የጉዞ
ማስታወሻ
ጉም አስጎምጉም
በመዘምር
ግርማ
የደብረ
ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጅኦግራፊና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች ለቱሪዝም ትምህርት ማሟያ የመስክ ጉብኝታቸውን
ወደ መንዝ ጓሳ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ቅዳሜ ታህሳስ 25፣ 2007 ዓ.ም. ያደርጉ ስለነበር ባላቸው የሶስት ሰው ትርፍ ቦታ ከትምህርት ክፍሉ ውጭ የመጣን
ሶስት መምህራንን አክብረው ይዘውን ስለሄዱ በማመስገን ልጀምር፡፡መኪናው የሐበሻ ቀጠሮ ልማዱን ሳይለቅ ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ላይ
እስኪመጣ ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ጅሩ መንገድ እንጠብቀው የነበርንው ሰዓት አክባሪ ሶስቱ መምህራን የበጋው የደብረ ብርሃን ቁር ሁለመናችንን ሲቆፍረን ነበር ያረፈድንው፡፡ ዩኒቨርሲቲው
በተከራያቸው ሁለት ቅጥቅጥ በሚባሉ የህዝብ መኪናዎች ጉዞው ተጀመረ፡፡ መኪናው ሙዚቃ አልነበረውምና የጠዋቱን ብርድ የሚያስረሳ የወጣቶቹ
ተማሪዎች የስልክ ላይ ሙዚቃና የመኪና ውስጥ ጭፈራ ተጀመረ፡፡ ተማሪዎቹ በራሳቸውም ያወርዱና ይዘፍኑ ጀመር፡፡
በጉዞዎች
ላይ የሚታዩ የጭፈራ አይነቶች እና የአዘፋፈን ስልቶች የራሳቸው የሆነ ውበት ይታይባቸዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በአድህኖ የተቀናጀ
የገጠር ልማት ማህበር ግብዣ ወርቅ ጉር ገብርኤል (ጎሼ ባዶ አቅራቢያ) ከአምስት ጓደኞቼ ጋር ለንግስ በምሄድበት ወቅት ምዕመናኑ
በዝማሬ ሲቀዛቀዙ አውራጇ የሚያበረታቱበት ግጥም
‹‹ኧረ
ሴቱ ፈዟል፣ ኧረ ወንዱ ፈዟል፣
ዝማሬ
ነው እንጂ ሌላ ምን ተይዟል››
የሚለው
ግጥም በመንዙ የተማሪዎች እና የኛ ጉዞ
‹‹ኧረ ሴቱ ፈዟል፣
ኧረ ወንዱ ፈዟል፣
ጭፈራ
ነው እንጂ ሌላ ምን ተይዟል››
በሚል
ተቀይሮ ሰማሁት፡፡
ተማሪዎቹ
በጉዟችን ወቅት የዘፈኗቸውን ዘፈኖች አዝማቾች እና የተወሰኑ ግጥሞቻቸውን እስኪ ላካፍላችሁ፡፡
1.
ኧረ እማማ ዘነቡ፣ ኧረ እማማ ዘነቡ
ጓሳን
የምናየው በማነው ሰበቡ?
2.
