ለእናቴ ስደውል በባዶ ቤት እያጣጣርኩ ነው ያለችኝ የትናንትናዋ አስደንጋጭ ምሽት
እናታችሁን እያሰባችሁ አንብቡት
ህዳር 26፣ 2015 ዓ.ም.
መዘምር ግርማ
በፊት በፊት ስልክ ያለው የቤተሰብ አባል ደውሎ ከእናቴ ጋር ያገናኘኛል እንጂ ስልክ አልነበራትም፡፡ ከተወሰኑ ወራት ወዲህ ግን እህቶቼ አነስተኛ ስልክ ስለገዙላት በወር አንድ ቀንም ቢሆን እደውልላለታሁ፡፡ ስደውል በደስታ ታናግረኛለች፡፡ ቤተሰባዊ ጉዳዮችን እያሳሳን እናወራለን፡፡ ማን እንደወለደ፣ ማን እንደተጣላ፣ ማን እንደታረቀ ወዘተ አውርተን እንሰነባበታለን፡፡ ሰሞኑን ግን ስልኳ አልሰራ አለኝ፡፡ ሳምንቱን በሙሉ ቢያንስ በየቀኑ ስደውልና አልሰራ ሲለኝ ከርሜያለሁ፡፡ ለሌሎች ስደውል የቻርጅ ችግር ነው ይሉኛል፡፡
ለብዙ ዘመን ከቤተሰቤ ጋር ቅርርብ የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ ለዓመታት የእናቴ ስም የጂሜል አካውንቴ የይለፍ ቃል ነበር፡፡ የእናቷ ስም ደግሞ የያሁ አካውንቴ ይይለፍ ቃል ሆኖ ነበር፡፡ ስለሆነም በየቀኑ ምናልባትም በቀን ብዙ ጊዜ አስታውሳቸዋለሁ፡፡ በፈረንጆቹ 2017 መግቢያ ላይ ቤተሰብ ላይ አንድ ጠንከር ያለ ትችት ያዘለ ጽሑፍ በእንግሊዝኛ ጽፌ ያስነበብኳት አንዲት ጓደኛዬ ‹‹ተዉ፣ እንደዚህ አትጻፍ፤ እኝህን አሮጊት ተዋቸው፡፡ የይቅርታ መጽሐፍ ተርጉመህ ቂም አትቋጥር!›› ብላኛለች፡፡ ጽሑፉን በእንግሊዝኛ ያደረኩት ቢያንስ ቤተሰብ አግኝቶት አንብቦት እንዳይቀየመኝ ነበር፡፡ ትንሽም ብትሆን የምታያይዘን ክር እንዳትበጠስ ብዬ ነበር፡፡
ትናንት ምሽት የቤተመጻሕፍቴን የታዳጊ ልጆች የሥነጽሑፍ ሥልጠና ስጨርስ ምልባት ብዬ ብደውልላት ስልኳ ጠራ፡፡ ግን አይነሳም፡፡ ከቤተመጻሕፍት ኮተቴን ይዤ እቤት ስደርስ ሰሞኑን ከባህርዳር መጥቶ እቤቴ አብሮኝ ሲዞርና ሲያድር የከረመውን ጓደኛዬን እኩለቀን ላይ ስለሸኘሁት ቤቱ ጭር አለብኝ፡፡ ሆቴል ሄዶ መቀመጥ ስለተደጋገመብኝ የእግር ጉዞ ላድርግ እያልኩ እያሰላሰልኩ ሳለ ነበር ከባህርዳሩ ጓዳዬ ጋር የዓለም ዋንጫ ስናይ የከረምነው ሌላ ጓደኛዬ የደወለው፡፡ ሄድኩ፤ ተዝናናሁ፤ ኳስ አይቼ መጣሁ፡፡
የሆነ የሚነግረኝ ነገር ኖሮ ይሁን አላውቅም ይህን ያህል ደጋግሜ ደውዬላት አላውቅም፡፡ ወንድሞቿ ወይም ጎረቤት ደህንነቷን ይነግሩኛል፤ አበቃ! ከምሽቱ 2፡45 ላይ ደወልኩላት፡፡ ተነሳ፡፡ እያቃሰተች ታወራኛለች፡፡ ስለ ስልኳ ሁኔታ ነገረችኝ፡፡ ቀጭኗ ቻርጀር ደብረብርሃንም ስትፈለግ ስለጠፋች ነው ሳትለኝ አልቀረችም፡፡ ስልኩ ባትሪው ድንገት እንደሚዘጋና እስካለ ድረስ እንደምናወራ አሳወቀችኝ፡፡
