ሐሙስ 30 ኦገስት 2018

የሥኬት ፈር-ቀዳጁ የደብረ ብርሃን ቆዳ ፋብሪካ





የሥኬት ሥልጠና ቡድናችን አባላት አርፍደው ስለነበር ከቀኑ 11፡00 ሳይሞላና የፋብሪካው ዋና ዋና ዘመናዊ የሥራ ክፍሎች ሳይዘጉብኝ ብቻዬን ከራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ወደ ጅሩ መስመር በእግሬ በጥድፊያ አቀናሁ፡፡ ከጅሩ መስመርም በጋሪ ተነስቼ ከአምስት ደቂቃ ገደማ በኋላ ፋብሪካው በር ላይ ደረስኩ፡፡ እዚያም በደረስኩ ጊዜ አቶ ኃይሉንና ሌሎችንም የማውቃቸውን ሰራተኞች አገኘሁ፡፡ ሰራተኞቹ የቤተመጻሕፍታችን አንባቢዎች በመሆናቸውና እንዲያውም የራሳቸው የመጻሕፍት ዕቁብ ጀምረው መጽሐፍ እየገዙ ያበረታቱንም ስለነበር ፈጽሞ ባይተዋርነት አልተሰማኝም፡፡  የተለያዩ የስራ ክፍሎችን ለሥራው ያላቸውን ፍቅር በሚያሳይ መልኩ አንድ በአንድ ያስጎበኙኝ ጀመር፡፡
የደብረ ብርሃን ቆዳ ፋብሪካ በጥቁር አባይ ጫማ አክስዮን ማህበር ስር ካሉት ሰባት የስራ ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ ከሃያ አንድ ዓመታት በፊት በአንድ ባለሐብት ተቋቁሞ በኋላ ላይ በልማት ባንክ በሃራጅ ለጥቁር አባይ ጫማ ፋብሪካ የተሸጠ ነው፡፡ የሥራ ክፍሎቹን በወፍ በረር እንቃኛቸው፡፡

1. ቢም ሃውስ
በተንጣለለው አዳራሽ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘው ይህ ሥፍራ መጋዘኑን ጭምር ያቀፈ ነው፡፡ መጋዘኑም አዲስ ቆዳ እንደመጣ የሚከማችበት ነው፡፡ ከመጋዘኑ ወደዚህ ሲል በአቅራቢያው ቆዳዎቹ የሚታጠቡባቸው ትልልቅ ገንዳዎች አሉ፡፡ ቆዳውን ከውኃ ጋር እያሽከረከሩ የሚያጥቡት ማሽኖች እንጂ ሰዎች እንዳልሆኑ ተረዱልኝ፡፡ ደም፣ ቁርጥራጭ ስጋ (በተለምዶ ደደብ የሚባለው) እና ጸጉርን የመሳሰሉት አላስፈላጊ ነገሮች ከቆዳዎቹ ላይ ይነሳላቸዋል፡፡
የቆዳን አያያዝ አስመልክቶ እርዱ በጥንቃቄ ቢሆን ይመከራል፡፡ ከቄራ የሚመጣው አስተራረዱም ሆነ አያያዙ ጥሩ ነው፡፡ የሚገፈፈው በንፋስ ነው፡፡ ቆዳ ከእርድ በኋላ መጋዘን ሳይቆይ ወደ ፋብሪካ ከገባ ለሥራ ቀና ይሆናል፡፡ የአገራችን የቆዳ ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ በህይወት ሳሉ የማይታጠቡና ቆዳቸው የሚበላሽ እንስሳት፤ እከክ የሚያጠቃቸው፤ ከግንድ ሲታከኩ ቆዳቸው የሚጎዳ ወዘተ አሉ፡፡ ይህም በፈብሪካውም ሆነ በአገራችን ሃብት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ስላለው ጥንቃቄው ከሁሉም ወገን ይጠበቃል፡፡ ይህን መልዕክት አበክረው የነገሩኝ የፋብሪካው ሰራተኞች የሚባክነው የሃገር ሃብት በየቀኑ ሲጣል ስለሚያዩ ምክራቸው በህብረተሰቡ ሊተገበር ይገባዋል፡፡
