አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማርኩት አማርኛ ከአንዳንድ ነጥቦች ጋር
እሁድ፣ ነሐሴ 2፣ 2015 ዓ.ም.
መዘምር ግርማ
ደብረብርሃን
አንዲት ሽቅብ የምትገለጥ ሲናር ላይን ደብተር ነበረች የመጀመሪያውን የዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ትምህርት የተማርኩባት፡፡ ‹‹የጽህፈት ክሂል አንድ›› የተባለው ትምህርት የተሰጠን በመምህር ግርማ ነበር፡፡ መጀመሪያ የገባን ቀን በመረጥነው ርዕስ ላይ አንቀፅ እንድንጽፍ የክፍል ስራ ተሰጠን፡፡ እኔ የጻፍኩት ከደብረብርሃን አንጻር የአዲስ አበባን ህዝብ የአለባበስ ዘይቤ በማነፃፀር ሲሆን፤ በተለይም ሴቶቹ ላይ አተኩሬያለሁ፡፡ ለጽሑፌ ውበት ግነት ጨማምሬና አንድ የገጠር ሰው ቢያይ በሚሰጠው አስተያየት መልክ አድርጌዋለሁ፡፡ ሙግት ወይም ገለጻ ከሚያደርግ አንቀፅም የምትሻገርና ወደ ትረካ የምታደላ ስለሆነች መምህር ግርማ በቀጣዩ ቀን ጽሑፎቻችን አርሞ ሲመጣ ለክፍሉ ተማሪ በሙሉ አነበባት፡፡ በተጉለት የአማርኛ ዘዬ ስለተንቆጠቆጠች ተማሪውም ዘና ብሎባታል፡፡ ባለፉት ዓመታት የጻፉ ተማሪዎችን ጽሑፍ ሲያስነብበን እንዳደረገው ሁሉ የኔንም የማን እንደሆነች አልተናገረም፡፡ በአንደኛ ደረጃ የትምህርት ጊዜዬ ግጥም እገጣጥም ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃም በአማርኛ ክፍለጊዜምንባብ ሳነብ በጥሩ ሁኔታ መተረኬን ጓደኞቼ ነግረውኛል፡፡ ለአስረኛ ክፍል ፈተና ዝግጅት የዳኛቸው ወርቁን ፈሊጣዊ አነጋገሮች መጽሐፍ ከኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ቤተመጻሕፍት መምህር ተራመድ ተውሶልኝ አንብቤያለሁ፡፡ የአስራ አንድ ወይም አስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜም ፍቅር እስከ መቃብርን አንብቤያለሁ፡፡ በጣም ዉሱን ተግባራት ቢሆኑም ከአማካዩ ተማሪ አንጻር ለአማርኛ ዝንባሌ አለኝ ለማለት ነው እነዚህን መጠቃቀሴ፡፡ ከቃላት ዓይነቶችና ተፈጥሮ እስከ አገልግሎታቸው፣ ከተሳሳተ የቃላት አጠቃቀም እስከ አራዳ ቋንቋና ሙያዊ ቃላት በክፍል ውስጥ የምንማረውን በቤተመጻሕፍት በመምህር ደረጀ ገብሬ መጽሐፍ እናጠናክራለን፡፡ የምንጽፋቸውን አንቀፆች ለክፍሉ ተማሪዎችና ለመምህራችን የማንበብ ዕድል ይሰጠናል፡፡ ስለ ሰካራም ዓይነቶችና ስለ ጀግና የጻፍኳቸው አንቀፆች ትዝ ይሉኛል፡፡ አንድ ቀን የቤት ሥረ ተሰጥቶን ሞጋች ጽሑፍ ጽፌ መምህራችን ርዕሱን ሲያዩት ጥሩ እንዳልሆነ መክረውኛል፡፡ ከዚችም ከዚያችም ፖለቲካ እየቃረምኩ ፓርቲው በተፈጠረ በሳምንታት ውስጥ የቅንጅት ደጋፊ ሆኜ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን የሚተች ጽሑፍ አዘጋጅቼ ነበር፡፡ ይኸውም ተሟጋች አንቀፅ ‹‹የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና በቀቀኖች አንድ ናቸው›› የሚል ርዕስ ነበረው፡፡ ዝርዝር አረፍተነገሮቹ ደግሞ ሁለቱ እንዴት አንድ እንደሆኑ ይሞግታሉ፡፡ መምህራችን ‹‹እናንተስ ተመርቃችሁ እዚያ አይደል የምትገቡት!›› አሉኝ፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ የጽሕፈት ክሂልና ፖለቲካን ማነካካት አልነበረብኝም፡፡ ለነገሩ ትምህርትን ፖለቲካን ለማስረፅ የተጠቀምኩት እኔ ብቻ አልነበርኩም፤ የጋዜጠኝነት መምህራችን የሕወሃትን ፍልስፍና ሊያሰርጽብን ይሞክር ነበር፡፡ ስሙ የማነ ነው፡፡ የአዲስ አበባን የግል ጋዜጦች እያመጣ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምንና የሌሎችን የፖለቲካ ጽሑፎች ከርዕስ አሰያየም እስከ ዝርዝር ጉዳያቸው ሲያበጥር ይውላል፡፡ ‹‹እንዴ መምህር፣ ይህ እኮ እንደዚህ ለማለት አይደለም›› ማለት አይቻልም፡፡ ያውም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ፀባይ! ያውም ለትግሬ መምህር! አጥንትህም አይገኝም!