ኧረ ምታው ምታው ምታው ባንገትህ
ቢገጥም ባይገጥም አንተ ምን ቸገረህ
ምንም ባይሳካ ሲኒየር ሆነህ
ስትመረቅ እኮ ቲቸር እኮ ነህ
(በዚህ ጉዳይ ተገርሜ መምህርነትን የሚወድ
ትውልድ ተፈጠረ ብዬ በማሰብ ከመኪና ስንወርድ ከተወሰኑ ተማሪዎች ጋር ባደረኩት ውይይት እንዳስተዋልኩት ከሆነ ተማሪዎቹ ዕጣ ፈንታቸውን
አውቀውታል፡፡ በኛ ጊዜ የስነትምህርት ተማሪዎች እኛን አፕላይዶችን ቲቺንግን ስያታልሏት ኖን ቲቺንግ አሏት እያሉ ዕጣ ፈንታችንን
የተነበዩልን ለነዚህ ተማሪዎች ከአሁኑ እንደተገለጠላቸው ተገነዘብኩ፡፡ እነርሱም አፕላይድ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡)
የታደሉ ሰዎች ጂኦ ይማራሉ
ሁለተኛ ዓመት ላይ ጓሳ ይሄዳሉ
ሲመረቁ ደግሞ ቲቸር ይሆናሉ፡፡
በድህረ ምረቃው መርሃ ግብር አ.አ.ዩ. ዶክተር
ታመነ ኪቲላ ፔዳጎጂ ሲያስተምሩን እንዳሉት ከሆነ በአስተማሪነት እቆያለሁ ብሎ የሚያስብ እና ሙያውን የሚወደው ሰው የተሻለ ያስተምራል፡፡ እናት ሃገር ሆይ! ሙያውን የሚወድ መምህር መጣልሽ፡፡ እንደሱ ዓይነቶቹን
ያብዛልሽ እልሻለሁ፡፡
3.
ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ
ጂኦ ድል አድርጎ ሲገባ
(ይህን ዘፈን የ1980ውን የምስራቅና መካከለኛው
አፍሪካ ዋንጫን እንደበላን ነው የሰማሁት አሉ አንዱ መምህር)
4.
የሚገርመውና በጉዟችን በተደጋጋሚ
የሰማሁት አውራጅና ተቀባይ የሚቀባበሉት ምልልስ ያለበት ግጥም
አውራጅ፡ ዴ በላንዴ
ተቀባይ፡ ዴ
አውራጅ፡ መኪናው ሲዲ የለውም እንዴ?
አውራጅ፡ ዴ በላንዴ
ተቀባይ፡ ዴ
አውራጅ፡ ጓሳ አልደረስንም እንዴ?
እዚህ አገር ዛፍ ብቻ ነው ያለ እንዴ?
5.
ያምራል አገሬ ኧረ ያምራል አገሬ ያምራል አገሬ
የትም የትም ዞሬ ባንቺ ነው ማማሬ
6.
ሰለሜ ሰለሜ
7.
የዓይኔ አበባ ነሽ የዓይኔ
አበባ
ቱሪዝም አበባ
ያይኔ አበባ
8.
ሃይ ሎጋ ሃይ ሎጋዬ ሆ
ሃይ ሎጋ
ይወለድና እንከፍ እንከፉ
ጋን ይሸከማል
ከነድፍድፉ
ይወለድና ሆዳም ሆዳሙ
ካፌ ይሰቅላል 12፡00 ሰዓት
እስክስታ የሚመታባቸውና
ዳንስ የሚቀልጥባቸው ዘፈኖችም ከስልኮች ጉሮሮ ይንቆረቆራሉ በየመሃሉ፡፡ የጉራጌኛ፣ የኦሮምኛ፣
የትግሪኛ እና የሌሎችም ቋንቋዎች ዘፈኖች ሰቀልጡ አረፈዱ፡፡
እንኳን ልከሽብኝ ልብሽን ወደኔ
እንደዋለ ያድራ ሲርገበገብ ዓይኔ
አባይ ጣናን ዞረሽ አምረሽ ተኳኩለሽ
ነይ በፈረሱ ጋልበሽ
ያው
አዝማሪ ስላልያዝን እና የተቀረጸ ዘፈን በመሆኑ አባይ ጣናን ዞረሽ ያለው ዘፋኝ መሃል ሜዳ ዞረሽ ብሎ ሊገጥምልን አልቻለም ፡፡
ይህን ሁሉ ጥበብ ሳይ ታዲያ የዩኒቨርሲቲያችን የባህል ማዕከል የልጆቹን የጥበብ ዛር ማባበል እንዳለበት ታየኝ፡፡
በ2002
ዓ.ም የታተመ የአዲስ አድማስ ጋዜጣን እያነበብኩ ነበር እየተጓዝኩ
የነበረው፡፡ አንዱ ገጽ ስለ እድሜ ልክ ድንግልና የሚያወራ ነበር፡፡ የጽሁፉ መነሻ አንዲት
ወጣት ‹‹ጓደኛዬ ወሲብ ስናደርግ ስላልደማሁ ድንግል አልመሰልኩትም›› ብላ ለጋዜጣው የጻፈችው ደብዳቤ ነበር፡፡ ስለድንግልና አይነቶች
እና ስለዕድሜልክ ድንግልና ማለትም ወሲብ እየፈጸሙም ሆነ ልጅ እየወለዱ ስለማይጠፋው አይነት የሚያትተውን ገጽ አንብቤ ቀድጄ ወደ
መኪናው የዕቃ ማስቀመጫ ቆጥ ወረወርኩትና ቀሪውን ንባቤን ቀጠልኩ፡፡ በነገራችን ላይ ጋዜጣ ሳነብ ያነበብኩትን ገጽ እየቀደዱ መጣል
ያስደስተኛል፡፡ ይህ ወረቀት ከቆጡ ወርዶ አንደኛዋ ተማሪ ላይ ያርፍባታል፡፡ ርዕሱን አይታ፣ ወረቀቱን ደባብሳ እና አገላብጣ ጣለችው፡፡
የሴቶች ጉዳይ በሴቶች ለመነበብ አለመፈለጉ ገርሞኝና የንባብ ፍራቻችንን ታዝቤ ንባቤን ቀጠልኩ፡፡
መንዝ ሳንደርስ በሚኒልክ መስኮት
ጉብኝታችን ላይ ተማሪ ታምሩ ዋቻራን ስለጉዞው ጠይቄው ‹‹አላማችን ቦታው ላይ ችግር ካለ ደካማ ጎኖቹን ለማየት እና ችግሩን ጠቁመን
ስፍራውን ለጎብኝ አመቺ ለማድረግ ነው›› ብሎኛል፡፡ ተማሪ የኔካሳ
ዮሴፍ ደግሞ መኪና ውስጥ በጠየኳት ወቅት‹‹ጓሳን አይተን ለመምጣት ነው ሃሳባችን፤ የፒስታውን መንገድ ሁኔታ የምታየው ነው ለቱሪስት
አይመችም፤ ለጉብኝት ጥሩ መኪና መኖር አለበት፤ ምግብና በቂ አገልግሎት የለም ተብሏል፤ መሻሻል አለበት›› በማለት የታያትን ሃሳብ
ሰንዝራለች፡፡ ቃልኪዳን ተስፋዬ ደግሞ ‹‹ሃገራችን የተለያዩ የተፈጥሮ ገጽታዎች አሏት - የተፈጥሮ ደን፣ አራዊቶች፡፡ ልማት ግን
መስፋፋት አለበት -ለቱሪስት እንዲመች፡፡ ፒስታው ደረጃው ቢስተካከል ጥሩ ነው፡፡›› ብላኛለች፡፡
ትምህርት ቤት ከመዘዞ ከተማ
ውጭ ጓሳ እስክንደርስ አለማየታችን ያሳሰባቸው ነበሩ፡፡ ‹‹ሊወድቅ የደረሰ ቤት ጋ ትምህርት ቤት ይላል፡፡ትምህርት አለ ወይ? መምህር አለ ወይ? ያስብላችኋል፡፡›› አለ አንደኛው ተጓዥ፡፡ ምንአልባት ትምህርት ቤቶቹ ከመንገዱ ርቀው ተሰርተው ሊሆን ይችላል፤ አላውቅም፡፡ በመንገዳችን አንድ ደብረ ብርሃን
