ቅዳሜ 29 ኦገስት 2015

ባለቤት-አልባው ቤተ-መንግስት



የጉዞ ማስታወሻ

በመዘምር ግርማ
አምሃየሱስ 1733 በመሰረቷት በአንኮበር ያለው ቤተመንግስት ሎጅ የዛሬው መዳረሻችን ነው፡፡ በመግቢያው በር አካባቢ ሆነን ወደ ዋናው ቤተመንግስት የሚያወጡ 468 ደረጃዎች እንዳሉ ተነገረን፡፡ እንሄድባቸዋልን ብላችሁ ነው? በሌላ ከብረት የተሰራ መደገፊያ አጥር ባለው መንገድ ሄደን ግቢውን ጎብኝተን ስንመለስ ነው የምንወርድባቸው፡፡ ሾላ፣ ጎተራ፣ የፈረንሳይ ቆንስላ፣ የእንግሊዝ ቆንስላ የሚባሉ ስፍራዎች እንዳሉ ተነገረን፤ አየናቸውም፡፡ ጋጀሎ የተባለው የጣሊያኖች ቆንስላ ግን ከስፍራው አራት ወይንም አምስት ሰዓት ያስኬዳል፡፡ የራቀበት ምክንያቱ መልዕክተኞቹ የነዋሪውን ሃይማኖት እንዳያስቀይሩ ነበር አሉ፡፡ በዚያ ስፍራ ለተቀበረው ጣሊያናዊ የእጽዋት ተመራማሪ መታሰቢያ የባህላዊ መድሃኒቶች ምርምር በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲና በጣሊያኖች ይካሄዳል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥንም የሚለካ ማሽን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቤተመንግስት ሎጁ ግቢ ውስጥ ተክሏል፡፡አልዩ አምባ፣ ደብረሲና፣ እመ ምህረት እና ወፍ ዋሻ በየገለጻው መሃል የምትሰሟቸው አጎራባች ስፍራዎች ናቸው፡፡
በአንኮበር ወረዳ 96 አብያተ ክርስቲያናት ሲኖሩ 56 ጥንታዊ ናቸው፡፡ በቤተክርስቲያኑ ሙዚየም አስር አስር ብር ከፍለን በሶስት ዙር እንጎበኝ ያዝን፤ ከመግቢያ ክፍያው 25 ብር በተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡ ሙዚየሙ አነስተኛ ቤት ሲሆን ዘመናዊ ሙዚየምም በአቅራቢያው እየተገነባ ነው፡፡ በየቤተክርስቲያኑ እና እቃ ቤቱ የተበታተኑትን ቅርሶች አሰባስቦ ለማስጎብኘት ጥሩ መላ ተዘይዷል፡፡ በሙዚየሙ ካየናቸው ውስጥ የብርና የነሃስ መቋሚያዎች፣ የወርቅ፣ የብርና የነሃስ ዘውዶች፣ ባለአምሰት መን ነገስታቱ የሚለብሱት ድርብ ብልኮ፣ በፈረስ ሲሄዱ እንዲመቻቸው የሚለብሱት ተነፋነፍ መሰል በእጅ የሚሰራ ባለወንበር ሰናፌል ሱሪ፣ ጥብቆ እና ዙሪያው ብር የሆነ የሞሰበወርቅ ልብስ ይገኙበታል፡፡ ከአድዋ መልስ የሞተው የምንሊክ ፈረስ የአባዞቢል ልብስ /ግላሱ እና ሰገጡ/ 118 አመቱ ነው፡፡ እሱንም አይተናል፡፡
ምን ይሄ ብቻ! እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ ከአሜሪካ ያስመለሱት የአጼ ምኒልክ የእጃቸው ዳዊት፣ ራስ መኮንን ያስመጡት እና 1928 አንኮበር ሙሉ በሙሉ በጣሊያን ስትመታ ጥቃት ደርሶበት የተሰነጠቀ የብር ደወል፣ አድዋ ደርሶ የመጣ ንጉስ ሳህለስላሤ ከህንድ ያስመጡት ልብሰ-ተክህኖ /መጎናጸፊያ/ በቀርቀሃ መያዣ የሚያዝ እና እዚያው የሚሰራ 15 ሰው የሚያጠላ ድባብ፣ 15 ኪሎ የሚመዝን የአጼ ምንሊክና የእቴጌ ጣይቱ የወርቅ ሊሻን እና የወርቅ ጥላ፣ዳር ዳሩ ወርቅ የሆነ የንጉስ ሳህለስላሴ የወርቅ ሰናፊሊ ቦታ ቦታቸውን ይዘው እዩኝ እዩኝ ይሏችኋል - እናንተ መሄዱን ከያዛችሁት! የወሌ ብጡልና የሌሎችም ፎቶዎች፣ ጣሊያን ያቃጠለው ቤተክርስቲያን የሸክላ ጉልላት እና የብር ከበሮ ሌሎቹ የስፍራው ስጦታዎች ናቸው፡፡ ዘማቾች ወደ አድዋ ሲሄዱ ሁሉም ነጭ ልብስ ለብሶ የቤተክርስቲያን ካህናት አረንጓዴ ሱሪ በቀይ ገበር ይለብሳሉ- ማነታቸው እንዲለይና ቅዳሴው እንዳይታጎል:: የካህናቱ ልብስ ታዲያ በክብር ተቀምጧል፡፡
ጥንታውያኑ አባቶች ከዕጽዋት ቀለም ሰርተው የጻፏቸውን የብራና መጻህፍት አይተናል:: አቡሻሃር (የዘመን አቆጣጠር የሚያሳይ መጽሐፍ) ስንክሳር፣ ግብረ ህማማት እና ፈትሉን ሰም ነክረው እንደሸራ ተጠቅመው የሰሩትን ስዕል አድንቀናል፡፡ የካቲተት 16 1888 በአውሳ ግምባር የተማረከን መሳሪያ እና ምንሊክ በአድዋ የያዙትን መሳሪያ አይተናል፡፡ የአጼ ምንሊክን መሳሪያ ለመንካት ሁሉም ተሸቀዳደመ፡፡

አዋጅ ለማወጅ ምንሊክ ገበያ አቁመው ነበር፡፡ እዚያ ገበያ ላይም ነጋሪት የሚጎሰምበትን ስፍራ አይተናል - ከሙዚየም መልስ ፡፡ 42 ነጋሪት በወቅቱ የነበረ ሲሆን አብዛኛው በያገሩ ተበታትኖ አሁን አንዱ ብቻ ነው ያለው፡፡ ህዝቡን ሰርቶ ለማሰራት ንጉስ ሳህለስላሤ ተሸክመው 10 ኪሜ ርቀት ያመጡት 2 ሜትር 60 ሴንቲሜትር የሚሆን ጠፍጣፋ ድንጋይ ጣሊያን ባነደደው የመድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን ፍርስራሽ በረንዳ ላይ አይተናል፡፡ ጉድ በሉ ብርታታቸውን!
