2022 ኤፕሪል 22, ዓርብ

ከተጉለት ቅንጅቶች ግንባር ቀደሙ - ጋሼ ወርቁ ወልደሚካኤል

 

በመዘምር ግርማ



በ1980ዎቹ ሳሲት ከተማ ስናድግ ከምናያቸው የቀድሞ ጦር አባላት አንዱ ነው፡፡ ሌሎች የቀድሞ ጦር አባላት እንዳገሩ ዘይቤ የሚወዱትን ሰው ‹‹አንቺ›› እያሉ በቁልምጫ ስለሚጠሩ እሱም በዚህ መልኩ ከሚጠሩ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ከወታደሮቹ ዉጪ ያሉትም እንዲሁ ይህንን ልማድ አስቀጥለው አንቺ እያሉ ይጠሩታል፡፡ እሱም አቤት ወዴት ሲል አውቀዋለሁ፡፡ ስለሱ ያለኝ የልጅነት ትውስታ በጣም ውሱን ነው ለማለት እችላለሁ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ጎረቤታችን ቢሆንም ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀይሮ ሄዷል፡፡ የቀድሞ ጦር አባላት ለሃገራቸው እንዳልደሙና እንዳልተጉ ቤት እንኳን የላቸውም፡፡ በቤት መስሪያ ዕድሜያቸው ያገለገሏት አገራቸው በነጻ አውጪ ወይም በአዲስ መንግስት እጅ ገብታ ፊት ስለነሳቻቸውና ማናቸውም የሃብት ምንጭ ከእነርሱ እንዲርቅ በስርዓት ስለተዘጋ ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ ሳሲት ከተማ ላይ መጠነኛ በሆነ የኑሮ ደረጃ ይኖራሉ፡፡

አንድ ቀን የሚያስቀናኝን ነገር ይዞ አየሁትና ተጠጋሁት፡፡ ያው እኔ ተማሪ ስለሆንኩ ያለችኝ ትንሽና አንድ ሰው  ብቻ የምታሰማ ሬዲዮ ናት፡፡ እሱ ግን ይዞ ያየሁት ሬዲዮ እስካሁን አላየሁትም፡፡ ምናልባት የጦርሜዳ መገናኛ ቢስተካከለው ነው፡፡ አንቴናው በጣም ረጅም ሲሆን ሬዲዮኑም ትልቅ ነው፡፡ እነሽርቦ ለድግስ ሄጄ አጎቴ አባይነህ ሠረቀ ጋ ያየሁት የጃንሆይ ጊዜ ሬዲዮ እንኳን አይስተካከለውም፡፡ ያንን አንጀት አርስ ሬዲዮ የወደድኩት ከሦስት ሜትር የሚረዝመው አንቴናው ሾርት ዌቭ የሬዲዮ ሞገድን ያለምንም ሻሻታና ሲርሲርታ በጥራት በማሰማቱ ነው፡፡ እናም ብዙ ቀን ከምሽቱ 11፡00 ሲቃረብ እሱ ደጅ ሄጄ እሰየማለሁ፡፡ ዝግጅቱ ለ11፡00 አምስት ጉዳይ ሲሆን በደወል ይጀምራል፡፡ አምስት ደቂቃ የዕለቱን ዜና ስንገምትና ያለፈውን ቀን ወሬ ስንተነትን እንቆያለን፡፡ ወቅቱ ህብረተሰቡ ከኢህአዴግና ከቅንጅት ወገን ሚናውን እየለየ የነበረበትና ቅንጅት መሆንን በግልጽ መናገር በቀበሌና በመንግስት ሰዎች ለግልምጫ የሚዳርግበት ጊዜ ነበር፡፡ ከሰኔ መጨረሻ 1997 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት አጋማሽ 1998 ዓ.ም. ያለው ጊዜ ነው፡፡ በጋዜጠኛ አማኑኤል በረከት አዋጅ የሚጀምረው የዶቼቨሌ ወይም የጀርመን ድምጽ ዝግጅት ዜናን ያስቀድማል፤ የሬዲዮ መጽሔት በብዛት በድምጸ-ነጎድጓዱ ጋዜጠኛ ነጋሽ መሃመድ ይከተላል፤ ስፓርቱ፣ የሳይንስ ዝግጅቱ፣ እንደየዕለት ተራው ይቀርባል፡፡ ለማድመጥ ከሚመጡ የቀድሞ ወታደሮች፣ አገር ወዳዶችና የቅንጅት ደጋፊዎች በየዜናው መካከል የሚቀርበው ትንታኔ ልዩ ነው፡፡ ከፖለቲካ ዉጪ ያለ ዝግጅትም ሲሆን የኤርትራ የውትድርና ትውስታና ሌሎችም ወጎች ይመጣሉ፡፡ 11፡50 ላይ ዝግጅቱ ሲያበቃ ትንሣኤ ኢትዮጵያ የአንድነት ድምጽ ራድዮ ከዋሽንግተን ዲሲ ስለሚለቀቅ ለማውራት ያለን የአስር ደቂቃ ጊዜ ነው፡፡ የትንሣኤ ሬዲዮን ሳደምጥ ምንድነው የሚለኝ ሰው አለ፤ ወይም ደግሞ ለማድመጥ የሚፈልግም አይጠፋም፡፡ ስለሆነም ከራሴ ሬዲዮ ሳደምጥ በተወሰነ መልኩ የጆሮጠቢ ሰለባ ላለመሆን ስለምሰጋ በዚያው በትልቁ ሬዲዮ በቡድን ማድመጥን እመርጣለሁ፡፡ ሳሲት ላይ ኢህአዴግ በጣት የሚቆጠር ድምጽ ቢያገኝም ከመንግስት የአፈና እርምጃ በኋላ ከተንሰራፋው የፍርሃት ቆፈን አንጻር የቅንጅት ደጋፊው በተገላቢጦሽ በጣት የሚቆጠር ሆኗል፡፡

