(ማህበራዊ ሚዲያችን ለምን የምንፈልገውን ሰው ብቻ ማሰባሰቢያ ሆነ?) እና ሌሎችም
የጽሑፉ ርዝመት 1496 ቃላት፤ የሚፈጀው ጊዜ በአማካይ 10 ደቂቃ
ስትራይቭ ማሲይዋ ይባላል፡፡ ዝምባብዌያዊ ቢሊየነር፣ ሥራ ፈጣሪና በጎ አድራጊ ነው፡፡ ዕድሜው 57 ዓመት፡፡ በቅርቡ ወደ ዳሬ ሠላም ብቅ ብሎ ከወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ጋር የንግግርና የምክር ቆይታ አድርጓል፡፡ እኔም እንግሊዝኛ ለምትረዱ ቪዲዮውን አጋራችኋለሁ፡፡ በትናንትናው ማለትም ሐምሌ 7፣ 2009 ምሽት ከሌሊቱ 8፡20 ድረስ ያስቆየኝ ስራ የዚህን ሰው የመድረክ ቆይታ ማድመጥና ማስታወሻ መውሰድ ነበር - ሰባት ገጽ ማስታወሻ በደብተሬ ወስጃለሁ፡፡ ለኔ በጣም ያስደሰተኝና ፍላጎቴ የተነቃቃበት ይህ ትምህርት እናንተን እንዴት እንደሚያደርጋችሁ አላውቅም፡፡ በስራ ፈጠራ፣ በቢዝነስ፣ በበጎ አድራጎት ምን ደረጃ ላይ እንዳላችሁ የምታውቁት እናንተ ስለሆናችሁ፤ በትምህርቱ ላይ የሚኖራችሁን ፍላጎት እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም፡፡
ጥቁር ሀብታም ሁሉ ናይጀሪያዊ ነው ብዬ ላመንኩት ለኔ ስትራይቭ ናይጀሪያዊ ነበር፡፡ ዛሬ ይህን ጽሑፍ ለማዳበር ስል የቃኘሁት አንድ ድረ-ገጽ ግን ግምቴ መሳሳቱን አስረዳኝ፡፡ ይሁን እንግዲህ፣ ማነው ናይጀሪያ ብቻ ትበልጽግ ያለው? አላሙዲን፣ ዳንጎቴ፣ ኖህ ሰማራ፣ ጃክ ማ፣ ቢል ጌትስ፣ ዋረን ባፌት፣ ኦፕራ፣ ትራምፕ እያልኩ ቢሊየነሮችን እግር በእግር እየተከታተልኩ ያለሁት ለምን ይመስላችኋል? መልሱን ከንባቡ በኋላ ልትገምቱት ትችላላችሁ፡፡
በዝምባብዌ፣ በዛምቢያና ስኮትላንድ የተማረው ይህ ሰው እናቱን የስኬቱ አርአያ ያደርጋቸዋል፡፡ ‹‹በሌሊት እየተነሳች የምትሰራበት ትጋቷ አርአያ ሆኖኛል›› ይላችኋል፡፡ የእርስዎስ እናት እንዴት ነበረች? እኔ ምናልባት አያቴ ልትሆን ትችላለች ትጉህ፡፡ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት በፊት እነሱ ቤት አይተኛም፡፡ ‹‹የርቀት ብትማሪ እኮ ዶክትሬት ትይዢ ነበር›› እላታለሁ ለአያቴ፡፡
በዝምባብዌ ይሰራበት የነበረው የቴሌኮም ድርጅት ስራ ወጣቱን የ26 ዓመት መሐንዲስ ሊያረካው አልቻለም፡፡ አንድ ሰው በአማካይ ስልክ ሊገባለት የሚችለው ካመለከተ ከ14 ዓመታት በኋላ መሆኑ ስላበሳጨው ስራ ለቀቀ፡፡ ለዚህም የስልክ ችግር መፍትሔ ይፈልግለት ገባ፡፡ ያም እንዴት እንጀራ እንደፈጠረለት ታያላችሁ፡፡
እኔኑ ራሴን ‹‹አሁን ባለሁበት ሁኔታ በትምህርት፣ በጊዜ አጠቃቀም፣ በሕይወት ዓላማ ልረካ ያልቻልኩት ለምንድነው?›› አስባለኝ፡፡ ‹‹አለመርካት የለውጥ መነሻ ነው›› ይላችኋል፡፡
