2015 ማርች 29, እሑድ

ከመንዝ ጓሳ እስከ እንግድዋሻ



የጉዞ ማስታወሻ
ከመንዝ ጓሳ እስከ እንግድዋሻ
መዘምር ግርማ እንደተረከው
መንደርደሪያ
ከአንድ ወር በላይ ዝግጅት የተደረገበት እና ከየካቲት 27 እስከ 29፣ 2007 ዓ.ም. በመንዝ ጌራ ምድር፣ በደብረሲና እና በሞጃ እና ወደራ ሊካሄድ የታሰበው ጉዞ በተለመደው የሰዓት መሸራረፍ ምክንያት መነሻው ከጠዋቱ 12፡00 ተብሎ የነበረው 2፡00 ላይ ይጀመራል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሽንጠ - ረጃጅም ‹‹ፈረሶች›› የአባይን ውሃ ቀምሰው ለመምጣት ወንዝ በመውረዳቸው በኪራይ ‹‹በቅሎ›› ይህን የባህል ማዕከል ተቀጥላ ጉዞ ጸሐይ ሞቅ ስትል ‹‹በቅሎዬ ስገሪ አርጊው ነሃ ነሃ፣ ወደ ሰላድንጋይ ወደ ሞፈር ውሃ›› እያልን በተውሶ ግጥም ጀመርንው፡፡
የጉዟችንን መርሃ-ግብር በየመገናኛ አውታሩ፣ ፊት-ገጽን ጨምሮ፣ በትነን፣ ተጓዡን ቀስቅሰን፣ የየወረዳዎቹን አመራሮች አነጋግረን እና አስደግሰን ስናበቃ የአባይ ጉዞ የእኛን ጉዞ ልናደርግ ባሰብንው ቀን ይደረጋል ሲባል የራስ ምታታችን ሆነ፡፡ አንድም ተጓዡ አባይን መርጦ የግቢው ዘፈን ‹‹እንጉርጉሮ ይብቃ›› ሲሆን፣ ሁለትም ‹‹ምን መንዝ ለቅሶ ተከትለን ብንሄድስ እናየው የለም?›› የሚሉት ገሸሽ ሲሉ፣ ሶስትም ‹‹ጉዞው አርብ ስለሆነ አይፈቀድልንም የሚለው ሰራተኛ ሲበረክት››፣  አራትም የባህል ማዕከሉ ሃላፊ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የጥበብ ድግስ ሊሳተፍ ሄዶ ያለ ሃሙስ ሳይመጣ ሲቀር እኔ ይህ ጉዞ እንዲደረግ ለማዕከሉ አባላት በስብሰባችን ያሳመንኩት፣ የየወረዳዎቹን አመራሮች ስፍራቸውድረስ ሄጄ ያነጋገርኩት እና የክተት አዋጅ ያወጅኩት ሰውዬ ሆዬ ‹‹እሸሸግበት ጥግ አጣሁ›› ፡፡
የዕለቱ ለት ያስረፈደን ተጓዦች በቡድን በየምንሄድበት ስፍራ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መማሪያ ክፍሎች ውስጥ ለማደር የምንተኛበትን ፍራሽ መኪና ላይ መጫኑ ነበር፡፡ ፍራሽ ሰጭው ያርፍድ፣ ወይንስ የኛ ችግር ይሁን አልተገለጠልኝም፡፡ ባለፈው ዓመት የአሜሪካ ሰላም ጓድ በዩኒቨርሲቲያችን ከተለያዩ በሶስት ክልል ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለመጡ 64 ሴቶች ልጆች ባዘጋጀው የአንድ ሳምንት መርሃ-ግብር ስሳተፍ አንድን ዝግጅት እንከን-አልባ ማድረግ እንዴት እንደሚቻል ካየሁበት ጋር ያሁኑን ሳነጻጽረው ምድርና ሰማይ ነው፡፡
በሰዓቱ ራሴ ብየው የነበረው ለጥቅስ የሚበቃ ቃሌ ‹‹ሁለት ሰዓት እኮ ማራቶን የሚገባበት ሰዓት ነው›› የሚል ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ሰሜን ሸዋ አንድ ወረዳ ላይ ሁለት ሚሊዮን ችግኞችን ሊተክል ላይ ታች ከሚለው ከአድህኖ የተቀናጀ የገጠር ልማት የመጣው አበበ ግሩም በብስጩ ድምጽ ‹‹የቅንጅት ችግር አለ - የተባለው ሰዓትና የተነሳንበት የሁለት ሰዓት ክፍተት አለው፡፡ እኔ በሰዓቱ ነው የመጣሁት፡፡ ሌላ ነገር ደግሞ፣ ፍራሽ ለመጫን እና ከመናኸሪያ መውጫ ለማምጣት ሲባል መኪናው በተባለው ሰዓት ዝግጁ አልነበረም›› ሲል አማሯል፡፡
በጉዞው ዋዜማ በፊት ገጽ ያማረርኩት ምሬት አሁንም የመስሪያ ቤቴን ክቡራን ሃላፊዎች ምላሽ ይፈልጋል፡፡ ምሬቱን ቃል በቃል እርስዎም አንብበው ይፍረዱ፡፡ ‹‹በዩኒቨርሲቲያችን ወደ አባይ ግድብ ለሚሄዱ ተጓዦች ውሎ አበል ተከፍሎ ለባህል ማዕከል ተጓዦች ግን ያልተከፈለው ለምንድነው? ሁሉም ዩኒቨርሲቲው በሚሰጣቸው ምንዳ የሚተዳደሩ አይደሉምን? የዩኒቨርሲቲው አመራር አምኖባቸው የፈቀዳቸው ጉዞዎች ሆነው ሳለ ለአንዱ እንደ ልጅ ለሌላው እንደ እንጀራ ልጅ ለምን ይደረጋል? አባይ ግድብ የሚሄዱትም ጉብኝት፣ ይሄም ጉብኝት!›› የሚል ነበር፡፡

አርብ የካቲት 27፣ የምንሊክ መስኮት
‹‹የምንሊክ መስኮት በጣም ነው የሚያስፈራው፤ በህልሜ ነው የሚመጣው፡፡ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ ንጹህ አየር ነው ያገኘሁት፡፡ ›› በማለት በአጫጭር አረፍተ ነገሮች ጣርማበር አቅራቢያ ባለው ገደላማ ስፍራ ጫፍ ወጥተን ቆላውን በአጉሊ መነጽር እያየን የተሰማትን ሁኔታ የገለጸችው እኔን አባቷን ተከትላ የሄደችው የሶስተኛ ክፍል ተማሪዋ ልጄ ሳትሆን የስራ ባልደረባዬ ተዋበች አብዱ ነች፡፡ ውብ ሃሳብ በተቆጠቡ ቃላት!
