መቶ አለቃ ላቀው ተሰማ
በቅርቡ በአገራችን በአገር በቀል ዕውቀት ላይ ያተኮሩ መጻሕፍት፣ የቴሌቭዥን ዝግጅቶችና ልዩ ልዩ ሁነቶች ስለበዙ በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት፣ ደብረብርሃን፣ ሳምንታዊ የሐሙስ ምሽት (11፡30-1፡00) ውይይት ላይ በተለይም በሳምንቱ ምን አነበባችሁ በሚለው በመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ምዕራፍ ላይ ሃሳቦች ይነሳሉ፡፡ ተሳታፊዎች ያነበቡትን ከስሜታቸው፣ ዕውቀትና ልምዳቸው ጋር እያዋሃዱ ያጋሩናል፡፡ ከማንበብ በዘለለም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ይሰጥ ዘንድ እንግዳ እንዲጋበዝ በተጠየቀው መሰረት መቶ አለቃ ላቀው ተሰማ ተጋበዙ፡፡ ትናንት ሐሙስ 20/08/2014 ዓ.ም ዝግጅቱ ከመጀመሩ ግማሽ ሰዓት ቀድመው ከዕለቱ አዘጋጅ ጋር በቤተመጻሕፍቱ ተገኙ፡፡ እኔም ቤተመጻሕፍቱን የማስጎብኘት ተግባሬን ፈጽሜ ለዕለቱ ዝግጅት የሚጠቅም ወግ ጀማመርን፡፡
ከውይይቱ በፊት ቅድመ-ዝግጅት ማድረጉ የተለመደ ነው፡፡ በእርግጥ የዕለቱ አዘጋጅና እንግዳው ያደረጉ ቢሆንም በጋራ አንዳንድ ነገሮችን ስናነሳሳ ቆየን፡፡ ስለ ንባብ ስንነጋገር በቤተመጻሕፍቱ ውስጥ ከማይነበቡ መጻሕፍት አንደኞቹ የታሪክ መጻሕፍት መሆናቸውን ገለጽኩ፡፡ ይህንንም እንድናርም መቶ አለቃ ላቀው አሳስበውናል፡፡ ይኸውም መጻሕፍቱን በማንበብና ለአባላት የተረዳነውን በማቅረብ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመውናል፡፡ የንባብ ልምዳቸውን፣ የሕይወት ገጠመኞቻቸውንና ጊዜው የፈቀደውን ሲያወጉን ቆይተው የዕለቱ ዝግጅት 1፡30 ላይ ተጀመረ፡፡ እርሳቸውም በሰዓቱ ለሁሉም ተሳታፊ ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ በቤተክህነት፣ በወታደር ቤትና በፖለቲካ ያላቸውን ተሳትፎ ጨምረው ነበር፡፡ ‹‹የኔ ትውልድ አገሪቱን ችግር ውስጥ የከተተም ቢሆን ያዳናትም ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር ቢኖርም በሶማሌ ጦርነት ብዙ ዋጋ ከፍለናል›› ብለውናል፡፡ በነበረው የእንግዳ ክፍለጊዜም ያነሷቸው ነጥቦች ሰፊ ቢሆኑም የተወሰኑትን አንኳር ነጥቦች በማስታወሻዬ ስለያዝኳቸው እነሆ፡፡
