ቅዳሜ 4 ማርች 2023

ስውር ምንጭ - የሐውለት አህመድ ‹‹አሽር ቤት›› መጽሐፍ ዳሰሳ ከትዝታዎች ጋር

ስውር ምንጭ

የሐውለት አህመድ ‹‹አሽር ቤት›› መጽሐፍ ዳሰሳ ከትዝታዎች ጋር

በመዘምር ግርማ

የካቲት 25፣ 2015 ዓ.ም.

ደብረ ብርሃን

 


ከልጅነት ሕይወቷ በተለይ ሰባቱን ዓመታት አስመልክቶ የተጻፈው ይህ ‹‹አሽር ቤት›› የተባለው መጽሐፍ 174 ገፆች ሲኖሩት ዋጋው 290 ብር ነው፡፡ ከሥነጽሑፍ ዘውጎች ለማስቀመጥ ከታሰበ ‹ሜሟ› ማለትም ማስታወሻ ሊባል ይችላል፡፡ አቀራረቡ እንደ አጭር ልቦለድ ስብስብ ያለ ነው የሚያስበለው አጫጭርና የራሳቸው ርዕሶች ያሏቸው ታሪኮች ስላሉት ነው፡፡ ከክፍል ክፍል ሲሸጋገሩ ለማንበብ የሚያጓጓና ልብ-ሰቃይ የሆነው ታሪኩ፤ እንደ ወጥ ረጅም ልቦለድ የተያያዘ ነው፡፡ ለማንበብ ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓታት የፈጀብኝን ይህን ታሪክ ትናንት ማታ ከእንቅልፌ በፊትና ዛሬ ጠዋት ከእንቅልፌ በኋላ አነበብኩት፡፡ የቃላቱ ብዛት በማባዛት ለሃያ ሺህ ቃላት የሚጠጋ እንደሆነ የገመትኩ ሲሆን የአንድን ኖቬላ ያህል ርዝመት አለው ለማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም እንደ አንድ ወደረኛ አጭር ልቦለድ ከአንድ ቁጭታ ሊነበብ የሚችል ሲሆን ለፈጣን አንባቢ ጊዜ አይወስድም፡፡ ግን በየመሃሉ ቆም እያሉ ማሰብና ማሰላሰል ስለሚኖር ጊዜ ቢወስድብዎትም አይገርምም፡፡  እንደኔ ያለው ደግሞ በመጽሐፉ ላሉት ታሪኮች በአጋጣሚ የተገኘ ቅርበት ያለው ሰው ምስክርነቱና የሚሰጠው ምላሽ በእጅጉ ይጠበቃል፡፡

