ሕይወቴ፣ ለአገሬ ኢትዮጵያና ለወገኖቼ ኢትዮጵያውያን ዕድገት የነበረኝ የሥራ ጥማት - ቅጽ አንድ
ደራሲ - ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ
ዘውግ - የሕይወት ታሪክ
የገጽ ብዛት -636
የታተመበት ጊዜ - ጥር 2012
ዳሰሳ - በመዘምር ግርማ
ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት፣ ደብረ ብርሃን፣ መጋቢት 2012
mezemirgirma@gmail.com
ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ በ1917 በሐረርጌ ተወለዱ፡፡ በአሰበ ተፈሪ፣ በሐረርና በአዲስ አበባ የተከታተሉት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው በጣሊያን ወረራና በሌሎችም ምክንያቶች መስተጓጎል ስለደረሰበት የጨረሱት ዕድሜያቸው ከመደበኛው ከፍ ብሎ ነው፡፡
በወለጋ፣ በሐረርጌ፣ በሲዳሞ፣ በወላይታና በአዲስ አበባ አስከ ረዳት ሚኒስትር ድረስ ባሉ የተለያዩ የስራ መደቦች አገራቸውን በላቀ ትጋት አገልግለዋል፡፡ አሁን በ95 ዓመታቸው በሚኖሩባት በአዲስ አበባ የጻፉትን ይህን የሕይወት ታሪካቸውን በኮምፒውተር የተየቡት ራሳቸው ናቸው፡፡
ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ጀምሮ ከካናዳውያን ጀስዊቶች አንጻር በጀመሩት ለኃይማኖታቸው የመሟገት እንቅስቃሴ ምክንያትነት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው ተቋርጦ ወደ ደብረ ዘይት አየር ኃይል ተላኩ፡፡ ከአጭር ጊዜም በኋላ ወደ አገር ግዛት ሚኒስቴር ተዛውረው የሚኒስትሩ የራስ አበበ አረጋይ ረዳት ለመሆን በቁ፡፡ ከራስ ባለቤት ከእመቤት ሆይ ቆንጂት አብነት ጋር በነበራቸው ዝምድና ምክንያት ከራስ ሊቀራረቡ የቻሉት ደራሲው ስለ ራስ አበበ አረጋይ አገር ወዳድነትና ጥረት ይነግሩናል፡፡ ወጣቱ ወልደ ሰማዕት የእርሳቸው የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርና ሰነዶችን እያነበበ ምላሻቸውን የሚጽፍ ረዳት ለመሆን በቃ፡፡ በሚኒስትር መስሪያቤቱ ይሰራ ስለነበረው የኢትዮጵያና የቅኝ ተገዥ ጎረቤቶቿን የወሰን ማካለል ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ነጥቦችን ያስይዙናል፡፡ ሕዳር 3 ቀን 1945 ዓ.ም በባለርስቶች መሬት ላይ ሰፍሮ በጭሰኝነት የሚገኝና በከተማም ሆነ በገጠር ርስትና ስራ የሌለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ በተለይ ጭሰኛው ግማሽ ጋሻ መሬት በርስትነት እየተሰጠው እንዲያለማ የሚያደርግ አዋጅ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ታውጆ ነበር፡፡ ደራሲው ከልጅ ኃይለማርያም ከበደና አቶ ግርማሜ ንዋይ ጋር በመሆን ይህን ተግባራዊ ለመሆን ያልቻለ አዋጅ ወደ መሬት ለማውረድ ሞክረው ነበር - በምጣኔ ሐብታዊ ችግር ሳይሳካ ቀረ እንጂ፡፡
ደራሲው የተቋረጠውን ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ቤሩት አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ለመሄድ በቁ፡፡ እዚያም በትጋት ለመማር መብቃታቸውን፣ አረብ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያሴሩትን ሴራ ማጥናታቸውንና ወደ ሃገራቸው መመለሳቸውን ከሳቢ ትዝታዎች ጋር እናነባለን፡፡
