እሑድ 16 ኖቬምበር 2014

በነሐሴ የገጠመኝ ችግር

በነሐሴ የገጠመኝ ችግር
የችግሬ ሁሉ መነሻ በጠባሴ ከሚገኘው ለ3 ዓመታት በኪራይ እኖርበት ከነበረው ቤት እስከ ነሐሴ 1፣ 2006 ድረስ ለቃችሁ ውጡ የሚል የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ነው፡፡ በግቢው ውስጥ ከምንኖረው 10 ግለሰቦች ለቆ መውጣት የቻለው 5 ሰው ብቻ ነው፡፡ ግቢውን ለሆቴል ፈልገንዋል ቢሉም እስከአሁን ስራ አልጀመሩም፡፡ ክረምትን ቢያቆዩን ወይም ከበጋው ቢነግሩን ምናለ? ከዚህ ግቢ ከወጣሁ በኋላ የገባሁበት የኮንዶሚኒየም ስቱዲዮ በሩን ለመዝጋት እና ለመክፈት ለበርካታ ደቂቃዎች መታገል ግድ ነው፡፡ እቃዎቼን የማጋዙ አድካሚና አድቃቂ ስራ በዕቃ ጋሪ አልጋዬንና የመጽሐፍት መደርደሪያዬን ወደ አዲሱ ቤቴ በማግባት ተጠናቀቀ፡፡ ጓደኞቼም ‹‹እንኳን ወደ ዘመናዊ ቤት በደህና መጣህ›› አሉኝ፡፡ ይህን የዘመናዊ አኗኗር ነገር ሳስበው ትዝ የሚለኝ የስራ ባልደረባዬ መምህር አብዮት ዲባባ ሲሆን እርሱም ‹‹ወደ ኮንዶሚኒየም ግባ›› ብሎኝ ምክሩን አልሰማ ስለው ‹‹ከሽንኩርት ጋር አንድ ቤት መኖር አቁም፤ ዘመናዊ ኑሮ ጀምር፤ ራሱን የቻለ ኩሽና እና መታጠቢያ ይኑርህ፡፡›› ይለኝ ነበር፡፡ ከአንድ ቤት ለቆ ወደ ሌላ ቤት የመግባትን ጣጣ እያሰብኩት እንጅ የአብዮትን ምክር ትክክለኛነት ሳልረዳው ቀርቼ አልነበረም፡፡
ለካ የሰው መዳኒቱ ሰው ነው!
አዲሱ ቤቴ ከገባሁ በኋላ አንድ ቀን አንዲት ዘመዴ ቡና አፍልታ ቤቱን መረቀችልኝ፡፡ እድሜ ይስጥልኝ የኔ እህት! በማግስቱ ግን ከቤት ለመውጣት በሩን ‹‹ተከፈት›› ብለው ‹‹አሻፈረኝ!›› ‹‹ነይ እስኪ ክፈችልኝ›› ብዬ ብጠራትና ብትሞክረው አልከፈት አላት፡፡ ተስፋዬ አሸናፊ እና ለማ ደምሴም ቢሞክሩት አልሆን ብሎ ምሳዬን እንደ እስረኛ በመስኮት ሰጥተውኝ ሄዱ፡፡ ከዚያም በኋላ ለአከራዬ ደውዬ ጉዳዩን አስረድቻት ‹‹ከሰዓት በኋላ ስብሰባ ቢኖርብኝም›› ብላ ባለሙያ ይዛ መጥታ ከሰዓት በኋላ አስከፈተችልኝ፡፡ የገነት በር ይከፈትልሽ የኔ እመቤት! በሬን ቆልፌ ስተኛ ‹‹ደሞ ነገ እንዴት ይከፈትልኝ ይሆን›› እያልኩ፣ ቆልፌ ወደ ስራም ሄጄ ‹‹እንዴት ከፍቼ እገባ ይሆን›› በማለት ስሰጋ ከረምኩ፡፡ ስጋት (አንዛይቲ) ደግሞ ከልክ በላይ የተሰጠኝ ሰው ሳልሆን አልቀርም፡፡