እኔም ቶሎ ቶሎ ሁኔታውን ጠየኳት፡፡ ቀኑን ሙሉ ደህና ስትሰራ መዋሏን፣ ከሰዓት በኋላ እንጀራ ስትጋግር መቆየቷን፣ ምናልባት ሞቃት ልብስ ስላለበሰች ብርድ መቷት ሊሆን እንደሚችል መጠርጠሯን ወዘተ ነገረችኝ፡፡ ያወራነው አምስት ደቂቃ አይሞላም፡፡
‹‹መዘምር፣ ከባሰብኝ እንድነግርህና ሰው እንድትጠራልኝ ግማሽ ሰዓት ቆይተህ ደውል፡፡››
‹‹ለምን አሁኑኑ ለወንድሞችሽ አልደውልላቸውም››
‹‹አይ አሁን ደህና ነኝ፡፡ ምንም አይለኝ፡፡ በኋላ ደውልልኝ፡፡››
ይህን እንደሰማሁ ማድረግ ያለብኝ አስቸኳይ ነገር ምንድነው ብዬ አሰብኩ፡፡ ያንን እያሰብኩም ማልከም ኤክስ ትዝ አለኝ፡፡ በጣም ብዙ የግልና የፖለቲካ ችግር ያሳለፈ ጥቁር አሜሪካዊ ታጋይ ነው፡፡ ልጆቿ አቅም በሌላቸው ሁኔታ እናቱ በአእምሮ ህመምተኞች ማገገሚያ ገብታ በነበረበት ጊዜ ሊጠይቃት ሄዶ በህመሟ ምክንያት ማንነቱን ልታውቅ ስላልቻለች በጣም አዝኖ ነበር፡፡ ቃል በቃል ባላስታውሰውም ያቺ ዘጠኝ ወር በማህጸኗ ተሸክማ የተንከባከበችኝ፣ ያቺ በከባድ ምጥ የወለደችኝ፣ ያቺ ስለ ዓለም ምንም በማላውቅበት ጊዜ ያበላችኝ፣ ያጠበችኝ፣ ሽንቴን ልብሷ ላይ ስሸና የማትጠየፈኝ .. እናቴ አይታኝ ማንነቴን ሳታውቀው ስትቀር የሚሰማኝን ስሜትና የልብ ስብራት ማን ይረዳልኛል መሰለኝ ያለው፡፡
ከተረጎምኩት መጽሐፍ ዳማሲንንንም ያስታወስኩ መሰለኝ፡፡ ከቤተሰቡ አባላት ሦስቱ ማለትም እናቱ፣ አባቱና ታናሽ ወንድሙ በሩዋንዳው የዘር ማጥፋት በግፍ መገደላቸው ተነግሮት ምናልባት ለሕይወት ልትኖር ትችላለች ብሎ ለገመታት ለታናሽ እህቱ ከመሞቱ ሰዓታት በፊት የጻፈላት በእንባ የታጀበ ደብዳቤ፡፡ ታሪኩን ለማታውቁት በኋላ እህቱ ደብዳቤውን አግኝታዋለች፡፡
አንድ ጨካኝ ሰውም አስታወስኩ፡፡ መለስ ዜናዊ ነው፡፡ በአንድ ለዩቱብ ቪዲዮ በተሰጠ የጽሐፍ ምላሽ ነበር፡፡ ቪዲዮው መለስ ዜናዊ ስላካበተው በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት የሚተርክ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይላል ቪዲዮውን ያዘጋጀው ተራኪ፤ ይሁን እንጂ መለስ ዜናዊ ይህ ሁሉ ሀብት እያለው እህቱን ጠላ ሻጭ፣ ወንድሙን ደሃ መምህር አድርጓቸዋል ይላል፡፡ ብዙ አስተያየት የተሰጠው ቢሆንም አንዱ ግን ‹‹ይህ ሰውዬ ቢሊየነር ሆኖ ሳለ፤ ገንዘብ እንደማይዘርፍ ለማሳያ ይሆኑት ዘንድ ለቤተሰቡ ምንም እገዛ አለማድረጉ ምን ያህል ጨካኝ እንደሆነ ያሳያል›› የሚል ነበር፡፡ እኔ ቢያንስ ብር ባይኖረኝ ለቤተሰቤ ጊዜ ስላልሰጠሁ ሌላ ጨካኝ ሳልሆን አልቀርም፡፡