የሚገኘውን የሃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤትን ዩኒፎርም የለበሰ ተማሪ
ብቻ ማየታችንን ሳስበው እኔንም ተማሪዎቹ የት አሉ? አስባለኝ፡፡ ስንመለስ የመንገዱ ሌላኛውን አቅጣጫ ስለምናይ አንድ ሌላ ትምህርት
ቤት በግድ አገኘን፡፡
ከባሽ ከተማ በኋላ ባለው ጉዟችን
የእርከን ስራና በእርከኑ ጥግ የመኖ እጽዋት በማየቴ ተደስቻለሁ፤ እንደ ጎሼ ባዶ ምን አልባት እስካሁን ካልተደረገ በዘመናዊ የማር
ምርት ቢታጀብ እላለሁ፤ የንብ መኖ የሚሆኑ ዛፎችንም መትከል ስለሚቻል፡፡ ችግሩ ግን ይህ ሃሳቤ እዚያ ያሉት ሃላፊዎች ዘንድ እንዴት
ይደርሳል የሚለው ነው፡፡ ባሽ ላይ ሆኖ ሸዋሮቢት ከተማን ማየት ጣርማበር ተራራ ላይ ሆኖ ደብረሲና ከማየት በላይ ልብን ይሰውራል፡፡
ዳኛቸው ወርቁ አቧራ የረጋበት የሚመስለው የሚለው ይፋት እውነትም እንደ ጥቁር ጉም መሳይ ነገር እንደሸፈነው ለማየት ችያለሁ፡፡ መንዝ ብዙ የባህር ዛፍ እና መጠነኛ የጽድ ደን ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ምን
ጊዜ ተከሉት ይህን ሁሉ ያስብላችኋል፡፡ ከደቡብ የመጡት ተማሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም ከመጡበት ስፍራ ጋር በማወዳደር ‹‹መንዝ ላይ
ልምላሜ ወፍ የለም›› ሲሉ ግን ገና እንደሚቀረን አሰብኩ፡፡
የአንኮበር ቤተመንግስት ሎጅን
የሚመስለው የጓሳ ማህበረሰብ አቀፍ ፓርክ የእንግዶች ማረፊያ እልፍኝ እና ጎጆዎቹ ከሩቅ በአስታ ጫካ ተከበው ከተራራውና ሸንተረሩ
ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታዩ አዕምሮን ያረጋጋሉ፣ መንፈስን ያድሳሉ፣ ሁለመናንም ይጣራሉ፡፡ በጎዴ ከተማ መልክ በአባይ ተፋሰስ አጥኝዎቹ
አሜሪካውያን ፊታውራሪነት በዘመናዊ መልክ ለመንዝ ህዝብ የአስተዳደር
ማዕከል ትሆን ዘንድ በ1959 የተቋቋመችው እና የዚያን ጊዜ የተጀመሩት የአስተዳደር ህንጻዎቿ አሁንም እንዳላለቁላት የሰማሁላት
እና ያነበብኩላት ከተማ መሃልሜዳ ለመድረስ 22 ኪሎሜትር ሲቀረን ፓርኩ ላይ ወረድን፡፡ ‹‹መሃልሜዳ መንዝ መሃል ሜዳ›› አለች
ዘፋኝ፡፡ ያኔ ከአሜሪካውያኑ ጋር አብሮ በሃላፊነት ይሰራ የነበረው ተጉለቴው ዶክተር ሃይለጊዮርጊስ ወርቅነህ ያነሳቸው የልማት ዕቅዶች
የበጉን እርባታና የእርሻውን ምርት ማዘመኑ አሁን መነሳሻውና መታወሻው ሰዓት አይመስላችሁም?