በትልቁ አዳራሽ በስተቀኝ ክፍል ተጨማሪ ትልልቅ በርሜሎች (ድራሞች) የሚያርፉባቸው ማቆሚያ ግንቦች እየተገነቡ አይተናል፡፡ እንዲያውም አንደኛው ግንበኛ ዓይኑ ውስጥ ሲሚንቶ ገብቶበት አውጥተንለታል፡፡ ሁሉም የሥራ ርብርቡ የሚያስቀና ነው፡፡ ‹‹በእውነቱ እኔስ ምን ያህል እየሰራሁ ነው?›› ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡
2. ታኒንግ
በዚህ ክፍል እያንዳንዳቸው እስከ 2200 ወይም 6000 ስኩየር ጫማ ቆዳ የሚይዙ በርሜሎች (ድራሞች) አሉ፡፡ ከእንጨት የተሰሩና ምናልባትም በአልኮል መጠጥ ዝግጅት በየቴሌቭዥኑ ያየናቸውን የሚመሳስሉ ናቸው፡፡ ቆዳው በተለያዩ ኬሚካሎች የመታሸት ሂደት ውስጥ ያልፋል፡፡ ከበርሜል በርሜልም ይገላበጣል፡፡ ከነዚህም ሂደቶች አንዱ የሆነው ቆዳው ከ14 እስከ 18 ሰዓት ለሚሆን ጊዜ ክሮም በተባለ ኬሚካል የመልፋት ሂደት ውስጥ የሚያልፍበት ነው፡፡ ክሮም ምርጥ የቆዳ መስሪያ ኬሚካል ነው፡፡ ቆዳን ሰማያዊ ያደርጋል፡፡ ያሳምራል፡፡ በሱ የለፋው ቆዳ ሰማያዊ ሲሆን የስራን ብቃት ያሳያል፡፡ መጀመሪያ ላይ አካላዊ የነበረው የቆዳ ማልፋት ስራ ካለቀ በኋላና ቆዳው በክሮም ከታሸ ሙቀትና ባክቴሪያን ይቋቋማል፡፡ ቢወጠርም አይጎዳም፡፡ ቢቀጣጠል መኪና የመጎተት አቅም አለው፡፡ ያ እርጥብ ቆዳ ለዐሥር ዓመታት በዚያ ሁኔታ መቆየት ይችላል ሲሏችሁ የኬሚስትሪንና የሣይነስን ገጸበረከት ከማመስገን በላይ ምን ማድረግ ይቻላችኋል?
3. ሪታኒንግ
ቆዳው እንዳስፈላጊነቱ በተለያዩ ቀለማት ይቀልማል፡፡ ይህም የሚከናወነው በበርሜል ውስጥ ነው፡፡ ዘይቶችና ሲንታኖች የሚባሉ የሚያሳምሩ ቅባቶች ናቸው ለማልፋት የሚጠቅሙት፡፡ በዚህኛው የበርሜሎች ስብስብ አካባቢ ወጣት ሰራተኞች እየተዘዋወሩ የስራውን ሂደት ሲቆጣጠሩ አይተናል፡፡ ድራሙ ሲዞር እየሾለኩ የሚጡ ቆዳዎችን ማንሳትና ማስገባት፣ የማሽኑን ስራና የኤሌክትሪክ ሁኔታውን መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ የሥራ ጋወን የለበሱ ሰራተኞች ይህን ይሰራሉ፡፡ በየደቂቃው ደግሞ በጋሪ ቆዳ የሚገፉ በቡድን የሚሰሩ ወጣቶችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ ሁሉም ባተሌ፣ ሁሉም ንቁ፣ ሁሉም ትጉህ ሲሆን በዓይናችን በብረቱ አይተናል፡፡