እናም ጋሼ ወርቁ ወልደሚካኤል በሬዲዮው ዜና ሲያስደምጠኝ ቆይቶ ቤት ቀየረ፡፡ የቀየረው ደግሞ ከከተማው ዳርቻ ወዳለ የኪራይ ቤት ነው፡፡ እንደኔ ሃሳብ ይህ ቤት አንደኛ ለሚሰራው የልኳንዳ ስራ አያመችም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ለኢህአዴግ ካድሮዎች ዛቻና ጥቃት ሊዳርገው ይችላል፡፡ አንድ ሁለት ቀን እዚያ ቤት ሄደን አውርተናል፡፡ አረቄ ይዘን ስናወራ አንድ ቀን ካስጨበጠኝ ነጥቦች አንዱ አይረሳኝም፡፡ ምናልባትም ኢህአዴግ እያደረገ የነበረውን አፈና ከቀጠለና የቅንጅትን አመራሮች ካሰረ የበታቹን ደጋፊም ያጠቃል በሚል ስጋት ያንን ፎቶ ኮፒ ተደርጎ የተቀመጠ ወረቀት ለማስወገድ ወይም ለመደበቅ አስቧል፡፡ ወረቀቱ የሕወሃትን ሰማኒያ ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች ስም ዝርዝር የያዘና ከቅንጅት የተላከ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት በምርጫና በዲሞክራሲ ህወሃትን መጣልና ነጻነትን መጎናጸፍ እንደማይቻል የተገነዘበው ጋሼ ወርቁ የተማርነው ወጣቶች የካርታ ንባብ እንድንማር አበክሮ ያሳስበን ነበር፡፡ ይህም ጦርነት አይቀሬ መሆኑን በመገንዘቡ ነበር፡፡ በወቅቱ በነበረው ትንታኔ መሰረት በሳሲት ምርጫ ጣቢያ የምርጫ ማጭበርበር ሙከራ መኖሩከህዝቡ ጋር በመሆን ለማክሸፍ መቻሉን በዝርዝር እርሱም የተሳተፈበትን የታዛቢነት ሚና በመግለጽ ነግሮኛል፡፡ በወረዳው ሦስት ሰዎች ከምርጫው በኋላ በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ሲሞቱ ጋሼ ወርቁ ግለሰቦቹ የነበራቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ በማስረዳት ግድያው በረቂቅ መንገድ የተካሄደና ፖለቲካዊ መሆኑን ነግሮኛል፡፡ከወረዳው ዉጪ የመጡና በምሽት የሚንቀሳቀሱ የፌደራል ወይም የሌላ ፖሊስ አካላት መኖራቸውን ከሌላ ምንጭም ሰምቻለሁ፡፡ ጫካ ወስደው አስፈራርተውኛል ያለኝም አለ፡፡ ሦስት የቅንጅት ቀስቃሾችን ታጣቂና ፖሊስ ወደ ወረዳው ከተማ ሰላድንጋይ ከየቤታቸው ሲወስዳቸው አይቼ በሃዘኔታ ስናገር የሰሙኝ የአንደኛው ዘመድ ሳይሆኑ የቀሩ ሰው ‹‹አርፎ አይቀመጥም ነበር!