ሐሙስ 31 ሜይ 2018

‹‹የሆሄ ጉዳይ ፈታኝ ነው፡፡›› መምህር ገብረሐና ዘለቀ


‹‹የሆሄ ጉዳይ ፈታኝ ነው፡፡›› መምህር ገብረሐና ዘለቀ
ሐሙስ ግንቦት 23፣ 2010 ዓ.ም. በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት በነበረው የውይይት ምሽት ‹‹የአማርኛ ፊደላት አጠቃቀማችን›› በሚለው ርዕስ ላይ ተወያይተናል፡፡ ርዕሱን የመረጠልን ሳሙኤል በለጤ ሲሆን ሊመርጥልን ያነሣሣውም በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን እንግዳ የሆኑ ፊደሎች በእጅ ተጽፈው ለትዝብት ፎቷቸው ተለጥፎ ማየቱ ነው፡፡ ቁልፍ የሚል ጽሑፍ ላይ የ‹ል› ቀለበት ዞራ ያለውን ምስል ልብ ይሏል፡፡
በውይይታችን ወቅት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጋብዘናቸው የተገኙልን መምህር ገብረሐና ዘለቀ በደብረ ብርሃን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሥነሕይወት መምህር ናቸው፡፡ የሰጡንን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ማስፈር ባልችልም አልፎ አልፎ እጠቅሳለሁ፡፡
እንግዳችን በሆሄ ቀረጻ ነው እንጂ በድምጻቸው ላይ እንዳልሰሩ ይናገራሉ፡፡ ለእርሳቸው ድምጹ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ በኦሮምኛ ፈትና በአማርኛ ፈት ተማሪዎች ላይ የተደረገ ምርምር አላቸው፡፡ በፊደል አቀራረጽ ላይ በቤተመጻሕፍቱ አባላት ላይ መጠነኛ ፍተሻ አድርገው በሥዕል መምህራን የአጻጻፍ ስልጠና ሊያሰጡ እንደሚችሉም ቃል ገብተውልናል፡፡
የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ ባዘጋጀው መዝገበ-ቃላት ላይ ሞክሼ ሆሄያትን እንዳልተጠቀመና አሁን በታተሙት የታች ክፍል ማስተማሪያ መጻሕፍት ላይም ፊደላቱ እንደሌሉ ነግረውናል፡፡ 
ስለ ድርብ ጽሑፍ ጉዳይ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች እንዳሉም ከማራኪ ገለጻቸው ተገንዝበናል፡፡
ፍልጹቅ ሆሄያት፣ ማለትም እንደ ‹ጐ› ዓይነቶቹ እየጠፉ ነው፡፡
የአጻጻፍ፣ ብዕር አያያዝ፣ የፊደል አጣጣል ነገር እየተበለሻሸ መጥቷል፡፡ ለዚህም የመጀመሪያ ተጠያቂዎቹ እኛ መምህራን ነን፡፡

ከተሳታፊዎች የተነሡ ሐሳቦችም ነበሩ፡-
ሀ. የአማርኛ ፊደላት ያሏቸው የተለያዩ ዓይነት ፎንቶች ስም አላቸው ወይ?
ለ. ‹ይዋ› የሚለው ድምጽ፣ ለምሳሌ ተቀባይዋ የሚለው ቃል ላይ እንዳለው፣ አንድ ራሱን የቻለ ፊደል አለው ወይ?
ሐ. በዉበታቸው የምናውቃቸው በእጅ ብቻ ሲጻፉ የምናውቃቸው ፊደላት አሁን እየጠፉ ነው፡፡
መ. ሁለት ነጥብ የት ገባች?
ሠ. የመጀመሪያውን የቴሌክስ ጽሑፍ ኢንጂኔር ተፈራ የራስ ወርቅ ካስተዋወቁን በኋላ ብዙ ዓይነት ጽሑፎች መጥተዋል፡፡
ረ. በእጅ ጽሑፍ ጊዜ ከባድ ፊደላትን መጻፍ የሚያስቸግረን ብዙዎች ነን፡፡
ሰ. ፊደላትን ማንበብም የሚያስቸግረው አለ፡፡
ሸ. የዶክተር አምሳሉ አክሊሉ  ‹‹የአማርኛ ፊደላትን ጠንቅቆ ያለመጻፍ ችግርና ዘላቂ መፍትሔ›› እንደሚለው ያሉ መጻሕፍት ለዚህ ችግር ሁነኛ መፍትሐየ ይሆናሉ፡፡
ቀ. ድምጹን የማናውቀው ሞክሼ ፊደል ምን ይሰራልናል?
ተ. ጽሑፍ ሲሞት ቋንቋው ሞተ ይባላል ወይ?

የእጅ ጽሑፍ ተኮር ትዝታዎችና ምልከታዎችም ተቃኝተዋል፡-
አራት ዓይነት ‹ይ› እንዳለ፡፡
በጽሑፋቸው የሚታወቁ ሰዎች እንዳሉና ያልሆነ ነገርም ጽፈው የተገኙ ሰዎች በዚያው ተደርሶባቸው እርምጃ እንደተወሰደባቸው፡፡
የእጅ ጽሑፋችን የራሱ ውበት፣ ስብጥርና ፈጠራም አለው፡፡ ለትውልድ እንዴት ይተላለፍ?
በንግግር ብቻ ሳይሆን በጽሑፍም የእንግሊዝኛ ተጽዕኖ አለብን፡፡ ታች ክፍል ነው አማርኛ ያለው፡፡ ከዚያ በኋላ አማርኛ የምንጽፍበት ዕድል አናሳ ነው፡፡
ስለ ንብረትነቱ ከተነሣ የቋንቋው ባለቤት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እንደ ምሣሌ ለማንሣት በአሁኑ ሰዓት ደቡብና ጋምቤላ ክልሎች ይጠቀሙበታል፡፡ ስለዚህ በምናደርገው የማሻሻያም ሆነ የአጠቃቀም ጉዳይ ሁሉንም ተጠቃሚ ማነጋገር አለብን፡፡
ከ‹ሀ› ወይስ ከ‹በ› ይጀመር?
ሁለተኛ ቋንቋ አድርገው ለሚናገሩት ወይም ለህጻናት ስለሚከብድ ማሻሻያ ይደረግ፡፡
የሌሉ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ድምጾች እንዲካተቱ የተደረጉ ጥረቶች ነበሩ፡፡
የላቲን ፊደል አጠቃቀም ሳይንሳዊ ነው ወይስ ፖለቲካዊ?
መሠረተ-ትምህርት ብዙ መጠነ-ሰፊ ፊደል-ተኮር ነገሮች የተነሡበት አጋጣሚ ነበር፡፡
ፈረንጆች የእጅ ጽሑፋቸውን ጠብቀው ቆይተዋል፡፡ ከርሲቭ (በተለምዶ ቅጥልጥል ጽሑፍ የሚባለው) ምናልባት የእጅ ጽሑፋቸውን ጠብቆ አቆይቶላቸው ይሆናል፡፡

ሁለት ወይም ሦስት እየሆኑ ስለ ጉዳዩ እንዲነጋሩ የተደረጉት ተሳታፊዎች ብዙ ሃሳቦችን አንስተው ጥለዋል፡፡
ዲቃላ ሆሄያትን (እንደ ‹ቋ› ያሉትን)፣ የ ‹የ›ን ዘሮች፣ የ ‹ኀ›ን ዘሮች መጻፍን ያካተተ መጠነኛ የጥያቄና መልስ ውድድርም ነበር፡፡ በዚህም የነበሩ ክፍተቶች በግልጽ ሊወጡ ችለዋል፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...