ዓርብ 29 ጃንዋሪ 2016

መጽሐፍ ግምገማ




በጥላሁን ጣሰው
(ደራሲና የሥራ አመራር አማካሪ)
የመጽሐፉ ርዕስ - ሁቱትሲ
 የገጾች ብዛት - 236
ዋጋው - 59.75 ብር
መዘምር ግርማ “ሁቱትሲ” በሚል ርዕስ የተረጎመውን የኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ መጽሐፍ አንብቤዋለሁ። ስለተርጓሚው የቋንቋ ጥራትና ምጥቀት ዶ/ር ያዕቆብ ለመጽሐፉ ከሰጡት ቀዳሜ ቃል በላይ የምለው የለኝም። በዚህ ግምገማ የማተኩረው በመጽሐፉ ውስጥ ከምንተዋወቃቸው ሰዎች ሦስቱን በመውሰድ ከወግ፣ ሃይማኖትና ባህል በመነሳት ንጽጽር በማድረግ ቀደም ብለው መጽሐፉን ያነበቡት በጥልቀት እንዲያስተውሉት፣ ያላነበቡትና ወደፊት የሚያነቡት ትኩረት እንዲያደርጉበት አጽንዖት ለመስጠት ነው።
ኢማኪዩሌ ኃጢያትና ክፋት ሳይኖራት እንደ እዮብ በፈተና ውስጥ የምታልፍ ናት። ትምህርት ቤት ውስጥ ዘረኛው መምህር ሁቱዎች ቁሙ፣ ቱትሲዎች ቁሙ፣ቱዋዎች ቁሙ እያለ ሲጠይቅ የምን ዘር (በመዘምር አማርኛ ዘውግ) እንደሆነች ስለማታውቅ ከመቀመጫዋ ሳትነሳ የቀረች ልጅ ነበረች። ወላጅ አባቷ ይህን ሲሰማ መምህሩን በማነጋገር ይህን አወጋገን እንደተቃወመ ይሰማናል። መምህሩ ግን ኢማኪዩሌን በክፍል ውስጥ ጠርቶ ቱትሲ ስል ትቆሚያለሽ ብሎ ይነግራታል። ይህች የዋህ፣ ቅን ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደምናገኘው እግዚአብሔርን የሚፈራ ግን የሚፈተን ሰው እሷም በእግዚአብሔር ቸርነት በወላዲት አምላክ አማላጅነት ለወሬ ነጋሪ የተረፈች እንደሆነች ትነግረናለች።
በወቅቱ የሩዋንዳ ሕብረተሰብ በአደገኛ የሥነልቦና ቀውስ ውስጥ መሆኑን ለማሳዬት በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸው ቄሱን ነው። ቄሱ ከፍራትና ከጥቅም አንጻር ነገሮችን በማዬት እንደ ጲላጦስ ለመሆን እንኳን የማይደፍሩ ናቸው። “እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ  በነዚህ ሰዎች ላይ አልፈርድም” ለማለት እንኳ ድፍረቱ የላቸውም። እንደ አንድ ሃይማኖት አባት “ሁላችሁም የአንድ ቤተክርስቲያን ልጆች ናችሁ። ማንም በወንድሙ ላይ ቆንጨራ ቢመዝ ኃጢያተኛ ነው። ይህን ተላልፎ ወንድሙ ላይ እጁን ለመሰንዘር የሚፈልግ በኔ ሬሳ ላይ ይራመድ።” ብለው ለማውገዝ ጥንካሬ የሌላቸው ናቸው። በቅርቡ ክርስቲያንና ሙስሊም ተጓዦች ላይ ኬንያ ውስጥ አልሸባብ ነጣጥሎ ለመግደል ሲሞክር እስላሞቹ ክርስቲያኖቹን ከገደላችሁ እኛንም ግደሉን ያሉበትን ያህል መንፈሳዊ ጥንካሬ ለመንፈስ ልጆቻቸው ሞት አላሳዩም። ሴቶቹን ደብቀው የሚያስቀምጡበት ዓላማም ከወደፊት ጥቅም አንጻር የተሰላ መሆኑ የሚታወቀው ምስኪን ተደባቂዎቹን የተደባቂዎቹ ዘር በደል ይፈጽም ነበር ብለው በማውራት ሲያሸማቅቋቸው ነው። እንደ አንድ መንፈሳዊ አባት “እናንተን እግዚአብሔር የሚፈትናችሁ ስለሚወዳችሁ ነው። ብጹዕ ናችሁ። ፈተናውን ታልፉታላችሁ። በናንተ ላይ የሚፈጸመው ሁሉ ትክክል አይደለም።” ብለው አያጽናኑም። ራሳቸው ተስፋ አጥተው ተደባቂዎቹንም ተስፋ ቢስ ያደርጋሉ። ይልቁንስ ቄሱ በፍራት ተውጠው የሁቱ ጽንፈኞችን ሃሳብ እንደሚደግፉ ለጽንፈኞቹ ዘረኞች በመናገር ቀውሱን ያባብሱታል። እንደ አንድ መንፈሳዊ አባት ሁላችሁም ልጆቼ ናችሁ። አንዳችሁን ከአንዳችሁ አላበላልጥም። ምህረትና ትህትና እናገራለሁ።” ለማለት አልቻሉም። አንዲቷን ቤተክርስቲያ በዘር ከፋፈሏት ማለት ነው። ሁቱዎች ብቻ የሚያመሰግኑባትና የሚቀድሱባት ዓይነት። በዘመኑ ሩዋንዳ በመንፈስም ደረጃ የደረሰችበትን ዝቅጠት አመላካች ገጸ ባሕሪ ናቸው።