ምንሊክና ጣይቱ 1875 .. በአንኮበር ነው የተጋቡት፡፡ የአንኮበርን 1928 ጣሊያን ባላባቶቹን ልምታ ብሎ በከባድ መሳሪያ ካቃጠለው በኋላ ጎረቤላ ከተማ ተመሰረተች፡፡ አዲስ ዓለም፣ እንጦጦ እያሉ አዲስ አበባ የገቡት ምንሊክ ትተው የሄዱት ስፍራ አንኮበር ላይ ሎጁን መስራት የተቻለው የቀድሞ ስፍራው ምን ይመስል እንደነበር ሰው በማጠያየቅ እና ፎቶ በማየት ነበር፡፡ የቀድሞውን ቤተ-መንግስት ስፍራዎች መለየት ተችሎ በግል ባለሃብት ለምርምር ቁፋሮ እንዲያመች ተብሎ ሎጁ ከምድር ሁለት ሜትር ከፍ ብሎ የተሰራ ነው፡፡ አሁንም ሎጁ ያረፈበት ምድር በተመራማሪዎች ይበረበራል - ፍቃድ ይዘው ከመጡ፡፡ ከዚህ ሰገነት በረንዳ ላይ ሆኖ እስከ አፋር ይታያል አሉ፡፡ ጠጅዎን እየኮመኮሙ መቆጣጠር ነው የአፋሮችንና የአርጎቦችን አገር! ታሪክ፣ ባህል እና ተፈጥሮ ተሸጠው እንጀራ ሲሆኑ በአይናችን አየን፡፡
በመጠኑም ቢሆን ግን አሁን በማህበረሰብ አቀፍ ኢኮቱሪዝም የአካባቢው ህዝብ ይጠቀማል፡፡ የተለያየ ቀናትና ሰዓታት ርዝማኔ ያለው የእግር ጉዞ ወደ ታሪካዊ እና ሰው ሰራሽ ስፍራዎች ይደረጋል፡፡ በዚህን ጊዜ አርሶ አደሩ መንገድ ይመራል፡፡ ፈረስ በማቅረብ፣ እቤቱ ለሚመጡት ጎብኝዎች የግብርና ስራ በማሰራትና የምግብ ዝግጅት ላይ በማሳተፍም ያስተናግዳል፡፡ በሎጁ ግቢ ውስጥ ያለው ባህላዊ ቤት የገበሬው ቤት ሞዴል ሲሆን በገበሬው ቤት መሄድ ለማይችሉ ጎብኝዎች 20 ዶላር የሚችለውን ያሳያል፡፡ 20 ዶላር ፊደል መማር፣ በኩራዝ መጠቀም፣ ቡና በጉልቻ ማፍላት፣ ጥጥ መፈልቀቅ፣ በመቃ እሳት ማንደድ እና ገብስ በሙቀጫ መሸከሸክ ይቻላል፡፡ ፡፡
‹‹የዘንድሮ የመስቀል በዓል በስፍራው ተከብሯል፤ ከበዓል አዘጋጅ ድርጅቶች ጋር በስፍራው አከባበር የተደረገ ሲሆን በዚህም ምክንያት የጎብኝው ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል፡፡ መንፈሳዊ ጉዞ አዘጋጅ ማህበራት እና ብዙ ጎብኝዎች ወደ ስፍራው እንዳይመጡ ዋነኛ ችግሩ የመንገድ ነው፡፡ ይህን ቦታ ከጠላት ለመሸሸጊያነት እንጅ ለቤተመንግስት አልነበረም ነገስታቱ ያቋቋሙት፡፡ ስፍራው የተዳከመው የዘይላ መንገድ ሲቆም ቢሆንም አሁንም በተሸለ መንገድ መታወስ ይችል ነበር፡፡ ለልምድ ልውውጥ ከሰሜን ሸዋ ውጭ እንሄዳለን፤ ሰሜን ሸዋ ውስጥ አለመሄዳችን ግን ድክመት ነው›› ያሉኝ አቶ ማሙሽን የዞኑን ቱሪዝም ለማቀናጀት የባህል ሃላፊዎች ቢያግዟቸው እላለሁ፡፡ ሱናርማ እና በጋ ቱርስ የተባሉ ድርጅቶች ወፍ ዋሻ ላይ የጀመሩት የቲሪስት ስፍራዎችን የማጎልበት ስራ መጓተቱ አንድ ችግር ነው ስለተባለ ምን ነካችሁ በሏቸው፡፡ ለጠየኳቸው ሁለት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነው ይህን ያወቅሁት፡፡


‹‹ወርቅ የተነጠፈበት የሚመስለኝ የምንሊክ አገር እንዲህ ያለ ነው ለካ›› ያሉ አንድ ተጓዥ አስቀውኛል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በምንሊክ ጊዜ ያመጡት የስልክ መስመር መከላከያ ስላልነበረው መብረቅ መታው፡፡ ስልክ መጀመሪያ እዚህ ጀምሮ አሁን ግን መጨረሻ ስልክ የገባለት ስፍራ ነው - ይታያችሁ የእድሉ ነገር፡፡ የጎብኝው ቁጥር ማነሱ እና እንዲያውም የውጭ ዜጎች ያው አልፎ አልፎም ቢሆን ስፍራውን ማዘውተራቸው የታሪኩ ባለቤቶችስ የታሉ ያስብላል፡፡ ዋጋው አባሯቸው እንዳይሆን የሎጁ ሃላፊዎች ቢያስቡበት ምናለ? አልጋና ዋና