አብዛኞቹን ታሪኮች ባለታሪኳ በፌስቡክ ገጿ በለቀቀችበት ወቅት ተከታትዬ አንብቤያለሁ፡፡ ያላነበብኳቸውም ነበሩ፡፡ ዛሬ ሁሉንም በአንድ ጥራዝ ማግኘቴ ስለጠቀመኝ እንኳንም ታተሙ ብያለሁ፡፡ ሁሉንም እንዳዲስ ለማንበብም ፍላጎቴ ነበር፡፡ የቋንቋ አጠቃቀሟን አስመልክቶ ለአረብኛ ቃላት የግርጌ ማስታወሻ ማስቀመጧ ማለፊያ ነው፡፡ አንዳንድ የእንግሊዝኛ ቃላት ቋንቋውን የማይችሉ ወገኖችን ግር ሊያስብሉ ቢችሉም መሰረታዊ የመረዳት ችግርን አያመጡም ባይ ነኝ፡፡ እንግሊዝኛ የአማርኛ ንግግርና ጽሑፋችን እንዲሁም የሕይወታችንም ጌጥ ስለሆነ፡፡ አረብኛ የሙስሊሙ ህብረተሰብ፣ ግእዝ የክርስቲያኑ እንደሆነው ሁሉ እንግዚዝኛም የትምህርት ቤት ደጅ የረገጥን ሰዎች ንግግር ማድመቂያ ነው፡፡ ‹‹የደራሲዋ የአጻጻፍ ዘዬ ራሷ ደራሲዋ ነች›› እንደሚሉት የሥነፅሑፍ አሳብያን የአማርኛ፣ የአረብኛ፣ የእንግሊዝኛና የአርጎብኛ ውህድ በመጽሐፏ እናገኛለን፡፡ የሐውለትን አቀራረብ በቋንቋ ብቻ ሳይሆን በአጻጻፍ መላዋም ማየት ይቻላል፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ምልልስ፣ ትረካ፣ ገለጻ፣ ግነትና ልዩ ልዩ ዘይቤዎች በጽሑፏ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ጌጦች ከልቦለድ አላባውያን ጋር አሰናስላ በፈጠራዊ ኢ-ልቦለድ ምድብ ሊገባም የሚችል ማስታወሻ አስነብባናለች፡፡ ይህን ድምዳሜ ሳቀርብ ከአጻጻፍ ዘዴ አንጻር እንጂ የተባለው ታሪክ አልተፈጸመም ማለቴ እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡ በቀላልና ግልጽ አቀራረብ የቀረበው መጽሐፉ አረብኛንና የቁርአንን ትምህርት ሁኔታና ተፈጥሮ ያስተዋውቃል፡፡ ፊደላቱንና የአነባበብ ዘየውንም ያሳያል፡፡ ይህን ለመሞካከር ላሰበ መጽሐፉ መነሻ ይሆነዋል፡፡ 

ጽሑፌን የሚያሳምሩልኝ የትዝታ ጌጦች ስላሉኝ በተኖረ ልምድ ላይ ተመስርቼ የሚከተሉትን ገፆች አብረን እንቆያለን፡፡ እኔ በቄስ ትምህርት ቤት ባልማርም እዚያ የተማሩ ልጆች ከሚነግሩኝና ስለቄስ ትምህርት ቤት ካነበብኩት ጋር የአሽር ቤትም ነገር ተመሳስሎብኛል፡፡ በአንዲት ቤት ሁሉም ተማሪ መማሩ ያመሳስለዋል፡፡ የሦስቱ የደብረብርሃን አሽር ቤት ተማሪዎችን ብሽሽቅ ጉዳይ ሳነብ ሳሲት ደብተራ ዘለቀ ጋ የሚማሩት ተማሪዎች ከመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚደርስባቸው የግጥም ውረፋ ትዝ አለኝ፡፡ በቄስ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ መጨረስ መኖሩን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በአሽር ቤት ግን ቁርአንን ማንበብ ግድ ነው፡፡ ሐውለትም ከሁለት ጊዜ በላይ አንብባለች፡፡ የኔ ጥያቄ ትርጉሙን ትረዳዋለች ወይ የሚለው ነው፡፡ ለውህ የተባለውን መጻፊያ የጣውላ ቁራጭ የመሬም የልጅ ልጅ መሊካ ስታጸዳ አይቼዋለሁ፡፡ ወደ አሽር ቤቴ ልሂድ ስትልም ስለምሰማ ቃሉ አሁን አዲስ አልሆነብኝም፡፡ የመጻፊያውን ነገር ስናነሣ አሽር ቤትን ከቄስ ትምህርት ቤት የሚለየው  ነገር ነው፡፡ ቄስ ትምህርት ቤት ከብዙ ቆይታ በኋላ ወደ ጽሐፈትና ሥዕል የሚያመሩ ልጆች እንጂ አብዛኛው መጻፍ እንደማይማርና እንደማይችል ነው የሰማሁት፡፡ የቁም ጽሕፈት የሚለምዱት በሂደትና ምናልባት በስተመጨረሻ ነው፡፡ እንደ አሽር ቤቱ ሁሉ መድ ወይም ቀለም ከእጽዋት የሚያዘጋጁትም ሆነ ብራና የሚፍቁት በኋላ ነው፡፡ ሽምደዳውም ተመሳሳይነት አለው፡፡ የትምህርት ስርዓቱም መምህሩ ሁሉንም ሳይሆን የመጨረሻዎቹ ከፍተኛ ደረጃዎች ላይ ያሉትን ያስተምራሉ እንጂ ሌላው እርስ በእርሱ እንደሚማማርና እርሳቸው ፈትኖ ከደረጃ ወደ ደረጃ ለማሳለፍና የመማማሩን ስርዓት ለመከታተል ነው የሚያስፈልጉት፡፡ የማስተማር ስርዓቱ የሁለቱም ኃይማኖቶች ምርምሮች እንደተሰራበት ሰምቻለሁ፡፡ የሙስሊሙን የኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት የፊዚክስ መምህራችን አህመድ ለማስተርሳቸው መስራታቸውን የኔም የሐውለትም መምህራችን የነበረውና የአሁኑ የሥራ ባልደረባዬ ዶክተር ሰይድ ነግሮኛል፡፡ እንደ ዶክተር ኃይለገብርኤል ዳኜ ዓይነቶቹ ደግሞ በሁለቱም ላይ የሰሩ አሉ፡፡ ከኃይማኖቱ ዉጪ ያሉት የሚሰሩት የራሱ የሆነ ውጫዊ ምልከታ ስለሚኖረው ጠቀሜታው የጎላ ይመስለኛል፡፡