›› በማለት አበሳጭተውኛል፡፡ ያ የቅንጅት ቀኝ እጅ የነበረ ወረዳ በአዋጅና ማስፈራሪያ እንዲሁም እስር ጋጋታ ተመልሶ ሰጥ ለጥ ብሎ ለመገዛት ጫንቃውን አዘጋጀ፡፡ ጋሼ ወርቁን ለጥቂት ደቂቃዎች ሳገኘው ወሳኝ ነጥቦችን አጋርቶኝ ያልፋል፡፡ አንድ ቀን ጥቅምት 1998 ዓ.ም. ይመስለኛል አግኝቶኝ አንድ ጥያቄ ጠየቀኝ ‹‹መዘምር፣ በአሁኑ ሰዓት ለኢህአዴግ በጣም እየሰራ ያለው ማነው›› አለኝ፡፡ እኔም ከመለስ እስከ በረከት፣ ከህላዌ እስከ ጁኔዲ ጠራሁለት፡፡ ‹‹አይደለም! ሚሚ ስብሃቱ ነች!›› አለኝ፡፡ ኢህአዴግ የተቃውሞ ጎራውን ደቁሶ አመራሩን ካሰረ በኋላ የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ በሚል ለምትሳለቀው የቀድሞ የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኛ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የአየር ሰዓት ሰጥቷት ትደመጥ ስለነበር ነው ጋሼ ወርቁ ይህን ማለቱ፡፡ የፖለቲካው ሂደት እንደሚታወቀው እየተበላሸና ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ ስለሄደ ሁላችንም ዝም አልን! ጋሼ ወርቁንም ሳገኘው ከሰላምታ በቀር ፖለቲካ አናወራም፡፡ በቁርጥ ቀን ግን የአገሩ ቀኝ እጅ ሆኖ ስላገኘሁት አከብረዋለሁ፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ አንድ ቀን አገር ቤት ሄጄ ከቤተሰብ ጋር ቡና ተፈልቶ ስናወራ ‹‹ጋሼ ወርቁ የሞተ ዕለት›› ሲሉ ሰማሁና ድንግጥ አልኩ፡፡ በጣምም አዘንኩ፡፡ ለቅሶውን ባለመስማቴ ተናደድኩ፡፡ ኤርትራ ሆኖ እናቱ ሰላድንጋይ ድረስ በእግራቸው ወጥተው ስልክ ደውለው እንደሚያገኙት የነገረኝ፤ ሳይረዳቸው ህይወታቸው በማለፉ የሚሰማውን ሃዘን የሚገልጽልኝ፣ በቤት ኪራይ ተንከራቶ መኖሩ፣ ለአገሩ ያለው ቀናኢነት፣የመካኒክነት ዕውቀቱና በዚያም ሰውን ለማገልገል ያለው ቀናነት ሌላም ብዙ ብዙ አስታውሼ አዘንኩ! ለአካባቢያችን እንዲሁም ለአገራችን በተለያዩ ጊዜያት በችግሯ የቆሙላት፣ የሚመጣውን አደጋ የጠቆሟት፣ ነቅተው ያነቁ አርቆ አሳቢዎች ነበሩ፡፡ ጋሼ ወርቁም ከእነርሱ አንዱ ነው፡፡ አሁን ላይ ሆነን የእነዚህ ወገኖች ማስጠንቀቂያ ገብቶን ይሆን?ከልብ የማከብረውና በጀግንነቱ የማደንቀው ወንድሜ ጋሼ ወርቁ ወልደሚካኤል ዛሬ ትዝ ብሎኝ ይህንን ማስታወሻ ስለጻፍኩ በጣም ደስተኛ ነኝ!       

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...