ዋና አገልግሎቶችን ብትጠይቁ ጨዋታው በዶላር ነው፡፡ አካባቢውን ማገዝ ካለባቸው መስሪያ ቤቶች አንዱ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሲሆን በባህል ማዕከል ሲምፖዚየም ብቻ ነው የቱሪዝም ባለድርሻዎችን የሚጠራው - ከዚያ ዝም ይላል - ከስፍራው ያገኘንው ወቀሳ ነው፡፡ ምንሊክ ያስተከሉትን የመጀመሪውን ባህርዛፍ ቆሞ አየንው፡፡ ባህር ዛፍ ስል የቤተክርስቲያኑ የሙጋድ እንጨት ፈላጭ የነበሩት ዘውዴ ነሲቡ ትዝ አሉኝ፡፡ እንደ እርሳቸው ዓይነት ስራ በመስራት የሚተዳደሩት አባት ለመጸወታቸው ጎብኝ ‹‹የነፍስ ገበያ ይሁንላችሁ›› እያሉ ይመርቃሉ፡፡
በላ ልበልሃ የሚባባሉበትን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አይተን ምንሊክ ከቴዎድሮስ የተማሩትን ታክስ አስተዳደር ተግባራዊ አድርገው እንደነበር ሰማን፡፡ ምንሊክ ቴዎድሮስ ሲሞቱ ሃዘን አውጀው ካላዘናችሁ እኔ ጫካ ሄጄ አዝናለሁ ብለው ነበር አሉ ለጋሻ ጃግሬዎቻቸው፡፡ ያውቃሏ ውለታቸውን!
የአድዋ ድልን ለመዘከር በዚህ ወር ልንሄድባቸው ካሰብናቸው ስፍራዎች አንዱና የመጀመሪያው የነበረው አጼ ምንልክ የተወለዱበትና የጎራው ገበየሁ አጽም ያረፈበት አንጎለላ ነበር፡፡ የካቲት 16 እሱን ጎብኝተን ቀጥሎ እቅድ የያዝንለትን ሌላ ከደብረ ብርሃን አቅራቢያ የሚገኝ ስፍራ ልቼን ለመጎብኘት እንዳሰብንው ሳይሳካ ሲቀር የአንኮበር ጉዞ እንዳይታጎል ሰግተን ነበር፡፡ ሦሥተኛው ስፍራ አንኮበር፣ የካቲት 23 ቀን 2007 .ም፣ ሰኞ፣ ስራም ዝግ ስለሆነ ብዙ ሰው ይሄድበታል ብለን አስበን የነበረ ቢሆንም በየምክንያቱ አራት ሰውም ለማሰባሰብ ከብዶን ባሳር እኔ፣ ይድነቃቸው ሶሎሞን፣ ተክለሃይማኖት ገብረማርያም እና ጌጤ ፈለገ ከጠዋቱ 120 ከደብረብርሃን መናኸሪያ መኪናው በእዬዬ ተነስቶልን ጎረቤላ ከተማ 310 ላይ ደረስን - 42 ኪሜ የኮረኮንች መንገድ ጉዞን አጠናቀን፡፡
ከጎረቤላ ከተማ ወደ አንኮበር አጭር የእግር ጉዞ ስናደርግ አምና በአሜሪካ ሰላም ጓድ ድጋፍ ከየትምህርት ቤቱ የመጡ ታዳጊ ሴት ተማሪዎችን ይዘን ወደዚህ ስፍራ ያደረግንው ጉዞ ትዝ አለኝ፡፡ አምና ማርቸዲሳችን ተቀርቅሮበት ከነበረው ስፍራ በታች ስንደርስ አንድ በባንዲራ ያሸበረቀ መኪና ይመጣል፡፡ እንዲያሳፍረን ስንለምን አቁሞልን ስንገባ መኪና ውስጥ ያሉት የማውቃቸው ሞጃዎች ኖረዋል፡፡ በእዚህ ዕለት እዚህ ስፍራ በፍጹም አልጠበቅኋቸውም ነበር፤ ምክንያቱም አገር በቀል ቱሪዝም ብዙም አልተለመደምና ነው፡፡የሞጃ ባህል እና ቱሪዝም /ቤት የሚያስተባብረው የአገርህን እወቅ ክበብ በአንኮበር ቤተመንግስት አብሮን ጉብኝት ሲያደርግ ሁላችንም ተደስተናል፡፡ ለጉብኝት በመነሳሳታቸው አድንቁልኝ፡፡ ግን ከሞጃ እውነት አስር መኪና ጎብኝ ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ ወደ ጉብኝቱ ያልሄደው ሰው በዚያን ቀን ምን ሰራሁ ብሎ ራሱን ቢጠይቅ መልሱ ምን እንደሚሆን እንጃ፡፡ እባካችሁ ሞጃዎች ባህል ወዳዱን ልጃችሁ አቶ ሃይሌ ገብረማርያምን ተጠቀሙበት፡፡ እንደ አንኮበሩ አስጎብኛችን ገለጻ ‹‹ታሪክ ከጓሮ ነውና የሚጀምረው፡፡›› ከአርብ የካቲት 27 እስከ እሁድ የካቲት 29 ደግሞ በመንዝና ተጉለት የዩኒቨርሲቲያችን የባህል ማዕከል አባላት የሆንን ከመቶ በላይ ሰዎች የምናደርገውን ጉዞም ከዚህ ቅጥ አምባሩ ከጠፋበት ጽሑፌ በተሻለ እንደማስጎበኛችሁ ቃል ልግባ!