4. የምርምር ድረም - በደንበኛ ስሩልን ተብሎ የሚመጣውን ናሙና ቆዳ ዓይነት በአነስተኛ መጠን ሞክሮ መስሪያ የምርምር ቦታ ነው ይህኛው፡፡ ያንን ቆዳ ሰርቶ በተባለው ዓይነት ለማምጣት ልምድና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሲሆን እስከ ዐሥር ጊዜ የሚሞክሩ ይኖራሉ፡፡ ሞክረው ሞክረው የሚፈለገው ዓይነት አንዴ ከመጣላቸው ግን ያንን የመዘገቡትን ሂደት ተከትሎ ወደ ምርት መግባትና በታዘዘው መጠን ማዘጋጀት ነው፡፡ የድራም ነገር አልቆ ልክ ከመጋዘኑ ፊትለፊት በዚህኛው የአዳራሹ ጥግ ሌላ ክፍል አለ፡፡ እንደሚከተለው ነው፡-

5.  ሰሌክሽን (መረጣ)
ቆዳዎች በያይነታቸው፤ ከደረጃ አንድ እስከ ሰባት (አፐር፣ ኤክስፖርት ሺፕ ላይኒንግ፣ ሺፕ ጋርመንት፣ ላርጅ፣ ስሞል፣ ኤክስትራ ላርጅ ወዘተ) እየተባሉ ረጅም ጠረጴዛ ላይ የሚመረጡበት ክፍል ነው፡፡ ሰባተኛው ደረጃ ተወጋጅ ቆዳ ነው፡፡ ሲወገድም የመግዣ ዋጋውን ጨምሮ ለዚህ ቆዳ የተለፋበትና የወጣበት ሁሉ ይታጣል ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ፋብሪካ 65 በመቶ ገደማ የበግና ከ10 እስከ 25 መቶ የፍየል ቆዳ አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡ የበሬ ቆዳ አይጠቀሙም፡፡ የበሬ ለመስራት የሚያስፈልጉ ማሽኖች ስለሌሉ አሁን እየተሰራ ካለው የፋብሪካው ማስፋፊያ ስራ በኋላ የሚካሄድ ይሆናል፡፡ ያኔ ጥቁር አባይ ከሌሎች ፈብሪካዎች የሚገዛው የበሬ ቆዳ በራሱ ፋብሪካ ይሸፈናል፡፡
ዘግይተው የመጡት ባልደረቦቼ ተካተው ጉብኝቱም ስራቸውን ጨርሰው በተቀላቀሉን በአቶ ኤርሚያስ ወሰኑ አስጎብኝነት ቀጠለ፡፡ የዚህን ፋብሪካ በር ስንረግጥ ስለ ቆዳ ምንም የማናውቅ የነበርነው አሁን ምስጢሩ እየተገለጠልን ነው፡፡ በመጀመሪያ ወደፋብሪካው በር ስንመጣ ያየነው የስራ ትጋትና ጥድፊያ ፋብሪካ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚካሄድ ግንዛቤያችንን አሻሽሎልናል፡፡ አዲስ ዓለ፣ አዲስ ትዕይንት፣ አዲስ መገለጥ!