‹‹ስለ መስኮቱ ምንም አልነገራችሁን እኮ›› ያለው ኪሩቤል ሮሬሳ እንደመሃንዲስነቱ እቅጩን ይፈልጋል፡፡ እኛ የቋንቋ አስተማሪዎቹ አስተባባሪዎች ግን ቋንቋ አጥሮን ይሁን ቅንጅት ይችን ጉዳይ ረስተናት ኖሯል፡፡ ስፍራው የስጋ ደዌ በሽተኞች ይጣሉበታል እንዲሁም አርበኞች ይሸሸጉበታል መባሉን ብንነግረው ጥሩ ምስል ይኖረው ነበር ኪሩቤል፡፡
ጃንሆይ አጼ ኃይለ ስላሤ አንድ ወቅት በጣርማበር ወይንም በሌላ ስሟ በጫሬ ሲያልፉ በመስኮት ወጣ ብለው ለነዋሪው ‹‹እኛ እምንለው! እዚህ እምትኖሩት ወዳችሁ ነው ወይንስ ተገዳችሁ? ቆፈኑን እንዴት ቻላችሁት ልጆቼ? ተዉ ሰፈራ እንውሰዳችሁ!›› ቢሏቸው ‹‹አይ ጃንሆይ ይችን የመሰለች ወርቅ አገር የት ያገኙልናል?›› ብለው መልሰውላቸዋል እየተባለ በሚተረትላት ትንሽዬ የሰው-ሰራሽ ዋሻ ዳር ከተማ ትኩስ አንባሻ በሻይ ግሩም ቁርስ በላን፡፡ ያንን ዋሻ ሲቆፍር ሰዉ እንዴት እንደተሰቃየ ማን ያውቃል? የዳኛቸው ወርቁን የእንግሊዝኛ ልብ ወለድ ‹‹ማሚቴን›› አስታወስኩ፡፡ ፍራሽ ጭነው፣ እኛን ተሸክመው ዳገታማውን የኮረኮንች ጎዳና የጀመሩት በቅሎዎቻችን ምስጋና ይግባቸውና የመንዝን የጉዞ ጠፍር እንሰበስብ ገባን፡፡
አርባሃራ መድሃኔዓለም
መዘዞን እና ባሽን አልፈን ይገም ከተማ ስንደርስ አንዱ ከዕቅዳችን ውጭ በስነ- ትምህርቱ መምህር በመኮንን ጌታቸው ምክር ያካተትንው ዘንድሮ ሰዎች አርባሃራ መድሃኔዓለም ሲሉት ወደሰማሁት ገዳም አጭር የእግር መንገድ ጀመርን፡፡ አፋፍ ስንደርስ ሹል ጉልላቱ ብቅ ብሎ ሲታየን በውበቱ ተማርከን ሹሌን አልን፡፡
ከቤተክርስቲያኑ ጉዞ መልስ አንድ ሃይለኛው ወልደሃኔ ሙሉነህ የሚባል የ11 ዓመት ልጅና የይገም ትምህርት ቤት የ5ኛ መ ክፍል ተማሪ ውጤቱን የሚያሳይ መግለጫ ይዞ አይቼው ወዳረፍንበት ሻይ ቤት ጠርቼ ሳይለት አማርኛ 42 ከመቶ እና ሌላውንም በአብዛኛው ከዚያ ያልተሻለ አምጥቶ ሳይ አዘንኩ፡፡ አማካይ ውጤቱ 53.7 ሆኖ ከ48 ተማሪ 31ኛ የወጣውን ይህን ተማሪ መምህርት በስንትወርቅ ታደሰ ‹‹የተማሪው ውጤት ጥሩ ቢሆንም ከዚህ የበለጠ እንዲሻሻል የወላጅ ድጋፍና ክትትል አይለየው›› ሲሉ የውጤት መግለጫው ላይ በጻፉት ማስታወሻ አሞካሽተውታል፡፡ እርሱንና ሌሎች ልጆችን አስቤ የያዝኳቸውን ብዕሮች፣ እርሳሶች፣ ከረሜላዎች፣ ቸኮሌቶችና ሌሎችም ዕቃዎች በመስጠት በአስርት ብሮች በሚሆን ወጭ እነርሱን አስደስቼ እኔም ተደሰትኩ፡፡ መከርኳቸውም፡፡
አንተ ጎዳና 
መንዝ ተኮር አመራሮችና የምርጫ ተወዳዳሪዎች አንዲት የቤት ስራ ልስጣችሁ፡፡ ከጣርማበር ጀምሮ እስከ መሃል ሜዳ ያለው መንገድ ጭራሽ የሚገርም ነው፡፡ ከ1955-58 ባሉት አመታት የመንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ መንገዱን ያሰራው በህይወት የሌለው ዶክተር ኢንጂኔር ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህም ሆነ ራሱን አደራጅቶ አውቶቡስ ገዝቶ መናኸሪያ ሰርቶ እና ጮካ ጮካ መኪና አስተዳዳሪዎች መርጦ ክቤ የተመታው የመንዝና ግሼ ህዝብ ሞተውም ሆነ ቆመው ያዝናሉ፡፡ የጌራ ምድር ወረዳ አስተዳዳሪው  አቶ ሙሉጌታ ‹‹መንዝ አምስት ወይንም ስድስት ወረዳዎችን ይይዛል›› ብለውኝ ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ህዝብ ከብሄራዊው ዳቦ ትንሽ ይገምጥ ዘንድ ለምን አትሯሯጡለትም? እነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ድንቅ ስራ እንኳን ብትሰሩ እንግዳ በየት መጥቶ ያመሰግናችኋል? በመሃል ሜዳ - መርሃቤቴው የአስፋልት መንገድ ጥሩ ጅማሮነት ግን እንስማማለን፡፡  ‹‹መንዝ የተረሳና ልማት የጠማው አካባቢ ነው›› የሚለው የአቶ ሙሉጌታ ቃል በጆሯችሁ ሊያቃጭል ይገባል፡፡ በጄ?
መንዝ ጓሳ
ጓሳ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ደርሰን ገና ሳንጎበኝ ምሳ በልተን ለመመለስ ወደ መሃል ሜዳ ስንጓዝ በስተግራ ባለው ሜዳ የዝንጀሮ መንጋ ፈሶበት አየን፡፡ ረጅም መንገድ እያየናቸው ሄድን፡፡ ያው ግን አብዛኛው የኛ ሰው ግድም የሰጠው አልመሰለኝ - ለእንስሳ ያለው ፍቅር ዝቅ በማለቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ‹‹ምግቡ ጥሩ ነው፤ ርካሽ ነው፤ በዚህ ዋጋ ይህ ምግብ እዚህ ቦታ መገኘቱ አሪፍ ነው›› ያለኝን ጎብኝ ከእንስሶቹ ይልቅ ምግቡ አስደስቶት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ኢንስፔክተር ይሁን ሽፈራው ከአብዛኛው ሰው በተለየ ሁኔታ ‹‹ሰሜን ሸዋ ውስጥ ያለሁም አልመሰለኝ፤ በአረንጓዴ ወቅት ብንመጣ እንዴት ያምራል! የዝንጀሮ መንጋው ያስደስታል፤ የምንሊክ መስኮት ላይ ሆነህ የኅብረተሰቡን አሰፋፈር ስታይ ያስደንቅሃል›› ሲል ያልጠበቀው ነገር እዚህ ስፍራ በመኖሩ አደነቀ፡፡
ማማ፣ ጌራ እና ላሎ የሚባሉ ሶስት ከጎንደር የመጡ ወንድማማቾች ከ400 ዓመታት በፊት ያቋቋሙት ነው በተባለው መንዝ ጓሳ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ከምሳ በኋላ 25 ኪሎሜትሩን መንገድ ከመሃል ሜዳ ተመልሰን ደረስን፡፡ አስጎብኛችን አቶ አበበ ጥሩ ማብራሪያ ካደረገልን በኋላ ጥያቄዎችንም ጠያይቀንና የእንግዶቹን ማረፊያዎች ቃኝተን በእግር የተለያዩ የስፍራውን አካባቢዎች ለማየት እንቅስቃሴ ጀመርን፡፡ ስፋቱ ከ72 እስከ 100 ስኩየር ኪሎሜትር ይሆናል የሚባለውን ስፍራ ለመጎብኘት የሶስት ቀናትና የአራት ሌሊት ቆይታ ያስፈልጋል፡፡ የኛ ጉብኝት ግን መጠነኛ ቅኝት ነው የሚሆነው፡፡ በጽድ ጫካ ውስጥ አልፈን የአስታና የጓሳ ምድሩን በሚገባ ከቃኘን በኋላ ይፋትን የምናይበት ስፍራ ላይ ደረስን፡፡ ከዚያ ደጋማ ስፍራ ቁልቁል ወደ አጣዬ ማማተር ልብን ይሰውራል፡፡ የጦስኙ ሽታ፣ በስፍራው መሆን የሚሰጠው የአዕምሮ ሰላም፣ የንፋሱ ሽውታ እና የመልከዓምድሩ አይነ ግቡነት እዚሁ ዋሉ እደሩ ብሎ አንቆ ይይዛል፡፡ አሜሪካውያኑ ተመራማሪዎች እዚያ መኖሪያ  ሰርተው የሚኖሩት መች በደህና ነው! አንዱ ግን የሚኖርበት ቤት የድንጋይ ካቡ ተንዶበት ሞቷል ሲሉኝ አንጀቴን በላው፤ እናቱ ውሃ ግተው ሳያስታምሙት ማረፉ ያሳዝናል! ለጉብኝታችን ይረዳ ዘንድ የያዝንው የእግር ኳስ ስለነበር እየተጫወትን ትንሽ ጊዜ ካሳለፍን በኋላ ቀይ ቀበሮ ትገኝበታለች ወደተባለው ስፍራ ሄድን፡፡ በዚያም በየቀበሮ ጉድጓዱ ብንዟዟር ቀበሮ የገባችበት ይጠፋል፡፡ አበበ እንደተጨነቀ ያስታውቃል፡፡ ‹‹እዚህ ጋ በዚህ ሰዓት ብዙ ቀን ትታይ ነበር፤ ትናንትም አይቻታለሁ›› በማለት ተቆጨ፡፡ በዚህ ስፍራ የማታ ጸሐይ እየሞቅንና እያወራን ፎቶ ስንነሳ፣ በአጉሊ መነጽርም ቀበሮ ስናፈላልግ ቆየን፡፡ ከአንድ እስከ ሁለት ሰዓት ከሚሆን ቆይታ በኋላ ተሳፍረን ወደ መሃል ሜዳ እየጨፈርን ሄድን፡፡
በተያዘልን በነጻነት ቡና ቤት ራት እየበላን እና መጠጥ እየጠጣን ከወረዳው አመራሮች ጋር ስለ መንዝ ጓሳ ውይይት አደረግን፡፡ በውይይቱ ላይ ከኛ ከጎብኝዎች ወገን የተነሳው የመጀመሪያው ነገር ‹‹የመንዝ ህዝብ ራሱ ስፍራውን ማየት አለበት፤ ሰርግን የመሳሰሉ በዓላትን እዚያ እያከበረ አውቆ ማሳወቅ አለበት፡፡ ከሌላ ፓርክ ለምን ብርቅዬ እንስሳትን አታመጡም?›› የሚል ሲሆን ሃላፊዎቹም አምነውበት ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ተግባብተናል፡፡ ከሌላ ፓርክ እንስሳት አምጡ ለሚለው ሃሳብ ተመራመሩበት የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በጣም አንገብጋቢ የነበረው ጥያቄያቸው ግን ‹‹በጓሳው ምድር ላይ እንደ አረም እየበቀለ ጓሳውን ሊያጠፋው በደረሰው አረም በ‹‹ነጭሎ›› ላይ እንድትመራመሩልን የድረሱልን ጥሪ እናስተላልፋለን!›› የሚል ነው፡፡ ‹‹ጓሳ ልብሴ፣ ጓሳ ጉርሴ›› እያለ በጓሳው ክልል ውስጥ የቤት እንስሳት ለሚያስገቡ ሰዎች እንስሳቶቻቸውን እስከማረድ የሚከብድ ቅጣት እየጣለ ስፍራውን ጠብቆ ላኖረው ኅብረተሰብ የጓሳ አደጋ ላይ መውደቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያሳውጅ ነው፡፡ ‹‹ጓሳ እንዴት ቆየ ተብሎ ቢጠናልን እና የአካባቢ ጥበቃው ወደፊትም በዘመናዊ መንገድ እንዲካሄድ ያግዘን ነበር›› ሲሉ የወረዳው ሃላፊዎች ሌላ ጥያቄን ለዩኒቨርሲቲው ልዑካን አቅርበዋል፡፡ ‹‹የቱሪዝም ትምህርት ክፍል ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ላይ ቢከፈት ለእኛ ያግዘን ነበር›› ብለው መንዞች ባቀረቡት ሃሳብ ግን አልስማማም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ደቡብ፣ ሰሜን፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ኢትዮጵያን ማን ሊጎበኝለት ነው መንዝ የሚሄደው? የትኛው ትምህርት ክፍል ነው በሰሜን ሸዋ ላይ እዚህ ግባ የሚባል የመስክ ጉብኝት ተማሪዎቹን ይዞ የሚወጣው? ቱሪዝምስ ቢከፈት መንዝና ሌሎች የሰሜን ሸዋን ስፍራዎች በአይኑ ሙሉ ያያቸዋል ወይ? ሰሜን ሸዋ መች ለሽርሽር ያመቻል?
