ቅዳሜ 16 ኦገስት 2025

በቁርባኑ ሰሞን የተቀበረው ጠ.ሚ.ና ደስታውን መግለጽ ያልቻለው ጭቁን ሕዝብ

 

‎መለስ ዜናዊ ሞተ ከተባለበት ቀን ከአርባ ቀን በፊት እንደሞተ ይገመት ስለነበር (ኢሳት፣ ኢትዮጵያን ሪቪው ወዘተ በዘገቡት ...) መሞቱ ሲነገር አልደነቀኝም። ጨካኝ አምባገነን መሪ ስለነበረ ‎በመሞቱ አገሬ ትለወጣለች ብዬ በማሰቤ ደስ አለኝ። የተሻለ ቀን ይምጣ አይምጣ ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም ነበር።

‎ጠዋት 2:00 ላይ ወደ ባንክ ሄድኩ። የታክሲው ሹፌር ዜናውን እንደሰማ ገልፆ ምናልባት ረብሻ ከተነሣ በማለት በጊዜ ወደ ቤት እንድንገባ መከረን።

‎ምን እንደሚከሰት እርግጠኛ አልነበርኩም።

‎ወደ ባንክ ሄጄ 8,000 ብር አወጣሁ።

‎ተመልሼ ገንዘቡን እቤት አስቀምጬ ወደ ዩኒቨርስቲ ሄድኩ። የክረምት ተማሪዎች በየቦታው ቆመዋል። መምህራን ወደ ክፍል አልገቡም። 

‎ወደ መምህራን መዝናኛ ክበብ ስገባ ብዙዎቹ ወደ ቴሌቪዥኑ ተጠግተው ይከታተላሉ። አንድ መምህር ያለቅሳል። ለሥርዓቱ ቅርበት ነበረው። ቴሌቪዥኑ በተደጋጋሚ የመለስን መሞት በሰበር ዜና እያስታወሰ የሀዘን ዋሽንት በተደጋጋሚ ይለቃል። ቀስ በቀስ የትካዜ ስሜት ይሰማኝ ጀመር። ምክንያቱም የዋሽንቱ ዜማ ነበር። ላውንጁን ትቼ ወጣሁና ከፕሮፓጋንዳው ተላቅቄ ለማሰብ ለራሴ ጊዜ ሰጠሁ። የተጀመረውን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሁኔታ ስመለከተው ህዝቡ የሀዘኑ ተካፋይ እንዲሆን ለማድረግና አመጽ እንዳይነሣ ከወር በላይ ቀድመው ሰርተውበታል። 

‎በዚያን ሰሞን የመንግስት ሚዲያዎች የብሔራዊ ሀዘኑን በመዘገብና በማስተባበር ሥራ ተጠምደው ከረሙ። እነ ስብሃት ነጋም ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለመጠይቅ መለስ ቢሞት የሚመጣ ለውጥ እንደማይኖርና ማንም ገብረማርያምም ሆነ መሐመድ) ቢመጣ የሚሠራ ሥርዓት መዘርጋቱን ተናገሩ። 

‎በወቅቱ አንድ ሰው ከነገሩኝ ዉጪ የመለስን ሞት አስመልክቶ የደስታ አከባበር ያካሄደ አልነበረም። በየአረቄ ቤቱ የተገናኙ የደርግ ወታደሮች በሹክሹክታ ደስታቸውን መግለጻቸውን ነገሩኝ። በከተማም በገጠርም ውሎ ተዋለ። ህዝቡ ተገዶ አለቀሰ። ቤተመንግሥትም ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ። እኔ አልሄድኩም። የለቅሶ አጣሪ ኮሚቴ በየቦታው ተቋቁሞ እንደነበር ይወራል። 

ከአስረኛ ወይም ከሱ ተቀራራቢ ፎቅ በመለስ ሞት አዝኖ እራሱን አጠፋ ስለተባለው ወጣት ሰምታችኋል? አጣሪ አካል ቢያጣራው ጥሩ ነው። ምናልባት በመለስ ሞት ተደስቶ አይተውት በበቀል ጥለውትስ ቢሆን?

 ከሰሞኑ በቲክቶክ ያየሁት በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የመለስን ሞት በዘፈንና በእስክስታ ያሳለፉት ለኔ አዲስ ነገር ነው። ዕድለኞች ናቸው። በአገር ውስጥ ነፃነት ቢኖር ህዝቡ በደስታ የሚያሳልፋት ቀን ትመስለኛለች። ህዝቡ ደስታውን እስካሁን አላከበረም። አረሳሱለት እንጂ የመለስ ሞት በደስታ ማለፍ ያለበት ነበር። ምክንያቱም ይህችን አገር በጎሳ ከፋፍሎ ለፍጅት ስላዘጋጀን ነው። 

‎መንግስት ህዝቡ በሀዘን ስሜት ውስጥ እንዲገባ ባያደርግና ህዝቡ የበቀል እርምጃዎችን ባይፈራ ህዝባዊ አመጽስ ሊነሣ አይችልም ነበር? 

‎ለመሆኑ የመለስ ሞት ጊዜ ምን ታስታውሳላችሁ?

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በቁርባኑ ሰሞን የተቀበረው ጠ.ሚ.ና ደስታውን መግለጽ ያልቻለው ጭቁን ሕዝብ

  ‎ ‎መለስ ዜናዊ ሞተ ከተባለበት ቀን ከአርባ ቀን በፊት እንደሞተ ይገመት ስለነበር (ኢሳት፣ ኢትዮጵያን ሪቪው ወዘተ በዘገቡት ...) መሞቱ ሲነገር አልደነቀኝም። ጨካኝ አምባገነን መሪ ስለነበረ ‎በመሞቱ አገሬ ትለወጣለ...