ሰኞ 7 ኦገስት 2017

መጽሐፍ ስናነብ መምረጥ አለብን?






የመጸሐፍ ነገር ከተነሳ በዓለማችን እስካሁን ስንት መጻሕፍት ለህትመት በቅተዋል የሚለውን ጉዳይ እንይ፡፡ ጉግል ወደ መቶ ሠላሳ ሚሊዮን የሚጠጉ መጻሕፍት ለሕትመት እንደበቁ ያስረዳናል፡፡ ይህ የሆነው አንድ ደራሲ በአንድ ወቅት ያወጣውን መጽሐፍ አንድ ብለን ቆጥረን እንጂ ያሳተማቸውን የመጽሐፍ ቅጂዎች ብዛት ቆጥረን አይደለም፡፡ ብዛቱ ያስደምማል - በዓመት ዐሥር ሺህ ገዳማ መጻሕፍት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ ይታተማሉ፡፡ ቁጥሩ ብዙ የተጋነነ እንዳይመስላችሁ - ግዕዝም በሕይወት ዘመኑ በዐሥር ሺዎች መጻሕፍት ታትመውበታል፡፡



‹‹ኩሎ አመክሩ ወዘሠናየ አፅንዑ›› ባይ ተከራካሪዎች በዕለተ እሁድ 16/11/2009 በደብረ ብረሃን ከተማ በተምሳሌት ኪነጥበባት የኪነማዕድ ዝግጅት ላይ ‹‹መጽሐፍ አንዴት ተደርጎ ይመረጣል?›› ሲሉ ሞግተዋል፡፡ ‹‹አንብበን አተረጓጎማችንን ማስተካከል እንጂ እንዴት ይህን አላነብም ይህን አነባለሁ ብለን ማዕቀብ እንጥላለን?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹መጥፎውን ካላነበብህ ጥሩውን ልታውቅ አትችልም፡፡ የተነሱት ሐሳቦች የማይመቹን ከሆነ መተው አንችልም ወይ?›› ብለው ሞግተዋል፡፡ ወንፊት እንደሚያጠለው ሁሉ ከተነበበ በኋላ የመምረጥ ችሎታ ጠቃሚነቱ ታይቷቸዋል፡፡ ባጠቃላይ ለነሱ መጽሐፉ ሳይሆን አወሳሰዳችንና አተገባበራችን ከግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ከመራጮች ወገን በተደጋጋሚ የተነሣው ደራሲ ማን ይመስላችኋል? ‹‹የሱን መጻሕፍት ካነበባችሁ ጉዳችሁ ፈላ! እንደሱ ዓይነቶቹን ችላ በሏቸው! ያለዚያ ወዮላችሁ፤ ሰማይ ይደፋባችኋል!›› ትባላላችሁ፡፡ ኦሾ ጉድህ! ሰውን ለማስፈራራትና ከዚህ መጽሐፍ ታቀቡ ለማለት አይደለም የኛ ክርክር መሆን ያለበት፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው!



የንባባችን ዓላማ ምንድነው? ለመዝናናት፣ ለምርምር፣ ክህሎትን ለማዳበር፣ መረጃ ለማግኘት፣ አመለካከትን ለማነጽ፣ ለማጥናት? በዚህ ምክንያት ምርጫ ማድረግ ግድ ይለናል፡፡



በኛ አገር የህብረተሰቡ አንባቢ ያለመሆንና የብዙ መጻሕፍት ያለመዳረስ ችግር አለ፡፡ ስለዚህ የህብረተሰቡ አካላት ምናልባት ወደ ንባብ ከመጡና መጻሕፍትን ማግኘት ከቻሉ የየምርጫቸውን መጻሕፍት ማንበብ አለባቸው፡፡ በባለፈው የንባብ ፌስቲቫላችን በተሰጠ የዓይን እማኝነት ከጀርመኖች፣ ከጣሊያኖችና ከሌሎችም ህዝቦች ጋር ሲነጻጸሩ አንባቢዎች በተባሉት አሜሪካውያን ዘንድ እንኳን ሁለት ሦስተኛው ህዝብ በዓመት አንድ መጽሐፍም አያነብም ተብሏል፡፡ በጣም አንበቢው ሰው አነበበ ቢባል እንኳን አምስት ሺሀ ገደማ መጸሕፍትን በሕይወት ዘመኑ ሊያነብ ይችላል ብለው አስተያየት የሰጡ ጸሐፊ አሉ፡፡ ዳቢት፣ ንቃይ፣ ታናሽ፣ ታላቅ፣ ወርች፣ ሽንጥ፣ ሳልገኝ፣ ጎድን (ሳብራዳ)፣ ፍርምባ፣ ጭቅና፣ ኪርኪሳ፣ ፍሌቶ፣ ደንደስ፣ ሻኛ፣ ሹልዳ፣ ነብሮ እያለ የሥጋ ዓይነቶችን ሲቆጥርና ሲበላ ወይም ሲመኝ ለሚውል ሰው እንደ አብዛኛው አሜሪካዊ ንባብ የሕይወቱ አካል ስላልሆነ የምንነጋገረው ከተወሰነው የህብረተሰብ አንባቢ ልምድና ተግባር በመነሳት ይሆናል፡፡ የንባብ ልማድ ከልጅነታችን ስላልዳበረ ነው ንባባችን ችግር የገጠመው፡፡ ምናልባት ኦባሳንጆ እንደሚሉት መልሰን መማር ባይኖርብንም ቀለል ባሉ ንባቦች ራሳችንን ብናላምድ መልካም ነው፡፡ ባህላችን ጭራሹኑስ ማንበብን ያበረታታል ወይ? ብላችሁ ብትጠይቁ ማንበብና መጠየቅ የሚበረታታ አይመስለኝም፡፡ የሃይማኖት መጻሕፍትን እንኳን የሚያነበው አማኝ ስንት ነው? ከሚነበቡት ነገሮች ተደራሽነት ባሻገር የመጻሕፍት እገዳ፣ የአንባቢያን የቋንቋ ችግር ወዘተ. የየራሳቸው ተጽዕኖ እንዳላቸው በማስረገጥ ወደ ቀጣዩ ምክንያት እንሂድ፡፡



