2020 ፌብሩዋሪ 23, እሑድ

የእሁዱ ግብር በደብረ ሆላንድ (The Sunday Banquet at Debre Holland)


የእሁዱ ግብር በደብረ ሆላንድ
(The Sunday Banquet at Debre Holland)
በመዘምር ግርማ (mezemirgirma@gmail.com)
14. 06.2012


ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ በዕለቱ ያደረኩትን ምልከታ፣ የጠየኳቸውን ሰዎች አስተያየት እንዲሁም ethiopiapoultry.com የተባለውን የድርጅቱን ድረገጽ ተጠቅሜያለሁ፡፡

መንደርደሪያ
ከመጓዛችን በፊት ባሉት ቀናት የሆነውን በመጻፍ ልጀምር፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ምሕንድስና መምህሩ ሕንዳዊው ዶክተር ጀሚር ከረጅም ጊዜ ቀጠሮ በኋላ የደብረ ሆላንድን ኃላፊ አርኖልድን ወደ ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት አመጣው፡፡ አርኖልድም ቤተመጻሕፍቱን ጎበኘ፡፡ እሱ እየሰራ ስላለውም ስራ አስረዳኝ፡፡ የድርጅቱን ስኬት አስመልክቶ እሁድ ለሚደረገውም ግብር እንደተጋበዝኩ ነገረኝ፡፡ እኔም ስለምጎበኘው ነገር እንደምጽፍና በብሎጌ እንደምለቅ ነገርኩት፡፡ ‹‹ስንት ነው የምታስከፍለው››  በማለት ጠየቀኝ፡፡ እኔም እንደማላስከፍል ነገርኩት፡፡
ስለ ዶሮ እርባታው በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ ድርጅቱን ከሚያውቁ ሰዎች ጋር ተነጋገርኩ፡፡ በዚህም ውይይት የድርጅቱ አሰራር እስካሁን ከምናውቀው ለየት እንደሚል ተረዳሁ፡፡ ጫጩቶቹ ከሆላንድ እንደሚመጡ፣ በፋብሪካው ውስጥ ላለችው ለእያንዳንዷ ስራ አንድ የሆላንድ ድርጅት በቅርበት እንደሚያማክር፣ አንዲትን ዶሮ በሁለት ቀን ሦስት እንቁላል እንደሚያስጥሏት  ወዘተ ለማወቅ ቻልኩ፡፡
ዕለቱ ከመድረሱ በፊት ልሂድ አልሂድ በደንብ አልወሰንኩም ነበር፡፡ ዶክተር ጀሚር እሁድ ከሰዓት በኋላ ጦስኝ አምባ ሆቴል እንድጠብቀው ሲነግረኝ ለመሄድ ወሰንኩ፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን አብረውኝ የነበሩት ሁለት ጓደኞቼም ለመሄድ ስለተስማሙ ሄድን፡፡ ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች፣ መምህራንና ሰራተኞች በአራት መኪኖች ሄድን፡፡ እኔ የነበርኩባት የዶክተር ጀሚር መኪና ከሹፌሩ በተጨማሪ አንድ ሰው ብቻ የምትይዝ ኖራ ሁለታችን ተሳፈርንባት፡፡