ባየው ነገር መደሰቱን ገልጾ ‹‹ሰዉን የሚያስደስት ነገር ይኖር ይሆን? እያልኩ እየፈራሁ ነው የመጣሁት፤ ሰዉ አንሄድም ሲል ግን ሰብረን ነው የመጣንው›› ያለው የባህል ማዕከሉ ሃላፊ ዝናወርቅ አሰፋ የገባቸውን ቃሎች ዩኒቨርሲቲው ቢፈጽም አበጀህ ያስብለዋል፡፡
አስታ እና ጅብራን የሚያካትት የእጽዋት ቅርስ፣ አንኮበር ሶረኔን እና ቅልጥም ሰባሪን ጨምሮ ብርቅዬ አዕዋፍን፣ ቀይ ቀበሮንና ጭላዳ ዝንጀሮን የመሰሉ በሃገራችን ብቻ የሚገኙ እንስሳትን የሚይዘው ጥብቅ ስፍራ የመንገድ ችግር ብቻ አይደለም ያለበት፡፡ የእንግዶች ማረፊያው ምድጃ እና ኩሽና ከማከራየት በዘለለ ምግብ ቢያዘጋጅ እና የአገልግሎቱን አድማስ ቢያሰፋ ጥሩ ይሆናል፡፡ ‹‹አንድ እንግዳ ቢመጣ ለማስተናገድ የተሟላ ነገር የለም›› እንዲል አበበ ግሩም፡፡
ጎንደር ፣ ባሌ፣ አቡነ ዮሴፍ (ወሎ) እና ጓሳ ብቻ ያለችው ቀይ ቀበሮ በሌላው ዓለም እግር እስኪነቃ ቢዞሩ አያገኘኟትም፡፡ በማግስቱ 12፡00 ሰዓት ላይ ወደ ደብረሲና የመልስ ጉዞ ስናደርግ ይህችን ብርቅዬ እንስሳ መንገዳችንን ስታቋርጥ አይተናት ቆመን እና ቀርበን ለማየት በቃን፡፡ ለአበበም ስልክ ደውዬ እንዳየኋት ነግሬ አስደሰትኩት፡፡ 
ስንመለስ አበበ እንዲህ እያለ ያስቀን ገባ -
‹‹ሚስት ከመዘዞ፣ ምን ተይዞ፤
ሚስት ከማማ፣ ከሆነማ፤
ሚስት ከግሼ፣ ይሁን እሺ፡፡››
ቁም ነገርም አለው አቤ፣ ‹‹የመንዝ ኅብረተሰብ ችግር ውስጥ ያለ ስለሆነ የአካባቢ ጥበቃው ከእርከን ስራ በዘለለ ቢሰራበት›› የሚል፡፡
ከደብረሲና መልስ ይህ አስተያየት ተሰጥቷል - ‹‹ከላልይበላው ጉዟችን ይህኛው በልጦብኛል፤ ሁሉ ነገር በቅንጅት ተደርጓል፡፡ በቡድን ተበልቷል፤ ታድሯል፤ ቀድሞ እዲዘጋጅ ተደርጓል›› ተዋበች አብዱ፡፡ ተዋበች ግን የዘነጋሽው ነገር ቢኖር ትምህርት ቤት ውስጥ እንድናድር ወረዳውን አናግረን የነበረው ነገር ሳይፈጸምልን ቀርቶ ነጻነት ቡና ቤት አድረናል፡፡ በእርግጥ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ‹‹የአንድ አልጋ እየከፈላችሁ ፍራሻችሁን መሬት ላይ እያነጠፋችሁ አምስትም ስድስትም እየሆችሁ በነጻ ተኙ›› ብለው ባለቤቱ አቶ ካሳዬ ስለፈቀዱልን በሙሉ ተጓዡም በአንድ ቤት ባይሆን የተወሰንን ሰዎች እየሆንን በትናንሽ ቡድኖች ስናወራ አድረናል፡፡
የመንዝን ጉዳይ ሳንጨርስ በመጨረሻም ደብረ ብርሃን ከተመለስኩ በኋላ ስለ ጓሳ የሰማሁትን ወግ ላውጋችሁ፡፡ በቀደምት ጊዜያት ጓሳ በጣም ሽፍታ የሚበዛበት ስፍራ ስለነበር ተማሪን ጨምሮ ማንም ሰው በታጣቂ አጀብ ነበር የሚያልፍበት፡፡  ባለቤታቸው ሳር እያበላቸው ሳይሆን ወደሌላ ስፍራ ጓሳን አቋርጦ እየሄደ እንደሆነ ለማረጋገጥ ከብቶች አፋቸውን ታስረው የሚሄዱበት የነበረው ይህ ስፍራ አንድ ሰው ከብቶቹን አስገብቶበት ሳር ሲያበላ ከተገኘ ከብቱ ይታረድበታል፤ እርሱም ይገረፋል፡፡ አንደኛው አስገራፊ አቶ ወልዴ ሸረሸር ይባሉ እንደነበር መንዜው አቶ ቀማው አጫውተውኛል፡፡ ወደፊት ከአቶ ወልዴ ልጆች ጋር ብራና ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ትሞክራለች፡፡
ቅዳሜ፣ የካቲት 28፣ ደብረሲና
በጣርማበር ዋሻ እንደደረስን ጠባቂዎቹን አስፈቅደን በዋሻው ውስጥ በእግር መንገዱ የእግር ጉዞ አድርገን ይፋት እና ደብረሲና በግልጽ በሚታዩበት ስፍራ ላይ ስንደርስ ዝናወርቅ ከዳኛቸው ወርቁ ልብወለድ ከአደፍርስ ላይ ስለነዚህ ስፍራዎች የሚያትተውን የመጀመሪያውን ገጽ አነበበልን፡፡ ከዚያም ደብረሲና ከተማ ገብተን የደራሲ ዳኛቸው ወርቁን አደባባይ እና ሐውልት አየን፡፡ የዳኛቸው ወርቁ ሐውልት በአዲስ መልክ ተሰርቶ በማየታችን ባለፈው ዓመት ወደስፍራው በግላችን ደራሲውን ለማሰብ ተጉዘን የነበርንው ጓደኛሞች ተደሰትን፡፡ ከዚህ በኋላ ቁርሳችንን በልተንና ፍራፍሬ ገዝተን ወደ ሰላድንጋይ ከተማ ጉዟችንን ጀመርን፡፡
በሰሜን ሸዋ የታወቀ መስህብ አንኮበርና መንዝ ጌራ ነው፡፡ ከነዚህ ስፍራዎች ሌላ ያልታወቀ ስፍራ ልናይ ነው የሄድንው በቀጣዩ ቀን፡፡ ሰላድንጋይ ከተማ ሳንደርስ ተጓዡ ደብረምጥማቅ ማርያም ላይ ወርዶ በእግር ወደ ጻድቃኔ ማርያም ሄዶ ተሳልሞ ሰላድንጋይ ከተማ ሊገባ ቻለ፡፡ ከዚያም ከአንድ አለት ወደተፈለፈለው ወደ ዳግማዊ ላሊበላ ምስካበ ሃዙናን መድሃኔዓለም ገዳም አቀናን፡፡ 41 የሱባዔ ክፍሎች ያሉትና ሶስት አብያተ ክርስቲናትን በአንድ በር ገብተው የሚያዩበት ገዳም በጥቂት ሰዎች ለመሰራት ሁለት ዓመትም አልፈጀበት፡፡ በዋነኝነት ፍልፍል አብያተክርስቲያኑን የሰሩት፣ ያሰሩት እና አሁንም እያስተዳደሩት ያሉት አባት ናቸው እኛን ያስገበኙን፡፡
ቀጥሎ ሰላድንጋይን ሰላድንጋይ ያስባላትን ግዙፍ ድንጋይ ጎብኝተን እላዩ ላይ ቆመን ፎቶ ተነስተን ወደ አጼ ምንሊክ ቅድም አያት ወደ ልዕልት ዘነበወርቅ ሰገነት አቅንተን ጉብኝታችንን ጀመርን፡፡ ይህን ስፍራ በቅርቡ በስፍራው የተተከለውና እየተገነባ ያለው የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ግዛቱን ተሻምቶታል፡፡ ከሰገነቱም ቤተክርስቲያኑ ጎልቶ ይታያል፡፡ ምን ይሻል ይሆን?
