ሰኞ 13 ማርች 2023

ልቼ፣ የአፄ ምኒልክ መናገሻ ከተማ ወድማለች

 

ልቼ፣ የአፄ ምኒልክ መናገሻ ከተማ ወድማለች

የጉዞ ማስታወሻ

በመዘምር ግርማ

መጋቢት 3፣ 2015 ዓ.ም.

 

የአድዋን ድልና የጥቁሮች የታሪክ ወር የሆነውን የካቲትን በማሰብ በ2007 ዓ.ም. እንጎበኛቸዋለን ካልናቸው ሦስት ታሪካዊ ከተሞች ማለትም አንኮበር፣ አንጎለላና ልቼ አንዷ የሆነችው ልቼ በወቅቱ ሳትጎበኝ ቀረች፡፡ ሌሎቹን ጎብኝተን በጉዞ ማስታወሻ ያስተዋወቅነውና ሌሎች ጎብኝዎችን ለመሳብ የቻልንበት ወግ ሳይደርሳት ቀረ፡፡ ቀኑ ደርሶ የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት የጉዞ ማህበር አባላት ለዚህች ቀን ተቀጣጠርን፡፡ ዘንድሮ ከዘጠነኛው የአንጎለላ የእግር ደርሶ መልስ ጉዞና የአንኮበር ጉዞ በኋላ ልናያት ቆርጠናል፡፡ 

እሁድ ጠዋት በአጋጣሚ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን 16ኛው የግማሽ ማራቶን ውድድር ከጫጫ እስከ ደብረብርሃን ይካሄድ ኖሮ መንገድ ለትራንስፖርት ተዘጋ፡፡ ይህን ያላወቁና ቀድመው ያለተነሡ አባላት በከተማው መካከል የተቀጣጠረው ቡድናችን ስላመለጣቸው ቀሩ፡፡ እነሱን ሌላ ቀን ትጎበኛላችሁ ብለን 15 አባላት በእግራችን ወደ ልቼ አቀናን፡፡ ስንጓዝ እንደወትሮው የታሪክ ርዕሶችን እያነሣን ለመወያየት ያመቸን ዘንድ በአራት ቡድኖች ተከፍለናል፡፡ በውይይትም ጥሩ መንገድ አሳለፍን፡፡

አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በግምት አራት ኪሎሜትር የሚሆነውን መንገድ አገባደን ልቼ ደረስን፡፡ ለታዕካ ነገሥት ልቼ ኢየሱስን ቤተክርስቲያን ካህናት ስለ ጉብኝት ፍላጎታችን አስረድተን እገዛቸውን ጠየቅን፡፡ አንድ ቄስም ባማረ ሁኔታ ያስጎበኙን ጀመር፡፡

ቤተመንግሥቱ በነበረበት ቦታ ላይ የተገነባው ዘመናዊ የቤተክርስቲያን ሕንፃ ተጠናቋል፡፡ በስተደቡብ አቅጣጫ በግቢ ውስጥ አፄ ምኒልክና አፄ ዮሐንስ ስምምነት የፈጸሙበት ቦታ ላይ የነበሩት ድንጋዮች ቤተክርስቲያኑ ሲታነጽ በስህተት መነሳታቸውን ነገሩን፡፡ በስተሰሜን የቤተመንግሥት ፍርስራሽ ይገኛል፡፡ በስተምስራቅ ደግሞ የበፊቱ ሰገነት በነበረበት ዲብ እንዳለ ሆኖ የቤተክርስቲያኑ መቃኞ ተሰርቶበታል፡፡

አስጎብኛችን እንዳሉን የአንኮበሩ ቤተመንግሥት የአፄ ምኒልክ አያቶች ሲሆን ይህኛው ግን የእርሳቸው ነው፡፡ እኛም ከታሪክ ንባባችን ይህ ቦታ ቤተመንግሥታቸው የነበረበት መሆኑን አንብበናል፡፡ ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 49-50 የጻፉትን እንመልከት ‹‹በዋና ከተማቸው በልቼም ሦስት ቀን የቆየ ግብር አብልተው ሕዝቡን አስደሰቱት፡፡ ስለዚያ ግብር ሁኔታ ማሳዣ ሲጽፉ ‹… የተሠራው አዳራሽ ትልቅ ነበር፡፡ በአዳራሹም ለምግብ ማቅረቢያ 150 ረጃጅም ገበታ ተዘርግቶ ነበር፡፡ ወታደር፣ ሲቢል፣ መኳንንት፣ ቄስ፣ የልቼና ያካባቢዋ ታላላቅ ሰዎች ሁሉ ተጠርተው ነበር፡፡ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከትግራይና ከመላው ኢትዮጵያ ታላላቅ ሰዎች መጥተው ነበር፡፡› … በግብሩ ጊዜ በአዳራሹ ውስጥ ንጉሥ ምኒሊክና መሐመድ አሊ በአንድነት ተቀምጠው ታዩ፡፡››

