2023 ጁላይ 9, እሑድ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማርኩት አማርኛ ከአንዳንድ ነጥቦች ጋር

 

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማርኩት አማርኛ ከአንዳንድ ነጥቦች ጋር

እሁድ፣ ነሐሴ 2፣ 2015 ዓ.ም.

መዘምር ግርማ

ደብረብርሃን

 

አንዲት ሽቅብ የምትገለጥ ሲናር ላይን ደብተር ነበረች የመጀመሪያውን የዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ትምህርት የተማርኩባት፡፡ ‹‹የጽህፈት ክሂል አንድ›› የተባለው ትምህርት የተሰጠን በመምህር ግርማ ነበር፡፡ መጀመሪያ የገባን ቀን በመረጥነው ርዕስ ላይ አንቀፅ እንድንጽፍ የክፍል ስራ ተሰጠን፡፡ እኔ የጻፍኩት ከደብረብርሃን አንጻር የአዲስ አበባን ህዝብ የአለባበስ ዘይቤ በማነፃፀር ሲሆን፤ በተለይም ሴቶቹ ላይ አተኩሬያለሁ፡፡ ለጽሑፌ ውበት ግነት ጨማምሬና አንድ የገጠር ሰው ቢያይ በሚሰጠው አስተያየት መልክ አድርጌዋለሁ፡፡ ሙግት ወይም ገለጻ ከሚያደርግ አንቀፅም የምትሻገርና ወደ ትረካ የምታደላ ስለሆነች መምህር ግርማ በቀጣዩ ቀን ጽሑፎቻችን አርሞ ሲመጣ ለክፍሉ ተማሪ በሙሉ አነበባት፡፡ በተጉለት የአማርኛ ዘዬ ስለተንቆጠቆጠች ተማሪውም ዘና ብሎባታል፡፡ ባለፉት ዓመታት የጻፉ ተማሪዎችን ጽሑፍ ሲያስነብበን እንዳደረገው ሁሉ የኔንም የማን እንደሆነች አልተናገረም፡፡ በአንደኛ ደረጃ የትምህርት ጊዜዬ ግጥም እገጣጥም ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃም በአማርኛ ክፍለጊዜምንባብ ሳነብ በጥሩ ሁኔታ መተረኬን ጓደኞቼ ነግረውኛል፡፡ ለአስረኛ ክፍል ፈተና ዝግጅት የዳኛቸው ወርቁን ፈሊጣዊ አነጋገሮች መጽሐፍ ከኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ቤተመጻሕፍት መምህር ተራመድ ተውሶልኝ አንብቤያለሁ፡፡ የአስራ አንድ ወይም አስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜም ፍቅር እስከ መቃብርን አንብቤያለሁ፡፡ በጣም ዉሱን ተግባራት ቢሆኑም ከአማካዩ ተማሪ አንጻር ለአማርኛ ዝንባሌ አለኝ ለማለት ነው እነዚህን መጠቃቀሴ፡፡ ከቃላት ዓይነቶችና ተፈጥሮ እስከ አገልግሎታቸው፣ ከተሳሳተ የቃላት አጠቃቀም እስከ አራዳ ቋንቋና ሙያዊ ቃላት በክፍል ውስጥ የምንማረውን በቤተመጻሕፍት በመምህር ደረጀ ገብሬ መጽሐፍ እናጠናክራለን፡፡ የምንጽፋቸውን አንቀፆች ለክፍሉ ተማሪዎችና ለመምህራችን የማንበብ ዕድል ይሰጠናል፡፡ ስለ ሰካራም ዓይነቶችና ስለ ጀግና የጻፍኳቸው አንቀፆች ትዝ ይሉኛል፡፡ አንድ ቀን የቤት ሥረ ተሰጥቶን ሞጋች ጽሑፍ ጽፌ መምህራችን ርዕሱን ሲያዩት ጥሩ እንዳልሆነ መክረውኛል፡፡ ከዚችም ከዚያችም ፖለቲካ እየቃረምኩ ፓርቲው በተፈጠረ በሳምንታት ውስጥ የቅንጅት ደጋፊ ሆኜ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን የሚተች ጽሑፍ አዘጋጅቼ ነበር፡፡ ይኸውም ተሟጋች አንቀፅ ‹‹የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና በቀቀኖች አንድ ናቸው›› የሚል ርዕስ ነበረው፡፡ ዝርዝር አረፍተነገሮቹ ደግሞ ሁለቱ እንዴት አንድ እንደሆኑ ይሞግታሉ፡፡ መምህራችን ‹‹እናንተስ ተመርቃችሁ እዚያ አይደል የምትገቡት!›› አሉኝ፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ የጽሕፈት ክሂልና ፖለቲካን ማነካካት አልነበረብኝም፡፡ ለነገሩ ትምህርትን ፖለቲካን ለማስረፅ የተጠቀምኩት እኔ ብቻ አልነበርኩም፤ የጋዜጠኝነት መምህራችን የሕወሃትን ፍልስፍና ሊያሰርጽብን ይሞክር ነበር፡፡ ስሙ የማነ ነው፡፡ የአዲስ አበባን የግል ጋዜጦች እያመጣ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምንና የሌሎችን የፖለቲካ ጽሑፎች ከርዕስ አሰያየም እስከ ዝርዝር ጉዳያቸው ሲያበጥር ይውላል፡፡ ‹‹እንዴ መምህር፣ ይህ እኮ እንደዚህ ለማለት አይደለም›› ማለት አይቻልም፡፡ ያውም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ፀባይ! ያውም ለትግሬ መምህር! አጥንትህም አይገኝም!

