ዓርብ 8 ጁን 2018

ሴት ተመራማሪዎችና የምርምር ተግዳሮቶቻቸው

በትዝታ ገበየሁ

tizitageb12@gmail.com

መምህርት ትዝታ ገበየሁ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሐብት መምህርት ናቸው፡፡



የዩኒቨርስቲ መምህራን በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ውስጥ ማስተማር፣ በየጊዜው ምርምሮችን መስራትና የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጥናትና ምርምር ለመምህራን ከመማር ማስተማር ስራቸው ጎን ለጎን ሊያከናውኑት ግድ የሚል ተግባር ነው፡፡ ምርምር ተከታታይ ትግበራን ብዙ ጊዜ መመደብንና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ስራ ነው፡፡

በዩኒቨርስቲዎች  በማስተማር ላይ ያሉ መምህራን የምርምር ስራቸውን ሲያከናውኑ ከመደበኛ የማስተማር ስራቸው ላይ የተወሰኑ ሰዓቶች ይቀነሱላቸዋል፡፡ ምክንያቱም ለመመራመር ያስችላቸው ዘንድ የሚያስፈልጋቸውን ጊዜ ሰፋ ለማድረግ ሲባል ነው፡፡ 

ምርመር የሚሰሩ መምህራን ማበረታቻ ይሆናቸው ዘንድ ክፍያም ይከፈላቸዋል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ በጎ እገዛ ለምርምርና ለተመራማሪዎች እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ውስጥ በየዪኒቨርስቲዎቻችን ያሉ ሴት መምህራን ለምን የሚፈለገውን ያህል ምርምር ላይ አይሳተፉም? ለመመራመር በሚነሱበት ሰዓትስ ምን ችግሮች ይገጥሟቸው ይሆን? ምንስ መፍትሄ ለተግዳሮቶቻቸው እንስጥ? በዛሬው ዕለት ብዕሬን ያነሳሁለት ርዕሰ- ጉዳይና ልመልሰው የወደድኩት ጥያቄ ይህ ነው፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ሴት መምህራን በተለይም ደግሞ በቤት ውስጥ ከሚስትነት ባለፈ ኃላፊነት ያለባቸው ከሆነ  ለመመራመር ቢፈልጉም ያቅታቸዋል፡፡ ምክንያቱም የማስተማር ስራቸውን በቶሎ አጠናቀው ወደየቤታቸው መሔድና በቤት ውስጥ ደግሞ ልጆቻቸውን፣ ባሎቻቸውን ብሎም ቤተሰቦቻቸውን መንከባከብ ስላለባቸው ነው፡፡ ሴት ልጅ የቱንም ያህል ጠንካራ፣ ቆራጥና ብርቱ ሰራተኛ ብትሆን አብዛኛውን ጊዜ ልጅ የመንከባከቡ ኃላፊነት ከምትወደው ስራዋ ወደኋላ ያስቀራታል፡፡ ምርምር ማካሄድ ብትፈልግ እንኳን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ባላጠናቅቀውስ? ጀምሬ ባልጨርሰውስ?  ቤቴን ቢጎዳብኝስ? የሚሉ ስጋቶች ከተሳትፎዋ እንድትቆጠብ ያስገድዷታል፡፡

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የወንዶች የበላይነት ነግሶ በሚስተዋሉባቸው ሀገራት አድገው ተምረው ስራ ለያዙ ሴት መምህራን የባሎች እገዛ እንደ ግዴታ መውሰድና መተግበር ከባድ ሊሆን ስለሚችል ሴቷ ሁሉን ኃላፊነት ከመውሰድ ውጪ አማራጭ አይኖራትም፡፡ የኃላፊነቶች መደራረብ ደግሞ በማስተማር ስራዋና በምርምር ግዴታዋ ላይ አሉታዊ ተፅ  ይኖረዋል ማለት ነው፡፡

በምርምር ስራ ላይ ተሳትፎ እያደረገች ያለች መምህርትንና ምንም የምርምር ተሳትፎ የሌላትን መምህርት ለማነጋገርና ለምርምር ስራቸው ተግዳሮት የሆኑባቸውን ጉዳዮች ለማወቅ ጥረት አድርጌ ነበር፡፡

በቅድሚያ በምርምር ስራ ውስጥ ተሳትፎ ያላት የኬሚስትሪ  ትምህርት ክፍል መምህርት የሴት መምህራንን የምርምር ተግዳሮቶች እንዲህ አስረድታኛለች፡፡

