ማክሰኞ 30 ጁን 2026

አንድ ሳምንት ከደብረብርሃን እስከ ሶማሊላንድ ድንበር

 

‎‎








‎‎



 






አንድ ሳምንት ከደብረብርሃን እስከ ሶማሊላንድ ድንበር

‎‎መዘምር ግርማ

ሰኔ 2018 ..

‎‎

ሰኞ፣ ሰኔ 15

ጠዋት ከደብረብርሃን ተነሣሁ። በቅርቡ ወደ ጅማ ለማህበራዊ ጉዳይ ሄጄ ከመክረሜ በቀር ከዓመታት ጉብኝት አልባ ጊዜ በኋላ የተንቀሳቀስኩበት ጊዜ ነው። ለጉብኝት የማያመቹና ደስተኝነት የሌለባቸውን ዓመታት እያሳለፍን ነው፡፡ ስለሆነም ይህን አጋጣሚ ፈልጌዋለሁ፡፡ ሰው በእንደዚህ ዓይነቱ ጊዜ አእምሮውን የሚያዝናናበትን መንገድ ካልፈለገ ቋሚ ድባቴ ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡  

ወደ አዲስ አበባ በሚሄደው መኪና ውስጥ ካገኘሁት ራሽያ የተማረ መሐንዲስ ግማሽ መንገድ ከሄድን በኋላ ወግ ጀመርን፡፡ ከሰሜን ሸዋ የአንዱ ወረዳ ተወላጅ መሆኑን፣ በጦርነት ውስጥ ተዟዙሮ ለመስራት የሚያስገድድና ችግሮችንም የሚያስተናግድበት ሁኔታ ውስጥ እንዳለ፣ የአገር መለስ እድር ውስጥ እንደሚሳተፍ፣ የስራ መቀዛቀዝ እንዳስቸገረው ወዘተ አወጋልኝ፡፡ በሚማርበት ጊዜ የሚያስታሰውን ነገርም በትዝታ አወጋልኝ፡፡ ለአብነት ራሽያም ሆነ ዩክሬን ምግብ በሳንቲም ደረጃ እንደነበረ አስታወሰ የአሌክሳንደር ፑቲን የአገር ልጅ በሚል ይኮራ እንደነበርም ገለጸ፡፡ የበውቀቱ ስዩምን ግጥም አስታወስኩት

‹‹ሐበሻው ፑሽኪን

ወንጀለኛ ቢሆን ዓለም አሸባሪ

አራጅ ቢሆን ኖሮ ቤት ንብረት መዝባሪ

ፑሽኪን አሌክሳንደር

‹ባያቱ አበሻ ነው› መች እንለው ነበር፡፡››

 

አብሮኝ የተጓዘው ሰው የራሽያ ሴቶች ኢትዮጵያዊ ወንድ ስለሚወዱ ቋንቋውን ቶሎ ለመማር እንደሚያነሣሣም አወጋልኝ። ከፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም የሕይወት ታሪክና ከሌሎችም ምንጮች ያነበብኩትንና የማውቀውን እየተጠቀምኩ ለመረዳትና ለማውጋት ሞከርኩ፡፡

በአዲስ አበባ የአትሌቲክስ ልምምዱን የሚያደርግ አትሌት ወዳጄን ላምበረት ስለተቀጣጠርን አገኘሁትና ለሁለት ሰዓታት ያህል አወጋን። በእንጦጦ ጫካዎች ስለሚያደርገው ልምምድና በስፖርት ያልፍልኛል በሚል ስላለው የተስፋ ሕይወት አወጋልኝ።

አመሻሽም በአንድ የቤተመጻሕፍት ጉዳይ ስብሰባ ስለነበረኝ ቦሌ ተገኘሁ።አነቃቂና ተስፋ ሰጪውን ስብሰባ ጨርሼ የቦሌን ዘመናዊ ገጽታና እየጨመረ ያለ ዉበት ሳደንቅ አመሸሁ። ደብረብርሃን የሚጠመቀው ሐበሻ ቢራ ቦሌ ላይ 250 ብር ይሸጣል። በአንድ ጽዱ ባር ሐበሻን ሳጣጥም ሰፈሬን ጠባሴን እያስታወስኩ ነበር። ሁለቱን ጠጥቼ ተኛሁ።

ማክሰኞ ሰኔ 16

ዕለቱን በአካላዊ እንቅስቃሴና አዎንታዊ ይዘት ያላቸውን አነቃቂ መልዕክቶችን በእንግዳ ማረፊያው ከሚገኘው ቴሌቪዥን (affirmations) በመስማት ጀመርኩ። ጨጨብሳ በጣዕሙ ከሚያስታውቅ ንፁህ ማር በልቼ በወተት አወራርጄ ቀኔን ጀመርኩ። ቁርሱ ማህበሩ የያዘልኝ አልጋ አካል ነው። ከእንግዳ ማረፊያው የከተማ አውቶቡስ ለመሳፈር ስሄድ ቦሌ ድልድይ ጋ አንዷ መንገደኛ አንዲትን ቢጫ የምንኩስና ልብስ የለበሱ ምፅዋት ጠያቂ እናት "እማማ ደህና ነዎት?" ብላ ስታቅፋቸው ሳይ ርህራሄዋ አስቀናኝ። በአውቶቡስ ወደ ስድስት ኪሎ አቀናሁ። ግራና ቀኝ የተለዋወጠ ከተማ ነው፡፡ መንገዶቹ መስፋታቸውና መዋባቸው በግልጽ ይታያል፡፡ ሙሉ ቀን ስላለኝ በጉብኝትና ጓደኞቼን በመጠየቅ ለማሳለፍ አስቤያለሁ። በኤሌክትሪክ አውቶቡስ ተሳፍሬ ወደ ስድስት ኪሎ ሄድኩ። በአውቶቡሱ ምክንያት ከሃያ ዓመት በፊት የነበረውን የአዲስ አበባ የዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ሕይወቴን አስታወስኩ። ስድስት ኪሎ ደርሼ ጓደኛዬን ስጠብቅ ዩኒቨርስቲው ፊት ለፊት ካለ ወንበር ላይ ተቀምጬ ነበር። ከግራና ከቀኜ ምፅዋት የሚጠይቁ ችግረኛ አዛውንቶች አሉ። በስተቀኜ ያሉት አዛውንት ሁለት ሰዎች አጠገባቸው አስተኝተዋል፡፡ የአገሪቱ ቀዳሚ ዩኒቨርሲቲ ስለ ልመና ምን እንደሚያስብ አላውቅም፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ነጠላ ለብሰው ወደ ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ። የሰኔ ኪዳነምህረት መሆኗ ትዝ አለኝ። አዲስ አበባ የኢትዮጵያን የቀን አቆጣጠር በቀላሉ የማስታውስባት ከተማ መሆኗም ትዝ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ምጽዋት ጠያቂዎች የታቦቶቹን ስም ስለሚጠቀሙ በዚያ ስለማውቅ ነው፡፡ ደብረብርሃን ግን ካሌንደር በአፕሊኬሽን በመጠቀም ወይም ሰው በመጠየቅ ስለሆነ ስለሚያስቸግረኝ የአውሮፓውያንን የቀን አቆጣጠር እጠቀማለሁ፡፡

