ሐሙስ 25 ጁን 2020

መጽሐፍ ግምገማ

መጽሐፍ ግምገማ

በደራሲ ጥላሁን ጣሰው 

መዘምር ግርማ “ሁቱትሲ” በሚል ርዕስ የተረጎመውን የኢማኪዩሌ ኢሊባጊዜ መጽሐፍ አንብቤዋለሁ። ስለተርጓሚው የቋንቋ ጥራትና ምጥቀት ዶ/ር ያዕቆብ ለመጽሐፉ ከሰጡት ቀዳሜ ቃል በላይ የምለው የለኝም። በዚህ ግምገማ የማተኩረው በመጽሐፉ ውስጥ ከምንተዋወቃቸው ሰዎች ሦስቱን በመውሰድ ከወግ፣ ሃይማኖትና ባህል በመነሳት ንጽጽር በማድረግ ቀደም ብለው መጽሐፉን ያነበቡት በጥልቀት እንዲያስተውሉት፣ ያላነበቡትና ወደፊት የሚያነቡት ትኩረት እንዲያደርጉበት አጽንዖት ለመስጠት ነው።
ኢማኪዩሌ ሐጢያትና ክፋት ሳይኖራት እንደ እዮብ በፈተና ውስጥ የምታልፍ ናት። ትምህርት ቤት ውስጥ ዘረኛው መምህር ሁቱዎች ቁሙ፣ ቱትሲዎች ቁሙ፣ቱዋዎች ቁሙ እያለ ሲጠይቅ የምን ዘር (በመዘምር አማርኛ ዘውግ) እንደሆነች ስለማታውቅ ከመቀመጫዋ ሳትነሳ የቀረች ልጅ ነበረች። ወላጅ አባቷ ይህን ሲሰማ መምህሩን በማነጋገር ይህን አወጋገን እንደተቃወመ ይሰማናል። መምህሩ ግን ኢማኪዩሌን በክፍል ውስ ጠርቶ ቱትሲ ስል ትቆሚያለሽ ብሎ ይነግራታል። ይህች የዋህ፣ ቅን ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደምናገኘው እግዚአብሔርን የሚፈራ ግን የሚፈተን ሰው እሷም በእግዚአብሔር ቸርነት በወላዲት አምላክ አማላጅነት ለወሬ ነጋሪ የተረፈች እንደሆነች ትነግረናለች።
በወቅቱ የሩዋንዳ ሕብረተሰብ በአደገኛ የሥነልቦና ቀውስ ውስጥ መሆኑን ለማሳዬት በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸው ቄሱን ነው። ቄሱ ከፍራትና ከጥቅም አንጻር ነገሮችን በማዬት እንደ ጲላጦስ ለመሆን እንኳን የማይደፍሩ ናቸው። “እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ  በነዚህ ሰዎች ላይ አልፈርድም” ለማለት እንኳ ድፍረቱ የላቸውም። እንደ አንድ ሃይማኖት አባት “ሁላችሁም የአንድ ቤተክርስቲያን ልጆች ናችሁ። ማንም በወንድሙ ላይ ቆንጨራ ቢመዝ ሃጢያተኛ ነው። ይህን ተላልፎ ወንድሙ ላይ እጁን ለመሰንዘር የሚፈልግ በኔ እሬሳ ላይ ይራመድ።” ብለው ለማውገዝ ጥንካሬ የሌላቸው ናቸው። በቅርቡ ክርስቲያንና ሙስሊም ተጓዦች ላይ ኬንያ ውስጥ አልሸባብ ነጣጥሎ ለመግደል ሲሞክር እስላሞቹ ክርስቲያኖቹን ከገደላችሁ እኛንም ግደሉን ያሉበትን ያህል መንፈሳዊ ጥንካሬ ለመንፈስ ልጆቻቸው ሞት አላሳዩም። ሴቶቹን ደብቀው የሚያስቀምጡበት ዓላማም ከወደፊት ጥቅም አንጻር የተሰላ መሆኑ የሚታወቀው ምስኪን ተደባቂዎቹን የተደባቂዎቹ ዘር በደል ይፈጽም ነበር ብለው በማውራት ሲያሸማቅቋቸው ነው። እንደ አንድ መንፈሳዊ አባት “እናንተን እግዚአብሔር የሚፈትናችሁ ስለሚወዳችሁ ነው። ብጸዕ ናችሁ ። ፈተናውን ታልፉታላችሁ። በናንተ ላይ የሚፈጸመው ሁሉ ትክክል አይደለም።” ብለው አያጽናኑም። ራሳቸው ተስፋ አጥተው ተደባቂዎቹንም ተስፋ ቢስ ያደርጋሉ። ይልቁንስ ቄሱ በፍራት ተውጠው የሁቱ ጽንፈኞችን ሃሳብ እንደሚደግፉ ለጽንፈኞቹ ዘረኞች በመናገር ቀውሱን ያባብሱታል። እንደ አንድ መንፈሳዊ አባት ሁላችሁም ልጆቼ ናችሁ። አንዳችሁን ከአንዳችሁ አላበላልጥም። ምህረትና ትህትና እናገራለሁ።” ለማለት አልቻሉም። አንዲቷን ቤተክርስቲያ በዘር ከፋፈሏት ማለት ነው። ሁቱዎች ብቻ የሚያመሰግኑባትና የሚቀድሱባት ዓይነት። በዘመኑ ሩዋንዳ በመንፈስም ደረጃ የደረሰችበትን ዝቅጠት አመላካች ገጸ ባሕሪ ናቸው።