ሙስሊሞች በአረብኛ ትምህርት አእምሯቸውን እንደሚያሰሉ ሐውለት የገለጸቸው እውነት ነው ባይ ነኝ፡፡ የቤተክህነት ትምህርትም እንደዚሁ ስለሚባል፡፡ ልዩነቱ የቤተክህነት ትምህርት የተማሩ ሰዎች ግእዝ ከአማርኛ ጋር ስለሚቀራረብ የበለጠ ዕድል ያላቸው ይመስላል፡፡ በዚያ ያለፉት ታዋቂ የአማርኛ ደራስያን መሆናቸው አይካድም፡፡ ይህን ዕድል ምናልባት በሙስሊሞች ዘንድ እንዳናገኘው የሆንን ይመስለኛል፡፡፡ ለዚህም ምክንያት ሊሆን የሚችለው ልጆቹ አረብኛን አቀላጥፈው ችለው በቋንቋው የመጻፍና የማሳተም ዕድል ስለሌላቸው ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ወደ አረብና ሙስሊም አገራት የመሄድ ዕድል ያላገኙትን አስመልክቶ ነው፡፡ በእርግጥ እኛ ስላላነበብንና ዕድሉ ስለሌለን እንጂ በዘርፉ ተጽፏል፡፡ ወደፊትም ማንበብና ማወቅ ያለብን ብዙ የአረብኛ ሥነጽሑፍና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ አለ፡፡ በቢቢሲ ስለ አፍሪካ የእስልምና ተማሪዎች የትምህርት ሁኔታ ያነበብኩት ተማሪዎቹ ምግብ ከህብረተሰቡ የሚለምኑበት ሁኔታ በደብረብርሃን የለም፤ ለበዓላት ስጦታ ለመጠየቅ ወደሚያውቋቸው ሙስሊሞች ቤት ከመሄዳቸው ውጪ፡፡ በሌሎች ገጠራማና ተማሪዎች ከወላጆቻቸው ርቀው በሚኖሩባቸው ቦታዎች ግን ሳይኖር አይቀርም፡፡