በመላው አዲስ አበባ መንገዶቹ ተቀያይረዋል። ከላም በረት ወደ ቦሌ ስሄድም ይህንኑ አይቻለሁ፡፡ ያ የማውቀው ከተማ አልመስል አለኝ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ግቢዎችም ከዉጪ ሳያቸው ተለዋወጡብኝ። አካሄዴ ሁለት የፒኤችዲ ተማሪዎች የሆኑ ጓደኞቼን ለማግኘት ነው። እንዲያውም ሌላ ፒኤችዲ የተመረቀ የሥራ ባልደረባዬም አገኘሁ። የቀድሞ የስራ ባልደረባዬ የነበረ መምህርም ስልክ እያወራ ሰላም ብሎኝ አለፈ። ብዙ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ስራ እየለቀቁ መሆኑን አስታወስኩ። ስላየኋቸው ለውጦች ጓደኞቼን ስጠይቃቸው እነሱም ፈዘው እየተመለከቱት መሆኑን ነገሩኝ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሃብታም ልጆች የሚማሩበት መሆኑን ሰማሁ። የፒኤችዲ ተማሪዎች በተወሰነ ክፍያ ዶርም ማግኘት ይችላሉ። ኬኔዲ ቤተመጻሕፍትን ድንክ ያስመሰለው ዲጂታል ቤተመጻሕፍት አጠገቡ ተሰርቷል። ነባሩ የኦሲአር ህንፃም ከፊት ለፊቱ በተሰራው ፎቅ ምክንያት አጥሯል፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ፊት ለፊት የነበረችው ድባብ መናፈሻ የለችም። ሰፊ ግራር ተቆርጧል። ስድስት ኪሎ በሩ የነበረችው የኮካ መዝናኛና ኮፒ ቤት የለችም። እነ ኢሳይያስ አፈወርቂንና አብዮታዊ ታጋዮችን ጭምር ያስተናገደው አሴ ባር የለም። ወደ መነን መንገድ ያሉት የኮንቴነር ኮፒ ቤቶችም የሉም። ከዩኒቨርስቲው ፊትለፊት ያለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የግንብ አጥሩ ተነስቶ በግቢው አትክልትና ዛፎች መካከል ወንበሮች ተቀምጠው ሳይ መስሪያ ቤቶች ለህዝቡ ክፍት ነን ማለታቸው ይሆን አልኩ። ኤፍቢኢ ግቢ ትንሽ ቆንጆ ስቴዲየም ተሰርታለች። በቅርቡ ለማታውቁት የዱሮው የየካቲት የፖለቲካ ትምህርት ቤት ነው። አንበሳ ግቢ አንበሶቹ ጠፍተውና አጥሩ ተነስቶ በየመሃሉ ወንበሮች ጣል ጣል የተደረጉበት ካፌ ተከፍቷል። ቡና ጠጣሁና ሃምሳ ብር ከፈልኩ። 'የተቆለፈበት ቁልፍ' በሚለው የዶክተር ምህረት ደበበ ልቦለድ የኛ አገር ቤቶችና መስሪያ ቤቶች ለምን አጥራቸው አይነሳም፣ እንደ አሜሪካስ ለምን ክፍትና ግልጽ አይሆኑም የሚለው ሙግቱ ትዝ አለኝ። የሱ ሃሳብ እየተተገበረ ይሆን? ወደ አራት ኪሎ ቦርሳዬን አዝዬ በእግሬ አዘግም ያዝኩ፡፡ ከስድስት ኪሎ እስከ አራት ኪሎ አራት ጊዜ ሰዎች ኦሮምኛ ሲናገሩ ሰማሁ፡፡ ቋንቋውን የተወሰነ ስለምረዳ ወሬ ስሰማ ወረድኩ፡፡

ከአራት ኪሎው ዩኒቨርሳል መጻሕፍት መደብር 'Threads of Memory' የሚል ርዕስ ያለው የሐረርን የሰርግ ባህል የተመለከተ መጽሐፍ ገዛሁ። በመንገዴ አነበዋለሁ።

ጠዋት ያልተመቸው ሌላ የፒኤችዲ ተማሪ ወዳጄ ወመዘክር ያነብ ኖሮ ስቴዲየም አካባቢ አገኘሁት። ከትምህርቱ ጎን ለጎን ኑሮውን ለመደጎም በግል ትምህርት ቤቶች እንግሊዝኛ ያስተምራል። ወይንስ ከስራው ጎን ለጎን ይማራል ልበል? ሚያስተምርበት የግል ትምህርት ቤት አብዛኞቹ ሙስሊሞች ናቸው። ስግደቱ ትምህርት ቤቱን መስጊድ አስመስሎታል አለኝ። ክፍያው ለሁለት ይሁን ለሦስት ወር ተርም ከስድሳ ሺህ መሻገሩን ነገረኝ፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ካሉት መምህራን 40 ፐርሰንት የእንግሊዝኛ መምህራን እንደሚሆኑ ግምቱን ነገረኝ። Grammar, vocabulary, reading, writing, spoken, TOEFL, English for Ethiopia እያለ የሚቀጥል የእንግሊዝኛ ትምህርቶች ዝርዝር ሲኖር ሁሉም የየራሳቸው መምህራን አሏቸው።

‎‎ከሜክሲኮ ወደ ፉሪ ባቡር ለመያዝ በአውቶቡስ ጉዞ ጀመርኩ። የባቡር ቲኬት ቀድሜ በድረገፅ ቆርጫለሁ። ጉዞዬ ሌሊት ነው። ከጀሞ ሦስት ወደ ፉሪ በባጃጅ ሄድኩ። ጣቢያው ከአዲስ አበባ ከተማ ዉጪ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ይገኛል። ባዶ ሜዳ ላይ ያረፈው ጣቢያው ገና አልነቃም። የሸራ ዳስ ጥለው ሻይ ቡና የሚሸጡ አጠገቡ አሉበት። በየደቂቃው የሚጮሁና የሚያንዣብቡ ኤሮፕላኖች ስሰማና ሳይ በአንድ የአሜሪካን የአውሮፕላን ማረፊያ በየደቂቃው አንድ አውሮፕላን ሲነሳ ሌላ ያርፋል የሚል መስማቴ ትዝ አለኝ። የኛም የአውሮፕላን ማረፊያ የአፍሪካ መገናኛ እየሆነ ሳስብ ደስታ ተሰማኝ፡፡ እንደ አህጉር ብዙ እንደሚቀረን ግን ሌላው ቢቀር ‹አውሮፕላን እንዴት ይበራል?› ከሚለው የአብርሃም ደበሌ መጽሐፍ ያሉንን የአውሮፕላኖች ቁጥር ስረዳ ገብቶኛል፡፡ ተሳፋሪዎች ምሽት አንድ ሰዓት ተገኙ ብንባልም እኔ ቀድሜ 11:00 በፊት ተገኝቻለሁ። እስከ ምሽት 3:00 ጠበቅን። የነዳጅና የሰው ባቡር ይለያያል። የነዳጁን ቦቴ ቀጣጥሎ አየሁት። የሰዉም ባቡር ሲመጣ 16 ካርጎ ቆጠርኩ መሳፈሪያ ሰዓታችን እስኪደርስ ከተጓዦች ጋር ወግ ጀመርኩ። የመከላከያ ሰራዊት አባሎች ሐረር አቅራቢያ ወደሚገኘው ካምፓቸው እየሄዱ ነው። ወደ ባይደዋ፣ ሶማሊያ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከመሄዳቸው በፊት የአስር ቀን እረፍት ወስደው እየተመለሱ እንደሆነ ነገሩኝ። ወታደራዊ የደንብ ልብሱን የለበሰ ሲያዩ ይስቁበታል። በእረፍቱ የሲቪል ልብስ መልበስ አለበት ይላሉ። ከአዲስ አባበና ከክልል ከተሞች ዉጪ ቢሄድ ለእረፍት መሄዱን ስለማያውቁለት ሊያስጠቃው ይችላል አሉ። ያገኘኋቸው ብዛት የደቡብ ተወላጆች ናቸው። ስለወታደር ሕይወት ነገሩኝ፡፡ ግልጽነት አላቸው፡፡ ብሔሬን ገምቱ ስላቸው አሳስተው ገመቱ፡፡ ዕድሜዬን ግን በትክክል ገመቱ፡፡ ከደብረብርሃን ጓደኛዬ ደህና መግባቴን ለማጣራት ሲደውል ባቡሩን ማየቴንና ‹‹16 ሰላም ባስ ተቀጣጥሎ ይመስላል›› ስል ወታደሮቹ ‹‹መረጃ አትስጥ›› አሉኝ፡፡ በወታደር ቤት ቢሆን ያስቀጣህ ነገር አሉኝ፡፡

በኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ድረገፅ የቆረጥኩት 1486 ብር ቲኬት በወንበር ስቀምጦ ይወስደኛል። በአልጋ ተኝቶ መሄዱን አልፈለኩትም፡፡ ውድ በመሆኑ ሳይሆን ተቀምጦ መሄድን ስለመረጥኩ ነው፡፡ ዋጋው በእርግጥ ከወንበሩ ከእጥፍ ይበልጣል፡፡ የባቡሩ ወንበር ከአውቶቡስ ወንበር ቢሻልም ሌሊቱን መጓዙ አድካሚ ነበር። ጨለማውም አገር ለመጎብኘት አያስችልም። በየኬላው ቁጥጥር አለ። የታጠቁ ፌደራል ፖሊሶችም ይመጣሉ። ቲኬት የቆረጥነው በዲጂታል መታወቂያችን ስለሆነ በአንድ ምክንያት የሚፈልገን አካል ስርዓቱን ሃክ ካደረገው አለቀልን። መታወቂያው ዝርዝር ማንነትን ስለሚያሳይ አጋላጭነት አለው።

ረቡዕ ሰኔ 17 ድሬዳዋ

12 ሰዓት ጉዞ በኋላ ድሬዳዋ ጠዋት 3:00 ገባን። 200 ብር ከፍዬ በባጃጅ ወደ ሳቢያን ሰፈር ስሄድ ባቡር ጣቢያው የሚገኘው በከተማዋ ዳርቻ ኖሮ ያየሁት ትዕይንትና የቤቶቹ የገጠር ቤት መምሰል አስደንግጦኛል፡፡ በከተማዋ አጠገብ በሚገኝ ተራራ ላይ ትንንሽ ቤቶች ሳይ ጎርፍ ፍራቻ የተሰሩ መሰለኝ፡፡ ወራሪው የዚያድ ባሬ ወይም የሶማሊያ ጦር ከተማዋን ጥሶ እንዳይገባ የተጠመደ ፈንጂ ያበት ቦታ መሆኑንም ተረድቻለሁ፡፡ ምናልባት ፈንጂውን አምክነውት ይሆን? ሳቢያን ሄጄ ቤርጎ ፍለጋ ያዝኩ፡፡ ሾፌሩ ትልቅና ቅንጡ የሆነውን ሆቴል ቢያሳየኝም እዚያ ሆቴል በ3500 ብር ከምይዝ ብዬ በ1000 ብር በሌላ እንግዳ ማረፊያ ያዝኩ፡፡  ሳቢያን፣ ሰይዶ ሰፈር ያረፍኩበት እንግዳ ማረፊያ እንደገባሁ መዝጋቢው መታወቂያዬን በስልኩ ፎቶ አንስቶ ያዘ፡፡ በከተማው የእንግዳ ማረፊያዎች የእንግዶች ስም ዝርዝር በዲጂታል እንደሚያዝ ነገረኝ፡፡ በሰይፉ ሾው የቀረቡት የድሬዳዋ ፖሊስ ባልደረቦች ሲናገሩ ስለሰማሁ አዲስ አልሆነብኝም፡፡ ማንም ሰው ድሬዳዋ ከገባና አልጋ ከያዘ በድሬዳዋ ፖሊስ ዕይታ ውስጥ ነው፡፡ ማረፊያው ቀዝቃዛ ሻወር ያለውና የተሟላ ሰፊ ክፍል ነው። ቀዝቃዛውን ሻወር በቀን ሁለት ጊዜ ታጥቤበታለሁ። ደብረብርሃን ላይ ‹ሙቅ ሻወር አለ› የሚለው ማስታወቂያ እዚያ አይታሰብም፡፡ የሚለበሰው አንሶላ ነው። ብርድልብሱ ወንበር ላይ ተጣጥፎ ለደንቡ ተቀምጧል።

ከእንግዳ ማረፊያው ፎቅ ላይ ካለው ካፌ ሄጄ መለዋ የተባለችውን ምግብ ቀመስኳት፡፡ የደብረብርሃኗ ፈጢራ በማር ነች፡፡ አምበሾቅ ያለበት ስፕሪስ ጭማቂ ጠጣሁ፡፡ አምበሾቅ የተባለው ፍራፍሬ ጣፋጭ ነው፡፡ አስተናጋጇፀባይ ያላትና ተግባቢ ነች፡፡ እጄን ጠረጴዛው ላይ ደገፍ ብየ ሳለ ምን እንደሚያስተክዘኝ ጠየቀችኝ፡፡ ደህና እንደሆንኩ ገለጽኩላት፡፡ ስለ ድሬዳዋ ጉድጓድ መሆንና መሞቅ ነገረችኝ፡፡ እኔም ስለ ደብረብርሃን ቅዝቃዜ ነገርኳት፡፡ ምክንያቱን ስትጠይቀኝ ምናልባት ከፍታው አንዱ ሊሆን መቻሉን እንደምገምት ነገርኳት፡፡ ድሬዳዋ ከባህር ጠለል በላይ 1276 ሜትር ስትሆን ደብረብርሃን 2840 ነች፡፡ ልጅቱ አማርኛም ኦሮምኛም ትችላለች፡፡ መሐል ሜዳ ደግሞ 3132 እንደሆነ ነገርኳት፡፡ ዉኃ ባዘዝኳት ቁጥር ‹‹የቀዘቀዘ?›› በማለት ትጠይቀኛለች፡፡ እኔም ሲደጋገምብኝ ‹‹ለመሆኑ ድሬዳዋ ውስጥ ያልቀዘቀዘ የሚያዝ ሰው አለ?›› ብዬ ጠየቅኋት፡፡ እንደሌለ ነገረችኝ፡፡ በሌላ ቀዝቃዛ ቦታ ሰርታ ይሆን? ወይስ ለምዶባት? አመሻሽ ላይ በአቅራቢው ካለ ዳቦ ቤት ሙሸበክና ባቅላባም ገዝቼ አሳሽጌ ወደ አባይ ግሮሰሪ ወስጄ የተወሰነውን በላሁ፡፡ የሰሞኑ የጉዞ ላይ አመጋገቤ እንደተገኘ ሆኗል፡፡ ምግቦቹ በጣም ጣፋጭ ስለሆኑ በእኔ ዕድሜ ላይ ላለ ሳይሆን ለልጆች ይስማማ ይሆናል ብዬ ገመትኩ፡፡   

የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ መምህርና ለኔም የድህረ ምረቃ የክፍሌ ልጅና ጓደኛዬ የሆነው ብርሃኑ በጥሩ መስተንግዶ አክርሞኛል። ከተማዋንም አስጎብኝቶኛል።ኮኔል ሰፈርን አይቻለሁ። የጋሪ ፈረስ ሐውልት ተሰርቶለት አይቻለሁ። የምድር ባቡር ሰራተኞች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ሰፋፊ የቆዩ ቤቶችንም አይቻለሁ። የጅቡቲ ቆንስላም የጅቡቲ ዜጎች ቀዝቃዛ አየር ፈልገው ሲመጡም ይሁን ለሌሎች ጉዳዮች ስለሚያስፈልግ ተከፍቷል።ጫት ተራው ሰፊና ትዕይንቱም አስገራሚ ነው። ጫት የሕዝቡ የዕለት ከዕለት ኑሮ አካል ነው። በየቦታው በመንገድ ዳር ባሉ ዛፎች ስር ሳይቀር ይቃማል። የጫት ገራባ በየስፍራው ተጥሎ ይታያል። በርካታ ሰፈሮችን ያየሁ ሲሆን በየዘፈኑ የምንሰማቸው እነ ከዚራ፣ ሸንኮር፣ ለጋሃሬ ወዘተ ስማቸውን አስጠብቀው ቀጥለዋል፡፡ የግሪክ ማህበረሰብ ቤተክርስቲያንን አይቻለሁ፡፡  ልጆች በርካታ ቋንቋዎችን የሚችሉበት ሰፈር እንዳለም ተረድቻለሁ፡፡

 

ሐሙስ ሰኔ 18

በጠዋት ተነስቼ በእግር ልዘዋወር ብዬ ከተንቀሳቀስኩ በኋላ አንድ ጀበና ቡና ቤት አገኘሁ፡፡ በረንዳ ላይ ቁጭ ብዬ ወደ ውስጥ ሳማትር "kottaa buna dhugaa" የሚል ጽሑፍ አየሁ። ኦሮምኛን የሚያስቀድም ቤት መሰለኝ። በእርግጥ ከተማዋ የኦሮሞና ሶማሌ ክልሎች በባለቤትነት የሚፎካከሩባትና አመራሩም በተወሰኑ ዓመታት ልዩነት በብሔር እየተፈራረቁ እንደሚመሯት ሰምቻለሁ፡፡ ያው ብሔር የአገራችን ፖለቲካ የተቃኘበት መንገድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዩኒቨርሲቲው አማርኛ፣ ኦሮምኛና ሶማሊኛ ቋንቋዎች ይሰጣሉ፡፡

የቡናዋ እመቤት "የአዲስ አበባ ሰው ነህ?" ስትል ጠየቀችኝ። እንግዶች እናስታውቃለን መሰለኝ፡፡ አንድ አዛውንት በደጅ እያለፉ ሰዓት ጠየቁኝ። ሰዓት ነግሬያቸው ቡና ጋበዝኳቸው። የኦሮምኛ ቅላፄ የሚናገሩት አዛውንት ከሩቅ ሰፈር በእግራቸው እየመጡ መሆኑን ነግረውኝ መንገዳቸውን ቀጠሉ። ሂሳብ ልከፍል ብር ሳወጣ በኢብር አለችኝ። መልስ ስለሌላት መቶ ብር በጥሬ ልትወስድ አልቻለችም። አፕሊኬሽኑ እንደሌለኝ ተናግሬ በቴሌብር ከፈልኩ። ቴሌብርን ብዙም የምትጠቀምም አልመሰለኝም። የቤቱ ባለቤት ስልክ እንደሆነና እሷ ጋ ሊገባ እንደሚችል ነገረችኝ፡፡ ችግረኛም ምፅዋት የሚጠይቀው የኢብር ቁጥሩን ጽፎ በዚህ ላኩልኝ በማለት ነው።  የኢብር አካውንታቸውን ጽፈውና አሳሽገው አጠገባቸው አድርገው መንገድ ዳር ይቀመጣሉ፡፡ ልጆችም ወደተለያዩ ቦታዎች ሲሄዱ ገንዘብ ይዘው ይጠፋባቸዋል ተብሎ አይሰጋም፡፡ ደውለው በዚህ ቁጥር ክፈሉልኝ ይላሉ፡፡ በከተማዋ ጉሊት ዕቃ ማለትም ፍራፍሬ፣ ጭሳጭስ ወዘተ ይዘው የሚቀመጡ ሴቶችም አሉ።

በመንገድ ላይ አንድ የሚያውቀኝ ሰው አገኘሁ፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ መምህር ሲሆን ደብረብርሃን መጥቶ በነበረበት ወቅት ቤተመጻሕፍቴን ማየቱን ነገረኝ፡፡ ወደ ቤተሰቡ ለመሄድ የአውቶቡስ ቲኬት ለመቁረጥ እየሄደ ስለነበር አብሬው ሄድኩ፡፡ ስለ ዩኒቨርሲቲያቸውም ነገረኝ፡፡ ዩኒቨርሲቲውን ባለመጎብኘቴ አዝናለሁ፡፡ ሌሎችም በርካታ ያልጎበኘኋቸው ቦታዎች አሉ፡፡ አንድ ጎብኚ ከቤቱ ሲወጣ የሚጎበኙትን ቦታዎች ማወቅ አለበት፡፡ የሙዚየም፣ የአስጎብኚ፣ የሚጎበኙ ቦታዎችን የሚገልጹ ማብራሪያዎች አስፈላጊነት ገባኝ፡፡ አንድ እንግዳ ማረፊያ ከርሞ መምጣት በቂ አይደለም፡፡ ይህን የተረዳው መምህር ጓደኛዬ የድሬዳዋን ኮሪደር ልማት በዚህ ምሽት አስጎበኘኝ፡፡ እንደሌሎች ከተሞች ኪሪደር የተባለው የከተማ ማስዋብ ስራ በየቦታው የማይታይባት ድሬዳዋ ይህን የኮሪደር ሰፈር በማግኘቷ ህብረተሰቡ ሲዝናና ይታያል፡፡ የቀድሞው ባቡር ሀዲድ ይታያል፡፡ አሁንም እንደሚሰራና አሮጌው ባቡር እንደሚሄድበት ተረዳሁ፡፡ የቀድሞው የባቡር ሐዲድ ከምን እንደገባ፣ ተፈላጊ ስለሆነ ያለአግባብ እንዳሸጥ የሰጉ ሰው ከዓመታት በፊት የጠየቁኝ ትዝ አለኝ፡፡  በዚህ ሰፈርና ከዚያም ስመለስ ያየኋቸው ህንጻዎች ድሬዳዋ ትልቅ ከተማ መሆኗን መሰከሩልኝ፡፡ ስገባ ያየሁት የገጠር መሳይ ትዕይንት ያሳደረብኝ ስሜትም ጠፋ፡፡ የህብረተሰቡ አለባበስ፣ የኑሮ ሁኔታ፣ ሕይወትን ቀለል አድርጎ ማየቱ ከደጋማዋ ደብረብርሃን እጅግ ለየት ያለ መሆኑ ያስታውቃል፡፡ ደብረብርሃን ያለ ጉብኝትና በድባቴ በርከት ላሉ ዓመታት የቆየሁትም በድሬዳዋ አየርና ገጽታ ተዝናናሁ፡፡  

