ቅዳሜ 16 ኤፕሪል 2022

አፍሪካን ጨርሼ ሳላይ ሌላ አላይም ብዬ …

 


አፍሪካን ጨርሼ ሳላይ ሌላ አላይም ብዬ …

መዘምር ግርማ

ሚያዝያ 7 2014 .

ደብረ ብርሃን

 

በዚህ ጽሑፍ ሰሞኑን ስላደረኩት ጉዞ፣ ስለ ዋናና ንዑሳን ዓላማዎቹ፣ እንዲሁም ስለምልከታዎቼ መጠነኛ ሃሳብ አጋራችኋለሁ፡፡ የዉጪ ዕድልን ለመማር ወይም ለመኖር ስል ሞክሬው አላውቅም፡፡ እንዲያው ሃሳቡም አልመጣልኝም፡፡ ድንገተኛ የሆኑ ዕድሎች ናቸው ዉጪ እንድሄድ ያደረጉኝ፡፡ ተመጋጋቢ የበጎ ፈቃድ ስራዎች 2017 ወደ ጆንስበርግ፣ 2019 ወደ አክራ ወስደውኝ ሲያበቁ፣ በኮቪድ ምክንያት የጉዞ ዕድል ጠፍቶና ሲሰረዝ ከርሞ እነሆ 2022 ተመልሶ የጆሃስበርግ ዕድል መጣ፡፡ 

‹‹ዘወትር ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ለአንድ ሰዓት ያህል የሚገናኝና የተወሰነ ጊዜህን የሚፈልግ የልጆች ጨዋታዎች የምርምር ቡድን አለ፤ ለመሳተፍ ከፈለግህ ግባ›› ያለችኝ ዶርካስ ነበረች፡፡ እሺ ብዬ ገባሁ፡፡ እሷንስ ማን አስተዋወቀህ ለሚል ቤንጃሚን እላለሁ፡፡ ቤንጃሚንንስ ለሚል የበጎፈቃድ ስራ ፍላጎት እያለ ይሄዳል፡፡ ዝርዝሩ በ‹‹ብዕረኛው የሞጃ ልጅ›› አለ፡፡

የምርምር ቡድኑ በኮቪድ የተቋረጠ ስራውን ለመቀጠል ስለቻለ ሳምንታዊ ስብሰባችንን እያደረግን፣ በየግል የሚሰጠንን የንባብና የጽሑፍ ስራ እየሰራን ቆየን፡፡ በአካል ለመገናኘት ደግሞ በዚህ ወር ዕቅድ ተያዘ፡፡ ይህንንም በማሰብ ኦንላይን ቪዛ ለማግኘት ከሚችሉት 14 አገራት አንዷ ዜጋ ስለሆንኩ ኦንላይን ለሁለት ሳምንት ስሞክር አልሰራ ስላለኝ ወደ ደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ አዲስ አበባ ተጉዤ ቪዛ ጠየቅሁ፡፡ የቪዛ ክፍያው ከበፊቱ 2000 ብር ወደ 1000 ብር ቀንሷል፡፡ ጥሩ አድርገዋል፡፡      

ቪዛ ይሰጠኝ አይሰጠኝ ስጠራጠር ከርሜ መድረሱ በስልክ ተነገረኝ፡፡ ይህንንም ስሰማ ለጉዞ ስሄድ እግረመንገዴን እንደምወስድ ነርኳቸው፡፡ በዚህም መሰረት አርብ ዕለት ማለዳ ወደ አዲስ አበባ ሄጄ የኮቪድ 19 ምርመራ ካደረግሁ በኋላ ወደ ብስራተገብርኤል ሄጄ ፓስፖርቴን ወሰድኩ፡፡ በታክሲ ስመለስ አጋዝያን ቁጥር አንድ ትምህርት ቤት ስሙ መቀየሩን አየሁ፡፡ አይ ታሪክ!  ወዲያውኑ ወደ ብሔራዊ ባንክ ሄጄ የዉጪ ምንዛሬ ስጠይቅ የሚፈቀድልኝ 100 ዶላር መሆኑን ገልጸው በፓስፖርቴ ላይ ጻፉ፡፡ የታክሲ የማይሆን ገንዘብ መውሰድ አሳፋሪ ነው ብዬ ተዉት ብያቸው ወጣሁ፡፡ በማግስቱ ቅዳሜ ረፋድ የኮቪድ ምርመራ ውጤቴ ኔጌቲቭ መሆኑ በስልክ የጽሑፍ መልዕክት ደረሰኝ፡፡ ፖዘቲቭ ቢሆን ጉዞው ይታጎል ነበር፡፡ ወደ ቦሌ መድኃኔዓለም ሄጄ ከፒሲኤል የምርመራ ማዕከል የኮቪድ ውጤቴን ተረከብኩ፡፡ ቦታው ለአየር ማረፊያው ቅርብ ስለሆነ ግራንድ በተባለ የእንግዳ ማረፊያ አልጋ ያዝኩ፡፡ በማግስቱ እሁድ ማለዳም ራይድ ጠርቼ ወደ አየር ማረፊያ ሄጄ ቼክ ኢን አደረግሁ፡፡ ኦንላይን ቼክ ኢን ማድረግ ወንበርም ለማማረጥ እንደሚረዳ ባውቅ አላደረኩም ነበር፡፡ የያዝኳት አንድ ትንሽ ቦርሳ ስለነበረች ብዙም ጊዜ አልፈጀሁም፡፡

