እሑድ 9 ጁላይ 2023

አማርኛ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ

 

አማርኛ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ  

በመዘምር ግርማ

እሁድ ሐምሌ 2 2015 ..

ደብረብርሃን

 

በዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ትምህርት ክፍል ብቻ የተወሰነው የአማርኛ ትምህርት በአሁኑ ወቅት በተለይ በአራት ዘርፎች ሊመደቡ የሚችሉ የትምህርት ዓይነቶች አሉት፡፡ እነርሱም የጋዜጠኝነትና ተግባቦት፣ የባህልና ሥነጽሑፍ፣ የሥነልሣን እንዲሁም የክህሎት ናቸው፡፡ አንድ የዲግሪ ተማሪ በእነዚህ ምድቦች ያሉትን የትምህርት ዓይነቶች በሙሉ መውሰድ ይገባዋል፡፡  

ጋዜጠኝነትና ተግባቦት ተማሪዎች ስለ ጋዜጠኝነት፣ ተግባቦት ብሎም ሕዝብ ግንኙነት መሰረታዊ ጽንሰሐሳቦች ዕውቀት የሚጨብጡበት፣ በተግባር የሚለማመዱበትና ለወደፊቱ የሥራ ዓለም ራሳቸውን የሚያዘጋጁባቸው ትምህርቶች ምድብ ነው፡፡ ልምድ ባላቸው መምህራን የሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶች በፈተና፣ በጽሑፍ ሥራ እንዲሁም በልዩ ልዩ የልምምድ ተግባራት የተማሪውን ብቁ መሆን ይፈትናሉ፡፡ የግል፣ የጥንድና የቡድን ስራዎችን በመሥራት፣ የቤተመጻሕፍት ተጨማሪ ንባብ በማድረግና ወደ ቤት የሚወሰዱ ስራዎችን በመሥራት ተማሪዎች ራሳቸውን ያበቃሉ፡፡

ተመሳሳይ አካሄድን የሚከተለው የባህልና ሥነጽሑፍ ምድብ ተማሪዎች በአማርኛ የሚተላለፉ የባህል፣ የትውፊት፣ የሥነቃልና ተያያዥ ዕውቀትን የሚመረምሩበት ነው፡፡ የአጭርና ረጅም ልቦለድ፣ የግጥም፣ የተውኔት፣ የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍና የሒስ ትምህርትም የሚሰጠው በዚሁ ክፍል ነው፡፡ ባህልን የሚያጠናውና ምናባዊ ሥነጽሑፍን ጉዳዬ ብሎ የሚይዘው ይህ ክፍል በምናብ እየተጓዙ ለመዝናናትና የደራስያንንና አሳብያንን የምናብ ውጤት በሳይንሳዊ መንገድ ለመተንተን ያስችላል፡፡

ሥነልሣን በበኩሉ የቋንቋውን መዋቅር፣ ሥነድምፅ፣ አውዳዊ አጠቃቀም፣ የተግባቦት አላባውያን፣ ሥነልቦናዊና ማህበራዊ ገጽታ  የመሰሉ ዘርፎችን የያዘ የቋንቋ ሳይንስ ጥናት ነው፡፡ በቃላት፣ በሰዋስውና በልዩ ልዩ አውዶች በሚጠቅሙ የቋንቋው ባህርያት ላይ ያተኮረው ስነልሣን ተማሪዎች የሚጠቀሙበትን ቋንቋ ምንነት ለማወቅ፣ ለመመራመርና በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል መሰረታዊ ዕውቀትና ክህሎት የሚጨብጡበት ነው፡፡

የክህሎት ትምህርት ምድብ ደግሞ አራቱን የቋንቋውን ክህሎቶች ከልምምድ ጋር አጣምረው የሚማሩበት ሲሆን ከጀማሪ እስከ ከፍተኛ የሚሄዱ የትምህርት ዓይነቶች በየዘርፉ ምርምር ባደረጉና የማስተማር ልምድ ባላቸው መምህራን ይሰጣሉ፡፡ ማድመጥ፣ መናገር፣ ማንበብና መጻፍን ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተማሩት ላይ የሚቀጥል ክፍል ይማራሉ፡፡ የክህሎት ትምህርት ለሌሎቹ ለሦስቱ ምድቦች መነሻነ መሠረት ነው፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኛ፣ የሥነጽሑፍ ሰውም ሆነ የሥነልሣን ተመራማሪ ያለ ጥሩ የቋንቋ ክህሎት የትም አይደርስምና፡፡

ከላይ ካየናቸው አራት የትምህርት ምድቦች በዘለለ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚሰጡ የጋራ ትምህርቶችን ይወስዳሉ፡፡ በትምህርት ክፍሉ የሚወስዷቸው የምርምርና ዘገባ አጻጻፍ፣ የትርጉም ትምህርት፣ ግዕዝ አንድና ሁለትና ሌሎችም አገር በቀል ዕውቀትን የሚጨብጡባቸው ናቸው፡፡ ትምህርትዎን በተግባር ለማዳበር ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲን ያየን እንደሆነ የዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል በሥነጽሑፍ ምሽቶቹ፣ በመጽሐፍ ክበቡ በሚደረገው ውይይት፣ በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄደው ዓመታዊ የባህልና ቋንቋ አውደጥናት እገዛ ያደርግልዎታል፤ ዕድሎቹን ያመቻቻል፡፡