በዚች ግጥም እንሰናበት -
እንጦጦ አፋፉ ላይ ብርድ እንዳይበርደን፣
እግዚአብሔር መርቆ ጣይቱን ሰጠን፡፡

ዩኒቨርሲቲያችን ውሎ ይግባ፤ ላልይበላን አሳየን!


የጉዞ ማስታወሻ (ተጻፈ በመዘምር ግርማ)
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ላዘጋጀው ጉዞ ቅዳሜ፣ ሐምሌ 26፣ 2006 ዓ.ም. ከደ/ብርሃን ከጠዋቱ 1፡30 ለመነሳት ቀጠሮ ተይዞ ነበር፡፡ ሆኖም በዕለቱ ከጠዋቱ 4፡15 ሸዋሮቢት ልንቃረብ በሚገባን ሰዓት ላይ ከሰማያዊ ሆቴል አንደኛ ፎቅ በመስታዎት ወደ ውጭ የካፊያ ውስጥ ትዕይንት እያየን የየነፍሳችንን እንፈጽም ነበር፡፡ አንዱ ‹‹ከትግርኛ በፊት በምንጃር አማርኛ ተናጋዎች ነበሩ፡፡›› ሲል ሌላው ደግሞ ‹‹ኃይለስላሴ የአማራን የበላይነት አስፍኗል፤ የአማርኛ መስፋፋት የአማራይዜሽን መስፋፋት ነው፡፡›› ብሎ ምላሽ ሲሰጥ መኪናችን ደግሞ ሕገ-ጎዳና ተላልፈሃል ተብሎ ተይዟል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ጉዞው አሁን ድረስ መቆየቱም ያስቀጣ ነበር፡፡ የትራፊክ ፖሊሷ ‹‹በሉ ቶሎ ሂዱ›› ብለው ነው መሰለኝ አውቶቡሱ አፍንጫውን ወደ አስመራ በር አሾለ፡፡ ከግምሽ ሰዓት ገደማ በሌላ አውቶቡስ ቀሪዎቻችን ተከተልን፡፡ የሰዓት አለመከበር ይታሰብበት! ከሰባ የሚበልጥ ሰው ከሶስት ሰዓት በላይ ሲባክንበት በዚህች አገር ምጣኔ ሐብት ላይ ምን ዓይነት ጥላ ያጠላ ይሆን?
የዳኛቸው ወርቁን ስነ-ጽሑፋዊ ርስቶች ጣርማበርን፣ ደብረሲናን፣ አርማንያን፣ አብዲላቅን ወ.ዘ.ተ. አልፈን የሰንበቴንና የሸዋሮቢትን ሁለመና እያደነቅን ሳለን አይኔ በመስኮት አማትሮ መንገድ ዳር የሚሰግዱ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ቢያይ ‹‹ይህች አገር በግሸኖች ጸሎት ነው የቆመችው›› የሚለው አያቴ ግሸን ተሳልማ የመጣች ሰሞን የነገረችኝ ምልከታዋ ላይ እነዚህንም ሙስሊሞች ጨመርኩ፡፡ አንዱ የቡድናችን አባል በስልክ ስለ ደምወዝ ጭማሪ በምትሐተ መስኮት የተወራው ደረሰኝ በማለቱ የብዙው ተጓዥ አትኩሮት ላፍታ ወደ ገንዘብ ሄደ፡፡ ‹‹አላልኩህም ዱሮም ከ35-40 በመቶ እንጂ ከዚያ በላይ ሊጨመር አይችልም፤ ከየት ያመጣል መንግስት?›› የሚል አስተያየትም ተደመጠ፡፡
ወደ ቆላው እየገቡ ሲሄዱ የህዝቡ አኗኗር፣ አሰፋፈርና አጋጋር ከደጋው መለየቱን ይታዘቧል፡፡ ውሃ በጀሪካን ቀድተው ለረጅም ርቀት በጀርባቸው ከደረታቸው ጋር በጠፍር/በገመድ/ አስረው የተሸከሙትም ሆኑ በአህያ የሚያጓጉዙት እንደ ደብረ ብርሃን ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ያገኙ ዘንድ ጸልዩ፡፡ አንድ ገጣሚ የቡድናችን አባል ‹‹ግመሉን ከሩቁ ሳየው የደረቀ ግንድ ይመስለኛል›› ብሎ የተረበበትን የበርሃውን መርከብ አይቼ ሳልጠግበው መኪናው ሽው ይልብኛል፡፡ ‹‹ዋጋው ሰላሳ ሺህ ብር ነው›› ማለትን ሰማሁ፡፡ አልደነቀኝም፤ ላም ነው፣ ፈረስ ነው፣ ፍየል ነው፤ መች ይበዛበታል? እናንተዬ የኋላ እግሮቹ ሁለት ጊዜ ሳይታጠፉ አይቀርም፡፡ ያገሬ ሰው የግመሉን ስም እየረሳው ‹‹ያ እንትኑ›› እንደሚል ሳወሳ ቆላው ያገሬን ሰው ዘንግቶት እርሱም ቆላውን ዘንግቶ እንደኖረ እና እኔን ልጁን እንደራሴ አድርጎ እንደላከኝ ስናገር በኩራት ነው፡፡
በከሚሴ ካገኘኋቸው አምስት በአስራዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ካሉ ወንድ ልጆች መካከል አራቱ ኦሮምኛ ይናገራሉ፡፡ ልጆቹ እንደነገሩኝ ከሆነ ሁሉም በጫማ ማስዋብና የውሃ መያዣ እቃ በመሰብሰብን በመሸጥ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ‹‹ኑ ምሳ እንብላ›› ስላቸው ‹‹አይ እኛ የክርስቲያን አንበላም›› ሲሉኝ ከተማቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚበዙበት መሆኑን ስለተረዳሁ ቅር አላለኝም፡፡ አህመድ የተባለው ልጅ መኪና ገጭቶት እነደሚያውቅ ሲነግረን አንዱ መምህር ሊያሳክሙት ሐኪም ቤት ቢወስዱት የቁስል ፕላስተር ባለመኖሩ የማሳከም ጥረታቸው አልተሳካም፡፡ ይሄኔ እኮ ሌላኛው ሐኪም ቤት የፕላስተር ክምር የመደርደሪያ በር አላዘጋ ብሏል፡፡ እነሆ አንድ ቁም ነገር ለትዳር ፈላጊዎች - ሐኪም ቤቱ አካባቢ አንዲት የጥቁር ቆንጆ ልጅ አለች ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ሁለቱ የኦሮሚያ ባንኮች እዚያ ቅርንጫፋቸውን ስለከፈቱ ልማቱን ማፋጠናቸው አይቀርም፡፡ ጫት ያገሩ ጌጥ ነው፡፡ እንደ ደብረ ብርሃን በማይታይ መያዣ ተይዞ አይኬድም፡፡ እንደ ችቦ ይዞ መሯሯጥ ነው፡፡ ምናለ ጫትን ግን አንድ ብንለው!
