ቅዳሜ 24 ጁላይ 2021

የፆም ጣዕም

 

ደራሲው በፆም ክብደቱን ለመቀነስና ጤናማ ለመሆን የቻለ በቀን አንድ ጊዜ ተመጋቢ ነው፡፡ የፆምን ሕይወት
በተግባር እየኖረ፣ ሌሎችን እያማከረና ከዓለም ዙሪያ የተጻፉ ምርምሮችን እያነበበ ያዘጋጀውን ይህን መጽሐፍ
ይዞላችሁ ቀርቧል፡፡
 ‹‹በወለድኩ ቁጥር ክብደቴ ይጨምራል እንጂ አይቀንስም፡፡ ራሴን ጠልቼ ነበር፡፡ ገመድ ብዘልም
አልቀነስኩም፡፡ ስሮጥ መንገዱ አይመቸኝም፡፡ መንገድ ላይ በምሮጥበት ጊዜ አላስፈላጊ ነገር የሚናገሩኝም
ሰዎች ያናድዱኛል፡፡ በፆምና በቀላል እንቅስቃሴ የምፈልገው ክብደት ላይ ለመድረስ ችያለሁ፡፡›› ደራሲው
በከፈተው የመማማሪያ መድረክ የተለወጠች ግለሰብ
 አንድ ሰው በዕድሜ ዘመኑ 540 ኩንታል ምግብ ይመገባል፡፡
 አንድ ጤነኛ ሰው ዉኃ ካገኘ ያለምግብ ሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ መቆየት ይችላል፡፡
 በዓለም ዙሪያ 2.8 ሚሊዮን ህዝብ በምግብ በሚመጣ ውፍረት ምክንያት ይሞታል፡፡ በኢትዮጵያ የውፍረት
መጠን ከሃያ በመቶ በላይ ነው፡፡ ከልክ በላይ ውፍረት ደግሞ ከስድስት በመቶ በላይ ነው፡፡ እርስዎ በእጅዎ
ባለው የማያስከፍል ያለመብላት ውሳኔ ጤናማ መሆንና ሕይወትዎን መታደግ ይችላሉ፡፡
 በቀን ሦስቴ መመገብ ከጥቂት መቶ ዓመታት ወዲህ የመጣ ነው፡፡ ባህላዊ እንጂ ሥነሕይወታዊ ምክንያትም
የለውም፡፡
 ቀኑን ሙሉ መብላት ትክክለኛ የአኗኗር ዘይቤ አይደለም! ከቁርስ፣ ምሳ፣ እራት አባዜ እንውጣ! ከምንበላው
እኩል ስለምንበላበት ጊዜ እንወስን፡፡ ከምግብ በኋላ ረጅም ጊዜ ስንቆይ ሰውነታችን ስብን ለማቅለጥ፣
ለመታደስና በሽታን ለመከላከል ዕድል ያገኛል፡፡
 የጤናችንን ሁኔታ በቀላሉ ለማወቅ፣ መመገብ ስላለብን ምግብ ይዘት ለመገንዘብ፣ የፆምን አሰራር
ለመረዳትና ስለምግብ ጥያቄያችን መልስ ለማግኘት የሚረዳን መጽሐፍ!
 ገንዘብዎን ይቆጥቡ፣ ጤናዎን ይጠብቁ፣ ዕድሜዎን ያርዝሙ፣ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት ይከተሉ!


ዓርብ 16 ጁላይ 2021

የባላምባራስ አበራ ሠይፈ ዜና መዋዕል

 ‹‹አገራችን ተጉለት ውልዳችን ደንገዜ፣

ባቱ ያዘናል እምቢ ስንል ጊዜ፡፡ 

ኧረ ሳሲት ሳሲት ትንሿ ከተማ፣

የሚበላው ስንዴ ጉዝጓዙ ቄጠማ፡፡››          

እነዚህንና ሌሎችን ግጥሞች እየሰማሁ ነበር ሳሲት ከተማ ያደኩት፡፡

ከኛ ቤት አጥር ለአጥር የሚገናኝ አንድ ትልቅ ግቢ አለ፡፡ ፖሊስ ጣቢያም፣ እስር ቤትም፣ አስተዳደርም፣ ህብረት ሱቅም ነበር፡፡ ፊት ለፊት ስለሆነ ይታየናል፡፡ 1980ዎቹ አጋማሽ እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ የተከሰቱትን ነገሮች ታዝቤያለሁ፡፡ ሰዎች በዱላ እየተደበደቡ ወደ እስር ቤት ይመጣሉ፡፡ ፖሊስም ሆኑ የአስተዳደር ሰዎች ሰውን በሰላም ‹‹ እጅህን ስጥ›› ወይም ‹‹ለምርመራ ትፈለጋለህ›› ብለው ሳይሆን ‹‹ ቅደም!›› ብለው እየተሳደቡ በጥፊ፣ በሰደፍ ወይም በዱላ እየተማቱ ነው የሚያመጡት፡፡ ይህን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ማለትም እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ የዩኒቨርሰቲ ተማሪም ሆኜ አይቻለሁ፡፡ የምቀርባቸውን የፖሊስ አባላት በቅርቡ ስጠይቅ ወደ ጣቢያ አልሄድም ብሎ ካላስቸገረ መመታት እንደሌለበት ነግረውኛል፡፡ 1980ዎቹ አጋማሽ ሰዎች መሳሪያ አላችሁ፣ ስለ መንግሥት መጥፎ ነገር ተናግራችኋል፣ ተቃዋሚ ናችሁ ወይም የሆነ ጥፋት አጥፍታችኋል ተብለው ይታሰሩ፣ ይገረፉና ባስ ሲልም ያለ ፍርድ ይገደሉ ነበር፡፡ በግርፊያ ወቅት ሲጮሁ፣ ሲናዘዙ ወይም ሰው ጠቁሞባቸው እንጂ ጥፋቱን እንዳላጠፉት ሲናገሩ የምሰማው በልጅ አእምሮዬ ተቀርጿል፡፡ በዚያ ጣቢያ የኢህአዴግ ወታደሮች በቋሚነት ይኖሩ ነበር፡፡

በሳሲት ብዙ አስደማሚ ነገሮች ነበሩ፡፡ የሰው ሞትም ከፍተኛ ነበር፡፡ ከቤታችን ፊት ለፊት ያለው ባለሱቅ ተጌ በጋሻው የተባለው ጎረቤታችን ራሱን በጥይት ሲያጠፋ አንድ ቀን እራት እየተሰራ እሳት ስንሞቅ የጥይቱን ድምጽ ሰምተናል፡፡ የኔ ክርስትና አባት ጋሼ አስራተ ደጀኔም ወደቤተክርስቲያን ሲሄድ ነው ሰዎች በጥይት የገደሉት፡፡ በለውጡ የተገደሉ፣ ራሳቸውን ያጠፉ፣ ቋሚ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው፣ የተሰደዱ፣ ያለወላጅና አሳዳጊ የቀሩ፣ ብዙ ችግር ያዩ አሉ - መከራ ያየውን ሁሉ ቤቱ ይቁጠረው፡፡  