በጉዞ ላይ አንድ የአፍሪካ ፊልም አየሁ፡፡ አንዲት ወጣት አንድን ባለሃብት ቀርባ የምታማልልበት ወይም የምታጠምድበትን ሁኔታ ያሳያል፡፡ የሚያገኛቸውን ያላገቡ ወንዶች‹‹ኋላ እንዳትታለሉ፤ ተጠንቀቁ፤ መርጣችሁ አግቡ›› እያለ የሚመክር የኛ እኩያ የሆነ ልጅ ያለው ሰው ትዝ አለኝ፡፡ ወገኖቼ፣ ከስራ ሁሉ ከሩቁ ሲያዩት አማላይ፣ ሲቀርቡት ግን ገዳይ አየሁ አውሮፕላኑ ውስጥ፡፡ የበረራ አስተናጋጅነት ስራ ነው፡፡ ሆስተሶች የሚባሉት እህቶቻችን የሚሰሩት ስራ ብዛት፣ የሚያዩት ጠባይ ዓይነት፣ የሚገፉትና የሚሸከሙት ዕቃ ክብደትና ብዛት! ያንን ሁሉ የመንገደኛ ሻንጣ ከመቀመጫዎቹ በላይ ያለው ቦታ ክፍቱን ሲሆን ገፍቶ መዝጋት ከባድ ነው፡፡ አደንቃቸዋለሁ! ይህን ሁሉ የስራ ሁኔታ ሳይ በኬኒያ ኤርዌይስ ስሄድ ያየሁት አንድ ረጅምና ጡንቻማ የበረራ አስተናጋጅ ዓይነቱ ነው ለዚህ ስራ መሆን ያለበት አልኩ፡፡ ተሳፋሪን በቆንጆ ሴት ለማማለል ካላሰቡ በቀር፡፡

ጆሃንስበርግ ደርሼ ከሆቴል የተላከውን ሹፌር ጥበቃ ተያያዝኩ፡፡ ሁለት መንገደኛ የሚጠብቁ ኢትዮጵያውያንን አግኝቼ አውሮፕላን ማረፊያው በተሰየመለት ኦሊቨር ታምቦ ሃውልት ስር ፎቶ አነሱኝ፡፡ በቅርብ ርቀት ሳዳምጣቸው የሚያወሩት ስለ አማራ ህዝብ በፖለቲካ ጫና መጎዳት ነው፡፡ በ1950ዎቹ ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት ወደ ቤሩት ሲሄዱ በካይሮ አየር ማረፊያ በግብጽ መንግስት የሚደገፉ የኦነግ አመራሮችን ያገኙት ደጃዝማች ወልደሰማያት ገብረወልድ ሰዎቹን በኦሮምኛ አናግረው ሁኔታውን የተረዱበት መንገድ ትዝ አለኝ፡፡ በዘመናት መካከል ኢትዮጵያዊ በዉጪም ሆኖ አገሩን አይረሳም፡፡ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ ሆኜ የኢትዮጵያንና የደቡብ አፍሪካን የአየር ሁኔታ መለያየት ገምቼ ወይም የአየሩን ሁኔታ ከጉግል አይቼ ተስማሚ ልብስ አለመያዜ ራሴን እንድታዘበው አደረገኝ፡፡ አንዲት ጃኬት ባልይዝ በዚህ ክረምት አልቆልኝ ነበር፡፡     