ከመድረክ ላይ ለምትጠይቀው የታንዛኒያ ተወላጅ ምላሽ በመስጠት መድረኩን የተቆጣጠረው ማሲይዋ ትዊተር የለውም፡፡ ፌስቡኩ ግን በዛሬዋ ዕለት 2 473 163 አባላት አሉት፡፡ ‹‹ትዊተር ከፍቼ እንድትከተሉኝ ሳይሆን የጋራ መድረክ እንዲኖረንና እንድንነጋገር እንዲሁም እንድንሰራ ነው የምፈልገው›› ይላል፡፡ ፌስቡክ በማሳተፍ መጠኑ ከፍተኛ ያለው ይህ ገጹ በርካታ የስራ ፈጠራ ምክሮችና ውይይቶች የሚስተናገዱበት ነው፡፡ እሱ የሚለጥፋቸው ብቻ ሳይሆኑ እሱ በለጠፋቸው ምክሮችና ጽሑፎች ላይ የሚንሸራሸሩት መልሶች፣ ውይይቶችና ክርክሮች በአባላቱ ተሳትፎ ከማናቸውም የፌስቡክ ተጠቃሚ በላይ ያደርገዋል፡፡ ፌስቡክንና ስራውን እንዴት እንዳመጣጠነ ሲናገር ከአንድ ዩጋንዳዊ የዕድሜ ባለጸጋ ያገኘውን ምክር እንደ ሕይወት መርህ መጠቀሙን ያነሣል፡፡ ይህም ‹‹ለአስፈላጊዎች ነገሮች ጊዜ ፈልጉ፤ በጣም አንገብጋቢ ለሆኑ ጉዳዮች ግን ጊዜ ውለዱ›› ይላል፡፡ ለእናንተ ስል ጊዜ እወልዳለሁ፤ ጊዜ አድኜ አመጣለሁ›› ይላቸዋል፡፡
ወገኖቼ፣ ለኔና ለእናንተ አስፈላጊውና ጊዜ ልንወልድለት የሚገባው ገር ምንድነው? ለእርሱ እኛን ማስተማርና ማሰልጠን ግድ የሚለው ነገር ሆነ - የደረሰበት የአስተሳሰብ ደረጃ! ድፍን አፍሪካን ያስተምራል፡፡
‹‹እናንተ ባለሐብት ለመሆን ሳይሆን የአፍሪካን ችግሮች ለመቅረፍ ተነሱ እንጂ ገንዘቡ ከዚያ ለራሱ ይጨነቃል›› ይላችኋል፡፡ ‹‹በርካታ ፍላጎቶችና ችግሮች ያሉባት አፍሪካ ትፈልጋችኋለች፡፡››
የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ድርጅት የኢኮኔት ዋየርለስ መስራችና ስራ አስፈጻሚ የሆነው ይህ ሰው አፍሪካ ወደ ኋላ የቀረችባቸው ነገሮች ያሳስቡታል፡፡ ይህ የታላላቆቹ ስራ ፈጣሪዎች የታናናሾቹን ማሰልጠንና መደገፍ ጉዳይ በአሜሪካ እጅግ የታወቀና የተሰራበት ቢሆንም እኛ ጋ ገና ነው፡፡ ‹‹እስከዛሬ እንዲህ ስላልተደጋገፍን ቀኑ ዛሬ ነው›› ይላል፡፡ መቼ ማለት ብቻ! - በተግባርም ዘምቷል፡፡
‹‹መጽሐፍ ከምጽፍ ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያ ብጠቀም እናንተን የተሻለ እንደማነቃቃ ስላወቅሁ ነው እዚያ የምንገናኘው›› ለሚላቸው ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን የሚመልሰውና ጽሑፎቹን የሚጽፈው ራሱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹ብፈልግ ግማሽ ደርዘን ወጣት መቅጠር እችል ነበር›› ሲል ሌላውን የማያሰራ አቅጣጫ ያሳየናል፡፡
‹‹እናንት የአፍሪካ አሊባባ፣ ጉግል … መስራች የምትሆኑ ወጣቶች ትልቅ ድርጅት ስትመሰርቱ ግን ስሙን አፍሪካዊ አድርጉት - ልክ አንኔው ክዌሲ ቴሌቪዥን፡፡ የአስተሳሰብ አድማሳችሁን አስተካክሉ፡፡ የተለያዩ ዳራዎች ያሏቸው 54 አገሮቻችን የናንተን የተለየ የአስተሳሰብ አድማስና አተያይ ይሻሉ፡፡››
ወጣቶች ወደፊት በምን ዘርፍ ይሰማሩ ትላለህ?
