ቅዳሜ 31 ዲሴምበር 2016

አምቦ በዚህ ሰሞን


(ማሳሰቢያ፡- ማስታወሻዬን በሰዓቱ ለማድረስ ከሞባይል ላይ መገልበጥ ያለበት የአንድ ሰዓት ቃለመጠይቅ አለኝ፡፡ በዚህም ምክንያት ሙሉው ጽሑፍ እስኪደርስ በዚች አዝግሙ፡፡ አስተያየታችሁን ግን አትንፈጉኝ፡፡)

በመዘምር ግርማ
ሕዳር 25፣ 2009 ዓ.ም.
ስለ አምቦ ምን ስሰማ ነበር?
መኖሪያ ቤቴ ከሚገኝባት ከደጋማዋ ደብረብርሃን ወደ አምቦ ለመሄድ ስነሳ ስለ አምቦ መረጃ ለማሰባሰብ እንኳን ጊዜ አላገኘሁም ነበር፡፡ አንድ አካባቢውን የሚያውቁ ሰው ግን ‹‹አምቦ ቅርብ ነች፡፡ ትንሽ ሞቅ ትላለች፡፡ ነቀምት ብትዘልቅ ግን ጥሩ ነበር፡፡ ትክክለኛዋ ኢትዮጵያ ያለችው ወለጋ ነው፡፡ እዚህ ጋ ምንጭ፣ እዚያ ጋ ፏፏቴ፣ አለፍ ብሎ ጫካ … እንዴት ደስ እንደሚል!›› ብለውኛል፡፡
‹‹ከወለጋ ቀጥሎ ኦሮሞነትን ጠንከር አድርጎ የሚይዝ፣ ጀግናና ጠንካራ ሕዝብ ነው የአምቦ ሕዝብ፡፡ ጥሩ አየር አለው፤ ለጥ ያለ ሜዳ ነው፤ ፍራፍሬ አለው፡፡›› ብለውኛል አንድ ኦሮሞ ምሁር፡፡
‹‹በደርግ ጊዜ ጥይት ፋብሪካ ስለነበርና ፋብሪካውም የአምቦ ሕዝብ ጀግና በመሆኑ እንደተሰራ ስለሚነገር የአምቦ ሕዝብ ይህ መንግስት ሲገባ በጣም የተጋተረ ሕዝብ ነው፡፡ በዚያም ምክንያት አምቦ አሁን ምንም ዓይነት ልማት የለውም፡፡›› የሚለውን አስተያየት ስሰማው ቆይቻለሁ፡፡ ልማቱንም ሆነ ጥፋቱን አይቼ እንደምናገር ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡
ስለ አምቦ የነገሩኝ ሌላ ሰው እንዳሉት ‹‹ሰፋሪዎቹ ኦሮሞዎች ስለሆኑ ኦሮምኛ በብቸኝነት የሚወራበት ቋንቋ ነው፡፡ በምርጫ 97 ብዙ ሰው ሞቷል፡፡ ህዝቡ ንቅ ነው፡፡ የህዝብ ጥላቻ ግን የለበትም፡፡››
‹‹ዳዊት ስትደግም ስመህ ነው የሚከፈተው፤ እንጀራም ስትበላ ዝም ብሎ አይዘነጠልም›› እንዲል ጋሽ ሳሙኤል ይህን ጽሁፍ በዚህ መልኩ ከምንጀምረው እስኪ ለርስዎ የክፍል ስራ ይሰጥዎት፡፡ ውድ አንባቢ እውነት እውነት ስለ አምቦ ምን ያስባሉ? የተወሰኑ ነጥቦችን እስኪ ይጻፉልኝ፡፡
አጥንታችን ድረስ ፍርሐት ገባ
በመኪናችን ከሁለቱም በፊት የተለጠፉትን የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አርማዎች ላጥን፡፡ ታርጋው ግን ሊነሳ አይችልም፡፡ ወደፊት ለዩኒቨርሲቲ ስራ ስንንቀሳቀስ የግል መኪና ታርጋ (ኮድ 2 ወይም 3) ሊሰጠን ይገባል፡፡ ለደህንነታችን ሲባል የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አውቶቡስ ባለፈው ሰንዳፋ ላይ ተመትቷል፡፡ አዳማም ላይ ሰራተኞቻችን ተደብድበዋል፡፡ አርማችንን ስንልጥ ‹‹ዚስ ኢዝ ቢዮንድ ወርድስ›› አሉ አንዱ የታሪክ ሊቅ በብስጭት፡፡ ‹‹የእኛን ኦሮምኛ እንደ ኦሮምኛ አይቆጥሩትም›› የሚለውን የመሳሰሉ አስተያየቶች ይሰጡ ጀመር፡፡ ‹‹እኛስ እንዲህ አለፍን፤ ልጆቻችንስ ወደፊትስ?›› ያሉም አሉ፡፡