ወደ ዋናው ጉዳዬ ልመለስ፡፡ የአገረሰብ ርዕሰጉዳዮችን የሚያስተምረውን የፎክሎር ትምህርት መምህር መስፍን ሰጥተውናል፡፡ ዶርሰንንና ማሪያ ሊችን ለትውር እየጠቃቀሱ ስለ አገረሰባዊ አመጋገብ፣ አለባበስ፣ ትውን ጥበባት፣ ቤት አሰራር፣ ሕክምና አስተምረውናል፡፡ ትምህርቱ አሳታፊ እንዲሆንም በየአካባቢዎቻችን ካለው ልማድና ባህል ጋር ላማስተሳሰር በመጠያየቅና በመወያየት እንድንማማር ያደርጋሉ፡፡ ስነቃልን በተመለከተ በዶክተር ፈቃደ አዘዘ በዚሁ ርዕስ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ተጠቅመናል፡፡ ቆይቶ ሰለሞን ተሾመ ዳጎስ ያለ የፎክሎር መጽሐፍ ጻፈ እንጂ ማጣቀሻዎቹ በሙሉ የእንግሊዝኛ ነበሩ፡፡ እንግሊዝኛው ከአማርኞች አንጻር ለእኛ በመንፈቅ አምስት የእንግሊዝኛ ኮርሶች ለምንወስደው የእንግሊዝኛ ተማሪዎች ሳይቀለን አይቀርም፡፡ አማርኞች የሚያሳዝኑኝ ሁሉን ነገር የሚሰሩት ከእንግሊዝኛ መጻሕፍት ተርጉመው ነው፡፡ የሚያቀርቡት በአማርኛ ስለሆነ በጥራት መቅረብ አለበት፡፡ እንደኛ እንደ እንግሊዝኛ ተማሪዎች የተወሰነ መሳሳትን የማይፈቅዱ መምህራን አሏቸው፡፡ አማርኛን በንዑስ የምንማረውንም የተመለከትን እንደሆነ የተወሰኑ በቋንቋው አፍ ያልፈቱ ልጆች አሉ፡፡ ይህም ትግርኛና ኦሮምኛን አይጨምርም፡፡ እነሱ የራሳቸው ቋንቋዎች በንዑስ ስለሚሰጡ በአፍመፍቻዎቻቸው ለመማር ችለዋል፡፡ አማርኛን በንዑስ የሚወስዱት በቋንቋው አፍያልፈቱ ተማሪዎች ታዲያ በትጋት ስለሚያጠኑ ሁልጊዜ ውጤታቸው ከእኛ በላይ ነው፡፡ እኛ አማርኛን በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደ ቀላል የማየት ልማድ ስላለን በዚያው ቀጥለን ቢ እና ሲ መቃም ለምደናል፡፡ በዚህ ዓመት አያት እንደሆነ ደውሎ የነገረኝ የአብአላው አፋር ጓደኛዬ ዋሲያ ረቢሳ ሲማ አማርኛን በንዑስ ተምሯል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለዞኑ በምትቀርበው በመቀሌ ስለተማረ ትግርኛም ይችላል፡፡ አማርኛ የመረጠበትን ምክንያት እሱ ያውቃል፡፡ ለነገሩ ዋሲያ ስሙ እስከአያቱ በአፋርኛ ስለሆነ ‹‹ኢትዮጵያዊ ስም ያለኝ ኩሩ ኢትዮጵያዊ›› እያለ ስለሚናገር የትኛውንም ቋንቋ ቢማር አይደንቅም!