ሹፌሩና አብራው የምትሰራው ሰው መጡ፡፡ ሁለቱም ነጮች ናቸው፡፡ እንግዳ ማረፊያው ጋ እስክንደርስ ብዙ ነገር አወሩልኝ፡፡ እኔም ስለ አገሬ ነገርኳቸው፡፡ በደቡብ አፍሪካ 8 በመቶ ህዝብ ብቻ ግብር ከፋይ መሆኑን፣ 53 በመቶ ስራ ፈት በመሆኑ ወንጀል መበራከቱን፣ በኮቪድ እረፍት ጊዜ ህዝቡ የባቡር ሃዲዱን አፍርሶ እንደሸጠው፣ ባቡሮቹ የሚጠቀሙበትን የመዳብ ሽቦም እንደወሰዱት፣ ይባስ ብለው ባቡሮቹን መኖሪያ እንዳደረጓቸው፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርት በነጻ ይሁንልን ብለው የዩኒቨርሰቲውን ምክትል ቻንስለር ማገታቸውን ወዘተ ነግረው እኔም በቆይታዬ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዳደርግ መከሩኝ፡፡ በዌጅውድ የእንግዳ ማረፊያ ደርሼ የተቀበለኝ ጄክስ ግዙፍ ፈረንጅ ነው፡፡ ከአሁን በፊት በቪሌጅ ግሪን ያገኘኋቸው ሰዎች ያሉትን እንግሊዝኛ ቀየር አድርጎ ነገረኝ፡፡ ‹‹I own this place.›› የሚለውን በ ‹‹I am the owner.›› ተክቶ፡፡ ያኔ ያልኩት ይህችን ነገር አዲ አበባ ላይ አትላትም፤  አጼ ምኒልክም ሆኑ ራስ አበበ አረጋይ ፈረንጅ የኢትዮጵያን መሬት የኔ ነው እንዳይል ሰርተዋል፡፡ አሁን ግን የደቡብ አፍሪካን ነገር መመርመር እንደሚገባኝ ገባኝ፡፡     

አዲስ አበባ ላይ 100 ዶላር አልቀበልም ያልኩት አገሬን በመቀየሜ ይሁን፣ ስርዓቱን በመታዘቤ፣ ወይም እንደ ሊጋባው በየነ ‹‹ጠጅ ጠጣ ሲሉት ዉኃ እየለመነ…›› አላውቅም፡፡ የጉዞው ወጪዎች በጠሪዎቼ ተሸፍነዋል፡፡ እንደበፊቱ ጉዞዬ ሁሉ የታክሲውን ሳይቀር እንዲሸፍኑ ጠይቄያለሁ፡፡ ይህም ለወጪ ብቻ ሳይሆን ለደህንነትም ጥሩ ነው፡፡ አንድ ነገር መግዛት ብፈልግ፣ ገንዘብ ለሆነ በአዘጋጆቹ ለማይሸፈንና ዕቅድ ላልተያዘለት ነገር ቢያስፈልገኝ ኢትዮጵያን እያማረርኩ ዝም ማለት ብቻ ነው አማራጬ፡፡ ለ2017ቱ ጉዞዬ 200 ዶላር የሰጠኝ ብሔራዊ ባንክ ያንን ነፈገኝ፡፡ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2019 500 ዶላር ስለሰጠኝ ደግሞ ለመሄድ አፈርኩ፡፡ የአንድ ባንክ ደብረብርሃን ቅርንጫፍ ለዋና መስሪያ ቤት እንዲጽፍልኝ ጠይቄው ‹‹ልትሸጠውስ ቢሆን›› ብሎኝ ስለነበር ደግሜ አልሄድኩም፡፡ ከኢትዮጵያ ስወጣ አንዲትም ዶላር አላያዝኩም ነበር፡፡ በዚህም አድራጎት ከጥቂቶች ሳልመደብ አልቀርም፡፡