እንደ ፓርኩ ኃላፊ እንደ አቶ
አበበ ገለጻ ከሆነ ፓርኩ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በማህበረሰቡ የሚጠበቅ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ ወደክልሉ ሰውና ከብት ካስገቡ ከፍተኛ
ቅጣት ይጣልባቸው ነበር - ፓርኩ በባህላዊ አስተዳደር በነዋሪው ሲተዳዳር፡፡ ትኩስ የነብር ለምድ፣ የቀጨሞ ሙቀጫ (ቀጨሞ ውስጡ ክፍት ነው አሉ) እና አንድ ሺህ ዳውላ እህልን ዓይነት የማይፈጸሙ
ቅጣቶች ማህበረሰቡ ራሱን ከስፍራው እንዲያገል ለማድረግ ይጣሉ ነበር፡፡ በተወሰነ ጊዜ እየዘጋን እየከፈትን ብንጠቀምበት ይሻላል
ያሉት ከጎንደር መጡ የተባሉት የመንዝ መስራች ሁለት ወንድማማቾች ስፍራውን ሲከባከቡት እንደኖሩ አስጎብኛችን ነግረውናል፡፡ ከሰው
ንክኪ ለተከለለው ስፍራ አመራር አቋቁመው ከ3 እስከ 5 ዓመት ድረስ ይጠብቁትና ጓሳውን ይጠቀሙበታል፡፡ ማገዶ እንጨት ቢኖርም ዋናው
ለቤት መስሪያ የሚጠቀሙበትን ጓሳ ነው በጣም የሚፈልጉት፡፡ ‹‹ጓሳ ደማችን ነው ብለው ስለሚያምኑ አሁም ይጠብቁታል›› ብሎናል አቶ
አበበ፡፡
የዩ.አይ.ኤ.ኤ ተራራ ክብካቤ
ሽልማትን ያገኘው እና በዘመናዊ መልክ እ.ኤ.አ. በ2003 የተመሰረተው
መንዝ ጓሳ በሰሜን ኢትዮጵያ በአፍሮ አልፓይን ተራሮች ክልል ውስጥ ይገኛል፡፡ ማስጎብኘቱና ዘመናዊ አሰራሩ እ.ኤ.አ.
ከ2009 ጀምሮ እንደጀመረ፣ እንዲሁም በጀርመኑ የፍራንክፈርት ዙኦሎጂካል ሶሳይቲ እና በአውሮፓ ህብረት እገዛ እንደተቋቋመ ተነግሮናል፡፡
ቀይ ቀበሮ፣ አንኮበር ሰሪን የተባለች ወፍ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እንዲሁም ሌሎች እንስሳት በስፍራው ይገኛሉ፡፡ዝንጀሮዎቹ ዋሻ ውስጥ ካደሩ
ጅብ ስለሚበላቸው ገደል ላይ ያድራሉ፡፡ አብዛኞቹን እንስሳት ለመጎብኘት በጠዋት መነሳትና ርቀት መንገድ መሄድ ግድ ይላል፡፡ የማህበረሰብ
ጥብቅ ስፍራው አላማ ማህበረሰቡን መጥቀም ነው - ጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤት የመሳሰሉትን የህዝብ መገልገያዎች መስራት፣ በዕደ
ጥበብ በተለይ በባና ስራ ህዝቡን መጥቀም እና በአጠቃላይ ስነህይወታዊና ባህላዊ ሃብቶችን መንከባከብ ፡፡ የጓሳ ክልል 7800 ሄክታር ይሸፍናል፡፡
ፓርኩ የሚያስጎኛቸውን ሁሉ ጎብኝቶ
ለመጨረስ አንድ ጎብኝ የሶስት ምሽቶችና የአራት ቀናት ጉብኝት ያስፈልገዋል፡፡ 11 አልጋ እና 6 ክፍል መኝታ ቤት በስፍራው ሲኖር
ጎብኝዎች በብዛት ከመጡ በድንኳን ያድራሉ ወይንም ወደ መሃል ሜዳ ከተማ ይሄዳሉ የሚል መረጃ ተሰጥቶናል፡፡ ፓርኩን በአመት ከ300