‹‹ሩዋንዳ ወደነበረው እየሄድን ነው›› ብለው ወደኔ ጠቆም አደረጉ፡፡
‹‹ዛፍ የለም፤ ተራሮች በዛፍ አልተሸፈኑም›› የሚል ምልከታውን እያነሳልን አብሮን የተጓዘው የቡድናችን አባል አንዲትን ለልማት ስራ የመጡ እንግሊዛዊት አስታወሰኝ፡፡ ‹‹ሁለት ሰዓት ሙሉ ተጉዘን የረባ ዛፍ ሳናይ እንቅር›› ነበር ያሉት እንግሊዟ፡፡
የሩዋንዳው ነገር ግን መልሶ ትዝ አለኝ፡፡ የዘር ማጥፋትን በወጣትነቷ ያየችው ሩዋንዳዊት ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ አንዴ ወደ ሰርግ ስትሄድ የነበረውን ስሜቷን ጽፋዋለች፡፡ እኔም ያን ዓይነት ፍርሐት ተሰማኝ፡፡ ስጋትና ጭንቀት ተደራረበብኝ፡፡ ሁቱትሲ ከገጽ 53-54 እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹ከተወሰኑ ወራት በኋላ ከዚህ የባሰ የሚረብሽ ክስተት ገጠመኝ፡፡ ዳማሲንና እኔ ከማታባ ወደ ኪጋሊ ለሠርግ እንሄዳለን፡፡ ረጅም፣ ወበቃማና አቧራማውን ጉዞ እያገባደድን ሳለን የመንገደኞች ማጓጓዣ ተሸከርካሪያችን ድንገት ቆመ፡፡
ቢያንስ 300 የሚሆኑ ኢንተርሃምዌዎች መንገዳችንን ዘግተው ቆመዋል፤ የሁሉም አለባበስ ለዓይን ይቀፋል፤ አስተያየታቸውም እጅግ ያስፈራል፡፡ ብዙዎቹ አላፊ አግዳሚው ላይ እየጮሁና እየተሳሰደቡ በቡድን ሲጨፍሩ የጠጡ ወይንም አደንዛዥ እጽ የወሰዱ ይመስላሉ፡፡ ነጂው ወደፊት ለመሄድ በጣም ስለፈራ ተሸከርካሪውን ወደኋላ ሊመልሰው እንደሆነ ነገረን፡፡ አብረነው የሁለት ሰዓቱን ለውጥ መንገድ እንድንሄድ፣ አሊያም ወጥተን በእግራችን እንድናዘግም አማራጭ ሰጠን፡፡
‹‹ተሽከርካሪው ውስጥ እንቆይ›› አለ ዳማሲን፡፡ ‹‹እነዚህ ሰዎች አብደዋል፡፡›› እኔ ግን በተለይ በነዚህ ወረበሎች ተግባር ለመፍራት ባለመፍቀዴና በሌሎችም ምክንያቶች ተሸከርካሪው ላይ መቆየቱን አልመረጥኩትም፡፡
‹‹እንውረድ እንጂ ሠርጉ ያመልጠናል እኮ›› አልኩት፡፡ ‹‹በእግራችን ብናዘግም ቤተ-ክርስቲያኑ ጋ አሁን እንደርሳለን፡፡››
ከተጓዦቹ ግማሽ ከሚሆኑት ጋር ወረድን፡፡ እንደወጣንም አልፏቸው የሚሄደውን ሰው መታወቂያ ከሚያዩት ኢንተርሃምዌዎች ብዙዎቹ ገጀራ እንደያዙ አየን፡፡ ንዴት ተሰማኝና ‹‹ማነው መብቱን የሰጣቸው?›› ስል ጠየቅሁ፡፡
ዳማሲን ተጨንቆ ‹‹ብንመለስ ጥሩ ይመስለኛል፣ ኢማኪዩሌ፡፡ ስለነዚህ ሰዎች መጥፎ ነገሮች ሰምቻለሁ፡፡ ተይ በእግራችን ወደ ቤታችን እንመለስ›› አለኝ፡፡