ፒተርን አገኘሁት፡፡ የማላዊ ተወካይ ነው፡፡ በአፍሪካ ቤተመጻሕፍት በጋና ያገኘሁትንና ለአንድ ሳምንት አብሮኝ የቆየውን ባብዙ ልምድ የቤተመጻሕፍት ዳይሬክተር ግሬይ ኒያሊን አስታወሰኝ፡፡ ፒተር ራስታ ነው፡፡ እውነተኛ ስሙ ኮንድዋኒ ነው፡፡ ‹‹በአፍሪካ ስም ክርስትና ስለማያነሱ ፒተር ክርስትና ስሜ ነው›› አለን፡፡ ‹‹ለአውሮፓዊም እንዲቀል ብዬ እጠቀመዋለሁ›› ሲል አከለበት፡፡ ፒተር በአገሩ በማላዊ አጼ ኃይለሥላሴ ስለጎበኙትና እስካሁን በስማቸው ተሰይሞ ስለሚጎበኘው የዞምባ ተራራን ጉዳይም ነገረኝ፡፡

በዚህ ስብሰባ በእኔ እንግሊዝኛ ያልተወዛገበ፣ በስሜ እንግዳነት ያልተቸገረ የለም ለማለት እችላለሁ፡፡ እኔም እንደፒተር የአውሮፓ ስም ሳያስፈልገኝ አይቀርም፡፡ ያማረ እንግሊዝኛ መናገር ግን የግዕዝን ስም ወደ አውሮፓዊ ስም እንደመቀየር አይቀልም፡፡ እንግሊዝኛዬን ሳስበው ያ በአጭሮች ሰፈር ረጅም የሚባለውና ረጅሞች ሰፈር ሲሄድ አጭር መሆኑን የተገነዘበው ልጅ ትዝ አለኝ፡፡

እሁድ ማምሻና ማታ የዝግጅቱ አስተባባሪ ፕሮፌሰርና ባለቤቷ ወደ እንግዳ ማረፊያው መጥተው እኔንና ፒተርን ወደ መሃል ከተማ ወስደውን ዙሪያ ገባውን ለረጅም ሰዓት በመኪና እያዞሩ አስጎበኙን፤ ጋበዙን፡፡ የከተማው ህዝብ ስብጥር፣ የመዝናኛ ቦታዎች ይዞታና ስያሜ ዓይነት፣ ሐይቆችን፣ ድልድዮችን፣ … ከተማዋ የዓለም ህዝብ ተሰባጥሮ የሚኖርባት ነች ለማለት ያስደፍራል፡፡ በዚህ ጉዞ የተገለጠልኝ ነገር ቢኖር የደቡብ አፍሪካ ነገር ሰፊ ምልከታ የሚያስፈልገው እንጂ የነጭ ቅኝ-ገዢ ሰፋሪ ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ ለመቶዎች ዓመታት ዝርያዎቻቸው በሰላምም በጦርነትም የኖሩ ነጮች ከጥቁሮች ጋር ልዩ መስተጋብር የሚያሳዩባት አገር ነች፡፡   

ጠዋት በሚያማምሩና በዛፍ በተሸፈኑ ሰፈሮች መካከል እያለፍን ወደ ስብሰባ ስንሄድ በየደጁ ወደየቤቱ መቅረብ የጥይት ሲሳይ እንደሚያደርግ የሚያሳዩ ማስታወቂያዎች አየን፡፡ ‹‹Armed response›› የሚለው ማስታወቂያ ሰውዬው በቤቱ በሌለ ጊዜ የሚከፍተው መሆኑንና ሰው ሲጠጋና አላርሙ ሲጮህ የግል ጥበቃ  ድርጅቶች ከአራት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ እንደሚደርሱ ጄክስ ነገረኝ፡፡ የወር ደሞዜ አንድ መቶ የአሜሪካን ዶላር ገደማ መሆኑን ለፒተርና ለእንግዳ ማረፊያው ባለቤት ለጄክስ ነግሬያቸው አብቃቅቼ በመኖሬ ተደንቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመንግስት ሰራተኞች ከከፍተኛ ተከፋዮች መመደቤን ስጨምርበት የኢትዮጵያን ህዝብ ማክበራቸውን ከሁኔታቸው አየሁ፡፡ ፒተር ከወሬዬ፣ ከአገሬ ሁናቴ፣ ከአዝማሚያዬን አይቶ የመከረኝ አውስትራሊያ ሄጄ ለመኖር እንድሞክር ነው፡፡ እስኪ አስብበታለሁ ኮንድዋኒ፡፡