ወደ ዋናው ጉዳዬ ልመለስ፡፡ የአገረሰብ ርዕሰጉዳዮችን የሚያስተምረውን የፎክሎር ትምህርት መምህር መስፍን ሰጥተውናል፡፡ ዶርሰንንና ማሪያ ሊችን ለትውር እየጠቃቀሱ ስለ አገረሰባዊ አመጋገብ፣ አለባበስ፣ ትውን ጥበባት፣ ቤት አሰራር፣ ሕክምና  አስተምረውናል፡፡ ትምህርቱ አሳታፊ እንዲሆንም በየአካባቢዎቻችን ካለው ልማድና ባህል ጋር ላማስተሳሰር በመጠያየቅና በመወያየት እንድንማማር ያደርጋሉ፡፡ ስነቃልን በተመለከተ በዶክተር ፈቃደ አዘዘ በዚሁ ርዕስ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ተጠቅመናል፡፡ ቆይቶ ሰለሞን ተሾመ ዳጎስ ያለ የፎክሎር መጽሐፍ ጻፈ እንጂ ማጣቀሻዎቹ በሙሉ የእንግሊዝኛ ነበሩ፡፡ እንግሊዝኛው ከአማርኞች አንጻር ለእኛ በመንፈቅ አምስት የእንግሊዝኛ ኮርሶች ለምንወስደው የእንግሊዝኛ ተማሪዎች ሳይቀለን አይቀርም፡፡ አማርኞች የሚያሳዝኑኝ ሁሉን ነገር የሚሰሩት ከእንግሊዝኛ መጻሕፍት ተርጉመው ነው፡፡ የሚያቀርቡት በአማርኛ ስለሆነ በጥራት መቅረብ አለበት፡፡ እንደኛ እንደ እንግሊዝኛ ተማሪዎች የተወሰነ መሳሳትን የማይፈቅዱ መምህራን አሏቸው፡፡ አማርኛን በንዑስ የምንማረውንም የተመለከትን እንደሆነ የተወሰኑ በቋንቋው አፍ ያልፈቱ ልጆች አሉ፡፡ ይህም ትግርኛና ኦሮምኛን አይጨምርም፡፡ እነሱ የራሳቸው ቋንቋዎች በንዑስ ስለሚሰጡ በአፍመፍቻዎቻቸው ለመማር ችለዋል፡፡  አማርኛን በንዑስ የሚወስዱት በቋንቋው አፍያልፈቱ ተማሪዎች ታዲያ በትጋት ስለሚያጠኑ ሁልጊዜ ውጤታቸው ከእኛ በላይ ነው፡፡ እኛ አማርኛን በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደ ቀላል የማየት ልማድ ስላለን በዚያው ቀጥለን ቢ እና ሲ መቃም ለምደናል፡፡ በዚህ ዓመት አያት እንደሆነ ደውሎ የነገረኝ የአብአላው አፋር ጓደኛዬ ዋሲያ ረቢሳ ሲማ አማርኛን በንዑስ ተምሯል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለዞኑ በምትቀርበው በመቀሌ ስለተማረ ትግርኛም ይችላል፡፡ አማርኛ የመረጠበትን ምክንያት እሱ ያውቃል፡፡  ለነገሩ ዋሲያ ስሙ እስከአያቱ በአፋርኛ ስለሆነ ‹‹ኢትዮጵያዊ ስም ያለኝ ኩሩ ኢትዮጵያዊ›› እያለ ስለሚናገር የትኛውንም ቋንቋ ቢማር አይደንቅም!

