ሰኞ 21 ኖቬምበር 2022

ሚስት የማይገኝባቸው 12 መንገዶች - ትናንት ለመጻሕፍት አሰባሳቢው ቡድን እንደተረኩትና እንዳዝናናኋቸው


ሚስት የማይገኝባቸው 12 መንገዶች

ትናንት ለመጻሕፍት አሰባሳቢው ቡድን እንደተረኩትና እንዳዝናናኋቸው

 

ትናንት እሁድ የኑዛዜ ቀን ነበር፡፡ ለአምስት አናዘዙኝ፡፡ እኔ ለራሴ በዋዜማው ቅዳሜ አመሻሽ በአዳራሽ አረቄ ቤት አረቄየን ስለጋ፣ ማታ በሸገር ሃውስ አዝማሪ ቤት ሐበሻ ቢራዬን ስጠጣ፣ እሱ ሰልቸት ሲለኝ ከግራና ቀኝ እንደ መላዕክት ከከቡቡኝ ጓደኞቼ አራዳ ቢራ በተለያየ ጣዕም ሳጣጥም ነበር፡፡ አዝማሪ አንኮበሬው እያለ ያሞጋግሰኛል፡፡ የዱሮ ጓደኞችህ የት ሄዱ ይለኛል፡፡  

ጠዋት ሲነጋ አንድ ሰዓት አልፏል፡፡ ድንግጥ ብዬ እቤቴ ማን እንዳመጣኝ ራሴን ጠየኩ፡፡ ለጓደኞቼ ደውዬ ጫፍ ጫፉን ተረዳሁ፡፡ ወደ ጫጫ መሄድ እንዳለብኝ የገባኝ ከአፍታ በኋላ ነበር፡፡ ቅሌን ጨርቄን ሳልልና ስጨናበስ የጫጫ መኪና ይዤ በአጭር ጊዜ ደረስኩ፡፡ የማታው ስካር አልለቀቀኝም፡፡  ከተማዋን ስቃኝ ቆይቼ እንግዶቻችን መንበረ ሆቴል መሆናቸውን ነገሩኝ፡፡ ሄጄ ስጋ ሲበሉ አየሁ፡፡ አወራን፡፡ ያው ጠዋት መብላት ስለተውኩና ቀን ቀን የመመገብ በቀን አንዴ ተመጋቢ ስለሆንኩ፡፡ በኋላ ቤተማርያምም ደረጀም መጡ፡፡ ከአፍታ በኋላ ወደ ምኞቴ ፀሐይ ቤተመጻሕፍት አቅንተን ከአዲስ አበባ የመጣውን 1500 መጽሐፍ በቅርቡ ባሰራናቸው ሦስት መደርደሪያዎች ላይ ደረደርን፡፡ እኔ እንደሆንኩ አሁንም እንደተጫጫነኝ ነኝ፡፡ ሁለት ቁርስ ዳቦና ሁለት ሻይ ወደምሳ ሰዓት ላይ ወሰድኩ፡፡ ተሰናብተን ወደ ደብረብርሃን ሄደን የጌጤ ዋሚ ወደሆነው ጌትቫ ሆቴል ጎራ አልን፡፡

በጌትቫ ሆቴል የደብረብርሃኑ የመጻሕፍት ማሰባሰብ አመንጪና ከቡድኑ አስተባባሪዎች አንዱ ቤተማርያም ብዙ ምግብ አዘዘልን፡፡ በረንዳ ላይ በተዝናኖር በላን፡፡ መጠኑ በጣም አነስተኛ ቢሆንም ጣፋጭ ነው፡፡ ከሥጋ ውጪ ብዙም የላቸውም፡፡ ስንት ሺ ብር ከፍሎ እንደሆነ እሱ ነው የሚያውቀው፡፡ ለምሳ ብዙ ሰዓት ቢያቆዩንም አይቆጨንም፡፡፡ የሆነው ሆኖ አለ ዶክተር …

 የሆነው ሆኖ ምግቡ እስኪመጣ ድረስ ብዙ ወግ ተወጋ፡፡ ቀልድና ጨዋታ ይችላሉ፡፡ ሁለት ሴትና ሁለት ወንድ አባላት ያለው የአዲስ አበባ ቡድን አጋፋሪውን በዋና ጨዋታ አመንጪነት የመደበ ይመስላል፡፡ ሌሎቹ ለማድመጥና በየመሃሉ ሃሳብ ለማቀበል ይመስላል አመጣጣቸው፡፡ ከሳቅ ከጨዋታው በኋላ አንድ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በሃንጎቨር ሲሰቃይ የነበረ ሰው ስካሩ ወጣለት፤ የጨዋታውን መሪነት ተረከበ፡፡ እኔው ነኝ፡፡

