በመዘምር ግርማ
ሰነፍ ተማሪ ማነው ብለን ብንጠይቅ የተለያዩ መልሶችን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ብዙ ሰው ሰነፍ የመባል ዕድል ገጥሞት ያውቃል ለማለት እደፍራለሁ፡፡ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ ትምህርት ሰነፍ ትባላላችሁ፡፡ ለዚህ ማስረጃም ከመቶው ያላችሁ ነጥብ ዝቅተኛ መሆኑ ይሆናል፡፡ በፈተና መውደቃችሁ ለስንፍናችሁ ማስረጃ ይሆናል፡፡ የቤት ስራና የክፍል ስራ አለመስራታችሁም እንዲሁ፡፡ ሌላው ሰነፍ ትምህርቱ እየገባው ለመስራት የማይሻና ጊዜውን በሌላ አልባሌ ነገር ላይ የሚያሳልፍ ሊሆን ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ዓይነት ሰነፍ ላይ ያተኮረ ሃሳብ ለማጋራት ይህን ጽሑፍ ጫር ጫር (ወይም በኪቦርድ ስለሆነ ጠቅ ጠቅ) አድርጌያለሁ፡፡
ተማሪዎች አንድን ትምህርት ለመቀበል ያላቸው ሁኔታ የተለያየ ይሆናል፡፡ ፈጣን፣ መካከለኛና ዝቅተኛም ይሆናል፡፡ ለዚህም ልዩ ልዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የልጆቹ የትምህርት አቀባበል፣ የመማሪያ ስልታቸውና መምህሩ የሚያስተምሩበር መንገድ አለመጣጣም፣ ከቀደሙ ክፍሎች ለዚያ ትምህርት አስፈላጊውን የቀደመ ዕውቀትና ክህሎት አለማግኘት ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሰነፍ የተባለው ተማሪ የሚገጥመውንና በአንድ የክፍል ደረጃ ለሚሰጥ ትምህርት የቀደመ አስፈላጊ ዕውቀት ይዞ አለመገኘቱ የሚያስከትለውን ችግር በተለይ ቀጥሎ እንመልከት፡፡
በተለያዩ ትምህርት ዓይነቶች መሰረታዊ የሚባለውን ዕውቀትና ክህሎት መጨበጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ በእንግሊዝኛ ትምህርት ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ፣ መቁጠር አስፈላጊ ነው፡፡ ከኤ አስከ ዜድ ቆጥሮ መጨረስ መሰረታዊ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ቆጥሮ መጨረስ ስንል ድምጻቸውን ማወቅ፣ ድምጻቸውንና ቅርጻቸውን ማዛመድ መቻል እንዲሁም ካፒታልና ስሞል የተባሉትን መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚያም በተለያዩ ቃላት ውስጥ ገብተው ሲነበቡ የሚኖራቸውን ድምጽና አንዳንዴም የሚያመጡትን ልዩነት መማር ያስፈልጋል፡፡ ይህንና ተያያዥ የእንግሊዝኛ ፊደላትን መሰረታዊ ሁኔታ አለማወቅ በቀጣይ ክፍሎችም ሆነ የትምህርት ሂደት የሚያመጣውን ችግር አስቡት፡፡ በላይ ክፍሎች እንግሊዝኛ የማስተማሪያ ቋንቋ ሲሆን የሚኖረውን ድርብርብ ጣጣም ልብ በሉ፡፡ በአንዱ ቀን ትምህርት ላይ የሌላው እየተደራረበ ሲሄድ ብዙ ነገር ይበላሻል፡፡ ያ ሁሉ ችግር የሚቃናበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ያንን የሚያቃናው የተማሪው በዕድሜ ሂደት መብሰል ነው? ወይንስ የጥሩ መምህር መገኘት? የወላጅ ክትትል? የሚቃናበት መንገድ ካልተገኘስ? ልጁ ከልጅነት እስከ ዕውቀት በእንግሊዝኛ እንደተቸገረና ትምህርቱን እንደጠላው ሊዘልቅ ይችላል፡፡ ይህን የእንግሊዝኛን ሁኔታ አነሳሁ እንጂ ነገሩ በሌላም ትምህርት ማጋጠሙ አይቀርም፡፡ በሂሳብም መሰረታዊ የሂሳብ ምልክቶችንና ቁጥሮችን ያላወቀ ተማሪ ለተደራራቢ ችግር መጋለጡ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ያለፈው ቀን ትምህርት የዛሬን የቤት ስራ ወይም የክፍል ስራ ለመስራት አስፈላጊነቱ አሌ አይባልም፡፡ በአማርኛስ ቢሆን! ተመሳሳይ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ እንደተገለጸው ያለ ችግር ይገጥማል፡፡ ይህ ሁኔታ ለሁሉም ትምህርት ይሰራል፡፡ ተማሪዎች በዚያ ችግር ውስጥ ሳሉ የሚከታተላቸው ወይም የስንፍናቸውን ምክንያት የሚረዳላቸው ይኖር ይሆን? ወይንስ እኔ ሰነፍ ነኝ ብለው ችግራቸውን ተቀብለው እንዲኖሩ ይገደዳሉ? በቀጣዩ አንቀጽ እንየው፡፡
ይህን ጽሑፍ ልጻፍ ወይንስ ምን ላድርግ የሚለውን ሳልወስን በማስታወሻ ደብተሬ ይዤ የቆየሁት ጉዳይ ‹‹ A plight of plights is studying a lesson or learning something that you really do not understand because you don’t have the necessary background. Worrying Unnecessarily!›› ማለትም ‹‹የስቃዮች ሁሉ ስቃይ የቀደመ ዕውቀቱ የሌላችሁን አንድን በእውነት የማትረዱትን ትምህርት ወይም ነገር መማር ነው፡፡ መጨነቅ ሳያስፈልግ መጨነቅ!›› የሚል ነበር፡፡ አዎን፣ መሰረታዊ ዕውቀቱና ክህሎቱ የሌለንን ትምህርት እንጠላ ይሆናል፡፡ በምንጠላበት ሁኔታ ድጋፍና እንድንወደው የሚያደርግ ነገር ካላገኘን ከዚያ ትምህርት ጋር እየተቆራረጥን መሄዳችን አይቀሬ ነው፡፡ ይህም ትምህርቱን የመጥላት ሁኔታ በተማሪው ላይ አላስፈላጊ ጫና ይፈጥራል፡፡ በትምህርት ወቅት አለመከታተል፣ በመምህራን እንደ ልግመኛ መወሰድ፣ በፈተና ወቅት በግምት መሙላት፣ አሳይመንት በሰው ማሰራት፣ መኮረጅ፣ በዚያ ትምህርት ከሚገኙት ክህሎትና ዕውቀት ምክንያት ተዛማጅ ትምህርቶች ላይም የውጤትና ፍላጎት መጥፋት፣ ከክፍል መውደቅ ወዘተ ሊከተሉ ይችላል፡፡ የቀደመ ዕውቀቱ የሌለንን ትምህርት መማር እንዴት ተደራራቢ ችግርችን እንደሚያስከትል ካየን ዘንዳ ምን ዓይነት መፍትሔ ሊኖር ይችላል የሚለውን እንመልከት፡፡ መፍትሔው ከትምህርት ተቆጣጣሪ አካላት፣ ከመምህራን፣ ከወላጆች፣ ከተማሪዎች፣ ከተመራማሪዎች ወዘተ ሊመጣ ይችላል፡፡ አንድን ትምህርት ለማስቻል ከመዋዕለሕጻናት ጀምሮ አንድ ልጅ ላይ የሚፈሰው ሀብት ከፍተኛ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሀብት በትክክለኛው መንገድ እየፈሰሰና ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ማረጋገጥ ያሻል፡፡ በትንሽ እገዛ ሊስተካከል የሚችልን ችግር ችላ ማለት ለዘላቂ ችግርና ድርብርብ ጫናዎች ይዳርጋል፡፡ ልጆችም በትምህርት ጎልብተው ሊደርሱ የሚገባቸው ደረጃ ላይ ይደርሱ ዘንድ ይህን ችግር መፍታት ያሻል፡፡ ለመማር ዝግጁ የሆነ አእምሮ ይዞ የተወለደን ልጅ ባልተገባ ሁኔታ ሰነፍ እያሉ ስም ከማውጣት የስንፍናውን መንስኤ አጥንቶ ማገዝ ከምስቅልቅል የትምህርት ህይወት ያድናል፡፡ ስንፍናው ከትምህርት አሰጣጡ ሊሆን ይችላል፡፡ አለያም ለተማሪው የተጋነነ ውጤት በመስጠት በዚያ ትምህርት ጥሩ እንደሆነ በማሳየት ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተማሪውም፣ መምህሩም ሆነ ወላጅ ችግሩን ልብ ሳይሉት ቆይተው ተደብቆ ቆይቶ ሊወጣ ይችላል፡፡ አንዳንድ አስደናቂ ነገሮችም ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ አንደኛው በግል ትምህርት ቤቶች የሒሳብ ትምህርት አሰጣጥን ብናይ ለአንድ ተማሪ ሒሳብን በአማርኛም በእንግሊዝኛም የሚሰጡ አሉ፡፡ በሁለቱም ተምሮ ሒሳብ የማይችለው የግል ትምህርት ቤት ተማሪ ብዙ ነው፡፡ ወላጅን ለማማለል የሚደረገው በሁለቱም ቋንቋዎች ሒሳብንም ሆነ ሌሎቹን የማስተማር ዘዴ የሽወዳ ስራ መሆኑን ያሳብቃል፡፡ የመንግስት ተቆጣጣሪ ሲመጣ በአማርኛ እንደሚማር ይናገራሉ፡፡ የተማሪውን ትኩረት በበርካታ ትምህርቶች ከመበተን ሥርዓተ-ትምህርቱ እንደሚያዘው በአማርኛ አስተምረው ትክክለኛውን ክህሎት ቢስጨብጡት የተሻለ ይመስላል፡፡ የሒሳብ ነገር ከተነሳ አይቀር ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ያነበብኩት በትምህርት ሚኒስቴር የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው በመንግስት ትምህርት ቤቶች ያለው የተማሪ ቁጥር መብዛት፣ ክትትል ያለመኖር፣ የመጻሕፍት እጥረት ወዘተ በሒሳብ ትምህርት አገሪቱ ብዙ እንድትቸገር እንዳደረጋት ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ መሻሻል ያለበት ነገር አለ፡፡ ይህም ለሌሎችም ትምህርቶች ይሰራል፡፡ በተቻለ አቅም ጥረትና ትብብር ማድረግ ያሻል፡፡
አንድ ተማሪ ከአንድ የክፍል ደረጃ ወደ ሌላኛው ሲሸጋገር አስፈላጊውን የትምህርት ይዘት ማወቁን ማረጋገጫ ሁነኛ መንገዶችን መቀየስ አስፈላጊ ነው፡፡ ይዞ ላልተገኘውም በሰዓቱ እገዛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እገዛውንም በቤተሰብ፣ በመምህር፣ በአስጠኚ እንዲሁም የኦንላይን የትምህርት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ማድረግ ይቻላል፡፡ ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ ሆኖለት በትምህርት ጫፍ የሚደርሰውን ጎበዝ ተማሪ እንደምናደንቀውና እንደምናበረታታው ሁሉ ከታች ያለውንና በብዙ ችግሮች የተተበተበውን ተማሪ ማየት ያሻናል፡፡ ‹‹ስራ ስራ ስራ›› ብለን ብንመክረው ለውጥ ላይመጣ ይችላል፡፡ እንዴት እንደሚሰራ ላያውቅ ስለሚችለማሳየት አለብን፡፡ ለማጠቃለል ያህል ሰፊ ጥናት የሚፈልገውንና ከትምህርት ስርዓታችን ችግሮች አንዱ የሆነውን ይህን ችግር መምህራንና ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች፣ ወላጆችም ሆኑ ተማሪዎች ልብ እንዲሉት አሳስባለሁ፡፡