ወታደሮቹ ድንገት አንድ ነገር ከሰሙ ምሽት ላይ ያንን የወታደር ካምፕ ዙሪያውን ከበው በካምፑ ስር ጠመንጃ አጥምደው ያደፍጣሉ፡፡ ለማንኛውም በዚህ የኢህአዴጎች ካምፕ ስር ስላለን ብዙ ነገር አይተናል፡፡ ገጠር ዞረው ብዙ ሰው ይዘው ይመጣሉ፡፡ አንድ ቀን ያመጧቸውን እስረኞች ከበን ስናይ አንዱ ‹‹ለሽንት ፍቀዱልኝ›› ሲሉ አልተፈቀደላቸውም ነበር፡፡ ‹‹አንተ የሽፍታ አብሊ፣ አጠጪ! አርፈህ አትቀመጥም!›› አላቸው፡፡ ያመጧቸው የመሳሪያ ጥቆማ ተሰጥቷቸው ወይም ሽፍታ አደን ሄደው ይሆናል፡፡ ወታደሮቹ አያርፉም ነበር፡፡ በየሰዓቱ ከጣቢያው ከፍ ብሎ በሚገኘውና ከፍተኛ ቦታ ላይ ባለው የስብሰባ አዳራሽ በረንዳ ላይ ሄደው አንቴናቸውን ዘርግተው በጦርሜዳ መገናኛ ያወራሉ፡፡ ሰው ገድለው አስከሬኑን ይዘው መጥተው ለህዝቡ ያሳያሉ፡፡ እኔም የሞተ ሰው አይቻለሁ፡፡ እነሱም ተገድሎባቸው ሲቆጩ አይቻለሁ፡፡ ወታደሮቹ ልጆችን ልብ ስለማይሉና ስለማያባርሩ ሁሉንም ነገር የማየት ዕድል ነበረኝ፡፡ ብዙ ሰዎች በግቢው ውስጥ ባለ ቤት ውስጥ ታስረው ሲውሉና ወደ ዉጪ ሳይወጡ ሲቀሩ ምክንያቱ አይገባኝም ነበር፡፡ አንድ ጥጋት ቁጭ ያለ ሰው አሁን ሳስበው ተገርፎ አድሮ ታሞ ወይ ተጎድቶ ይሆናል፡፡ ለሦስት ለአራት በጉማሬና በዱላ ተፈራርቀውበት ይሆናል፡፡ በጣም ይገረፍ የነበረው አጎቴ ደምሴ ብርሃነ ዛሬ ሲያጫውተኝ ‹‹ያኔ እኮ ቄሶቹን ይዛችሁ፣ መስቀልና ልብሰ ተክህኖ ለብሳችሁ ለምኑልኝ፣ ነገ ሊገድሉኝ ነው ብዬ ለአባትህ ልኬህ ነግረህ ሕይወቴን አትርፈህልኛል፡፡ እንዴት እረሳኸው ይለኛል፡፡›› እኔ ግን አላስታውሰውም፡፡  

ባላምባራስ አበራ ሠይፈ የአባቴ ወዳጅ ስለሆኑ ከልጅነታችን ጀምሮ ወደቤታችን ይመጡ ነበር፡፡ ጠላ ወይም አረቄ  እየጠጡም የዱሮውን ያወራሉ፡፡ እናቴም ግጥሞቹንና ቀልዶቹን እስከ አሁን ድረስ ትነግረኛለች፡፡ በልጅነቴ ወደ ቤታችን ሲመጡ ከነበረው የማስታውሰው ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ 1986 .. ይመስለኛል ሳሲት ከተማ አንድ ነገር አየሁ፡፡  የሁለተኛ ክፍል ተማሪና የሰባት ዓመት ልጅ ነበርኩ፡፡

ባላምባራስ አበራን አንድ ቀን ወታደሮችና ታጣቂዎች እያጣደፉ አመጧቸው፡፡ ፖሊስ ጣቢያው በር ላይ ሲደርሱም የሆነውን በልጅ ዓይኔ አይቻለሁ፡፡ ከደረት ኪሳቸው የጸሎት መጽሐፋቸውን አወጡ፡፡ የኔ አባት እንዲጠራላቸው አደረጉ፡፡ ቀረበ፡፡ የያዙትን ገንዘብም በአደራ ሰጡት፡፡

ሲያመጧቸው ምን እንደተከሰተ፣ ይደብድቧቸው ወይ ምን ይሁኑ አላውቅም፡፡ በማግስቱ ይሁን በሌላ ቀን ከሳሲት ከተማ አናጺ አስገድደው ይዘው ሄደው ሳይሆን አይቀርም ቤታቸውን አፍርሰው ቆርቆሮውንና ጣራው የተዋቀረበትን እንጨት ይዘውት መጡ፡፡ ቤታቸው ከሳሲት 30 ደቂቃ በእግር ከሚያስኬደው ወሮ በሚባለው ቦታ ነበር፡፡ ቤታቸውን አውቀዋለሁ፡፡ ምክንያቱም አባቴ እዚያ መሬት ተከራይቶ ያርስ ስለነበርና ስለምሄድ ነው፡፡ ገንዘብ የሚያወጣ ነገር ሁሉ ከባላምባራስ ቤት መጣ፡፡ በግ፣ በሬ፣ ብቻ ሁሉም መሰለኝ፡፡ እህልም ቢኖር አይቀርም፡፡ ልጆቻቸው ቤተሰቦቻቸው ምን ይሆናሉ የሚለው አይታወቅም፡፡

ባላምባራስ ምን አጥፍተው እንደታሰሩ ለማወቅ ለልጆች አእምሮ ከበድ የሚል ነገር ነበር፡፡ ባላምባራስን ከዚያ በኋላ አይቻቸው ልወቅ አልወቅ እርግጠኛ ባልሆንም ያየኋቸው የማስታውሰው ጊዜ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለሁ ወደ ሳሲት ለክረምትና በዓል እረፍት ከደብረብርሃን ስሄድ ነበር፡፡ የት ቆይተው እንደመጡ አላውቅም፡፡ በዚያን ጊዜ ባየሁት መሰረት ባላምባራስ በየመጠጥ ቤቱ ከሰው ጋር ሲያወጉ የሚታዩ፣ በመንገድ ቀስ ብለው የሚራመዱ ከዘራቸውን ይዘው፣ ምራቃቸውን ከዋጡ ሰዎች ጋር እያወጉ የሚሄዱ ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ 1993-1996 ባሉት ዓመታት ነበር፡፡ ባላምባራስ አበራ ሠይፈ ሽቅርቅር ናቸው፡፡ እንኳን ሳሲት ደብረብርሃንም እንደእርሳቸው ሽቅርቅር አላየሁም፡፡ እንደ ጆኒ ወከር ጅንን ያሉ የሞጃ ባላባት ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሁልጊዜ ጥቁር ሱፍ ኮትና ሱሪ ከነጭ ሸሚዝና ክራባት ጋር ስለሚለብሱ ነው፡፡ ቆብ ይደፋሉ፡፡ ከዘራም አይለያቸውም፡፡