በቅርቡ ከአንድ ያገር ውስጥና ከአንድ የዉጪ ታዋቂ ሰዎች ጋር ፍቅር እንደያዘኝ በፌስቡክ ማስነበቤን በመግለጽ ሳቅ አስጀመርኳቸው፡፡ እንዲያው ደግሞ በሞቴ የአዲስ አበባው ቡድን ፎቶፎቢክ ስለሆነ መሰለኝ ፎቶው ከእጄ ሊገባ አልቻለም፡፡ ብቻ ቀብረር ያሉ አራት የአዲስ አበባ አራዶችን እየሰባችሁ አንብቡ፡፡ በአዲስ መስመር፡፡

ያወጋሁትን ሁሉ ሞገቱ፤ የመጻፍ ፍላጎት አለኝ ስላቸው ብትጽፈው ጥሩ ነው አሉኝ፡፡ አሁን ይህ ምኑ ይጻፋል! እስኪ ፍረዱ፡፡

1.     - ሴቶችን እንደ እህት ማየት

ሁለት ናቸው፡፡ ቀይና ጥቁር የአምላክ ፍጡር አለ አሉ በጋምቤላ ቄስ መስሏቸው ባርከን ብለው ያስገደዱት ሰው ቅዳሴና ቡራኬ ሲጠፋው፡፡ ቀይና ጥቁር፡፡ ሁለቱንም እንደ እህት ስለተቀበልኳቸው በፍቅር ዓይን ማየት ተስኖኛል፡፡ እነሱንና ሌሎችን እንስት አሜሪካውያን በጎፈቃደኞችን ይዤ በየአረቄ ቤቱ፣ በየጠጅ ቤቱ፣ በየአዝማሪ ቤቱ ስዞር ‹‹አይ የሴት ልጅ ጡር!›› ይለኛል የኦሮምኛ መምህሬ፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ‹‹አንቺ እባክሽ እሱን ጠብሰሽ ሁለት ዓመት ኮንትራትሽን አራዝሚ፡፡ እንደሚወድሽ አውቃለሁ፡፡ ሲያይሽ፣ ስምሽን ሲጠራ ላይጣል!›› ትላለች አንዷ፡፡ ሁለታችንም መሬት መሬቱ እያየን መሽኮርመም!

2.     - መኝታ ያጡ ሴቶችን ማሳደር

አንድ ቀን አንዷ በጎፈቃደኛዋ ደብረብርሃን መሸባት፡፡ አንተ ቤት አሳድረኝ አለችኝ፡፡ ያው እኔ ራሴ እንደ በጎ ፈቃደኛ እታያለሁ - እንደ ሠላም ጓድ፡፡ ድንክ አልጋ አለችህ ወይ ብላኝ ነበር፡፡ ቤት ያፈራውን የኔን አልጋ ተጋራን፡፡ እኔ አልጋ ልብሱን፣ እሷ ብርድ ልብሱን ለብሰን፡፡ አንድ ጠርሙስ አረቄ ሾሜላት ስትጠጣና ፊልም ስታይ አደረች፡፡ Both of us were sober! እኔም አረቄ አያሰክረኝ-  እንኳን ሳልጠጣው፡፡ እሷም ዋና ጠጪ ነች፡፡ ያው ከአሜሪካውያን በአንዴ ሁለት ወይም ሦስት ትኩስ መጠጥ መጠጣትን፣ ለምሳሌ ቡና፣ ሻይና ወተት፤ አልፎ አልፎ የኢንሳኒቲ እንቅስቃሴ መስራትን፣ ለበጎፈቃድ መትጋትን ስለተማርኩ ያንን በተገበርኩ ቁጥር አስታውሳቸዋሁ፡፡ የሳሲቷ አክሰቴ ዓለምፀሐይ አበበ ‹‹አንተንማ ከልጃገረድ ጋር ነበር ቤት ውስጥ መዝጋት!›› እያለች ታበሽቀኛለች፡፡ ልጃገረድ የሚባል ጉዳይ እንደሌላ አምናለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ከማንም ጋር ብትዘጊኝ አይሆንም፡፡ ይቺ እኔ ቤት ያደረችዋ እኮ ምናልባት ሴቶችን እንጂ ወንዶችን በፍቅር የማታይ ትሆናለች፡፡ ብታይስ ማን ያያታል!