የአማርኛ ሥነጽሑፍ ትምህርት ለዘዋሪና ስራፈት የእንግሊዝኛ ተማሪ አይሆንም፡፡ የአ.አ.ዩ. እንግሊዝኛ ትምህርት ክፍል ተማሪን ያደድባል፡፡ አያሰሩንም፡፡ በአማርኛ ትምህርታችን እናልምጥ ብንል ግን የሥራችንን ያህል እናገኛለን፡፡ ላለመውደቅ ማጥናት ግድ ይላል፡፡ ያለዚያ ቋንቋውን አውቃለሁ ብሎ መታበይ በኤፍ ሰይፍ ያስቀስፋል፡፡ ማለቴ አብዛኞቹ አብረውኝ የተማሩት የአዲስ አበባ ልጆች ፊልም ውስጥ እንዳሉት ፈረንጆች እያወሩ በእንግሊዝኛ ትምህርት ከሲ እንደማይዘሉት ነው፡፡ ‹‹ያውም እንግሊዝኛ! ለዚያውም አዲስ አበባ! በቃ ተጫርክ፡፡ ከአዲስ አበባ ልጅ ጋር እንዴት ይሆንልሃል?›› የተባለልኝ ትንቢት ፉርሽ ሆነ፡፡ በአማርኛውም እንደሆነ ‹‹ያውም አማርኛ፣ ያውም ከአማሮች ጋር!›› ተብለው ሊሆን የሚችሉት የደቡብ ልጆች ልካችንን አሳይተውናል፡፡ የአማርኛ ሥነግጥም ይኖራል ብዬ በንዑስ ለመውሰድ የገባሁበት አማርኛ ሥነግጥም ብጠብቅ ብጠብቅ የለውም፡፡ የተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው የሥነጽሑፍ መሰረታውያን መጽሐፍ ላይ ካነበብኩት በላይ አልተማርኩም፡፡ ጋሽ ዘሪሁን የዝርው ልቦለድ በተለይም የአጭር ልቦለድ ትምህርት ሰጥተውናል፡፡ ትምህርቱ ስለተዋሃዳቸው ከትውር እስከ ትንታኔ ሲያስተምሩ በቃላቸው ነበር፡፡ የአርአያን ውሱን ክፍሎች ክፍል ውስጥ አንብበውልናል፡፡ ስዕሎቹንም አይተናል፡፡ እርሳቸው ካሰናዱት የአጭር ትረካዎች ስብስብ ‹ልብወለድ አዋጅና ሌሎችም … › የአፈወርቅ ገብረኢየሱስን የወልደዞፍና የወለተዞፍን ታሪክ አንብበውልናል፡፡ ያንን ትረካ ወደ ግጥም ቀይሬው መጀመሪያ ለዶርሜ ልጆች፣ ቀጥሎ ለክፍሌ ልጆች በመጨረሻም ባህል ማዕከል በአንድ ምሽት አንብቤዋለሁ፡፡ የታደሰ ሊበንን ጅብ ነች፣ ዉሻውና መንገዶቹ … የተመስገን ገብሬን የጉለሌው ሰካራም አንብበናል፡፡ ትንተኔዎችንም አንብበናል፡፡ በዚህ ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ደማሙ መምህራችን ስለሚያዝናኑን እንወዳቸው ነበር፡፡ ሌላኛው የሥነጽሑፍ ትምህርት የመምህርት ሰላማዊት ሲሆን ‹የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ቅኝት› ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፈውን ሁሉ የሥነጽሑፍ ስራ ከነደራሲውና እስካገኘው የሂስ ምላሽ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ የአማርኛ አነሳስ ላይ የተሰጡ መላምቶች፣ በ14ኛው ክፍለዘመን ለአፄ አምደ ጽዮን የተጻፉ መወድስ ግጥሞች፣ በ16ኛው ክፍለዘመን መሰለኝ የተጻፉ የአባ ጎርጎርዮስ ደብዳቤዎች፣ የኦርቶዶክስና የካቶሊክ የአማርኛ በራሪ ጽሑፎች፣ በውጪ አገር ሰዎች የተጻፉ ክታቦች፣ የማተሚያ ማሽን ሲመጣ የታተሙ ጽሑፎች፣ ጦቢያ፣ አግአዚ …. እያለ እኛ ዘመን ላይ ግጥም ይላል፡፡ በአስተማሪያችን የተመረጡትን ዋና ዋና መጻሕፍት ማንበብ ግድ ነው፡፡ ለአስር ማርክ አምስት ልቦለዶችን አንብበን ተንትነናል፡፡ እኔስ በንዑስ ስለሆነ በመንፈቅ አንዲት ትምህርት ነች፤ በዐቢይነት የሚወስዱትን ስቃይ አስቡት፡፡ ለዚህ አስረጂ የሚሆነኝ አንድ ቀን የጂማውን ልጅ ዋሴን ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ኬኔዲ ቤተመጻሕፍት አግኝቼው ወደ ዶርም እንሂድ ስለው ‹‹እስኪ አንቺ ሂጂ፤ እኔ እኮ አማሮ ነኝ፡፡›› ያለኝ ነው፡፡
