ዓርብ 25 ኖቬምበር 2022

ተጉለቴዎቹን የልማት አርበኞች በጥያቄ የወጠርኩበት ቀን

 

ተጉለቴዎቹን የልማት አርበኞች በጥያቄ የወጠርኩበት ቀን

 

በዚህ ሳምንት ከሁለቱ አረጋውያን ባለትዳሮች ጋር ተገናኘን፡፡ ልብ ለልብ ተግባብተናል፡፡ እንደ ልጃቸው ያዩኛል፡፡ ታዲያ እኔም ዕድሉን ተጠቅሜ የምጠይቃቸው ጥያቄዎች ስለነበሩኝ ላሻይ ቡና ስናርፍ ብቻ ሳይሆን ስራም እየሰራን እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ያቺን ግማሽ ቀን የልማትና የአገር ጉዳይ ነበር ያነጋገረን፡፡ አንዲትን መጽሐፍ መደርደሪያ ላይ አይተው ስለሷ ብዙ ሃሳቦች ቢኖሯቸውም ከጊዜ እጥረት አንጻር በአንዲት አረፍተነገር ቶሎ ሃሳባቸውን ጣል አድረገው ወደ ሌላ ማለፍ ግድ ይላቸዋል፡፡ እኔም ከነሱ መጻሕፍት ለማንበብ ቅድሚያ ስለምሰጠው፣ አንብቤ ስለወደድኩት፣ ቀልቤን ስለሳበው ወዘተ እናገራለሁ፤ እጠይቃለሁ፡፡ የዕድሜ ልክ ትምህርት፣ ጉዞና ልምዶቻቸው ይናገራሉ፡፡ በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሚነሳ ወሬ ምናልባት የሦስት የአገር ባለውለታዎችን ስም እናነሳ ይሆናል፡፡ ከዚያ ደግሞ የሆነ ህንጻ አይተን ወሬያችን ይቀየራል፡፡ ወይ አንዳችን ሌላ ወሬ እናመጣለን፡፡ ‹‹ንገሪው፤ ንገረው›› ይባባላሉ፡፡ ማስታወሻ አልያዝኩም፡፡ በፊታችን፣ በእጃችን፣ በዓይናችን ድብልቅልቅ ስሜታችንን ገልጸን ወደ ሌላ ወሬ እናልፋለን፡፡

እነርሱ ስለኔ ያሉት ሲጠቃለል፡፡ ታታሪ መሆኔን፣ ሃሳቤን በተግባር ሰርቼ ማሳየቴን፣ የሌላን አካል እገዛ ሳልፈልግ መጣጣሬንና ሁለገብነቴን ወደውልኛል፡፡ በአንድ አገር ግለሰብ ትልቅ ሚና እንዳለው ብዙሃኑ መገንዘብ እንዳለበትና ሁሉን ነገር መንግስት ይስራው ማለት እንደማያስፈልግ ነግረውኛል፡፡ የኔም ሃሳብ ይኸው ነው፡፡

እነርሱ ብዙ ትልልቅ ስራዎች የሠሩ ሲሆን እኔ ስለስራዎቻቸውና ስራዎቻቸውን ስለሚዘውረው ፍልስፍናዎቻቸው ጠይቄያቸዋለሁ፡፡ ጥያቄና መልሱን ቃል በቃል ሳይሆን ዋናው ነጥብ ላይ በማተኮር አቀርባለሁ፡፡

ጥያቄ፡ የስራችሁ ባላራዕይ ማነው?

መልስ፡ እኔ ነኝ (ሴትዮዋ)፡፡ ያነሳሱኝም አባቴ ናቸው፡፡

ጥያቄ፡ ቅድሚያ ትኩረት የምትሰጡት ለቤተክርስቲያን ልማት ወይስ ለሌላ ዓይነት ልማት? ይህን መጠየቄ ሰው ለቤተክርስቲያን አስር ሚሊዮን እየሰጠ ለትምህርት ቤት አስር ብር ስለማይሰጥ ነው፡፡