የኢማኪዩሌ አባት በመንግሥት ከአድልዎ ነጻ የሆነ ሥርዓትና ሕጋዊነት የሚያምን ነው። ስለዚህ በትምህርት ቤቶች በዘር የሚከፋፍለውን አስተማሪ ለማስተካከል በከንቱ እንደሞከረው ሁሉ ጭፍጨፋው በጀመረበት ወቅት የዘር ጭፍጨፋውን አቃጅና አስፈጻሚ ለሆኑት የመንግሥት ሹማምንት እየተሠራ ያለው ሥራ ትክክል ስላልሆነ የመንግሥት ሹማምንት ጣልቃ ገብተው በሃላፊነት ጭፍጨፋውን እንዲያስቆሙ ሲወተውት በዚያው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚገደል ነው። ወንድ ልጁ ፍጅቱን ለማቆም ወይም ካልተቻለ ለመሰደድ የሚያቀርብለትን ሃሳብ በመንግሥትና በሕግ በመተማመን በእንቢታ የቆመ አባት ነው። የመንግሥት መዋቅሮች የዘር ሴራ ማውጠንጠኛ በሆኑበት ሁኔታ በመንግሥትና በሕግ ላይ እንደዚህ የጸና እምነት ያለው ሰው በሃይማኖትና ዓለማዊ መጽሐፎች ውስጥ ማነጻጻሪያ ሊሆን የሚችል ለጊዜው ትዝ አይለኝም። መኖሩንም እጠራጠራለሁ። የኢማኪዩሌ መጽሐፍ የዚህ ዓይነት ተምሳሌት ፈጥሯል።
በኢማኪዩሌ መጽሐፍ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናውቀውን ጳውሎስን የሚስተካከል ሁቱ ተወላጅ አናይም። ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን አሳዳጅ የነበረ ሲሆን በኋላ ተመልሶ ለክርስትና መስዋዕት የሆነ ነው። በሩዋንዳ አማጽያን ካምፕ ሁቱዎችን ብናይም በአደባባይ የቱትሲ መግደያ መሣሪያውን ጥሎ “ከእንግዲህ በቃኝ። በቱትሲዎቸ ላይ እጄን አላነሳም። ብትፈልጉ እኔንም ግደሉኝ፣’’ ብሎ ነውጠኞቹን የሚጋፈጥ ሰው በመጽሐፉ አይታይም። እንዲህ ዓይነት ሁቱዎችን ለምፍጠር ምናልባት በመሸሽ ፈንታ ተፋጥጦ በመቆም ብትፈልጉ ግደሉኝ ሃሳባችሁ ትክክል አይደለም የሚሉ ቱትሲዎች በብዛት ባለመኖራቸው ጥቂት የጳውሎስ ዓይነት ሁቱዎች አልወጡ ይሆናል። ይህ ከሆነ ደግሞ የሩዋንዳ ሕብረተሰብ በዚያን ወቅት የመጣበትን መዓት ለመቋቋም የማይችል ነበር ማለት ነው። 
በኢማኪዩሌ መጽሐፍ ውስጥ ቀሳውስቱ በመንፈስ ልጆቻቸው መሃከል በፍራትና በጥቅም ታውረው ቤተክርስቲያኒቱ የዘር ቅርጽ ስትይዝ ሳይከላከሉ፣ የመንግሥት ተቋማት የዘር አድማና ሴራ መጠንሰሻ ማዕከልነት ተቀይረው በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ይሆናል ብሎ ከመጠንቀቅ አይሆንም በሚል ተስፋ ጸጥ ብሎ ቆሞ እናገኘዋለን። ሩዋንዳ ወደ ፈተና ገባች። ክፉው ሁሉ ተፈጸመባት።በቸርነቱ የተረፉት ቂምን ሳይሆን ምህረትን አደረጉ። የኢማኪዩሌ ታሪክ ይህ ነው።
መዘምር ተርጉሞ ስለቀረበልን ምስጋና ይግባው። ልብ ያለው አንባቢ ልብ ይበል።

