ማሳሰቢያ፡- ይህ ጽሑፍ የዘንድሮውን የአርበኞች በዓል አከባበር አስመልክቶ
የተጻፈ በመሆኑ የአንዲት ግራርንና የአርበኞችን ታሪክ በጥልቀት አይዳስስም፡፡ ያንን የምትፈልጉ አንባብያን ባለፉት ዓመታት የጻፍኳቸውን
ጽሑፎች እንድታነቡ እመክራለሁ፡፡
በዓል በሚበዛበት በዚህ በሚያዝያ ወር፣ በተለይ በመጨረሻው ሳምንት፣ ስራ
በዝቶብኝ ከረምኩ፡፡ በወሩ የመጨረሻው እሁድ ቅዳሜ የተለያዩ ጥሪዎች ነበሩብኝ፡፡
ሀ. የዩኒቨርሲቲያችን
ባህል ማዕከል ዓመታዊውን አገር አቀፍ ዓውደ ጥናት ያካሂድ ነበር፡፡
ለ. ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት 75ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ ያዘጋጅ
ነበር፡፡
ሐ. የሞጃ አርበኞች ዓመታዊ በዓል ነበራቸው፡፡
መ. የአንዱ ወዳጄ ሠርግ ነበር፡፡
ሠ. የጓደኛዬ ልጅ ክርስትና ነበር፡፡
ሐሙስ
(26/8/9)
ይህን ሁሉ ዝግጅት አብሮ ማስኬድ ስላቃተኝ ተጨነቅሁ፡፡ ዘወትር ሐሙስ
ማታ በሚከናወነው የውይይትና የሥነጽሑፍ ምሽታችን የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ቤተሰቦችን ስለ አርበኞች አወያየን፡፡ በዚሁ
ሳምንት በቤተመጻሕፍቱ የአርበኞችን ሳምንት አስመልክተን በሁሉም የሽያጭ መጻሕፍት ላይ የ10 በመቶ የዋጋ ቅናሽ አድርገን ነበር፡፡
የተወሰኑ ሰዎች ገዛዝተዋል፡፡ እንደሚያነቡም ባለ ሙሉ ተስፋ ነን፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት ታሪክ አዋቂው አቅራቢያችን አቶ አዲሱ ሞላወርቅ
የጅሩ ተወላጅ በመሆናቸው ስለራስ አበበም ሆነ ስለሌሎቹ አርበኞች ሲሰሙ ያደጉ መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ እስኪ ከትምህርታቸው በጥቂቱ
ላቃምሳችሁ፡- ‹‹የአገሩን ታሪክ የማያውቅ ህዝብና አባቱን የማያውቅ አንድ ነው፡፡ ትውልዱ ታሪክ-ጠል እና አባቶቻችን የሚንቋቸውን
አውሮፓውያንን የሚናፍቅ ሆኗል፡፡ ታሪክን ለማሳወቅ ሃላፊነት ያለብን በመሆኑ እንዲያነቡና አባቶቻችን ሳያነቡና ሳይማሩ የአገር እሳቤ
እንዴት እንዳዳበሩ እንዲገነዘቡ ማገዝ ያስፈልገናል፡፡ ስለ አያቶቻችን ሳናውቅ አገራዊ ስሜት ልናሳድግ አንችልም፡፡ አባቶቻችንና
እናቶቻችን ከ1000 ኪሎሜትር በላይ ሄደው ሞተው ያቆዩልንን ታሪክ ለምንድነው የማናቆየውና የማንወደው ብላችሁ እስኪ ጠይቁ፡፡ የኛን
ታሪክ በብዛት የጻፉት ነጮች ናቸው - እንደፈለጉት እያደረጉ፡፡ እኛ ምን እየሰራን ነው?››
ዐስራ ስድስት ሰዎች በተገኘንበት ውይይት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው
ስለነበር እናንተ ያልተገኛችሁት ሰዎች ደግሞ እስኪ ለጥያቄዎቹ የየራሳችሁን መልስ ስጡን፡-
ሀ. ቅኝ ተገዝተናል ወይስ አልተገዛንም?
ለ. መገዛት ነው መወረር የሚለውን ሰው አወቀልን አላወቀልን ምን እንጠቀማለን?
ሐ. የሞሶሎኒ ዕቅድ ተሳክቶ ነበር ወይ?
መ. ስለዚህ ታሪክ ማውራታችን አሁን ምን ይጠቅመናል?
ሠ. ሃገራዊ ስሜት ጠፍቶ እንዴት ጠበን ጠበን ጋጣ ውስጥ መጣን?
ረ. የአሁኑ ትውልድ ስለ ሐገር ሲነሳ የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ለምን
ይላል?