የአማርኛ ሥነጽሑፍ ትምህርት ለዘዋሪና ስራፈት የእንግሊዝኛ ተማሪ አይሆንም፡፡ የአ.አ.ዩ. እንግሊዝኛ ትምህርት ክፍል ተማሪን ያደድባል፡፡ አያሰሩንም፡፡ በአማርኛ ትምህርታችን እናልምጥ ብንል ግን የሥራችንን ያህል እናገኛለን፡፡ ላለመውደቅ ማጥናት ግድ ይላል፡፡ ያለዚያ ቋንቋውን አውቃለሁ ብሎ መታበይ በኤፍ ሰይፍ ያስቀስፋል፡፡ ማለቴ አብዛኞቹ አብረውኝ የተማሩት የአዲስ አበባ ልጆች ፊልም ውስጥ እንዳሉት ፈረንጆች እያወሩ በእንግሊዝኛ ትምህርት ከሲ እንደማይዘሉት ነው፡፡ ‹‹ያውም እንግሊዝኛ! ለዚያውም አዲስ አበባ! በቃ ተጫርክ፡፡ ከአዲስ አበባ ልጅ ጋር እንዴት ይሆንልሃል?›› የተባለልኝ ትንቢት ፉርሽ ሆነ፡፡ በአማርኛውም እንደሆነ ‹‹ያውም አማርኛ፣ ያውም ከአማሮች ጋር!›› ተብለው ሊሆን የሚችሉት የደቡብ ልጆች ልካችንን አሳይተውናል፡፡ የአማርኛ ሥነግጥም ይኖራል ብዬ በንዑስ ለመውሰድ የገባሁበት አማርኛ ሥነግጥም ብጠብቅ ብጠብቅ የለውም፡፡ የተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው የሥነጽሑፍ መሰረታውያን መጽሐፍ ላይ ካነበብኩት በላይ አልተማርኩም፡፡ ጋሽ ዘሪሁን የዝርው ልቦለድ በተለይም የአጭር ልቦለድ ትምህርት ሰጥተውናል፡፡ ትምህርቱ ስለተዋሃዳቸው ከትውር እስከ ትንታኔ ሲያስተምሩ በቃላቸው ነበር፡፡ የአርአያን ውሱን ክፍሎች ክፍል ውስጥ አንብበውልናል፡፡ ስዕሎቹንም አይተናል፡፡ እርሳቸው ካሰናዱት የአጭር ትረካዎች ስብስብ ‹ልብወለድ አዋጅና ሌሎችም … › የአፈወርቅ ገብረኢየሱስን የወልደዞፍና የወለተዞፍን ታሪክ አንብበውልናል፡፡ ያንን ትረካ ወደ ግጥም ቀይሬው መጀመሪያ ለዶርሜ ልጆች፣ ቀጥሎ ለክፍሌ ልጆች በመጨረሻም ባህል ማዕከል በአንድ ምሽት አንብቤዋለሁ፡፡  የታደሰ ሊበንን ጅብ ነች፣ ዉሻውና መንገዶቹ … የተመስገን ገብሬን የጉለሌው ሰካራም አንብበናል፡፡ ትንተኔዎችንም አንብበናል፡፡ በዚህ ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ደማሙ መምህራችን ስለሚያዝናኑን እንወዳቸው ነበር፡፡ ሌላኛው የሥነጽሑፍ ትምህርት የመምህርት ሰላማዊት ሲሆን ‹የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ቅኝት› ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፈውን ሁሉ የሥነጽሑፍ ስራ ከነደራሲውና እስካገኘው የሂስ ምላሽ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ የአማርኛ አነሳስ ላይ የተሰጡ መላምቶች፣ በ14ኛው ክፍለዘመን ለአፄ አምደ ጽዮን የተጻፉ መወድስ ግጥሞች፣ በ16ኛው ክፍለዘመን መሰለኝ የተጻፉ የአባ ጎርጎርዮስ ደብዳቤዎች፣ የኦርቶዶክስና የካቶሊክ የአማርኛ በራሪ ጽሑፎች፣ በውጪ አገር ሰዎች የተጻፉ ክታቦች፣ የማተሚያ ማሽን ሲመጣ የታተሙ ጽሑፎች፣ ጦቢያ፣ አግአዚ …. እያለ እኛ ዘመን ላይ ግጥም ይላል፡፡  በአስተማሪያችን የተመረጡትን ዋና ዋና መጻሕፍት ማንበብ ግድ ነው፡፡ ለአስር ማርክ አምስት ልቦለዶችን አንብበን ተንትነናል፡፡ እኔስ በንዑስ ስለሆነ በመንፈቅ አንዲት ትምህርት ነች፤ በዐቢይነት የሚወስዱትን ስቃይ አስቡት፡፡ ለዚህ አስረጂ የሚሆነኝ አንድ ቀን የጂማውን ልጅ ዋሴን ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ኬኔዲ ቤተመጻሕፍት አግኝቼው ወደ ዶርም እንሂድ ስለው ‹‹እስኪ አንቺ ሂጂ፤ እኔ እኮ አማሮ ነኝ፡፡›› ያለኝ ነው፡፡