ከአሁን በፊት የግእዝ ዕውቀት ያለውና በዘመናዊውም ቴክኖሎጂ በዲግሪ ተመርቆ የሚሰራው ንጋቱ ግርማ በቤተመጻሕፍታችን እንዳቀረበልን ያለ ትምህርት ነው የመቶ አለቃም፡፡ የኢትዮጵያውን ዕውቀት ባላቸው ንባብና ግንዛቤ መጠን ከዉጪው ዓለም ጋር ያስተሳስሩታል፡፡ በአጠቃላይ ስንመዝነው አቀራረባቸው መንፈሳዊ አስተሳሰባቸውንና ያሉበት የንባብ ደረጃ ያሳየናል፡፡ በታሪክ፣ በአገርበቀል ዕውቀትና በኃይማኖት ላይ ያተኮረ ንባብ አላቸው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡
ከእለቱ አዘጋጅ ከፋሲል ገዳሙ የቀረበላቸው የመጀመሪያ ጥያቄ ‹‹ጥበብን እንዴት ያዩታል?›› የሚል ሲሆን፤ እርሳቸውም አባቶቻችን የነበራቸውን ጥበብና ዕውቀት ከብዙ በጥቂቱ አካፍለዋል፡፡ ይኸውም በግዕዝ የተጻፉትንና ልዩ ልዩ ይዘትና አጠቃቀም ያላቸውን መጻሕፍት በመጠቃቀስ ነው፡፡ ኦሪትን፣ የአክሱማውያንን፣ የዛግዌን፣ የመካከለኛውን ዘመን፣ የዘመናችንን የዕውቀትና ጥበብ አካሄድ በተለያዩ አብነቶች አነሳስተዋል፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስም ንጉሥ ዳዊትን፣ ንጉሥ ሰለሞንንና ሌሎችንም ለንግግራቸውና ለምሳሌያቸው ማጠናከሪያ አንስተዋል፡፡
ንጋቱ ግርማ በትምህርቱ አንስቶልን የነበረውንና ከአገራችን ጥበቦች አንዱ የሆነውን መሰወርን ከስሪ ዲ፣ ፎር ዲ፣ …ሰቭን ዲ ጋር አያይዞት ነበር፡፡ እርሳቸውም መሰወርን ጨምሮ ዝናብ ማስቆምንና ማዝነብን አንስተዋል፡፡ በቅርቡ በቴሌቪዥን የሰሙትን ቻይናዎች ጎጃም ለመንገድ ስራ ላይ ዝናብ በአገሬው ባለሙያ እንዳስቆሙና አፄ ኃይለሥላሴ ጃማይካ ላይ ዝናብ የሚዘንብበትን ቀን ከደብተራ ጠይቀው መሄዳቸውን ከሌሎች መሰል አብነቶች ጋር ነገሩን፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ‹‹አባቶቻችን በአንድ ቀን ደብረ ብርሃንም ጎንደርም ይቀድሱ ነበር፤ በደመና በመጓዝ›› ይሉናል፡፡ ይህንንም ሊቃውንቱ ጥበባቸው መንፈሳዊነትና እግዚአብሔርን በመቅረብ የሚያደርጉ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ጥንቆላ በአንጻሩ በደንብ ያልተማሩና የማይመራመሩ የሚያደርጉት መሆኑን ጨምረዋል፡፡
‹‹እየሩሳሌም በአጋንንት ተገነባች፡፡ ለሰለሞን ነው አጋንንት የተሰጡት›› የሚለውን ጨምሮ የምሳሌዎቻቸው ማዳበሪያዎች ለእኔ አዳዲስ ነበሩ፡፡
የዕለቱ አዘጋጅ ለጠየቃቸው በርካታ ጥያቄዎች መልሶችን በአጥጋቢ ሁኔታ የመለሱት መቶ አለቃ ከተሳታፊዎችም ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልሶችን ሰጥተዋል፡፡ ከሁሉም ያነጋገረውና ቤቱን በአንድ እግሩ ያቆመው ከአንዲት ተሳታፊ የመጣው ጥያቄ ነበር፡፡ ይህችም ለመጀመሪያ ጊዜ በግብዣ የመጣች ልጅ ራሷን ስትገልጽ አባቷ ጥበቡን የሚያውቁ እንደነበሩና እሷ ሳትወለድ አባቷ ለእናቷ ‹‹የሚወለደው ልጅ ወንድ ከሆነ ምንም ችግር አይኖርብንም፤ ሴት ከሆነች ግን አንቺ እንደወተለደች፣ እኔ ደግሞ ከስድስት ወር በኋላ እንሞታለን›› ብለው ለእናትዮዋ መናገራቸውን ነገረችን፡፡ ቃላቸውም እውን ሆኖ ሁለቱም ወላጆቿ ከተወለደች በኋላ መሞተቸውን ገለጸች፡፡ እርሷም አገር ጥላ መሄዷን፣ አባቷ ያወጡላትን ስም መቀየሯን፣ የሕይወት ፈተናዋን ምክንያት ለማወቅ መጽሐፋቸውን ጭምር በማንበብ መጣጣሯን ተናግራ መፍትሔ ጠየቀች፡፡ አሳዘነችን! መቶ አለቃም ስለ ጉዳዩ ሲያስረዱ ይህን ዓይነት ነገር እንደሚከሰት ገልጸው አንዳንዴ በቤተሰቡ ላይ የሚመጣን መጥፎ ነገር ለማስቀረት ጽንስ እስከማቋረጥ ይደረሳል አሉ፡፡ ‹‹አባትሽ ያወጡልሽን ስም ተጠቀሚበት፤ አባትሽ ላንቺ ሲሉ ከባድ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ መመራመርና ማንበብም ከባድ ነው፤ አነበብኩ ያልሽው ፍትሐነገሥቱን ነው›› ብለው ሃሳብ ሰጧት፡፡ ካስፈለገ አባቷን አስነስቶ ማናገር እንደሚቻል ጠቅሰው ሙትን ረፍት መንሳት ስለማያሻ ይህን አንሄድበትም ብለዋል፡፡ አባቶቻችን መጥፎ ትውልድ ስለሚመጣ ለመጥፎ እንዳይጠቀመው ከመጻሕፍቴ ጋር ቅበሩኝ ይላሉም ብለውናል፡፡ የእሷም አባት ውሳኔ ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ መላምት አእርሳቸውም ሆነ ከአባላት ተነሣ! መጯጯህም ሆነ! ከብዙ ምልልስም በኋላ የቤተመጻሕፍቱ አባላት ይህን ትምህርት ለመማር ስለሚፈልጉ እንዲያግዟቸው ሲጠይቋቸውም ‹‹ምስጢሩ ጥልቅ ነው፤ ያለ ግእዝ ዕውቀት የሚሆን ነገር የለም፡፡ ከሦስቱ ‹ሀ› የቱን እንደምትጠቀሙ ካላወቃችሁ አይሰራም…›› ብለው የጉዳዩን ክብደት አስረድተዋል፡፡ በዚህም ብዙ ማጉረምረም ተከተለ፡፡ ‹‹የካቲት ጥሩ ወር ነው፡፡ አባቶቻችን በየካቲት አድዋ የቀናቸው ለዚያ ነው፡፡ ሰው እንደስሙ ይሆናል፡፡ ስንድር ስም እናያለን፡፡ ጥበቡ ሰፊ ስለሆነ ….›› ነገርን ነገር እያነሣው ብዙ አወጉ፡፡
ጥበብ፣ ጥንቆላ፣ አስማት፣ እርኩስ መንፈስ እያለ ከሚሄደው ወግ ወጣ ያለ ሃሳብ ያስተናገድነው በኔ ጥያቄዎች መሰረት ነው፡፡ እኔም የታሪክ አዋቂው ከመጡ አይቀር ዕድሉን ልጠቀም ብዬ ሦስት ጥያቄዎችን ጠየቅሁ፡፡ ከእነሱም አንዱ ክርስቲያናዊ ስላልሆነው የብሔረሰብ ጥበብ ምን ያስባሉ የሚል ሲሆን በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ አፄ ኃይለሥላሴ ጫምሲቱ ከሚባሉት የዝናብ ማስቆም ችሎታ ካላቸው ባለሙያዎች አንዱን ጋብዘው መጠቀማቸውን