ማክሰኞ 5 ኖቬምበር 2019

ቻይናን በኢትዮጵያዊው እይታ



26. 2. 2012

ዶክተር ሃይለሚካኤል ለማ ይባላል፡፡ ዛሬ ጠዋት በስራ ቦታው በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መዝናኛ ክበብ አግኝቼ በቅርቡ በሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና ስላደረገው አጭር ቆይታ አነጋግሬዋለሁ፡፡ ከጉብኝቱ እድንማርና እንድንወያይበት በመጋበዝ ቀጥታ ወደ ቃለመጠይቁ እንግባ፡፡  

1.    የሄዳችሁበት ዓላማ ምን ነበር?
ዝግጅት አላደረግንም፡፡ በአስቸኳይ ነው የተነሳነው፡፡ አካሄዳችን በዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ላይ ስልጠና ለመውሰድ ነው፡፡ ለሃያ ቀን ቆይተናል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሴት የዩኒቨርሲቲ አመራሮች አሉ፡፡ ምክትሎች ማለት ነው፡፡ የሴት ዋና ፕሬዚዳንት ስለሌለ፡፡ ወንድ አምስት ነን፡፡ ከአማራ ክልል ብቻ ነው ወንዶች የሄድነው፡፡
መጀመሪያ ግዋንዡ ከተማ ነበር የወረድነው፡፡ ከዚያ በሃገር ውስጥ በረራ ዢንዋ ወደሚባል ከተማ ሄድን፡፡ የህዝቡን የእንግዳ አቀባበልና ክብር አየን፡፡ ሰውን በቀና የሚያዩና የሚያከብሩ ናቸው፡፡ የሃገሩ ሁኔታ የተደመምኩበት ነገር ሙሉ በሙሉ ለምለምና አረንጓዴ ነው፡፡ ወጣ ገባ የሆነ አቀማመጥ ቢኖረውም  እንኳን ተራራውን እየበሱ መንገዶችን መሬት ለመሬት ሜዳ አድርገዋል፡፡ ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ ያየሁት ቻይና ነው - በመንገድና በአረንጓዴ በማልበስ፡፡
2.    የሌላ አገር ዜጎች አገኛችሁ? ከኛ ያላቸውስ ልዩነት ምን ይመስላል፡፡