ጉዱ ቅዳሜ ነው፡፡ ምግብ ለማዘጋጀት ጉድ ጉድ ብልም መብራት የለም፡፡ ውሃ ከይድነቃቸው ሶሎሞን ቤት በባልዲ ቀድቼ ስመጣ የመብራቱን አለመኖር አስቤ ወደ መስሪያ ቤት ለመሄድ ስዘጋጅ በሩ አልዘጋ ብሎ በግድ ተዘጋልኝ፡፡ የበሩ የብሎን ማስገቢያዎች በደንብ እና በትክክለኛው ቦታ ስላልተበሱ ቁልፉስ ቢሆን ምን ላይ ይያዝ? ከሰዓት በኋላ ስመለስ ‹‹ና ተከፈት›› ብለው ‹‹አንተ ማን ስለሆንክ እከፈትልሃለሁ!›› አይለኝም! ከዋናው መሸጎሪያ በላይ ያለችው ትንሽ መሸጎሪያ ስፕሪንጓ ለቆ ተቀርቅራ ቅርት አለች፡፡ የታችኛው ቁልፍ ይሰራል፤ እሷ ግን አላስከፍትም አለች፡፡ ቅዳሜ እውጭ አደርኩ፡፡ እሁድ ለአከራዬ ብደውል ‹‹ሰው ፈልገህ አሰራው›› አለችኝ፡፡ የፈለግሁት ሰው ደግሞ ‹‹ይህን በጉልበት በፌሮ ብረት ተከፈት ብለው የበሩ መስተዋት ሊሰበር ይችላል፤ ቁልፉም ከጥቅም ውጭ ይሆናል›› አለኝ፡፡ እሁድም እንዲሁ ታደረ፡፡ ቅዳሜና እሁድ ያሳደረኝ ጓደኛዬ መምህር ሳለአምላክ ጥላሁን ሲሆን እንደ ፈረንጅ አገር ባለ መኝታ ቤቶች አሳድሮ ቁርስ አብልቶ ይሸኘኛል፡፡ በአያሌው አመሰግናለሁ፡፡ ደጋግሞ ‹‹ኮንዶሚኒየም ቤት እንከናም ነው›› ይለኛል፡፡ መታጠቢያ ቤት ውስጥ የተዘጉ እና ቁልፉም በማስቸገሩ ሰው ሳይሰማቸው ውለው ያደሩ ሰዎች እንዳሉ ሳለአምላክ ነግሮኛል፤ ከሌሎችም ሰምቻለሁ፡፡ ሰኞ አከራዬ አንድ ባለገራዥ ይዛልኝ መጣች፡፡ እርሱም በሩን አይቶት ዛሬ ሚካኤል ስለሆነ ብሎ ነው መሰለኝ ‹‹ወደ ማታ እመጣለሁ ከቅዳሴ ሲወጡ›› ብሎኝ በሩን አይቶትና ካል የሚባለውን ቁልፍ በ420 ብር አጋዝቶ ተሰናበተኝ፡፡
በተቀጣጠርንበት ሰዓት ብጠበቀው ቀረ፡፡ ስደውልለት አያነሳውም፡፡ ማታ 12፡30 አካባቢ ደውሎ አልመጣም ነገ ጠዋት 1፡00 እመጣለሁ ብሎኝ እርፍ! ያገሬ ሰው ‹‹አናጢ፣ መናጢ›› ያለው ወዶ መሰላችሁ! ይህን አለመምጣቱን በሰማሁበት ጊዜ ወደ ደ/ብርሃን ከተማ ሄድኩ፡፡ ቤርጎም ያዝኩ፡፡ ለስራ ጉዳይ ወደ ከተማው ከመጣው አጎቴ ጋር አደርኩ፡፡ የቤርጎ የከፈለው እርሱ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ስናወራም ‹‹ኦባማ በቃ እንደበሬ ሆነ እኮ›› አለኝ፡፡ እርስዎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ወፈሩ ማለቱ ነው ወይ ሊሉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ግን ገበሬው ሁሉ መኪና ገዛ ማለቱ ነው ስልዎት ከልቤ ነው፡፡ አስተማሪ መኪና የሚገዛው ከስንት አንድ ሆኖ ሳለ ገበሬው እና ከአራተኛ ክፍል ያቋረጠው ጓደኛዎ ባለ ኦባማ ሲሆን ቅር እንዳይልዎት! ሰው ያለለትን ነው የሚያገኘው፡፡ እግራችን ደህና ይሁንልን፡፡ አድሬም ወደ ጠባሴ (ቀበሌ 09) ከንጋቱ 12፡30 አካባቢ ላይ መጣሁ፡፡ ጠዋት ዝናብ በመሆኑ ሰውዬው ሲዘገይብኝ ‹‹እንደኔ ያለ ሰው እንዲህ ከተፈጥሮ ጋር ይፋለማል›› አልኩ፡፡ በዚህ ወቅት በጓደኛዬ በአማን ቃዲሮ በር አጠገብ ከውጭ ሆኜ የሰውየውን መምጣት እጠባበቅ ነበር፡፡ ‹‹መዘምር ዛሬማ አማርኛሽም