አርብ ሰኔ 19 ሐረር

ማለዳ ወደ ሐረር ለመሄድ ተነሳሁ፡፡ በምቾት የእንግዳ ማረፊያ እንደ አዲስ አበባው ስወጣ ‹ቼክ አውት› ብሎ ያለኝ ስለሌለ ወጥቼ ሄድኩ፡፡ ከድሬዳዋ ወጥቼ ወደ ሐረር ስሄድ በመንገድ ሐረር  ላይ ጥንታዊቷ ሀርላ ከተማ የሚል ጽሑፍና ከተማ አይቻለሁ። ደንገጎን እንዲሁ፡፡ በስተቀኝ ስለተቀመጥኩ ማያ ከተማ የሚል ማስታወቂያ ሳይ ሃሮማያ ትዝ አለኝ፡፡ ወደ ግራ አሻግሬ ሳይ የሃሮማያ ሃይቅ ተንጣሎ ታየኝ፡፡ ደርቋል የተባለው ሃይቅ መልሶ መነሳቱ ያስደስታል፡፡ አወዳይንም አየኋት፡፡

የድሬዳዋ መኪና ሐረር እንዲገባ ሁለቱ ክልሎች ማለትም ኦሮሚያና ሐረር ስላልተስማሙ ተብሎ ሐማሬሳ ላይ ወረድን፡፡ ሐረር ከድሬዳዋ የተለየና ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ እንዳላት በማንሳት መኪና ውስጥ ወሬ ጀመርን፡፡ ከጎኔ የተቀመጠችው በድሬዳዋ በመምህርነት የምትሰራ የሐረር ልጅ ነች፡፡ ወሎና አፋር ውስጥ ማስተማሯን ነገረችን፡፡ አፋር ውስጥ ሙቀቱን መቋቋም እንዳቃታትና የሰራችው ፓስታ አጥሚት አንደሆነባት በአግራሞት አወሳች፡፡ ከሱማሌ ክልል ወደ ድሬዳዋ ለቅዝቃዜው ሲል መምጣቱን የነገረን አንድ ሰው በስተግራዬ ተቀምጧል። ድሬዳዋን ለቅዝቃዜ መምረጡ ሲገርመን ከጅቡቲ ደግሞ ወደ ሶማሌ ክልል እንደሚመጡ ነገረን፡፡

ከሐማሬሳ ወደ ሐረር ፎርስ የተባለውን ባጃጅ ያዝን፡፡ ሐረር ስንደርስ ጫት እንደ ጎመን ጎልት ላይ ተደርድሮ በጠዋት ይቸበቸባል፡፡ ሻጮቹ ሴቶች ናቸው፡፡ ከተማዋ እየተዋበች ነው፡፡ ቅድሚያ የመቀመጫዬን ብዬ ሱመያና ወንደርላንድ ሆቴልን ትቼ መጠነኛ የእንግዳ ማረፊያ ያዝኩ፡፡ ከደጅ ሰው ስጠይቅ 800 ብር ነው ቢሉኝም ስገባ ግን 900 ብር ሆኖ አገኘሁት፡፡ ምክንያት ያደረጉት ዕለቱ የምርቃት መሆኑን ነበር፡፡ ትክክለኛ አድራጎት አይመስለኝም፡፡ አልጋ ቤቱ የሙስሊሞች ንብረት በመሆኑ የትዳር የምስክር ወረቀት ከሌላቸው በስተቀር ወንድና ሴት ማደር አይችሉም መባሉን ሲሰሙ አልጋ ለመያዝ የመጡ የተማሪዎች ምርቃት እንግዶች የሆኑ ጥንድ ጥን የሆኑት ልጅ እግር ወጣቶች ተከዙ፡፡ አልጋ ብዙ ቦታ አልቆ ነበር፡፡ አልጋ ከያዝኩ በኋላ ወደ አንድ ወዳጄ ደወልኩ፡፡ ሐረር በር ጋ በፍጥነት መጣልኝ፡፡ ጀጎል ውስጥ ያለውን ብቸኛውን የመድኃኔዓለምን ቤተክርስቲያን አስጎበኘኝ፡፡ ከጀጎል ዉጪ ወጥተንም ጀጎልን ከሩቅ አየናት፡፡ ተራራ ላይ በትልቁ የተሰራ በእንግሊዝኛ የተጻፈ ሐረር የሚለውን ጽሑፍ ከሩቅ አየሁት፡፡ ከአራት ኪሎ የገዛኋት በሐረር የሰርግ ስነስርዓት ላይ የምታተኩረው መጽሐፍ ስለ ሐረሪዎች ጥሩ ሐሳብ ስለሰጠችኝ ቤተሰብነት ተሰምቶኛል፡፡ ሙስሊሞቹ ሐረሪዎች አደሬም እንደሚባሉ ተረዳሁ፡፡ የመጽሐፉ ደራስያን አንዳንድ የታሪክ ክስተቶችን ሲዘግቡ ግን ጥንቃቄ ማድረግ ሳይኖርባቸው አይቀርም፡፡ በመጽሐፉ በጨለንቆው ጦርነት 700 ሙሽሮች መስዋዕትት ከፍለዋል ተብሎ የቀረበው ተቀባይነት ይኖረው ይሆን? ምሽት ላይ ወደ ጀጎል ተመልሰን የገባነው በሐረር ኮሪደር አልፈን ነበር፡፡ በአካባቢው ወጣቶችና እንግዶች ፎቶ ይነሱ ነበር፡፡ በምሽቱ ብርሃን የተዋበው የጀጎል የውስጠኛ ክፍል ጠባብ በተጠረቡ ድንጋዮች የተዋቡ መንገዶች አሉት፡፡ የተጣላ እንኳን ቢገናኝ የሚታረቅባቸው ናቸው ይባላል፡፡ ፎቶ ተነሳን፡፡ ብቻህን ከመጣህ ጀጎል ውስጥ መንገድ ሊጠፋብህ ይችላል ተብያለሁ። ቀን ላይ ሌላ ሁለተኛ በር አይቼ ነበር፡፡ ከአምስቱ በሮች ሦስቱን አላየሁም፡፡ ምሽት ወደ መኝታዬ ስመለስ ድራፍት በመጠጣቴ ጥፋተኝነት እየተሰማኝ ነበር፡፡ በሙስሊም ባለይዞታነት የሚተዳደረው ቤት ይህንን ካወቀ በምሽት አውጥቶ ቢጥለኝስ! ለነገሩ አልኮል መጠጣት አለመጠጣቴን አልመረመሩኝም፡፡  በማግስቱ ጠዋት ወደ ጅግጅጋ ለመሄድ የቸኮልኩበት አንድ ምክንያት ነበር፡፡ ሐረር ያለውን ዘመዴን በወጪ ስለተጫንኩት፣ አላስከፍልም ስላለኝ እንዲሁም ነገ እኔ ቤት ታድራለህ ስላለኝ ነበር፡፡ በዚሁ ዘመዴ ጥቆማ በሐረር ያገኘኋት ሌላዋ የትውልድ ስፍራዬ የሳሲት ተወላጅ ‹መዘምር› የሚለውን ስሜን ያወጡልኝ አዛውንት ልጅ ነች፡፡ አጋጣሚው ይገርማል፡፡ ሐረር ከደረስኩ በኋላ ከድሬዳዋ ደውላ ‹‹ሳታገኘኝ ሄድክ›› ያለችኝ ሌላ አብሮአደጌ ስትሆን እዚያ መኖሯን ረስቼዋለሁ፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ የደረስኩበትን የምጽፈው በቦታው ያለ ሰው እንዲያገኘኝ በማሰብ ነበር፡፡ አላየችውም ማለት ነው፡፡ በሐረር የነበረው የራስ መኮንን ሐውልት ከጥቂት ዓመታት በፊት በነበረ ግርግር ጊዜ እንደፈረሰ ይታወቃል፡፡ ተመልሶ አልተገነባም፡፡ የራስ እምሩን ስም ግን በአንድ አዳራሽ በር ላይ አንብቤያለሁ፡፡ ራስ መኮንን ባቀኑት አገር በሐረርጌ ይህ መታሰቢያ ሲያንስባቸው እንጂ አይበዛባቸውም፡፡ ምስራቅ ኢትዮጵያ የብዙ ጀግኖች ደም የፈሰሰበት ነው፡፡ በጣሊያን ሁለተኛው ወረራ ጊዜ የነደጃዝማች ነሲቡ ዛማኔል ታሪክ አይረሳም፡፡ በወቅቱ ከምስራቅ ወደ ሸዋ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ መሰደዱም ይታወቃል፡፡ የሶማሌ ወረራ ያመጣው እልቂትና መስዋዕትነትም አይዘነጋም፡፡ በዚያ በረሃ እንደ ሰም የቀለጡ የኢትዮጵያ ልጆችን አስቧቸው፡፡ አዲስ መታሰቢያ ባይሰራ ነባሩ መፍረስ የለበትም!