‹‹እኔ በዚህ ስሩ በዚህ አትስሩ አልልም፡፡ የማህበረሰባችን ችግሮች ምንድናቸው የሚለውን አጥንታችሁ ተንቀሳቀሱ ነው የምላችሁ፡፡ የለውጥ ዕድሎች ያሉት ችግሮቹ ላይ ነው፡፡ ዕውቀቴና ክህሎቴ የትኛውን ችግር ለመፍታት ይጠቅማል የሚለውን ግን አትርሱ፡፡ ከዚህ በስተቀረ ሁሉም ዘርፍ የየራሱ ጥንካሬ አለው፡፡ በየትኛውም ዘርፍ ትልቅ ገንዘብ አለ - ግብርና፣ አይቲ፣ ሱፐርማርኬት …. ››
አሞራ በማዕበል የሚለው ለረጅም ጊዜ በፌስቡክህ ላይ በተከታታይ በተስተናገደው ጽሑፍ ላይ እስኪ ትንሽ ነገር በል፡፡
‹‹አሞራ እኮ ማዕበል ፈርታ ዛፍ ላይ አትወሸቅም፡፡ በማዕበሉ አልፋ ታድናለች፡፡ ከማዕበሉ ምን ተማርኩ ብለሽ ማሰብ አለብሽ፡፡ አፍሪካም ወደ ማዕበሉ እየመጣች ነው፡፡ አስደማሚ ለውጦች፣ ማዕበሎች፣ እርማቶች ይጠብቁናል፡፡ በዚያ ሁኔታ ውስጥ እንታገላለን እንጂ ሁኔታውን ራሱን አንታገለውም፡፡ ታላላቆቹ የምዕራቡ ዓለም ድርጅቶች የተመሰረቱት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት መሆኑን ልብ በይ፡፡ ታላቅ ማዕበል!››
አሁን ስትራይቭ ማሲዋ ወደኔ የአስተሳሰብ ደረጃ መጣልኝ - መዘምር ነኝ -
ባለፈው ስለ ስራ ፈጠራ ንግግር ሳደርግ ስራ ፈጣሪ ለመሆን ‹አይሰሩ - ሰሪ› መሆን አለባችሁ›› ብዬ ነበር፡፡ ይቺን አሁን ደገመልኛ! ‹‹ስትጀምሩት እኮ ምን ነካው ይህ ሰው ነው የሚያስብላችሁ›› አለ፡፡ ተቺዎች መቼም አሉ፡፡ በለንደን ፓርላመንት አደባባይ ያሉት ሐውልቶች ሲሰሩ የተቹ ነበሩ፡፡ አሁን ሐውልቶቹ አሉ፤ ተቺዎቹ ግን የሉም፡፡ ጭብጨባ!!!
‹‹ግትር ሳልሆን ችግርን ተቋቋሚ ነኝ፡፡ ማንም ሳይሰራው ለኔ የሚታየኝ የስራ ዕድል አለ፡፡ ስራ ፈጣሪነት ደግሞ በዘር ማንዘር አይመጣም፤ በስልጠና ነው - አንቺው ራስሽ ራስሽን አሰለጥኚው - እልሻለሁ፡፡ ፌስቡክ፣ ዋትዛፕ፣ የምንጠቀምበት ካፌ ሁሉ ስራ ፈጠራና ቢዝነስ መሆኑን ልብ በሉልኝ፡፡
‹‹ታዲያ ደግሞ ስራ ፈጠራ፣ ብር ማባዛት ብቻ አይደለም - ሰብዓዊ ነገርም አይጥፋ -
በስራ ፈጠራችን የህዝቡን ችግር መፍታት አንድ ነገር ሆኖ ማህበረሰባዊ ለውጥ አራማጆች የሚባሉም ሌሎች አሉ፡፡ ችግሮቻቸውን በለጋሾች ሳይሆን እዚሁ እኛው በኛው በቋሚነት እንድንፈታ የሚያስችሉ ጠንካራ ሰዎች፡፡
ስትራይቭ ማሲይዋ፣ ዝምባብዌያዊው ቢሊየነር፣ ትንነት እንደተነጋገርነው መድረክ ላይ ቃለ ምልልስ እያደረገ ነበር፡፡ ጠያቂዋ የጠየቀችው ቀጣይ ጥያቄ፡-
ወጣቶች ሀብት እንጂ እዳ እንዳይሆኑ ባለድርሻ አካላት ምን ማድረገ ይጠበቅባቸዋል?