ሌሎቹ ሁለት የአማርኛ ትምህርቶች የአማርኛ ሰዋስው ናቸው፡፡ ስማቸውን የረሳኋቸው አንድ ቀይና አንድ ጠይም መምህራን ያስተማሩን እነዚህ ትምህርቶች ከባድ ናቸው፡፡ ጠይሙ የኔ ሰው መሰለኝ፡፡ ቀዩ ደግሞ ፕሮፌሰር መሰሉኝ፡፡  የባዬ ይማምንና የጌታሁን አማረን የሰዋስው መጻሕፍት ሳያነብ እንደኔ በደብተሩ ብቻ የተማመነ ሲውን ማንም ላይነፍገው ይችላል፡፡ የእነዚህን ትምህርቶች ሁኔታ ሳስብ በአማርኛ ጥራትና ብስለት ከፍ ያለ ደረጃ የደረሱ የአሜሪካና የጀርመን ድምፅ ጋዜጠኞች፣ በሳል ቀደምት ደራስያን፣ የአገራችን ልሂቃን የሆኑ በርካቶች የቋንቋዎች ጥናት ተቋንም (የቋ.ጥ.ተ.) የቀድሞ ተማሪዎች አስታውሳለሁ፡፡ ጠቃሚዎቹን ሁለቱንም መጻሕፍት ለማንበብ ቀጠሮ ይዣለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ መዓዛ አሸናፊ የቋ.ጥ.ተ. ምሩቅ ነች ማለትን ሰምቻለሁ፡፡      