ሌሎቹ ሁለት የአማርኛ ትምህርቶች የአማርኛ ሰዋስው ናቸው፡፡ ስማቸውን የረሳኋቸው አንድ ቀይና አንድ ጠይም መምህራን ያስተማሩን እነዚህ ትምህርቶች ከባድ ናቸው፡፡ ጠይሙ የኔ ሰው መሰለኝ፡፡ ቀዩ ደግሞ ፕሮፌሰር መሰሉኝ፡፡ የባዬ ይማምንና የጌታሁን አማረን የሰዋስው መጻሕፍት ሳያነብ እንደኔ በደብተሩ ብቻ የተማመነ ሲውን ማንም ላይነፍገው ይችላል፡፡ የእነዚህን ትምህርቶች ሁኔታ ሳስብ በአማርኛ ጥራትና ብስለት ከፍ ያለ ደረጃ የደረሱ የአሜሪካና የጀርመን ድምፅ ጋዜጠኞች፣ በሳል ቀደምት ደራስያን፣ የአገራችን ልሂቃን የሆኑ በርካቶች የቋንቋዎች ጥናት ተቋንም (የቋ.ጥ.ተ.) የቀድሞ ተማሪዎች አስታውሳለሁ፡፡ ጠቃሚዎቹን ሁለቱንም መጻሕፍት ለማንበብ ቀጠሮ ይዣለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ መዓዛ አሸናፊ የቋ.ጥ.ተ. ምሩቅ ነች ማለትን ሰምቻለሁ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ስር አራት የትምህርት ክፍሎች ነበሩ፡፡ የዉጪ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ፣ የሥነልሣን (ማስተማሪያው እንግሊዝኛ የሆነ) እንዲሁም ቲያትር ጥበባት (ማስተማሪያው አማርኛ የሆነ) ነበሩ፡፡ አደረጃጀቱ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በዐቢይና በንዑስ ማስተማራቸው ተማሪው ሁለት ቋንቋዎችን አያይዞ እንዲማርና የተስተካከለ ዕውቀት እንዲኖረው ያግዛል፡፡ የህ አሰራር በዚህ ዘመን መቅረቱ ግን ትክክል አይመስለኝም፡፡ ክፍሎቻችን እንደ አጋጣሚ ሆኖ በየቋንቋዎቹ ማለትም በንዑስ በምንወስዳቸው የተከፋፈሉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በእኛ ክፍል የአማርኛና የትግርኛ (ሰባት ስለሆኑ ለትግርኛ ትምህርት ብቻ ይለዩናል እንጂ ሌላውን አብረውን ይማራሉ) ተማሪዎች ነበርን፡፡ ኦሮምኛ ለብቻው ነው፡፡ ፈረንሳይኛ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ አረብኛ የሚወስዱት በሌሎች ክፍሎች የተመደቡ ይመስለኛል፡፡ ተመርቀን ከወጣን በኋላ በመገናኛ ብዙኃን የሰማሁት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍልን ወደ ሦስት ማለትም አማርኛ፣ ትግርኛና ኦሮምኛ የከፈለው ውሳኔ መምህራን ያልተቀበሉት ሲሆን እስከ ፌደሬሽን ምክር ቤትም የደረሰ ነበር፡፡ የፖለቲካ ውሳኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሲያናጋው ያ የመጀመሪያው ስላልሆነ እንደበፊቶቹ ውሳኔዎች ሁሉ እሱም አለፈ፡፡ የእንቅስቃሴው መሪ የአማርኛና ኦሮምኛ መምህር አብርሃም ዓለሙም ከአገር ተሰደዱ፡፡ ያሳደገን የትምህርት ክፍልም ለሦስት ተከፈለ፡፡ የድህረ ምረቃ ትምህርቴን ልከታተል ስሄድ ደግሞ የቋንቋዎች ጥናት ተቋምንም አፈረሱት፡፡ ለመሆኑ ስንት ምሁራንን ያፈራና የራሱ ጥናታዊ መጽሔት ያለው ተቋም ይፈርሳል?