የዚች አህጉር ትልቁ ሀብት የህዝቧ አእምሮ እንጂ ሌላ ስላልሆነ እሱን የምንጠቀምበትን መንገድ መዘርጋት ግድ ይለናል፡፡ በአፍሪካ ደግሞ ከህዝቡ ስድሳ በመቶ ወጣት ስለሆነ ያንን ዕድል ተጠቅመን መለወጥ ይኖርብናል፡፡
በአሁኑ ሰዓት እኮ በሳምንት 500 አፍሪካውያን አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ ሜዲትራኒያን ባሕር ገብተው ይቀራሉ፡፡ ስራ ፍለጋ አውሮፓ የሚሄዱትን እነዚህን ወገኖቻችንን ወደ ታንዛኒያ ነው ማምጣት ያለብን፡፡ ስራ አንፍጠርና ከሰሐራ አናስቀራቸው፡፡ ይህ አጣዳፊ ችግር እያለብን መተኛት አይታሰብም፡፡ ለዚያ ነው እኔ እዚሀ የመጣሁት፡፡ ይህን ስናደርግ እንደ አባቶቻችን እንደነ ጁሊየስ ኒሬሬ ታላቅ ታሪክ መስራት እንችላለን፡፡
ሌላ ነገር ደግሞ በዚህ ዘመን አያንዳንዱ ከናንተ የሚወጣ ነገር ይመዘገባል፡፡ አስኪ ፌስቡኩንና ጉግሉን እዩት - ወረቀት የያዘውን አይለቅም እንደሚባው፡፡ የምትናገሩትን ነገር መጠንቀቂያው አሁን ነው፡፡ ቀጣሪዎች እኮ ሲቀጥሯችሁ የማህበራዊ ሚዲያችሁን ንገሩን ይላሉ፡፡ ያኔ አሁን የማይሆን ነገር ከተናገራችሁ ችግር ይመጣል፡፡ የናንተ የዛሬ ቃል እንደ ንግድ ስማችሁ ነች ማለት ይቻላል፡፡
እኔ ጸሎተኛና መንፈሳዊ ሰው ነኝ፡፡ እስኪ እርስ በእርሳችን ትዕግስትና አክብሮት ይኑረን፡፡ በእጅጉ የተሳሰርን ነን፡፡ አንድ ሳልናገር የማላልፈው ነገር ግን አለ፡፡ ማህበራዊ ሚዲያችን ለምን የምንፈልገውን ሰው ብቻ ማሰባሰቢያ ሆነ?
መሰሎቻችንን ስናሰባስብ ነው የምንውለው፡፡ እስኪ የሚቻቻል አህጉር ይኑረን፡፡ ለጎረቤታችን ስፍራ ይኑረን፡፡
የተሳታፊዎች ጥያቄዎችና የስትራይቭ መልሶች (ተመልሰውም አልተመለሱም ይሆናል)
የፈጠርከውን ስራ ለማቆም ስታስብና ካጠገብህ የፈጠርከውን ስራ የሚብቁ ሲኖሩ ምን ታደርጋለህ?
የፈጠርከውን ስራ ትተህ ተጨማሪ ገቢ ፍለጋ ወደ ሌላ ለመቀየር ስታስብ አንዴት ነው በነባሩ ላይ የምታተኩረው?
ማህበራዊ ሚዲያንና ስራን እንዴተ ታመጣጥናለህ?