‹‹በእግራችን? በተሽከርካሪ አራት ሰዓት የፈጀብን በእግራችንማ በሦስት ቀንም አያልቅልን፡፡ ደግሞ እውነት እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን እንደ ጸጥታ አስከባሪ አደራጅተው እኛ ቱትሲዎች ስለሆንን ብቻ ጉልበታቸውን ሊያሳዩን አይገባም፡፡››
የዳማሲን ፊት ላይ ከሚነበበው ፍርሃት ይልቅ የኢንተርሃምዌዎቹ ነገር ቀላል ሆኖ አገኘሁት፡፡ ሁልጊዜ ሳቂታ ገጽታ የነበረውና ምናልባትም ከማውቃቸው ሰዎች ሁሉ ጠንካራው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ግን በእርግጥ እንደፈራ አየሁ፡፡ ለወትሮው ምን እንደሚሻል እጠይቀው የነበረ ቢሆንም አንዳች ነገር ወደፊት እንድሄድ ገፋፋኝ፡፡
‹‹ና አልፈናቸው እንሂድ›› አልኩት፡፡ ‹‹ምንም አንሆንም፡፡››
‹‹ያንን እንዴት አወቅሽ? እንደማይገድሉን ያሳሰበሽ ምንድነው? መንግሥት የፈለጉትን እንዲፈጽሙ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ጸጥታ አስከባሪ አይነካቸውም፡፡››
‹‹ችግር በሚገጥመን ቁጥር የምትለውን እናድርግ ዳማሲን፡፡ እንጸልይ፤ እግዚአብሔር እንደሚጠብቀንም እንተማመን፡፡››
ከቁጡ ጽንፈኞቹ ቡድን አሥር እርምጃ ርቀት ላይ በመንገዱ ዳር ቆመን ጸለይን፡፡ እግዚአብሔር ለአጭሯ መልዕክት ይቅር እንዲለኝ ጠይቄው በደኅና ወደ ቤተ-ክርስቲያኑ እንደርስ ዘንድ ግን የእርሱን ድጋፍ እንደምንፈልግ ነገርኩት፡፡ ወደኬላው ሄድኩ፤ የተወሰኑ ወጣት ወንዶች አይተውኝ በገጀራዎቻቸው ጭኖቻቸውን መታ መታ ያደርጋሉ፡፡
‹‹አይ በፍጹም፣ አይሆንም ኢማኪዩሌ… ስለዚህ ነገር እርግጠኛ ነሽ?››
‹‹አዎን፣ አዎን በቃ ምንም እንዳልተከሰተ ሁን - እንዲያውም ምናልባት መቁጠሪያህን ከኪስህ ብታወጣ ሳይሻልህ አይቀርም፡፡››
ወደ ኢተርሃምዌዎቹ ስንሄድ መቁጠሪያዬን በእጄ አጥብቄ ይዣለሁ፡፡ ደርዘን የሚሆኑት ከበቡን፣ ላይ ታች አዩኝና መታወቂያ ደብተራችንን እንድናሳይ ጠየቁን፡፡ በመጀመሪያ ዓይናቸው ላይ ትክ ብዬ አየኋቸው፡፡ ከዚያም ፈገግ አልኩ፡፡ በመጨረሻም ሰነዶቹን ሰጠኋቸው፡፡ በጣም ደፋር በመሆን እንዳስቸገርኳቸው ታየኝ - አንዲት ቱትሲ ሴት እነርሱንም ሆነ ገጀራዎቻቸውን ለምን እንደማትፈራ ሊገባቸው አልቻለም፡፡ መታወቂያዎቻችንን መልሰው ሰጥተውን አሳለፉን፣ ሆኖም ግን በዳማሲን ዓይኖች ውስጥ ያየሁትን ፍራቻ በፍጹም አልረሳውም፡፡ ሲፈራ ሳየው የመጀመሪያ ጊዜዬ ሲሆን በሩዋንዳ ላይ አንዳች ክፉ ነገር እንደመጣባት የሚያሳየውን ስሜቴን ላናውጠው አልተቻለኝም፡፡››
ፍኖተ-ሠላም
በመንገዳችን ምንም ዓይነት ችግር ሳይገጥመን አምቦ ገባን፡፡ ይሄ ሁሉ ፍርሐት ታዲያ የምን ይሉታል ስል ራሴን ታዘብኩ፡፡ አምቦን ያለ ስሟ ስም እንድናወጣላት ያደረገን ምንድነው?