ሳላሳውቃችሁ እንዳላልፍ ሞጃ የወረዳችንና በአቅራቢያችን ያለች የገጠር መንደር መጠሪያ ነው፡፡ ሞጃ የባላባት አገርም ነች፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሞጃ ማለት ሃብታም ማለት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህም የተሰየው በዘውዳዊው መንግሥት ጊዜ የነበሩትን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሞጃዎች በማስታወስ ነው፡፡ ከ1953ቱ መፈንቅለመንግሥት በኋላ ሞጃዎች ከስልጣን እንደተወገዱ ተጽፏል፡፡

ከእርሳቸው ጋር የሚቀራረብ ልብስ የሚለብሱ አሁን ትዝ ያሉኝ ልጃምባው ናቸው፡፡ ልጃምባው ሳሲት የሚመጡና ልጆቻቸውን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ውጪ ልጆች እንዳሏቸው ይነገራል፡፡ እርጅና የተጫጫናቸውና ሲጋራ አሁንም አሁንም የሚያጤሱ ናቸው፡፡ በምርጫ 97 ድህረምርጫ ውዝግብ ወቅት ስለቅንጅት ጀብዱና እንዴት ያሸነፈውን ምርጫ ኢህአዴግ እንደካደው ስናወራ ልጃምባው ‹‹እናንተ እዚህ ስለቅንጅት ስታወሩ ኦነግ እንዳይገባና እንዳታርፉት›› ይሉን ነበር፡፡ ኦነግ ላይ የሚያተኩሩበትን ምክንያት አላጠናሁም፡፡

በነገራችን ላይ በዚያች ትንሽ ከተማ እኛ ቤት በጣም የሚያማምሩ ሁለት ትልልቅ የጽድ ጠረጴዛዎች ነበሩ፡፡ እግራቸውም ሁሉም ጽድ ነው፡፡ ለሁለት ሰው በግድ ነው የሚነሱት፡፡ በፊት በባላምባራስ አበራ በኩል የወሮ ማርያም ቤተክርስቲያን ሲሰራ የተገዙ ናቸው ሲባል ሳልሰማ አልቀረሁም፡፡ አባቴ የሚያወርሰኝ ነገር ምረጥ ካለኝ ከእነሱ አንዱን መርጬ ለጽሑፍ ስራዬ ብጠቀም ደስ ይለኛል፡፡

ባላምባራስ አበራ መንገድ ላይ ሳገኛቸው አንቺ እያሉ እንዳገራችን ወግ ሰላም ይሉኛል፤ ያበረታቱኛል፡፡ ባላምባራስን ደብረብርሃንም አገኝቻቸዋለሁ፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ እኔ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቄ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በረዳት ምሩቅነት ተቀጠርኩ፡፡ ከአንድ ዓመት ተኩል አገልግሎትም በኋላ ወደዚያው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ስነጽሑፍ የድህረምረቃ ትምህርቴን ለመማር ሄድኩ፡፡ ትምህርቱ ደምወዛችንን እያገኘን በከተማዋ ቤት ተከራይተን የምንማርበትና የትምህርት ወጪውን የመጣንበት ዩኒቨርሲቲ የሚሸፍንበት ነበር፡፡ አንድ ቀን ደምወዝ ሊመጣልን አንድ ቀን ሲቀረው ይሁን ወይም ገንዘብ ከባንክ ሳላወጣ ወይም እቤት ረስቼ እርግጠኛ ባልሆንኩበት ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ስለነበረብኝ ሄድኩ፡፡ በጠዋትም ኬኔዲ ቤተመጻሕፍት ትንሽ አንብቤ ወደ መማሪያ ክፍል ስሄድ ሱፍ የለበሱ፣ ቆብ የደፉና ከዘራ የያዙ አንድ ሽማግሌ አየሁ፡፡

ቀርቤ ሳያቸው ባላምባራስ አበራ ናቸው፡፡ እኔ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ የሚገባው ትምህርት በተማረ ብቻ መስሎኝ ነበር፡፡ ተጉለቶች ከባርስቶቻቸው ከነ ወይዘሮ ወላንሳ፣ ከነልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ዘንድ ሲመጡ፣ ቤተመንግሥትም ጃንሆይ ዘንድ እጅ ሲነሱ እነደነበር አላውቅም ነበር፡፡ ይህ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ ስድስት ኮሎ ካምፓስም ገነተልዑል ቤተመንግስት የነበረው ነው፡፡ በአጋጣሚው ተደነቅሁ፡፡ አንድ ደቂቃ ብዘገይ ወይም እርሳቸው ቢዘገዩ አላገኛቸውም ነበር፡፡ በጂኦሜትሪ ኮኢንሲደንስ የሚባል ጽንሰሃሳብ አለ፡፡ ሁለት መስመሮች በትክክል ሲገናኙ ያለውን ለመግለጽ ይጠቀሙበታል፡፡ የኛም ተፈጥሮ ያቀደችው ትክክለኛ ግጥምጥሞሽ መሆን አለበት፡፡

‹‹ባላምባራስ›› አልኳቸው፡፡

‹‹አቤት›› አሉኝ፡፡

‹‹አወቁኝ?›› ስላቸው

 ‹‹ነይ ሳሚኝ፤ አንቺ ወንድሜ ነሽ እንዴ እምትጠፊብኝ!›› አሉና በተጉለቴ ዘዬ ተሳሳምን፡፡

‹‹በደህና መጥተው ነው?›› ብዬ ጠየኳቸው፡፡

‹‹አዎ፣ እዚህ ጥናትና ምርምር ጉዳይ አለኝ›› አሉኝ፡፡ የትምህርት ክፍለጊዜዬ እስኪደርስ አብሬያቸው ሄድኩ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ኃላፊ ቢሮ እርሳቸው እየመሩኝ ገባን፡፡ ድሮ ስንቱን አይተውበት ይሆን በዚህ ግቢ ስልም አሰብኩ፡፡ ባላምባራስ አሁን ከአንድ ዜግነታቸው በላይ ማንም ምንም የማያውቅላቸው መንገደኛ ናቸው ለአዲስ አበቤ፡፡ ገብተንም ጸሐፊዋን አገኘናት፡፡