በዚህ የክረምት ወቅት፣ በነፋሻው አየር፣ ሰው ተራርቆ በተቀመጠበት በምቹው የዩኒቨርሲቲያችን መኪና ባይሆን ጉዞው አንዴት አንደሚከብድ! እንደኔ በመኪና ከተወሰኑ ሰዓታት በላይ ሄዶ የማያውቅ ሰው ይሸበር ነበር፡፡ ‹‹ሹፌር ሊጣላኝ ነው›› ብዙም አላልንም፡፡ ከሸዋ ስወጣ እና ከአዲስ አበባ ከሁለት መቶ ምናምን ኪሎሜትር ርቀት በላይ ስሄድ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ጭው ያለ ገደል አፋፍ ላይ ሆኜ ቁልቁል ሳይ የመኪና ዘዋሪነት በዓለም ትልቁ ሙያ መሆኑን እጅ ወደላይ ብዬ እቀበላለሁ፡፡ ከምቦልቻን ሳስብም እኛም ‹‹ምራቂት›› ካምፓስ ይኑረን በማለት ሃሳቤን በትህትና አቀርባለሁ፡፡
እኔ እስካየሁት ድረስ ወልደያ ሰዎች በተራሮች ተከበው ሲጨፍሩ የሚያነጉባት ጥሩ ከተማ ነች፡፡ በሃምሳም በመቶም ብር አሳደረችን፡፡ታሪክን ለማሰብ ጣይቱ ብጡል ትምህርት ቤት፣ ገነተ ልዑል ሆቴል የመሳሰሉትን አቅፋ ይዛለች፡፡ በማግስቱ እሁድ ሐምሌ 27 ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ጉዞ ወደ ላሊበላ ሆነ፡፡ ወደ ኮረኮንቹ መንገድ ስንገባ ቁንጮ ያለው ጥብቆ የለበሰ ትንሽ እረኛ ልጅ አየሁ፡፡ ምን አልባት እንደ አንዳንድ የተጉለት እረኞች ምሳውን አልቋጠረ ይሆናል፡፡ አዋዋሉ አያሳስብዎትም፡፡
ዋ! ላልይበላ!
እንደተለያዩ መዛግብት እና አፈታሪኮች ከሆነ ንጉስ ላሊበላ ይህን ስም ያገኘው በህጻንነቱ ንቦች እርሱ የነበረበትን ስፍራ ይከቡ እንዲሁም አፉ ላይ ያርፉ ስለነበር ማር እየመገቡት ነው ለማለት የአገውኛውን የ‹ማር› አቻ ቃል ‹ላል›ን በመጠቀም ላልይበላል ተባለ፡፡ በልጅነቱም የአባቱን ስልጣን ለማግኘት ባደረገው ጥረት አማሮች ረድተውት ነበር ይባላል፡፡ ውለታችውን የከፈላቸውም ከታች እስከ ላይ ስልጣኑን ለእነርሱ በመስጠት ነበር፡፡ ቤተ-መንግሰቱን በሙሉ አማሮች ሲሞሉት ቋንቋቸውም የቤተመንግስት ቋንቋ ወይንም ልሳነ ንጉስ ሆነ፡፡ እነሆ እስካሁም የአማሮች ቋንቋ ከአማሮችም በዘለለ ሌሎችም እየተጠቀሙበት የፖለቲካ ስራ ማከናወኛ ቋንቋ (political lingua franca) ሆነ፡፡ ለምሳሌ በአጼ ዮሐንስ አራተኛው ቤተ-መንግስት የንግግርም ሆነ የጽሑፍ ቋንቋ በመሆን አገልግሏል፡፡
ፕሮፌሰር ስርግው ሐብለስላሴ Ancient and Medieval Ethiopian History በሚለው መጽሐፋቸው ላይ የቅዱስ ላሊበን ገድል ዋቢ አድረገው እንደሚነግሩን ላሊበላ ‹‹የመንግስቱን ገንዘብ በፍጹም ለግሉ የማይጠቀም፣ ከሕዝቡ በቀረጥ መልክ የሚሰበሰበውንም ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለሕዝባዊ ስራ ብቻ የሚያውል ንጉስ ነበር፡፡ በእርግጥም እርሱ ኑሮውን መምራት የሚመርጠው እየሰራ ራሱን እንደ ገበሬ ደብቆ በሚሸጣቸው ከዕደ -ጥበብ ስራዎቹ በሚያገኘው ገንዘብ ነበር›› (279)፡፡ ላሊበላ የመንግስቱን ገንዘብ ለግሉ ያለመጠቀሙንና የራሱን ስራዎች እየሸጠ መተዳደሩን ሳስብ ከላሊበላ መልስ ለመጀመሪያ ጊዜ በጎበኘሁት በአንኮበር ቤተመንግስት ከመድሃኒዓለም ቤተክርስቲያን ፍርስራሾች መካከል የቤተክርስቲያኑ ደረጃ ላይ ደረጃ ከተሰራባቸው ድንጋዮች መካከል ያየሁት ንጉስ ሐይለመለኮት ከ5 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ተሸክመው ያመጡት 2 ሜትር የሚደረዝም ድንጋይ ትዝ አለኝ፡፡ ድንቅ አርዓያነቶች አይደሉምን?