የዕለቱ ዝግጅት በዊትስ ዩኒቨርሲቲ በዊትስ ክለብ ነበር የተካሄደው፡፡ በቦታው አምስት ሰዎች ስንገኝ 12ቱ ደግሞ ከየዓለማቱ በዙም አብረውን ይውላሉ፡፡ ከሦስት ቀን የጥናታዊ ጽሑፍ ዕቅድ ወይም ፕሮፖዛል የመጻፍ የመጀመሪውን ምዕራፍ እየሰራን ቆየን፡፡ የግል፣ የቡድንና የጋራ ስራ ስንሰራ ቆየን፡፡ ወደ ማታም ዶክተር ቴሬዛ ያዘጋጀቻቸው ሁለት ወጣት ሴቶች መጡ፡፡ እንሱም እንደ ኢትዮጵያው ቅልልቦሽ ዓይነት ጨዋታ ተጫወቱልን፡፡ እንግዲህ ይህን ዓይነቱን ጨዋታ እንዴት ዲጂታል እንደምናደርገው እናያለን፡፡ በአርግጥ ፕሮጀክቱ ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ምክንያቱም በቅኝግዛትና ግሎባላይዜሽን ተጽዕኖ ስር የወደቀችውን አህጉራችንን የአውሮፓ ዲጂታል ጨዋታዎች አጥለቅለቀዋታል፡፡ ወደቀደመው ለመመለስ ይህ ጅማሮ ያግዘን ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ ከ17 ተመራማሪ ሦስቱ ብቻ ነን ጥቁሮች፡፡ አፍሪካ ልጆቿን ከቅኝግዛት ለማላቀቅ ምሁራን የሏትም - ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን እንደ ጥቁር ካልወሰድን በቀር፡፡

ወደ እንግዳ ማረፊያ ስመለስ አንዲት በዚያ ያረፈች ምዕራባዊት ጋዜጠኛ አገኘሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ለዘገባ ለመግባት ብዙ ጊዜ አመልክታ ፈቃድ እንደከለከሏት ነገረችኝ። የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ሊፈጸም ትንሽ ቀናት ሲቀሩት መቀሌ ለአንድ ቀን መቆየቷንና በአውሮፕላን መመለሷን ነገረችኝ። ለምርጫም አዲስ አበባ ሄዳ ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ተመልሳ መግባት ስላልቻለች ኢትዮጵያ ውስጥ የምትከፍላቸው መረጃ አቀባይ ጋዜጠኞች አሏት። የእነሱን ቃል ትቀበላለች። የአንዱን ስም ነገረችኝ። ገለልተኛም እንደሆነ ነግሯታል። እኔም ቅልጥ ያለ የህወሐት ደጋፊ መሆኑን ነገርኳት። በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ነገር አወጋን። ወያኔ አዲስ አበባ ሳይደርስ ለምን ደረሰ ብላችሁ ዘገባችሁ ስላት "መንገዱን አውቀዋለሁ። ደብረሲና ከደረሱ ምን ቀራቸው።" በማለት ተከራከረችኝ። በመጨረሻ የሆነው ግን ይታወቃል። አሁንም ለመግባት ስለማትችል ወደ ጎረቤት አገር ጠጋ ብላ ለመዘገብ ትፈልጋለች። እስከዚያው አፍሪካውያን በራሺያ ጦርነት ላይ ያላቸውን ሃሳብና ጦርነቱ ያስከተለውን ጫና እየተዟዟረች ትዘግባለች። ስለኢትዮጵያ እኔን  ልጠይቅህ ያላለችኝ የእኔ ሃሳብ ብዙም ስለማይስማማት መሰለኝ። እንጂ ስለ ኢትዮጵያ ለመዘገብ እንዲህ ከፈለገች ባለስልጣን ወይም ፖለቲከኛም ባልሆን ከአንድ ዜጋ የሆነ ሃሳብ አታጣም። ወደ ወሬያችን መጨረሻ ላይ ስሜቷን ለመገምገም ብዬ "ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ እሰጋለሁ። የምትፈርስ አይመስልሽም?" በማለት ጠየኳት። "አዎ ሁሉም ነገር አብቅቶለታል። ሕወሃት በስልጣን ላይ ሳለ ብሔራዊ እርቅ ቢካሄድ ኖሮ ትድን ነበር" አለችኝ። በእኔ አስተሳሰብ ግን ኢትዮጵያ አትፈርስም!