የሆነው ሆኖ በትናንትናዋ ምሽት እናቴ ጣር ላይ መሆኗን ከነገረችኝ በኋላ ጨካኙ ልቤ እራራ፡፡ ምንነቱን የማላውቀው ስሜት ወረረኝ፡፡ በሃዘን ተውጬ ምንም ሳላደርግ አልቀረሁም፡፡ ተረጋግቼ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ሳስብ ሁለት አማራጮች መጡልኝ፡፡ አንደኛ ለወንድሞቿ መንገር፡፡ ቅርብ ስለሆኑ ሄደው እንዲያስታምሟት፣ ሐኪም እንዲጠሩላት፣ እንዲደግፏት፣ ዉኃ እንዲግቷት … ሌላኛው አማራጭ አፋጣኝ ምላሽ አገኝ ዘንድ ወደ ኢንተርኔት ገብቶ ማንበብ ነው፡፡ ሁለተኛውን አማራጭ ወሰድኩ፡፡ ላፕቶፔን፣ ታብሌቴንና ስልኬን ከፍቼ ወደ ጉግል አቀናሁ፡፡ ጊዜ ለመቆጠብና በአጭር ጊዜ ብዙ ሃሳብ ለማግኘት ሦስቱም ላይ የተለያዩ ሃሳቦችን ጻፍኩ፡፡ እነዚህ ናቸው፡-
‹‹በዕድሜ የገፋች ሴት ድንገት ሆድ ህመም ሲያማት››
‹‹ለድንገተኛ ሆድ ህመም የቤት ውስጥ መፍትሔ››
‹‹ቶሎ የሚገድሉ የሆድዕቃ አካባቢ ህመሞች››
በእርግጥ ህመሟን ስትነግረኝ ማስታወሻ ስይዝና ሆዷ የትኛው አካባቢ እንደሚያማት ስጠይቃት የተጠቀመችው የአማርኛ ቃል ትርጉም በሚገርም ሁኔታ አልገባኝም ነበር፡፡ ቃሉንም አሁን እረሳሁት፡፡ የተረዳሁት ግን ሁሉንም የሆዴ አካባቢ ብዬ ነው፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ ሆድዕቃ በሚል ለመጠየቅ ተገደድኩ፡፡ ደግነቱ ደግሞ በታብሌቴ የከፈትኩት ጉግል በአንድ ጊዜ ወደጎን እያሳለፍኩ በማነብበት ሁኔታ ምክንያቶቹን በአጭሩ ደረደራቸው፡፡ እኔም በማጠቃለያ መልክ የቀረቡትን ተጭኜ በመክፈት ዝርዝሩን ለማንበብ አልደፈርኩም፡፡ የስልኬንና የላፕቶፔንም መልሶች ማስታወሻ ላይ ጻፍኩ፡፡ ስለሚሰማት ነገር መጠየቅ ያለብኝን አወቅሁ፡፡ ያንን ስትነግረኝ ደግሞ ስልኩ ሳይዘጋ የበለጠ መረጃ ከኢንተርኔት በማግኘት የችግሩን ትክክለኛ ሁኔታ መረዳትና መፍትሔ መፈለግ እችላለሁ፡፡ ስለ ችግሩ በትክክል ባላወኩበት ሁኔታ ሰውም ብጠራ የባህል መድኃኒት ምናምን እያሉ የሚያባብስ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
