2024 ፌብሩዋሪ 20, ማክሰኞ

እሁድ ከደብረብርሃን ካምፕ ወደ ኦሮሚያ የተመለሱት አማራ ተፈናቃዮች ምን ገጠማቸው?

 

እሁድ ከደብረብርሃን ካምፕ ወደ ኦሮሚያ የተመለሱት አማራ ተፈናቃዮች ምን ገጠማቸው?

መዘምር ግርማ

ደብረብርሃን

ረቡዕ፣ የካቲት 13፣ 2016 ዓ.ም.

 

ከብዙ ጭንቀት በኋላ በዕለተ ማክሰኞ ምሽት 4፡15  ስልክ ደወልኩ፡፡ የደወልኩላቸው የአንደኛው ተማሪ አባት ያውቁኝ ዘንድ የልጃቸውን ስም ጠርቼ ‹‹የእከሌ መምህር ነኝ›› አልኳቸው፡፡ አወቁኝ፡፡ ከእርሳቸው ጋር ልዩ ትዝታ አለኝ፡፡ አንድ ቀን ልጃቸውን ከዘመድ የተላከ 800 ብር ልሰጠው ብዬ ወላጅ አምጣ አልኩት፡፡ እሱም አንድ ወጣት ይዞ መጣ፡፡ እኔም ‹‹ይህ ወላጅ አይሆንም!›› ብዬ መለስኩት፡፡ ከሰዓት በኋላም አባቱን ይዞ መጣ፡፡ ገንዘቡን ያሰብነው ሃያ ልጆች አነስተኛ ስራ እንዲጀምሩ ለእያንዳንዳቸው 800 ብር በመስጠት ነበር፡፡ ልጆቹ ያንን ገንዘብ ይዘው ፎቶ ተነስተው ለላኩልኝ ወዳጄ እልካለሁ፡፡ ይህም ልጅ እንደዚያው ለማድረግ ወላጅ ማምጣት ነበረበት፡፡ ስለሆነም አባቱ መጡ፡፡ ‹‹ትምህርት አልማር አለኝ፡፡ ጠላብኝ፡፡ እኔ እንዲማርልኝ ነው የምፈልገው፡፡ አትስጡብኝ፡፡›› አሉኝ፡፡ እኔም ይህን በመረዳት ‹‹በቃ! ንግዱ ይቅር፡፡ ለእለት ችግርዎ ያውሉት›› ብዬ ተማሪውን ወደ ቤተመጻሕፍት አንብብ ብዬ አስገብቼ ከሌሎቹ ጋር ቀላቀልኩት፡፡ ገንዘቡን ለአባቱ ሰጠሁ፡፡ የተቀበልኩት ምርቃት አንድ ሚሊዮን ብር የሰጠሁ ያህል ነበር! ቀደም ብለን ለ33 ልጆች ካሰፋነው የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ አንዱ ተጠቃሚ የእርሳቸው ልጅ ስለነበርም ያን እንደውለታ ያስታውሳሉ፡፡ ብቻ ሁኔታው ልብ ይነካል! ልጃቸውም እንደአብዛኞቹ ልጆች በኦሮሚያ ሳለ በአማርኛ ስላልተማረ ከስድስተኛ ወይም ከሰባተኛ ክፍል ወደ አንደኛ ተመለስ ተብሎ ይሆናል ትምህርት የጠላው፡፡ ልጆቹ ካዩት ሰቆቃና ካሳለፉት ግፍ እነዲሁም እየገፉ ካሉት ከባድ ሕይወት አንጻር ትምህርት የሚያስወድድ ሁኔታ ውስጥ አይደሉም፡፡ ለማንኛውም በምሽቱ የደወልኩት ለእርሳቸው ነው፡፡