 

ማክሰኞ ጠዋት አንድን መዋዕለህጻናት ጎበኘን፡፡ ዩቫል በተባለ የቀድሞ የነጮች ሰፈር ስንደርስ በርካታ የጽዳት ሰራተኞ ሰፈሩን ሲያጸዱ ነበር፡፡ ሰፈሩ ጽዳቱ እንደተጓደለ፣ የህንጻዎቹ ባለቤቶች ወደሌላ አገራት ሲሄዱ ወንጀለኞች ኪራይ እየተቀበሉ ህንጻውን እንደሚወርሱ ወዘተ ተነገረን፡፡ መዋዕለህጻናቱ ጋ የሄድነው ህጻናቱ መዝሙር እንዲዘምሩልን ነው፡፡ ቆንጆ ቆንጆ መዝሙር በቋንቋቸው ኢሲዙሉ ዘመሩልን፡፡ ስለሚያውቋቸው የልጆች ጨዋታዎችም ነገሩን፡፡ የምናናግራው በእንግሊዝኛ ስለነበር ‹ጌም› ስንል የዱር እንስሳት ያልን መስሏቸው ‹ነብር፣ ቀጭኔ፣ ዝሆን› ማለት ጀምረው ነበር፡፡ አስረድተን ወደምንፈልገው ወሰድናቸው እንጂ፡፡ ይህን የኢሲዙሉ ‹ድላላ› የሚለውን ቃል መጠቀም የተሻለ ሳይሆን ይቀራል፡፡ ልጆቹ ስሞቻቸው በሙሉ የአፍሪካ ስሞች በመሆናቸው ኮራሁባቸው፡፡ቡሲሶ ማቤናን የመሰለ ቆንጆ ስም፡፡ ኢትዮጵያ በእርግጥ አካሏ በፈረንጅ ቅኝ ባይያዝም አእምሮዋን የሸጠች ይመስለኛል፡፡ ከፈረንጅም ለመካከለኛው ምስራቅ! እስኪ ኢትዮጵያ መዋዕለህጻናት ሂዱ፡፡ ስማቸው ኢትዮጵያ ያላችሁ አይመስላችሁም እኮ፡፡ ምናልባት ከኦሮሞ ብረተኝነት መነሳሳት አንጻር የኦሮምኛ ስሞች እያቆጠቆጡ ካልሆነ በቀር፡፡ 

ከዚያ መልስ የዊትስን ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት ጎበኘን፡፡ ብዙ ቅርስና መዛግብት አላቸው፡፡ ትልቁን አዳራሽም አይተናል፡፡

ስብሰባችንን ቀጥለን ጥሩ ደረጃ አድርሰናል፡፡ ከፍ ያለ ፈንድ ከተገኘ በተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ ከተሞች ጥናቶችን እናካሂዳለን ተብሏል፡፡ ለአሁኑ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ማላዊ፣ እንግሊዝ፣ ኖርዌይና ፊንላንድን ይዘናል፡፡ ከአፍሪካ የምንወጣው እኔና ፒተርን ጨምሮ የቡድኑ አባላት በአፍሪካ ዲያስፖራ ልጆች ዘንድ ያለውን የጨዋታ ሁኔታ ለማጥናት ነው፡፡ ፈንዱ ተገኝቶ መሄድ ከቻልን በግሌ አንድ ስጋት አለኝ፡፡ ይኸውም አገሬን አፍሪካን ጨርሼ ሳልጎበኝ ወደ አውሮፓ ልወጣ በመሆኑ ነው፡፡

ማክሰኞ ማታ የዊትዋተርስራንድ ዩኒቨርሲቲን መቶኛ ዓመት ለማክበር ከተዘጋጁት አንዱ የሆነውን ዝግጅት ማለትም በአስር ሴትና የጾታ ድብልቅ ሁኔታ ያላቸው ሰዓሊያን የተዘጋጀ የስዕልና ቅርጻቅርጽ አውደርዕይ አየን፡፡ ድንቅ ነበር፡፡

