2017 ኦክቶበር 5, ሐሙስ

የቱ ግቢ?


ግቢ የሚለው ቃል ሲነሳ በእርስዎ አእምሮ ምን ይመጣል?
ጽሑፉን ከማንበብዎ በፊት አስተያየት መስጫው ላይ ይጻፉልኝ፡፡
ሁለት ዲያቆናት ግቢ ሲሉ የቤተክርስቲያኑን ቅጥር ግቢ ለማለት ይሆናል፡፡
ሁለት ሸኮች የመስጊዱን
ሁለት እስረኞች የእስር ቤቱን
ሁለት ኮማሪቶች የሆቴሉን
ሁለት ዳኞች የፍርድ ቤቱን….
በዕድሜ መስመር ወደ ኋላ ሄጄ ሳስብ ‹ግቢ› አንድ ትርጉሙ ይታየኛል፡፡ ይኸውም የብረታብረትና የሸክላ ስራ የሚሰራባቸው ስፍራዎች ግቢ ይባሉ ነበር፡፡ አንድ ሰው ‹‹እስቲ ግቢ ልሂድና ማጭድ ላሰራ፣ አያ ታችበሌ›› ሊል ይችላል፡፡ እነዚህ የዕደጥበብ ሰራተኞች ተገልለውና የራሳቸውን ሰፈር መስርተው የሚኖሩበት ቦታ ግቢ እንደሚባልና ልጆች እንደማይሄዱበት እናውቃለን፡፡ ተከብሮና ተፈርቶ የሚኖር አካባቢ ነው፡፡ ለመንደሩ ምስረታ መነሻ የሚሆነው ግን ሰዎቹ በማህበረሰቡ መገለላቸው ነው፡፡ እነሱም ወደ ሌላ ሰፈር እንዲሄዱ አይፈለጉም፡፡ ማህበር፣ እድር፣ ጋብቻም ውስጥ አይካተቱም፡፡ ዉበት አላቸው ቢባልም አይቀርቧቸውም፡፡ ሰውን አተኩረው ካዩ ‹ቡዳ› ተብለው ይሰደባሉ፡፡ ሲደነግጡ ‹አይበሉም› ስለሚባል - መብላት ብሎ ጣጣ! አሁንም ይህኛው የግቢ ትርጉሙ ነው በአእምሮዬ የሚመጣው፡፡ ‹‹ማጭድ ላላሰራ ወይ ቢላዋ፤ ግቢ አልሄድም›› ዓይነት ሃሳብ በውሳጤ ይመላለሳል ግቢ በተነሣ ቁጥር፡፡
ጊዜ ያነሣቸው ቃላት
ግቢ የሚለውን ቃል አሁን አሁን በተደጋጋሚ መስማቴ በፊት የነበሩ አንዳንድ ዘመን - አመጣሽ ቃላትን እንዳስታውስ ያደርገኛል - በሰፈርም ሆነ በፖለቲካው ዘንድ ሰው ሙጭጭ የሚልባቸው ቃላት ነበሩ፡፡ አሁንም ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ‹‹እንደ ወረዳ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ ቀላል፣ አደል…›› የመሳሰሉትን አስታወስኩ፡፡ ‹‹እንደ ወረዳ›› ሲሉ ‹‹እነዚህ ሰዎች ይህ ወረዳ ለአቅመ-ወረዳ አልደረሰም ማለታቸው ነው፤ ወይስ ወረዳ ተብዬ ማለታቸው ይሆን እላለሁ›› ጥሬ ቃሉን ብቻ እያሰብኩ፡፡ ድንገት ቦግ ያለች አጠቃቀም ነች፡፡ ቃሉ ሳይበረዝ በፊት ‹‹እንደ እህት ሆና አስታመመችኝ›› የመሳሰሉትን አባባሎች አስታውሳለሁ፡፡
‹‹ተው አትሽጥ ሲሉት በሬውን ሸጠና
ተው አትግዛ ሲሉት ምንሽር ገዛና
ደሞ እንደ ወንዶቹ ቆላ ወረደና
ሲነፋጠጥ መጣ ነጠቁኝ አለና››
በሚለው የቃል ግጥም ውስጥ ‹እንደ ወንዶቹ› ከሚለው አንጻር እዩልኝ እንደ ወረዳን - አስፋልት-የለሽ ወረዳ - ማለታቸው ይመስለኛል፡፡
የዩኒቨርሲቲ መምህራንስ?
በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት እንዲነሳ አድርጌ ነበር፡፡ ለማ ሚደቅሳ ‹ግቢ› ከበፊትም የነበረ እንደሆነና የሱ ታላላቆች ሳይቀር ይጠቀሙት እንደነበር ትዝ ይለዋል፡፡
አማን ቃዲሮ ግን ‹‹ግቢ ዩኒቨርሲቲን አይወክልም፡፡ የምን ግቢ ነው የሚወራው? ግቢ ኮምፓውንድ ነው እኮ፡፡ ስለ ካምፓስ ስለሆነ የምናወራው አንድ በሉኝ›› ይለናል፡፡
ለማ በበኩሉ ‹‹‹ግቢ እንገናኝ› ይባላል፤ ማለትም - ካምፓስ - አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ - 6 ኪሎ - 5 ኪሎ መሆኑ ነው›› ሲል ይቀጥላል፡፡ ሁለት ከምፓስ ሲኖር ዋናው ግቢምሚባ ነገር አለ፡፡ አአዩ ለዚህ አንድ ምሳሌ ነው፡፡ ‹‹በሌላ በኩል ሰፈራችን ውስጥ የያንዳንዱ ሰው ቤት ግቢ ነው››፡፡
አሁን ግቢ በጣም ዝነኛ ከመሆኑ የተነሣ አንድ ግቢ በሚል ቃል የሚጀምር አደረጃጀት አለ - ግቢ ጉባኤ ይባላል፡፡ ሰለግቢ ጉባኤ የሰማሁት ከዐሥር ዓመት በፊት ስለነበር ይህ ቃል እውነትም የቆየ ይሆን እንዴ አሰኝቶኛል፡፡ በተያያዘ ዜና ‹ግቢ› ቤተመንግስትንም ያመለክታል፡፡ ግቢ ገብርኤል የተባለው ለዚያ ይመስለኛል፡፡
እኔ ስማርም አልፎ አልፎ ቃሉ - ግቢ - ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ይመስለኛል፡፡ ኦሮሞ ጓደኞቼም በቋንቋቸው ሲያወሩ ‹ሞራ› የሚለውን ቃል ይጠቀሙ ነበር፡፡ የግቢ ትርጉሙ መሆኑ ነው፡፡
አጋጣሚዎችም አሉኝ ግቢን አስመልክቶ፡፡ ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻህፍት በዚህ በክረምት ስሰራ ተጠቃሚዎች መታወቂያ አስይዘው መጽሐፍ ስለሚዋሱ መጽሐፉን ሲመልሱ ምን ዓይነት ቀለም ነው መታወቂያው ስላቸው ‹‹የግቢ ነው›› ይሉኛል፡፡ ተማሪዎቹ በየዩኒቨርሲቲው የሚማሩ የደብረብርሃን ልጆች በመሆናቸው የተለያዩ ዓይነት መታወቂያዎች በየዩኒቨርሲቲው አሉ፡፡ ስለዚህ በኔና ነሱ መሃል ግቢ የሚለው ቃል ሊያግባባ አይችልም፡፡
በሌላ አጋጣሚዬ የመኪና ረዳት የሆነ ልጅ ባለፈው ከአዲስ አበባ ስንመጣ አንዲቱን ተማሪ ተዋውቋት ወሬ ጀመሩ፡፡ ከወሬው የሰማሁት ‹‹የት ነሽ ግቢ?›› የሚለው ጥያቄው አሰቆኛል፡፡ ግቢ ለሱ ምኑ ነው፡፡ ምናባት ለሱ ግቢ ተብሎ መጠራት የሚችለው መናኸሪያው መሆን ነበረበት፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ውጪ ላለው ግቢ ምኑ ነው? ተማሪዎች ‹‹ግቢ እንደዚህ አድርገን›› ሲሉ ሲሰማ ‹‹እኔም ከናንተው ቡድን ነኝ›› ለማለት የሚጠቀምበት ይሆናል፡፡ ስለ ትምህርት ቤታችሁ አውቃለሁ ማለቱ ይሆናል፡፡ እንደሷ ግቢን እንደሚያውቅ በማሳየት በመካከላቸው ያለውን ርቀት ለማጥበብ የተጠቀመበት ዘዴ ይመስለኛል፡፡
ዩኒቨርሲቲ የሚለውን መጥራት ካለመቻል?
ለኔ ከዋነኛ የግቢ ዝነኝነት ምንጮች ውስጥ አንዱ ይህ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲን አስተካክሎ መጥራት የሚችለው ሰው ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ መሄዱን ታዝቤያለሁ፡፡ ስለዚህ ግቢ ጥሩ መደበቂያ ነች፡፡ በር ላይ በጉልህ የተጻፈልንን ማንበብ ካልቻልን ለሌላ ዕውቀት ምን ዓይነት በር እንከፍታለን? ተመልካችነታችን የታለ?
ከዩኒቨርሲቲው ዉጪ ሆነው ስለ ዶርም፣ ካፌ፣ ክላስ፣ ላብ፣ ሳይሆን ባጠቃላይ ስለ ግቢ ነው የሚያወሩት፡፡ አፍ ላይ ደስ ይላል ልበል? አዎ፣ በእርግጥ ቅለትም አላት፡፡ ሁለት ፊደላት ናቸው፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...