በግምት ከአስር ደቂቃ ካልበለጠ ቆይታ በኋላ ደወልኩላት፡፡ አነሳቸው፡፡ ተሽሎኛል ብላ የሚሰማትን ነገረችኝ፡፡ ለማንኛውም ብዬ የያዝኳቸውን ጥያቄዎች ጠየኳት፡፡ ስትንቀሳቀስበት ህመሙ ይብስባት መሆኑን፣ ትኩሳት እንዳለው፣ ያስመልሳት እንደሆነ፣ እብጠት እንዳለው ጠየኳት፡፡ ምናልባት ትርፍ አንጀትም ከሆነ ብዬ ሳጠራ የሱም ምልክት አይሰማኝም አለች፡፡ ዉኃ መጠጣትን ስለመሳሰሉ ቀላል መፍትሔዎች አነሳሳሁላት፡፡ መዳኗን ነገረችኝ፡፡ በነገረችኝም ምልክት መዳኗን እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
አስረኛ ክፍል ሆነን ይመስለኛል በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ላይ የቀረበ አንድ ምንባብ ትዝ አለኝ፡፡ ይኸውም አንድ የአነስተኛ አውሮፕላን ፓይለት ድንገት ራሱን ስለሳተ አውሮፕላኑ ሊከሰከስ ባለበት ጊዜ ከመንገደኞቹ አንዱ ስለ ማብረር ምንም በማያውቅበት ሁኔታ በሬዲዮ ከበረራ ተቆጣጣሪዎች ጋር በመደዋወል አውሮፕላኑን እንዴት እንዳሳረፈውና ህይወታቸውን እንዳዳኑ ነው፡፡ በርቀትም ቢሆን፣ ሙያውም ባይኖረን ምናልባት ቴክኖሎጂን ተጠቅመን መፍትሔ እንሰጥ ይሆናል፡፡ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፡፡
ከዚያ በኋላ ከሃያ ደቂቃ ለሚበልጥ ጊዜ አወራን፡፡ ደውለን የማናውቀው ሦስት ልጆቿ በደቂቃዎች ልዩነት መደወላችንንና የአጋጣሚውንም ነገር ነገረችኝ፡፡ እኔም እርስበርስ ሳንደዋወል ሦስታችንም በአስር ደቂቃዎች ውስጥ ለእናታችን የመደወላችን ነገር ገረመኝ፡፡ ቴሌፓዚ የሚባለው ነገር የእናታችንን መታመም አሳውቆን ይሆን? እኔ ለታመመ ሰው የመድረስ ገድ እንዳለኝ ነገርኳት፡፡ አንድ ቀን አያቴ ታማ ደረስኩ፡፡ ሦስት ቀን ታማ መተኛቷንና ሰውነቷን ከሁለት ከፍሎ እንደሚያማት ነገረችኝ፡፡ ከዚያም ቢያንስ ያንን አስፈሪ ድባብ የሰፈረበትን ጨለማ ቤት የሚያሟሙቅና ህመሟን የሚያስረሳ ነገር መጣልኝ፡፡ ሴቶቹን ልጆች ከያሉበት ጠራርቶ ቡና ማስፈላት፣ ምግብ ማቅረብና ቤቱን ሰው ያለበት ማስመሰል፡፡ ተጫወትን፤ በላን፤ ጠጣን፡፡ እማማም ህመሜ ለቀቀኝ አለች፡፡ የእማማ ህመም በሰው መረሳት ሆኖም ሊሆን ይችላል፡፡ አርባ ልጅና የልጅ ልጅ እያላት ዘወር ብሎ የሚያያት አጥታ፡፡