ከዚህ ላይ በአእምሯችን ሊመጣ የሚችለው ጥያቄ ያ የቤተመንግሥት ግቢና አዳራሽ አሁን የት ገባ የሚል ነው፡፡ ያ ግብር ያበሉበት፣ የኖሩበት፣ ክፉና ደጉን ያዩበትና ያስተዳደሩበት ቤተመንግሥት ምልክቱም የለም፡፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጊዜ ቦታው ጥቅም ይሰጥ እንደነበር አስጎብኛችን ነግረውናል፡፡ የተከበረውን ቦታ ያጠፋው ስፍራውን በመሬት ላራሹ ለገበሬዎች ያከፋፈለው ደርግ መሆኑን አውስተው በ1989 ዓ.ም. የመሬት ድልድል በኢህአዴግ መንግስት ገበሬዎቹ እንዲነሡና ለቤተክርስቲያን ቦታውን እንዲሰጡ ተደርጎ በአሁኑ ጊዜ 12 ሄክታር ቦታ በቤተከርስቲያኑ ይዞታነት እንዳለ አስረድተውናል፡፡ ይህም ቦታ ሦስት ዙር የጥንቱን የቤተመንግሥት የካብ አጥር የያዘ ሲሆን ያንንም አጥር አይተናል፡፡ በግሌ የገረመኝ ነገር ገና ሥልጣን እንደተቆጣጠረ የአፄ ዘርዓያዕቆብን የመካከለኛው ዘመን እውቅ የደብረብርሃን ቤተመንግሥት ፍርስራሽ በትራክተር ጠራርጎ ያጠፋው የኢህአዴግ መንግሥት ይህን ስፍራ ለቤተክርስቲያንም አልሰጥም ብሎ በመኖሪያ መንደርነት እንዴት እንዳላጸናው ወይም በሌላ መንገድ አሻራውን እንዳላጠፋው ነው፡፡ ከቤተክርስቲያኑ ቅጽርግቢ ውጪ ወጥተን የአፄ ምኒልክ ጊዜ ጥቅም ትሰጥ የነበረችውን ያን ጊዜ በልዩ ሁኔታ የተገነባች ምንጭ አይተናል፡፡ ውኃም እየቀዱ የነበሩ የአካባቢው አርሶአደሮች ቀድተው ሰጡንና ጠጣን፡፡

ከምንጯ አለፍ ብሎ የበዛብህ መቃብር አለ፡፡ እሱንም ባሻገር አይተናል፡፡

‹‹አንተም ጨካኝ ነበርክ ጨካኝ አዘዘብህ፣

እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደብህ››

የተባለው በዛብህ በስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ተደጋጋሚ የአመጽ ሙከራ በማድረጉና በምህረትም ባለመመለሱ በኋላ ሞት ተፈርዶበት የነበረ ሰው ነው፡፡

አስጎብኛችን ‹‹ለስፍራው ለወደፊቱ ምን ይደረግ›› ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ቦታው መልማት እንዳለበት ገልጸው የእምዬ ምኒልክን ውለታ መመለስ እንዳብን አሳስበዋል፡፡ ስለአጼ ምኒልክ ደግነት ነገሩን፡፡ ፈጣሪ ባስመለከታቸው ሁሉ በዘመኑ የማይታመን ድንቅና መልካም ሥራ መሥራታቸውን ነገሩን፡፡

በመቀጠል በስፍራው ሎጅና ሙዚየም ለመስራት በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ባለፈው ዓመት የተጣለ የመሰረት ድንጋይ አየን፡፡ ስራው እንደሚጀመር ተስፋ አደረግን፡፡ በስፍራው ያለውን ታሪክ በቃል ከመገንዘባችን በዘለለ ለምልክት የሚሆን ቅርስ ባለመኖሩ ቅር እያለንንና የቤት ስራ እንዳለብን በመገንዘብ ወደ ደብረብርሃን በእግራችን ጉዞ ጀመርን፡፡ ውይይታችንንም አባላትን በመቀያየር ቀጠልን፡፡ ደብረብርሃንም ከቀኑ 6፡00 ላይ በሰላም ደረስን፡፡ 




 

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...