ላልይበላል፤ ላልያበላል
ላሊበላ ከተማ ገባን፡፡ እኔና የቡድናችን አባላት በሙሉ ዕድለኞች ነን ማለት ይቻላል፡፡ ዕድሜ ለዩኒቨርሲቲያችን ይህን ድንቅ ቅርስ ለማየት በቃን፡፡ ዋልያ ባር፣ ሬድ ሮክ ሆቴል፣ ስሊና ባርና ሬስቶራንት፣ ሻሎም ካፌ፣ ቤተ-አብርሃም ሆቴል፣ ሮሃ ሆቴል (ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ያሰሩት) ፣ አማን ሆቴል፣ ላል ሆቴል፣ ሰቭን ኦሊቭስ (እቴጌ መነን ያሰሩት) የስጦታ ዕቃ ሱቆች፣ ሱፐርማርኬቶች፣ የአየር መንገድ መስሪያ ቤት እና ሌሎችም በትንሿ ባለሁለት ቀበሌ ከተማ ያሉት ድርጅቶች ሁሉ ላልይበላ የሰራቸው ቅርሶች ባይኖሩ ይኖሩ የነበረ ይመስላችኋል?
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ካስተማርኳቸው በ2004 ዓ.ም. ከተመረቁ የእንግሊዝኛ ተማሪዎች የተወሰኑት እዚያ ላሊበላን በማስጎብኘት እንደሚተዳደሩ በስፍራው ያገኘሁት የቀድሞ ተማሪዬ ሳሙኤል ኮርሜ ነግሮኛል፡፡ ላል ይበላል ብቻ ነው ታዲያ የዚህ ንጉስ ስም መሆን ያለበት? ለእኔ ላል ያበላል ቢባልም ያስኬደኛል፡፡ ለኛ ለጎብኝዎች መንፈሳዊ ላል፣ በማስገብኘትና ስፍራው ላይ ለጎብኝዎች የተለያየ አገልግሎት በመስጠት ለሚተዳደሩት ስጋዊና ነዋያዊ ላል ይመግባል፡፡ በላሊበላ የአብነት ተማሪ የሆነ ትንሽ ልጅ አግኝቼ ‹‹15 የአብነት ትምህርት ቤት ክፍሎች አሉ፡፡ በያንዳንዱ ክፍል 40 ተማሪ ይማራል፡፡ ሴቶቹ ቀን ቀን ተምረው ማታ ወደቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ ወንዶቹ ግን ራቅ ካለ ቦታ ስለመጣን እየለመንን እንበላለን፡፡ ሕዝቡ በጥሩ ሁኔታ ይዞናል፡፡ ባጅም አለን፡፡ ላስጎብኛችሁ እንዴ?›› ብሎኛል፡፡
ወደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅጽረ ግቢ ስንጠጋ መግቢያ በሩ እንደማንኛውም ቤተክርስቲያን እንጅ ለየት ባለ መልኩ አልተሰራም፡፡ ከውጭ ሲታይ በቃ የአንድ መለስተኛ ከተማ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ነው የሚመስለው፡፡ አይናችንን ወደ ግቢው ስናማትር ግን ሁለት ትላልቅ ነጫጭ ጣራዎች በአየር ላይ አራት ግዙፍ የብረት ምሰሶዎች ተደግፈዋቸው ቆመው አየን፡፡ ወደግቢው ስንገባም የደብረ ብርሃኑ ቡድን እስኪሰባሰብ ድረስ አንድ ዲያቆን ሶስት ሴቶችንና አንድን ወንድ የውጭ ዜጎች ሲያስጎበኝ እንከታተለው ጀመር፡፡ ለዛ ባለው እንግሊዝኛ ከሞላ ጎደል ‹‹This is the first or the North Eastern group of rock hewn churches that were built by King Lalibela. This is the trench built to connect the eleven churches, but it is not working at this time. ›› ይህ አስጎብኝ ሲያስጎበኝ እንደሰማሁት ከሆነ የመጀመሪያው እና ትልቁ ቤተክርስቲያን ቤተ መድሃኒዓለም ከውጭ ካሉት 34 አምዶች ውስጥ ግማሾቹ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በተከሰተ የመሬት መቀጥቀጥ ወድቀው አዳዲስ አምዶች በተመሳሳይ ድንጋይ ታንጸዋል፡፡ እነሆ የደብረብርሃኑ ቡድን ከአስጎብኝው ጋር በሂሳብ ይከራከር ጀመር፤ ከስንት ጭቅጭቅ በኋላም ተስማምቶ ጉብኝታችን በይፋ ተጀመረ፡፡
ቤተ መድሃኒዓለም 38 አምዶች ከውስጥ እንዳሉት፣ የሁሉም አብያተክርስቲያናት አሰራር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስጢራትን እንደተከተለ፣ በውስጡ የሚገኘው አፍሮ አይገባ የተባለው መስቀልም በ1989 ዓ.ም. በ25 000 የአሜሪካን ዶላር ለአንድ ጎብኝ ተሸጦ ከሄደበት ከቤልጅየም ሀገር እንደተመለሰ በመናገር አስጎብኛችን ስራውን ‹‹ሀ›› ብሎ ጀመረ፡፡ አብያተክርስቲያናቱ ከታነጹ 800 ዓመታት ሲሆን ከዝናብና ከጸሐይ የሚከላከሏቸው ዳሶች ከተሰሩ ስድስት ዓመታቸው ነው፡፡ ዩኔስኮ ያሰራቸው ዳሶች እንደ ውጫዊ አምዶቹ ሁሉ በጣሊያኖች የታነጹ ናቸው፡፡ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ መቃብሮች ምሳሌ የሆኑ አምሳለ መቃብሮች በዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ አሉ፡፡ ይህ ቤተክርስቲያን 55 መስኮቶችና 3 መግቢያ በሮች አሉት፡፡ ከቤተክርስቲያኑ አሰራር በጣም የሚገርም ነገር ቢኖር መሰረቱ የተሰራው ከላይ ሲሆን የተጠረበውም ከላይ ወደ ታች ነው፡፡ ከላይ ወደ ታች መጥረብ ጀምሮ መስኮት አውጥቶ በዚያ መስኮት ገብቶ እየፈለፈለ ያንን የመሰለ ሕንጻ አነጸ ቅዱስ ላሊበላ፡፡