ከእናቴ ጋር ስንነጋገር ቆየን፡፡ ህመሟ ባይሻላት ኖሮ ወደ ሳሲት በማግስቱ ልሄድ አስቤ እንደነበር ገለጽኩላት፡፡ ለመሄድ የፈራሁት ግን ከዛሬ ጀምሮ በደሞዝ ጥያቄ ምክንያት የዩኒቨርሲቲ መምህራን የስራ ማቆም አድማ ስለተጠራን ፈርቼ የምሄድ እንዳይመስልብኝ መሆኑን ነገርኳት፡፡ ስለዚህም ጉዳይ ስናወራ ባለፈው ሳሲት እንደወረድኩ ደሞዜ ስምንት ሺ ብር ነው ስላት ያዘነችልኝን አስታወሰች፡፡ ስላለንበት አሳዛኝ ሁኔታም መረዳቷን አሁንም ገለጠችልኝ፡፡ እህል እንድጭን ብትነግረኝም እሺ አልልም፡፡ ምንስ አደርገዋለሁ! በመስከረም ወር ለሳሲት ቡክ ክለብ ውይይት ሄጄ ሳለ እሷ ቤት አድር ስለነበር ምግብም የበላሁት እዚያው ነበር፡፡ በአጋጣሚ ከያዝኩት ብር 200 ብር ስለቀረኝ ኤቲኤምም ስለሌለ ስቸገር አይታ ብር ልስጥህ ብላኝ ነበር፡፡ እኔም በዚች እሳፈራለሁ ብዬ በእምቢታ ጸናሁ፡፡ ለውይይት በየወሩ እመጣለሁ ብዬ ቃል ገብቼላት ያልሆነ መሰናክል ጋርጠውብኝ ቀረሁ፡፡ ከንባብ ዓላማ ማስፋፋት አንጻር ጫጫና ሸዋሮቢት፣ ማለትም ጠራና ይፋትን እየተሽከረከርኩ ተጉለትን በዓይኔ ገርምሜ አልፋታለሁ፡፡
አያይዤም መምህራን ጓደኞቼ በፊት በየወሩ ለወላጆቻቸው አንድ ሺ ብርና ከዚያ በላይ ተቆራጭ ሲልኩ የምሰጠውን አስተያየት ነገርኳት፡፡ ይህን ብር በወር ከመላክ የዓመቱን ወይም የሁለት ዓመቱን አድርገው ትርፍ የሚያስገኝ ስራ፣ አክስዮን ወይም አንድ የተሻለ ቋሚ ነገር ቢያደርጉላቸው እንደሚሻል እነግር እንደነበር አስታወስኳት፡፡ ምክንያቴም ጥገኝነትን ማስተማር እንደሌለብን ማስታወስና የኛም ኑሮ እየባሰበት ቢሄድ መርዳት ቢሳናቸው ቤተሰብ ችግር ላይ እንዳይወድቅ በማሰብ ነው፡፡ አሁን የደረስንበትን ልብ ይሏል፡፡ እኔ በፊትም አልረዳ አሁንም ዝም ነው፡፡ እናቴም መምህሩ ያለበትን ችግር እንደምትገነዘብ ነገረችኝ፡፡ እሷ እንኳን አምስት ቦታ መሬት ያላት ከበርቴ ነች፡፡ እህል ችግር እንደሌለባትና እንዲያውም ለልጆቿ እንደምትሰጥ አውቃለሁ፡፡ በቅርቡ ከአንዲት ከተዋወኳት ልጅ ጋር ጠላ እየጠጣሁ ስናወራ ከወሬ ወሬ ስለ እናቴ ተነስቶ ከዓመት በፊት እናቴ የጠየቀችኝን ነግሬያት ነበር፡፡ ‹‹መዘምር፣ ጤፍ ልሽጥ እንዴ›› ስትለኝ ‹‹አዎ፣ ሽጪ፡፡ ሃምሳ ብር ገብቶልሻል›› ነበር ያልኳት፡፡ ለልጅቱ ይህን እንደነገርኳትና ስትሰማ እንደወቀሰችኝ ለእናቴ ነገርኳት፡፡ እናቴም ምንም እንዳላስብ አሳስባ በወቅቱ በተቻለኝ መጠን እንደረዳኋት አስታውሳ አመሰገነችኝ፡፡
