ረቡዕ 25 ኦክቶበር 2017

ብድር ማስመለስ ተሳነን፤ ወይ ማስያዣ አልያዝን!





‹‹አበዳሪው ምን ያርግ ብሩ እንዲወልድለት
ተበዳሪው ምን ያርግ ልጆቹ እንዲያድጉለት
እኔስ የገረመኝ የዋሱ ሞኝነት››
ለአሁኑ ችግራችን የሚሆን የህዝብ ግጥም ስላጣን ይህን ተያያዥ ግጥም በመጋበዝ ጀመርን፡፡
1. በክፍል ጓደኛ መጭበርበር
2003 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኤፍ ካምፓስ የሚማርና በአንድ የምስራቅ ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምር ቆንጆ ልጅ ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን በድባብ መናፈሻ ሁሉም ጓደኞቹ ፀሐይ እየሞቁ ክፍለጊዜ እስኪደርስ ያሙታል፡፡ ከነዚህ ጓደኞቹ አንዱ ጓደኛዬ ስለነበር አጠገባቸው ሆኜ አዳምጣለሁ፡፡ አንዱ ልጅ ይህ ጓደኛቸው ስልክ አስደውለኝ እንዳለውና እንዳስደወለው፤ ካስደወለው በኋላ ሲያይ ግን ጓደኛቸው በስልኩ ውስጥ ገንዘብ እንደነበረው ይረዳል፡፡ ቁጭቱን በሆዱ ያዝ አድርጎ ዝም! ሁሉም የተነጠቁትን ገንዘብ እየተናገሩ ተደመረ፡፡ ብ ….. ዙ ብር ሆነ፡፡ ልክ የአገራችን ብሔራዊ ዕዳ በአሁኑ ሠዓት እንደበዛው ካቅሙ በላይ ሆነ፡፡ ይህ ልጅ ለመበደሩ ምክንያቱ ምን ይሆን? አመል ሳይሆን አይቀርም፡፡ ትምህርታቸው ስለገንዘብ ነገሮች በመሆኑ አንድ ቀን መምህራቸው ስለብድር አመላለስ ሲያስተምሩ እያቃለዱ ጠየቁ አሉ፡፡ እንዲህ በማለት "ከዚህ ክፍል ተበድሮ የማይመልስ አለ?" በማለት፡፡ ተማሪው ሁሉ ወደዚያ ዞረ አሉ፡፡ "ያልመለሳችሁ ቶሎ መልሱ ብድራችሁን" ብለው ትምህርቱን ቀጠሉ መምህሩ፡፡ ተማሪው በሳቅ!
2. በሰፈር ሰዎች መታለል
ዛሬ ከዚህ ያልተናነሰ ዚቅ ደብረብርሃን ተከሰተ - በሰባት ዓመቱ፡፡ ጓደኛሞች ተሰብስበን አንዱ ደወለልኝ፡፡ "ይህን ስልክ አላነሳም፤ 1000 ብር ነጥቆኛል" ብዬ ተናገርኩ፡፡ ከዚያም በቅደም ተከተል ገንዘብ የቀሙኝን በምሬት ዘረዘርኩ፡፡ ‹‹ጥሬ ገንዘብ ቆጥሬ ሰጥቼ!›› ተጀመረ ምክንያታዊ ቡጨቃ! "እኔንም ይሄን ያህል አስቀርቶብኛል! ከኔም ስንትና ስንት ብር ነጥቃኛለች! ደሞ ክህደቷ፡፡ እኔማ በኔ ሞኝነት እንዳልወሰደችው ነግሬያታለሁ፡፡ ሰጥቼሻለሁ የምትለው ደሞ!" መባባል ተጀመረ፡፡ የተበደሩባቸው የውሸት ግን ለጊዜው አሣማኝና አሣዛኝ ምክንያቶች ተነሱ፡፡ የጋራ ንግድ እንጀምር በማለት፣ የእቁብ ገንዘብ ሳይከፍሉ ከፍያለሁ በማለት፣ እቃ ወስዶ ባለመክፈል፣ የማትፈልገው ብር ካለህ ነገ እመልስላሃለሁ በማለት …. ፈልጌህ ነበር ብሎ ረፍት ነስቶ አገር የተሸበረ አስመስሎና ስትመጣ ጉዳዩን እነግርሃለሁ ብሎ ከስራ ቦታ ድረስ አሯሩጦ በማስመጣት፣ በቁልምጫ በመጥራትና የገሬ ልጅ እያሉ በማባበል፣ በርካታ ፈጠራ የተሞላባቸው ምክንያቶችን በመደርደር፡፡ ምን ነበር ጓደኝነትን ለሚያጠናክርና ለመልካም ነገር ፈጠራ ቢፈልጉ?