ቅዳሜ፣ ሰኔ 20

የጅግጅጋ መኪና ያዝኩ፡፡ የመንገዱ ሁኔታ ልዩ ልዩ ትዕይንቶች ያሉበት ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋት፣ በኋላ በአዳማና በአልዩአምባ ያየሁትን ግመል የተባለውን እንስሳ ከመኪና ውስጥ ሆኜ አየሁት፡፡ አንድ ቦታ አንድ ሽርጥ ያገለደመ ሰው ሁለቱን ሲነዳ አየሁ፡፡ ሌላ ቦታ ደግሞ በርከት ያሉ ግመሎች አንዲትን የግራር ዛፍ ከበው ሲበሏት አየሁ፡፡  ማዕድ የቀረቡ የቤተሰብ አባላት እንጂ እሾህ የሚበሉ አይመስሉም፡፡

በየቦታው ከቆርቆሮ ቤት ጀርባ የሚታይ ከሸራና ከጨርቅ የተሰራ ክብ ቤት መሳይ ነገር ይታያል፡፡ በሸዋ ዕይታ ሳስበው የእንስሳት ምግብ የሆኑት የገለባ ወይም ሳር ክምር መስሎኝ ነበር፡፡  ይሁን እንጂ ቆይቼ ቤት መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ሙቀቱን ለማቀዝቀዝ ይጠቀሙበታል፡፡ ፎቶውን በፌስቡክ ስለቀው እንደዚህ ከሆነ ኑሮ ቀላል ይሆናል የሚል አስተያየት አገኘሁ፡፡ በተለይ ቤት ሰርታ ሕይወቷን ለመቀየር የምታልም የአረብ አገር ዘመዴ አትኩሮት ሰጥታዋለች፡፡

ጅግጅጋ ጥሩ አየር ያላት ሙቀቷም ተመጣጣኝ የሆነ ከተማ ነች፡፡ አንዳንዴ ነፋስ ያስቸግራታል ይባላል፡፡ ሰናይ ሆቴል አልጋ ይዤ አነስተኛዋን ቦርሳዬን አሳርፌ የቶጎጫሌ መኪና የሚገኝበትን ቦታ ስጠይቅ ያገኘኝ ሰው ጫት ይዞ ወደ ቤቱ እየገባ ነበር፡፡ ስልክ ተለዋውጠን እስከማገኝ ድረስ ተከታትሎ አቅጣጫ ጠቆመኝ፡፡ ራሱ እየደወለ፡፡ እኔ ወደ መናኸሪያው ልውሰድህም ብሎኝ ነበር፡፡ በጣም ቀና ሰው ነው፡፡ በአንድ በከተማዋ የሚገኝ ቤተክርስቲያን ወደሚያገለግለው የቅርብ ዘመዴ ስልክ ደውዬ ስጠይቀው መጥቶ አገኘኝ፡፡ ቤተክርስቲያኑን አሳየኝ፡፡ ከዓመታት በፊት በአብዲ ኢሌ ጊዜ በነበረው ፖለቲካ ተኮር ጥቃት ስለተከሰተው ችግርና የኃይማኖት አባቶችና ምዕመናን ስለደረሰባቸው አደጋም አስረዳኝ፡፡

መኪና ስጠብቅ ቡና የጠጣሁበት በረንዳ ላይ ቡና የምትሸጠውን ልጅ ቡና 30 ብር፣ ሻይ 15 ብር መሆኑ ርካሽ መሆኑን በመግለጽ ወሬ ጀመርኩ፡፡ አጠገቧ የተቀመጠውም ወጣት ወሬ ጀመረ፡፡ ሲያወሩ ከአማራ ክልል የመጡ መሆናቸው ገባኝ፡፡ ‎‹‹አማርኛ ስንተኛ ቋንቋዬ ይመስላችኋል?›› ብየ ስጠይቃቸው ሁለተኛ እንደሚመስላቸው ነገሩኝ፡፡ አፍ መፍቻዬ መሆኑን ነገርኳቸው፡፡