80 በመቶ ድርጅት እንደተጀመረ ይጠፋል፤ ይህን መጥፋት እንዴት እንከላከል?
ጓደኞቻችሁና ወዳጆቻችሁ የፈጠራችሁትን የሚያበረታቱ ይሁኑ፡፡ የስራ ፈጣሪዎች መረብ ይኑረን፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢንተርኔት አለልን፡፡ እርስ በእርሰ ተደጋገፉ፡፡ ጎረቤታችሁ የሚሰራውን ማወቅ ጥሩ ነው፡፡ ምናልባት ዳንጎቴ የሚሰራን ከማወቅ በበለጠ አጠገባችሁ ያለው ሊጠቅማችሁ ይችላል፡፡
80 በመቶ የተፈጠሩ ስራዎች በተፈጠሩ ሰሞን ይጠፋሉ፤ ቢሆንም እናንተ መስጋት የለባችሁም፡፡
ያለብን ችግር ስራፈጠራ ሳይሆን ያለንን ድርጅት ምን ያህል እናሳድገው የሚለው ነው፡፡
ሕይወትንና ስራን እንዴት ታመጣጥነዋለህ ለሚለው እጅግ ጊዜ የሚየስፈልገውን ነገር እለያለሁ፡፡ ጊዜዬን እቆጣጠራለሁ፡፡ ሌላው የቀጠራችሁት ሰው የሚሰራውን ለዩለት፡፡ ስራዎቹን ቅድሚያ የሚገባውንና የማይገባውን ለዩ፡፡
ከሌላ ድርጅት ጋር ጥምረት ማድረግ የማይኖርብንና የሚኖርብን መሆኑን እንዴት እናውቃለን?
የአህጉሩን ትልልቁን ድርጅት የምትመሰርቱ ስለሆናችሁ ብቻችሁን አትሰሩትም፡፡ 90 በመቶ ውድቀትም ሆነ እድገትን ያመጣልና ግን በጥንቃቄ ይሁን፡፡ ከመግባታችሁ በፊት አጥኑ፡፡ ምን ዓይነት ክህሎት እንደሚያስፈልጋችሁ እወቁት፡፡
ሰራተኞቻችሁ ስራቸውን አነዲሰሩ ፍጹም ነጻነት ስጧቸው፡፡ የራሳችሁን ስርዓት ለድርጅቱ ንደፉ፤ በዚያም መሰረት ስሩ፡፡ የማያስፈልግበት ቦታ እየገባችሁ አታስቸግሩ፡፡ ባለሙያዎችን ከቀጠራችሁ በኋላ እምነት አትንፈጓቸው፡፡
ዝግጅቱ በኢንተርኔት በቀጥታ ይተላለፍ ስለነበር ከዚያም የመጡ ጥያቄዎች ነበሩ፡-
ከቻይኖች ጋር ስላለው ፉክክር ምን ትላለህ
እናሸንፋቸዋለን፡፡ እንድናሸንፋቸው ግን እንረዳቸው፡፡ እኔ ለአንድ ወር ቻይና ሄጄ ሳጠናቸው ነበር፡፡ የቻይናም የአሜሪካም አጋሮች አሉኝ፡፡ የእነዚህ ጥንካሬ ምንድነው ብሎ ማጥናት ያስፈልገናል፡፡ ዘ ፕሮፊት የተባለውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ገዝቼ በክዌሲ ቴሌቪዥን እያሰራጨሁ ነው፡፡ ስለስራፈጠራ የተሻለ ስለሚያስረዳንና እነሱን እንድናውቅ ስለሚያግዘን ነው፡፡ ሰዎች፣ ምርቶችና ሂደቶች የሚለውን ዝግጅት ብታዩት እንዴት ደስ ይለኛል መሰላችሁ፡፡ ሂደት የሚባለው አወቃቀራችንና የዘረጋነው ስርዓት ሲሆን የኛ ድርጅት ለምሳሌ በጥሩ ሁኔታ ስለተዋቀረ አንድ ሰራተኛ ሊሰርቅ ሲያስብ እንደርስበታለን፡፡
ቢዝነስና ህይወት እንዴት ይጣጣምልሃል?