ቤተ ማርያም ቅዱስ ላሊበላ መጀመሪያ የሰራት የፎቅ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ለመስራትም 9 ዓመታት ፈጅታለች፡፡ ፡፡ አጠገቧ 11 ሜትር ጥልቀት ያለው ለመካኖች ብቻ የሚያገለግል የማርያም ጸበል አለ፡፡ መካኖቹ ባልና ሚስት በጠፍር ታስረው ወደታች ይለቀቃሉ፡፡ ሌላው በዚህች ቤተክርስቲያን ያየንው ነገር ቢኖር በመስኮቶቹ ላይ ካሉት መስቀሎች አንዱ የሆነውን የናዚ አርማ ይመስላል ሲባል የምንሰማውን ምልክት ሲሆን ይህ መስቀል ግን የናዚው አርማ ተቃራኒ ነው፡፡ የናዚው አርማ ቀስቶቹ በሰዓት አዟዟር አቅጣጫ ሲሆኑ ይህ ግን በሰዓት በተቃራኒው ነው፡፡ የኛ ቡድን የአስጎብኛችንን ‹‹ይህ የናዚ መስቀል ነው›› የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቅረፍ ጥረት አድርጓል፡፡ የአስጎብኝ ነገር ይታሰብበት፡፡
ቤተ መስቀል ረጅምና ጣራው ላይ የመስቀል ቅርጽ ያለው ሲሆን ከላይ ወደታች በተሰሩት አብያተክርስቲያናት አጠገብ ባለው ስፍራ ወደጎን የተፈለፈለ ነው፡፡ ልደታ ሌላው በዚህ አቅራቢያየሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡
ቤተ ሚካኤል አምስት ታቦቶች አሉበት፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ከቤተክርስቲያኑ ወለል በታች 4 ሜትር ጥልቀት ባለው መቃብር ውስጥ የተቀበረበት፣ በመስቀል ቅርጽ የተሰሩ አምዶች ያሉበት ፣ የጥንት የንጉስ ላሊበላ ስዕል እና በድንጋይ ላይ የተቀረጹ የሐዋርያት ምስሎች የሚገኙበት ነው፡፡ ቤተ ጎለጎታም ሌላው በቤተ ሚካኤል አቅራቢያ የሚገኝ ቤተክርስቲያን ነው፡፡
ቤተ-ጊዮርጊስ በብዛት በፎቶ የምናየው በኖህ መርከብ አምሳል የተሰራው የንጉስ ላሊበላ የመጨረሻ ስራው ነው፡፡ ከቤተክርስቲያኑ ወገብ በላይ በ12ቱ ሐዋርያት ምሳሌ 12 መስኮቶች፣ ከወገብ በታች ያሉ 3 የሚከፈቱ በሮች ሲኖሩት ምንም ዓይነት ዕድሳት አልተደረገለትም፡፡ ዓለምን እየዞሩ ይጸልዩ የነበሩ ከእየሩሳሌም የመጡ ቅዱሳን አጽም እዚህ ይገኛል ተብለናል፡፡ ይህ ቤተክርስቲያን ከውጭ ሆነን ከላይ ወደ ታች ስናየው 15 ሜትር ቁመት አለው፡፡ ውስጡ ስንገባ ግን ቁመቱ 10 ሜትር ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ጣራው 5 ሜትር ውፍረት አለው ማለት ነው፡፡ ዩኔስኮ ይህን ቤተክርስቲያን ዳስ ያላለበሰውም ለዚህ ነው፡፡
ቤተ አማኑኤልን፣ ቤተ ገብርኤልን፣ ቤተ መርርዮስንና ቤተ ሊባኖስን ለማየት ያልታደልኩት አስጎብኝው የደብረ ብርሃኑን ቡድን እያቻኮለ ይዞ የጠፋበት አቅጣጫ ስለጠፋብኝ ነው፡፡ ከሌሎች ቤተክርስቲያኖች ጋር የሚያገናኝ የውስጣውስጥ መንገድ አለው የተባለለትን ስፍራም አላየሁትም፡፡ ‹‹ሁሌም የማይደርቅ ውሃ አለው፡፡ ሌላ ቤተክርስቲያን ወደ ሲኦሌ ምሳሌ ከመግባታችን በፊት ዩኔስኮ ጣራውን ያለበሰለት አለ፡፡ 73 ሜትር የሚረዝም የሲኦል ተምሳሌት በሆነ አይን ቢወጉ በማይታይ ዋሻ ውስጥ በቀኝ እጅዎ ግድግዳውን በግራ እጅዎ ጣራውን ይዘው ይሂዱ ሲባሉ በከሞት ወዲያ ሕይወት እና ትንሳኤ ካመኑ ሊሸበሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም የገነት ተምሳሌት የሆነውን በብርሃን የተሞላ ዋሻ ሲያዩ ግን ‹‹ይህም አለ›› ይላሉ፡፡›› ብለው የስራ ባልደረቦቼ ያላየሁትን በእዝነ ልቦናዬ ያላየሁትን አየው ዘንድ ረድተውኛል፡፡