ተቀይሯል›› ይለኛል፡፡ ስናደድ እና መላው ሲጠፋኝ እውነተኛው ስብዕናዬ ወጣ መሰለኝ፡፡ ሰውየው ወደ 2፡00 አካባቢ መጣና በሩን ገነጠለ፡፡ የራሴ ቤት እንዲኖረኝ መከረኝ፡፡ መልካም ነው፤ ሌሎችም፣ የስራ ባልደረቦቼም መክረውኝ አልሰማ ብዬ ነው፡፡ ብሰማስ ምን አመጣለሁ፡፡ አዲሱን ካል ቁልፍ ለመግጠም ሲሞር የብሎን ማገቢያዎቹ ቀዳዶች ስላስቸገሩት ወደ ስራው ቦታ መብሻ (ድሪል) ለማምጣት ሄዶ እስከ 6፡00ም አልመጣም፡፡ ሄዶም ካመጣ በኋላ በሩን በስቶ አስተካከለልኝ፤ መክፈትና መዝጋትም ተቻለ፡፡ ከሰውነቴ ላይ የሆነ ነገር ሲለቀኝ ተሰማኝ፡፡
‹‹መጣና ባመቱ ኧረ እንደምን ሰነበቱ?
እዚያ ማዶ ሆ…›› የሚሉት ልጆች አመቱን ጠብቀው ጎረቤት ሲያሞግሱ ይህን ጽሑፍ እየተየብኩ ነበር፡፡ የኔን አከራረም ይጠይቁኛል ብዬ ሳስብ የኔ ቤት ገባ ስለሚል አላዩትም መሰለኝ ወደ ሌላ ቤት ሄዱ፡፡ እኔና አንድ የደሴ ኮሌጅ የእንግሊዝኛ መምህር አጠገብ ላጠገብ ተቀምጠን አዳማ ራስ ሆቴል ስለ እንግሊዝኛ ማስተማር የዛሬ ሁለት ዓመት ስንሰለጥን የደላቸው በሆቴሉ ባለ መዋኛ ገንዳ ሲዋኙ ‹‹አየህ እኛ እዚህ ስንት እናነባለን እንጽፈለን እንጨናነቃለን እነሱ እንደዚህ ይዝናናሉ›› ብሎ እንደታዘበው ሁሉ የኛ አከራረም ከበድ ይላል፡፡ ባይጠይቁን ይሻላል፡፡ ግን ላገራችን ለውጥ ስለምሰራ እንጽናናለን፡፡
የሸቀጦች ጥራት
‹‹የተቀደደ ሱሪ ለብሰው ክፍል ሊያስተምሩ ሲመጡ የማይሸማቀቁ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን እየመጡ ነው›› ያሉኝ ነባር መምህር እንደታዘቡት ሁሉ የተቀደደ ልብስ የሚለብሱ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ ገበሬዎች፣ አናጢዎች፣ ሀኪሞች ባጠቃላይ ዜጎች ይኖራሉ፡፡ ለምን በሉ፡፡ ከምክንያቶቹም ውስጥ ዋነኛው ወደ ሐገራችን የሚገቡ ምርቶች ጥራት ማጣታቸው ነው፡፡ አንድ ህንዳዊ መምህር ሁለት ዓመት ለበስኩት ያሉኝ ጫማ ሁለት ሳምንት የተለበሰ አይመስልም፡፡ እኔ በ750 ብር የገዛሁት ጫማ ግን ገና ወር ሳይሞላው ነው ይላጥ የገባው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ መሸማቀቅ ያለብኝ እኔ ነኝ ወይንስ ይህን የሞተ ጫማ አገር ውስጥ ያስገባው? በየወሩ የሚቀየር ቁልፍ ለምን ወደ ሐገራችን ይገባብናል፡፡ የሸማቾች መብት ጥበቃ ባለስልጣን በራዲዮ ፋና ሕንጻ ስንትና ስንት ፎቅ ይዞ እና በየዞኑ ሳይቀር ቢሮ ከፍቶ ለሰራተኞቹ እኔ ከምከፍለው ግብር እየተከፈለው የማንን ጎፈሬ ያበጥራል! ስንትና ስንት ሺህ ብር የወጣበት ሞባይል ሲበላሽ ‹‹አይ እሱማ ሃይ ኮፒ እኮ ነው ምን ማድረግ ይቻላል?