ሳሲት - እንግድዋሻ
ከዚህ በኋላ ጉዞ ከሰላድንጋይ በስተምዕራብ 20 ኪሎሜትር ወደምትርቀው ወደ ሳሲት ከተማ የተደረገ ሲሆን ራት ተበልቶ ሜንሽን ፊዩር ሜንሽን ባሰራው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እረፍት ልናደርግ ስንሄድ ህዝቡ በሆታ ነበር የተቀበለን፡፡ ህዝባችን የተማረ ሰውን እንዴት እንደሚያከብር ልብ በሉ፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር፣ የዘጋቢ ፊልም ትዕይንት፣ የስነ-ጽሁፍ ምሽት እና ምክክር ተደርጎ በሁለት መማሪያ ክፍሎች እያወራን እንድናድር ተደረገ፡፡
በማግስቱ እንግዱ በተባሉ የአገሩ አቅኝ ስም የተሰየመውን አንድ ግዙፍ ታሪካዊ ዋሻ ለማየት ጠዋት 1፡00 ላይ የእግር ጉዟችንን ሳሲት ከተማን ለቀን ወደ ሰሜን አቅጣጫ የጠዋት ጸሐይ እየሞቅን፣ እዚያው ያስጋገርንውን ሁለት ዳቦ በሞሰብ ይዘን ጉዞ ጀመርን፡፡ ጥሩ ጫማ አንዲያደርጉ ለተጓዦች በበተንንው ማሳሰቢያ አስቀድመን ያሳወቅን ቢሆንም በነጠላ ጫማም የመጡ ነበሩ፡፡ አብረውን ካደሩትና ሞቅ ባለ መልኩ ካስተናገዱን የወረዳው የባህል ቡድን አባላትና ሰራተኞች እንዲሁም ከሳሲት ነዋሪዎች ጋር የምናደርገውን ጉዞ እኔ ከፊት ካለው ተጓዥ ጋር ሆኜ ነበር የምጓዘው፡፡ ዋሻው በር ጋ ልንደርስ ስንል ያለችውን አስቸጋሪ መንገድ ትተው በቀናው መንገድ እንዲመጡ እኔና ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች ስንነግራቸው የማይሰሙን ሰዎች ነበሩ፡፡ አደጋ ሊደርስባቸው ብሎ የዳኑ ሁለት ሰዎችም ነበሩ፡፡ ገና እዋሻው ውስጥ ከመግባታችን ከኋላ ከነበረው ቡድን ያሉ ተጓዦች ‹‹እንደዚህ አይነት መንገድ እንደሆነ አልነገርከንም፣ ቁልቁለት አለው አላልክም፣ አሁን ጸሐዩ ሳይበረታ እንመለስ›› ሲሉ አስገረሙኝ፡፡ ገና ዋሻውን ሳያዩት፣ ውስጣውስጡን ሳይጎበኙት፣ እዚያ የተገኘውን በርካታ የአገሬውን ነዋሪ ትተው መሄድ ሳይከብዳቸው፣ ሊመጣ ትንሽ ጊዜ የቀረውን ዳቦና ጠላ ሳይቀምሱት እንዲሁም ዋሻው ውስጥ ለማድረግ ያሰብናቸውን ብዙ መርሃ-ግብሮች ሳይታደሙ እንሂድ ሲሉ ደነቀኝ፡፡ አንድ አካባቢውን የሚያውቅና እየደጋገፈ የሚወስዳቸው ወጣት ሰጥተናቸው ተመለሱ፡፡ የቀረው ግማሹ ሰው ከአገሬው ጋር ግሩም ጊዜ ማለቂያውን ባላየንው ዋሻ ውስጥ አሳለፈ፡፡ በጠዋት እንደምንመጣ እንዳልተነገራቸው የነገሩን የዋሻው አቅራቢያ ስፍራ ነዋሪዎች የእድራቸውን ስብሰባ ከጠዋቱ አራት ሰዓት በዋሻው ውስጥ እንደጠሩ ነገሩን፡፡
ዋሻው ቢያንስ እኛ በዚያን ቀን ያየንው ክፍሉ የአንድ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ የሚያክል ሲሆን ከጣልያን የአምስት አመት ቆይታ ጋር የሚያያዝ ታሪክ አለው፡፡ ካሳዬ ወንዳፈረው የተባለ አርበኛ የእኔን አያት ዘነበ ድረሴን ጨምሮ የሳሲትና አካባቢውን ህዝብ በሙሉ ከነከብቱ እዚህ ዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እየተዋጋ አድኖበታል ማለትን ሰምቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዶክተር ሲቪል መሃንዲስ ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህም የህይወት ታሪካቸውን በሚተርከው መጽሃፋቸው ላይ ሳሲት አቅራቢያ ባለ ትልቅ ዋሻ እርሳቸው የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳሉ በመጋቢት 1931 ዓ.ም. ቤተሰቦቻቸው የነበሩበት ከ300 በላይ ጠመንጃ የያዘ ጦር የነበረው ህዝብ ተጨፍጭፎ ሴቶችና ህጻናት ስላልተገደሉ ተርፌ ለዚህ በቃሁ ይላሉ፡፡ ይህ ዋሻ ለእኔ እንግድዋሻ ይመስለኛል መጽሃፋቸው ላይ ካለው ገለጻ አንጻር ሳስተያየው፡፡ ስለዋሻው ታሪክና የወደፊት ሁኔታ ውይይት ተካሂዶ ሁሉም አካላት የየራሳቸውን የቤት ስራ ወሰዱ፡፡ በተለይ ነዋሪው መንገዱን ለማስተካካል ቁርጠኛ መሆኑን ገለጸ፡፡ የምሁራንን አትኩሮት ስለሚፈልግ የዩኒቨርሲቲያችን የታሪክና ተዛማጅ ጥናቶች ሊቃውንት ሄደው ቢጎበኙት የሚል ሃሳብ ዋሻው ውስጥ የተገኘንው ሰዎች ሰንዝረናል፡፡
በዋሻው መግቢያ ላይ ተቀምጦ የወረዳው የባህል ቡድን አባል የሆነችን ትንሽ ልጅ ያናግር የነበረው መምህር ዘላለም ተሸመ ‹‹ይህች ልጅ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን አንደኛ ነው የምትወጣው፤ አድጋ ሳይንቲስት ሆና በዚህ ዋሻ ላይ መመራመር ትፈልጋለች፤ አስጨብጭብላት›› ብሎኝ ለህዝቡ ነግሬ አስጨበጨብኩላት፡፡  
የወረዳው የባህል ቡድን የጀመረው ዘፈንና ፉካሮ በአባቶች ፉካሮና ሽላሎ ተተክቶ ከአፍታ በኋላም ሁለቱም ይፈራረቁ ገቡ፡፡
‹‹ጣሊያን መንገድ ሰሪ እንግሊዝ መሪ ነው፣
የዚህ ሁሉ ጠቅላይ ኃይለ ስላሤ ነው››
ሲሉ የፎከሩት አባት ከጃንሆይ ወዲህ የነገሱትን ስድስት አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ረስተዋቸው ነው መሰለኝ፡፡ ወይንም ከነዚህ ሁሉ እንደ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሁሉ ጃንሆይን አስበልጠው ሳይሆን አይቀርም፡፡
‹‹እናንተ የዋሻውን ታሪክ ማግዘፍ ስለፈለጋችሁ አንደኛው ሰውዬ እኔ ልጅ ሆኜ የማውቀው አባቴ እዚህ ዋሻ ውስጥ ፍየሎች ሲገቡብኝ ለማስወጣት ስመጣ ይህ ዋሻ እኮ አባቶቻችን ጣሊያንን የተዋጉበት ነው ሲለኝ ነው፤ የማውቀው ይህን ብቻ ነው ሲል ምንም አልሰማችሁትም፡፡  እስኪ ሌላ ሰው ደግሞ ይናገር ብላችሁ እሱን ችላ አላችሁት፤›› አለኝ መምህር ዘላለም ተሾመ ከጉዞው መልስ፡፡  ይህን ትችት በመጠኑም ቢሆን የምቀበለው ሰውየውን አቋርጠናቸው ከሆነና ትህትና ነፍገናቸው ከሆነ ነው፡፡ ታሪኩን የተሻለ የሚያውቁት ሰዎች ስላሉ እነሱ ይናገሩ ለማለት አስቤ ነበር በኔ ቤት፡፡ ‹‹ከመንዝ ይልቅ ለተጉለት ታዳላለህ፤ መሃል ሜዳ ከተማንና ገበያውን ቅዳሜ ጠዋት እንድንጎበኝና እንድንገበይ የታቀደው ሲሰረዝና በጠዋት ወደ ደብረሲና እንሂድ ሲባል እያወቅህ ዝም ብለሃል›› ያለኝን ግን አልቀበለውም፡፡ ምክንያቱም ገበያው ደብረሲና መገብየት ይችላል ብዬ በማሰብና ለቀሩት ስፍራዎች መጎብኛ በቂ ጊዜ ለማግኘት አስቤ ስለሆነ፡፡
‹‹እንግድዋሻን ያላዩት ሰዎች እንዲያዩት ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ እንደምሰብክ ቃል እገባለሁ፡፡ መንገዱ ግን ቶሎ ቢሰራ ጥሩ ነው - አንድ ሰው ቢጎዳ ገጽታ ስለሚያጠፋ›› ይላል አበበ፡፡
በመጨረሻም በሁሉም በጎበኘናቸው ስፍራዎች ስለተደረገልን መስተንግዶ፣ ስለተጓዦች መነሳሳት እንዲሁም ዩኒቨርሲቲያችን ስላደረገልን ትብብር በማመስገን መምህር ዘላለም ተሾመ ስለ አጠቃላይ ጉዞው ስሜቱን በገለጸበት አረፍተ ነገር ሃሳቤን ልቋጭ - ‹‹አርብ ዕለት በጓሳ ምድራዊ ዓለማችንን አየን፤ በማግስቱ ቅዳሜ በምስካበ ኃዙናን መድሃኔዓለም ገዳም የእግዚአብሔር መንበር ገነትን አየን፤ ነገር ግን እሁድ በመጨረሻም የሚያሳቅቀውንና የሚያስፈራውን የሲዖልን መንገድ አየን፡፡›› 














































Funny Dance and Music, Ethiopia

2015 ጃንዋሪ 24, ቅዳሜ

THIS IS A THREE DAY STORY




THIS IS A THREE DAY STORY THAT UNFOLDS IN KEMISE.