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ስር አራት የትምህርት ክፍሎች ነበሩ፡፡ የዉጪ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ፣ የሥነልሣን (ማስተማሪያው እንግሊዝኛ የሆነ) እንዲሁም ቲያትር ጥበባት (ማስተማሪያው አማርኛ የሆነ) ነበሩ፡፡ አደረጃጀቱ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በዐቢይና በንዑስ ማስተማራቸው ተማሪው ሁለት ቋንቋዎችን አያይዞ እንዲማርና የተስተካከለ ዕውቀት እንዲኖረው ያግዛል፡፡ የህ አሰራር በዚህ ዘመን መቅረቱ ግን ትክክል አይመስለኝም፡፡ ክፍሎቻችን እንደ አጋጣሚ ሆኖ በየቋንቋዎቹ ማለትም በንዑስ በምንወስዳቸው የተከፋፈሉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በእኛ ክፍል የአማርኛና የትግርኛ (ሰባት ስለሆኑ ለትግርኛ ትምህርት ብቻ ይለዩናል እንጂ ሌላውን አብረውን ይማራሉ) ተማሪዎች ነበርን፡፡ ኦሮምኛ ለብቻው ነው፡፡ ፈረንሳይኛ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ አረብኛ የሚወስዱት በሌሎች ክፍሎች የተመደቡ ይመስለኛል፡፡ ተመርቀን ከወጣን በኋላ በመገናኛ ብዙኃን የሰማሁት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍልን ወደ ሦስት ማለትም አማርኛ፣ ትግርኛና ኦሮምኛ የከፈለው ውሳኔ መምህራን ያልተቀበሉት ሲሆን እስከ ፌደሬሽን ምክር ቤትም የደረሰ ነበር፡፡ የፖለቲካ ውሳኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሲያናጋው ያ የመጀመሪያው ስላልሆነ እንደበፊቶቹ ውሳኔዎች ሁሉ እሱም አለፈ፡፡ የእንቅስቃሴው መሪ የአማርኛና ኦሮምኛ መምህር አብርሃም ዓለሙም ከአገር ተሰደዱ፡፡ ያሳደገን የትምህርት ክፍልም ለሦስት ተከፈለ፡፡ የድህረ ምረቃ ትምህርቴን ልከታተል ስሄድ ደግሞ የቋንቋዎች ጥናት ተቋምንም አፈረሱት፡፡ ለመሆኑ ስንት ምሁራንን ያፈራና የራሱ ጥናታዊ መጽሔት ያለው ተቋም ይፈርሳል?  

 

አማርኛ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ

 

አማርኛ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ  

በመዘምር ግርማ

እሁድ ሐምሌ 2 2015 ..

ደብረብርሃን

 

በዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ትምህርት ክፍል ብቻ የተወሰነው የአማርኛ ትምህርት በአሁኑ ወቅት በተለይ በአራት ዘርፎች ሊመደቡ የሚችሉ የትምህርት ዓይነቶች አሉት፡፡ እነርሱም የጋዜጠኝነትና ተግባቦት፣ የባህልና ሥነጽሑፍ፣ የሥነልሣን እንዲሁም የክህሎት ናቸው፡፡ አንድ የዲግሪ ተማሪ በእነዚህ ምድቦች ያሉትን የትምህርት ዓይነቶች በሙሉ መውሰድ ይገባዋል፡፡  

ጋዜጠኝነትና ተግባቦት ተማሪዎች ስለ ጋዜጠኝነት፣ ተግባቦት ብሎም ሕዝብ ግንኙነት መሰረታዊ ጽንሰሐሳቦች ዕውቀት የሚጨብጡበት፣ በተግባር የሚለማመዱበትና ለወደፊቱ የሥራ ዓለም ራሳቸውን የሚያዘጋጁባቸው ትምህርቶች ምድብ ነው፡፡ ልምድ ባላቸው መምህራን የሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶች በፈተና፣ በጽሑፍ ሥራ እንዲሁም በልዩ ልዩ የልምምድ ተግባራት የተማሪውን ብቁ መሆን ይፈትናሉ፡፡ የግል፣ የጥንድና የቡድን ስራዎችን በመሥራት፣ የቤተመጻሕፍት ተጨማሪ ንባብ በማድረግና ወደ ቤት የሚወሰዱ ስራዎችን በመሥራት ተማሪዎች ራሳቸውን ያበቃሉ፡፡

ተመሳሳይ አካሄድን የሚከተለው የባህልና ሥነጽሑፍ ምድብ ተማሪዎች በአማርኛ የሚተላለፉ የባህል፣ የትውፊት፣ የሥነቃልና ተያያዥ ዕውቀትን የሚመረምሩበት ነው፡፡ የአጭርና ረጅም ልቦለድ፣ የግጥም፣ የተውኔት፣ የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍና የሒስ ትምህርትም የሚሰጠው በዚሁ ክፍል ነው፡፡ ባህልን የሚያጠናውና ምናባዊ ሥነጽሑፍን ጉዳዬ ብሎ የሚይዘው ይህ ክፍል በምናብ እየተጓዙ ለመዝናናትና የደራስያንንና አሳብያንን የምናብ ውጤት በሳይንሳዊ መንገድ ለመተንተን ያስችላል፡፡

ሥነልሣን በበኩሉ የቋንቋውን መዋቅር፣ ሥነድምፅ፣ አውዳዊ አጠቃቀም፣ የተግባቦት አላባውያን፣ ሥነልቦናዊና ማህበራዊ ገጽታ  የመሰሉ ዘርፎችን የያዘ የቋንቋ ሳይንስ ጥናት ነው፡፡ በቃላት፣ በሰዋስውና በልዩ ልዩ አውዶች በሚጠቅሙ የቋንቋው ባህርያት ላይ ያተኮረው ስነልሣን ተማሪዎች የሚጠቀሙበትን ቋንቋ ምንነት ለማወቅ፣ ለመመራመርና በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል መሰረታዊ ዕውቀትና ክህሎት የሚጨብጡበት ነው፡፡

የክህሎት ትምህርት ምድብ ደግሞ አራቱን የቋንቋውን ክህሎቶች ከልምምድ ጋር አጣምረው የሚማሩበት ሲሆን ከጀማሪ እስከ ከፍተኛ የሚሄዱ የትምህርት ዓይነቶች በየዘርፉ ምርምር ባደረጉና የማስተማር ልምድ ባላቸው መምህራን ይሰጣሉ፡፡ ማድመጥ፣ መናገር፣ ማንበብና መጻፍን ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተማሩት ላይ የሚቀጥል ክፍል ይማራሉ፡፡ የክህሎት ትምህርት ለሌሎቹ ለሦስቱ ምድቦች መነሻነ መሠረት ነው፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኛ፣ የሥነጽሑፍ ሰውም ሆነ የሥነልሣን ተመራማሪ ያለ ጥሩ የቋንቋ ክህሎት የትም አይደርስምና፡፡

ከላይ ካየናቸው አራት የትምህርት ምድቦች በዘለለ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚሰጡ የጋራ ትምህርቶችን ይወስዳሉ፡፡ በትምህርት ክፍሉ የሚወስዷቸው የምርምርና ዘገባ አጻጻፍ፣ የትርጉም ትምህርት፣ ግዕዝ አንድና ሁለትና ሌሎችም አገር በቀል ዕውቀትን የሚጨብጡባቸው ናቸው፡፡ ትምህርትዎን በተግባር ለማዳበር ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲን ያየን እንደሆነ የዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል በሥነጽሑፍ ምሽቶቹ፣ በመጽሐፍ ክበቡ በሚደረገው ውይይት፣ በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄደው ዓመታዊ የባህልና ቋንቋ አውደጥናት እገዛ ያደርግልዎታል፤ ዕድሎቹን ያመቻቻል፡፡

የአስራ ስድስት ዓመታት ልምድ ያለው የትምህርት ክፍላችን ምሩቃን በጋዜጠኝነት፣ በህዝብ ግንኙነት ባለሙያነት፣ በአርታኢነት፣ በሃያሲነት፣ በመምህርነት፣ በባህልና ቱሪዝም ባለሙያነት፣ በአጠቃላይ በቋንቋ፣ ባህልና ኪነጥበብ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ባለሙያዎች ለመሆን ችለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት የሆኑት የአማርኛ ምሩቃንና መምህራን ትምህርታቸውን በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ በመቀጠል በየዘርፉ መምህራንና ተመራማሪዎች ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ቋንቋችን የማደግ ዕድሉን ተጠቅሞ ከተሰራበት ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ዕድል የሚሰጠን ሲሆን፤ ከዚህ የበለጠ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን፣ በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች የሚሰጡ የትምህርት ዘርፎች ትምህርት በአማርኛ እንዲሰጥና ለሁለንተናዊ ዕድገት እንዲጠቅም ሊሰራበት ይገባል እንላለን፡፡ በዚህም ስራ ንቁ ተሳታፊዎች ነን፡፡  በአፍሪካ ህብረት የሚያገለግል ቋንቋ ይሁን ሲባል፣ በአሜሪካ የሚያገለግል ቋንቋ ይሁን ሲባል እንዲሁም በቻይናና ሩሲያ ሲያስተምሩት ቋንቋው ያለውን እምቅ አቅም ተጠቅመው የበለጠ ተጽዕኖ ለመፍጠር ነው፡፡ ከዚያስ በላይ ምን ዓይነት ዓላማ ይኖራቸው ይሆን? እኛስ አማርኛን እንጠቀመዋለን፣ በሳይንሳዊ መንገድ እናጠናዋለን ወይስ የዳር ተመልካች ሆነን እንቆማለን?