ረቡዕ ማታ በፊት በአፓርታይድ ጊዜ የጥቁሮች እስርቤት የነበረውን ኮንስቲቲዩሽን ሂልን ጎበኘን፡፡ ብዙ ስቃይ የተፈጸመበትና ማንዴላና ጋንዲም የታሰሩበት ነው፡፡ ከጎኑ የደቡብ አፍሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተገንብቷል፡፡ የአገሪቱ ታሪክ ስፋትና ጥልቀት እየታየኝ ነው፡፡ ይህንን ከድረገጻቸው ማየት ስለሚቻል እንድታዩ እጋብዛለሁ፡፡ በፕሮግራሙ መሰረት ረቡዕ ማታ ራት በቴሬሳ ቤት ስለሆነ ከኢትዮጵያውያን ምግብ ቤት በያይነት እንድንገዛ ቴሬሳ ሃሳብ አቀረበች፡፡ ከዚያም ገዝተንና የጀበና ቡና ጠጥተን ወደ ቤት ሄድን፡፡ ጀበና ቤና ከምትቀዳው ልጅ በቀር ሁሉም ደቡብ አፍሪካውያን ናቸው፡፡ ሰፈሩ የኢትዮጵያውያን ቢዝነሶች አሉበት፡፡ ማስታወቂያዎችም በአማርኛ ናቸው፡፡

ቤት ሄደን እንጀራ አበላል ሳስተምርና ሌላም ቤት ያፈራውን ስንመገብ አመሸን፡፡ በቻልኩት መጠን በቀን አንድ ጊዜ ተመጋቢ ስለሆንኩ በቂ ምግብ ያለበትን ቦታ መርጬ እበላለሁ፡፡ የዚያን አገር ምግብ ሳይ ኢትዮጵያ በምግብ መበደሏን አስተውያለሁ፡፡ የቴሬሳ ፓርትነር (ባለቤቴ ስለማትለው ነው) የሆነው ሙሪስ የደቡብ አፍሪካ አልኮሆል ፖሊሲ አሊያንስ ውስጥ የሰራ፣ ከማንዴላ ጋር የሰራና መጽሐፍ የጻፈ፣ አሁንም በአልኮል ላይ የጻፈ ነው፡፡ በስራዎቹ እንዲያሳትፈኝ ጠይቄው ፈቃደኝነቱን ነግሮኛል፡፡ ፒተርና የህንድ ዝርያ ያላት ሮዝአንም በራት ግብዣው ላይ አሉ፡፡

በማግስቱ ጠዋት ፒተር ተሰናብቶኝ ቀድሞ ወደ አየርማረፊያ ሄደ፡፡ እሱን ፓውላ ስትወስደው እኔን ደግሞ ጄክስ ወደ ጆሃንስበርግ የአይሁድ ሆሎኮስትና የዘርማጥፋት ሙዚየም ወሰደኝ፡፡ እዚያ ሄጄ ስጎበኝ የአይሁድ፣ የናቢያ፣ የሩዋንዳና የሌሎችም የዘር ማጥፋት ታሪክ አሁን እንማርበት ዘንድ ቀርቧል፡፡ በመጨረሻም የደቡብ አፍሪካ የመጤጠልነት ወይም ዜኖፎቢያ አንድ ክፍል ተሰጥቶታል፡፡ ዳይሬክተሯ በደረስኩበት ቅጽበት ወደ አሜሪካ ስላቀናች ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ኢሜሌን ስለሰጠሁ እንጻጻፋለን፡፡ የእየሩሳሌሙ ያድ ቫሸም የሆሎኮስት ሙዚየሙ ወዳጄ ዶክተር ዴቪድ ዶች ወደ ስፍራው በዚህ ወር እንደሚመጣ ነገሩኝ፡፡ ተመልሼ እንዳገኘውም ጋበዙኝ፡፡ አይ! እኔ ብር የለኝም! አልኩ በሆዴ፡፡ ትስስር የመፍጠርና ኢትዮጵያ ላይ የዘርማጥፋትን አደጋ የመከላከል ዕድል አለኝ፡፡ መጽሐፌም በሰፊው እንዲዳረስ እንዲያግዙኝ ጠይቄያለሁ፡፡