ወደ ሃገር ተመልሰው የቀድሞ መስሪያ ቤታቸውን ለጥቂት ጊዜ ካገለገሉ በኋላ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት የፀጥታ ዲሬክተር ሆኑ፡፡ በዚያም የእንግሊዝ ታላቋ ሱማሌን ሴራና የእርሳቸውን ትንቅንቅ እናያለን፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ውህደት የሚጠይቁ የሱማሌ ላንድ መልዕክተኞችን ከንጉሠ ነገስቱ ጋር ስለማገናኘታቸውም እናነባለን፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም የኛ ዓላማ በሂደት አፍሪካም አንድ አገር እንዲሆን ነው እንዳሉ እንታዘባለን፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጭሰኞችን ባለመሬት የሚያደርገውና ኢትዮጵያን የአፍሪካ የእህል ጎተራ ያደርጋል የተባለለት የ1946 አዋጅ ገቢራዊ ለመሆን የወዳጅ አገሮች እርዳታ አስፈልጎት የአውሮፓ አገሮችና አሜሪካ ቢጠየቁ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ፡፡ የሶቭየት ሕብረት መንግስት በአንጻሩ 400 ሚሊዮን ሩብልስ አበደረ፡፡ በዚህም ገንዘብ የታቀደውን ልማት ለማልማት ወልደ ሰማዕት የልማት ምክር ቤት አባል ሆኑ፡፡ ልማቱ ከስራ ላይ እንዳይውል በምዕራባውያን መንግሥታት በኩል ከፍተኛ ጫና ይደረግ ስለነበረና ሚኒስቴሮች ሳይቀር በፈረንጆቹ ውትወታ የሴራው ተባባሪዎች በመሆናቸው ዕቅዱ በርካታ እክሎች ገጠሙት፡፡ በነዚህ ጊዜያት ወልደ ሰማዕት ሽንጣቸውን ገትረው ተሟገቱለት፡፡ በሚኒስትሩ በጄኔራል ሙሊጌታ ቡሊም ታጩ፡፡ ወዲያውም በሹመት ይህንኑ ስራ ወደሚያስተባብሩበት ወደ ሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር ተዛወሩ፡፡
በዚያም የአስተዳደር መምሪያ ዲሬክተርነት ስራቸውን እየሰሩ ሳለ ሚኒስትሩ በቤተመንግሥት ሆነው ያግዟቸው ነበረ እንጂ ደጃዝማች እርሳቸውን ወክለው ነበር የሚሰሩት፡፡ መስሪያ ቤቱን በዘመናዊ መንገድ በአዲስ ግቢ አደራጅተዋል፡፡ የአውራጃዎች የውስጥ አስተዳደር ሥልጣን ተጠንቶ መስፈርቱን ለሚያሟሉት በመስጠት የፌደራል ሥርዓት ግንባታ ሂደትም በሙከራ ላይ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሆነውና የዚያኔው የገጠር ልማት ኦፊሰሮች ማሰልጠኛ ኮሌጅ የነዚህ አውራጃዎች የተማሩ አስተዳዳሪዎች አንዲሰለጥኑበት ተደረገ፡፡ የሕዝባዊ ነኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር የሃገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያሻሽል የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ ከሶቭዬት ሕብረት በተገኘው ድጋፍ ከጣሊያን ወረራ በኋላ በእንግሊዝ ጫና ስር ለአስር ዓመታት የቆየችውን ደሃ ሃገር ራሷን ለማስቻል ይጣጣር ነበር፡፡ በዕቅዱ ስራ አጥ፣ ጭሰኛ፣ የከተማም ሆነ የገጠር ነዋሪ፣ ኋላቀር የሆኑ የዳር ሃገር ህዝቦች ሰርተው የሚለወጡበትን የገንዘብ፣ የማሽነሪ፣ የስልጠናና ሌሎችም ድጋፎችን ለማድረግ ታልሞ ከዜጎች የሚፈለገው መልካም ፈቃድ ብቻ መሆኑን ይታይ ነበር፡፡ ማህበራዊ ስራዎች እንዲሁም የህብረት እርሻና ሕዝብ የማስፈር ስራዎች ከዩጎዝላቪያና ከሶቭየት ህብረት በመጡ አሰልጣኞችና ባለሙያዎች ጭምር ተጀምረው ነበር፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው መሬት ላራሹ ንገሠ ነገሥቱ ለሃያ ዓመታት የጓጉለት ነበር ማለት ነው፡፡
የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ፈጽሞ አሁን በአደባባይ እንደሚወራለት እንዳልነበረ ደራሲው ለክስተቱ ከነበራቸው ቅርበት አስገንዝበውናል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት አድመኞቹ ወንድማማቾች ብርጌዲየር ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይና አቶ ግርማሜ ነዋይ ከሚወራላቸው በአንጻሩ ለአገር ዕድገት የማይቆረቆሩና ጊዜያቸውንም በዋል ፈሰስ የሚያሳልፉ ስለመሆናቸው የተለያዩ አብነቶችን እየጠቀሱ ያስረዱበት ነው፡፡ የሴራ ፖለቲካንና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ተግባር በማጠናቀር ያስረዳን የደጃዝማቹ መጽሐፍ ሁለቱ ከወንድማማችቹ ጋር አበሩ የተባሉት ጄኔራል ጽጌ ዲቡና ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ እስረኞች እንጂ አድመኞች እንዳልነበሩ ገልጸዋል፡፡ በምዕራቦች ‹‹ይችን ገንዘብ አትበሏትም›› ዛቻና ሴራ ምክንያት እንዲቋረጥ የተፈለገው በሶቭየቱ እርዳታ የሚደገፈው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የማሳደግ ዕቅድ በዚህ በ1953ቱ መፈንቅለ-መንግስት ሙከራ ነው የከሸፈው፡፡ የዕቅዱን መሪና አስተናባሪ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊን ጨምሮ አገራቸውን የሚወዱና ከጣሊያን ጀምሮ ሕይወታቸውን የሰጡላትን እነ ራስ አበበ አረጋይን በጠቅላላው 18 ባለስልጣኖች ሲረሸኑ የአሜሪካው አምባሳደር በአስፈጻሚነት እዚያው ቤተመንግስት ነበር፡፡ በመስኮት ዘሎ መሄዱም ተጠቅሷል፡፡
የህዝባዊ ኑሮ ዕድገት ዕጣ ባንዴ እንዴት እንደተንኮታኮተ ለማየት የዚህን ሴራ አፈጻጸም መረዳት በቂ ነው፡፡ ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት የትልቁ ዕቅድ ቀንደኛ ደጋፊ ስለነበሩ በምዕራቡ ሴራ ደጋፊ ሚኒስቴሮች ምክንያት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገለል እንዲሉ ተደረገ፡፡ ይህን የወላይታ አውራጃ ገዢነት ሹመት ተቃውመው ጠፍተው ከነበረበት ሲመለሱ ንጉሠ ነገሥቱ ተግሳጽና ምክር ሰጥተው አግባቧቸውና የወላይታውን ሹመት ተቀበሉ፡፡ ቀጥሎ የምናየው ያንን ቅዱስ ዓላማ እንዴት በራሳቸው ጥረትና የወላይታን ህዝብ በማስተባበር በተወሰነ ቦታ እውን እንዳደረጉት ነው፡፡
በወላይታ አውራጃ አስተዳዳሪነት የተመደቡት ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ቀደም ብለው ወደ ስፍራው ከመሄዳቸው በፊት በአዲስ አበባ ከሚገኙ የተለያዩ መስሪያ ቤትች ጋር በአውራጃው ስላቸው የልማት ስራ እየጠየቁ ለወደፊቱም የትብብር ጥያቄ ያቀርቡ ጀመር፡፡ አገር ጎብኚ መስለው ከጋደኞቻቸው ጋርም አውራጃውን ቀደም ብለው ጎበኙ፡፡ በውጪ ሃገር የተማሩትን የሕዝብ አስተዳደርና ከእንግሊዝ በርቀት የተማሩትን የምጣኔ ሐብት ዕውቀት እንዴት እንደሚጠቀሙት ከአጀማመራቸው እያየን ነው፡፡ ወደ አውራጃው ሄደው በሶዶ ከሰራተኞች ተዋወቁ፤ ያረጁ ህንጻዎችን አሳድሰው ለልማት፣ ፍትሕና ርትዕ ያላቸውን ቁርጠኝነትም አስገነዘቡ፡፡ የፍርድ ስርዓቱን ከጉቦ አላቀቁት፡፡ ከኢትዮጵያ በመጥፎ የወንጀል ድርጊቶች የሚታወቀውን አውራጃ በዘረጉት የጸጥታ መዋቅር ምክንያት ወንጀል የሌለበት አደረጉት፡፡ ቀደም ብሎ የአውራጃው አስተዳዳሪ በነበረው በጓደኛቸው በግርማሜ ንዋይ የተጀመረው የሰንተርያ መጠናከርና የሌሊት ገበያ መቅረት ለዚህ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የአውራጃውን ካርታ አስነሱ፤ የቤት ለቤት ሕዝብና ቤት ቆጠራ አካሄዱ፤ አውራጃውንም በአዲስ መልክ አዋቀሩ፡፡ የሶዶ ከተማ ቶፖግራፊ ካርታ ዝግጅት፣ የሬዲዮ ቴሌፎንና የስልክ መስመር መዘርጋት፣ የባንክ አገልግሎት መጀመር፣ የየብስ መገናኛ አገልግሎት መስፋፋት፣ የአየር መገናኛ አገልግሎት መሻሻል፣ የዘመናዊ የቧንቧ ውኃ አቅርቦት ሁሉ ለልማቱ መስመር ከቀደዱ ሁነኛ ተግባራት የተወሰኑት ነበሩ፡፡