እሑድ 31 ሜይ 2020

ሁቱትሲ


ሁቱትሲን ላላነበባችሁ ወዳጆቼ ለቅምሻ ያህል እነሆ፤
ሁለተኛው ዕትም እስኪወጣ።

መግቢያ
ኢማኪዩሌ እባላለሁ
ገዳዮቹ ስሜን ሲጠሩ ሰማኋቸው፡፡
እኔ በግንቡ በአንደኛው በኩል ስሆን እነሱ ደግሞ በሌላኛው አቅጣጫ ናቸው፤ አንድ ጋት የማይሞላ ውፍረት ያለው ጭቃና ዕንጨት ብቻ ይለያየናል፡፡ ንግግራቸው ጭካኔ የሚንጸባረቅበትና ቆርጠው መነሳታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
‹‹እዚህ ነችእዚህ የሆነ ስፍራ እንዳለች እናውቃለን፡፡ …. ፈልጓት - ፈልጓት ኢማኪዩሌን፡፡››
አካባቢው በሁካታ ተሞላ፡፡ ብዙ ገዳዮች መጥተዋል፡፡ በአእምሮዬ ይታዩኛል - ሁልጊዜ በፍቅርና በደግነት ሰላምታ ይሰጡኝ የነበሩ የቀድሞ ወዳጆቼና ጎረቤቶቼ በቤቱ ውስጥ ጦርና ገጀራ ይዘው ስሜን እየጠሩ ይዘዋወራሉ፡፡
‹‹399 በረሮዎችን ገድያለሁ›› ይላል አንደኛው ገዳይ፡፡ ‹‹ኢማኪዩሌ 400 ታደርግልኛለች፡፡ ይህን ያህል ከገደልኩ ምን እፈልጋለሁ!››
በትንሿ ምስጢራዊ መታጠቢያ ቤታችን ጥጋት አንድስ እንኳን የሰውነቴን ክፍል ሳላላውስ ተሸሽጌያለሁ፡፡ እንደኔው ሕይወታቸውን ለማትረፍ እንደተደበቁት ሌሎች ሰባት ሴቶች ሁሉ ገዳዮቹ ስተነፍስ እንዳይሰሙኝ ትንፋሼን ውጫለሁ፡፡
ድምጻቸው የሠራ አከላቴን ገማመሰው፡፡ በከሰል ፍም ላይ እንደተኛሁ፣ እሳትም ላይ እንደተጣልኩ ተሰማኝ፡፡ መላ ሰውነቴ የሕመም ውርጅብኝ ወረደበት፡፡ ሺህ የማይታዩ መርፌዎች ተቸከቸኩብኝ፡፡ ፍርሃት እንደዚህ የሚያርበደብድ ስጋዊ ሥቃይ ያስከትላል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡
ለመዋጥ ሞከርኩ፤ ጉሮሮዬ ግን ተዘግቷል፡፡ ምራቅ አልነበረኝም፤ አፌም እንደ ኩበት ደርቋል፡፡ ዓይኖቼን ጨፈንኳቸው፤ ራሴንም ለመደበቅ ሞከርኩ፤ ንግግራቸው ግን እየጎላ መጣ፡፡ ምንም ዓይነት ምኅረት እንደማያደርጉልኝ አውቃለሁ፤ በአእምሮዬም አንድ ሐሳብ ያስተጋባ ጀመር - ከያዙኝ ይገድሉኛል፡፡ ከያዙኝ ይገድሉኛል፡፡ ከያዙኝ ይገድሉኛል