አርብ
(27/8/9))
በማግስቱ አርብ ጠዋት ጉዞ ነበረብን፡፡ ወደ አንዲት ግራር፣ ሳሲት አቅራቢያ፣
በሰላድንጋይ መንገድ፣ እንሄድ ነበር፡፡ ጠዋት መናኸሪያ ደረስኩ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የሚሄደውና ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ከኔ ጋር
የሄደው ሳለአምላክ ጥላሁን መጣ፡፡ እኔም ባለፈው ዓመት ስላልሄድኩ እንደሱው ነኝ፡፡ ቆየት ብላ ሩት መጣች፡፡ የራስ አበበ ቤተመጻህፍት
ባልደረባ ነች፡፡ ከዚያም ለዚሁ ዝግጅት ስትል በዋዜማው ከአዲስ አበባ የመጣችው ብርቱካን ካብትህይመርም ብቅ አለች፡፡
በመጀመሪያ እኔ ሰው ካልመጣ እመለሳለሁ ይል የነበረው መምህር ሳለ አሁን
እየተረጋጋ መጣ፡፡ ቆየት ብለው ሁለት የህግ መምህራን ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ ገጣሚው መስፍን ወንድወሰንና ባልደረባው አብርሃም
ተቀላቀሉን፡፡ ከሆነ አይቀር ብለን ከመናኸሪያው ፊት ለፊት በመሰራት ላይ ባለው ህንጻ ምድር ቤት ላይ ቁርስ እንበላ ያዝን፡፡ የአዲስ
አበባው የማህደረ ሸዋ ልዑካን የሆኑ ሁለት ወጣት ትውልደ -ሞጃ ጋዜጠኞች መጡና ቁርሳቸውን በልተው ወደ ሰላድንጋይ በሚሄደው መኪና
ውስጥ ገባን፡፡ እዚያም ያለ ስራ አልተቀመጥንም ነበር፡-
ሀ. ቼ በለው ኧረ ቼ በለውን እየተቀባበልን ዘፈንን
ለ. ከዚያም ለተሳፋሪው የምናውቀውን የአርበኞች ታሪክ ለማስገንዘብ ተነስቼ ስጀምር መቀዛቀዝ ታየኝ፡፡ ወዲያው አካሄዴን
ቀይሬ በአርበኞች ግጥም መጣሁ - በጥሞናና በፍላጎት መከታተል መጀመራቸውን ሳውቅ ወደ ጉዳዬ ገባሁ፡፡ በጥያቄና መልስም በደንብ
ሊዳብር የቻለ ውይይት አደረግን፡፡
ሰላድንጋይ
ይህች የጠበለተኛ ከተማ እያማረባት ነው፡፡ አዲሱ ህንጻ ንብረትነቱ የአብቁተ ነው አሉ፡፡ መኪናው ከዱሮው በተለየ
መልኩ ይርመሰመሳል፡፡ ባጃጁ ምኑ ቅጡ! ያለ ብዙ ረፍት በቀጥታ ወደ ሳሲት አመራን፡፡ ሳሲት መገንጠያ ባለው የመንግስት አስተዳደር
ጽ/ቤት በአንዲት ፒካፕ መኪና ላይ በርካታ ወጣቶች ተጭነዋል፡፡ የወረዳው የባህል ቡድን አባላት መሆናቸውን ነጋሪ አላስፈለገኝም፡፡
በባንዲራ አሸብርቀው መኪናችንን ተከተሏት፡፡ የሳሲቱ መንገድ አስፋልትን ያስንቃል፡፡ የአገራችን መንገድ በአካባቢችን በሚገኘው ቀይ
አፈር የተሰራ ነው፡፡
ሳሲት
ሳሲቶችን ተዘዋውሬ ሰላም አልኳቸው፡፡ በሁለት ዓመቴ ስላገኘኋቸው ደስ አለኝ፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት በጻፍኩት ማስታወሻ
እንዳስተናገደችን የገለጽኩት እህታችን ዘነበች አስፋው በጸና ታማ ነበር፡፡ አሁን እያገገመች ባለችበት ሁኔታ ሄጄ መጠየቄ ደስ አለኝ፡፡
ራበን ባዩ ስለበዛ ምግብ ቤት ገብተው ምግብ ተመግበው በባጃጅ ወደ አንዲት ግራር አቀናን፡፡ አንድ ባጃጅ አምስት ሰው የምትይዝ
አነስተኛ ታክሲ ነች እዚያ፡፡ ምቹው መንገዳችን አገሩን ለመቃኘት ሁነኛ እድል ሰጪ ነው፡፡
አንዲት ግራር
ግራር ጋ ልንደርስ ትንሽ ሲቀረን ዓለም ገና የምትባል ‹ከተማ› ቢጤ ተቆርቁራ
በማየታችን ለካ ቆይተናል የሚል ስሜት ተሰማን፡፡ ግራር ደረስን፡፡ እኒያ በሩቅ ሲታዩን የነበሩት ሰዎች አሁን ቀርበው ሲያዩዋቸው