እኔ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቴን የተማርኩት በደብረብርሃን ነው፡፡ እስከ 8ኛ ከተማርኩበትና ተወልጄ ካደኩበት ሳሲት 92 ኪሎሜትር ርቄ በኪራይ ስማር የ11ኛና የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን በእነ ሐውለት ግቢ ተከራይቼ ነበር፡፡ አከራዬ የአቶ ወርቄ ቤተሰብ እነ እንግዱ ቢሆኑም መውጫዬ በነ ሐውለት በኩል ስለሆነ ከነሱ ጋር ነው ይበልጥ ቅርርብ የነበረኝ፡፡ በመጽሐፉ የተጠቀሰችው የሐውለት አክስት ወይዘሮ መሬም በጣም ደግና እንደ ልጅ የምታየኝ ነበረች፡፡ ስለ ኃይማኖት መቻቻል ለመግለጽ ካስፈለገ ሐውለት በመጽሐፏ ከጠቀሰችው በላይ አክስቷ መሬም ክርስቲያን ማግባቷ ይገልጸው ይሆናል፡፡ ከክርስቲያን ባሏም ሁለት ልጆችን ወልዳለች፡፡ ታናሽ እህቷ ሠሚራም ከኔ ጋር ተመሳሳይ የክፍል ደረጃ ላነበረች፡፡ ሐውለት ግን አራት ዓመት ትቀድመናለች፡፡ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ እሷ ወደ ዩኒቨርሲቲ ስለገባች በአካል አላውቃትም ነበር፡፡ ከእርሷ በፊት ግን ዝናዋን ከመምህራን ሰምቻለሁ፡፡ ከዚያም በዘለለ ቤተመጻሕፍት ካገኘሁት የአዲስዘመን ጋዜጣም ቃለምልልሷን አንብብቤያለሁ፡፡ የናቹራልም የሶሸልም ተማሪ እንዳልሆነች ልግለጽላችሁና የምን እንደሆነች ገምቱ፡፡

የደብረብርሃንን ብርድ በትክክል ስለገለጸችው የምለውም የለኝ፡፡ በስስ ቲሸርትና በዚያች የደንብልብስ የተቋቋምንበት የአራት ዓመት ጊዜ አስገራሚ ነው፡፡ ገል መታቀፍ ያለችው ዘዴ ለኛ ቤተሰብ ላልነበረን ልጆች የቅንጦት ነበር፡፡ ሐውለት በዚህ መንገድ በትጋት አጥንታ የደረሰችበትን ደረጃ ወደፊት ስለዓለማዊ ትምህርቷ ትስጽፍ ታጋራናለች ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ ከአክስቷና ቤተሰቧ ንዲሁም ከትምህርት ቤት መምህራን ስለሐውለት የሰማሁት አነሣስቶኛል፡፡ በኋላ በቴሌቪዥን ዜና አንባቢ ሆና ስትመጣ ለሁሉም የደብረብርሃን ልጅ፣ ሙስሊም፣ ሴት ሁሉ አነሣሽ ሆናለች ለማለት እችላለሁ፡፡

ከአርጎባ ዘመዶቿ የቅርቡን ትውልድ የተወሰኑትን አውቃቸዋለሁ፡፡ እናትና ልጆቹ ወለላና ሲቲም እኛው ግቢ ተከራይተው ይኖሩ ነበር፡፡ ስለ አያቶቿ እሰማለሁ እንጂ አልደረስኩባቸውም፡፡ ስለ ሴት አያቷ ደግነት ሳነብ የመሬምን ደግነት ስለማውቅ እንባዬ ችፍ ብሏል፡፡ በነገራችን ላይ ሐውለት በልጅነቷ እንዲኖራቸው ትመኘው የነበረው ቴሌቪዥን በቤታቸው የተገዛው በኔ ዕድሜ ነው፡፡ ብዙ ዜናና መዝናኛ ያየሁበትም ነው፡፡ ምናልባት እሷንም ጭምር፡፡

የኃይማኖት መቻቻልን አስመልክቶ ባለፈው ከደብረብርሃን ሙስሊሞች አንዱ ከሆነው ከግሪን ዞኑ ከድር ጋር ተገናኝቼ በለጠፍኩት ጽሑፍ እንዳልኩት ነው፡፡ ልዩነታችን ምንም አይታየንም ለማለት ይቻላል፡፡