መርሃባ በሚባለው የትራንስፓርት አቅራቢ ድርጅት ሚኒባስ ወደ ቶጎ ጫሌ ስሄድ አንዲት ሶማሌ ወጣት አጠገቤ ተቀምጣለች፡፡ ከመናኸሪያውም ቲኬት ስትቆርጥ አይቻት ነበር፡፡ መጀመሪያ ኒቃብ ለብሳ ነበር፡፡  በኋላ አወለቀችው፡፡ በምልክት ቋንቋ ወሬ ጀመርን፡፡ እኔ በጉግል በእንግሊዝኛ እየጻፍኩ የሶማሌኛ ትርጉሙን አሳያታለሁ፡፡ እሷ ትመልሳለች፡፡ የምትመልሰው ስለሚረዝም ጉግል ላይ በሶማሊኛ መጻፍ አልቻልኩም፡፡ 23 ዓመቷ ሲሆን አዲስ አበባንም ታውቃለች፡፡ ከሶማሌኛ ውጪ ቋንቋ አታውቅም፡፡ በመሃል ጣቷ የወሲብ ምልክት ስታሳየኝ መልዕክቱ ስላልገባኝ ዝም አልኳትና ሌላ ወግ ቀጠልኩ፡፡ በኋላ ስትደግመው ገባኝ፡፡ ምልክቱን ካሳየችኝ በኋላ የአንድ ቆንጆ ወጣትን ፎቶ ከስልኳ ስታወጣ ገባኝ፡፡ ባል አለኝ መሆኑ ገባኝ፡፡ እንደዚያ ከምትል ግን ቀለበት ካላት ብታሳየኝ ወይንም የቀለበት ጣቷን ብታመለክተኝ ይሻል እንደነበር በምልክት ስነግራት አልተስማማችም፡፡ ቆየት ብላ ታክሲ ውስጥ ለተሳፈረው ሰው ሐበሾችን በሶማሊኛ ማማት ጀመረች፡፡ በእርግጥ ከሱ በፊት ለእኔም በምልክት ሐበሻ ብዙ ብዙ ብላ በመሃል ጣቷ የወሲብ ምልክት አሳይታኛለች፡፡ ምንም ክፉ ስላልተናገርኩ በማላውቀው ቋንቋ ስታማኝ ምንም አልወጣኝም፡፡ ተሳፋሪዎቹም ምንም አላሉም፡፡ መንገድ ላይ በ100 ብር ከገዛሁት የተጠበሰ በቆሎ እሸት ሰጥቻት በልታለች፡፡     

ቶጎጫሌ ደረስን፡፡ በኢትዮጵያና ሶማሊላንድ መካከል የምትገኝ የድንበር ከተማ ነች፡፡ ወደ ሃርጌሳ መሄድ ፈልጌ መሆኑን አንድ ሶማሊኛ ተናጋሪ ጠየቀኝ፡፡ እንዳልሆነ ነገርኩት፡፡ ምናልባት ሰዎችን በህገወጥ መንገድ የሚያሸጋግር ይሆናል፡፡ በእግሬ የአገሬን ድንበር አቋርጬ ሱቆችን አይቼና የተወሰነ ጎብኝቼ ተመለስኩ፡፡ ምንም ዕቃ የመግዛት ፍላጎት ስለሌለኝ ከቶጎጫሌም ሆነ ከሌሎቹ ከተሞች አልገዛሁም፡፡ ሰዎችም ግዛልን ሲሉኝ አልተስማማሁም፡፡ ከቶጎጫሌ ስመለስ ባዶ እጄን መሆኔን ያየች ሶማሌ ሴት ብዙ የወታደር ሽርጥ ስለያዘች እንድይዝላት ጠየቀችኝ፡፡ አልይዝም አልኳት፡፡ በኢትዮጵያ ኬላ ላይ ፍተሻው ጦፈ፡፡ ፌደራል ፖሊሶቹ የተለያዩ ሰዎች የያዙትን ተመሳሳይ ዕቃ መሰብሰብ ጀመሩ፡፡ ወሰዱባቸው፡፡ እንዴት እንደሚያሸጋግሩ አውቀውባቸዋል፡፡ አንዱን የሌላ ሰው ዕቃ በትብብር የያዘ ሰው የፌደራል ፖሊሱ ‹‹ያንተ ከሆነ እስኪ ወላሂ በል›› ሲለው ‹‹አልልም›› አለ፡፡ እቃውም ተወሰደ፡፡ ‹‹ለሷ ብዬ ወላሂ ብዬ ሦስት ቀን ልፆም!›› አለ፡፡ በየመንገዱ በዉሃ ኮዳ ወተት የያዙ ሴቶች ለሽያጭ ያቀርባሉ፡፡ ፓስቲና በቆሎም ይሸጣሉ፡፡ ስመለስ ፓስቲ ልገዛ ዋጋውን ስጠይቅ ‹አፋርተን› ስትለኝ ሃምሳ ብር ስሰጣት መልስ ልትመልስ ስትሞክር ተዪው አልኳት፡፡ ዋጋው አርባ ብር መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ብዬ በቆሎ እሸት ስገዛ ሃምሳ ብር ሳሳይ አይሆንም ብለው ከዋሌቴ ውስጥ በምልክት መቶ ብሩን አሳይተውኝ ገዝቻለሁ፡፡ ቁጥሮቻቸው ከኦሮምኛ ጋር ይመሳሰላሉ፡፡ ይህንንም ከጉግል አረጋግጫለሁ፡፡ ወደ ጅግጅጋ ተመልሼ የአውሮፕላን ቲኬቴን ኦንላይን ቆርጬ አደርኩ፡፡ ለዚህች መንገድ 10,159 ብር ከፈልኩ፡፡ ዘንድሮ መጋቢት ላይ የተመረቀውን የሶማሌውን ታጋይ የሰይድ መሐመድ አብዱል ሐሰንን ሐውልትና አደባባይ ጎበኘሁ፡፡ ከጉግልና ከአዲስ ስታንዳርድ እንደተረዳሁት የእንግሊዝ፣ የጣልያንንና የኢትዮጵያን መንግስታት የተዋጋ የሶማሌ ‹ጀግና› ነው፡፡ 

 

እሁድ፣ ሰኔ 21

ከሆቴሉ አቅራቢያ የሚገኘውን የቅዱስ ሚካኤልን ቤተክርስቲን አየሁ፡፡ እሁድ ስለሆነ ምዕመኑ ያስቀድሳል፡፡ ፎቶና ቪዲዮ አንስቼ እንደተለመደው ለማህበራዊ ሚዲያ ተከታታዮቼ አጋራሁ፡፡ በዕለቱ ቁርስ የበላሁበት አንድ የሱማሌዎች የመሰለኝ ካፌ ውስጥ ስገባ አንድ ስዕል ተሰቅሏል፡፡ የግመል ስዕል ሲሆን ከስሩ አንድ ወንድና ሌላ ሴት ልጆች ወተት በባህላዊ መጠጫ ሲጠጡ ያሳያል፡፡ አስተናጋጇ ሂጃቧን ጠምጥማ አጠገቤ ቆማ ምን ልታዘዝ ስትለኝ ምን እንዳለ ጠየቅኋት፡፡ ብዙ የወተት ተዋጽኦ ብትጠቅስም ሻይና ኬክ አዘዝኩ፡፡ ከግመሉ ስዕል ስር ሁለት ክርስቲያን ወንድና ሴት ቁርስ እየበሉ በትግርኛ ያወራሉ፡፡ ሁሉም የሚጠቀምበት ቤት መሆኑ ገባኝ፡፡ የወትሮውን በቀን አንዴ አመጋገቤን በጉዞ ወቅት ማስቀጠል ስለሚከብደኝና የምፈልገውን ምግብ በበቂ ሁኔታ ስለማላገኝ የተገኘውን እበላለሁ፡፡ እቤቴ ስሆን በፈለኩት መጠን ስለማዘጋጅ በቀን አንዴ እመገባለሁ፡፡  ለክፍያው ኢብር ስለሌለኝ እንደምንም በንግድ ባንክ መላክ ቻልኩ፡፡ በወረቀት ብር መክፈል አይታሰብም፡፡  