አፋን ኦሮሞ - አፋን ሰበ ጉዳ
ጨልሟል፡፡ ጋቢና ያለው ጓደኛችን መስኮቱን ከፍቶ ‹‹መናኸሪያው የት ነው›› ብሎ አንዱን ወጣት ጠየቀው፡፡ መናኸሪያ አካባቢ አልጋ አይጠፋም ብሎ ነው፡፡ ‹‹ማል ጀደኒ?›› ሲለው የሚመልሰው ጠፋውና መልሶ መስኮቱን ዘጋው፡፡ ‹‹አንተ ታዲያ ኦሮምኛ እሞካክራለሁ ትል አልነበረም እንዴ?›› ብትሉኝ መልስ አለኝ፡፡ ስለ እውነት ለመናገር መናኸሪያ የሚል ቃል በኦሮምኛ ማንም አላስተማረኝም፡፡ ቢያንስ እኔም ይጠቅመኛል ብዬ አልጠየኩም፡፡ እኔ ይጠቅመኛል ብዬ ያሰብኩት መነ ጭሲቻ፣ ሲሬ፣ ኛታ፣ ወልገኢ ምናምን ነበር፡፡ የአማን ቃዲሮ፣ የታሪኩ አነጋ፣ የነብዩ ዓለማየሁ፣ የለሜሳ፣ የዝናወርቅ፣ የጥላሁን ግርፍ ነኝ፡፡ ይህን ስላላስተማሩኝ ወቀስኳቸው፡፡ አስበላችሁኝ! አልኳቸው፡፡ ከአምቦ መልስ ግን ያው መናኸሪያን እንደሚጠቀሙና እጅግ ካስፈለገ ቡፈታ ኮንኮላታ ሊባል እንደሚችል ነግረውኛል፡፡ አዳዲስ የኦሮምኛ ቃላት እና አገላለጾች እየፈሉ ነው በዘመናችን፡፡ በቋንቋው ቀናት፣ ወራት፣ ወቅቶች ሳይቀር እንደተሰየሙ ልብ ይሏል፡፡
ቀጥሎ ሌላ መንገደኛን ጠየቀ ጓደኛዬ፡፡ ‹‹ችግር የለም ላሳያችሁ›› ብሎ መኪናው ውስጥ ገብቶ ወደ ጀባትና ሜጫ ሆቴል ወሰደን፡፡ በአምቦ ማዕድን ውሃ ለ15 ዓመታት የሰራው ይህ ግለሰብ ቤተክርስቲያን ስሞ መምጣቱ ነበር እኛን ሲያገኘን፡፡ አልጋበዝም ብሎ ተሰናበተን፡፡ ‹‹አኒ ኢጆሌኮፊ ሴና መሌ ገቲ ዲሴ ሂንደርቡ›› የሚሉት አቶ ቤለማ ፉታሳ ሆቴል ነው ጅባትና ሜጫ፡፡
‹‹ኦሮምኛ የማንችል ሰዎች ግን ጉዳችን ነው፡፡ እናቴ ትችላለች፤ እኔ ግን አልችልም›› ላለችው የስብሰባችን ተሳታፊ ‹‹እንደ ሞባይል እኮ ነው ቋንቋ ማወቅ ማለት፡፡ እንማራለን፤ እንጠቀምበታለን፡፡›› በማለት የቋንቋው ተናጋሪ የሆነ መምህር ምላሽ ሰጣት፡፡
አምቦ ላይ ኦሮምኛንና አማርኛን አቀላቅሎ መናገር የተለመደ ነው፡፡ ለሁለቱም ቋንቋ ጆሮውን ከፍቶ ነው ሰው የሚጠብቀው፡፡ በአንጻሩ ምንም ኦሮምኛ የማይችሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አግኝቻለሁ፡፡ የአማራና ደቡብ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው እንደሚበዙ ሰምቻለሁ፡፡ አዳማ ላይ ካየሁት የሚለይ ከተማ ነው አምቦ በቋንቋ አጠቃቀም፡፡ አዳማ ሄዱ ማለት ባህርዳር ሄዱ ማለት ነው - በየድርጅቱ በር ላይ ከተጻፈው የኦሮምኛ ማስታወቂያ በስተቀረ፡፡