መቼም ስለ ሙስሊሞች ትምህርት ቤት ሲነሳ ቀድሞ ስለ ሙስሊሞች ማሰብና የኔ እሳቤ ምን ይመስል እንደነበር መግለጽ ያስፈልጋል፡፡ ከቆላ የሚመጡት የሐውለት ዘመዶች ክርስቲያን አይተን አናውቅም እንዳሉኝ ሁሉ እኔም ሳሲት ብዙም ሙስሊም አይቼ አላውቅም ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ግን ለማየት ችያለሁ፡፡ ቢሆንም እንግዳ ይሆኑብኛል፡፡ ኃይለማርያም ማሞ ስማር ብዙ ሙስሊሞች የክፍል ጓደኞች ሊኖሩኝ ቻሉ፤ በከተማውም ብዙ ሙስሊም አወቅሁ፡፡ ሲሰግዱ ማየት፣ ሲፆሙ ስለፆማቸው መረዳት፣ ስለ አለባበሳቸው መጠየቅ ወዘተ ችያለሁ፡፡ አርጎባ፣ ወርጂና አማራ ሙስሊሞችን ተዋወቅሁ፡፡ ሐውለት በመጽሐፏ እንዳለችውም ሆነ ከአሁን በፊት ከጉግል እንዳነበብኩት የደብረብርሃን ሙስሊም ብዛቱ አምስት በመቶ ነበር፡፡ አሁን ግን ለውጦች ያሉ ይመስለኛል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሙስሊምና ክርስቲያን ቁጥር በትክክል እንደማይታወቀው ሁሉ የደብረብርሃንም የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡ ለመላ ምት የተጋለጠ ነው፡፡ በዚህች የሙስሊሞች ቁጥር ዝቅተኛ በሆነባት ከተማ ሙስሊሞች የራሳቸው የሆነ ታሪክ አላቸው፡፡ በቀደምት መንግስታት ጊዜ ገብተው የነበሩት አረቦች በተለያዩ ጊዜያት ወደየአገሮቻቸው ቢመለሱም በትዳርና በወዳጅነት ከህዝቡ ጋር ተሳስረዋል፡፡ የሐውለትን አረብ እናት ወይም አከስት እርግጠኛ ባልሆንም ለእረፍት መጥታ አይቻታለሁ፡፡ የደብረብርሃን ሙስሊሞች ከቁጥራቸው ማነስ ውጪ በፍቅር መኖራቸውን አይቻለሁ፡፡ መጽሐፏም ምስክር ነች፡፡ ሙስሊሞች እንደ ደሴት በቁጥር ትንሽ ናቸው፡፡ አሽር ቤትን ሳስባትና አስተዋጽኦዋን ስረዳ ደግሞ ብዙዎች ትኖራለች ብለው የማይምቷት ስለሆነች ‹‹የደሴት ውስጥ ደሴት›› ልላት ቻልኩ፡፡ በተሻለ ሁኔታ የምድረበዳ ምንጭ ልትባልም ትችላለች፡፡ ይህን ሁሉ ቅሬታ አምጪና አወዛጋቢ ነገር የዚህ ጽሑፍ ርዕስ አድርጌው ነበር፡፡ በኋላ ቀየር አድርጌ ‹‹ፎር ዘ ፎለን›› ከሚለው›› ከሎረንስ ቢንየን ግጥም አንዲት መስመር ሃሳብ ወስጄ ርዕስ ሰጠሁት - ‹‹ከዕይታ እንደተወሰወረ የጉድጓድ ምንጭ›› እንዲል፡፡ ለሌሎቻችን በኃይማኖት ምክንያት የተሰወረች ነች -  አሽር ቤት፡፡