ጥያቄዎቻችንን በትጋትና በአድናቆት የሚቀበሉና የሚመልሱት ሰራተኞች በመልሳቸው አጥጋቢነት ያስደምሟችኋል፡፡ ፋብሪካው ኬሚካል 95 በመቶ የሚያስመጣው ከውጪ ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ብዛት ያላቸው ኦርጋኒክ ኬሚካሎች ናቸው፡፡ ክሮሙን አስመልክቶ እንደተነገረን አደገኛው ዓይነት አይደለም፡፡
በፋብሪካው 119 ሰራተኞች ሲኖሩ፤ አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ክፍል የራሱ ኃላፊ አለው፡፡ ፍሎር ኦፐሬተሮች፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ የቴክኒክ ማኔጀሮች፣ ፎርማኖች አሉ፡፡ ለፋብሪካው ስራ የተለያዩ አስፈላጊ ሙያዎች ሲኖሩ፤ በዋነኝነት ግን የኬሚስትሪና የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች ናቸው ስራውን እያስኬዱ ያሉት፡፡ አዲስ አበባ ሊድ የሚባል ተቋም ስላለ መሰረታዊ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የጨረሱ ሰዎች እዚያ የቆዳን ስራ  ይሰለጥናሉ፡፡ በኬሚስትሪ ላይም ስለቆዳ ኮመን ኮርስ ይወስዳሉ፡፡ የውጪ አገር የትምህርት ዕድልም ሲያገኙ እንግሊዝ ድረስ የሚሄዱ አሉ፡፡ በዚህ ፈብሪካ የኛው አገር ልጆች ስራውን መስራታቸው ያስመሰግናል፡፡ ዩኒቨርሲቲም ስለተማሩ ላይገርም ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እኛው አገር ላይ ይህንን ዓይነት የኛኑ ጥሬ ዕቃን መልክ የማስያዝ ስራ መሰራቱ በሌላም ዘርፍ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ለሃገር እድገትና እንቅስቃሴ መሰረታዊ ስራ እየተሰራ አይተናል፡፡
በፋብሪካው ትናንሽ መድማቶችና መቆረጦች  ካልሆኑ በስተቀር አደጋ አልተከሰተም፡፡  ሰራተኞቹ ካይዘን ሰልጥነዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ ለመጀመርም እየተዘጋጁ ነው፡፡ ከአብዛኞቹ ፋብሪካዎች እንደሚሻሉና ሌላ ቦታዎች ላይ መረማመድ እንኳን እንደሚያስቸግር መመልከታቸውን ነግረውናል፡፡
በዚህ ፋብሪካ ብዙ ጥንቃቄ እንደሚያሻ ተምረናል፡፡ ‹‹ከሚመለከተው ሰራተኛ በስተቀር መንካት ክልክል ነው፡፡›› ‹‹ቅድሚያ ለደህንነትዎ›› የሚሉ የጥንቃቄ ማስታወቂያዎችን አክብሮ መንቀሳቀስ ግድ ይላል፡፡  ሙሉ የጤና ዋስትናና ዓመታዊ የጤና ምርመራ ለሰራተኞች እንደሚሰጥ ሰምተናል፡፡
በስራውም በኩል የደቂቃዎች ስህተት ብዙ ገንዘብ ያከስራል፡፡ ባክቴሪያ እንዳይበዛ መጠንቀቅ ያሻል፡፡ ኢዛይሞቹ ቆዳውን ሾርባ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡
የመብራት ጉዳይ
ባንዴ 120 ሊትር ድፍድፍ ነዳጅ ለእንፋሎት ማዘጋጃ ይጠቀማሉ፡፡ ይህን የሚሰሩት ማለዳ ገብተው ዝግጁ አድርገው ይጠብቃሉ፡፡ መብራት ሲጠፋ የተለፋበትና 120 ሊትር የባከነበት ሰራ እንዳልነበር ይሆናል፡፡ ጄኔሬተርም ይጠቀማሉ፡፡ 60 ሰራተኛ ከማሽን ጋር ስለሚገናኝ የደሞዝ ኪሳራም ይኖራል፡፡ በመብራት ምክንያት ብዙ ኪሳራ እንዳለ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ ይህ ሃገር አቀፍ ችግረ አንገብጋቢ በሆኑ የስራ ቦታዎች ልዩ ትኩረት ቢሰጠው እንላለን፡፡ ለምሳሌ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መብራት አይጠፋም ለማለት የሚያስደፍር ነገር አለ፡፡