‹‹የአዳማ ሰው ከሌላው እስካሁን ከማውቀው ሰው ትንሽ መልኩ ለየት አለብኝ›› ያለኝ ጓደኛዬ እንደነበር አብረውኝ አምቦ ለሄዱት ስናገር አልተቀበሉኝም፡፡ ‹‹አሁን ከጋምቤላ በቀር እና ትንሽ ከአንዳንድ ደቡቦች በቀር እኛ ይሄን ያህል የሚወራ ልዩነት አለን?›› ነበር ያሉኝ፡፡
ሐገረ ሕይወት - አምቦ፣ አምቦ - ሐገረ ሕይወት
ዳግማዊ ምንሊክ የዳኑበት ፍልውሃ ነው፡፡ ሐገረ ሕይወት ሲሉ ሰየሟት ከተማዋን፡፡ አሁን አምቦ በሚባለው ስሟ ነው የምትታወቀው፡፡ መዋኛ ገንዳዎች አሉ፡፡ ፍልውሃ በሽ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሳይቀር አለ፡፡
የጀበና ቡና ያጥለቀለቃት ከተማ መሆኗን ለመታዘብ አፍታም አይፈጅብዎት፡፡ ሁሉም በየደጁ ቡና ይሸጣል፡፡ ሁሉም ጋ 3 ብር ነው የቡናው ዋጋ፡፡ ከፕላስቲክ ዘንቢል የሚሰሩ ሰዎችም በየዛፉ ስር ይታያሉ፡፡
ድንቂሲሳ ተመስገን እንደታዘበው ከአንድ ለእናቱ አስፋልቷ ጀርባ ብትጓዙ አምቦ ከተማ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ያለች ነች፡፡ እስኪ ይህን ኋላቀርነት ለማሻሻል የሚረዳን ሐሳብ ሰንዝሩ አንባቢያን፡፡
ደብረብርሃን ላይ በደንብ የማይሰማው ቅዳሴ አምቦ ላይ እጓዳዎ ድረስ ይመጣል፡፡ አነስተኛ የእስልምና እምነት ተከታዮች ቁጥር እንዳለና ወንጌላዊው ግን በርከት እንደሚል አጣርቻለሁ፡፡
ላሊሴ እንደነገረችኝ የስራ አጥነት ችግር ተንሰራፍቷል፡፡ የቀጣሪ ያለመኖር ችግር ነው ስራ አጥ ያደረገን ትላለች፡፡ ሰርግ እጠራሃለሁ ብላኛለቸ፡፡
በአንድ ወር ሁለት ጊዜ ከደብረ ብርሃን መውጣት ቱሪስት ያስብላል እንዴ?
ከደብረብርሃን የየዕለት ውሎ ልማዴ ወጣ ማለቴ አስደስቶኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲ መሄድ - ኮምፒውተር መጎርጎር - ፌስቡክ ላይ መጣድ -- ማታ ላይ ራስ አበበ ቤተመጻሕፍት ደረስ ማለት - ከዚያ ጌጤ ግሮሰሪ ጎራ ማለት - አምሽቼ እቤት መግባት - በጊዜ አጠቃቀም ችግሬ መናደድ!
በዚህ ወር ለአራት ቀናት መሐል ሜዳ፣ ለአራት ቀናት አምቦ ማሳለፌ ትንሽ የእለት አዋዋሌን ቀየር እንዳደርግ አድርጎኛል፡፡ ቱሪስት መባሌን ግን እንጃልኝ!
በሌላ ዜና
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ አምቦ ላይ ይደነቃሉ፡፡ በምን የሚደነቁ መሰለዎት? የአማራና ኦሮሞ እውነተኛው የዘር ምንጭ የሚለውን የፍቅር ምንጭ የሆነ መጽሐፍ መቶ ኮፒ ገዝቼ እንዳከፋፍል አንድ የአምቦ ሰው መክሮኛል፡፡ ገንዘብ ቢኖርማ!