ያነሰ ሰው የሚጎበኘው ሲሆን በብዛት የሚጎበኘው አዲስ አበባ በሚኖሩ የውጭ ዜጎች ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ጎብኝ በጣም አነስተኛ ነው፡፡
የፓርኩ ባለንብረቶች በአቅራቢያው
ያሉት የዘጠኝ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ፓርኩን ያቋቋመው የውጭ ድርጅት በተለያዩ ምክንያቶች ስፍራውን ለቆ በመውጣቱ የአማራ
ክልል የጓሳ ማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽ/ቤትን አቋቁሟል፡፡ ለሰራተኞች የሚከፈለውን ደሞዝና የስራ ማስኬጃውንም ከጉብኝቱ እና ዶክመንታሪ
ፊልም ከሚሰሩ አካላት ከሚገኘው ክፍያ ይሸፍናሉ፡፡ ሎጁ እንዳይድግ የመንገድ ችግር አለ፡፡ ጥበቃው ደካማ ስለሆነ የፓርኩ ተጠቃሚ
አይደለንም የሚሉ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ከአጣዬ እየመጡ ጓሳውን ያቃጥሉ ነበር፡፡
በስፍራው ያገኘናቸው ጀርመናውያን
ቱሪስቶችን ይዞ የመጣው ‹‹ጀርመን ሃገር 28 ዓመት ኖርኩ፤ አሁን ግን አዲስ አበባ ተመልሻለሁ›› ያለን ሐበሻ ‹‹የቱሪዝም ኢንዱስትሪው
እዚህ አገር ውድ ነው›› ብሏል፡፡ ‹‹ከጀርመን ተነስተህ፣ ግብጽ ደርሰህና አካባቢውን ጎብኝተህ 15 ቀን ተዝናንተህ ከነአውሮፕላን
መሳፈሪያው 300 ዩሮ ትከፍላለህ፤ እዚህ ግን 3000 ዩሮም የበረራ ወጭህን ሸፍኖ ሁለት ሳምንትም አያኖርህም፡፡ የኢትዮጵያዊና
የፈረንጅን ዋጋ መለያየት አስመልክቶ ጀርመኖቹ እናንተ አገር የጥቁር አፓርታይድ አለ ብለውኛል›› ብሎናል፡፡ ‹‹ልጄ ማስተርሱን
እያደረገ ነው፤ ኢትዮጵያ መጥቶ የተማረው አማርኛ ‹መብራት የለም፣ ውሃ የለም፣ ችግር የለም › የሚል ነው›› አለን፡፡
በጓሳ
በጥበቃ ስራ ላይ ለተሰማሩ አንድ ሰው ያቀረብኩት ጥያቄ ነበር፡፡ ይኸውም ‹‹መንዞች የጥንቱን የአባቶቻችሁን ትውልድ፣ ዘራችሁን
እንዴት ነው የምትቆጥሩት›› የሚል ነበር፡፡ ‹‹ምን እኔ ብዙም አላውቀውም፤ ግን የሚየውቁት ሲቆጥሩት ከመጀመሪያው ጀምረው ጉም አስጎምጉም ብለው ነው የሚጀምሩት፡፡›› አሉኝ፡፡ የዚህንም ጉም አስጎምጉም
የሚለውን ትርጉሙን ሳሰላስል ቆየሁ፡፡ ጉም አንዴ መጥቶ አስገምግሞ አደባይቶ ያልፋል፤ ዝናቡን፣ በረዶውን፣ ካፊያውን እና ውሽንፍሩን
አውርዶት፡፡ ወይንም ዳኛቸው ወርቁ እንደሚለው ጀጅሮ፣ ወይንም ተጉለቶች እንደሚሉት በነሃሴ እኝኝ ብሎ፣ አፍኖ፣ መብረቅ በመብረቅ
አድርጎት፡፡ መሬቷ ከመስከረም ወዲህ አትረጋም ይላሉ ዝናቡ እስካለ ድረስ፡፡ ልክ እንደወላድ ያደርጋታል፤ ወልዳ የምትገላገለው ጸደይ
ሲገባ ነው፡፡ ያ አንድ ትውልድ መሆኑ ነው ወደ ሰዎች ሕይወት ስናመጣው፡፡ መንዞችም ትውልዳቸውን ከዚህ ጉምና ውጤቱ ጋር አዛምደውታል
ማለት ነው ጉም አስጎጉም ሲሉ፡፡ ከመንዝ በመጣሁ በማግስቱ አያቴን አግኝቻት ስለዚህ ጉዳይ ማለትም ስለ ጉም አስጎምጉም ስጠይቃት