የወረዳ ከተሞች ማስተር ፕላን ዝግጅትና የከተሞቹ ወደ ዘመናዊነት መቀየር፣ የአውራጃው የእርሻ ልማት፣ የህዝብ ማስፈር፣ የእርሻ ባለሙያዎች ምደባ፣ የልዩ ልዩ ሰብሎች ልማትም በብዙ ጥረቶች ሕዝብንና ሚኒስቴር መስሪያ ቤትችን በማስተባበር የተደረሰበት የልማት ድል ነው፡፡
ዩኔስኮ፣ የስዊድን ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት፣ እንዲሁም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወላይታን በማድነቅና ዝናዋን በመስማት ሊጎበኙ ችለዋል፡፡ የስዊድን ፓርላማ አባላት ሊጎበኙ በመጡበት ወቅት ደጃዝማች በመኪና አደጋ ምክንያት አዲስ አበባ ሆስፒታል ተኝተው ስለነበር ከነአልጋቸው ወደ ስፍራው በአውሮፕላን በረው አካባቢውንና ልማቱን ለማስገብኘት መቻላቸው የነበራቸውን ቀናኢነት ያሳያል፡፡
ተዓምር ሊባል የሚችልና የመንገዶች ባለስልጣን መሐንዲሶች አይተውት አንሰራም ‹‹በጣም ደፋር ነህ›› ያሉትን ትልቁን የኦሞ ወንዝ ድልድይ ደጃዝማች ሕዝብን አስተባብረው ከእንግሊዝ 47 ሜትር ርዝመት ያለው ተገጣጣሚ ድልድይ በማምጣት ሰርተው በንጉሠ ነገሥቱ አስመረቁት፡፡ በብላቴ ወንዝ ላይ የተዘረጋውም የብረት ድልድይ ሌላ አይቻልም የተባለ ነገር እንደተቻለ ያሳዩበት ነው፡፡
የፋኦ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዓሊ አልቶም በአስር ቀን የወላይታ ቆይታቸው ባካሄዱት ጥናት ሪፖርት ‹‹የተፈጸሙት የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ኢንተሌክቹዋልስ (ምሁራን) ጭምር ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡›› በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የፋኦና አይቢአርዲ ጥናትና የዋዱ መቋቋምን በዳሰሰው ክፍል ዋዱ ምን ያህል ገንዘብ እንደፈሰሰበትና በቸልተኝነት የሕዝብ ገንዘብ እንዳለቀበት በቁጭት ተናግረዋል፡፡ ዋዱ እርሳቸው የማይመሩትና በፈረንጆች የሚተዳደር መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የኢንቬስተሮች ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎች በአውራጃው እንዲስፋፉ ባደረጉት የማግባባትና የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራ በየዘርፉ ኢንቬስተሮች ገብተው ምርታቸው በየሁለት ቀኑ በአውሮፕላን ከስፍራው ወደ አውሮፓ እንዲጫን አድርገዋል፡፡ ትምህርት፣ ትምህርት በሬዲዮና ጤናም ተስፋፍተዋል፡፡
ይህን ሲሰሩ በዚያን ባልሰለጠነ ወቅት ያጋጠሟቸው ችግሮች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ብዙ እንቅፋቶችን እየተጋፈጡና ዙፋን ችሎት ድረስ እየተከሰሱ ነበር፡፡ ለሦስት ወራት ደምወዝ ሳይከፈላቸው፣ ተመድበው የነበሩ ፖሊሶች ተቀንሰውባቸው፣ ባላባቶች ከባድ ቅስቀሳ እያደረጉባቸው፣ ሕዝብ እንዲነሳባቸውና መንገድ ስራው እንዳይቀጥል ቅስቀሳ ተደርጎባቸውና አደጋ ለማድረስ ተሞክሮባቸው ሁሉ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ጋሬጣ መካከል ሕዝብን አስተባብረው የሰሩት ስራ አሁን በብዛት ደብዘው ጠፍቶ ሲያዩት እንዴት ከሃምሳ ዓመት በላይ ወደኋላ እንደሄድን እያሰቡ ይቆጫሉ፡፡