ገዳዮቹ በራፉ ላይ አሉ፤ በማንኛዋም አፍታ እንደሚያገኙኝ አውቃለሁ፡፡ ገጀራው ቆዳዬን አልፎ ሲገባና አጥንቴ ድረስ ሲቆራርጠኝ የሚሰማኝ ስሜት ምን እንደሚመስል አሰብኩት፡፡ ወንድሞቼና ወላጆቼም ትዝ አሉኝ፤ ሞተው ወይንም በሕይወት እየኖሩ እንደሆነ፣ በገነት ከአፍታ በኋላ እንገናኝም እንደሆነ አለምኩ፡፡
እጆቼን እርስ በርሳቸው አጣመርኳቸው፤ የአባቴን መቁጠሪያም ጥብቅ አድርጌ ያዝኩ፤ በለሆሳስም መጸለይ ጀመርኩ - እባክህ እግዚአብሔር ሆይ፣ እባክህ እርዳኝ፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ እንድሞት አታድርገኝ፣ እንደዚህ አይሁን፡፡ እነዚህ ገዳዮች እንዲያገኙኝ አታድርግ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስህ ከጠየቅን እንደሚሰጠን ትነግረናለህእንግዲህ ጌታዬ እየጠየኩህ ነው፡፡ ወይ በለኝ፡፡ እባክህን እነዚህን ገዳዮች ወዲያ እንዲሄዱ አድርጋቸው፡፡ ኧረ በዚህ መታጠቢያ ቤት እንድሞት አታድርገኝ፡፡ እባክህ፣ እግዚአብሔር፣ እባክህ፣ እባክህ፣ እባክህ አድነኝ፡፡
ገዳዮቹ ከቤቱ ወጥተው ሄዱ፡፡ እኛም እንደገና መተንፈስ ጀመርን፡፡ ሄደዋል፤ ሆኖም ግን በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ ብዙ ጊዜ ይመላለሳሉ፡፡ ሕይወቴን እግዚአብሔር እንዳተረፋት አምናለሁ፤ ሆኖም ቁምሣጥን በምታክል መታጠቢያ ክፍል ውስጥ ከሰባት ሌሎች ሰዎች ጋር በፍርሃት እየተርበደበድኩ ባሳለፍኳቸው 91 ቀናት መትረፍ ከመዳን በጣም የተለየ አንደሆነ እማራለሁይህ ትምህርትም ለዘለቄታው ለውጦኛል፡፡ ይህ ትምህርት በጅምላ ጭፍጨፋ ውስጥ የሚጠሉና የሚያሳድዱኝን እንዴት መውደድ እንዳለብኝ - ቤተሰቤን ያረዱትንም ሁሉ እንዴት እንደምምር ዕውቀት የቀሰምኩበት ነው፡፡
ስሜ ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ ነው፡፡ ይህ በታሪክ ብዙ ሕዝብ ካለቀባቸው ጭፍጨፋዎች በአንዱ እግዚአብሔር እንዴት እንደተገለጠልኝ የሚያሳይ ታሪክ ነው፡፡

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...