3.     - አንደኛው የዚህ ዓመት ግቤ ግላዊ ዕቅዶቼን ማሳካት ነው፡፡ ያው የምትወቅሱኝ ሦስት በ‹ት› ፊደል  የሚጨርሱ ነገሮች፡፡ ሳለአምላክ መቼም ለጠባሴው ገብርኤል የተሳለውን በሬ አይረሳውም፡፡ ለጥምቀት ያደርሰው ይሆናል፡፡ ሁለተኛው የበጎፈቃደኝነት ግቦቼን ማሳካት ሲሆን በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት አምሳል የግል አብያተመጻሕፍትን በአገራችን ማስፋፋት አንዱ ንዑስ ክፍል ነው፡፡ በአማራ የሠላም ጓድ በኩል የምሰራው የበጎፈቃድ ስራ ሌላው ነው፡፡ እና ሚስት የማይገኘበት መንገድ የእስከዛሬው ስለሆነ ሌላ መንገድ መቀየሴን ነገርኳቸው፡፡ ያም መንገድ የምመርጣትን የሚስት ዓይነት የያዘና ውጤትና አማራጭ እያመጣ ያለ ሲሆን ለጊዜው ምስጢር አድርጌ ይዤዋለሁ፡፡

4.        -  ቆንጆ ሴት ስታይ ተጀንነነህ ማለፍን ተማር፡፡ አጠገቧ ስትቀርብ አትወለካከፍ፡፡ አትሽቆጥቆጥ፡፡ ብታናግርህም ጉዳይዋን ሰምተህ አስተናግድ እንጂ ወደ ፍቅር ለመቀየር አትሞክር፡፡ ቆንጆይቱ ያንተ ላትሆን ብትችልስ? ቆንጆ ሚስት ያለችውና እሸት የዘራ ብቻውን አይበላም እንዲሉ ይቀጣጥፉልሃል፡፡ ብዙ ዓመት የለመደች ማጋጣ ትሆንና አመሏ አይለቃት ይሆናል፡፡ አንዱ ልጅ እንዳለኝ ብዙ ዓመት የወሊድ መቆጣጠሪያ ከተጠቀመች ላትወልድ ትችላለች ብሎ ይሰጋል፡፡ አዎ የዛሬ ልጅ በ15 ዓመቷ ጀምራ ለ15 ዓመታት ተጠቅማ ይሆናል፡፡ ልክ ነው ልጁስ! ከታች ይብራራል፡፡

5.     - ከታች ክፍል ጀምሮ በትምህርትም ሆነ በንባብ የሰማሁትን ሁሉ የመቀበል አዝማሚያ ስላለኝ ብዙ ሃሳቦችን ወደ ሕይወቴ አስገብቻለሁ፡፡ ወስኛለሁ፡፡ እነዚያ ሃሳቦችም እኔን ቀርጸውኛል፡፡ እና እኔን የመሰለች ሴት ፈለግሁ፡፡ የለችም፡፡ እንኳን ደብረብርሃንና አዲስ አበባ፣ ሳሲትና መሐልሜዳ፣ ደብረሲናና ሸዋሮቢት የትም የለችም፡፡ እኔን ትምሰል የሚል አባዜ ከምን እንደመጣ አላውቅም! መስላ የተገኘች ጊዜ ደግሞ ኩራቷና የፍላጎታችን ርቀት አስገራሚ ነው፡፡ መሰልክን ሳይሆን ካንተ ሃሳብ የምትርቀውን በማፍቀርና በማግባት መርጋቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡  

6.     - ቆንጆ፣ ፀባየኛ፣ ትሁት፣ ስኬታማ ወዘተ እንኳን ብትሆን አልፈልጋትም፡፡ አሁን ያለሁበትን ሁኔታ ወድጄዋለሁ፡፡ ብቸኝነትን ማጣጣም፡፡ ያው ግን የጉግልን ምክር እያነበብኩ ነው፡፡ የዩቱብም ሃሳቦች አስተሳሳቤን እያነጹት ነው፡፡ እቀየር ይሆን?