ወላይታን ከጎበኙ በርካታ ሰዎችና ኃላፊዎች አድናቆት ተቸረዋል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ለጉብኝትም ተጋብዘዋል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ጎብኝት አንዱ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ልጃቸውን ያሳከሙበትና እርሳቸውም የሕክምና አገልግሎት ያገኙበት ነበር፡፡ አሜሪካውያን ስላሰናከሉት ኢትዮጵያውያንን ያበለጽግ የነበረ ልማት ሲነሳባቸው አለመውደዳቸውን ያወሱናል፡፡ በትምህርት ቤት ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ለተማሪዎች ንግግር እንዲያደርጉ ተጋብዘው ስለ ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክና ሥልጣኔ ሲያያሩ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አስቁመዋቸዋል፡፡ ከጎበኙት የአሜሪካን ስልጣኔም በወፍ በረር ያስቃኙናል፡፡
በስዊድን ጉብኝታቸውም የሃገሩን ልማት፣ የሲዳ ዳይሬክተርን ልዩ ትጋት፣ የአዝዕርት ንጉሥ በተባለው በጤፍ ላይ የሚያደርጉትን ምርምር ወዘተ ያስቃኙናል፡፡
ከሰባት ዓመታት የወላይታ አገልግሎት በኋላ ሕዝቡ አይሂዱብን ሲል ወደ ሲዳሞ በሹመት ተዛወሩ፡፡ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ምክትል እንደራሴ ሆኑ፡፡ በሲዳሞ አለቃቸው ሆነው የሚጠብቋቸው እንደራሴ ክቡር ሌተና ጄኔራል ነጋ ኃይለሥላሴ ሲሆኑ የደጃዝማችን ወላይታን በልዩ ሁኔታ የማልማት ተግባር አይተው እንደ ተገንጣይዋ የናይጀሪያ ግዛት ባያፍራ መሪ በመቁጠር ‹‹ኮሎኔል ኡጁኩ እንደምን አሉ?›› ይሏቸው ነበር፡፡ በስተኋላም መግባባት ተስኗቸው ደጃዝማች በነጻነት በሚሰሩበት ሁኔታ መንገዱ ተመቻቸ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ የብላቴን ወንዝ ሸለቆ ሲጎበኙ የሄሊኮፕተር አደጋ እንደደረሰ ደጃዝማች በሄሊኮፕተሯ ውስጥ ነበሩ፡፡ ከአደጋው ጋር የተያያዘ ብዙ ወግ አውግተዋል፡፡ በየወረዳው ድንገተኛ ጉብኝት እየደረጉ ህዝብን የሚጨቁኑትን እየቀጡ መማማሪያ የሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ የመንግሥት ተሸሚዎችንና ሰራተኞችን አንቅተዋል፡
ሐዋሳ ከተማ የተመሰረተው በሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር የሶቭየት እርዳታ በማግኘቱ ምክንያት ነው፡፡ ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ማሰልጠኛ ኮሌጅ በቦታው ተቋቁሟል፡፡ ከበርካታ የልማት ስራዎቻቸው ውስጥ የሐዋሳ ሞያሌ ኢንተርናሽናል መንገድና በመንገዱ ላይ ያሉ ከተሞች ልማት ተጠቃሽ ነው፡፡ ዕቅዱ እንደ ሌሎች በርካታ ዕቅዶቻቸው ‹‹መቅሰፍት›› እና ሌሎችንም ከባባድ ስሞች በሚሰጡት በደርግ ተኮላሽቶባቸዋል፡፡ የመንደር ማሰባሰብ፣ የወህኒ ቤቶች ልማት፣ ከቤተክርስቲያን ጋር የተያያዘ የትምህርት ልማትና የኢንቬስትመንት መስፋፋት በሲዳሞ ከሰሯቸው ስራዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ከሲዳሞ ወደ ወለጋ የተቀየሩት በተለያዩ ጥቅም ፈላጊ ጄኔራሎች የአላስበላ አለን ሴራ ወይም ለወለጋ ልማት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በመፈለጋቸው ይሆናል፡፡