Script writer – Mezemir Girma
Primary Learning Objective – The primary learning objective of this episode is to teach children learn and apply some safety rules around the house.
Secondary Objective: The secondary objective is to develop in children an awareness of some of the cultural features of their societies.
Synopsis: Olyad falls down from a big Shola tree while he was trying to take some fruits down. He injured his leg and he was given a massage by a local physiotherapist. His friend, Fuad, tells his classmates that Olyad was sick, and the whole class visited the sick boy. Olyad’s parents, the teacher, and the students raise some safety issues, and they stress the need for the application of the safety rules in children’s lives. The following day, Olyad recovers and walks to school.

[Olyad is asleep in bed.]
Dad: Olyad, haven’t you woken up?
Olyad: Dad I am sick.
Dad: Oh my son! Is last night’s accident still affecting you?
Olyad: Dadi, I cannot move my leg.
[Dad goes to Olyad’s room, looks at Olyad’s left leg and tries to see the swelling, which was big.]
Dad: Oli let me call Etye Zenebech, and I will be back.  My love, please take care of our son until I call her.
[Dad rides his horse to Etye Zenebech’s home to call her.]
Dad: Morning Etye.
Etye Zenebech: Morning.
Dad: Etye Zenebech, you are hard working. I see you working in this garden every time I come here.
Etye Zenebech: I was at the church in the early morning, and I have just started weeding.
What brought you here this morning? Is everything safe?
Dad: Olyad fell from the Shola tree yesterday.
Etye Zenebech: Oh my son, why did he climb that big Shola tree?
Dad: We did not see him. He used the ladder and the ladder fell. He wanted to eat the Shola fruits.
 [Dad took Etye Zenebech on horseback to his home.]
Etye Zenebech: Oli, my lion, the good boy, I never forget the water you fetched me from the stream. Where is he sleeping? [She goes to his room.]
[Mom carries Olyad and takes him to the mattress on the floor.]
Olyad: Oh my leg! Eh! Eh! Eh!
Dad: Oli, you will recover soon! Etye Zenebech will treat you well.
Etye Zenebech: Bring some hot water and butter.
Olyad: Don’t touch my leg please Mama Zenebech. It is painful! Mama Zenebech, please leave me alone, go to your home. I will go to school with my friends.
Fuad: [calling from outside] Olyad, the sun has risen, let us go to school. Hurry up please!
Dad: Fuad, he will not go to school today. He is sick. You will visit him when you come back.
Fuad: Oh my friend! Let me visit him now.
Dad: Fuad he will say he has to go with you. Please go with Shambel and Addis.
Fuad: Ok Olyad’s father. We will visit him in the afternoon.
Dad: Yes, when you go please watch out the dogs at Worke’s house.
Fuad: Ok I will not get closer to where the dog sleeps.
[Etye Zenebech washes Olyad’s leg with hot water and starts to smear it with the butter. Olyad weeps.]
 Dad: Olyad please don’t cry. You will recover soon.
Olyad: Don’t touch that part Mama Zenebech. Uuuuu!!
Mom: Oli, once you finish this, I will make you a good breakfast.
Dad: You will make him a good chechebsa.
[Etye Zenebech wraps the knee with a bandage and finishes the treatment.]
Etye Zenebech: Olyad you will walk safe just tomorrow. Let me go home. I will bring you milk after I milk the cows.
Dad: You will go after you drink coffee Etye Zenebech.
Etye Zenebech: You know I have to look after the cows till the kids come from school. Let me go just now please.
Mom: Okay Etye Zenebech. Please come in the afternoon when the kids come back and replace you look after the cows.
Mother Zenebech: Bye! Olyad!  Nagaatti olii!
Mom: Dad I am making the coffee. Please take Oli to the main room.
[Dad takes Oli to the main room.]
[Mom brings coffee and all the coffee gears.]
Dad: Olyad, drink this cup of tea. I and your mother will drink coffee.
Mom: Oli, didn’t I tell you not to climb that tree? Didn’t I say that you should ask us to bring you fruits down? What if the ladder fell on the girl?
Dad: [to Mom] My love, last time you remember that he spilt the boiling water from the stove on his sister’s leg when he was walking fast.
[Olyad cries.]
Dad: Why are you crying? It is your mistake, isn’t it? Drink the cup of tea now.
[Olyad drinks the cup of tea.]
Mom: Have you forgotten what the nurse told you when she treated your sister?
Olyad: She said, “Keep everything clean including pets and play carefully.”
Mom: She also told you, above all, to respect family orders.
Dad: Don’t sit on things tilted. Do you remember this?
Olyad: She also told me not to put into my mouth a dirty material or anything that is not food.
Dad: You just know everything it is only when it comes to applying these that you fail. How would you forget her advice?
Olyad: Dad, I wanted Shola when you were away. I wanted to give it to my sister because she asked me to give her.
Mom: Whoever says whatever they want to say, will you expose yourself to danger? She is a small kid. Why didn’t you tell her to wait till father comes?
[Dad goes out, climbs up the tree using the ladder and brings as much Shola fruits as possible. As he comes back the main room, he saw twenty five of Olyad’s classmates coming to his home with their teacher.]
Dad: [calling out to Olyad] Olyad your teacher and classmates are here to visit you.
Olyad: [looking to the door] Oh! Where are they?
Dad: Oh have you come? Please go in.
Wasiya: Ok sir! How is Oliyad?
Dad: He is good. Let us go in and you will see him.
Teacher: Good morning Oliyad’s father. Is your dog tied?
Dad: Good morning miss Etsegenet. Yes! It is in its cage. Don’t worry. Come in, please.
Teacher: Is Oliyad doing well? It is Fuad who told me this morning, and I decided to bring the students here during their break time.
Dad: Yeah! He is recovering. Please go in.
[All of them go into the house.]
Teacher: Olyad how are you doing?
Olyad: I am good.
Teacher: Can you show me your sick leg?
Olyad: Yes.
Teacher: Oh it is a minor injury. It will come to normal soon.
Dad: We hope so.
Teacher: I want students who are the members of the Red Cross to remind us something. What did the nurse teach you last time? What are the preventable problems you may face?
Shewa: Don’t play on dirty places.
Beeminet: What about fire?
Teacher: Yes it is the most destructive thing if used improperly.
Kahsay: Teacher, in addition to this, we should void slippery places that result from spilling water on surfaces.
Abdu: Children must use electric materials carefully. Don’t touch switches with wet hand if they are vulnerable.
Sakote: Bathing and swimming should only be with the guidance of with parents or grownups.
Hadas: Children should avoid using chemicals and drugs except with the help of grownups.
Teacher: Can you tell us what you mean by chemicals and drugs?
Hadas: Teacher, chemicals are things like detergents and acid. Drugs are that doctors give us when we are sick. The nurse told us last time that we should not take tablets or any medicine prescribed for other people.
Hundesa: Avoid touching and using sharp materials and keeping away from kitchens.
Zinash: Don’t touch your eyes with dirty hands. I want to add to what Hadas just said. Even if a certain medicine is prescribed to us, we should take the amount we are ordered to take.
Kelkay: Use the dust bin properly. As to drugs, they should be paced where children cannot reach.
Teacher: Cool. Children I really appreciate you for your advice.  It gives a good lesson for children who don’t know anything about safety.
Mom: Children, even if some kids knew, they may not apply what they know. Our son climbed up that huge tree and fell down. This happened not because he didn’t know that he would fall, but because he is careless.
Teacher: Olyad why did you do that?
Olyad: I wanted Shola fruits.
Teacher: Would you, for example, rush to a running cow because you wanted to drink milk?
Olyad: No.
Teacher: The same is true here. You shouldn’t have climbed up that tree.
Olyad: Sorry teacher.
Teacher: Children, you have seen what happened to him, yes? Please be careful when you play, walk or do anything.
[Dad gives them all Shola fruits and they start eating. They drink the milk Etye Zenebech brought.]
Mom: Olyad!
Olyad: Yes Mom!
Mom: Why don’t you sing them the song that I sang for you last time?
Olyad: Which song mom?
Mom: Since they are eating Shola fruits, sing them ‘Yeshola Fire.*’
Olyad: Before that I have some advice to children. They should also take care of their younger siblings.
[They start to sing.]
Olyad: Yeshola fire nesh
Yeshola fire nesh
Yeshola fire nesh
Lafuachilish
Mom: Yeshola fire nesh
Yeshola fire nesh
Yeshola fire nesh
lafuachilish
Olyad: Meseretish girum
Mom: sholaye
Olyad: Keyet new minchish?
Mom and all the other people: Solaye!