‹‹በኛ በተጉለቶች ዘንድ ሰው ሲበዛ ነው እንደዚያ የሚባለው፤ በለቅሶም በሰርግም ሰዉ ጉም አስጎምጉም ነው ከተባለ እንደ አሸን ፈላ ማለት ነው›› ስትለኝ
‹‹ይህም አለ›› ብዬ ‹‹ሌላ መንዜ ዘር ቆጠራ አዋቂ አዛውንት እስካገኝ
ልጠብቅ›› ብዬ ዝም አልኩ፡፡
ተማሪዎቻችን
ጠዋት ያስረፈዳቸው ነገር ከዩኒቨርሲቲው ምግብ ቤት ምግብ ማስቋጠር ኖሮ እነሱ የቋጠሩትን ፍርፍር፣ እኛም ጓደኛችን መምህራቸው የያዙትን
ስንቅ ጓሳ ግቢ ውስጥ በላን፡፡ እርስዎ ጓሳ መሄድ በሚፈልጉ ጊዜ ስለምግብ ጉዳይ የየማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራውን ሰዎች ማነጋገር ይኖርብዎታል፡፡ እያበሰሉ እንዲመገቡ ሁኔታው ይመቻችልዎታል፡፡ የጓሳ ሎጅ ግንቡ ከአካባቢው በሚገኘው ጥቁር ድንጋይ የተገነባ ሲሆን ጣራው ደግሞ በእንጨት
ተዋቅሮ ሳር የለበሰ ነው፡፡ እጽዋትን፣ ጭላዳ ዝንጀሮን፣ ፍልፈል የቆፈራቸውን ጉድጓዶች፣ የአካባቢውን የገጠር ቤት፣ የህዝቡን አሰፋፈር
እንዲሁም አኗኗር ለማየት ችለናል፡፡ ከተማሪዎቻችን ጋርም የተወሰነ ርቀት የእግር ጉዞ አድርገን አካባቢውን ቃኝተናል፡፡ የጦስኙ
ሽታ፣ የአስታው እና የጓሳው ትዕይንት፣ የመልከአምድሩ ወጣ ገባነት ሁሉ ቀልቡን ያልሳበው ጎብኝ ከመካከላችን አልነበረም፡፡ ከተምኞችና
የከተማን ህይወት የለመዱ ስለበዙ በየስፍራው ቁጭ ማለትና ሲሄዱም ማለክለክ የጉዞው አካል ነበር፡፡ ለተማሪዎቻችን በእንግሊዝኛ ማለክለክ
‹‹ቱ ፓንት›› እንደሆነ ነግሬያቸው የአንድ ኢትዮጵያዊን ተማሪ ገጠመኝንም ነገርኳቸውና በሳቅ ፈረሱ፡፡ ተማሪው አሜሪካ የትምህርት
ዕድል ደርሶት ጥቁር ፓንት ለብሶ እንዲሄድ የደረሰው የአለባበስ መመሪያ ያሳስበዋል፡፡ ግማሽ ደርዘን ቅያሪ ጥቁር ፓንት ገዝቶም
ይሄዳል፡፡ እንደገባም አሜሪካውያኑ የታል ጥቁሩ ፓንት ሲሉት ቀበቶውን ፈቶ ያሳያቸዋል፡፡ ግን በአሜሪካውያን እንግሊዝኛ ፓንት ማለት
ሱሪ ማለት ነበር፤ ተማሪውም ይህን አላወቀም ነበር፡፡ በኛ አገር ፓንት የምንለው ደግሞ በአሜሪካን አንደር ዌር ይባላል፡፡
በአጠቃላይ
ጉዳይ ከሌለው አንድን ስፍራ ሄዶ ለማይጎበኘው ለኛ ሰው ይህን ዓይነቱ አጋጣሚ የማይገኝ ነው፡፡ እኔም መንዝን እስካሁን ሳላይ ቆይቼ
ስላየሁት ደስተኝነት ተሰምቶኛል፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ይህን ዓይነት ጉዞ ማስጎብኘቱ ቢቀጥል የሚል አስተያየቴን
እሰጣለሁ፡፡ በቅርብ ያሉትን ስፍራዎች ሲጎበኙ አካባቢውን በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ለማገዝ ያመቻል፡፡ ሌላ ሩቅ ስፍራ ከሆነ
ግን ወጪውም ከፍተኛ ነው፡፡
አሪፍ
ምላሽ ይስጡሰርዝ