ቅዳሜ 31 ዲሴምበር 2016

ከሃያ ሳምንታት በኋላ (After Twenty Weeks)




የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቀድሞ (2008 ዓ.ም. ተመራቂ) ተማሪዎች ስራ ከያዙ ገና በጣት የሚቆጠሩ ወራት ብቻ ነው ያስቆጠሩት፡፡ ቢበዛ አራት ወር ቢሆናቸው ነው፡፡ የንግድ ባንክን ፈተና እየተፈተኑ ባለበት ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ስለ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ይወያያሉ፡፡ ‹‹ለዩኒቨርሲቲያችን ምን እናድርግ?›› በማለት ያሰቡትን ለማሳካት በየሳምንቱ በመስቀል አደባባይ ይገናኙ ነበር፡፡ ብዛት ያለው ህዝብ በዚያ ስፍራ ባንዴ መገኘቱ ደግሞ ስብሰባዎቻቸው ፍቃድ ስላልነበሯቸው አንድ ፈተና ነበር፡፡ ለማንኛውም በሃሳቡ ያመኑትና እስከመጨረሻው የዘለቁት ምሩቃን ገንዘብ አዋጥተው በዩኒቨርሲቲው ሲማሩ ይቸግሯቸው የነበሩትን የአካውንቲንግ፣ የማኔጅመንት እና የኢኮኖሚክስ መጻሕፍት ገዙ፡፡
በትናንትናው ዕለት በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት አዳራሽ የተጋበዝን እንግዶች አድናቆታችን ልክ አልነበረውም፡፡ ቅልብጭ ያለቸው መርሃ ግብራቸው የምሩቃኑ ተወካዮች ከአዲስ አበባ ድረስ ረፍታቸውን ተጠቅመው በመምጣት የተሳተፉባት፣ ብሎም መምህራን፣ ኃላፊዎችና ተማሪዎች የተጋበዙባት ነበረች፡፡ የምሩቃኑ ሰብሳቢ አቶ መሰረት መምህራን ፈተና የሚያወጡት ከነዚህ ከተገዙት መጻሕፍት እንደሆነ ጠቅሶ ተማሪዎች አንብበው ውጤታቸውን እንዲያሻሽሉና ግንዛቤያቸውን እንዲያዳብሩ መክሯል፡፡መሰረትም ሆነ ጓደኛው ኦሜጋ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲን አመስግነዋል፡፡ ቤታቸው እንደሆነና አብረውት እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል፡፡ ኦ ሄንሪ የጻፈው ‹‹አፍተር ትዌንቲ ይርስ›› የሚለውን አጭር ልቦለድ መሰረት አድርገው ከሃያ ዓመታት በኋላ የተገናኙ የባህርዳር ተማሪዎች ነበሩ፡፡ መሰረት የእነዚህን ተማሪዎች አርዓያነት በመጥቀስ ወደፊት ዩኒቨርሲቲያቸውን እንዲያስታውሱ ተማሪዎችን አሳስቧል፡፡ የነመሰረት ተግባር ሃያ ዓመትም ያልቆየና ምናልባትም ሃያ ሳምንታት የቆየ ድንቅ ተግባር መሆኑን መገንዘብና አርዓያነታቸውን መከተል ያስፈልጋል እላለሁ፡፡  
የመጨረሻው መጀመሪያ፡-
በስፍራው በመገኘት የመከሩንን ዶክተር ሰይድን አመሰግናለሁ፡፡ የኮሌጁ ዲን አቶ ደረጀና የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ለቀና ትብብራቸውና የምሩቃኑን ምኞት ለማሳካት ላደረጉት እገዛ ምስጋና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ባለፉት ወራት በትምህርት ብዛትና በተከታታይ ምዘና ጋጋታ ሰልችቼ ለነበርኩት ለመምህራቸው እነ መሰረት ‹‹መጻሕፍትን እንዴት እናንብብ›› በሚል ርዕስ የ15 ደቂቃ ገለጻ እንዳደርግ ስለጋበዙኝና አስደሳች ቆይታ እንዳደርግ ምክንያት ስለሆኑኝ አመሰግናለሁ፡፡  
ለማሳረግ ያህል፡-
አንድ መርሃ ግብር የተሳካለት ከሆነና ስሜትን ቆንጥጦ የሚይዝ ከሆነ እንባ እንባ ይለኛል፡፡ ትናንትም የተሳካ ዝግጅት ያደረጉት ምሩቃኑ እንባ እንባ እንዳስባሉኝ መደበቅ አይኖርብኝም፡፡


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...