Olyad: Gomzhiche metahugn
Mom and all the other people: Sholaye
Olyad: Abet mamarish!  
Mom and all the other people: Solaye!
Olyad: Abet mamarish!  
Mom and all the other people: Solaye!
Olyad: Eyew yanchi wubet
Mom and all the other people: Sholaye
Olyad: Melken akelaw
Mom and all the other people: Sholaye
Olyad: Min ale endanchi
Mom and all the other people: Sholaye
Olyad: Hulum bidelaw
Mom and all the other people: Sholaye
Olyad: Hulum bidelaw
Olyad: Hulum bidelaw
Olyad: Yeshola fire nesh
Yeshola fire nesh
Yeshola fire nesh
Lafuachilish
Mom and all the other people: Yeshola fire nesh
Yeshola fire nesh
Yeshola fire nesh
Lafuachilish
[Mom gives the children a big ambasha in a gebete, and they eat chatting. They leave the room saying good bye and wishing Olyad a swift recovery.]
 ON THE NEXT DAY
[Fuad comes to Olyad’s house and the two go to school singing the song they sang the previous day.]
Etye- a title given to old women as a form of respect
·         ‘Yeshola Fire’ is an Amharic song by the late legendary singer Tamirat Molla.

2015 ጃንዋሪ 22, ሐሙስ

የጉዞ ማስታወሻ - ጉም አስጎምጉም



የጉዞ ማስታወሻ
ጉም አስጎምጉም
በመዘምር ግርማ
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጅኦግራፊና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች ለቱሪዝም ትምህርት ማሟያ የመስክ ጉብኝታቸውን ወደ መንዝ ጓሳ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ቅዳሜ ታህሳስ 25፣ 2007 ዓ.ም. ያደርጉ ስለነበር ባላቸው የሶስት ሰው ትርፍ ቦታ ከትምህርት ክፍሉ ውጭ የመጣን ሶስት መምህራንን አክብረው ይዘውን ስለሄዱ በማመስገን ልጀምር፡፡መኪናው የሐበሻ ቀጠሮ ልማዱን ሳይለቅ ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ላይ እስኪመጣ ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ጅሩ መንገድ እንጠብቀው የነበርንው ሰዓት አክባሪ ሶስቱ መምህራን  የበጋው የደብረ ብርሃን ቁር ሁለመናችንን ሲቆፍረን ነበር ያረፈድንው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተከራያቸው ሁለት ቅጥቅጥ በሚባሉ የህዝብ መኪናዎች ጉዞው ተጀመረ፡፡ መኪናው ሙዚቃ አልነበረውምና የጠዋቱን ብርድ የሚያስረሳ የወጣቶቹ ተማሪዎች የስልክ ላይ ሙዚቃና የመኪና ውስጥ ጭፈራ ተጀመረ፡፡ ተማሪዎቹ በራሳቸውም ያወርዱና ይዘፍኑ ጀመር፡፡
በጉዞዎች ላይ የሚታዩ የጭፈራ አይነቶች እና የአዘፋፈን ስልቶች የራሳቸው የሆነ ውበት ይታይባቸዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በአድህኖ የተቀናጀ የገጠር ልማት ማህበር ግብዣ ወርቅ ጉር ገብርኤል (ጎሼ ባዶ አቅራቢያ) ከአምስት ጓደኞቼ ጋር ለንግስ በምሄድበት ወቅት ምዕመናኑ በዝማሬ ሲቀዛቀዙ አውራጇ የሚያበረታቱበት ግጥም
‹‹ኧረ ሴቱ ፈዟል፣  ኧረ ወንዱ  ፈዟል፣
ዝማሬ ነው እንጂ ሌላ ምን ተይዟል››
የሚለው ግጥም በመንዙ የተማሪዎች እና የኛ ጉዞ
 ‹‹ኧረ ሴቱ ፈዟል፣  ኧረ ወንዱ  ፈዟል፣
ጭፈራ ነው እንጂ ሌላ ምን ተይዟል››
በሚል ተቀይሮ ሰማሁት፡፡

ተማሪዎቹ በጉዟችን ወቅት የዘፈኗቸውን ዘፈኖች አዝማቾች እና የተወሰኑ ግጥሞቻቸውን እስኪ ላካፍላችሁ፡፡
1.      ኧረ እማማ ዘነቡ፣  ኧረ እማማ ዘነቡ
ጓሳን የምናየው በማነው ሰበቡ?
2.     ኧረ ምታው ምታው ምታው ባንገትህ
ቢገጥም ባይገጥም አንተ ምን ቸገረህ
ምንም ባይሳካ ሲኒየር ሆነህ
ስትመረቅ እኮ ቲቸር እኮ ነህ
(በዚህ ጉዳይ ተገርሜ መምህርነትን የሚወድ ትውልድ ተፈጠረ ብዬ በማሰብ ከመኪና ስንወርድ ከተወሰኑ ተማሪዎች ጋር ባደረኩት ውይይት እንዳስተዋልኩት ከሆነ ተማሪዎቹ ዕጣ ፈንታቸውን አውቀውታል፡፡ በኛ ጊዜ የስነትምህርት ተማሪዎች እኛን አፕላይዶችን ቲቺንግን ስያታልሏት ኖን ቲቺንግ አሏት እያሉ ዕጣ ፈንታችንን የተነበዩልን ለነዚህ ተማሪዎች ከአሁኑ እንደተገለጠላቸው ተገነዘብኩ፡፡ እነርሱም አፕላይድ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡)
የታደሉ ሰዎች ጂኦ ይማራሉ
ሁለተኛ ዓመት ላይ ጓሳ ይሄዳሉ
ሲመረቁ ደግሞ ቲቸር ይሆናሉ፡፡
በድህረ ምረቃው መርሃ ግብር አ.አ.ዩ. ዶክተር ታመነ ኪቲላ ፔዳጎጂ ሲያስተምሩን እንዳሉት ከሆነ በአስተማሪነት እቆያለሁ ብሎ የሚያስብ እና ሙያውን የሚወደው ሰው የተሻለ ያስተምራል፡፡  እናት ሃገር ሆይ! ሙያውን የሚወድ መምህር መጣልሽ፡፡ እንደሱ ዓይነቶቹን ያብዛልሽ እልሻለሁ፡፡
3.     ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ
ጂኦ ድል አድርጎ ሲገባ
(ይህን ዘፈን የ1980ውን የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫን እንደበላን ነው የሰማሁት አሉ አንዱ መምህር)
4.     የሚገርመውና በጉዟችን በተደጋጋሚ የሰማሁት አውራጅና ተቀባይ የሚቀባበሉት ምልልስ ያለበት ግጥም
አውራጅ፡ ዴ በላንዴ
ተቀባይ፡ ዴ
አውራጅ፡ መኪናው ሲዲ የለውም እንዴ?
አውራጅ፡ ዴ በላንዴ
ተቀባይ፡ ዴ
አውራጅ፡ ጓሳ አልደረስንም እንዴ?
እዚህ አገር ዛፍ ብቻ ነው ያለ እንዴ?