በፋብሪካው 2ኛው ክፍል
መጭመቂያ ማሽኖች የዚህ ክፍል ድምቀቶች ናቸው፡፡ ጣራውን ታኮ በተሰራ ማንጠልጠያ የሰንሰለት ጋሪ ላይ ተንጠልጥለው እንዲደርቁ ቤቱን ሲዞሩ የሚውሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የሚመስሉ ቆዳዎች በመጀመሪያው ክፍል እንዳየናቸው ተሽከርካሪ በርሜሎች ሁሉ በስራ ላይ ያለውን ፋብሪካ ድምቀት ሰጥተውታል፡፡ አገሩ ደብረ ብርሃን ስለሆነ የመድረቂያ ጊዜያቸው ረጅም ነው፡፡ ሞጆ በግማሽ ቀን የሚደርቀው እዚህ ሦስት ቀንም ሊወስድበት ይችላል፡፡
ጊዜው ደርሶ የደረቀውን ቆዳ ስቴኪንግ ማሽኖች ያለሰልሱታል፡፡ ሌላ ደግሞ ሙቀትና ርጥበትን ጠብቆ የሚያሽ ማሽን አለ፡፡ የቆዳውን ውፍረት እየለካ የሚያለሰልሰው ማሽን ቀጣዩ ነው፡፡ ቆዳው እንዲያብረቀርቅ የሚያደርግ ማሽን አለ፡፡ ማቅለሚያ፣ መለኪያ ማሽን… ከ70 በላይ አውሮፓና ቻይና ሰራሽ ማሽኖች ብዙ ናቸው፡፡ ዘመናዊ ማሽኖች ብቻ ሳይሆኑ እነሱን ኦፐሬት የሚያደርጉትም ልጆች ዘመናዊነት ይታያችሁ! ከሁለት ሰራተኞች በቀር የደብረብርሃንና አካበቢው ተወላጆች ናቸው፡፡ ድርጅቱ በወጣቶች ስለሚተማመን የብዙ ክፍሎች ስራ አስኪያጆች ወጣቶች እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
አፐር፣ ላይኒንግ፣ ጋርመንት፣ ግላቭ እየተባለ ቆዳው እንዳገልግሎቱና መጠኑ መለየት እየጀመረ ነው፡፡ ልስላሴውን ልነግራችሁ አልችልም፡፡ የፋብሪካውን አርማ እየመቱ ማሸግ የመጨረሻው ስራ መጀመሪያ ነው፡፡
ፋብሪካው የፍሻሽ ቆሻሻውን ችግር ለመፍታት ዘመናዊ ትሪትመንት እያሰራ ነው፡፡ በጥቂት ወራት የሚደርሰው ይህ ማጣሪያ እስካሁን ያለውን የሚተካ ሲሆን ሃያ ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡
ይህ ፋብሪካ ቆዳን ለአገራችን፣ ለአፍሪካና ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንጂ ልብሶችንና ጫማዎችን አይሰራም፡፡ አዲስ አበባ ያለው የጥቁር አባይ ፋብሪካ ነው ጫማ የሚሰራው፡፡ የአገራችን የፖሊስ፣ የመከላከያና ሌሎችም ድርጅቶች አባላት ጫማ ከፋብሪካው ያዛሉ፡፡ የምስራቅ አፍሪካ አገራትም እንዲሁ፡፡
ዓላማችን ፋብሪካ ውስጥ ያለውን የስራ ትጋት አይተን ለግላችን ስኬት ለመጠቀም ወይም ትምህርት ለመውሰድ ነበር፡፡ ብዙ እዚህ ጋ ያልጻፈኳቸውን ትምህርቶች አግኝተናል፡፡
አስፈላጊውን የጥራት ደረጃ ሳያሟሉ ቀርተው የሚወገዱ ቆዳዎችና ቁርጥራጮችም በእጅ በሚሰሩ አነስተኛ ካፒታል ባላቸው ሰዎች ይፈለጋሉ፡፡ በጣም አነስተኞቹም ለመቀመጫ መስሪያና ለችፑድ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ረገድ ለመስራት ያሰቡ ጎብኝዎችን ፋብረካው እንደሚያበረታታ ተነግሮናል፡፡ የምሰራች በሉ!