ድንገተኛ መልዕክት ደረሰኝ፡፡ ይኸውም ፒተር የኮቪድ ምርመራው 72 ሰዓት ስላለፈው በረራው አመለጠው የሚል ነው፡፡ ቴሬዛ በዋትሳፕ የላከችልኝ ይህ መልዕክት የደረሰኝ የሙዚየሙን ነጻ ዋይፋይ እየተጠቀምኩ ስለነበር እንጂ ስልኬማ አይሰራም፡፡ በአስቸኳይ ስልክ አስደውለውኝ ሹፌሯን ጠራሁ፡፡ ወደ አየረ ማረፊያ ወሰደችኝ፡፡ ቴሬሳ 1000 ራንድ ፒተር እንደከፈለው ሁሉ የአስቸኳይ የኮቪድ ምርመራ ገንዘብ በፓውላ ስልክ ላከችልኝ፡፡ ፓውላ አየር ማረፊያ ጥላኝ ሌላ ሰው ልታመጣ ጠፋች፡፡ ኤቲኤሙን ወደ ምድርቤት ወርጄ አገኘሁት፡፡ ኤቲኤሙ ጋ ወደ 15 ደቂቃ ለሚሆን ጊዜ ተንደፋደፍኩ፡፡  ለካ ማስገባት ያለብኘ ከዱ የተላከላትን የፓውላን ስልክ ነበር፡፡ በኤርፖርት ሴኩሪቲ እገዛ ተሳካልኝ፡፡ ሴኩሪቲው ሲጠጋኝ ፈርቼ ነበር፡፡ ምክንያቱም በ2017 በዚሁ ቦታ ሊዘርፉኝ ስለሞከሩ ነው፡፡ ገንዘብ ሳወጣ እድጠነቀቅና ዝርፊያ እንደሚያሰጋኝ አስጠንቅቆ ለምርመራ ወደ ሁለተኛ ፎቅ ላከኝ፡፡ በሊፍት ወጣሁ፡፡ ምርመራው ቢያንስ ሁለት ሰዓት ይፈጃል አሉኝ፡፡ በስንት ልመና አለቆቻችንን አናግር ብለው ረድተውኝ ለጉዞዬ አንድ ሰዓት ሲቀር ይደርሳል ብለው መረመሩኝ፡፡ ናሙና ሰጥቼ መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየቀኑ ተጨማሩ 100 ዶላር ከፍለህ በረራህን አፕግሬድ አድርግ ሲለኝ ከሚከርም የኮቪድ ምርመራ ውጤት ማስፈለጉ ቢነግረኝ ምን ነበር! ለፒተርስ ቢሆን! እሱም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው የሚበረው፡፡ ፒተር በማግስቱ በራሪ ነው፡፡ ፒተርና ቴሬዛ መጡልኝ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰልፍ ወሰዱኝ፡፡ ሰዓቱ አልፏል ብለው አትሰለፍም አሉኝ፡፡ በስንት ልመና ተሰለፍኩ፡፡ ሰልፉ ፎቀቅ ማለት አቅቶት የመብረሪያ ሰዓቱ 8፡10 ሞላብኝ፡፡ ካመለጠኝም እቀራለሁ ብላ ከእኔ በኋላ የተሰለፈች ሌላ ሴትዮ ከፊት ያለትን የሌላ አገር ተጓዦች ሁሉ አውሮፕላኑ አመለጠን፤ ‹‹ቦርዲንግ›› እያለች እየለመነች ስንትና ሰንት ፍተሻ አልፈን የመጨረሻው ጋ ስንደርስ አንዱ ፍተሻ ዲኦዶራንቱ አያልፍም አለኝ፡፡ አይለፍ ብዬ ሰጥቼው አለፍኩ፡፡ ቅሚያ የተለመደ ነው፡፡ እየሮጥን አወሮፕላኑን ሰዓቱ ካለፈ በኋላ አገኘነው፡፡ ተሳፈርን፡፡ ከሁለት ከደቡብ አፍሪካ ወደ እስራኤል በኢትዮጵያ በኩል ከአናታቸው ጋር ከሚያልፉ የአንደኛና ሁለተኛ ክፍል ተማሪ አይሁድ ህጻናት ጋር እንግሊዝኛ እያወራሁ፣ ሁለት አጫጭር የአፍሪካ ፊልም እያየሁ መጣሁ፡፡ ታክሲ ይዤ እዚያው ግራንድ እንግዳ ማረፊያ ሄጄ አደርኩ፡፡ በማግስቱ ደብረብርሃን መጣሁ፡፡ አንድ ከአሁን በፊት ወደ ዉጪ ለስልጠና የሄደ መምህር ሲያገኘኝ ያለኝ ቃል ትክክለኛና ለሁሉም የሚሰራ ነው - ‹‹በእኛም ሙያ ዘርፍብዙ ዕድል አለ፡፡ ታዲያ ስንፍናውን እንዴ አናድርገው!››   

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...