አንባቢያን የንባብ የምቾት ቀጠና አላቸው፡፡ ዘውግ ይመርጣሉ፡፡ ልቦለድ፣ ስነልቦና፣ የሕይወት ታሪክ፣ ግጥም፣ ፍልስፍና፣ ሙያዊ ነገር፣ ወዘተ. - ከአንዱ ይሆናል ፍላጎታቸው፡፡ በተያያዘ ወሬ ማሰባጠር ጥሩ እንደሆነ ለአንባቢያን ማስገንዘብ ይኖርብናል፡፡



በውይይታችን ላይ ጨርሶ አላነብም ላሉ ግን መልዕክት አለኝ፡፡ ታሪክን የማያነብ ታሪክን የመድገም ዕድል አለው፡፡ ከትናንት ካልተማርን ዛሬንና ነገን በትክክል ለመኖር እንቸገራለን፡፡ ‹‹እንዴት እናንብብ›› የሚል መጽሐፍም ስለወጣ ብታነቡት አይከፋም፡፡ ‹‹ምን ዓይነት ቃላት ቢይዝ ነው የሚያሳብደው›› ያልሽው ልጅ ንባብ ብዙ ጉልበት ስላለው አንብበሽ ድረሺበት፡፡ መቀመጥ መቻልም ማንበብን ለማዳበር ወሳኝ ነገር ነው፡፡ መጽሃፍ ሲወፍር ደግሞ ደስ ይበላችሁ እንጂ ለመቼ አልቆልኝ አትበሉ፡፡ ደራሲው ጉዳዩን በጥልቀት ዳሶታል ማለት ነው፡፡



አንብበን እንደ ወንፊት እናጣራ በሚለው ብዙም አልስማማም፡፡ የምናነበው ነገር ስብዕናችንን ስለሚቀርጽ የተገኘውን ማንበብ የለብንም፡፡ በተዘዋዋሪ ሳናውቀውም ቢሆን በጥሩም ሆነ በመጥፎ ተጽዕኖ ስለሚያሳድርብን መምረጥ ይኖርብናል፡፡



የምንመርጠው በባህልና በቤተሰብ በተቀረጽንበት ስብዕና መሰረት ሊሆን ይችላል፡፡ መሆን ያለበት የሚመስለኝ ግን እንዲህ ነው፡፡ ራሳችን የራሳችንን የነገ ህይወት መቅረጽ ግድ ይለናል፡፡ እንስሶች ናቸው ከአካባቢየቸው ጋር ተስማምተው የሚኖሩት፡፡ ሰዎች ግን አካባቢያችንን መቅረጽና መለወጥ አለብን፡፡ የህይወታችንንም መንገድ ራሳችን መጥረግ አለብን፡፡ ከዚያ የሕይወት መርሆ ጋር የሚሄድ ንባብ ማንበብ ይኖርብናል፡፡ ለመምረጥ የሚያስገድደን እርሱ ነው፡፡



ካላነበብን ጥሩውን እንዴት እናውቀዋለን ለሚለው ሀሳብ የተወሰኑ ምክሮች አሉኝ፡፡ የምናምናቸውን ሰዎች ምክር መስማት፣ ዳሰሳዎችን ማንበብ፣ ደራሲውንና ይዘቱን ማገናዘብ ወዘተ ጠቃሚ መንገዶች ናቸው፡፡



ስለንባብ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችም አሉ፡፡ ጫት እየቃሙ ማንበብ ጥሩ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ስህተት ነው፡፡ የተወሰኑ አንባቢዎች የተሳሳተ ነገር ያደርጋሉና እኛም እነዚያን ነገሮች ማድረግ አለብን ማለት አይደለም፡፡ አንብቦ ጨርቅን መጣልም ጥሩ አይደለም፡፡

ለመሰናበት ያህል ማንበብ የመርሳት በሽታን ይከላከላል፤ ለመረጃ ቅርብ ያደርጋል፤ ሙሉ ሰው ያደርጋል፡፡




ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...