መጀመሪያ በአንድ ብር በኋም በአንድ ብር ከሃምሳ ያስተምሩ የነበሩት የደብረብርሃን አሽር ቤቶች ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ገብቶኛል፡፡ በብዙ መቻቻልና አብሮነት የኖሩትን ጓደኞቻችንን አፍርተውልናል፡፡ የአረብኛ አጻጻፍ ከቀኝ ወደ ግራ ከመሆኑ ውጪ ምንም አላውቅም ነበር፡፡ ክርስቲያኖች የሙስሊሙን የሚማሩባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ከሰው ሰምቻለሁ፡፡ ሙስሊሞችም የክርስቲያን ይማራሉ፡፡ ወዳጄ ወሎዬው ዑመር እንዳለው ዳዊት ደግሟል፡፡ ይሁን እንጂ ዳዊት ውስጥ ያሉት የታቦታት ስዕሎች ዳዊቱ ሲነበብ ስለማይታዩና በአብረቅራቂ ጨርቅ መሸፈን ሳላለባቸው ጨርቁን መግዣ ብር ስጪኝ ያላቸው እናቱ ‹‹ከእንግዲህ አትዳቁን፤ ማንበብ ከቻልክ ይበቃሃል›› ብለው እንዳስቆሙት ነግሮኛል፡፡ የአማርኛ ንባብ ለመቻል የቄስ ትምህርት ቤት ለሙስሊሞች ተመራጭ ነበር፡፡ አብሮነትንም ያስተምረናል፡፡ ሐውለት ስለቁርአን ትምህርት ስታወሳ በአእምሮዬ የነበረው ጥያቄ ዘመናዊ ትምህርቷን መቼ እየተማረች ነው የሚል የነበረ ሲሆን ከፈረቃ ውጪና ቅዳሜና እሁድ እንደምትማር ከመጽሐፉ ግማሽ በኋላ ሳነብ ምላሽ አገኘሁ፡፡ በሷ ዕድሜ ትምህርት በፈረቃ መሆኑን ማወቄ አስገርሞኛል፡፡ ምክያቱም እኔ ሳሲት ከአምስተኛ ክፍል በኋላ ነበር ፈረቃ የጀመርኩት፡፡ የአሽር ቤት ትምህርት ለእረፍት ወደ ሌሎች ቦታዎች ሲኬድ እንኳን የማይቋረጥ መሆኑ ገርሞኛል፡፡ ቁጥጥሩ ጥብቅ መሆኑ ለትምህርቱ ጥራት የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የቅጣትና ሥነሥርዓት ሁኔታን ጠቀሜታ ደራሲዋ ገልጻዋለች፡፡ ይህም ለዘመናዊ ትምህርት ያለውን አስተዋጽኦ አንስታለች፡፡ የግእዙም አለው እንደሚባለው ነው፡፡ ትምህርት አሰጣጡ ፉክክርም መረዳዳትንም ያቀናጀ በመሆኑ ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡   

ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄ እንደመጣሁ የተቀጠርኩት ደብረብርሃን ነው፡፡ የተከራየሁበት ቤት መታጠቢያ ቤት ሰለሌለው መታጠቢያ የት እንደሚገኝ ስጠይቅ መስጊድ እንዳለ ነገሩኝ፡፡ ሄጄ ሳጣራም መስጊዱ ለገቢ ማመንጫ ታስቦ አገልግሎቱን እንደሚሰጥ ተረዳሁ፡፡ የተወሰነ ጊዜም ታጠብኩ፡፡ የመስጊድን ግቢ ሁኔታ ተረዳሁ፡፡ የመስጊዱ በረንዳም በጫማ የማይረገጥ መሆኑ ገባኝ፡፡ እነ መሬም ጋ ስላደግሁ የሙስሊም ፍራቻ ለቆኛል ለማለት እችላለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአመጋገብ ሥርዓት የሙስሊምና ክርስቲያን በሚል በኢህአዴግ መንግሥት የተከፈለውን አመጋገብ ጥሰን እኔና ሊሻን ከናስር ጋር እንመገብ ነበር፡፡ ሻወሩም አላስደነገጠኝም፡፡ ኃይማኖትንና ኃይማኖተኞችን መጠራጠርና መጠየቅ ስጀመር ሃያ ዓመት እየተጠጋኝ ሲሆን በተለይ ለሙስሊሞች ግን ጥያቄዬና ሙግቴ ጠንከር ያለ የሆነው የአያን ሂርሲ አሊን ሁለት ማስታወሻዎች ወይም ‹ሚሟ› ስላነበብኩ፣ ንግግሮቿን ስለተከታተልኩ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹ ምዕራባውያን የኃይማኖት ነቃፊዎች ትኩረታቸው እስልምናን ማጥቃት ላይ ስለሆነ የዚያ ተጽዕኖ አለብኝ፡፡ የነሱ ምክንያት ክርሰትና በበቂ ሁኔታ ተተችቷል የሚልና ከአክራሪ እስልምና ፋር የተቆራኘ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሙስሊምን እንደ ቤተሰቤ እንደማይ የምረዳው ሙስሊም ጓደኞቼን ያለምንም ልዩነት ስቀርብ ነው፡፡ የሐውለትንም መጽሐፍ በፍቅር ሳነብ ያ እሳት የበለጠ ተቀጣጠለ፡፡ በሰፊው የሚወራላቸው ግን ያልሰራንባቸው እሴቶች አሉን፡፡ ለምሳሌ አብሮ የሚበላ ሕዝብ የሚለውን ላንሳ፡፡ አብሮ ሲበላ ብዙም ስላላየሁ የሃሳቡ ደጋፊ አይደለሁም፡፡ በትምህርት ቤት የተማርነው ወይም የሕዝቡን ትስስር ለማጉላት የመጣ ይመስለኛል፡፡ እውነት ከሆነ የበለጠ ቢሰራበት እናተርፍበታለን፡፡ የሙስሊም፣ ክርስቲያንና ሌሎች ኃይማኖቶች መቻቻልም ከወሬ ባለፈ ሊሰራበት እንደሚገባ የገባኝ የሐውለትን መጽሐፍ ካነበብኩ በኋለ ነው፡፡ አብሮነትን የሚሸረሽር ብዙ ድርጊት ስላለ ብዙ ስራዎች ይጠብቁናል፡፡ ስለ እውነት ለመናገር እኔ አብሮ የመብላቱን ነገር አለ ብዬ እንደማልቀበለው ሁሉ የኃይማኖት መቻቻል አለ የሚለውንም እምብዛም አልቀበለውም ነበር፡፡ አለማወቄን ግን ሐውለት አሳወቀችኝ፡፡

ከታሪካችን አብሮነትን የሚያጎሉትን ብንመርጥ ለዛሬም ሆነ ለወደፊት ሕይወታችን ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ብዙ አማኝ ባለባት አገር አንዳንድ አፍራሽ ነገሮች ከብዙ ጎኖች ይሰማሉ፡፡ ለምሳሌ በወዳጄ በአሊሹ ሙሜ የተተረጎመውን የማልከም ኤክስን ታሪክ ሳነብ ያገኘሁት ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም ማልከም ከአሜሪካ ሐጂ ሄዶ ሁለት የእንግሊዝ ቅላጼ ባለው እንግሊዝኛ የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ማግኘቱን የሚገልጽበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በክርስቲያን ነገሥታት ተጨቁነውና ቁጥራቸው ዝቅ ተደርጎ የሚኖሩ ሙስሊሞች የሚኖሩባት አገር ተደርጋ መገለጿ ትክክል ነወይ? ምን ይህ ችግር እኮ ከኃይማኖት ውጪም አለ፡፡ በብሔር አስተሳሰብ ውስጥ ያለ ጓደኛዬ በ2002 ዓ.ም. ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ መቻል እንጂ መቻቻል የለም›› ያለኝን ዓይነት አስተሳሰብ ሊሞገትና መልሶ ሊታይ አይገባውም ትላላችሁ? ብሔርና ኃይማኖት አብረናቸው ኖርንም ተውናቸው የሕይወታችንና የታሪካችን አካል መሆናቸው ስለማይቀር በመልካም ጎናቸው ቢጻፍባቸውና ብንነጋገርባቸው ይጠቅም ይመስለኛል፡፡