‹‹እንዴት አደርሽ ልጄ?››

‹‹ደህና፣ እግዚአብሔር ይመስገን፤ አረፍ ይበሉ፡፡››

ተቀምጠው መጠየቅ ጀመሩ፡፡

‹‹አለቃሽ አልገባም? ያንን ደብዳቤ ዛሬም አልጻፈልኝም?››

‹‹አልገባም፡፡ አልጻፈልዎትም አባቴ፡፡ እስኪ ሌላ ቀን ይምጡ፡፡››

‹‹ከመገናኛ ድረስ ነው የመጣሁት፡፡ እንዲያው ተንገላታሁ፡፡ እባክሽ ንገሪልኝ›› ሰሞኑን ደሞ እመጣለሁ፡፡›› አሏት፡፡

ከጸሐፊዋም ተሰነባብተን ወጣን፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲው ዋና በር ድረስ ሸኘኋቸው፡፡ በራሴ ግን ያዘንኩበት ነገር ነበር፡፡ እሱም ምንም ገንዘብ ሳልይዝ ስለወጣሁ ሻይ ቡና ባለመጋበዜና የታክሲ ባለመስጠቴ ነው፡፡ እርሳቸው ሊኖራቸው ቢችልም እንደጡረተኛነታቸው እንደኔ ያለ ልጅ መደገፍ አለበት፡፡  ተበሳጨሁ፡፡

ባላምባራስ ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡት ከሰሜን ሸዋ አርበኞች ዋና ፀሐፊነታቸው ስላስነሷቸው የአርበኝነታቸውንና የሌሎቹን አርበኛ አለመሆን ለማጻፍ ነው፡፡ በሌላ ቀን እንደተሳካላቸው ሰምቻለሁ፡፡ የአርበኞች የባህር መዝገብ በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ይገኛል፡፡

ተመርቄ ወደ ስራ ከተመለስኩ በኋላ አንድ ቀን ደብረብርሃን ከተማ ሳገኛቸው ደስ አለኝ፡፡ ሻይ ቡና ብለን አውግተን ተለያየን፡፡ በሌላ ቀን ግጥምጥሞሹ እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ባለ ቀን አገኘኋቸው፡፡  ሶኒ ቴፕሪከርደር ከአስር ባዶ ካሴት ጋር ቀደም ብየ ለምርምር ስራ ገዝቼ ነበር፡፡ የመመረቂያ ምርምሩን በመጽሐፍ ትንታኔ ላይ ስላደረኩት ቴፑን ሳልጠቀምበት ቆይቼ በዚያን ዕለት ግን ስለተጉለቱ ታዋቂ ሽፍታ ስለአየለ ዝቄ ህይወት እህቱን ልጠይቅ ከተማ ሄጄ ጠይቄያለሁ፡፡ ከዚያም በኋላ ወደ አጂፕ ሰፈር በእግር ስንቀሳቀስ ነበር፡፡ ባላምባራስም ቤታቸው እዚያው አካባቢ ስለነበር ተገናኘን፡፡ በዚያች ቴፕ ሪከርደርም የሚከተለውን ቃለመጠይቅ ሰጡኝ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለታችን በዚያች ቀን የመገናኘታችን ዕድል አንድ አንድ ሚሊዮንኛ ሊሆን ይችል ይመስለኛል፡፡ ቴፕ ሪከርደር ይዤም መገናኘታችን እንደዚያው፡፡ እንኳንም ሆነ፡፡ በዚህ መጽሐፍ ምክንያትም ለህትመት በቃ!

‹‹የሞአ አንበሳ ሕገመንግሥት እንዴህ የራሱ አመራር አለው ሲሉ፤ ሞአ አንበሳ የጃንሆይ ልጆች አልጋ ወራሽ እንግሊዝ አገር የኢትዮጵያ ንጉሠነገሥት መንግሥት ተብለው ንጉሥ ተብለዋል እንዲሁ በሌሉበት አገር፡፡ ያን ደብዳቤ ጽፈው ጎሼ መንደርህወርቅ፣ ባለአምባራስ አበራ ሠይፈ፣ ደበበ ይጎሸሙ የሚባል በራሳቸው ማህተም ሊቀመንበር አድርገው እኔን ንጉሥ ነኝ ብለው ልከዋል፡፡  መንግስት ደግሞ በኛ የሚያምኑትን እንድናሰባስብ ፈቅዷል፡፡ ባንዲራዬን እያውለበለብኩ ሳሲት ገብቼ ጥሩነሽ የመቶ አለቃ ኪዳኔ ሚስት ደጅ ቆሜ ቅዳሜ ገበያተኛው ሲመጣ እልልል.. ይላል፡፡ ‹‹ምንድነው እልልታው አንተ›› ሲሉኝ፤ ‹‹እኔ ምን አውቃለሁ! እኔ የሞአ አንበሳ ሊቀመንበር ነኝ፡፡ እናንተ በቻርተር ስለፈቀዳችሁ በኛ የሚያምነውን እመዘግባለሁ፡፡›› እልልታው ይቀልጣል፡፡

‹‹ወዲያ ወዲህ ብለው አሰሩኝ፡፡ ሞት ተፈረደብኝ፡፡ አልሞትኩም፡፡ 33 ሰው ተገድሏል፡፡ 52 ሰዎች አምልጠናል፡፡ 52 አንዱ እኔ ነኝ እጄን ሰጠሁ፡፡ ተከራከርኩ፡፡ 6000 ብርና 6 ዓመት ተቀጣሁ፡፡ 2 ዓመት ከሰባት ወር በክርክሩ ሂደት ደብረብርሃን ታሰርኩ፡፡ መንግሥት ሁኔታውን ሲመረምር በቻርተር የተፈቀደ ነው ብለው ‹‹ምን አጠፋ ይሄ ሰውዬ! መንግስትን አልበደለ፡፡ ዓላማና ፕሮግራሙን ከህዝብ ነው ያስተዋወቀው›› አሉ፡፡ ባለው መንግሥት አምናለሁ፡፡ ደግሞ ሲመጡ ኢህአዴጎችን ሳሲት ጠልቷቸዋል፤ እህል ውኃ እያበላሁ፡፡ እንጀራ በወጥ ከቤቴ እያሰራሁ፡፡ ሳጣ ገንዘብ እየሰጠሁ 60 ብር 70 ብር እየሰጠሁ፤ እንጀራ ሳሲት ያን ጊዜ እርካሽ ነው፡፡ ኢህአዴጎችን አገር ያስገባኋቸው እኔ ነኝ፡፡ እረድቻቸዋለሁ፡፡ ለዓላማቸው ነው የተዋጉት፡፡ ምን አሏችሁ እያልኩ፡፡ ሁለት ዓመት በሰላም ተቀመጥሁ፡፡