ለማስመለስ የተደረጉ ጥረቶች ተወሱ፡፡ በሞባይል ሜሴጅ ምላሽ የሚሰጡ አሉ፡፡ ‹‹አንቺ ጥሩ ልጅ አልነበርሽም ወይ? ለዚች ብር ምን እንደዚህ ያደርግሻል! ካገር አልጠፋ! አክስታችን ሞታ አገር ቤት ሄጄ ነው፡፡ (ሦስት ደርዘን አክስት ያላ ይመስል በየቀኑ አንድ ትገድላለች!)›› የትዳር አጋሮቻቸው አማላጅነት እንኳን አለመስራቱ ተወሣ፡፡ ባልና ሚስት ካንድ ‹አጭበርባሪ› ባህር ይቀዳሉ እንዲሉ፡፡ ያላበደሩት ሰዎች ምን አለባቸው! ዛሬም መልካም ጓደኝነታቸውን አስቀጥለዋል፡፡ ወጥመዱን እንዴት እንዳለፉት ያወሳሉ! ያበደርን ግን ወይ ምስጋና የለ፣ ምን የለ! ተበድረው ቤታቸውን ያደራጁ እንዳሉ ሁሉ በብሩ የተዝናኑበትም አይጠፉም፡፡ ነገ ብዙ ጓደኞቻችን ሲመጡና የአውጫጭኙን መጀመር ሲረዱ የየራሶቻቸውን ታሪኮች በቁጭት ያወጋሉ፡፡ ለማሸማቀቅ ብፈልግ እነዚህን ተበዳሪዎች ታግ አደርጋቸው ነበር፡፡ ገጠመኝ ካላችሁ ተጨማሪ የማጭበርበሪያ መንገዶቻቸውን ንገሩን፡፡ እስከዚያው የናንተን ገጠመኝ ፃፉልኝ፡፡ ወስደው ያስቀሩባችሁንም ኮሜንት ላይ ስማቸውን ጽፋችሁ መልሱልኝ በሉ፡፡
3. አጥማጅ የስራ ባልደረቦች
እስከ 2005 ድረስ ለበርካታ የስራ ባልደረቦቼ አበዳሪ ነበርኩ፡፡ ደሞዝ እስኪመጣ ድረስ ማን ጋ ስንት ብር እንዳለኝ ሳስብ እከርማለሁ፡፡ እንትና ጋ 65፣ እንትና ጋ 1200፣ እንትና ጋ 2000፣ እንትና ጋ 34 ወዘተ፡፡ ወይ አልጽፈው! ወይ ባንክ አይደለሁ! ወይ ባይመልሱ ማስያዣ አልያዝኩ! ደሞዝ ሲመጣ የሚመልሱ አሉ፡፡ የማይመልሱም አሉ፡፡ ስድስት ወር አቆይተው የሚያመጡም አሉ፡፡ ባገኙኝ ቁጥር ‹‹ብርህን ሳልመልስ፤ ቆይ ደሞዝ ሲመጣ›› የሚሉኝ አሉ፡፡ ከተበዳሪው በላይ ስሳቀቅ ቆየሁ፡፡ ዓይናቸውን አየት ሳደርግ ብሬን አምጣ የሚል አስተያየት እንዳይመስልብኝ ስሰጋ እቆያለሁ፡፡ ‹‹ከባለፈዋ ጋር የሚመለስ 200 ብር ጨምልኝ›› እባላለሁ፡፡ ከባንክ አውጥቼ ሰጥቼ ሲመልሱልኝ ባንክ አላስገባውም፡፡ አባክነዋለሁ፡፡ ቢመልሱም የቆብኩትን አስጠፉኝ ማለት ነው፡፡ ቆይቶ ተበዳሪዎቼን ማራቅ ጀመርኩ፡፡ አንዱ ገንዘብ ቸገረው፡፡ መሄጃ አጣ፡፡ በየወሩ የማበድረው እኔ ነበርኩ፡፡ አትምጣብኝ ብዬዋለሁ፡፡ ከነጓደኛው ‹‹ክፉ ሰው›› የሚል ስም አውጥተውልኛል፡፡ ታዲያ ክፉ ሰውን እንዴት አበድረኝ ይበል፡፡ ምላሼንም ይገምታል፡፡ ሌላ ጓደኛውን ጠይቆት ኖሯል፡፡ ያ ጓዳኛው ደግሞ ምንም ሱስ የሌለበትና ተበድሮኝ የማያውቅ ነው፡፡ ‹‹ኤቲኤም አልሰራ አለኝ፤ ነገ ሰኞ የምሰጥህ 300 ብር ስጠኝ›› ሲል ጠየቀኝ፡፡ ሰጠሁት፡፡ ወዲያውኑ አብሮን ለነበረው ለዚያ ጓደኛችን ሰጠው፡፡ እሱም ‹‹እኔ ከሱ አልፈልግም፤ ይቅርብኝ›› አለ፡፡ በልምምጥ ተቀበለው፡፡ ገንዘብ ቆጥብ ስለው የማይሰማኝ ሰው ለምን ገንዘብ ይጠይቀኛል ብዬ ስለማምን ነበር በሱ ላይ ያን ውሳኔ የወሰንኩት፡፡ ወስዶም ለሱስ ነው፡፡ ተበድሮኝ አያውቅም፡፡ ጓደኛ ራሱን እንዳያሻሽል መንስኤ መሆንም ይመስለኛል ማበደር፡፡ አሁን የስራ ባልደረቦቼን የአበድረኝ ጥያቄ ፈጽሞ አስቀርቻለሁ፡፡
ለመሰናበቻ፡፡ ምን ጊዜም ስንጽፍ የልጅነታን ነገር ትዝ ይለናል - ያለፈው፡፡ ሳሲት ከተማ ላይ አንድ ደግ ሰው አለ፡፡ ባም ጋባዥ ነው፡፡ ሰዎች ስለሱ ሲያወሩ የሰማሁት ነገር ይገርማል፡፡ ‹‹ጋሼ እኮ ከተበደረም አይመልስም፤ ካበደረም አይጠይቅም›› ያሉት ነገር ገርሞኛል፡፡ የማይመልሰው እየረሳው ሳይሆን አይቀርም፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school.

  Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school. The Shenes said they wanted to aven...