጋር የሰሩት ስዕልና የአንዳንድ ሰዎች እየጠፋ ያለ ትዝታ ብቻ ቀርቷል፡፡ ሕግ አጥንታ በአሜሪካ አየር ኃይል በመስራት ላይ የምትገኘው ዲሻንታል መንፈሷ እንዲደሰትና ‹‹ትምህርት ቤቴን እይልኝ›› የሚለው ጥያቄዋ እንዲመለስ እሰራለሁ፡፡ በብዛት አሜሪካውያኑ ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ ለጥያቄዎቻችን መልስ ስለማይሰጡን የሰራሁትን ለመንገር እቸገር ይሆናል፡፡

በትምህርት ቤቱ ያገኘኋቸውና ተማሪዎችን በሳምንት ሦስት ቀን ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት እየያዙ የሚመጡት ትጉህ መምህር በደብረ ብርሃን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የኮምፒውተር ስልጠና ዕድል ተሰጥቶ ብዙ መምህራን አንፈልግም ብለው እርሳቸው እየሰለጠኑ መሆኑን ነገሩኝ፡፡ እኔም ከእርሳቸው ጋር ኮሌጅ ሄጄ የስልጠናውን አሰጣጥ አየሁ፡፡ ከየትምህርት ቤቱ የተሰባሰቡ 16 መምህራን እየሰለጠኑ ነው፡፡ የኮምውተሩ ስልጠና ስላለቀ ከሰልጣኞቹ ጋር በመነጋገርም የስድስት ቀናት የእንግሊዝኛ አጠናን ስልጠና መስጠት ጀምሬያለሁ፡፡ ነገ ሰኞም ሁለተኛውን ክፍለጊዜ ይቀጥላሉ፡፡ አንዱ በር ሌላውን ይከፍታል፡፡

ከጠባሴ መድኃኔዓም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታዬ ብዙ ተምሬያለሁ፡፡ ይህን ሁሉ ችግር የምፈታው ግን የትኛውን ቦታ ብይዝ እንደሆነ አልገባኝም! ከወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት እስከ ከንቲባ፣ ከዞን አስተዳዳሪ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ይህን ሁሉ ችግር እያዩ ዝም ብለዋል፡፡ መምህሩ በደንብ እንዲያስተምር፣ ርዕሰመምህሩ በደንብ እንዲመራ፣ ተማሪው እንዲተጋ፣ ወላጅ ምግብ እንዲያቀርብ፣ ለወላጅ የስራ ዕድልና የገቢ ምንጭ እንዲመጣ!

 


በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...