7.     - ነጭ ማግባት የበታችነት ይመስለኛል፡፡ ባይሆን ከኢትዮጵያ ውጪ የሆነች ጥቁር ባገባ ደስ ይለኝ ይሆናል፡፡ ሳለአምላክ ዚኖሜኒያ ማለትም ከህብረተሰብህ ውጪ ያለን ሰው የመውደድ አዝማሚያ አለህ ያለኝ ከአስር ዓመት በላይ አይቶ የተናገረው ስለሆነ ትክክል ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ሳይሆን፤ ሩቅ አሳቢ የትም ማደሪያ የማያገኝ እንዳልሆን፡፡

8.     - ‹‹አንተ nerd፣ አንባቢ፣ ዝጋታም! ቤትህ እንኳን ሴት መጥታ አታውቅም፡፡ ወሬ አትችልም፡፡ ካንተ ጋር ሁለተኛ አልገናኝም፡፡ ስለ መጽሐፍ ባይሆን እየተገናኘን እናወራለን፡፡›› ብላ ልትሰናበተኝ ለምትሰናዳ ልጅ ‹‹ኧረ ተይ! ወሬ እንኳን መች አስወራሻለሁ? እያቋረጥኩሽ አወራ የለም እንዴ!›› ስላት ‹‹አይ! ምን ዋጋ አለው? በሳሲት ጀምሮ በቡክ ክለብ ለሚጨርስ ወሬ! ከራስ አበበ ካልቀረህና ስለ መጽሐፍ ማውራት ካላቆምክ ቻው!›› ‹‹ቻው በቃ!›› እኔን የምትመስልና አንባቢ ልጅ ብትሆንም ቤተመጻሕፍቱን የምትጠላ በመሆኗ ሚስት የማይገኝበት መንገድ ተተገበረ፡፡ ‹‹በፌስቡክ ያሉህ ጓደኞች ሳይቀሩ እንዳንተው ስለሆኑ ይህን ሁሉ ደረቅ ነገር ይወዱልሃል፡፡ ሕይወትህ ይህ ብቻ መሆኑ በጣም ያስጠላል!›› 

9.      - ልጅ መውለድ አትወድም አይደል! የዓለም ህዝብ 8 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ አገሪቷም ፍቅር ነስቷታል፡፡ ስለዚህ ተወው አታግባ፡፡

10.  - ኑሮ ተወዷል፣ እንኳን ለሚስትህ ታበላ አንተም በቀን አንዴ መመገብ አለቻልክም፡፡ አርፈህ ተቀመጥ፡፡

11.  - የኢትዮጵያ የዕድሜ ጣራ ላይ ደርሰህ ልትሞት ስለሆነ ተወው፤ ሚስት ትቅርብህ፡፡

12.  - ለትዳር ጥሩ አመለካከት የለህም፡፡ ያገቡት ሲደሰቱ አላየህም፡፡ በቃ አትጨናነቅ፡፡

ይህን ሁሉ አወራሁ፡፡ ብዙ ሙግት ገጠመኝ፡፡ ከምክሮቹ የማስታውሳቸው

1.     የሴት ጓደኛ ትኑርህና በሂደት አዝማሚያውን እየው፡፡

2.     ረጅም ጊዜ ወስዶ የሚሞግት ሰው ያስፈልግሃል፡፡

3.     ይህ አካሄድህ ትክክል አይደለም፡፡ ላስነብብ ምናምን እያልክ የምትለፋው ትውልድ ለመቅረጽ ነው አይደል!

4.     በራስህ ዓለም ውስጥ አትኑር፡፡ ወዘተ፡፡

በእርግጠኝነት ደግመው ሊያገኙኝ እንደሚፈልጉ ነገሩኝ፡፡ የማወራበትን የአማርኛ ቅላጼ፣ ግልጽነት፣ ፍጥነት ወዘተ አይተው ሲስቁ ውለው ሄዱ፡፡

ብዙ ሃሳብ ረስቻለሁ፡፡ የቡድኑ አባላት ካስታወሱኝ እጨማምርበታለሁ፡፡ የኔ ሃሳብ ግን ባጠቃላይ በዓሉ ግርማ ለገጸባህርዩ እንዳለው ‹‹ከአድማስ ባሻገር›› ነው፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...