መንገዱና አካሄዳችን
እንደሚታወቀው ደብረ ብርሃን ብዙ ኢንቬስትመንት እየጋበዘች ነው፡፡ የጅሩ መንገድ ግን አልተሻሻለም፡፡ እኛም እየሄድን ያለው በዚሁ መንገድ ነው፡፡ መንገዱ በቅርቡ የፍጥነት መቀነሻ በትራክተር እየተከመረ ተሰርቶለታል፡፡ በሱ ላይ እየነጠርን በጅሩ መንገድ የተወሰነ (ቢበዛ አንድ ኪሎሜትር) ከሄድን በኋላ ወደ ቀኝ ወደ ጎሼ ባዶ መንገድ ታጠፍን፡፡ የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ግራ ትተን መሆኑ ነው፡፡ ጎሼ ባዶን በአድህኖ የገጠር ልማት ማህበር በኩል በአስተርጓሚነት ስራ ብዙ ጊዜ ጎብኝቻለታለሁ፡፡  በዚያ መንገድ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሄደን ወደ ግራ ወደ ቢርቢርሳ ቀበሌ ታጠፍን፡፡ ይህ 1.1 ኪሎሜትር መንገድ በደብረ ሆላንድ ዶሮ እርባታ ኃ/የተ/የግ/ማ በ2.4 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ነው፡፡
ቀኑ የተወሰኑ ነጫጭ ደመናዎች እዚህም እዚያም የተበታተኑበት የጠራ ሰማይ የሚታይበት፣ ከአቧራው በቀር አገር ፍቅርና የመዝናናት ስሜት የሚያመጣ ነገር ያለበት ነው፡፡ ከከተማ ጫጫታ እፎይ ያስባለን የገጠር ትዕይንት እውነት ለመናገር አስደሳች ነበር፡፡ ዶክተር ጀሚር የእንግሊዝኛ ዘፈን ከፍቶ እየኮመኮመ ትኩረቱን በመኪና መንዳቱ ላይ አድርጓል፡፡ ስለሃገራችን አየር ንብረት ስጠይቀው በአመዛኙ ጥሩ ሆኖ ትንሽ አለመስማማት እንዳለውና በተለይ ለቆዳው የፀሐይ መከላከያ እንደሚቀባ ነገረኝ፡፡ እኛ ጥቁሮች ያለን ሜላኒን እዚህ ለመኖር እንደተፈጠርን ምስክር ነው፡፡ ለነጮቹም ግን ረጅም የበረዶ ወቅት በሃገራችን አለመኖሩ የኛን አየር ተመራጭ እንደሚያደርገው አያጠራጥርም፡፡

የቢርቢርሳ ቆይታችን
በስፍራው ደረስን፡፡ የሰማይን ሁሉንም ጫፎች ምንም ነገር ሳይካልላችሁ የምታዩበት ነው፡፡ ደብረ ብርሃን ውስጥ በኃይለማርያም ማሞ ግቢ ብቻ ያየሁት ትዕይንት መሆኑ ነው፡፡ አድማሱን እያየሁ የህይወት ግቦቼን መከለሴ አልቀረም፡፡ አርኖልድ ከነባለቤቱና ቤተሰቡ ተቀበለን፡፡ ሴቶቹ በሙሉ የሐበሻ ቀሚስ ለብሰዋል፡፡ አውላላ ሜዳ ላይ የተገነባው ፋብሪካ ጅማሮ እንጂ መጨረሻ እንዳልሆነ እወቁ፡፡ የወደፊቱን የማስፋፊያ ፕሮጀክት ፎቶ ከታች ተመልከቱ፡፡
 ወደ ግብር አዳራሹም ገባን፡፡ በክብ በክብ ተጋባዥ እንግዶችና በአበሻ ቀሚስ ያሸበረቁት የፋብሪካው ሰራተኞች ተቀምጠዋል፡፡ በነገራችን ላይ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ለመስጠት ድርጅቱ ነው የሐበሻ ቀሚስ ስጦታውን ያቀረበላቸው፡፡ የከተማው የሐበሻ ቀሚስ ሳይሆን የገጠሩ ቢሆን እንዴት እንደሚያምር አትጠይቁኝ፡፡
ደብረ ሆላንድ የራሱ ሶላር ሲስተም ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አሰርቷል፡፡ የከርሰ ምድር ውኃ 1.6 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ አስቆፍሯል፡፡ የሚሉና ሌሎችን መረጃዎች በመጥቀስ ‹‹ለሌሎች ኢንቬስትመንቶች ትምህርት የሚሰጥ ነው›› ብሎታል ባሶ ኮሚኒኬሽን በኖቬምበር 29፣ 2019 የፌስቡከ ዕትሙ፡፡  
የኔ ምልከታ ጠለቅ ያለ ትንታኔ እንዳይሆን የሚያደርገወው ነገር በዘርፉ ያለኝ ግንዛቤ ጠለቅ ያለ አለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው ጽሑፌ በዓይን በሚታየውና በሚወራው ነገር ላይ ብቻ ማተኮሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዕለቱ ለግብዣ የተያዘና የጉብኝት መርሃግብርም ያለመኖሩ እይታዬን ገድቦታል፡፡ በእርግጥ ለጋዜጠኞችና ለጸሐፊያን የተወሰነ ጉብኝት ተፈቅዶልን አድርገናል፡፡ ያስቀረነውንም በፎቶው ላይ ልታዩት ትችላላችሁ፡፡
ፋብሪካው ከከተማ ወጣ ያለበት ምክንያት የዶሮ እርባታ ንክኪ የማይፈልግ በመሆኑ ነው፡፡ ለአካባቢው የሚቆረቆር እንደሆነና ለእኛም ትምህርት እንደሚሰጥ ተገንዝቤያለሁ፡፡
ሰዎቹ ነቅለው ገብተዋል፡፡ ልጆቻቸውም የሚማሩት እዚሁ ነው፡፡ በርቀት በኢንተርኔት ይማራሉ፡፡ ለትንሹ ልጅ መምህርት ከሆላንድ ቀጥረውለት መጥታ እዚሁ እየኖረች ታስስምረዋለች፡፡ በዕለቱ ብዙ ፈረንጆች አይተናል፡፡