ምስጋና
አስጎብኛችን ኤርሚያስ ወሰኑ ባለፈው ዓመት እንጦጦ ቤተመንግስትን ስንጎበኝ ‹‹ብራና አስነኩኝ›› ብሎ አስጎብኝውን ሲጠይቅ ነበር ለቆዳ ዘርፍ በሙሉ ልቡ የሚሰራ ወጣት መሆኑን ያወኩት፡፡ ፋብሪካውን እንድንጎበኝ በመፍቀድና ጉብኝቱንም በመምራት ላደረገልን ቀና ትብብር የቡድኑ አባላት ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡ እሱን ብቻም ሳይሆን ሁሉንም የፋብሪካውን ሰራተኞች እናመሰግናለን ለማለት እንወዳለን፡፡
ከጽሑፉ በኋላ 1
በጽሑፌ ሰበብ በዚህ ጉብኝት ላይ በምናደርገው ውይይት ውስጥ የአካባቢ ብክለት ጉዳይ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ፋብሪካው ሁኔታውን ለማሻሻል ብዙ ጥረቶችን እንዳደረገ ተረድተናል፡፡ የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ አለማግኘትና በፋብሪካው ዙሪያ የመኖሪያ ስፍራ እንዲሆን መፈቀዱ እንደችግሮች ተነስተዋል፡፡ ችግሮቹ በቅርቡ ተፈተው እንደምናይ ያለው ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ያሳያል፡፡
ከጹሁፉ በኋላ 2
በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሐፍት የሐሙስ የሥነጽሑፍ ምሽት የጉብኝቱን ነገርና የፋብሪካውን የስራ አካሄድ ተወያይተንበታል፡፡
እኔና ኤርሚያስ ወሰኑ የፋብሪካውን የቆዳ ቁርጥራጭ ቆሻሻ አወጋገድ ለማስተካከል እንዲረዳን ወደ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ አቅንተን ብዙ ተስፋ ሰጪ ነገሮችን አግኝተን ተመልሰናል፡፡ በዚህ ጥረትም ያ በማስወገጃ ቦታ አለመኖር ምክንያት ተከምሮ የሚሸተው ቆሻሻ መፍትሔ ካገኘ አስገራሚ ይሆናል፡፡ ውጤቱን አብረን እናየዋለን፡፡
ከጽሑፉ በኋላ 3
ታክመን የምንድንበትን፣ ተምረን የምንለወጥበትን፣ ብዙ መድህን የምናገኝበትን ዘመናዊ ነገር ሀሉ ከውጪ አገር እንደምናስመጣ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ሞተሩ የውጪ ምንዛሬ ነው፡፡ ይህን ምንዛሬ የምናገኘው እጅግ ውሱን ከሆኑ ዘርፎች ሲሆን፤ የቆዳው ኢንዱስትሪ አንዱ ነው፡፡ ታዲያ ለምን 35 የቆዳ ፋብሪካዎች ሲዘጉ ዝም አልን? በተሻለ ሁኔታ እንዲሰቱ መንገዱን ማመቻቸት ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ ከጸሐፊዎችም ጭምር፡፡                                                     ይቀጥላል። Because you read this I give you this mobile card as an encouragement. If you are the first one, inform me. number: 55125341922384
በእንግሊዝኛም ይተረጎማል።
ሥራ አስኪያጁንም በቃለመጠይቅ እናቀርባለን።

3 አስተያየቶች:

  1. ከቆዳ ፋብሪካው የሚለቀቀው ክሮም የተባው ኬሚካል ህዝቡን ለቆዳ በሽታ እየዳረገው እንደሆነ ከህዝባዊ ውይይቶች ሰምቻሁ፡፡ይህ የሚታከምበት ዘዴ ካለ አካተህ ብትጽፈው መልካም ነበር፡፡

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. ከቆዳ ፋብሪካው የሚለቀቀው ክሮም የተባው ኬሚካል ህዝቡን ለቆዳ በሽታ እየዳረገው እንደሆነ ከህዝባዊ ውይይቶች ሰምቻሁ፡፡ይህ የሚታከምበት ዘዴ ካለ አካተህ ብትጽፈው መልካም ነበር፡፡

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  3. መዜ ጥሩ ቅኝት ነው። ሌሎች አነስተኛ ድርጅቶች ብዙ አሉ በኪሳራ የሚጠፉም በሽ ናቸው። ወደ ስኬት ጎዳናው የሚሻገሩበትን ድልድይ ብትሰሩ መልካም ነው።

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...