የአጎቴ ልጅ ገንዘብ አበድረኝ ብሎ መጣብኝ ባለፈው፡፡ በየሚዲያው ሃብታም ነው ሲባል ሰምቶ ይሄ ሁሉ ድርጀት ስላለህ እባክህ ተቸገርልኝ አለኝ፡፡ እኔ ደግሞ ያ ገንዘብ የድርጅቱ እንጂ መች የኔ ነው አልኩት፡፡ ድርጅቱም እናንተም ህይወት ይኑራችሁ፡፡ በነገራችን ላይ የምኖረው እንግሊዝ ነው፡፡ ልጆቼም የክፍል ጓደኞቻቸው ሃብታም ነው ሲሉ ስለሚሰሙ ይጠይቁኛል፡፡ እኔ ግን እንደ አባት እንጂ እንደ ስራ አስኪያጅ ልጆቼንም ሆነ ባለቤቴን መቅረብ ስለማልፈልግ ድንበር አበጅለታለሁ፡፡
ቅን ነህ፤ ለሌላው ታስባለህ፡፡ በዚህ አህጉር ያለውን ማሳደድ እንዴ አለፍከው?
የአፍሪካ ምርት የአህጉሩን ፍጆታ ሸፈኖ ጥራት የሌለውን የውጪ ምርት መተካት የሚችለው እንዴት ነው?
ወጣቱ ሊሰማራበት በሚፈልገው የስራ ዘርፍ ዕውቀቱና ክህሎቱ ላይኖረው ይችላልና ምን ትመክረናለህ?
አፍሪካ የደኸየችው በእምነተ ሰበብ ነው ይባላል፡፡ እንተ ታዲያ አማኝ ሆነህ እንዴት ልትለወጥ ቻልክ ?
ከተሳታፊዎች የተጠየቀ ነበር፡፡
ገበያ ስለማጠያየቅ፣ መረጃ ስለማፈላልግና ሃሳብህን ለኢንቬስተር ስለማካፈል ስለጻፍኩት ጉዳይ የጠየቃችሁት ልከ ነው፡፡ ጥንቃቄ ብዙ ትርፍ ያመጣልናል፡፡ ባለፈወ ሰባት መቶ ሚሊየን ዶላር አስይዤ የላኳቸው ሰራተኞቼ በዓለም ታሪክ በግል ባለሀብት የመጀመሪያውን ታላቅ ቦንድ ሊገዙ ነበር አካሄዳቸው፡፡ ስንትና ስንት ሰው ጠይቀው ላለመግዛት ወስነው መጡ፡፡ እንዲህ ያለ ጥንቃቄና ንቃት ያሻል፡፡
ጥራቱ የወረደ ምርትን አስመልክቶ በተጠየቀው ላይ ሁሉም አካላት፣ መንግስት፣ መያዶች፣ ተጠቃሚዎችም ሆኑ ስራፈጣሪዎች የተሳተፉበት አሰራር መኖር ይኖርበታል፡፡ አካባቢያችንን የጠበቀ፣ ቀጣይነቱን ያረጋገጠ፣ ደህንነታችንን የጠበቀ የፈጆታ እቃዎች ስርጭት ሊነረን ይገባል፡፡ ግንዛቤው ማደግና ስርዓቱ መዘረጋት አለበት፡፡ ታማኝነት ትልቁ ሀብት ነው፡፡ እሱን ወደ ስርዓታችሁ ካስገባችሁ ….
እምነት ከስኬት ጋር ይያያዛል ወይ ብለን ከጠየቅን ማናቸውንም እምነት አከብራለሁ፡፡ ብዙ የተለያየ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር እሰራለሁ፡፡ አሁን በምናገርበት ርዕስ ግን ሁላችንም የየራሳችን አተያዮች አሉን፡፡
ስራ ፈጣሪዎች ብዙ ነገር መስራት የለባቸውም፡፡ አንዱን አድምታችሁ ብትሰሩት ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡
ለወጣቱ አቅጣጫ እንድናሳየው እንጂ ገንዘብ እንድንሰጠው አያስፈልግም፡፡
100 000 ልጆችን እረዳለሁ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 40 000ዎቹ ወላጅ አልባዎች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ስራ ፈጣሪ ማህበራዊ ሃላፊነተም አንዳለበት አይዘንጋ፡፡
https://www.facebook.com/strivemasiyiwa/
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