ዝግጅቱና የተሰጡ አስተያየቶች
እስኪ አሁን ደግሞ በቦታው ከተገኙት እንግዶች የቃረምነውን እነሆ፡-  
‹‹ተመሳሳይ ሥራ ለመሥራት ተነሳስቻለሁ፡፡ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡›› መምህር ሠውነት ተስፋዬ
‹‹የመጣሁት ከጓደኞቼ ጋር ነው፡፡ ጓደኞቼ እንሂድ ብለውኝ ነው፡፡ በሰዎች ግፊት መልካም ነገር ይመጣል፡፡ መግቢያ እንዳልጠየቅ ፈርቼ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ አየን፡፡ ልምድ መቀመር አለብን ሁላችንም፡፡›› መምህር ሃብታሙ መኮነን

ዝግጅቱ አንድ አንድ እያለ እየተሟሟቀ፣ ተጋባዦቹም እየተሟሉ ሄዱ፡፡ የመግቢያ ንግግር በአርኖልድ ተደረገ፡፡
የኢቨንት ኦርጋናይዘርና ድግስ አቅራቢ ድርጅቶች የተጠበቡበት ዝግጅቱ የድምጽ ማጉያ ካለመኖሩ በቀር ምንም አይወጣለት፡፡  
‹‹ከብቶቻችንና እኛ ንጹህ ውሃ አግኝተናል፡፡ ችግራችንን ይረዱልናል፡፡ እየመጡ ይጠይቁናል፡፡›› አንድ የአካባቢው አርሶአደር ካቀረቡት ንግግር፡፡
የወረዳው አስተዳደር ‹‹ደብረ ሆላንድ ከወረዳው ኢንቬስትመንቶች አንዱና ውጤታማ የሆነ ነው፡፡ 80 000 ዶሮዎች አሏቸው፡፡ ጠንካራ ድርጅት ነው፡፡ የሚጎድሉም ነገሮች አሉ፡፡ እየተነጋገርን እናስተካክላቸዋለን፡፡ በመንግሥት በህግ የተፈቀዱ ድጋፎችን እናደርጋለን፡፡ የምሳ ፕሮግራም ተብሎ ግብዣው በመዘግየቱ መጀመሩን አበስራለሁ፤ እንዲጀመርም አሳስባለሁ፡፡›› የሚል አስተያየት ሰጥተው ተሳታፊውን ፈገግ አስብለውታል፡፡  
የድርጅቱ ተቀጣተሪ የነበረን ሰው ድርጅቱ ዋስ ሆኖ የእንቁላል አከፋፋይ አድርጓል፡፡ ይህ ለሌሎችም ሊለመድ የሚገባ ጥሩ አሰራር ነው፡፡ ደብረ ሆላንድ በደብረ ብርሃን ከተማ ቀበሌ 09 ለሚገኙ የጤና መድህን ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች 18000 ብር ከፍሎ መድናቸውን ሸፍኖላቸዋል፡፡ የቼክ ርክክቡም በዝግጅቱ ላይ ተካሂዷል፡፡
ደረጃውን የጠበቀ ግብር የጾም መያዣውን አስመልክተው አድርገዋል፡፡ በሁሉም ነገር ደስተኞች ነን፡፡ ለወደፊቱ ደግሞ የቡድን ፎቶ ቢኖር ለድርጅቱም ለፋይል ይሆነዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሌላ ቀንም ጠርተው የፋብሪካውን አሰራር ያስጎበኙን ይሆናል፡፡ የእንቁላል ሽያጩ በጥሩ ሁኔታ እየሄደላቸው እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡

ድረገጻቸውስ ምን ይላል?
የድርጅቱን ድረገጽ ለመቃኘት ባደረግነው ሙከራ የሚከተለውን ቃርመናል፡፡ በኢትዮጵያ ለ10 ዓመት ሰርተዋል፡፡
ድርጅቱ ሌሎችን የውጪ ድርጅቶች በቴክኖሎጂው በዶሮና ስሕይወታዊው ኢንዱስትሪ ለማገዝ መዘጋጀቱን ያሳየ፤ ድርጅቱ ከሥራ ፈጣሪዎችና ከኢንቬስተሮች ጋር አብሮ ለመስራትም እንደሚፈልግ የገለጸ ነው፡፡
ለአካባቢው ህብረተሰብ የስራ ዕድልና የስልጠና ዕድሎችን ፈጥሯል፡፡ ለህብረተሰቡ በሚሰጡት ሥልጠና ስለ ዶሮ በሽታ መከላከል፣ አመጋገብ፣ ስለሚጠጡት ውሃና የክትባት ህግ ያስገነዝባሉ፡፡
በኔዘርላንድና ኢትዮጵያ ልምድ ያለው ድርጅቱ በኢትዮጵያ ፍቃድ ስላለውና የህጉን ሁኔታ ስለሚያውቅ መምጣት የሚፈልጉትን እንደሚያግዝና አብሮም እንደሚሰራ ገልጧል፡፡ 
ደብረዘይት በቀን 90 000 እንቁላል የሚያመርተው በ60 ትጉህ ሰራተኞች ብቻ ነው፡፡ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ኢንቬስት እያደረገ ያለው ድርጅቱ በደብረብርሃኑ ፋብሪካ የህብረተሰቡ የእንቁላልና የስጋ ፍጆታ እንዲሟላ ሌት ተቀን ይተጋል፡፡
በቀን 33 000 እንቁላል በቢርቢርሳ ይመረታል፡፡ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ጫጩቶች አሉ፡፡ የሥጋ ዶሮዎች ያቀርበል፡፡ ቴክኖሎጂው ዘመናዊ ነው፡፡
ከአካባቢ ጋር የተስማማ እርሻ፣ የኃይል መቆራረጥ እንዳያሳስበው ዘመናዊ የነፋስና የፀሐይ የኃይል ማመንጫዎች ያስገጠመ ነው፡፡   
ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ድረገጻቸውን ሳይ በደችና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ብቻ መሆኑን ታዝቤያለሁ፡፡ ወደ አማርኛ እንድተረጉመው ስራ አስኪያጁን አማክሬው ፈቅዶልኛል፡፡
የኛም ባለሐብቶች ከዚህ ተምረው ለሃገር የሚጠቅም ስራ እንዲሰሩ አሳስባለሁ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...