እናቴ ለኔ ጥሩ አመለካከት ያላት ሰው ነች፡፡ አንድ ቀን የአማርኛ የእጅ ጽሑፏን ለማየት ብዬ እስኪ እዚህ ወረቀት ላይ ጻፊ ስላት የጻፈችው ‹‹መዘምር ጎበዝ ነው›› የሚል ነበር፡፡ ትረካ መተረክ ስለምትችል በሷ ተስቤም ይሆናል ቋንቋና ሥነጽሑፍ ያጠናሁት፡፡ እሷ ለእኔ ጥሩ አመለካከት አላት ብቻ ሳይሆን ሰውም ለኔ ያለው ይመስላታል፡፡ አንድ ጊዜ ‹‹ሳሲት አንተን የሚጣላ የለም›› ያለችኝን አስታወስኩ፡፡ ለረጅም ጊዜ ለትዳር ጥሩ አመለካከት አልነበረኝም፡፡ አንደኛው ምክንያት ምናልባት አሷና አባቴ ጥሩ ትዳር ስላላሳዩንና ስለተፋቱ ይሆናል፡፡ እንዳገባና እንድወልድ በተደጋጋሚ መክራኛለች፤ ለምናኛለች፤ ምክሩን በአንደኛው ጆሮዬ ሰምቼ በሌላው ባፈሰውም፡፡ ሌላ ሰው ከአንገት በላይ ቢመክርም የእናት ግን ልባዊ ነው፡፡
ብዙ ቤተሰባዊ ነገር አውግተንና ደህና መሆኗን ነግራኝ ተሰናበትን፡፡ ዕውቀትን አምኜና ተጠቅሜ፣ እናቴን ከሞት አፋፍ ለመመለስ ተጣጣርኩ፡፡ አጋጣሚው ግን መፍትሔውንም ሳልነግራት በራሷ ጊዜ ዳነችልኝ! ይህ አጋጣሚ ለሁላችንም የሚሰጠው ትምህርት አለ፡፡ ይኸውም ቤተሰቦቻችንን መተው እንደሌለብን ነው፡፡ በስራ ጉዳይ ትተናቸውም ከሆነ ይህንን ነገር ቆም ብለን እናስብበት፡፡ ስራስ የሚባለውን ነገር ቆም ብለን ልናስብበት አይገባም ወይ? ቤተሰብን ከበተነ ምኑን ስራ ሆነ? እኔም በቅርቡ የተወሰነ እየጻፍኩበት ያለው ጉዳይ በዚህ በገጠር-ጠልነት ምክንያት ወይም በአገሪቱ የስራና ኑሮ ስሪት ምክንያት አዛውንቶችን ገጠር ጥሎ ወደ ከተማ እየኮበለለ ስለሚከማቸው ወጣት ጉዳይ ነው፡፡ ጊዜና ሁኔታ ከፈቀደ የችግሩን መጠን ለመቀነስ የማበረክተው ነገር አለኝ፡፡ ጉዳዩም በአእምሮዬ ከተጠነሰሰ ቆይቷል፡፡ አንድ ምሳሌ ባነሳ አንድ ጊዜ ወጣት ሴቶች በአንድ ትልቅ መስሪያ ቤት ግቢ ሳር ሲያርሙ አየሁ፡፡ ጠጋ ብዬ ተዋወኳቸው፡፡ ከሳር ውስጥ አረም ሲያርሙ ምን እንደሚሰማቸው ጠየኳቸው፡፡ ዓላማው ይገባቸው እንደሆነም ተነጋገርን፡፡ በቀልድ ‹‹የአባታችሁ ጤፍ የሚያርመው ጠፍቶ፣ እናንተ እዚህ ከተማ ገብታችሁ ሳር ታርማላችሁ›› ስላቸው ሳቁ፡፡ ተለያየን፡፡
ለስንብት፡፡ ሳሲት አጎቴ ጋ፣ ዘመድ አዝማድ ጋ ዛሬ ጠዋት ደወልኩ፡፡ ተጠያየቁ አልኳቸው፡፡ እናቴም ጠዋት ሄዳ የተከሰተውን እንደነገረቻቸው ነገሩኝ፡፡ አንድ ሰውና አንድ ቁና እህል እንደማያስተማምን ነገሩኝ፡፡ ልጆቻቸውን ወደ ከተማ እንዳያሰድዱ መከርኳቸው፡፡ በነሱ ጥረት ይሳካ ይሆን?