ማክሰኞ 6 ፌብሩዋሪ 2018

አርአያ - የመጽሐፍ ማጠቃለያ


ደራሲ - ግርማቸው ተክለሐዋርያት

የታተመበት ዘመን 1951

ዘውግ - ልቦለድ

ይህን መጽሐፍ ያገኘሁበት ታሪክ በራሱ መነገር አለበት፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ቆይታዬ በ2003 ዓ.ም. ነው እጄ የገባው፡፡ ስድስት ኪሎ ግቢ በር ላይ ዘርግቶ ከሚሸጥ ነጋዴ አግኝቼ በዐስር ብር ይመስለኛል የገዛሁት፡፡ ሳላነበው እስከዛሬ አቆየሁት፡፡ ይሄው ጊዜው ደርሶ ለመነበብ በቃ፡፡ ይህ የመጽሐፉ ቅጂ የጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ንብረት የነበረ ነው፡፡ ተማሪዎች ያነበቡት ስለሆነ የያዙት ማስታወሻ፣ ያሰመሩበት፣ የቃላት ፍቺ የጻፉበት ሁሉ አለበት፡፡ በ1950ዎቹና 60ዎቹ አማርኛን እንዴት በቁምነገር እንደሚማሩት ተገንዝቤያለሁ፡፡ አማርኛውን በእንግሊዝኛ የፈቱበትም አለ፡፡ አብዛኛው የተጉለት አማርኛ ዘዬ ነው መጽሐፉ የተጻፈበት፡፡ ለማናቸውም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ልቦለዱን ማንበብ ግድ ነበር፡፡ ይህ ትምህርት (ዊንጌት) ቤት የመጻሕፍት ክምችቱን ለምን እንደሚያሰርቅ አላወኩም፡፡ አሁንማ ቴክኒክ ትምህርት ቤት ስለሆነ ልቦለድ ላይኖረውም ይቸላል፡፡

መጽሐፉን ክፍል አምጥተው አለፍ አለፍ እያሉ ያነበቡልንና ያሳዩን በንዑስ አማርኛ እማር ስለነበር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ነበሩ፡፡ ዝርው ልቦለድ የሚል ትምህርት አስተምረውናል፡፡ የኢትዮጵያን ልቦለዶች ታሪክ ያስቃኘን ይህ ትምህርት ብዙም እንድናነብ አያስገድድም ነበር፡፡ በቅርቡ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ ፖለቲካው ዩነቨርሲቲ ስለገባ ይህን ጉዳይ በጽሑፍ ግልጽ ዓይነት ፈተና ቀርቶ የደራሲ ስምና ዓመተ-ምህረት መጠየቅ ጀምረናል ብለዋል፡፡ አዲስ ተማሪ ሆኜ ስገባ ገለጻ ያደረጉልን እኚሁ ዶክተር ቁጭታቸውን ያኔም አይቻለሁ፡፡ ምን ታደርጉታላችሁ! እኛም ብዙም የምናነብ ዓይነት አይደለን - በኔ እይታ የእንግሊዝኛ ተማሪዎች የንባብ ልምዳችን የደከመ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ቅኝት የተባለው ትምህርት የተሻለ አስነብቦናል፡፡ መምህርት ሠላማዊት መካ እናመሰግናለን! ለአስር ማርክ አሳይመንትሽ አምስት ልቦለድ ማንበብ ግድ ነበር፡፡

አርአያ የገጸባህሪው ስም ነው፡፡ ከሸዋ ተወላጆች ሐረርጌ ላይ ይወለዳል፡፡ በትምህርቱ ትጉህ ስለነበር አንዲት ፈረንሳዊት ወደ ፓሪስ ወስደው አስተማሩት፡፡ በዚያም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ፈጽሞ በእርሻ ሙያ ከተመረቀ በኋላ ወደ እናት አገሩ ተመለሰ፡፡ ትንሽ የቢሮክራሲን ውጣውረድ አየ፡፡ በእናት አገሩም እየሰራ ሳለ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ ትወራለች - በ1928 መሆኑ ነው፡፡ አርአያም ወደ ማይጨው ይዘምታል፡፡ በማይጨው ጦራችን ከደረሰበት ሽንፈት በኋላም በአርበኝነት ተሰማራ፡፡ አርአያ ሚስቱን ስርጉትን ያገኘው በዚሁ በአርበኝነት ዘመን ነው፡፡ አገሪቱ ነጻ ስትወጣም ወደ አዲስ አበባ ገብቶ ህይወቱን ጀመረ፡፡ ልቦለዱ ታሪካዊ ልቦለድ ሲሆን የወቅቱን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ያስገነዝባል፡፡ የፍቅርና ሌሎች አማላይ ልቦለዶች ማንበብ ለለመደ ሰው ሊሰለች ቢችልም በታሪክ ላይ ፍላጎት ላለው ሰው ሁነኛ የእውቀት ምንጭ ነው፡፡