ይህን ጽሑፍ ልጽፍ የቻልኩት በርካታ ኢትዮጵያውያን ለአማርኛ ቋንቋቸው ልባዊ ፍቅር ቢኖራቸውም ቋንቋቸው ምን ያህል እምቅ አቅም እንዳለው የግንዛቤ እጥረት ሊኖርባቸው እንደሚችል ከልምድ በመመልከቴ እኔም በሚገባኝ ልክ ያንን እንዲገነዘቡ ለማስቻል ነው፡፡ በአስርት ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ቋንቋውን ይናገሩታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ ሊጽፉበት ይችላሉ? ለመሆኑ በቋሚነት የአማርኛ ጽሑፎችን የሚያነቡ በበቂ ቁጥር ይኖራሉ? በየሙያ ዘርፎቹ በበሳል ባለሙያዎች የሚቀርቡ የአማርኛ ዝግጅቶችን በንቃት የሚከታተሉ ምን ያህሉ ይሆኑ? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ እጅግ ከባድ ሲሆን፤ መልሱንም ለማግኘት ራሱን የቻለ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መልሱ ከተገኘ ግን ቋንቋችን ምን ዓይነት መንገድ ላይ እንዳለ ለማወቅ የሚረዳ ይመስለኛል፡፡  

አንዳንዶች አማርኛ መጻፍ ቢችሉም በቋሚነት መደበኛ የሆነ የጽሑፍ ግንኙነት ለማድረግ ዕድሉ ስላልተመቻቸላቸው ወይም ስላልፈጠሩ ከደብዳቤና የግል ማስታወሻ በዘለለ አይጽፉበት ይሆናል፡፡ የአማርኛ የእጅ ጽሑፋቸው ተዳክሞ መጻፍ እየረሱ ያሉ እንዳሉ ሳትታዘቡ አትቀሩም፡፡ ንግግርም የሆነ እንደሆነ ምን ያህል የተስተካከለ፣ የሃሳብ ፍሰቱን የጠበቀና ከባዕድ ቃላት የፀዳ ንግግር ማድረግ እንችላለን የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ አጥርቶ ማሰብና ያንንም በማያሻማ ሁኔታ መግለጽ የሚቻለው ከዉጪ ቋንቋዎች ይልቅ በተለይ በአገሬው ቋንቋ መሆኑ እውን ሆኖ በዚህ ላይ አልተሰራበትም፡፡ ከሥርዓተ ትምህርት፣ ከቋንቋ ፖሊሲ፣  ከፖለቲካ ውሳኔዎች ጋር የተያያዙ አማርኛን የሚመለከቱ ጉዳዮች ቢኖሩም በተለይ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ትምህርት ሲሰጥበት አይተው ለማያውቁና ቋንቋውን ከመናገር እምብዛም ላልዘለሉ መረጃ መስጠትና ለበለጠ ምርምር መገፋፋት አስፈላጊ ነው፡፡

አንድ ቋንቋ በህብረተሰብ ውስጥ ለዕለት ከዕለት ሕይወት በመግባቢያነት ከሚሰጠው ግልጋሎት በዘለለ በትምህርት፣ በአስተዳደር፣ በምርምር፣ በፖለቲካ፣ በመገናኛ ብዙኃን ወዘተ ዓይነተኛ መደበኛ ሚና ይጫወታል፡፡ አማርኛ በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች እየሰጠ ያለው፣ ሲሰጥ የነበረውንና ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት ይህ ነው ወይንም ሊሆን ይገባዋል ብለን በቁጥር ባናስቀምጠውም ግዙፍ አቅም የነበረው፣ ያለውና ሊኖረው የሚችል መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ቋንቋችን በትምህርት ዘርፍ ከሚሰጠው ግልጋሎት አንጻር አንዲቱን ብቻ መርጬ ልጽፍባት ወደድኩ፡፡ ይኸውም አማርኛ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ሲሰጥ ያለውን ሲሆን በተለይ በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርትና ይዘት ላይ አተኩሬ እየተሰጡ ያሉትን የትምህርት ይዘቶች፣ አሰጣጣቸውን፣ የጥናቱን አቅጣጫና ስፋት እንዲሁም የምሩቃኑን አቅም ለማስገንዘብ ሞክሬያለሁ፡፡

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...