መምህርት መቅደስ ጌራወርቅ የሁለት ልጆች እናት ብትሆንም የመምህርነት ስራዋን ከጀመረችበት ቀን አንስቶ ምርምሮችን እየሰራች ትገኛለች፡፡ ‹‹ሴት መምህራን ብዙ ኃላፊነቶች ቢኖሩባቸውም ከቤት ውስጥ ስራቸውና ከማስተማር ተግባራቸው ባሻገር ምርምር መስራት ያላቸውን እውቀትና ክህሎት ለማዳበር ያግዛቸዋል›› ብላኛለች፡፡ ሴት ተመራማሪዎች ለመረጃ ስብሰባ በሚወጡበት ጊዜ ረጅም ርቀት ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ከመጓዝ አንስቶ መረጃ እስከመከልከል የደረሱ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሟቸው ነግራኛለች፡፡

ሁሉም ሰው ሴትም ሆነ ወንድ በምርመር ስራው ውስጥ እንቅፋት እንደማያጣው በማሰብና እኛ ሴቶች ላይ ብቻ የተከሰተ ፈተና አለመሆኑን መቀበል የሚችል ቀና ልቦናና ስራን በአግባቡ ከፋፍሎ መስራት ዋነኛ የስኬት ሚስጥሮች መሆናቸውን / መቅደስ ረገጥ አድርጋ ትናገራለች፡፡ በቤት ውስጥ ከትዳር አጋሯ ጋር በተግባቦት መኖር መቻሏና የትዳር አጋሯ እገዛ የምርምር ስራዋ ላይ እንድታተኩር ድጋፍ እንዳደረገላት ብሎም የራሷም ቁርጠኝነት እስከአሁን ላጠናቀቀቻቸውና አሁንም  በመስራት ላይ ላለቻቸው የምርምር ስራዎች እገዛ እንዳደረጉላት ገልፃልኛለች፡፡

ቀጥዬ ያገኘኋት ሴት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የኢንጅነሪንግ ኮሌጅ መምህርት ስለ ሴትነትና ምርምር እንዳወራት ስጠይቃት ፈቃደኛ ብትሆንም ስሟን እንድገልፅ ግን ፈቃድ አልሰጠችኝም፡፡ መምህርቷ የሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርት ስትሆን የአንድ ሴት ልጅ እናት መሆኗን ገልፃ በቤቷ ውስጥ ከፍተኛ የስራ ጫና እንዳለባትና በትምህርት ክፍሏም ከፍተኛ የማስተማር ግዴታ እንዳለባት በቆይታችን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ‹‹ማስተማሩንም የማልተወው ሆኖብኝ ነው፤ እንኳን ምርምር ልሰራ›› ብላም ፈገግ አሰኝታኛለች፡፡ ከባለቤቷ ጋር ያላቸው መተጋገዝ እንዴት እንደሆነ የማወቅ ጉጉት አድሮብኝ ስለነበር ጥያቄውን አንስቼባት ነበር፡፡ ባለቤቷ እሷንም ሆነ ልጇን በሙሉ ልቡ የሚወድ ቅን ሰው ቢሆንም የቤት ውስጥ ስራ ፈፅሞ የማይሆንለት መሆኑን ነግራኛለች፡፡ ‹‹በመሆኑም ሙሉ ሰዓቴን በማስተማር ስራና ቤተሰብን በመንከባከብ አጠፋለሁ፡፡ ለምርመር ግዜ ያስፈልጋል፡፡ እሱ ደግሞ የለኝም፡፡ የራስ ተነሳሽነቴንም እጠራጠረዋለሁ›› ብላለች፡፡

በመጨረሻ ለመረዳት ከቻልኳቸው ነገሮች አንዱ ለሴት ተመራማሪዎች ዋነኛው ተግዳሮት የቤት ውስጥ የስራ ጫና ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡ ከሴቶቹ ከራሳቸው የተነሳሽነት ማነስ የቤተሰቦቻቸው ድጋፍ አናሳ መሆንበምርምር ስራዎቻቸው የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ለምሳሌ የመረጃ አሰጣጥ ሂደት ላይ ለሴት ተመራማሪዎች ትክክለኛ መረጃ አለመስጠት ፆታዊ ትንኮሳና የመሳሰሉት እንደ ተግዳሮት ያየኋቸው ሲሆኑ ሴት ተመራማሪዎች ጠንካራ መንፈሰ-ብርቱ ለተሰማሩበት የስራ መስክ የተሰጡ መሆን እንደሚገባቸው ማስተዋል ያሻዋል፡፡ ስራን ከፋፍሎ በተቀመጠው እቅድ መሰረት መተግበር ብሎም የስራንና የግል ሕይወትን ለይቶ ማየት ለሴት ተመራማሪዎች በምርምር ስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዙ መንገዶች  ናቸው፡፡

በመሆኑም ሴት መምህራን ከማስተማር ባለፈ ጥናትና ምርምር ላይ መሳተፍ ለወንድ መምህራን ብቻ የወጣ መመሪያ እንዳልሆነ ተረድተው በምርምር ስራዎች ላይ መሳተፍ እንዲችሉ   እመክራለሁ፡፡ አበቃሁ፡

                                                    

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...