‹‹በሁለተኛው ዓመት ወደኋላዬ በፊጥኝ አስረው ወሰዱኝ፡፡

‹‹ምን አጠፋሁ?››

‹‹ቅደም ብቻ! ሂድ›› አሉኝ፡፡

‹‹ወዴት ልቅደም?››

‹‹ዝም ብለህ ሂድ፡፡››

‹‹ወዴት ልሂድ? ለመግደልም እንደሆነ እሬሳዬን ከዘመድ አታርቁት፡፡ ጉዳያችሁን ንገሩኝ፡፡ አንድ ሰው ይቅደምልኝ፡፡››

‹‹ወደፊት ቅደም!›› አሉኝ፡፡ ሳሲት አወጡና አሰሩኝ፡፡ ጫማዬን አስወለቁና እበር ላይ አስቀመጡና ንቀውኛል የትም አይሄድም ብለው እመንደር ሲገቡ አመለጥሁ፡፡ ከቤቴ ባሻገር ከባለወፍጮው ከሸዋረጋ ሚስቴ ገንዘብ ተበደረችልኝ፡፡ ጣርማበር በእግሬ ስወጣ በመገናኛ ተነጋግረው መስቀሌ ገዳም ተያዝሁ፡፡ አንድ ሰውዬ የጠጄ ጌታ የጮማዬ ጌታ ብሎ ቡና ቤት ጋበዘኝ፤ ሻይ ገዛልኝ፡፡ ነጭ አረቄና ሻዩን ስጠጣ 30 ወታደር ገብቶ ቁጭ አለ፡፡

‹‹ወንድሞቼ እናንተ እኩ እንዲያው እኔን የምትፈልጉ መሰለኝ፡፡ ምንድነው ጉዳዩ›› ስላቸው፡፡

‹‹ቀላል ነው ጉዳዩ፡፡ እርስዎን መንግሥት ይፈልግዎታልና ሰላድንጋይ እንዲሄዱ ይነሱ›› አሉኝ፡፡

‹‹አቅም የለኝ፡፡ በእግሬ አሁን ከሳሲት መጣሁ፡፡ መኪና ይምጣልን፡፡ እዚሁ አስተኙኝ ልደርና በመኪና እወርዳለሁ፡፡ በእግሬማ እሬሳዬ እንደሆነ ነው እንጂ አልሄድም፡፡››

‹‹የዚህን ሁሉ መሳፈሪያ ማን ይከፍላል?›› አሉ፡፡

‹‹አንድ ደካማ ሽማግሌ እኔ አንድ ሰው ቢይዘኝ እበቃለሁ፤ አትወስዱኝም እንዴ?››

‹‹ለእርስዎማ ቢያንስ 30 ወታደር ያስፈልጋል፡፡›› አለኝ፡፡

‹‹መሳፈሪያ እከፍላሁ መኪና ይምጣ፡፡››

‹‹ትንሽ ሽጉጥ አምስት ጥይት የምትጎርስ አለችኝ፡፡ ያችን ሽጉጥ የማደርጋት እዚህ ላይ ነው፡፡ ሽጧ ተያዘች፡፡ ሄድን፡፡ አረጋ የሚባል ሰው ቤት ኩበት ተደርድሯል፡፡ እዚያ ስንተኛ ሌሊት ውዳሴ ማርያም እደግማለሁ፡፡ ፀሎቴን ሳደርስ እንዲያው ሁሉም አፉን ከፍቶ እንቅልፍ ወስዶታል፡፡ አሃ! አልኩና ያችን ሽጉጥ አገኘኋት፡፡ እኩበቱ ውስጥ ደበኳትና ደፈንኩት፡፡ ሲፈልጉ ሽጉጥ የለም፡፡

‹‹የት አደረሰከው?›› አሉኝ፡፡

‹‹እንዴ ወሰዳችሁ! እኔ ምን አውቅላችኳለሁ፡፡››

‹‹ቢፈተሸ ምንም፡፡ ወዲያ ቢባል ወዲህ ምንም፡፡ ተያዝሁ፡፡ መኪና ሲመጣ ሰላድንጋይ ስንወርድ ሁለት ሁለት ብር ነው ከጣርማበር ሰላድንጋይ የሚከፈለው፡፡ እከፍላለሁ ብዬ ነው ያለሁት፡፡ 30 ወታደር ገብቶ ልክክ ብሏል፡፡ ክፈል አሉኝ፡፡ ሁለት ብር ከፈልኩና የራሴን

‹‹እኔ ምን አውቅልሃለሁ! እሰርግ ቤት መሰለህ የመጣሁት? ምን አውቅልሃለሁ! አልኩና እርቦኛል ወንድሞቼ እከፍላለሁ አልኩና 100 ብር አውጥቼ አሳየኋቸው፡፡ ያኔ መቶ ብር ዶባ ነገር ነው፡፡ ብሉ ወንድሞቼ ምሳችሁን ብሉ አልኳቸው፡፡ ማሙዬ ኃይሌ ቤት ገባን ምሳችንን ልክክ አደረግን በላን፡፡ ለምግቡና ለተጠቀምኩት 4 ብሬን ከፈልኩና

‹‹ክፈል›› አሉኝ

‹‹እንዴ! አረ ወግድ! ዘወር በል! መሳፈሪያንም ምግብንም ሰውየው ከፈለ፡፡ አወጣና አስተዳደሩ እሸቱ ታሞ ተኝቷል አማቶቹ ቤት

 ‹‹ባላምባራስ አበራ መጥቷል›› አለው፡፡

‹‹ማን አምጣ አለህ! በተገኘበት ይገደል ተብሎ የለም እንዴ! እዚያው በተገኘበት መግደል ሲገባህ፡፡ ውሰዱና ግደሉ!›› አለ፡፡ ‹‹ሻንጣ ይዣለሁ ብቅአምባ የሚባለው ሰላድንጋይ ሊገድሉኝ ሲወጡ የከተማው ሰው ሴት ነሽ ምንድነሽ ግልብጥ አለና ወጣ፡፡ ታጣቂውም እያቀባበለ ወጣ፡፡ 

‹‹ምን አደረገ ይሄ ሰውዬ? በምቀኛ እንጂ፡፡ ኢህአዴግን የተቀበለ ነው ተብሎ ደርግ ደበኛ አድርጎት ኖረ፡፡ ደሞ እናንተ እንዴት ትገድሉታላችሁ?››

‹‹እንዴት እናድርግ ይኸን ሰውዬ ህዝቡ እንደዚህ የሚደግፈው ነው፡፡ ሳሲትም ተይዞ ተለቋል፡፡ ምንድነው›› አሏ፡፡

‹‹2000 ብር ዋስ ይጥራና ይሂድ፡፡ ዋስ ጥራ›› አለኝ፡፡

‹‹ወንድሞቼ እኔ ዋስ የለኝም፡፡››

‹‹ወለተመድህን እህትህ ነች፤ አትዋስህም?›› አሉኝ፡፡

‹‹እህቴ ነች፡፡ ሰው ሲበደር እንኳን መክፋውን አስቦ ነው፡፡ 2000 ብር ዋስ የምጠራው 2000 ብር ሳይኖረኝ ከየት አምጥቼ ልከፍላት ነው? እህቴንማ ዕዳ አልነክርም፡፡ እሞት እንደሆነ መሞቴ ነው፡፡ እንኳን 2000 ብር 2 ብር ዋስ አልጠራም!››

