ረቡዕ 24 ሜይ 2017

የትምህርት ቤቶቹ የስፖርት ድግስ፤ የጉዞ ማስታወሻ፤ መዘምር ግርማ እንደጠረቀው



በየሁለት ዓመቱ የኩሳዬ ትምህርት ቤትና የዳዎ ትምህርት ቤት የስፖርት ፌስቲቫል ስለሚካሄድ በ10/9/2009 ወደስፍራው ያቀናነው ሦስት የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ልዑካን ቡድን አባላት አረፋፍደን ነበር የደረስነው፡፡ መቼም በቅጥቅጥ መኪና ስንጓዝ ይቺ ቅጥቅጥ ለምን ከአገራችን እንደማትጠፋ ጠየቅ አደርጋለሁ፡፡ ለሰው መሳፈሪያ የሚሆን መኪና ይመጥነናል፡፡ መኪና መግዣ ገንዘብ እንደሆነ መውጣቱ አልቀረ፡፡ ስለሆነም የሚመለከተው ይመልከተው በማለት ወደሌላ ጉዳይ አልፋለሁ፡፡ ለዚያውም አዳሩ ካፍ እስከገደፉ ጢም ብሎ ሞልቶ ነው የሚሄደው፡፡  ኮርቶመጋላ ላይ ሳይቀር ሰው እንደሚጫን አገሬው መኪና ውስጥ ሲያወራ ነበር፡፡ ይህን መቼም አታኑም አይደል!በእጃቸው ጥብቅ አድርገው ብረቷን ይዘው በአየር ላይ እየተንሳፉ ሲሄዱ መኪናዋ እንደፎቅ ሆነች ማለት ነው፡፡ የጭነት መኪና እንዳሆነ ግንዛቤ አድርጉ፡፡
እነዋሪ ልንደርስ ስንል ተማሪዎች ይዞ ይጓዝ የነበረ መኪና መንገዱን ስቶ ዘንበል ማለቱን ስናይ እንኳንም ተሳፋሪዎቹ አልተጎዱ አልን፡፡
የእነዋሪ ጥብስ፣ ያው የጅሩ ሰንጋ ባጠቃላይ፣ ልዩ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡ በልተናልና ግድ ስለሚለን! ሸክላ ጥብስ ስለማልወድ ይህንን ግማሽ ኪሎ ስጋ አስጠብስልን አልኩት፡፡ ሦስት ነን፡፡ ‹‹በቃ ውስጥ ስለሚጠበስላችሁ 15 ብር ያስጨምራል - የዘይቱ ምናምን - መቶ ብራችሁ ቻለ›› አለን፡፡ እስኪ ይሁን እያልን ገባንና መጣች ያች የፈረደባት ጥብስ፡፡ እንጀራው በመረቅ ሟሙቶ እንጀራ አነሰን፡፡ ግማሽ እንጀራ ጨመሩ - ሦስት ብር አስጨመሩን፡፡ አንድ እንጀራ ስድስት ብር ነው ማለት ነው ብዬ ለነዋሪ አዘንኩ፡፡ የጅሩ ሆቴል ቆይታችን ይህን ይመስላል፡፡ በየመንገዱ የማውቃቸውን ሰዎ ሰላም እያልኩ ወደ መናኸሪያ!
ከእነዋሪ ኩሳዬ ቅርብ መንገድ ስለሆነ ክፍያውም ስድስት ብር ብቻ ነው፡፡ ኩሳዬ ደርሰን የኩሳዬን እምብርት (የራስ አበበን ግቢ) ጎበኘን፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ሐውልት ሊገነባ እንደታቀደ ሰምቻለሁ፡፡ ይበል ብያለሁ፡፡ ኩሳዬ ላይ ቦታ ስንጠይቀው ‹‹ካስፋልቱ ሄድ ብሎ›› ያለን ልጅ አስቆኛል፡፡ አስፋልት ጅሩን አያውቃትም - እነዋሪ ከተማው ውስጥ ግን ለህዝቡ ጤና ተብሎ ተሰርቷል መሰለኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነት አሰራር ተጀምሯል በወረዳ ከተሞች፡፡ ቁልቋል በከበባቸው ቤቶች የሚኖሩት ኩሳዬዎች የውሃ ነገር አልሞላላቸውም፡፡ ውሃ ላይ ቆመው ውሃ ስለሚጠማቸው በአህያ መጫን ግድ ይላቸዋል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ መጀመሪያም የተጋነነ በጀት ክልሉ ያዘ፡፡ ያንንም ገንዘብ ያለአግባብ አባክነው ጥቅም ላይ ሳያውሉ ቀሩ፡፡ የተበላሸ ዕቃ ገጠሙለት፡፡ ችግሩን ለማስተካከል እየተሞከረ መሆኑን ያየሁት አምና ተሰቅሎ የነበረው የላሜራ ብይድ የውሃ ጋን ወርዶ ዘንድሮ የፕላስቲኩ ስለተሰቀለ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኑ ቅርብ እንደሆነ ያየነው ከጎበኘነው በኋላ ነው፡፡ በውሃው ልማትም ሆነ በቤተክርስቲያኑ ስራ ሁለት ሰዎች ተደጋግሞ ይመሰገናሉ - አንደኛው በትምህርት ሌላኛው በመከላከያ ዘርፍ ያሉ ናቸው፡፡ ማን ማን እንደሆኑ ገምቱ፡፡