‹‹ቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናቱን ሲያንጽ አምላክ ‹ስራው ባንተ ስም ይሁን እንጂ እጨርስልሃለሁ› ብሎታል፤ ‹‹ቀን ላይ ሲሰራ እየሰራ ማታ ወደ ቤተመንግስቱ ይሄድና በማግስቱ ሊሰራ ሲመጣ ስራው ጨምሮለት ያገኘዋል›› የሚለው የአስጎብኛችን ንግግር ያላግባባበት ጊዜ ነበር፡፡ ስነ-ሕንጻንና ሐይማኖትን ያቀላቅሏቸዋል፡፡ በቅዱስ ላሊበላ ዘመን የነበሩት ለድንጋዩ መፈልፈያ የተጠቀማቸው መሮና አካፋ የመሳሰሉ ዕቃዎችን ራሱ በሰራው ልዩ ሳጥን አስቀምጧቸው የነበረ ቢሆንም አሁን ግን እዚያው ወደሚገኝ ሙዚየም ተዛውረዋል፡፡
የተጓዦች አስተያየት
‹‹አይቼው የማላውቀውን ታሪክ በማየቴ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ በሐገራችን የዚህ ዓይነቶች ነገሮች ማየት አስደሳች ሲሆን አለ ብለን የማንጠብቀው ነው፡፡ ትኩረት ያልሰጠሁት ቦታ ነበር፡፡ በዚህም አዝናለሁ፡፡›› የምስራች ታደሰ
‹‹መንገድ መግባት አለበት፣ ህብረተሰቡም በጣም ደሃ ነው፡፡ ከአየር መንገዱ በኋላ ብቻ እኮ ነው አስፋልት ያለው፡፡ ›› ገበያው ስጦታው
‹‹አገር አውቄያለሁ፤ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ተዋውቄያለሁ፤ በመጻሕፍት የማውቀውን በተግባር ማየት ችያለሁ፡፡›› መሰረት ሸዋንግዛው
‹ከአድካሚ ስራ በኋላ ሰራተኛው ከፍተኛ የመንፈስ እርካታ ያገኘበት እና ታሪካዊ መዳረሻ ቦታው ላይ ያለውን የአስተሳሰብ ከፍታ ያሳየ ጉዞ ነበር፡፡ ላሊበላን ያላየ ኢትዮጵያዊነቱን ሊጠራጠር ይገባዋል፡፡ የአውሮፓውያን የህዳሴ ዘመን አሳቢዎቹ የታሪክ ሰነዶችን እንደመረመሩት ሁሉ እኛም እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ምሁርነታችን ላሊበላን በየዘርፉ ልንመራመርበት ይገባል፡፡ የአፍሪካ የስነ-ሕንጻ እና የስነ-ጽሑፍ ሕዳሴ መነሻ ይሆናል፡፡ በዘር ሐረጋችን ያለው እና የነበረው የአስተሳሰብ ልዕልና ምን ላይ እንደደረሰ ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ እንቆቅልሽ፣ ምስጢር እና ቅኔ ስለሆነች በሰከነ መንፈስ ልትመረመር ይገባል፡፡ የስልጣኔ ሕዳስ መነሻ ሐሳብ በኛ ዘንድ አለ፡፡›› ጌታመሳይ ተፈራ
‹‹ከጣና ደሴቶችም በልጦብኛል፡፡›› ቅድስት ወ/ሰማያት
‹‹ቆቦ ተወልጄ አድጌ ያላየሁትን ቦታ በማየቴ ደስተኛ ነኝ፡፡›› ደስዬ ደጉ
በድንጋይ ቴክኖሎጅ ረገድ የዕድገታችንን አመጣጥ ስናየው ከአክሱም አንድ ቋሚ ድንጋይ ወደ ድንጋይ ቤቶች ስራ አድገናል፡፡ በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ላይ በአክሱም ሐውልት ቅርጽ የተፈለፈሉ መስኮቶች ይገኛሉ፡፡ ላሊበላ የአክሱማውያንን አምኖበት አሳድጎ ነው ያመጣው፡፡ ‹‹ላሊበላ ከእየሩሳሌም ሲመለስ 6 ወር አክሱም ተቀምጦ የድንጋይ ቴክኖሎጅን ተምሮ ነበር›› ብሎ አስጎብኝው ነግሮናል፡፡ እነዚህን የመካከለኛው ዘመን እድገቶች ደግሞ ብናሳድግ ኖሮ… ኢዮብ ከበደ
ቅዱስ ላሊበላ ይህንን የአብያተክርስቲያናት ሰንሰለት የሰራው ምዕመናን ወደ እየሩሳሌም ለመሄድ በወቅቱ በነበረው ሁኔታ ስለተቸገሩ እንደ አማራጭ ነው፡፡ የአንድ ሰው ሃሳብና ቁርጠኝነት እንዴት ሃገርን እንደሚለውጥ ያየንበት ጉዞና ስፍራ ነው፡፡ ጉዞው ጥድፊያ አለው፤ አንዱን ቦታ በደንብ ሳያስጎበኙ ወደ ሌላው ያጣድፋሉ፡፡ አስጎብኝው በጣም ይፈጥናል፤ የኛም መርሃ ግብር እንደዚያው፡፡ ከ3፡00- 7፡00 ሰዓት ድረስ መሰለኝ በላሊበላ የቆየንው፡፡ ያልሄዳችሁ ሄዳችሁ እንድታዩት፣ ከቻላችሁ ከአንድ ሳምንት ያላነሰ ቆይታ እንድታደርጉ ይሁን፡፡ የመኪና ዘዋሪዎቹና የተጓዦቹ ግንኙነት መግባባት በተሞላበት ሁኔታ ይሁን፡፡ ጉዞው ውሎ አበል ቢኖረው የተጓዡን ምቾት ይጨምራል፤ ብዙ የሚዝናኑና ልዩ ልዩ ስፍራዎችን በእረፍት ጊዜያቸው የሚጎበኙ ሰዎች ያሉበት መስሪያ ቤት ደግሞ ያተርፋል እንጅ አይከስርም፡፡
ላልይበላ ከተማ ባለው በሰብሊ ካፌ ባየናት ለብዙዎች አርዓያ መሆን በምትችል ማስታወቂያ እና በእኔ ግጥም እንሰናበት ‹‹የደምወዝ ጭማሪውን ምክንያት በማድረግ 10 ፐርሰንት የዋጋ ቅናሽ አድርገናል፡፡››
ቻይናዎች በግንብ ቢታጠሩ
ግብጾች ፒራሚድ ቢሰሩ
የላሊበላን ድንቅ ስራ
እዩት ደምቆ ሲያበራ!

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...