ሐውለት ከክርስቲያን ጓደኞቿ ጋር የቀረበ ግንኙነት አላት፡፡ ፎርፌ የምትፎርፍበት፣ ለውህ የምታስመልስበት፣ የፍቅር ደብዳቤ የምታመላልስበት፣ ፀጉሯን የምትሰራበት፣ ለክርቲያኖች የመዝሙር ዜማ የምትይዝበት፣ ሥላሴና ጊዮርጊስ አብያተክርስቲያኖች የምትገባበት፣ ቡሄ የምትጨፍርበት ገጠመኝ ሁሉ ከቤተዘመድና ቤተሰብ ወግ ጋር ሳቢ ነው፡፡ መጽሐፏ ደብረብርሃንን ከሙስሊም ዕይታ ለማየትም ጠቃሚ ነው፡፡

በልጆች ዓለም ያሉ እንደ አፈር መብላት፤ በነፍሳት፣ በአይጦችና በሳማ ሰውን ማስፈራራት፣ በኤሊ መጫወት፣ ድንኳን መስበር፣ አለቅነት፣ ዘመድ ጥየቃ ወዘተ የመጽሐፉ ጌጦች ናቸው፡፡ የሐውለት የእርግብ እርባታ ታሪክ ራሱን የቻለ መጽሐፍ የሚወጣው ሙያና ታሪክ ይመስለኛል፡፡ ተመሰጡበት፡፡

በ1980ዎቹ የነበረችውን ደብረብርሃን ከተማን በሚገርም ሁኔታ ገልጻታለች፡፡ መንገዶቹ፣ ቤቶቹ፣ ጋሪዎቹ፣ ሰዎቹ፣ የእምነት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶቹ፣ ብቻ ምንም አልቀራትም፡፡ ስለ ጋሪዎቹ ስትጽፍ የደብረብርሃን ፈረሶች የሚል ጻፍኩትና በድረገጽ የታተመ አንድ የልጆች መጽሐፌን ትዝ አስባለችኝ፡፡ አሽር ቤቱ አጠገብ ያሉት ዉኃ የሚሰጧቸው እናት የሳሲት ትምህርት ቤት ጎረቤት ደጋግ እናቶችን አስታወሰኝ፡፡ የወታደሮች ኮቸሮ፣ የሚሰግዱት ወፎች፣ የወር እንትን፣ የቁርዓን ገጾች፣ የመስጂድ ሐቅ፣ ሂጃብ አስተሳሰር፣ የሚሚ ኩበቶች ብቻ ሃሳቦቹና ርዕሶቹ የተስፋየ ገብረአብን አጓጊ ርዕሶች አስታወሱኝ፡፡ እናንተም የመሐመድ ሰልማን ወይም የአቤል የአዲስ አበባ ጉዶች አጻጻፍ ዘዬ ትዝ ሊላችሁ ይችላል፡፡ ሌላው ጉዳይ ርዕሱን አይቶ ለመገመት አለመቻሉ መጽሐፉን ማንበብና የጉዳዩን ምንነት እስኪያውቁ ድረስ ልብ መሰቀሉ አይቀርም፡፡  

የሙስሊሞችን የዓለም እይታ ለመረዳት ብዙ ማንበብና መጠየቅ እንዳለብን አሁን እየገባኝ ነው፡፡ ልጆቻችውን በኃይማኖታቸው ለማትጋት አሽር ቤት የሚልኩትን ወላጆች ማድነቅም አለብን ተረድቻለሁ፡፡ ለካ የጉዳየን ጫፍ ነው ገና የያዝነው፡፡ መጽሐፉን አስመልክቶ የተሰማኝንና የመጣልኝን አወጋሁ እንጂ እናንተ አንብባችሁ ምን አንደምትሉ አላውቅም፡፡ እኔ በበኩሌ ታሪኩ በተፈጸመበት ከተማ የተመረቀውን ይህን መጽሐፍ በዚያችው ከተማ ማንበቤ ልዩ ስሜት አሳድሮብኝ ስላለቀብኝ ግን ተበሳጨሁ!

መልካም ንባብ!

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...