የወለጋ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሆነው እንደተመደቡ ነቀምቴን ጎብኝተው በቀጣዩ ጊዜ አውራጃዎችንና ወረዳዎችን ከተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ጋር ጎብኝተዋል፤ አጥንተዋል፡፡ ይህ ለቀጣይ ልማት መሰረት ይሆናል ተብሎ የታሰበው ጥናት በመጽሐፍ መልክ ተጠርዞ ለሚመለከታቸው ሚኒስትሮችና ለንጉሠ ነገሥቱ ቀርቧል፡፡ አንብበው ምላሽ ለመስጠት አልፈለጉም ወይም በክፉ እንዲታይ ተደርጓል፡፡ ይህ የአርባ አምስት ቀናት ጉብኝት 4300 ኪሎሜትር የሸፈነ ከባድ ጉብኝት ሲሆን እስከ ሱዳን ጠረፍ ሄደውበታል፡፡ ጀርመኖች የአካባቢውን ኦሮሞዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያፈነግጡ የሚያስተምሩበትን ቦታ ጎብኝተው አስጠንቅቀዋል፡፡ የወሎ ስደተኞች በወለጋ በራሳቸው ፈቃድ ሰፍረው አግኝተዋቸዋል፡፡ ግፍ የሚፈጽሙ ሹመኞችን ቀጥተዋል፤ ሽረዋል፡፡ ከጉብኝት መልስም ረዘም ላሉ ቀናት የስራ ኃላፊዎችን ሰብስበው የተለያዩ የልማት ቡድኖችን በጥናቱ መሰረት አቋቁመዋል፡፡
ደጃዝማች ሴራዎችን ያጋልጣሉ እንዳልነው ‹‹ያልተደበቀው የወሎ ረሃብ›› በሚለው ክፍል የወሎ ረሃብ በቀኃሥ መንግስት እንዳልተደበቀና የጋዜጠኛው ዮናታ ዲምቢልቢ አገላለጽ ለዓለም ሕዝብ የተደበቀ ወይም ሳያየው የቀረ ለማለት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ጋዜጠኛው በመንግሥት ተጋብዞ የመጣና ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እርዳታ ለማግኘት ታስቦ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ገንዘብ እንዲዋጣ በተደረገበት ሁኔታ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ደብቀው ነበር የሚለውን ይቃወማሉ፡፡ ረሃብተኞቹን ለመርዳትና በሌሎች ጠቅላይ ግዛቶች ለማስፈር የተደረጉ እርሳቸውም የተሳተፉባቸውን ጥረቶችም ያሳያሉ፡፡
በመሬት ላራሹ ሰልፍ በጸጥታ ኃይሎች ላይ ይደርስ ስለነበረው ጉዳትና ስለጄኔረል ይልማ ሺበሺ አቤቱታ፣ ስለ ክቡር ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ካቢኔ ሥራ መልቀቅና ስለ የልጅ እንዳልካቸው ካቢኔ መተካት፣ እንዲሁም ስለ ልጅ ሚካኤል እምሩ ስልጣን መያዝ ያወጉናል፡፡ ከነቀምት ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት መገደዳቸውም እናነባለን፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ራሷን ችላ እንድትተዳደር ለማድረግ የተቋቋመ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ቢሰሩም በኮሚቴውና በጳጳሱ መካከል በነበረ አለመስማማት ዕቅዱ አለመተግበሩን ይተርኩልናል፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ የመጨረሻ ቀናት ሰሞን ደራሲው ለበርካታ ቀናት ከልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ጋር ስላደረጉት ውይይት እንገነዘባለን፡፡ በስተመጨረሻም ብዙ ከሞት አፋፍ የተረፉባቸውን ተዓምራዊ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎችም ዘርዝረዋል፡፡
ለቤተሰቡ ጊዜ የሌለው፣ ለልማት ሕይወቱን የሰጠ፣ የተግባር ሰው፣ መፍትሔ በኪሱ ብላቸው የሚገልጻቸው የማይመስለኝ ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ በድንቅ አተራረክ ያቀረቡልንን አይጠገቤ መጽሐፍ አንብቤ ስጨርስ ባያሌው ለስራና አገሬንና ወገኔን ለማገልገል ተነሳስቻለሁ፡፡
የሸገር ኤፍኤም የጨዋታ እንግዳ ዝግጅት የሰጡት ከሃያ በላይ ክፍል ያለው ቃለመጠይቅም መጽሐፉ ላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች በሚገባ ስለሚያብራራ ከንባባችሁ ጎን ለጎን እንድትከታተሉት እጋብዛለሁ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