ፈገግታቸው ደስ ይላል፡፡ ማንነታቸውም ተረዳን፡፡ የወደቀችውን ግራር ወደ ጎን አድርገን ክብ ሰርተን ቆምን፡፡ የዕለቱ መርሃ-ግብር
በግሩም ሁኔታ ቀጠለ፡፡ የሞጃ አርበኞች ሰብሳቢው የአቶ አያሌውና የወረዳው አፈጉባኤ የአቶ ለጤ ንግግሮች ዝግጅታችንን በጥሩ ሁኔታ
ከፈቱልን፡፡ ከእንግዶች ደግሞ የአዲስ አበቦቹ ጋሻው ደበበና የተክለሐይማኖት ማሞ ተራ ተከታይ ነበር፡፡ ጋሻው ያቀረበው ግጥም አበባበቡም
ሆነ ይዘቱ ግሩም ነበር፡፡ ግጥሙ ልብ ይገባል፡፡ አንዴ እጄን ከደረቴ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከኪሴ ያስደርገኝ ነበር፡፡ ተክለሐይማኖት
ስለ ማህደረ ሸዋ ገለጻ አድርጎ
ዓላማቸውንና የአባላቱን መልዕክት አደረሰ፡፡ በየመሃሉ የሞጃ ባህል ቡድን ውዝዋዜና ግጥም ሌሎችንም ስራዎች አቅርቧል፡፡ አባቶችም
ፉካሮና ቀረርቶ አቀረቡ፡፡ አንድ ካህን ቡራኬ ሰጥተው ዳቦ ቁረስ ተባልኩ፡፡ ‹‹ኧረ አይሆንም ስንት ትልቅ ሰው እያለ›› ብልም
አልሆነም፡፡
ቆረስኩ፡፡ ዳቦ ታደለ፡፡ አረቄም ተሰጠን፡፡ የዘንድሮው በዓል በመንግስት ሃላፊዎች፣ በሞንታርቦና በባህል ቡድን የታጀበ ቢሆንም
ከነዋሪው ህዝብ በኩልና ከተማሪው የቁጥር መመናመን ይታይ ነበር፡፡ አንደኛው ምክንያት በአካባቢው ለቅሶ መኖሩ መሆኑን ሰማን፡፡
አሸዋ፣ ድንጋይ፣ ሲሚንቶና ብሎኬት ተዘጋጅቶለት
የግንባታውን መጀመር እየተጠባበቀ የሚገኘው የአንዲት ግራር አጥር የሞጃ ሃላፊዎች ቀና ውጥን ነው፡፡ በርቱልን፡፡ ይህ ጅምር ብዙ
ስራዎች እንዲሰሩ ሌሎችን ያነሳሳል፡፡
የመልስ ጉዞ
በፒክአፕ መኪናዋ እንግዶቹ ቅድሚያ ተሰጥቶን ወደ ሳሲት አቀናን፡፡ ከዚያም ሳለአምላክ ቤቴን እንዳሳየው በጠየቀኝ
መሰረት ወደ እናቴ ቤት ወሰድኳቸው፡፡ ትንሽ ቀደም ብዬ እንደምንመጣ የነገርኳት ታናሽ እህቴ ጋበዘችን፡፡ ቡና ተፈላ፡፡ አያቴንም
አገኘኋት፡፡ ደስ የሚል ጊዜ አሳልፈን እንግዶቼን ሰላድንጋይ ድረስ ሸኝቼ ልመለስ መኪና ውስጥ ገባን፡፡ ሰላድንጋይም በገና ሆቴል
ወረዳው ሌላ ግብዣ አዘጋጅቶ ኖሮ በጥሩ ሁኔታ ተጋበዝን፡፡ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን፣ የአፈ- ጉባኤና የባህል ጽ/ቤቶች ሰዎች ለእኛ
ሲሉ ተፍ ተፍ ሲሉ ስለነበር ውለታቸው አለብን፡፡ እንግዶቼን ወደ ደብረብርሃን ሸኝቼ ወደ ሳሲት ልመለስ ነው ሰል ጋዜጠኞቹም እኛም
ልንመለስ ነው አሉ፡፡ ሦስታችን ተመልሰን በተክለሐይማኖት ቤት አመሸን፡፡ እስከ ሦስት ሰዓትም አቶ ደምሴ ስለአርበኞች ግሩም ትምህርት
ሰጡን፡፡ አንድ የሚሳሳቱት ነገር የለም፡፡ እኔ እንዲያውም ለእርሳቸው ቃለመጠይቅ ማድረግ ከአቅማችን በላይ መሆኑን ነግሬያቸዋለሁ፡፡
ወደ ቤቴ ሄጄ ከቤተሰብ ጋር ስጫወት ቆየሁና ሌሊቱን ይታይ የነበረ አንድ ጽሑፍ ስለነበረኝ ሳይ አደርኩ፡፡ በማግስቱም ዘመዶቼን
ጠያይቄ ጠዋት 3፡30 ወደ ሰላድንጋይ ሄድኩ፡፡ እዚያም ዘመድ ጠያይቄ ሰመሻሽ ወደ ደብረብርሃን ተመለስኩ፡፡ ብዙ የተዘነጋ ነገር
ሊኖር ይችላል፡፡ የነበራችሁ ሰዎች በአስተያየት አዳብሩልኝ፡፡ በመጨረሻም አርበኞቻችንን ያከበርነው ሁሉ የዚህ ዘመን አርበኞች ነን፡፡
ተቃዋሚ አለ?