5.     ያምራል አገሬ ኧረ ያምራል አገሬ ያምራል አገሬ
የትም የትም ዞሬ ባንቺ ነው ማማሬ
6.     ሰለሜ ሰለሜ
7.     የዓይኔ አበባ ነሽ የዓይኔ አበባ
ቱሪዝም አበባ
ያይኔ አበባ
8.     ሃይ ሎጋ ሃይ ሎጋዬ ሆ
ሃይ ሎጋ
ይወለድና እንከፍ እንከፉ
ጋን ይሸከማል
ከነድፍድፉ
ይወለድና ሆዳም ሆዳሙ
ካፌ ይሰቅላል 12፡00 ሰዓት
እስክስታ የሚመታባቸውና ዳንስ የሚቀልጥባቸው ዘፈኖችም ከስልኮች ጉሮሮ ይንቆረቆራሉ በየመሃሉ፡፡ የጉራጌኛ፣ የኦሮምኛ፣ የትግሪኛ እና የሌሎችም ቋንቋዎች ዘፈኖች ሰቀልጡ አረፈዱ፡፡

እንኳን ልከሽብኝ ልብሽን ወደኔ
እንደዋለ ያድራ ሲርገበገብ ዓይኔ
አባይ ጣናን ዞረሽ አምረሽ ተኳኩለሽ
ይ በፈረሱ ጋልበሽ
ያው አዝማሪ ስላልያዝን እና የተቀረጸ ዘፈን በመሆኑ አባይ ጣናን ዞረሽ ያለው ዘፋኝ መሃል ሜዳ ዞረሽ ብሎ ሊገጥምልን አልቻለም ፡፡ ይህን ሁሉ ጥበብ ሳይ ታዲያ የዩኒቨርሲቲያችን የባህል ማዕከል የልጆቹን የጥበብ ዛር ማባበል እንዳለበት ታየኝ፡፡
በ2002 ዓ.ም  የታተመ የአዲስ አድማስ ጋዜጣን እያነበብኩ ነበር እየተጓዝኩ የነበረው፡፡ አንዱ ገጽ ስለ እድሜ ልክ ድንግልና የሚያወራ ነበር፡፡ የጽሁፉ መነሻ አንዲት ወጣት ‹‹ጓደኛዬ ወሲብ ስናደርግ ስላልደማሁ ድንግል አልመሰልኩትም›› ብላ ለጋዜጣው የጻፈችው ደብዳቤ ነበር፡፡ ስለድንግልና አይነቶች እና ስለዕድሜልክ ድንግልና ማለትም ወሲብ እየፈጸሙም ሆነ ልጅ እየወለዱ ስለማይጠፋው አይነት የሚያትተውን ገጽ አንብቤ ቀድጄ ወደ መኪናው የዕቃ ማስቀመጫ ቆጥ ወረወርኩትና ቀሪውን ንባቤን ቀጠልኩ፡፡ በነገራችን ላይ ጋዜጣ ሳነብ ያነበብኩትን ገጽ እየቀደዱ መጣል ያስደስተኛል፡፡ ይህ ወረቀት ከቆጡ ወርዶ አንደኛዋ ተማሪ ላይ ያርፍባታል፡፡ ርዕሱን አይታ፣ ወረቀቱን ደባብሳ እና አገላብጣ ጣለችው፡፡ የሴቶች ጉዳይ በሴቶች ለመነበብ አለመፈለጉ ገርሞኝና የንባብ ፍራቻችንን ታዝቤ ንባቤን ቀጠልኩ፡፡
መንዝ ሳንደርስ በሚኒልክ መስኮት ጉብኝታችን ላይ ተማሪ ታምሩ ዋቻራን ስለጉዞው ጠይቄው ‹‹አላማችን ቦታው ላይ ችግር ካለ ደካማ ጎኖቹን ለማየት እና ችግሩን ጠቁመን ስፍራውን ለጎብኝ አመቺ ለማድረግ ነው››  ብሎኛል፡፡ ተማሪ የኔካሳ ዮሴፍ ደግሞ መኪና ውስጥ በጠየኳት ወቅት‹‹ጓሳን አይተን ለመምጣት ነው ሃሳባችን፤ የፒስታውን መንገድ ሁኔታ የምታየው ነው ለቱሪስት አይመችም፤ ለጉብኝት ጥሩ መኪና መኖር አለበት፤ ምግብና በቂ አገልግሎት የለም ተብሏል፤ መሻሻል አለበት›› በማለት የታያትን ሃሳብ ሰንዝራለች፡፡ ቃልኪዳን ተስፋዬ ደግሞ ‹‹ሃገራችን የተለያዩ የተፈጥሮ ገጽታዎች አሏት - የተፈጥሮ ደን፣ አራዊቶች፡፡ ልማት ግን መስፋፋት አለበት -ለቱሪስት እንዲመች፡፡ ፒስታው ደረጃው ቢስተካከል ጥሩ ነው፡፡›› ብላኛለች፡፡
ትምህርት ቤት ከመዘዞ ከተማ ውጭ ጓሳ እስክንደርስ አለማየታችን ያሳሰባቸው ነበሩ፡፡ ‹‹ሊወድቅ የደረሰ ቤት ጋ ትምህርት ቤት ይላል፡፡ትምህርት አለ ወይ? መምህር አለ ወይ? ያስብላችኋል፡፡›› አለ አንደኛው ተጓዥ፡፡  ምንአልባት ትምህርት ቤቶቹ ከመንገዱ ርቀው ተሰርተው ሊሆን ይችላል፤ አላውቅም፡፡ በመንገዳችን አንድ ደብረ ብርሃን የሚገኘውን  የሃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤትን ዩኒፎርም የለበሰ ተማሪ ብቻ ማየታችንን ሳስበው እኔንም ተማሪዎቹ የት አሉ? አስባለኝ፡፡ ስንመለስ የመንገዱ ሌላኛውን አቅጣጫ ስለምናይ አንድ ሌላ ትምህርት ቤት በግድ አገኘን፡፡
ከባሽ ከተማ በኋላ ባለው ጉዟችን የእርከን ስራና በእርከኑ ጥግ የመኖ እጽዋት በማየቴ ተደስቻለሁ፤ እንደ ጎሼ ባዶ ምን አልባት እስካሁን ካልተደረገ በዘመናዊ የማር ምርት ቢታጀብ እላለሁ፤ የንብ መኖ የሚሆኑ ዛፎችንም መትከል ስለሚቻል፡፡ ችግሩ ግን ይህ ሃሳቤ እዚያ ያሉት ሃላፊዎች ዘንድ እንዴት ይደርሳል የሚለው ነው፡፡ ባሽ ላይ ሆኖ ሸዋሮቢት ከተማን ማየት ጣርማበር ተራራ ላይ ሆኖ ደብረሲና ከማየት በላይ ልብን ይሰውራል፡፡ ዳኛቸው ወርቁ አቧራ የረጋበት የሚመስለው የሚለው ይፋት እውነትም እንደ ጥቁር ጉም መሳይ ነገር እንደሸፈነው ለማየት ችያለሁ፡፡  መንዝ ብዙ የባህር ዛፍ እና መጠነኛ የጽድ ደን ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ምን ጊዜ ተከሉት ይህን ሁሉ ያስብላችኋል፡፡ ከደቡብ የመጡት ተማሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም ከመጡበት ስፍራ ጋር በማወዳደር ‹‹መንዝ ላይ ልምላሜ ወፍ የለም›› ሲሉ ግን ገና እንደሚቀረን አሰብኩ፡፡
የአንኮበር ቤተመንግስት ሎጅን የሚመስለው የጓሳ ማህበረሰብ አቀፍ ፓርክ የእንግዶች ማረፊያ እልፍኝ እና ጎጆዎቹ ከሩቅ በአስታ ጫካ ተከበው ከተራራውና ሸንተረሩ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታዩ አዕምሮን ያረጋጋሉ፣ መንፈስን ያድሳሉ፣ ሁለመናንም ይጣራሉ፡፡ በጎዴ ከተማ መልክ በአባይ ተፋሰስ አጥኝዎቹ አሜሪካውያን ፊታውራሪነት  በዘመናዊ መልክ ለመንዝ ህዝብ የአስተዳደር ማዕከል ትሆን ዘንድ በ1959 የተቋቋመችው እና የዚያን ጊዜ የተጀመሩት የአስተዳደር ህንጻዎቿ አሁንም እንዳላለቁላት የሰማሁላት እና ያነበብኩላት ከተማ መሃልሜዳ ለመድረስ 22 ኪሎሜትር ሲቀረን ፓርኩ ላይ ወረድን፡፡ ‹‹መሃልሜዳ መንዝ መሃል ሜዳ›› አለች ዘፋኝ፡፡ ያኔ ከአሜሪካውያኑ ጋር አብሮ በሃላፊነት ይሰራ የነበረው ተጉለቴው ዶክተር ሃይለጊዮርጊስ ወርቅነህ ያነሳቸው የልማት ዕቅዶች የበጉን እርባታና የእርሻውን ምርት ማዘመኑ አሁን መነሳሻውና መታወሻው ሰዓት አይመስላችሁም?
እንደ ፓርኩ ኃላፊ እንደ አቶ አበበ ገለጻ ከሆነ ፓርኩ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በማህበረሰቡ የሚጠበቅ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ ወደክልሉ ሰውና ከብት ካስገቡ ከፍተኛ ቅጣት ይጣልባቸው ነበር - ፓርኩ በባህላዊ አስተዳደር በነዋሪው ሲተዳዳር፡፡ ትኩስ የነብር ለምድ፣ የቀጨሞ ሙቀጫ (ቀጨሞ ውስጡ ክፍት ነው አሉ) እና አንድ ሺህ ዳውላ እህልን ዓይነት የማይፈጸሙ ቅጣቶች ማህበረሰቡ ራሱን ከስፍራው እንዲያገል ለማድረግ ይጣሉ ነበር፡፡ በተወሰነ ጊዜ እየዘጋን እየከፈትን ብንጠቀምበት ይሻላል ያሉት ከጎንደር መጡ የተባሉት የመንዝ መስራች ሁለት ወንድማማቾች ስፍራውን ሲከባከቡት እንደኖሩ አስጎብኛችን ነግረውናል፡፡ ከሰው ንክኪ ለተከለለው ስፍራ አመራር አቋቁመው ከ3 እስከ 5 ዓመት ድረስ ይጠብቁትና ጓሳውን ይጠቀሙበታል፡፡ ማገዶ እንጨት ቢኖርም ዋናው ለቤት መስሪያ የሚጠቀሙበትን ጓሳ ነው በጣም የሚፈልጉት፡፡ ‹‹ጓሳ ደማችን ነው ብለው ስለሚያምኑ አሁም ይጠብቁታል›› ብሎናል አቶ አበበ፡፡