ትምህርት ቤት ስንደርስ ፌስቲቫሉ ቀልጧል፡፡ ተማሪዎች ቡድናቸው ግብ ሲያስመዘግብ እየጨፈሩ ሜዳውን ይዞራሉ፡፡ ሳሲት ትምህርት ቤት ዓመታዊ የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር ሲካሄድ የነበረውን የልጅነት ትውስታ ቀሰቀሰብኝ፡፡ 1500 ሜትር የፈላ ትምህርት ቤት በተለይም የውቤ ነበር፡፡ ሳሲቶች ምን እንደምናሸንፍ ጠፋኝ፡፡ እምቧይባድ አጭር ርቀት ላይ ዳኜ የተባለ ተርብ ነበረው፡፡ የወረዳው ምርጦች  ሸዋሮቢት ሄደው በስፖርትም በጥያቄና መልስም ተወዳድረዋል፡፡ ተሳታፊ የነበራችሁ ትዝታችሁን ጻፉልን፡፡ ዳምጠው አድማሱን እንዲጽፍ ለማነሳሳት ነው፡፡ ተመለስን ወደ ጅሩ ፡-  አቶ አሳምነውን አግኝተነው በቤተመጻሕፍቱ አቀባበል አደረገልን፡፡ በጥሩ ሁኔታ የተያዘ ቤተመጻሕፍት ነው፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሰራዊት ከሚለው መጽሐፍ ስለ ራስ አበበ አረጋይ አበበልን፡፡ ከዚያም ወደ መምህራን ቤት ሄደን ተጋበዝን፡፡ ስለትምህርትና ስለተለያዩ ነገሮች ተነሣ፡፡ መምህራንና ሰራተኞች ያላቸው ቤተሰባዊ ፍቅር ያስደስታል!
አቶ አሳምነው ባለፈው ዓመት የለገስኳቸውን መጻሕፍት ከርዕሰመምህሩ ቢሮ ተቀብሎ አምጥቶ መዝግቦ አሳየኝ፡፡ እስከዛሬ ድረስ ለጥቅም ሳይውሉ መክረማቸው እሱንም አሳዝኖታል፡፡ የ580 ብር መጻሕፍት አግዘኸናል ያለኝ ግን አልተዋጠልኝም፡፡ እኔ ጊዜው ረዝሞ ካልረሳሁት በስተቀር የአንድ ሺህ ብር መጽሐፍ ነበር የሰጠኋቸው፡፡ ጠፍቶባቸው ይሆን እንዴ? አቶ አሳምነው መምህራንን ››እናንተ ሳይኮሎጂ አታነቡ፣ ምን አታነቡ፤ መመሪያውን አታውቁት፤ በቀደም ያ ልጅ መባረር የለበትም ብዬ መመሪያውን ያሳየኋችሁ እኔ ነኝ›› እያለ ይወቅሳቸዋል፡፡ ድፍረቱ ገረመኝ፡፡ እኛ መምህራን እናነባለን እንዴ? በፊት የሕብረተሰብ መምህር እንደነበረና አሁን በፍላጎቱ ወደ ቤተመጻሕፍት ሰራተኝነት እንደገባ ነገረኝ፡፡ ተግባቢና የዕውቀት ሰው ነው፡፡ መምህሩ በሳይክል ብር እያለ እነዋሪ ነው የሚውለው የሚል ነገርም አወጋኝ፡፡ ቤት ስራ ጀምረዋልና ከክፍለጊዜያቸው በኋላ ትምህርት ቤት ግቢ አይታዩም፡፡ ባለፈው ዓመት ለመደራጀት ገንዘብ ስላጡ ቦታውን ለገበሬ ሊሸጡት ነው ያለኝ ነገር ለማናቸውም ተስተካክሏል ማለት ነው፡፡ የአቶ አሳምነው ባለቤት የበቻሬ የልጅ ልጅ በመሆኗ ከራስ አበበ ትዛመዳለች - ራስ አበበ አረጋይ በቻሬ፡፡
ለውድድር ከመጣው ከዳው ትምህርት ቤት አንድ የደብረ ብርሃኑን የራስ አበበ ቤተመጻሕፍት የሚያውቅ መምህር አገኘን፡፡ መምህሩ በክረምት መርሃግብር ዩኒቨርሲቲ ስለሚማር ነሐሴ 12፣ 2008 ባደረግነው የአጤ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ልደት አከባበርና ውይይት ላይ እንደተገኘ ሲነግረኝ አስታወስኩት፡፡ ትምህርት ቤቶቹ በስልጠና ቢታገዙ ጥሩ ነው የሚል ሐሳብ መጥቶልኛል፡፡