ከአፍሪካና ከላቲን የሄዱ ነበሩ፡፡ የኛ በአብዛኛው ዝምተኛና ጨዋ ማህበረሰብ ሲሆን እነዚያ በአንጻሩ ተጫዋች ናቸው፡፡ የወሬያቸውን ፍሬ ሐሳብ ለመያዝ እንኳን ከባድ ነው፡፡ ከአፍሪካ የጋና፣ የናይጀሪያ፣ የሴራሊዮን የመሳሰሉት አሉ፡፡ የቻይና መንግስት የንግድ ሚኒስቴር ነው ወጪውን የሸፈነው፡፡ የሰለጠንነው ስለ አመራር ሳይሆን ቻይና ከአሜሪካ ስላላት ልዩነት ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ስላላቸው ልዩነት አስገንዘበውናል፡፡  
3.    ያስገረመህ ነገርስ?
ያስደመኝ ነገር ቢኖር የከተሞቻቸው ንጽሕና ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው የጽዳት ሰራተኛ ነው፡፡ የተጠቀምከውን መጣያ ቅርጫት በየቦታው አለ፡፡ መንገዳቸው በሁለት በኩል ሆኖ ከግራም ከቀኝም ከአራት እስከ ስድስት መኪና የሚያስኬድ አለው፡፡ ሌላ ያስደሰተኝ ድልድዮቻቸውና ህንጻዎቻቸው በጣም ዘመናዊ መሆናቸው ነው፡፡ ሙዚየምም አስጎብኝተውናል፡፡ 3 ቴክኖሎጂ አሳይተውናል፡፡ አብዛኛው ስራቸው በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑም ይመስላል በመንገዶቻቸው ላይ እንደ ህዝብ ብዛታቸው ሰው አይታይም፡፡
4.    ያሳዘነህስ?
የኛና የነሱ ልዩነት ነው ያሳዘነኝ፡፡ መቶ ዓመትም የሚበቃን አይመስለኝም በዚህ ባህላችን፡፡ የመጀመሪያው እንለወጥ ብለን ካሰብን የሚያስፈልገን የአመለካከት ለውጥ ነው፡፡ እነሱ ለሃገራቸው ያላቸው ክብር፣ ቁርጠኝነት፣ ፍቅርና የሥራ ታታሪነት ልነግርህ አልችልም፡፡ እያንዳንዱ የገጽታ ግንባታ ነው፡፡ የመሪያቸውን ንግግር ያለበትን ትልቅ መጽሐፍ ሰጡን፡፡ የስልጠናው ርዕስ ሊባል የሚችለው የገጽታ ግንባታ ነው፡፡ አንዳንዶቹ መሪያቸውን እንደ መልዓክ ያዩታል፡፡ እያንዳንዱን ስራቸውን በተለይ ከአሜሪካና አልፎ አልፎም ከእንግሊዝ ጋር ነው የሚያነጻጽሩት፡፡ በጉብኝቴ ወቅት ለማኝና ሊስትሮ አላየሁም፡፡ ትራፊክ ፖሊስም ያየሁት አንድ ቦታ ብቻ ነው፡፡ አቧራ የሚባል ስለሌለ ይመስለኛል ሊስትሮ የሌለው፡፡ በአንድ ሆቴል ጫማ የሚያጸዳ ማሽን አይቻለሁ፡፡
5.    ከእነሱ ምን እንማር?
የአመለካከት ለውጥ ማምጣትን እንማር እላለሁ፡፡ እርስ በርስ መባላት ሳይሆን ወደ ስራ ማተኮር ግድ ይለናል፡፡ ጠዋት ማታ ሞባይል ስንከፍት ፖለቲካ  ሆነ የምናየው፡፡ ሰው እየታረደ ሌላ ገንቢ ነገር ማየትም መስማትም አልተቻለም፡፡
6.    አሰለጣጠናቸውስ?
የሚገርመው ተማሪ ተኮር ምናምን የሚባል የለም፡፡ መምህር ተኮር ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ሻይ ረፍትም የላቸውም አሉ፡፡ በኛ ጫና ነው የተፈቀደው፡፡ እነሱ የፈለጉትን ብቻ ነው የሚያስተምሩት፡፡ ያሰለቻል፡፡ ትልልቆቹ ፕሮፌሰሮች በአስተርጓሚ ነው የሚያቀርቡት፡፡ ስልጠናው እምበዛም አልተመቸኝም፡፡ ከስልጠናው ይልቅ የተመቸኝ የመስክ ጉብኝቱ ነው፡፡
7.    እኛ ኢትዮጵያውያን ውጪ ሄደን የመኮረጅ አቅማችን ምን ይመስላል?
ብዙም ስላልቆየን ልንኮርጅ አንችልም፡፡ በእርግጥ ለጠቢብ ሰው አንዲት ቃል ትበቃዋለች ይባላል፡፡ ወደዚያ ለመግባት የምናስብ አገር አይደለንም፤ ‹‹ይህ የኔ፣ ያ ያንተ›› እየተባባልን፡፡ ዝንተ ዓለም ብጥብጥ ውስጥ ነን፡፡ ሃምሳ ዓመት ሞላን፡፡ እንደየግለሰቡና እንደየቆይታውም ይለያያል መኮረጅ መቻሉ፡፡  ቻይኖች ብዙም ምስጢር የሚያሳዩ አልመሰለኝም፡፡ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ሆነን ቤተሙከራና ትምህርት አሰጣጣቸውን አላስጎበኙንም፡፡ የተግባር ክንውናቸውን አላሳዩንም፡፡ ፍላጎታቸው እንድናደንቅ ይመስላል፡፡ አሜሪካንን አጣጥፈው ለመሄድ አምስት ዓመት የሚፈጅባቸው አይመስለኝም፡፡ ቴክኖሎጂ በእጃቸው ነው፡፡ የሕዝብ ቁጥር፣ የወታደር ቁጥር ወዘተ፡፡
የእንግሊዝኛ ጋዜጣ የለም፤ ማህበራዊ ሚዲያ ዝግ ነው፡፡ ጋዜጣው በቻይንኛ ነው፡፡ የምናድርበት ውስጥ ያለው የቻይንኛ መጽሐፍ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ስሙ የተጻፈው በቻይንኛ ነው፡፡ እያንዳንዷ ወንዝ በጥንቃቄ ተሰርታ መናፈሻ ነች፡፡ አንዲት ውሃ ጠብ አትልም፡፡ ወንዞችና ሃይቆች በአብዛኛው ሰው ሰራሽ ናቸው፡፡ የከተማውን ውሃ ያጣሩታል፡፡
8.    የአሁኑን ጉዞህን ከኬንያ ጉዞህ ጋር እስኪ አነጻጽርልኝ እስኪ፡፡
ኬኒያ ምንም አላየሁም፡፡ ቻይና ቆይታዬ ሆን ብለው ስለወሰዱን ብዙና አጥጋቢ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ምናምን መኮረጅ እንጂ ማስኮረጅ አይፈልጉም፡፡
አሰልጣኛችን ‹‹አሜሪካ በአንድ ዓመት 47 ቢሊየን ዶላር በስኮላርሽፕ አግኝታለች፡፡ ከእዚህ ውስጥ ብዙው የቻይና ነው፡፡ ስለዚህ ራሳችን ማስተማር አለብን፡፡›› አለ፡፡ እኔም ‹‹ከአሜሪካ ምን ተማራችሁ›› ስለው፡፡ ‹‹እነሱ መች ይታወቃሉ!›› አለ፡፡ ‹‹አሜሪካ ለተማረ ዜጋችን ቅድሚያ ከምንሰጥ ለራሳችን ነው መሆን አለበት፡፡›› ብሎኛል፡፡
ማታ ማታ ከህጻን እስከ ሽማግሌ ውጭ ላይ በቻይና መሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ እየተዝናኑ ስፖርት ይሰራሉ፡፡ በእግር ሽርሽር ያደርጋሉ - በተለይ ሴቶቹ፡፡
ባህላቸውን እንደሚወዱ ያየሁት በቋንቋቸው በመጠቀማቸውና በሞራላቸው ቢሆንም ሃይማኖት ግን የላቸውም፡፡ በአንጻሩ ክርስትና እየገባ ነው፡፡ በራሪ ወረቀት የሚሰጡ አይቻለሁ፡፡ ነገር ግን ቻይኖቹ ምዕራባውያን እንዳይገቡ ሁሉንም ነገር ዘጋግተዋል፡፡  