አነሳሁ፡፡ እርሳቸውም ይህንን አምነው ሐረርም ዝናብ ሲጠፋ ሴቶቹ እርጥብ ቅጠል ተሸክመው ከተማውን ሲዞሩ እንደሚዘንብ ገልጸውልናል፡፡ እንዳዩት በአመዛኙ የብሔረሰብ ጥበብ በቅጠላቅጠል መሆኑን ነገሩን፡፡ ሌላው ጥያቄ ስለተጉለት ነበር፡፡ እርሳቸውም የተጉለትን የሺዎች ዓመታት ታሪክ፣ እንዲሁም ከአፋር ጋር ስለሚዋሰን በቅድመታሪክም ያለውን ቦታ አስረድተውናል፡፡ ተጉለትን ስናነብ ግን ‹ጉ›ን አጥብቀን መሆን እንዳለበት አስረድተውናል፡፡ እንደዚያ ሲነበብም ትርጉሙ ላገሩ እድገት ተጣጣሩለት እንደሚሆን ነግረውናል፡፡ በራስ አበበ አረጋይ ስም ቤተመጻሕፍቱን መሰየሜንም ከተጉለት ጋር አያይዘውታል፡፡
እንደ ከተማው ነዋሪነታቸው የደብረብርሃንን ያለፉትን የሃያ ዓመታት ለውጥና የወደፊት ዕጣፈንታ በእርሳቸው ዕይታ እንዲነግሩንም ጠይቄ ነበር፡፡ ‹‹ደብረብርሃን አቀማመጧ ስለፈቀደላት ነው እዚህ የደረሰችው፡፡ ከዚህ የበለጠ ታድጋለች፡፡ ከአዲስ አበባም ትበልጣለች፡፡ አሁን ዘርዓያዕቆብ ቢመጡ አያውቋትም፡፡ በእናንተ ዕድሜ አንደኛ መዲና ቢቀር ሁለተኛ ትሆናለች፡፡ ከስምጥሸለቆና ከጂቡቲ ጋር ያላት ቅርበት፣ የአማራ ህዝብ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ያለው ትስስርና በብዝሃነት ደረጃ የኢትዮጵያ መገለጫ መሆኗ ልዩ ያደርጋታል፡፡ በአዲስ አበባ የተፈጠረውን ትንግርት ማረጋጊያ ትሆናለች፡፡ ሙስሊሞችና ልዩ ልዩ ኃይማኖቶች መኖራቸውም የከተማዋን ህዝብ ስብጥር የሚያሳይና ለእድገቷ የሚጠቅም ነው፡፡›› ብለውናል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ በጥሩ ሁኔታ እያደገች አይደለም፡፡ አንድ ፎቅ ወደ ላይ እየወጣ ሌላው ታች ነው፡፡ ይህንን በብዙ ስብሰባዎች ተናግረናል፡፡ ሙስናው አፍኖ ይዟታል፡፡ እዚያ ላይ ምን ይሰራ የሚለው ያወያያል፡፡›› ሲሉም ጨምረውበታል፡፡
እኔ በግሌ ካሁን በፊት በተወሰነ መጠን ስለ መናፍስት መኖር በዩቱብ ቪዲዮ ‹‹ጎስት ሃውንቲንግ›› ላይ በቪዲዮ የሚታዩ መናፍስትንና የማናገር ጥበቦችን አይቼ ነበር፡፡ መቶ አለቃ ይህንን ፈረንጆች ከእኛ እንደወሰዱ ያላቸውን እምነት ሲነግሩን ጉዳዩ ምርምርና ፍተሻ የሚያሻው መሆኑ ታይቶኛል፡፡
በመጨረሻም ለቤተመጻሕፍቱ አባላት ምስጋናና ምክር ሲለግሱ ከመቀመጫቸው ተነስተው ነበር፡፡ ስናነብ እንዳንመርጥ፣ ተሰባስበን መወያየታችን የሚደነቅ መሆኑን፣ ወደፊትም እንደሚመጡና እንደሚሳተፉ በመናገር የዕለሩ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ጻፍኩ እንጂ ያወጉት ብዙና ጥልቅ ነው፡፡