መምህር የዕውቀት አባት፣ የትውልድ ቀራጭ፣ ራሱን እንደ ሻማ አቅልጦ የሚያበራ የሚለው የሚገባን ቀድሞ ያስተማሩን መምህራንን መጨረሻ ስናይ ነው፡፡ ሙሉ ቀን ትምህርት ቤት የሚውሉት፣ ቅዳሜና እሁድ ቱቶሪያል እየጠሩ የሚያስተምሩት፣ የኛን ሕይወት ለመለወጥ ለቀጣዩ ክፍለጊዜ ቀን ከሌሊት ሲዘጋጁ ሕይወትን ያልኖሩ መምህራን ነበሩን/አሉን፡፡
መምህርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያሳዝን ሁኔታ የሚሰጠው ደረጃ፣ ክብርና ቦታ ዝቅ እያለ ምናልባትም ከመጨረሻው ደረጃ እየደረሰ ነው፡፡ በዚህች በዕውቀት በምትመራ ዓለም ኢትዮጵያ ዕውቀትንና የዕውቀትን አባትና እናት ገፍታ የትም ስለማትደርስ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በእርግጥ ለመምህር ብቻ ሳይሆን ለትምህርት ስርዓቱ የተሰጠው ቦታ እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡ ሳይንሳዊ ባልሆነ ማህበረሰብና ለመማር ቦታ በማይሰጥበት አገር ይህ ለምን ሆነ ብሎ የሚጠይቅም እምብዛም የለም፡፡
የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን የዩኒቨርሲቲና የኮሌጁን መምህር የተሻለ ጥቅም እንደሚያገኝ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲውና የኮሌጁም በእነሱ በደሞዝ ተበለጥን፣ የደረጃ ዕድገት ተከልክለናል እያለ ያማርራል፡፡ ነገሩን ቀረብ ብለን ስናየው ግን ሁለቱም ከመቶ ዶላር በታች የሚከፈላቸው፣ በዚያችም ደሞዝ ከዓለም ገበያና ከሃብታሞች እኩል ተወዳድረው ሸቀጥ ለመግዛት የማይችሉ ናቸው፡፡ ልልበስ ቢሉ ቻይና የምታመርተውን መግዛት አይችሉም፡፡ ወደ ሱቅ ቢሄዱ የቻይናን ምርት መግዛት አይችሉም፡፡ ይህን መቶ ዶላር እንዴት ይገዛዋል፡፡ የአገር ውስጥ የግብርና ምርትም ዓመት ከዓመት ዋጋው እየናረ ነው፡፡ ገበያ ላይ ተወዳድረው ገዝተው ለመኖር አልቻሉም፡፡ የእህል ዋጋ የታወቀ ነው፤ የቤት ኪራይም እንዲሁ፡፡ ችግሩ አገራዊ ችግር ሆኗል፡፡
መምህሩ ብሎም የመንግስት ሰራተኛው ዋጋውን እንደሌላው ነጋዴ ጨምሮ የሚሸጠው ሸቀጥ በእጁ ላይ የለውም፡፡ ሌሎች ባላቸው ሸቀጥ ላይ ዋጋ ጨመሩ፡፡ ገበሬው በእህል ላይ፣ የእጅ ሙያተኛው በሙያ ክፍያው ላይ፣ የጉልበት ሰራተኛውም በቀን ክፍያው ላይ ጨመረ፡፡ መምህሩና መንግስት ሰራተኛው ግን መንግስትን ተማምኖ በመንግስት ስራ ኖሯል፡፡ አሁን ማጣፊያው አጥሮታል፡፡
ጊዜያዊ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ምንድነው? የምጣኔሃብት ባለሙያዎች፣ የመንግስት ኃላፊዎችና የሰራተኛ ማህበራት ተሰብስበው ይነጋገሩበት፡፡ መምህሩም ይጠየቅ፡፡ ምርምርም ይሰራ፡፡ ውጤቱም ይተግበር፡፡ አሁን መምህሩን ለማኖር ባለፉት ሰባት ዓመታት አራት እጥፍ በጨመረው ኑሮ ልክ ደሞዙ አራት እጥፍም ቢጨመርለት መኖር አይችልም የሚል ትንታኔ ሰምቻለሁ፡፡ ጣራ የነካው ኑሮ ሊስተካከል ይችላል? የተነሱ ድጎማዎች ሊነሱ ይችላሉ? ቢመለሱ ያስተካክሉታል?
ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንደሚሰራ ሰው ያየሁትን ለመግለጽ ያህል ዩኒቨርሲቲ የዕውቀት፣ ቴክኖሎጂና ክህሎት ማዕከል ሆኖ ሰርቶ የሚያሰራ ሆኖ ተቀርጿል? አልተቀረፀም፡፡ ቢሆንማ ኖሮ ቢያንስ ለህብተረሰቡ ዘመናዊ የግብርና ስልቶችን ለማሳየትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ በሰፊው ሰርቶ ማሳያ መሬት ወስዶ እያለማ ቢያንስ እንደዚህ ባለው ወቅት ለመምህሩና ለሰራተኛው የምግብ ግብዓት በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርብና የኑሮ ውድነቱንም ያረጋጋ ነበር፡፡ ከአጀማመሩም ይህ የታሰበበት አይመስልም፡፡ በዩኒቨርሲቲ ላውንጅ ሳይቀር ቫት የሚከፍል፣ የግለሰቦች መበልፀጊያ ለመሆን የተገደደና በችግር ውስጥ የሚገኝ መምህር ነው፡፡ የሚበለጽጉት ዉሱን ሰዎች ናቸው፡፡ ለዓመታት ያየነው መምህሩ በልፋቱ ባቆመው የትምህርት ስርዓት ውስጥ ሚሊየነር የሆኑ ሹመኞችን ነው፡፡ መምህሩ ለቤት ኪራይ የሚበቃ ደሞዝ አጥቶ ከመሃል ከተማ ተገፍቶ ሲወጣ በርካታ ቤቶችን ሰርተው የሚያከራዩ የትምህርት አመራሮችን ነው፡፡ መንግስት ይህን ለማስተካከል ይፈልግ ይሆን? ሌሎችን በትምህርት ዘርፉ ውስጥ የሚታዩ የአመራር፣ የተደራሽነት፣ የጥራት፣ የትምህር ቤቶች መዘጋት ወዘተ ችግሮች ሌላ ጽሑፍና ጊዜ ይፈልጋሉ እንጂ ዘንግቻቸው አይደለም፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