የዩ.አይ.ኤ.ኤ ተራራ ክብካቤ ሽልማትን ያገኘው እና በዘመናዊ መልክ እ.ኤ.አ. በ2003 የተመሰረተው  መንዝ ጓሳ በሰሜን ኢትዮጵያ በአፍሮ አልፓይን ተራሮች ክልል ውስጥ ይገኛል፡፡ ማስጎብኘቱና ዘመናዊ አሰራሩ እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ እንደጀመረ፣ እንዲሁም በጀርመኑ የፍራንክፈርት ዙኦሎጂካል ሶሳይቲ እና በአውሮፓ ህብረት እገዛ እንደተቋቋመ ተነግሮናል፡፡ ቀይ ቀበሮ፣ አንኮበር ሰሪን የተባለች ወፍ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እንዲሁም ሌሎች እንስሳት በስፍራው ይገኛሉ፡፡ዝንጀሮዎቹ ዋሻ ውስጥ ካደሩ ጅብ ስለሚበላቸው ገደል ላይ ያድራሉ፡፡ አብዛኞቹን እንስሳት ለመጎብኘት በጠዋት መነሳትና ርቀት መንገድ መሄድ ግድ ይላል፡፡ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራው አላማ ማህበረሰቡን መጥቀም ነው - ጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤት የመሳሰሉትን የህዝብ መገልገያዎች መስራት፣ በዕደ ጥበብ በተለይ በባና ስራ ህዝቡን መጥቀም እና በአጠቃላይ ስነህይወታዊና ባህላዊ ሃብቶችን መንከባከብ ፡፡  የጓሳ ክልል 7800 ሄክታር ይሸፍናል፡፡
ፓርኩ የሚያስጎኛቸውን ሁሉ ጎብኝቶ ለመጨረስ አንድ ጎብኝ የሶስት ምሽቶችና የአራት ቀናት ጉብኝት ያስፈልገዋል፡፡ 11 አልጋ እና 6 ክፍል መኝታ ቤት በስፍራው ሲኖር ጎብኝዎች በብዛት ከመጡ በድንኳን ያድራሉ ወይንም ወደ መሃል ሜዳ ከተማ ይሄዳሉ የሚል መረጃ ተሰጥቶናል፡፡ ፓርኩን በአመት ከ300 ያነሰ ሰው የሚጎበኘው ሲሆን በብዛት የሚጎበኘው አዲስ አበባ በሚኖሩ የውጭ ዜጎች ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ጎብኝ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ 
የፓርኩ ባለንብረቶች በአቅራቢያው ያሉት የዘጠኝ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ፓርኩን ያቋቋመው የውጭ ድርጅት በተለያዩ ምክንያቶች ስፍራውን ለቆ በመውጣቱ የአማራ ክልል የጓሳ ማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽ/ቤትን አቋቁሟል፡፡ ለሰራተኞች የሚከፈለውን ደሞዝና የስራ ማስኬጃውንም ከጉብኝቱ እና ዶክመንታሪ ፊልም ከሚሰሩ አካላት ከሚገኘው ክፍያ ይሸፍናሉ፡፡ ሎጁ እንዳይድግ የመንገድ ችግር አለ፡፡ ጥበቃው ደካማ ስለሆነ የፓርኩ ተጠቃሚ አይደለንም የሚሉ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ከአጣዬ እየመጡ ጓሳውን ያቃጥሉ ነበር፡፡
በስፍራው ያገኘናቸው ጀርመናውያን ቱሪስቶችን ይዞ የመጣው ‹‹ጀርመን ሃገር 28 ዓመት ኖርኩ፤ አሁን ግን አዲስ አበባ ተመልሻለሁ›› ያለን ሐበሻ ‹‹የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እዚህ አገር ውድ ነው›› ብሏል፡፡ ‹‹ከጀርመን ተነስተህ፣ ግብጽ ደርሰህና አካባቢውን ጎብኝተህ 15 ቀን ተዝናንተህ ከነአውሮፕላን መሳፈሪያው 300 ዩሮ ትከፍላለህ፤ እዚህ ግን 3000 ዩሮም የበረራ ወጭህን ሸፍኖ ሁለት ሳምንትም አያኖርህም፡፡ የኢትዮጵያዊና የፈረንጅን ዋጋ መለያየት አስመልክቶ ጀርመኖቹ እናንተ አገር የጥቁር አፓርታይድ አለ ብለውኛል›› ብሎናል፡፡ ‹‹ልጄ ማስተርሱን እያደረገ ነው፤ ኢትዮጵያ መጥቶ የተማረው አማርኛ ‹መብራት የለም፣ ውሃ የለም፣ ችግር የለም › የሚል ነው›› አለን፡፡
በጓሳ በጥበቃ ስራ ላይ ለተሰማሩ አንድ ሰው ያቀረብኩት ጥያቄ ነበር፡፡ ይኸውም ‹‹መንዞች የጥንቱን የአባቶቻችሁን ትውልድ፣ ዘራችሁን እንዴት ነው የምትቆጥሩት›› የሚል ነበር፡፡ ‹‹ምን እኔ ብዙም አላውቀውም፤ ግን የሚየውቁት ሲቆጥሩት ከመጀመሪያው ጀምረው ጉም አስጎምጉም ብለው ነው የሚጀምሩት፡፡›› አሉኝ፡፡ የዚህንም ጉም አስጎምጉም የሚለውን ትርጉሙን ሳሰላስል ቆየሁ፡፡ ጉም አንዴ መጥቶ አስገምግሞ አደባይቶ ያልፋል፤ ዝናቡን፣ በረዶውን፣ ካፊያውን እና ውሽንፍሩን አውርዶት፡፡ ወይንም ዳኛቸው ወርቁ እንደሚለው ጀጅሮ፣ ወይንም ተጉለቶች እንደሚሉት በነሃሴ እኝኝ ብሎ፣ አፍኖ፣ መብረቅ በመብረቅ አድርጎት፡፡ መሬቷ ከመስከረም ወዲህ አትረጋም ይላሉ ዝናቡ እስካለ ድረስ፡፡ ልክ እንደወላድ ያደርጋታል፤ ወልዳ የምትገላገለው ጸደይ ሲገባ ነው፡፡ ያ አንድ ትውልድ መሆኑ ነው ወደ ሰዎች ሕይወት ስናመጣው፡፡ መንዞችም ትውልዳቸውን ከዚህ ጉምና ውጤቱ ጋር አዛምደውታል ማለት ነው ጉም አስጎጉም ሲሉ፡፡ ከመንዝ በመጣሁ በማግስቱ አያቴን አግኝቻት ስለዚህ ጉዳይ ማለትም ስለ ጉም አስጎምጉም ስጠይቃት ‹‹በኛ በተጉለቶች ዘንድ ሰው ሲበዛ ነው እንደዚያ የሚባለው፤ በለቅሶም በሰርግም  ሰዉ ጉም አስጎምጉም ነው ከተባለ እንደ አሸን ፈላ ማለት ነው›› ስትለኝ ‹‹ይህም አለ›› ብዬ  ‹‹ሌላ መንዜ ዘር ቆጠራ አዋቂ አዛውንት እስካገኝ ልጠብቅ›› ብዬ ዝም አልኩ፡፡
ተማሪዎቻችን ጠዋት ያስረፈዳቸው ነገር ከዩኒቨርሲቲው ምግብ ቤት ምግብ ማስቋጠር ኖሮ እነሱ የቋጠሩትን ፍርፍር፣ እኛም ጓደኛችን መምህራቸው የያዙትን ስንቅ ጓሳ ግቢ ውስጥ በላን፡፡ እርስዎ ጓሳ መሄድ በሚፈልጉ ጊዜ ስለምግብ ጉዳይ የየማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራውን ሰዎች ማነጋገር ይኖርብዎታል፡፡ እያበሰሉ እንዲመገቡ ሁኔታው ይመቻችልዎታል፡፡ የጓሳ ሎጅ ግንቡ ከአካባቢው በሚገኘው ጥቁር ድንጋይ የተገነባ ሲሆን ጣራው ደግሞ በእንጨት ተዋቅሮ ሳር የለበሰ ነው፡፡ እጽዋትን፣ ጭላዳ ዝንጀሮን፣ ፍልፈል የቆፈራቸውን ጉድጓዶች፣ የአካባቢውን የገጠር ቤት፣ የህዝቡን አሰፋፈር እንዲሁም አኗኗር ለማየት ችለናል፡፡ ከተማሪዎቻችን ጋርም የተወሰነ ርቀት የእግር ጉዞ አድርገን አካባቢውን ቃኝተናል፡፡ የጦስኙ ሽታ፣ የአስታው እና የጓሳው ትዕይንት፣ የመልከአምድሩ ወጣ ገባነት ሁሉ ቀልቡን ያልሳበው ጎብኝ ከመካከላችን አልነበረም፡፡ ከተምኞችና የከተማን ህይወት የለመዱ ስለበዙ በየስፍራው ቁጭ ማለትና ሲሄዱም ማለክለክ የጉዞው አካል ነበር፡፡ ለተማሪዎቻችን በእንግሊዝኛ ማለክለክ ‹‹ቱ ፓንት›› እንደሆነ ነግሬያቸው የአንድ ኢትዮጵያዊን ተማሪ ገጠመኝንም ነገርኳቸውና በሳቅ ፈረሱ፡፡ ተማሪው አሜሪካ የትምህርት ዕድል ደርሶት ጥቁር ፓንት ለብሶ እንዲሄድ የደረሰው የአለባበስ መመሪያ ያሳስበዋል፡፡ ግማሽ ደርዘን ቅያሪ ጥቁር ፓንት ገዝቶም ይሄዳል፡፡ እንደገባም አሜሪካውያኑ የታል ጥቁሩ ፓንት ሲሉት ቀበቶውን ፈቶ ያሳያቸዋል፡፡ ግን በአሜሪካውያን እንግሊዝኛ ፓንት ማለት ሱሪ ማለት ነበር፤ ተማሪውም ይህን አላወቀም ነበር፡፡ በኛ አገር ፓንት የምንለው ደግሞ በአሜሪካን አንደር ዌር ይባላል፡፡
በአጠቃላይ ጉዳይ ከሌለው አንድን ስፍራ ሄዶ ለማይጎበኘው ለኛ ሰው ይህን ዓይነቱ አጋጣሚ የማይገኝ ነው፡፡ እኔም መንዝን እስካሁን ሳላይ ቆይቼ ስላየሁት ደስተኝነት ተሰምቶኛል፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ይህን ዓይነት ጉዞ ማስጎብኘቱ ቢቀጥል የሚል አስተያየቴን እሰጣለሁ፡፡ በቅርብ ያሉትን ስፍራዎች ሲጎበኙ አካባቢውን በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ለማገዝ ያመቻል፡፡ ሌላ ሩቅ ስፍራ ከሆነ ግን ወጪውም ከፍተኛ ነው፡፡

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...