መልስ፡ እኛ የአካባቢ ልማትም ቢቀድም ችግር የለብንም፡፡ ቤተክርስቲያን ላይ ቅድሚያ የሰጠነው ቤተክርስቲያኑ አባቴ ያሰሩት ስለነበረና ስላረጀ መታደስ ስላለበት ነው፡፡ የዚያን ጊዜ አንድ ነጥብ አምስት ሚዮን ብር የወጣበት ቤተክርስቲያን ነው፡፡ አስበው አሁን ቢሆን፡፡ ከአሁን በፊት ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች መጥተው ህብረተሰቡ ኃይማኖታችንን ያስቀይሩናል ብሎ በመስጋት ስላልተቀበላቸው እኛ ቀድመን ቤተክርስቲያን ላይ ሰርተን አሳየን፡፡ ከዚያ ነው ወደ ሌላው ልማት የገባነው፡፡

ጥያቄ፡ ስራችሁ ለምን በአንድ ወረዳ ተወሰነ (በነገራችን ላይ ይህን ጥያቄ በ2008 ወይም 2009 ዓ.ም. የአምስት ዓመት ዕቅዳቸውን ሲያስተዋውቁ መድረክ ላይ ጠይቄያቸው ወደ ሌላ ወረዳ እንደማያስፋፉ ገልጸውልኝ ነበር፡፡)

መልስ፡ እኛ ዝቅ ብለን በትንሹና ድምጻችንን አጥፍተን ነው የምንሰራው፡፡ በሰሜን ሸዋ ሙሉ መስራት እንችል ነበር፡፡ ብንሰራ ግን ወያኔ መጥቶ ብትንትኑን ስለሚያጠፋው ድምጻችንን አጥፍተን በውሱን ቦታ ሰራን፡፡

(ሃሳቤ - ምናልባት አሁን የማስፋፊያው ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፡፡)

 ጥያቄ፡ ልጆቻችሁ አገር ውስጥ ናቸው ወይስ ዉጪ?

መልስ፡ ዉጪ ናቸው፡፡

ጥያቄ፡ ለምን ከአገራቸው ተነቀሉ?

መልስ፡ ምን መሰለህ፣ አንደኛው ከኛ በላይ ቤተክርስቲያን ሳሚ ነው፡፡ እዚህም በጣም ይመላለሳል፡፡ ቄሶቹንም ከእኛ በላይ ይቀርባቸዋል፡፡

(ይሁን እስኪ ብዬ ተስማምቻለሁ፡፡)

ተጉለት የሚባለው የቱ ነው በሚለው ላይ እየተሳሳቅን አውግተናል፡፡ አንዳንዱ ትክክለኛው ተጉለት ሞጃ ነው፣ ሳሲት ነው ይላል፡፡ እነሱም እንዲህ ብለውኛል ‹‹የዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ አገር፣ የልዑል ራስ እምሩ አገር፣ የወይዘሮ ወላንሳ አገር ትክክለኛው ተጉለት ነው፡፡›› proper ተጉለት ብለውኛል፡፡ ስለዚህ ይህን ጽሑፍ ሳያነቡ የማይቀሩት ዶከተር አበበ ሐረገወይንና እኔ ትክክለኛ ተጉለቴዎች ነን ማለት ነው፡፡ አትከፋፍለን እንዳትሉኝ፤ ጎሼባዶም ተጉለት ነው፡፡ እንግዶቼ ባይሆን ሁለቱን ተጉለት በትዳር አቀላቅለዋል፡፡ ወደ ከተማ ስንወጣ ስለቀድሞው የደብረብርሃን ዝነኛ ሰው ስለ ኃይለመስቀል ወንድማገኘሁ ቤታቸው አጠገብ ስንደርስ፣ ስለ ሐኪም ግዛው፣ በከተማው የመጀመሪያ የሆነውን ‹ሥላሴ ሕንጻ›ን ወዘተ አነሳሳን፡፡ ጨዋታቸው አይጠገብም፡፡ እኔም የምረዳቸውና የማወጋቸው እንደ አሁን ትውልድ ሆኜ ሳይሆን በንባብና በታሪክ ዝንባሌዬ እንደዘመናቸው ሆኜ ነው፡፡ ለምሳሌ የነራስ እምሩን ሳወራ ከአገሬ አዛውንቶችና ከመጻሕፍት ባገኘሁት ታሪክ አስውቤ ነበር፡፡  የቀደመውና የራቀው ትውልድ የቤተሰቦቹን አገር መለስ ብሎ ማየት፣ ከቻለ የልማት ስራ መስራት፣ መነጋገር እንዳለበት ያሳየኝ አጭር ግን የማይረሳ ቆይታ ነበር፡፡

 

 

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...