‹‹ሂድ እንግዲያው፤ እቤትህ ሂድ!›› አሉኝ፡፡

‹‹ወደ ፈረስ መጋለቢያ (በሳሲትና ሰላድንጋይ መካከል ያለ ቦታ) ሊገድሉኝ ነው፡፡ ብር ይዣለሁ፡፡ ገንዘብ አለኝ፡፡ ሆቴል ቤት ተኛሁ፤ ሌሊት ሹፌሩን ተቃጠርኩና የመኪና ሙሉ ዋጋ ከፈልኩና በመኪና ደብረብርሃን! መኪናው አደረሰኝና ተመለሰ፡፡ ሰላድንጋይ ሲፈልጉ ምንም! ከደብረ ብርሃን የሥላሴ ቀን ነው የደረስኩት ሥላሴን አበርኩና በላንድሮቨር ተነሳሁና ሸኖ! ሸኖ ገሰሰ የሚባል የአማቴን እህት ያገባ አለ ገሰሰ ቤት አረፍኩ፡፡ ጳጉሜ 4 ቀን ኢህአዴጎች መጡ፡፡ ወይዘሮ የሺ ገደቤ የሚባሉ ቡና ቤት ምሳዬን ስበላ

‹‹ባላምባራስ አበራ የሚባል አድሃሪ እንዲህ እንዲህ አድርጎ መንግሥትን ለመገልበጥ የሚሰራ ሰውዬ ቅንብቢት ወረዳ ነው ተብሏል፡፡ እሱን ያገኘ ሰው 2000 ብር ይሸለማል›› እያሉ እኛን ትልቁን ሰውዬ ያጫውታሉ፡፡ እኔ እዚያ ቁጭ ብዬ እሰማለሁ፡፡ አዬዬ፡፡ መልኬን አያውቁኝም፡፡ እጄን ታጠብኩና

‹‹ጋሼ ገሰሰ አሳፍረኝ›› ስለው

‹‹ነገ ቅዱስ ዮሐንስ ሆኖ ዓመት በዓል ሳትውል አትሄድም›› አለኝ፡፡

 ‹‹እንዴህ ነውና! ያንተን ሙክት ስበላ እኔ ልበላ!››

‹‹ጳጉሜ 4 ቀን ተነሳሁና አዲስ አበባ! በማግስቱ ተያዘ፡፡

‹‹አበራ የት ሄደ? አንተ ቤት ነበር!››

‹‹እናቴ ሞተው፣ ልጄ ሞቶ ለቅሶ መጥቶ ነበር፡፡ ኢህአዴጎች አላስቀምጥ አሉኝ ብሎ ሞረት ዜና ማርቆስ ሊመለኩስ ወረደ፡፡›› ሞረት መለኩሴውን ሁሉ ሲበጠብጡ አንድ አጭር መለኩሴ አልተገኘም አጡ፡፡

‹‹ከዚህ እንዳመለጥሁ ወይዘሮ ፈሰሰች ወንድምሁን የምትባል የሻለቃ ቦጋለ ሚስት እህቴ ነች፡፡ እሷ ስደርስ መያዜን ሰምታለች

‹‹እንዴት አመለጥህ? እንዴት ለቀቁህ?›› አለችኝ፡፡

‹‹አይ፣ ለቀውኛል፤ ደህና ነኝ›› ስል ደነገጠች፡፡

‹‹እንግዴህ  ሽፍታ አስቀመጠች ብለው ያስሩኛል ብላ ሰግታለች፡፡ ሳይ ደንግጣለች፡፡

 ‹‹እንዴት አስበሃል!›› አለችኝ፡፡

‹‹አይ፣ እኔ ልመለኩስ ደብረሊባበኖስ መውረዴ ነው›› አልኳት፡፡ ጳጉሜ 4 ቀን ነው፡፡

‹‹አይ ታዲያ የቅዱስ ዮሐንስ በግ ይቀራል እንጂ፤ እንካ!›› አለችና 200 ብር ሰጠችኝ፡፡ 200 ብር ያን ጊዜ እንደ 20 000 ብር ነው፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ሄድኩና አልባስ ልገዛ አስቤ የልጄ ክርስትና እናት አለች፡፡ እሷ ሄድኩ፡፡ እሷም ክው አለች ደነገጠችና

‹‹ተይዘዋል ብለው ሰምተን ነበር እንዴት አመለጡ?›› አለች፡፡

‹‹አይ፣ ለቀውኛል ምንም አይደል›› አልኳት፡፡

‹‹አሁን አንዴት ነው ሃሳብዎ?››

 ‹‹አይ፣ ደብረሊባኖድ መሄዴ ነው፡፡›› 

‹‹! ምን ሁነው ነው የሚመነኩሱት? ልጅ ነዎ! ሰይጣን ይፈታተንዎታል፡፡ የምን ምንኩስና ነው? ማናባቱ እንዳይመጣ ነው! እኔ አንድ እጀራ እበላ እንደሆነ እኔ ግማሽ እርስዎ ግማሽ እንበላለን፡፡ ቁጭ በሉ!›› አለችኝ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ባሏም ከተፍ አለ፡፡ ጌታቸው ደሴ ይባላል፡፡

‹‹እንዴ፣ ባላምባራስ ናቸው እንዴ?›› አለና እንባው እንዲያው በቁመቱ፡፡ ‹‹ከየት መጡ? ገድለዋቸዋል ነበር ያልነው፡፡›› አለ፡፡ ‹‹አይ፣ ለቀውኛል፡፡››

‹‹እሳቸው እመለኩሳለሁ ብለው ነገ ደብረሊባኖስ ››

 ‹‹! የምን ምንኩስና? ምን!››

‹‹እመኪና ገባን፤ ያዘና መርካቶ፡፡ ታጣፊ አልጋ፣ፍራሽ፣ ብርድልብስ ገዛና ይኸው መኝታዎ፡፡ እኛ ይኖራሉ፡፡ ማባቱ እኛ ቤት ይመጣል? እረፉና ቁጭ በሉ›› አለኝ፡፡ አምስት ወር ተቀመጥሁ፡፡ በአምስተኛው ወር ‹‹ጌታቸው አንቀባረህ አስቀምጠኸኛል፡፡ ጉልበት አለኝ፤ ሰርቼ ልብላ፤ በማርያም ዘበኝነት አስቀጥረኝ›› አልኩት፡፡