በየሚሄዱባቸው ቦታዎች ያሉ ሰዎች በስልካቸው እየደወሉ ብትመጡ እናደርስባችኋለን ያሏቸውን የግፍ አገዳደል ስለነገሩን ስጋት ላይ ነን፡፡ የፖለቲካውም ነገር ስላላስተማመነ ደህንነታቸውን የሚጠብቅ አካል ይኖራል ብሎ የሚያምን ሰው አልገጠመኝም፡፡ የደወልኩላቸው ተፈናቃይ ባኮ እንደገቡ ነገሩኝ፡፡ ባኮ ሸዋ ውስጥ ነው፡፡ ከአምቦ ይርቃል፡፡ የተጠለሉት በሳምንት ውስጥ ሊበጣጠስ በሚችል ከገበያ የሚገዛው ሸራ ውስጥ ነው፡፡ የተወሰዱት ከነቤተሰባቸው ነው፡፡ ምን እንደሚፈልጉ ስጠይቃቸው ‹‹ማሰብህ ብቻ በቂ ነው!›› አሉኝ፡፡ ‹‹እንመለሳለን ብለን በምንም ነገር አላሰብንም፡፡ ባለፈው ሳምንት በድንገት እዚያው ደብረብርሃን ውስጥ ወዳዘጋጁት ቦታ አስገቡን፡፡ አትወጡም ተባልን፡፡ ተከለከለ፡፡ እዚያም ውለን አድረን ከደብረብርሃን ጫጫ ድረስ የአማራ ክልሎቹ አመጡን፡፡ ከጫጫ የኦሮሚያው ‹መከላከያ› ተረከበን፡፡ አምቦ ዙሪያ ነው የምትሰፍሩት ብለው በመከላከያ አምቡላንስ ተቀበሉን፡፡ ጥሩ አቀባበል አደረጉልን፡፡ 15 ኪሎ ሩዝ ሰጥተውናል፡፡ አንተስ ደህና ነህ ወይ? ቤተሰብህስ?›› አሉኝ፡፡

እኔ ደህና መሆኔን ነገርኳቸው፡፡ ቤተሰቦቼ ያሉበት ሳሲት አቅራቢያ በድሮን የተመቱ ሰዎች መኖራቸውን ገልጬ የኔ ቤተሰቦች ግን ለጊዜው ደህና መሆናቸውን ነገርኳቸው፡፡

ልጃቸው እንደተኛና ጠዋት እንደሚያገናኙን ነገሩኝ፡፡

ግርታ ገባኝ፡፡  ለአሁኑም ቢሆን ፈጽሞ ሰላም ይሆናሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. እና የስራ ባልደረቦቼ ከደብረብርሃን ወደ አምቦ ስንሄድ የመጠቃት ወይም የሆነ አደጋ የማጋጠም ስጋት ጠብቀን ነበር፡፡ ስንደርስ ግን በቀለ ባየታ ቶለሳ የተባሉ አንድ ድንቅ የአምቦ አዛውንት መንገድ ላይ በስተቀኝ ስንሄድ አይተው እንግዶች መሆናችንን አውቀው ተቀብለው ምግብ ቤት አሳይተው ስለ ኢትዮጵያዊነት እያወጉልን ራት በልተን እስክንጨርስ ጠብቀው ወደ ማደሪያችን የሸኙንና በአምቦ በሰላም ከርመን የተመሰለስነው ትዝ አለኝ፡፡

ብሔራዊ ፈተናም በዩኒቨርሲቲ መሰጠት በጀመረ ዓመት ወደ ነቀምትና ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲዎች ለመፈተን የሄዱ መምህራን ሲመለሱ ቃለመጠይቅ አድርጌ ስለቆይታቸው ጽፌ ነበር፡፡ የጽሑፉ ርዕስ ‹‹ከወለጋ መርዷቸው ሲጠበቅ ተሸልመው የመጡት አማሮች›› የሚል ነበር፡፡ ‹‹ይህን ጽሑፍ ስታነቡ በአገር ፍቅር ስሜትና ኢትዮጵያ ተስፋ እንዳላት በመረዳት እንደማታለቅሱ ዋስትና አልሰጣችሁም!›› የሚል ማሳሰቢያም ነበረው፡፡

 