እና ምን አለፋችሁ መቼ በትምህርት ቤትና በራስ አበበ ግቢ ጉብኝት ያበቃል የኛ ቆይታ! ይህ ተርብ የቤተመጻሕፍት ሰራተኛ አገር ላሳያችሁ ብሎ ይዞን መሄድ፡፡ የቲያትር ቤት የወንበር አቀማመጥ በመሰለ አደራደር የተደረደሩ ተራሮችን አይተን ሆዳችን ባባ፤ ደስ አለን፤ ብረሩ ብረሩ አለን፤ የሳሲትን መንገድም አቅጣጫውን አየሁት፡፡ በነገራችን ላይ የሞጃና ወደራንና የሞረትና ጅሩን ወረዳዎች የሚያገናኝ የጠጠር መንገድ እየተሰራ ነው፡፡ ጅሩ ቅርባችን ሳይሆን አይቀርም ለሞጃዎች፡፡ ሳሲት ብዙ ወሬዎች አሉ ስለጅሩ፡፡ ስርጦቹን ራስ አበበና ወታደሮቻቸው እየወጡ እየወረዱ ከጣሊያን ጋር እንደሚዋጉባቸው አሳምን ሲነግረኝ እኔ ራሴ ይህን አስቸጋሪ መንገድ መሄድ እንደሚከብደኝ እያሰብኩ አድናቆቴን ለሸዋ አርበኞች! ‹‹እዚች ጋ አንድ ጀግና ተመቶ አርፏል፡፡ መጀመሪያ መሳሪያ አልነበራቸውም - በኋላ ግን ማርከው የኃይል ሚዛኑ ተስተካከለ›› እያለ ታሪክን የኋሊት አስቃኘን፡፡ የውሃ ጋኑ ታች ቆላው ላይ ነው፡፡ ውሃው ሞልቶ ይፈሳል፤ በባህላዊ መስኖ የለማውን አገር አየነው፡፡ ባለመስኖዎቹና የኩሳዬ ነዋሪዎ በውሃ ያለባቸውን ግጭት ፍቱላቸው - አስታርቋቸው - እትዬ ዘወድነሽ መሯታል የውሃው መቆራረጥ ነገር፡፡ ሚኪና ሩት አገሩን ማስጎብኘት እንደሚቻል ሃሳብ እያቀረቡ እኛ አገራችንን የማየት ልማድ ለምን እንደሌለን ሲጠይቁኝ ነበር፡፡ እነዚህን በሃያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች በማስጎብኘቴ ደስ ብሎኛል፡፡ ሚኪ ጸጉሩን እንደራስ አበበ አጎፍሮ ነበር፡፡ ሁለት ገጽ የጉዞ ማስታወሻ በወረቀት ጽፎ ኮምፒውተር ቤት ሰጥቷል፡፡ ከዚያ በፍላሽ ወስዶ ለእናንተ ለማጋራት፡፡ ደረሰልህ ወይ በሉት ደውላችሁ - 0912906228 - አንቺ ማነሽ- አደራ መጥበስ አይቻልም፡፡
ማታ ተመልሰን በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ያው ሐሙስ ስለነበር የውይይትና የስነጽሑፍ ምሽቱ ላይ የጉዟችንን ሪፖርት አቀረብን፡፡ እኔ ስለ ሕዝቡ፣ ሚኪ ስለ አካባቢው እና ሩት ስለ ታሪኩ፡፡ ያልሄዱ ቢቆጫቸውም አሳምን የላከላቸውን የጅሩ ዳቦ እንዳምናው እየበሉ ታድመዋል፡፡ የሚጋገረው ዳቦ ብዛት ለቁጥር አዳጋች ነው፡፡ የስፖርት ወይስ የዳቦ ፌስቲቫል! ለጥቅምት አቦ ሁላችሁም ተጠርታችኋል፡፡ ያኔ አገሩ ይለመልማል - ይምራል አሉ፡፡
ረስቼው 1. በፈረስ ሲታረስ ለመጀመሪያ ጊዜ አየሁ፡፡
ረስቼው 2. መኪና ውስጥ ስንሄድ ያገኘኋቸው እናት ንቃተህሊና ይገርማል፡፡ ሸዋዎች ቀላሎች አይደሉም ያስብላችኋል!
ረስቼው 3. መንገዱን አስፋልት እንዲያደርጉት መቀስቀስ ያሻል፡፡
ረስቼው 4. የኩሳዬን ትምህርት ቤት ያሰራው ሜንሽን ነው፡፡
ረስቼው 5. ኩሳዬ ብዬ በይነመረብ ላይ በአማርኛ ብፈልግ ብዙ ነገር አገኘሁ፡፡ በነገራችን ላይ በአማርኛ ጉግል ላይ ብትፈልጉ ብዙ ነገር አለ፡፡
በመጨረሻም ሌላ ብዙ አውቄ የረሳኋቸው ነገሮች ስላሉ ሄዳችሁ እንድታዩ ይሁን!


1 አስተያየት:

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...