‹‹ራበዎ? ጠማዎ?›› አለኝ፡፡

‹‹አይ አልጠማኝም፡፡ እኔ ሳልሰራ መብላቱ ከበደኝ፡፡ እኔ እንግዴህ ወዴህ እርም ነው አልበላም! አስቀጥረኝ›› ስለው እምቢ አለኝ፡፡ የመኮንን አዝብጤ ወንድም ዶክተር ሞገስ የሚባል አብሮ አደጌ አለ፡፡ እሱ ቤት ሄድኩ፡፡ አማከርኩት፡፡

‹‹እናለብስሃለን ልብስም ለምንድነው?›› አለኝ፡፡

‹‹አይ እኔ እንዲያው ሰርቼ ልብላ!›› አልኩት፡፡

‹‹አንድ ሰውዬ ጨዋ ሰው ፈልግልኝ ዘበኛ ብሎኛል፡፡ አሁን ምሳችንን እንብላና እደውላለሁ›› አለ፡፡ ምሳ በላና ደውሎ ‹‹ጥሩ ጨዋ ሰው አግኝቻለሁ›› ሲለው ወኪሉን ላከ፡፡ ወኪሉ መጣ እሚቀጥር፡፡

‹‹ሰውዬው መኳንንት ነው፤ ሐብታም ነው፡፡ ሰው መጋደል ስለበዛ ሸሽቶ የመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ሃያም ሰላሳም ብር ይበቃዋል፡፡ የአሽከር ወጥ አይበላም፡፡ አንተ ከምትበላው አብላው፤ አጠጣው›› ሲለው ጊዜ አቀረበኝ፡፡ ሴትዮዋ ወይዘሮ አማረች ይባላሉ፡፡ የተባሩት መንግሥታት ነው የሚሰሩት፡፡ እሁድ ቀን ብቻ ነው መናፈሻ የሚውሉት፡፡ ሌላ ቀን ክበብ ነው የሚውሉት ለምግብም አይመጡ፡፡ የቤቱ ኃላፊ ሆንኩ ቁጭ አልኩ፡፡ እህል አንድ ኩንታል ይገዛል፡፡ ያንን ይጋግሩና አሽከሮቹ እሆቴል ይሸጡ ኖሯል፡፡ ይህን ስሰማ ጊዜ

‹‹ለምንድነው? የምንበላው እኛ ነን፡፡ አንድ እንጀራ ዉጪ እንዳይሸጥ!›› አልኩና ከወሩ አሳለፍኩት፡፡ በወሩ የምገዛው እኔ ነኝ፡፡ ብር ሰጡኝ፡፡ ተቀበልኩ፡፡

‹‹አለ፤ አላለቀም!›› አልኳቸው፡፡

‹‹አይ ግዙ›› አሉና ሰጡኝ፡፡ በሁለት ወሩም አላለቀም፡፡ ሁለተኛ ወር ሰጡኝ፡፡ አሁንም አስቀምጬዋለሁ ያን ብር፡፡ አሁንም አላለቀም፡፡ እንጀራ መሸጡ ሲቀር

‹‹የሁለት ወሩም እኮ አለ፤ አላለቀም፤ አስቀምጬዋለሁ ያን ብር›› ስላቸው፤

 ‹‹ከየት እየመጣ? ምን እየበላችሁ?›› አለ ሰውዬው፡፡ አንድ ከአዋሳ የሚስቱ አጎት የሆነ ሰው መጣ፡፡ መኪናዋን እጥብጥብ አደረኩና ጠራረኩና ሲያይ 20 ብር 30 ብር ይሰጠኛል፡፡

 ‹‹አረ እንዴት ነው? እህል ኩንታል ሙሉ እንገዛ ነበር አሁን የሁለት ወር የሦስት ወር ገንዘብ አለ፡፡ እኝህ ዘበኛ ተንኮለኛ ናቸው፡፡ በደንብ ቁጥጥር ይዘው፡፡ እህል ይሸጥ ነበር መሰለኝ›› ሲል፤

 ‹‹እርሳቸው?›› አለ፡፡

‹‹አዎ!›› ‹‹አቶ ፋሲል›› አለኝ፡፡ ስሜን ቀይሬያለሁ፡፡

‹‹አቤት››

‹‹ይምጡ›› አለኝ፡፡

‹‹ዘበኛ ፈልጉ›› አለኝ፡፡

‹‹ምን የሚሆን?››

‹‹ቤቱን የሚጠብቅ››

‹‹ምን አጠፋሁ እኔ?››

‹‹አይ ሌላ ሰው ፈልጉ፡፡ እርስዎ ሽማግሌ ነዎት መጠበቅ አይችሉም፡፡ በእርስዎ ኃላፊነት ሰው ቅጠሩ፡፡ ሌላ ስራ ይፈለጋል፡፡›› አለኝ፡፡

‹‹እንዴ ይኸ ነገር! ደስ አለኝ›› በኔ ኃላፊነት ከሆነ አልቀረሁም ስል አንድ ቄስ እሚንከራተት አገኘሁና 50 ብር ነበር ደሞዜ 100 ብር ነው የሚሰጡኝ ከቅጥሬ በላይ፡፡ 100 ብር እሱን አስቀጠርኩ ድርጅት አለው ምግብ ከነሱ እየሆነ ሹፌር ቀጥሮ በመኪና እየሄድኩ 300 ብር አደረገና ደሞዝ ከፋይ አድርጎ ቀጠረኝ ያን ጊዜ 300 ብር!››

 አጼ ፋሲል ስድስተኛ አያቴ ናቸው፡፡ ባላምባራስ ሣህለማርያም በሻህ፣ እኔ፣ እነራስ እምሩ ስድስተኛ ልጆች ነን*፡፡ ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ እኮ ያንተ አናት ዘነበ ድረሴ ያለበት የሳቸው ርስተጉልት ጠጅ እሚጠጣበት ነበር፡፡ የልጅ ኃይለሥላሴ ቤት ነበር፡፡ ደጃዝማች ኃይለሥላሴ የራስ እምሩ አባት ናቸው፡፡ ራስ እምሩ ሲያረጁ ለአሽከሮቻቸው አንድ ጋሻ መሬት፣ አንድ ፎቅ፣ ንብረታችን አካፈሉ፡፡ አሽከርንም ልጅንም እኩል አካፈሉ፡፡ ሴትዮዋ ለኃይለሥላሴ አቤት አሉ፡፡

‹‹ርስቱንም ጉልቱንም ለሰው አካፈሉት፤ ሰጡት›› ሲሉ

‹‹የሷን ርስተና ጉልት አልነካሁም፡፡ የራሴን ሰጥቻለሁ፡፡ መብቴ ነው፡፡ አገልግለውኛል፡፡ ልጆቼም ልጆቼ ናቸው፡፡ አሽከሮቼንም ከልጆቼ ለይቼ አላያቸውም፡፡ እርስዎም ይስጡ እንደኔ፡፡ የሷን አልነካሁም ምን አገባት›› አሉ፡፡