አምቦ የገባን ዕለት ምሽት
በዚህ ምሽት አቶ በቀለ ባየታ ቶለሳን መንገድ ላይ አገኘናቸው፡፡ ‹‹እናተ አምቦ ላይ ሆናችሁ በቀኝ ትሄዳላችሁ እንዴ?›› ብለው ገሰጹን፡፡ እንግዶች መሆናችንን ታዝበዋል መሰል ‹‹ኑ በግራ›› ብለው የዘውን ሄዱ፡፡ ጠይም፣ ግዙፍ አዛውንት ናቸው፡፡ ምግብ ፈልገን እንደምንዞር ሲረዱ ወደ ባላምባራስ ገብረሥላሴ ቤት ይዘውን ሄዱ፡፡ ምግብ መኖር አለመኖሩን እራሳቸው ገብተው ጠይቀው እንድንገባ ጋበዙን፡፡ እኛን ከፊት ለፊታቸው አስቀምጠው እንደ ስብሰባ መሪ ተመቻችተው ተቀመጡ፡፡ ከማያልቀው የወግ ማዕዳቸው ለሦስት ሰዓት እንዳቋደሱን ስነግራችሁ በአግራሞት ነው፡፡
ወቅታዊውን የፖለቲካ ሁኔታ መረዳቸውን ለማሳየት ይመስላል እንዲህ ተቀኙ፡- ‹‹ከውጭ አገር ሱቅ በሪሞት ኮንትሮል ሲያዘጉ ኢህአዴግ በጉልበት ሊያስከፍት ይሞክራል፡፡ በፖለቲካ እንደተበለጠ ጥርጥር የለውም፡፡ የሚሻለው የውጭዎቹን በፖለቲካ ለመወዳዳር መሞከር ነው፡፡›› አሉ፡፡
ከመንግስትም ላለመጣላት ይመስላል ‹‹እኔ ከመንግስታት ሁሉ የምወደው ኢህአዴግን ነው›› ሲሉ ጨመሩ፡፡ ‹‹ምክንያቱም እንዲህ ዝነኛ የሆንኩት በሱ ጊዜ ነዋ!››
ባይ ዘ ዌይና ኮማንድ ፖስት የሚሉትን ሐረጋት በየደቂቃው ይጠቀማሉ፡፡ ሌላም እንግሊዝኛ አለቻቸው - ኮንትሪቢውሽን ትባላለች፡፡ የራት ሂሳቡ አንድ ሰው ላይ እንዳይጫን ሁላችሁም ብር አውጡ ሲሉ መከሩን፡፡ ይህ ጥበብ ኮንትሪቢውሽን ይባላል በእርሳቸው እንግሊዝኛ፡፡ እንግሊዝኛቸው ለክፉ አይሰጥም፡፡ ትግሪኛም በጥሩ ሁኔታ አብሮን ከተጓዘው የኤርትራ ተወላጅ ጋር አውርተዋል፡፡ ሽን የሚለውን ቅጽል ተጠቅመው ሌላ ቃልም ለዓለም አስተዋውቀዋል ጋሽ በቄ - ቶኩሜሽን ትባላለች፡፡ አንድነት ኃይል ነው ለማለት ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነቴን ነው እንጂ ዘር ቆጠራ አላውቅም፡፡ እኔ ሥልጣን ብይዝ ለኦሮሞ ካዳላሁ ምም ሰው አትበሉኝ፡፡ እናቴ አማራ ነች፡፡›› የሚለውን ለማጠናከር ነው ቶኩሜሽንን የተጠቀሙት፡፡
‹‹አብሮ ተኝቶ ገላ መደባበቅ ምንድነው?›› ላሉን ለአቶ በቀለ የመጣንበትን ጉዳይ ለመናገር ብዙም አላቅማማንም፡፡ የመጣንበትን ጉዳይ ሲረዱ አሁንም ሌላ ቅኔ ተቀኙ፡-
‹‹በጭፍን ጨለማ እንዳይቀር ገሚሱ
የነቃ እንዲነቃ ያዘዋል ሳይንሱ››
ደብረብርሃንና አምቦ እህትማማች ከተሞች እንዲሆኑ እንዲረዱን ጥያቄ ስጠይቃቸው እንዲህ ሲሉ መለሱልኝ፡- ‹‹እህትማማችማ ናቸው እኮ! እናንተ አልገባችሁም እንጂ፡፡ ይቺ ሐገረ-ሕይወት ነች! ያች ደብረ ብርሃን፡፡ ኢየሱስ እኔ መንገድም፣ ብርሃንም ሕይወትም ነኝ ብሏል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ አንድ አድርጓቸዋል፡፡›› በማለት መለሱልኝ፡፡ በየሄድኩበት የማይለቀኝን አይሁድ ተጠቅመው ምሳሌ ቢሰጡም ምላሻቸው ደስ ብሎኛል፡፡