የዛሬው የስልክ ጥሪ እነዚህን ከአሁን በፊት የታዘብኳቸውን ምልከታዎች አስታወሰኝ፡፡ ከአሁን በፊት የታዘብኳቸው ጉዳዮች እንደሚያሳዩት መንግስት ከፈለገ ሰዎች በሰላም መኖር እንደሚችሉ ነው፡፡ አንድ አማራ መምህር ደምቢዶሎ ሄዶ ፈትኖ መምጣት ከቻለ ከደምቢዶሎ ወዲህ ባለ ቦታ ሌላ አማራ ለምን ይሞታል! ስደት፣ የግፍ ግድያ፣ አካል ጉዳትና ሌሎችም አሰቃቂ ድርጊቶች ለምን ይፈጸማሉ? መንግስት እነዚህ ከደብረብርሃን የተመለሱ አማራ ተፈናቃዮች በሰላም እንዲኖሩ ከፈለገ እንደሚኖሩ አስባለሁ፡፡ በአምቦና በባኮም የተደረገላቸው አቀባበል ይህንኑ ያሳያል፡፡

 

በደብረ ብርሃን ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ከሁለት መቶ ያላነሱ የኦሮሚያ ተፈናቃይ አማራ ልጆችን በሳምንት መጨረሻ ቀናት ስናስነብብ፣ ስናስተምር፣ ስንመግብና ስናበረታታ ቆይተናል፡፡ ይህን ልናደርግ የቻልነው ጊዜ ተርፎን አይደለም፤ ገንዘብም የለንም፤ አቅማችንም ውሱን ነበር - ነውም፡፡ የደብረብርሃን ህዝብ በሚያደርገው ድጋፍ፣ በቤተመጻሕፍት መረባችን ምክንያት የተዋወቅናቸው ወገኖቻችን በሚያደርጉልን እገዛ፣ የቤተመጻሕፍቱ አባላት የሆኑ ወጣቶች በድህነት፣ በኑሮ ውድነትና ተስፋ መቁረጥ እየተገረፉ በሚያደርጉት ልገሳና በጎፈቃደኝነት ነው፡፡ እነሱ ሳይመቻቸው ቅዳሜና እሁድን ከቤተክርሰቲያን ቀርተው፣ ስራቸውን አስታጉለው፣ እረፍታቸውን ትተው ለእነዚህ ልጆች አስበው ሲያስተምሩ፣ ሲመግቡና ሲያበረታቷቸው ቆይተዋል፡፡ አንድ ቀን አርባ ተፈናቃይ ልጆች ቢመጡ በቀጣዩ ዘጠና ይመጣሉ፡፡ ስድሳና ሰባ አማካይ የልጆች ዕለታዊ ቁጥር ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በአጠቃላይ ከወይንሸት ካምፕ ቤተመጻሕፍቱን ብዙ ልጆች አይተውታል፡፡ ከትልልቆቹ የቻይና ካምፕና ባቄሎ ካምፕ ተብለው ከሚጠሩት የሚመጡት ዉሱን ናቸው፡፡ ዋነኛው ምክንያት የቦታው እርቀት ነው፡፡ ለመጀመሪያ ዙር ተመላሽ ተብለው ሊሄዱ የተዘጋጁት ወደ ልዩ ጊዜያዊ ማቆያ ከገቡ በኋላ ዉጪ ባሉት ዘንድ የነበረውን መሸበር የምገልጽበት ቃል የለኝም፡፡ አሁንም ልገልጸው አልችልም፡፡ ለማናቸውም ሄዱ፡፡ ከሄዱ በኋላ ስለሚገጥማቸው ሁኔታ ያለን ስጋት ጽኑ ነው፡፡

 