›› ሲባሉ ከብስጭት በቀር ምን ይውጥዎታል፡፡ በትግራይ ስላለው የጋብቻ ስርዓት እና ሙሽራው ስለሚጠበቅበት ግዴታ ያስረዳኝ የትግራይ ተወላጅ ያለኝን ነገር ይህን ሁሉ አገር ሄጄ ላምጣው፡፡ ‹‹ያንተ ሚስት በወርቅ ሳትንቆጠቆጥ ከታየች ይህች ማነች ሳይሆን ይህች የማነች ሚስት ብለው እርሷን ሳይሆን አንተን ነው ሰዎች የሚሰድቡህ›› ብሎ እንዳለው ሁሉ አንድን የተጎሳቆለ ኢትዮጵያዊ ያየ ሰው ያንን ጎስቋላ ሳይሆን መንግስቱን ነው የሚወቅሰው፡፡ መንግስት አንድ የሁላችንም አባት የሆኑ ትልቅ ሽማግሌ ሰውዬ እንዳልሆኑ ይገባኛል፡፡ መንግስት የሚመስለኝ ሁላችንም ነን፡፡ በኮንዶሚኒየም ሕንጻዎች አሰራር ያለውን ንቅዘት ዝም የምንል ዜጎች፣ ሐላፊዎች፣ ነጋዴዎች፣ ስራ ተቋራጮች ሁሉ!
የጋራ ቤቶች ወንጋራነት
ያገሬ ደማሞች እንደሚሉት ከሆነ ‹‹የጋራ ወንጋራ›› ነው ማለቴ አያስወቅሰኝም፡፡ የጋራ ቤት መስራት እርግጥ ነው ቦታ ይቆጥባል፡፡ እርግጥ ነው ቤት መስሪያ ገንዘብ ለሌለው ሰው ጊዜያዊ መፍትሔ ይሰጣል፡፡ አሁን ማን ይሙት የላይኛውን ቤት ቆሻሻ የታችኛው በምን ዕዳው ነው የሚያስታምመው! ከጋራ ቤቶች ችግር የሌለበት አይታችሁ ይሆን ወዳጆቼ? በሩ፣ ሲንኩ፣ የመጸዳጃው ቤት ዕቃዎች፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎቹ ለእርስዎ አገልግሎት ሳይሆን ራስ ምታት ለመስጠት የተጣሉብዎት ዕዳዎች ናቸው፡፡ ‹‹በቀላሉ የተሰራ የገጠር ቤት ምን አለበት?›› ስል ነበር፡፡
በተንገላታሁባቸው 4 ቀናት እንዳየሁት ስደት ክፉ ነው፡፡ እኔስ በወገኔ መሃል፣ በሰላም አገር ሆኜ ነው፡፡ ከሃገራቸው ወጥተው በጦርነት ውስጥ እየማቀቁ የሚኖሩትን ሰዎች አሰብኳቸው፡፡ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆኜ ያጋጠሙኝ ነባር አዲሱን ተማሪ አናናቂ ከሰሜን ሸዋ እና ከወሎ የመጡ ተማሪዎች መኖሪያ አሳጥተው ያሰቃዩኝ ትዝ አለኝ፡፡ ጉልቤ (bully) እንዲጠፋ እፈልግ ነበር፡፡ ያው አይኑን ማጥፋት የማይቻል ስለነበረ ማለት ነው፡፡
ለበጎ ነው
‹‹ኮንዶሚኒየም በዚህ ሁኔታ ከተቀበለህ ይህ ቤት የሆነ ደግ ነገር ያመጣልሃል›› በማለት መልካም ምኞቱን የገለጸልኝ የሐረሩ ተወላጅ መምህር አሸናፊ ምን ዓይነት በጎ ነገር እንደተመኙልኝ ግልጽ አላደረጉልኝም፡: ይህንንም መናገር የቻልንው ቤቶቹ ቢሰሩ እንደሆነ አንክድም፡፡ እሰይ ቤት ይሰራ! ግን በጥሩ ሁኔታ ይሁን፡፡ አንዳንድ አከራዮች ውለው ይግቡ፡፡ የእነርሱ ቤት ባይኖርልን የት እናርፍ ነበር? እኔ ያየኋቸውን አይነት የአዲስ አበባ አከራዮችን ግን ውለው ይግቡ የሚለው ምርቃት ይበዛባቸዋል፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...