9.    ምግብና መጠጣቸው እንዴት ነው?
በየቦታው ሙቅ ውሃ ስላለ እየቀዱ መጠጣት ነው፡፡ ጁስ፣ ቀዝቃዛ ውሃ፣ ቡና፣ ሻይ፣ ወተት እንደልብ ነው፡፡
ምግቡም ብዙ ዓይነት አለ፡፡ ቁርስ ላይ በጣም ብዙ አማራጭ አለ፡፡ ብዙ የዩኒቨርሲቲም ሰራተኛ ይበላል፡፡ ምሳና ራት ላይ ለኛ ብቻ ስለሚቀርብ ዓይነቱ ይቀንሳል፡፡
10. ከኢትዮጵያ አንጻርስ?
አንድ ቀን እንኳን ስለ ኢትዮጵያ አያወሩም፡፡ ስለመኖራችንም አያውቁም፡፡ የእንግሊዝኛ ጣቢያቸው ሲጂቲቪ ስለ ኢትዮጵያ አንድ ቀን ብቻ ነው ያቀረበው፡፡ አሜሪካ ሸቀጣሸቀጥ እንዳይገባ ያደረገችውን ነገር ላይ በብዛት ያወራል፡፡
11. አመሰግናለሁ
እኔም ይህን ዕድል ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...