እነዚህ ተፈናቃዮች በእጅጉ የሚያሳዝን ሕይወት ያሳለፉና እያሳለፉ ያሉ ናቸው፡፡ ደብረብርሃን እንዳይቆዩ እርዳታ ቆሟል ብለውኛል፡፡ እርዳታ ብቻም ሳይሆን ቤት ተከራይቶ ለመኖር አይችሉም፡፡ ሁሉ ነገር ታጥሯል፡፡ እስረኞች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ለአካል ጉዳተኛ ልጄ የተሰጠኝን ዊልቼር የሚገዛ ፈልግልኝ ብለው ልጃቸውን የላኩብኝ እናት አሉ፡፡ የሚገዛ ሰው ግን አላውቅም፡፡ ሌላዋ እናት እሁድ 10/06/16 ሦስት ልጆቻቸውን ይዘው መጥተው ለአንዷ ስለተሰፋው የደንብ ልብስ አመስግነው ወደ ወለጋ ሊሄዱ የመሆናቸውን ወሬ አስረድተውኛል፡፡ በብዛት አዋቂዎችን አላገኘሁም፡፡ የተሸበሩት ልጆች ግን ሁሉንም ጉዳይ ነግረውኛል፡፡ እኝህ እናት ስላሉት አማራጮች ስጠይቃቸው ደብረብርሃን መቅረት እንደ ወንጀል መታየቱን አልሸሸጉኝም፡፡ ወደ ወሎም ለመሄድ እዚያ ያሉትን ዘመዶቻቸውን አያውቋቸውም፡፡ አክስትም አጎትም ቢባሉ በደህናው ቀን ስላልጠየቋቸው የመሄድ ድፍረት የላቸውም፡፡ ልሂድ ቢሉስ መሳፈሪያ ይኖራቸው ይሆን? ልጆቹ ዛሬ ቤተመጻሕፍት ሊያነቡ መጥተው ነገ ስለመመለሳቸው እርግጠኞች አይደሉም፡፡  

 

የደወልኩላቸውን ተፈናቃይ ‹‹የወለጋዎቹስ እንዴት ሆኑ?›› ብዬ ጠየኳቸው፡፡ መረጃ የላቸውም፡፡ ደብረብርሃን ላሉት ደውዬ በደህና እንደገቡ ነግረውኛል፡፡ ወደፊትም እከታተላለሁ፡፡ መኪኖቹ ከአምቦና ወለጋ ወደ ደብረብርሃን ሲመለሱ ሌሎቹን በየተራ እንደሚወስዱ ትናንት ምሽት ያገኘሁት ልጅ ነግሮኛል፡፡ የሚመልሳቸው አንድ የትራንስፓርት ድርጅት ኮንትራት ይዞ ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡ በአሁኑ አካሄድ ቅድሚያ የተሰጣቸው እዚያ ተመን ኖሯቸው ግብር የሚገብሩትን ነው ተብሏል፡፡ የስም ዝርዝራቸውም ከዚያው ከኦሮሚያ ይኖሩበት ከነበረው ስፍራ መጥቶ ነው፡፡ ግብር የማይገብርና የሰው መሬት ተከራይቶ የሚያርሰውን ለጊዜው አልወሰዱም፡፡ በሂደት ይወስዱ ይሆናል፡፡ የደብረብርሃን ሰዎች ስጋት ግን እነዚህን መሬት ያላቸውን ሰዎች ለምን ወሰዷቸው የሚል ሲሆን፤ ምናልባት ወደፊት ሰላም ሲሰፍን መሬታችንን መልሱ ብለው በህግ እንዳይጠይቁ ይሆን ወይ የሚል ነው፡፡

የእነዚህ ተፈናቃዮች ጉዳይ አሁንም እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ሰላም ባልሰፈነበትና እርግጠኝነት በሌለበት ሁኔታ ባይሄዱ እጅግ ተመራጭ ነው! 

ልጆቹን በመጨረሻ ቀናችን ያልኳቸው ትዝ ይለኛል፡፡ ‹‹ሁላችሁም ስልኬን፣ ስሜንና የቤተመጻሕፍቴን ስም ያዙ፡፡ አዲስ ነገር ሲኖር ደውሉልኝ፡፡ አገር ሰላም ከሆነ ወለጋ ያላችሁበት ጋ መጥቼ ቤተመጻሕፍት እንከፍት ይሆናል!››

ብቻ ሰላም እንደናፈቀን እንዳንቀር!

 

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...