የአስራ ስድስት ዓመታት ልምድ ያለው የትምህርት ክፍላችን ምሩቃን በጋዜጠኝነት፣ በህዝብ ግንኙነት ባለሙያነት፣ በአርታኢነት፣ በሃያሲነት፣ በመምህርነት፣ በባህልና ቱሪዝም ባለሙያነት፣ በአጠቃላይ በቋንቋ፣ ባህልና ኪነጥበብ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ባለሙያዎች ለመሆን ችለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት የሆኑት የአማርኛ ምሩቃንና መምህራን ትምህርታቸውን በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ በመቀጠል በየዘርፉ መምህራንና ተመራማሪዎች ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ቋንቋችን የማደግ ዕድሉን ተጠቅሞ ከተሰራበት ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ዕድል የሚሰጠን ሲሆን፤ ከዚህ የበለጠ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን፣ በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች የሚሰጡ የትምህርት ዘርፎች ትምህርት በአማርኛ እንዲሰጥና ለሁለንተናዊ ዕድገት እንዲጠቅም ሊሰራበት ይገባል እንላለን፡፡ በዚህም ስራ ንቁ ተሳታፊዎች ነን፡፡  በአፍሪካ ህብረት የሚያገለግል ቋንቋ ይሁን ሲባል፣ በአሜሪካ የሚያገለግል ቋንቋ ይሁን ሲባል እንዲሁም በቻይናና ሩሲያ ሲያስተምሩት ቋንቋው ያለውን እምቅ አቅም ተጠቅመው የበለጠ ተጽዕኖ ለመፍጠር ነው፡፡ ከዚያስ በላይ ምን ዓይነት ዓላማ ይኖራቸው ይሆን? እኛስ አማርኛን እንጠቀመዋለን፣ በሳይንሳዊ መንገድ እናጠናዋለን ወይስ የዳር ተመልካች ሆነን እንቆማለን?

ይህን ጽሑፍ ልጽፍ የቻልኩት በርካታ ኢትዮጵያውያን ለአማርኛ ቋንቋቸው ልባዊ ፍቅር ቢኖራቸውም ቋንቋቸው ምን ያህል እምቅ አቅም እንዳለው የግንዛቤ እጥረት ሊኖርባቸው እንደሚችል ከልምድ በመመልከቴ እኔም በሚገባኝ ልክ ያንን እንዲገነዘቡ ለማስቻል ነው፡፡ በአስርት ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ቋንቋውን ይናገሩታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ ሊጽፉበት ይችላሉ? ለመሆኑ በቋሚነት የአማርኛ ጽሑፎችን የሚያነቡ በበቂ ቁጥር ይኖራሉ? በየሙያ ዘርፎቹ በበሳል ባለሙያዎች የሚቀርቡ የአማርኛ ዝግጅቶችን በንቃት የሚከታተሉ ምን ያህሉ ይሆኑ? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ እጅግ ከባድ ሲሆን፤ መልሱንም ለማግኘት ራሱን የቻለ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መልሱ ከተገኘ ግን ቋንቋችን ምን ዓይነት መንገድ ላይ እንዳለ ለማወቅ የሚረዳ ይመስለኛል፡፡  

አንዳንዶች አማርኛ መጻፍ ቢችሉም በቋሚነት መደበኛ የሆነ የጽሑፍ ግንኙነት ለማድረግ ዕድሉ ስላልተመቻቸላቸው ወይም ስላልፈጠሩ ከደብዳቤና የግል ማስታወሻ በዘለለ አይጽፉበት ይሆናል፡፡ የአማርኛ የእጅ ጽሑፋቸው ተዳክሞ መጻፍ እየረሱ ያሉ እንዳሉ ሳትታዘቡ አትቀሩም፡፡ ንግግርም የሆነ እንደሆነ ምን ያህል የተስተካከለ፣ የሃሳብ ፍሰቱን የጠበቀና ከባዕድ ቃላት የፀዳ ንግግር ማድረግ እንችላለን የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ አጥርቶ ማሰብና ያንንም በማያሻማ ሁኔታ መግለጽ የሚቻለው ከዉጪ ቋንቋዎች ይልቅ በተለይ በአገሬው ቋንቋ መሆኑ እውን ሆኖ በዚህ ላይ አልተሰራበትም፡፡ ከሥርዓተ ትምህርት፣ ከቋንቋ ፖሊሲ፣  ከፖለቲካ ውሳኔዎች ጋር የተያያዙ አማርኛን የሚመለከቱ ጉዳዮች ቢኖሩም በተለይ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ትምህርት ሲሰጥበት አይተው ለማያውቁና ቋንቋውን ከመናገር እምብዛም ላልዘለሉ መረጃ መስጠትና ለበለጠ ምርምር መገፋፋት አስፈላጊ ነው፡፡

አንድ ቋንቋ በህብረተሰብ ውስጥ ለዕለት ከዕለት ሕይወት በመግባቢያነት ከሚሰጠው ግልጋሎት በዘለለ በትምህርት፣ በአስተዳደር፣ በምርምር፣ በፖለቲካ፣ በመገናኛ ብዙኃን ወዘተ ዓይነተኛ መደበኛ ሚና ይጫወታል፡፡ አማርኛ በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች እየሰጠ ያለው፣ ሲሰጥ የነበረውንና ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት ይህ ነው ወይንም ሊሆን ይገባዋል ብለን በቁጥር ባናስቀምጠውም ግዙፍ አቅም የነበረው፣ ያለውና ሊኖረው የሚችል መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ቋንቋችን በትምህርት ዘርፍ ከሚሰጠው ግልጋሎት አንጻር አንዲቱን ብቻ መርጬ ልጽፍባት ወደድኩ፡፡ ይኸውም አማርኛ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ሲሰጥ ያለውን ሲሆን በተለይ በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርትና ይዘት ላይ አተኩሬ እየተሰጡ ያሉትን የትምህርት ይዘቶች፣ አሰጣጣቸውን፣ የጥናቱን አቅጣጫና ስፋት እንዲሁም የምሩቃኑን አቅም ለማስገንዘብ ሞክሬያለሁ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...