ባጃጅ ውስጥ አቀማመጡ ወንድ ከወንድ ሴት ከሴት መሆኑን ያስገነዘበኝ አጋጣሚም አለ፡፡ ሴቷ ከመሃል እንድትገባ ስጋብዝ ወደ ሴቷ ትሁን አሉ፡፡ የአዲሱ እስልምና ተጽዕኖ መሰለኝ፡፡ የእስልምና እየተቀየረ መሄድ በስፋት ተጽፎበታል፤ አንብቤያለሁም፡፡ ዘይት በትንንሽ ላስቲኮች እየተቀነሰና እየተቋጠረ ሲሸጥ አይቻለሁ፡፡ ቦርጭ የሌለው ትራፊክ ያለው ጅጅጋ ነው፡፡ ምናልባት ታማኝ ይሆናሉ፡፡ ‎‎መንገድ ላይ ቦርሳዬን አዝዬ ስሄድ አንድ ድልድይ አጠገብ የተቀመጠ ፖሊስ ‹አንተ!› ብሎ ጠራኝ፡፡ አቤት ብዬ ሄጄ በሰላምታ እጁን ጨበጥኩት፡፡ ምን እንዳዘልኩ ሲጠይቀኝ የራሴን የተለበሰና ያልተለበሰ ልብስ እንደሆነ ስለግረው አሰናበተኝ፡፡ ሱማሌዎች ክርስቲያን ምግብ ቤት ገብተው እንጀራ እንደሚበሉም አየሁ

 ለመልስ ጉዞው ወደ አየር ማረፊያው ስሄድ የሚሻለውንና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለውን መኪና የማገኝበትን መናኸሪያ ዘመዶቼ አሳዩኝ፡፡ መቼም የመረጃን ጠቃሚነት አልነግራችሁም፡፡ ጉግልንም ሆነ ሰዎችን መጠየቅ ጉዞዬን አቅልሎልኛል፡፡ ወደ አየር ማረፊያ ስሳፈር ዕቃ ያዝልኝ የሚሉ ሴቶች አስቸገሩኝ፡፡ በትህትና እንደማልችል ነገርኳቸው፡፡ አየር ማረፊያውም ጋ ስደርስ እንዲሁ ተረባርበው ጨቀጨቁኝ፡፡ ገንዘብ እንስጠህም ያሉኝ ነበሩ፡፡ ከኮንትሮባንድ ወጥመድ አምልጬ አየር ማረፊያው ግቢ ስደርስ እፎይታ ተሰማኝ፡፡ የምስራቅ ኢትዮጵያ ኮንትሮባንዲስቶች አምስት የማጥመጃ መንገዶች ጉግል ላይ አሉ፡፡

በመኪናው ውስጥ ያገኘሁት ወጣት ለሰባት ዓመታት እዚያ የሰራና ወደ አማራ ክልል በዝውውር እየሄደ ያለ ነው፡፡ ሸበሌን ተከትሎ የለሙ ከተሞች መኖራቸውን ነገረኝ፡፡ ከሸበሌ የራቁት ቦታዎች ድርቅ እንደሚያጠቃቸው አስረዳኝ፡፡ ብሔር ዘለል ጋብቻ መኖሩን ስጠይቀው ሶማሌዎች አልፎ አልፎ ከኦሮሞ ሙስሊም ሴቶች ጋር እንደሚጋቡ ነገረኝ፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ጋብቻ በሶማሌም ውስጥ በጎሳ ነው፡፡ አንድ እኔና ጓደኛዬ በዕድሜ የምንበልጠው አማራ ሙስሊም አንዲት ሶማሌን ማግባቱንና አምስት ልጆች መውለዱን ጓዳዬ ነግሮኛል፡፡ ሶማሌዎች ቋንቋቸው በርከት ያሉ የጉሮሮ ድምፆች ያሉት መሰለኝ፡፡ ሻይ በኒዶ ወተት ሲጠጡ ብዙ ቦታ አይቻለሁ፡፡ በጅግጅጋ በአህያ የሚጎተት ቢዮሌ የሚባል የውሃ ጋሪ አለ፡፡ የሶማሌ ህዝብ በተለያዩ አገሮች ተበታትኖ ይኖራል፡፡ አክራሪ እስልምና ከግብፅ በመጡ የሙስሊም ወንድማማችነት የእስልምና መምህራን በሶማሊያ እንዴት እንደተስፋፋ አያን ሂርሲ አሊ በሰፊው የራሷን አስተዳደግ በምሳሌነት በማንሳት ጽፋለች፡፡ ፍልስጤም ነጻ ትሁን የሚል ጽሑፍ ግድግዳ ላይ አይቻለሁ፡፡ የፊት ሙሉ በሙሉ መሸፋፈንና ሌሎችን ምልክቶች ሳይ በእኛም አገር ይህ ችግር እያቆጠቆጠ መሆኑን ተጠራጥሬያለሁ፡፡ በምስራቅ ኢትዮጵያ አስደሳች የአንድ ሳምንት ቆይታ ማድረጌ አገሬንና ወገኔን የበለጠ ለማወቅ ዕድሉን ከፍቶልኛል፡፡  ቦርሳ ተሸክሜ መዞሬና የጉዞ ስሜት መኖሩ የተወሰነ ያጨናንቃል፡፡ መኪና ቢኖረኝ ኖሮ ከደብረብርሃን እየነዳሁ ልሄድ የምችል አይመስለኝም፡፡ የብሔር ታርጋዬን ለጥፌና የተጉለት አማርኛዬን እያወራሁ እዚያ መድረሴ ያጠራጥራል፡፡ ምናልባት ጉዞ ካቀዳችሁ ብትጠቀሙበት የጉዞዬ አጠቃላይ ወጪም 30 000 ብር ነው፡፡ በረራችን በአውሮፕላን ቶሎ አለመምጣት ምክንያት በአንድ ሰዓት ዘግይቶ አዲስ አበባ በሰላም ደረስን፡፡ ደመና ከጋረደኝ በቀር በመስኮት አገሬን አይቻለሁ፡፡  አዲስ አበባ ቦሌ ደርሼ ከአውሮፕላን ማረፊያው በእግሬ ስወጣ በአንድ ስክሪን ላይ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ፎቶ ተለጥፎ እንኳን ደህና መጡ በሚል ጽሑፍ ታጅቧል፡፡ በዕለቱ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ ሰሞኑን በተለያዩ አገሮች ስላሉ የሶማሌ ማህበረሰብ የተናገሩት አነጋጋሪ ሃሳብ ሳስበው ከመስተንግዶው ጋር አልሄድ አለኝ፡፡  ለማንኛውም በቀጣናው ሰላም እንደሚመጣና በፍቅር እንደምንኖር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሰኔ 22 ሰኞ ከቤቴ በወጣሁ በሳምንቱ ደብረብርሃን በሰላም ገባሁ፡፡

 

 



አንድ ሳምንት ከደብረብርሃን እስከ ሶማሊላንድ ድንበር

  ‎‎ ‎ ‎ ‎ ‎‎   ‎ አንድ ሳምንት ከደብረብርሃን እስከ ሶማሊላንድ ድንበር ‎‎ መዘምር ግርማ ‎ ሰኔ 2018 ዓ . ም . ‎‎ ‎ ሰኞ፣ ሰኔ 15 ‎ ጠዋት ከደብረብርሃን ...