አምቦ ላይ ከእርሳቸው በፊት የሚመርቅ እንደሌለና የኢሬቻው የዘንድሮ መራቂም እንደሆኑ ለመረዳት እያለሁ፡፡
በአበበች ሆቴል
አበበች መታፈሪያ ከአምቦ ባለሐብቶች አንዷና የአካባቢው የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ናቸው፡፡ በየረብሻና ግርግሩ (እንደፈለጋችሁ ልትጠሩት ትችላላችሁ - ካጠፋሁ ይቅርታ የፖለቲካ ዓላማ ግን የለኝ በቃላት አጠቃቀሜ) ሆቴላቸው ዱላ ይቀምሳል፡፡ ሥልጠናችን የነበረው በምቹው ሆቴል ነበር፡፡
‹‹የአካባቢው ማህበረሰብ በእንግዳ ተቀባይነቱና አክባሪነቱ የታወቀ ነው፡፡ ሰላማዊና የማይረሳ ጊዜ እንደምታሳልፉ ተስፋ አደርጋለሁ፡:›› በማለት አቀባበል ያደረጉልን አንድ ባለስልጣን ስንለይም ‹‹ደብረ ብርሃኖችማ አንድ ነን እኮ፡፡ ዱሮ እኮ አንድ ነበርን- ሸዋ! አሁንም ግን አንድ ነን፡፡›› ብለውናል፡፡ እኛም አጨብጭበንላቸዋል፡፡
አስተናጋጃችን አምቦ ዩኒቨርሲቲ አራት ካምፓሶች ሲኖሩት ግቢውን ስጎበኝ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ቤተመጻሕፍትንም አይቼ አድንቄያለሁ፡፡
ቡድናችን ጉደርን ለመጎብኘት የነበረው እቅድ ተሰረዘ፡፡ ዶክተር መረራ በመታሰራቸው የተነሳ ነው ይህ መሆኑ፡፡
ሃሳብ እንጂ ብር የለኝም የሚለው ዩኔስኮ ባዘጋጀው በሞባይል ስልክ፣ በታብሌትና በላፕቶፕ የተደገፈ ተግባር-ተኮር የጎልማሶች ስልጠና ላይ ለመገኘት ነበር ዘጠኝ ሰዎ ያለው ቡድናችን ወደ አምቦ ያቀናው፡፡ ‹‹በታብሌት እንዲማሩ የሚለው የሚያጋጭ ይመስለኛል - ንብረት ስለሆነ፡፡›› ያሉ ሰው ነበሩ፡፡ ፊደል ቆጥሮ የጨረሰ ሰው ታብሌት አያሻውም ያለው ማነው? አዲስ አበባ የሚገኘው ሊሴ ገብረማርያም ለአንድ ተማሪ በዓመት 110 000 ብር፣ አሜሪካን ስኩል 8 000 ዶላር በተርም በሚያስከፍሉበት አገር ለአንድ ጎልማሳ የ220 ዶላር ታብሌት ማይክሮሶፍት ልስጥ ሲል የአስተማሪ ምቀኛ ገባው፡፡ ይህ ምቀኝነት ግን አይሰራም ብዬ አስባለሁ፡፡
እጅግ የሳበኝ የሞባይል ትምህርት ተግባራዊ ሆኖ ለማየት እሻለሁ፡፡ እኛ የሚነበበውን ነገር ለማዘጋጀት ነበር እዚያ ሦስት ቀን የቆየነው፡፡
ከስብሰባው ላይ ከሳቡኝ ነገሮች አንዳንዶቹ፡-
‹‹አምፖል ብትቀባባው ከተቃጠለ እኮ አይሰራም፡፡ እንደሚባለው ችግሮቻንን ከምንጫቸው ማየት ይኖርብናል፡፡›› ልቀጥል -
ሁሌ ማነቃነቅ ምንድነው? ንቅናቄ? ወይ መትከል ነው ወይ መንቀል ነው፡፡
ምንሊክን ግማሹ በግራ ግማሹ በቀኝ ያስቀምጣቸዋል፤ እኔ ግን መሐል ላይ ነው የማደርጋቸው፡፡ የትምህርት አዋጃቸውን እዩልኝ- ልጁን ያላስተማረ ርስቱን ይቀማል፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school.

  Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school. The Shenes said they wanted to aven...