የኢማኪዩሌ አባት በመንግሥት ከአድልዎ ነጻ የሆነ ሥርዓትና ሕጋዊነት የሚያምን ነው። ስለዚህ በትምህርት ቤቶች በዘር የሚከፋፍለውን አስተማሪ ለማስተካከል በከንቱ እንደሞከረው ሁሉ ጭፍጨፋው በጀመረበት ወቅት የዘር ጭፍጨፋውን አቃጅና አስፈጻሚ ለሆኑት የመንግሥት ሹማምንት እየተሠራ ያለው ሥራ ትክክል ስላልሆነ የመንግሥት ሹማምንት ጣልቃ ገብተው በሃላፊነት ጭፍጨፋውን እንዲያስቆሙ ሲወተውት በዚያው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚገደል ነው። ወንድ ልጁ ፍጅቱን ለማቆም ወይም ካልተቻለ ለመሰደድ የሚያቀርብለትን ሃሳብ በመንግሥትና በሕግ በመተማመን በእንቢታ የቆመ አባት ነው። የመንግሥት መዋቅሮች የዘር ሴራ ማውጠንጠኛ በሆኑበት ሁኔታ በመንግሥትና በሕግ ላይ እንደዚህ የጸና እምነት ያለው ሰው በሃይማኖትና ዓለማዊ መጽሐፎች ውስጥ ማነጻጻሪያ ሊሆን የሚችል ለጊዜው ትዝ አይለኝም። መኖሩንም እጠራጠራለሁ። የኢማኪዩሌ መጽሐፍ የዚህ ዓይነት ተምሳሌት ፈጥሯል።
በኢማኪዩሌ መጽሐፍ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናውቀውን ጳውሎስን የሚስተካከል ሁቱ ተወላጅ አናይም። ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን አሳዳጅ የነበረ ሲሆን በኋላ ተመልሶ ለክርስትና መስዋዕት የሆነ ነው። በሩዋንዳ አማጽያን ካምፕ ሁቱዎችን ብናይም በአደባባይ የቱትሲ መግደያ መሣሪያውን ጥሎ “ከእንግዲህ በቃኝ። በቱትሲዎቸ ላይ እጄን አላነሳም። ብትፈልጉ እኔንም ግደሉኝ፣’’ ብሎ ነውጠኞቹን የሚጋፈጥ ሰው በመጽሐፉ አይታይም። እንዲህ ዓይነት ሁቱዎችን ለመፍጠር ምናልባት በመሸሽ ፈንታ ተፋጥጦ በመቆም ‹ብትፈልጉ ግደሉኝ ሃሳባችሁ ትክክል አይደለም› የሚሉ ቱትሲዎች በብዛት ባለመኖራቸው ጥቂት የጳውሎስ ዓይነት ሁቱዎች አልወጡ ይሆናል። ይህ ከሆነ ደግሞ የሩዋንዳ ሕብረተሰብ በዚያን ወቅት የመጣበትን መዓት ለመቋቋም የማይችል ነበር ማለት ነው።  
በኢማኪዩሌ መጽሐፍ ውስጥ ቀሳውስቱ በመንፈስ ልጆቻቸው መሃከል በፍራትና በጥቅም ታውረው ቤተክርስቲያኒቱ የዘር ቅርጽ ስትይዝ ሳይከላከሉ፣ የመንግሥት ተቋማት የዘር አድማና ሴራ መጠንሰሻ ማዕከልነት ተቀይረው በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ይሆናል ብሎ ከመጠንቀቅ አይሆንም በሚል ተስፋ ጸጥ ብሎ ቆሞ እናገኘዋለን። ሩዋንዳ ወደ ፈተና ገባች። ክፉው ሁሉ ተፈጸመባት።በቸርነቱ የተረፉት ቂምን ሳይሆን ምህረትን አደረጉ። የኢማኪዩሌ ታሪክ ይህ ነው።
መዘምር ተርጉሞ ስለቀረበልን ምስጋና ይግባው። ልብ ያለው አንባቢ ልብ ይበል።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school.

  Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school. The Shenes said they wanted to aven...