ከረጅም ባጭሩ አርአያ ይህን ይመስላል፡፡ ከኢትዮጵያ ቀዳሚ ዘመናዊ ልቦለዶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በመሐል በመሐል ስዕሎች አሉት - በእማእላፍ ሕሩይ የተሳሉ፡፡ አርአያም ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዲሉ ለትውልድ አርአያ እንዲሆን ይመስላል የስሙ አሰያየም፡፡ የሃምሳዎቹ ልቦለዶች ስነምግባር ስለሚመክሩ ይህ ጭብጥ የተለመደ ነው፡፡ መጽሐፉ በ1930ዎቹ መጨረሻ ተጽፎ ቆይቶ ነው የታተመው፡፡ የደራሲው ቤተሰብ ታሪክም መሰል ይላል፡፡ የአባታቸውን ታሪክ ማንበብ ለዚህ ይረዳል፡፡ የፈረንሳይኛ ቃላት፣ አገላለጾችና ጥቅሶች በመጽሐፉ አሉ፡፡ ዛሬ እንግሊዝኛ ጣል እንደሚደረገው መሆኑ ነው፡፡ ግማሽ መቼቱም ፈረንሳይ፣ ፓሪስ ነው፡፡


ከድርሰቱ የወሰድኳቸው ጥቅሶች፡-

‹‹አዎን ለዘላለም በሚያስደንቅ ተአምር ኢትዮጵያ ነጻነቷን መልሳ  አገኘች፡፡ ነገር ግን እንግዴህ እንዳለፈው ተመልሳ ትተኛ ይሆን?፤ ያንድነትን ጥቅም የነጸነትን ዋጋ በዚህ ባምስት ዓመት መከራ አጥንታውና ተረድታው ይሆን? ጠላት ካደረገባት የጉዳት ስራ ውስጥ ወደ ፊት የሚጠቅም ትምህርት አግኝታበታለችን?፤ ኀይልና ሥልጣኔ ከምን እንደሚገኝ ተረድታዋለችን? ወዳጆቿንና ረዳቶቿን ለወደፊት ለይታ ዐውቃለችን፤ ደማቸውን አፍሰው የተሠዉላትን ቸሮች ልጆቿን ለወደ ፊት ታስባቸዋለችን? አንድነትና ኅብረት፣ ሙያና ምግባር የነጻነቷ ዋስ መሆናቸውን ተገንዝባው ይሆን? … እንደዚህ ብዙ ነገር ይስብ ነበር፡፡››

ለጥያቄው መልስ አለዎት? 



“Le Plus grand defaur de la penetration ce n’est pas de n’aller point jusqu’au bout, mais c’est de depasser”
‹‹ሲራቀቁ ያለው ታላቅ ጉድለት በነገሩ ባለመድረስ አይደለም፡፡ የነገሩን ወሰን አልፎ በመሄድ ነው እንጂ›› ፈረንሳዊው ዱክ ደ ላሮሽኩኮ
‹‹ጥበብን የሚፈልግ ከተፈጥሮ ጓደኛው በታች አይውልም፡፡›› ቀ. ኃ. ሥ
‹‹ገንዘብን ቆጥባት፤ ነገር ግን አትውደዳት፣ ፍቅሯ ኃይለኛ ነው፤ ሳይታወቅኽ ባሪያዋ እንዳታደርግኽ፡፡››
‹‹የጊዜን ዋጋ የማያውቅ ትልቅ ሊሆን አይችልምና፣ ጊዜህን በከንቱ እንዳታባክን››
‹‹በጣም አስቸኳይ የሆኑ ብዙ ጉዳዮች እያሏችሁ በሌሎች አትድከሙ፡፡››
“Celui qui voie les interets permanents en souffrance ou en peril et qui se tait, ne trahit pas seulment la verite, il trahit son pays.” DE LAMARTINE
‹‹መሰረታውያን ጥቅሞች ሲጎዱ ወይም ባደጋ ላይ ሲሆኑ ዝም የሚል እውነትን ብቻ አልካደም፤ አገሩንም ከዳ›› ደ ላማርቲን
‹‹እኛ የተማርነውን ወጣቶች አገራችን ስንገባ ገዢዎቻችን በደኅና ዐይን አይመለከቱንም፡፡ ለነጻነት ፍቅር እንዳለንና በተለይ ላገራችን ጥቅም ማሰባችንን ስለሚያውቁት የምናድግበትንና ቁም ነገር የምንሠራበትን መንገድ ሁሉ ተከታትለው ይዘጉብናል፤ ስለዚህ ሁሉ ወደ ፈተና እንጂ ወደ ደስታ እንደማልሄድ ይታወቃል፡፡››
‹‹ኢትዮጵያ አገራችን ምንም ባንድ መንግሥት ያለች አንድ አካ ብትሆንም በያውራጃዎቹ የመቀናናትና የመናናቅ መንፈስ መኖሩ የተረጋጠ ነው፡፡››

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...