ጃንሆይ ሲወርዱ ያው እርሳቸው በክብር፡፡ ልጃቸው ሚካኤል እምሩም ጠቅላይ ሚኒስትር እስከመሆን ደርሷል፡፡

‹‹ስምንት መቶ ጦር አለው፤ ለእያንዳንዱ 1000 ብር ይከፍላል ይሉኛል፡፡ እንኳን እኔ አለቃዬ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ይህ ብር አላቸው? አያሌው ጎበዜ ጨዋ ሰው ናቸው፡፡ ግብር እያበሉ ሰባት ቀን ስብሰባ አደረግን፡፡ ሚሊቴሪ ልብስ አለኝ፡፡ እግዚአብሔር ይስጣቸው፤ ጫማዬን አድርጌ የጀግና መለዮ አድርጌ እከበራለሁ፡፡ ስብሰባ ባህርዳር እሄዳለሁ፡፡ የአርበኞች ማህበር አገሬ ተጉለት ላይ አንቀላፊኝ ነው የተመሰረተው፤ ሐውልት እንዲተከል አስፈቅደን ነበር፡፡ አሁን ደሞ መንግሥት ከስራ አገደኝ፡፡ ደሞዜን አግደው በፐርሰንት 210 ብር እየበላሁ እንድቀመጥ ተደረገ፡፡ ደሞዜ 600 ነበር፡፡ አሁን ጓደኞቼ እኔን ያጣሉኝ ሰዎች ሲጣሉ በተከሰሰበት ወንጀል ያልተመሰከረበት ስለሆነ መብቱን እንዳያጣ 600 ብሩን እየበላ ይጠባበቅ የሚል ደብዳቤምስጢር አውጥተው ሰጡኝ፡፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሰስኩ፡፡ ሃብት አላቸው እነሱ፡፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምን አደረገ፤ አከራከረ አከራከረና ይገባዋል አይገባውም ሳይል መብቱ የወረዳ ፍርድ ቤት ነው ክሱን ዘግተነዋል አለና ዘጋብኝ፡፡ አሁን ያንን 600 ደሞዜን አገኛለሁ፡፡ ለምን፣ በጉባኤ ተወስኖልኛል፡፡ ከስራም እንድወጣ የተወሰነው አላግባብ ነው፡፡ የተሰስኩበትን ወንጀል ሁለት ዓመት ተከታትለን ባላምባራስ አበራ ሰውየው አርበኛ የሚያከብራቸው ጉቦ የማይበሉ ጥሩ ጨዋ ናቸው ከሚባል በስተቀር መንግሥትን አልበደሉም ተባለ፡፡››

‹‹እሚያስፈልግ ከሆነ የዋሸሁትንም ሆነ የተናገርኩትን ድምጹን ብሰማው ደስ ይለኛል፡፡ የለፈለፍኩትን፡፡ ሐሰት ከሆነ አግዚአብሔር ይመስክር፡፡›› አሉኝ ብዙ ታሪክ ስለአካባቢያችን ሰዎችና ስለህዝቡ ሁኔታ ከነገሩኝ በኋላ፡፡  መጽሐፍ ቅዱስንም ይጠቅሳሉ፡፡ በቅርቡ ስላረፉ ዘላለማዊ እረፍትን እመኝላቸዋለሁ፡፡

ከሰሞኑ በዚህ መጽሐፍ ለህትመት መቃረብ ሰሞን በደብረብርሃን በከፈትኩት በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት የጥበብ ምሽት የባላምባራስን ታሪክ ሳወጋ አንፔር አንዱዓለም የተባለችው የቤተመጻሕፍታችን አባል ድንገት

‹‹አያቴ ናቸው እኮ!›› አለችኝ፡፡ እስከዛሬ ያልነገረችኝም ፈርታኝ መሆኑን ተረዳሁ፡፡

ከሆነ ጥሩ ብዬ የልጃቸውን የእርሷን አጎት የነቃጥበብን ስልክ ተቀብዬ ደውዬ ስላባቱ ምን እንደሚያስብ ጠየኩት፡፡ነገረኝ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

‹‹1986 ነው የታሰረው፡፡ አንድ ቀን ማታ መጥተው ሊያስሩት ወሰዱት፡፡ እንጀራ እናታችን አትውሰዱብኝ ብላ ስትጮህና እግራቸው ላይ ስትወድቅ በሰደፍ መቷት፡፡ ጠዋት 200 ሲነጋ ለምን አትወስዱትም ልትገሉት ነው እንጂ አለች፡፡ ጠብቄ ጨርቆስ የእናቷ የወንድም ልጅ ስለነበር በሱ ምክንያት ተሯሩጣ አዳነችው፡፡ ወደ አይሰራውም ወንዝ ሊወስዱት ነበር፡፡ ወደ እስር ቤት ወሰዱት፡፡ ደብድበውት ልብሱን እንኳን መልበስ አይችልም ነበር፡፡ ማለዳ 1100 ለቀውት መጣ፡፡ 6 ዓመት ያህል ሸሽቶ ስሙን ቀይሮ አዲስ አበባ ኖሯል፡፡ በተገኘበት እንዲረሸን የሚል አዋጅ ወጥቶበታል፡፡ ዞሎና እምብሴ ላይ ተያዘ፡፡ የተወረሰበት መሬት ሁሉ በጋዜጣ ወጥቶ ነበር፡፡ ቤት ስለቅ ጋዜጣው ጠፍቶብኝ ነው፡፡ ወታደርም ተማርኮበታል ብለው ጽፈዋል፡፡ 230 ቆርቆሮ የፈጀ ቤታችንን አፍርሰው 30 ቆርቆሮ ለእንጀራ እናታችን ትተውላት ወደ ሰላድንጋይ ወሰዱት፡፡ ከብቶቻችን በግ፣ በሬ፣ አህያ ሁሉም ተነድቶብናል፤ ተወስዶብናል፡፡ እኔ የአባትነት ፍቅሩን አላውቀውም፡፡ ያደኩት በሰው እጅ ነው፡፡››

*ባላምራስ የአፄ ፋሲል ስንተኛ ትውልድ መሆናቸው ላይ የቁጥር ስህተት ያለ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ትውልድ 30 ዓመት ቢሆን እንኳን ከጎንደሩ አጼ ፋሲል እስካሁን 400 ዓመት በላይ ስላለና ብዙ ትውልዶች ስላሉ ነው፡፡ በመገዘዝ፣ ቡልጋ፣ ሸዋ 1603 የተወለዱትአፄ ፋሲል በየዘር ሐረግ በባለሙያዎች ተጠንቶ ቢቀርብ ለታሪካችን አንድ ግብዓት ይሆናል፡፡

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...